<link rel="stylesheet" href="https://cdn.plyr.io/3.7.8/plyr.css" />
ወደ ካታሎግ ተመለስAPCየሐዋርያቱ እምነት
የሐዋርያቱ እምነት ·Videoከእንግሊዝኛ ተተርጉሟል

APC-02 አብ

ሙሉውን ጽሑፍ ያንብቡ

ከተመሳሳይ ተከታታይ ትምህርት 2 ኛ ትምህርት ጋር የተያያዘ ቪዲዮ ሲሆን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠይቃል፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር አስተማማኝ እውነቶችን ሊያስተምረን ይችላል ወይንስ የሰው ቋንቋ ለዚህ ተግባር በቂ አይደለም? ስለ እግዚአብሔር ያለን እምነት ለክርስቶስ ተከታዮች ተግባራዊ ጠቀሜታ አለው? ሁሉም ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የተወሰኑ እምነቶች አሏቸው ፣ እነሱ በጣም አስፈላጊ ናቸው ፣ ሁሉንም ነገር ማለት ይቻላል ይነካሉ? የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ለመዞር የተጋለጡት ለምንድን ነው? ሌሎች ሃይማኖቶች ከክርስቲያኖች ጋር አንድ አይነት እግዚአብሔርን ያመለክታሉ? ስለ መንፈስ ቅዱስ አንድነት አስተምህሮ የተሳሳቱ መንገዶች ምንድን ናቸው? የአብ ኃይል ማለት እርሱ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ፈቃዱን ይጫንበታል ማለት ነው? እግዚአብሔር ከምድራዊ ፣ ከሰው አባቶች ጋር ተመሳሳይ እና የተለየ በምን ነገሮች ነው? አባቶች ሊሳሉ ከሚችሉት የእግዚአብሔር አብነት ምን ተግባራዊ ትግበራዎች ናቸው? ደካማ አባቶች ያሏቸው ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን አብነት በአዎንታዊ ብርሃን ውስጥ እንዲመለከቱ ማበረታታት እንዴት ይችላሉ? የእግዚአብሔር አብነት ለ 목회 አገልግሎት ምን አይነት አንድምታ አለው? የእግዚአብሔር ዓላማዎች በእኛ የተፈጸሙ መሆናቸውን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? የማይለወጥ እግዚአብሔር አእምሮውን እንዴት ሊለውጥ ይችላል? የሰው ልጅ የመቤት ዋና ግብ ምንድን ነው? በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ውስጥ ስለ ፍጥረት ቀናት ዋና ዋና የወንጌል ትርጓሜዎች ምንድን ናቸው? አንድ ዓይነት ቁርጥ ውሳኔ ላላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ስለ ፍጥረት ምዕራፍ 1 በተለያዩ መንገዶች እንዴት ማንበብ ይችላሉ? የእግዚአብሔር መልካምነት የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ምን ተግባራዊ አንድምታዎችን ማግኘት እንችላለን? ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በሁሉም ነገር ላይ ያለው ፍፁም ስልጣን ስላለው እውነታ እንዴት ሊሰማቸው ይገባል?


From the transcript

ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡

በርካታ ሃይማኖቶች “አምላክ” ብለው የሚጠቅሱዋቸውን ፍጥረታት ያመልካሉ፡፡ ይህም አንድ ቀልብን የሚስብ ጥያቄ ያስነሳል፤ ሁሉም የሚያመልኩት በተለያዩ ስሞች የሚጠሩ ተመሳሳይ ፍጥረታትን ነውን? ወይስ የተለያዩ አማልክትን ያመልካሉ? ምንም እንኳን በርካታ የተለያዩ ሃይማኖቶች “አምላክ” የሚለውን ተመሳሳይ ስም ቢጠቀሙም ይህን ሲሉ የተለያዩ ነገሮችን ማለታቸው መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያብራራል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን ይህም በክርስቲያኖች የሚመለከው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ያም ማለት የሌሎች ሃይማኖቶች አማልክቶች አስመሳዮች፣ ጣዖታት እና የሐሰት አማልክት ናቸው ማለት ነው፡፡ ክርስትና የመጽሐፍ ቅዱሱን አምላክ በማወቁ ላይ ጠንካራ ትኩረት የሚያደርገው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ ነው፣ የመፍጠር፣ የማጥፋት እና የማዳን ኃይል ያለው እርሱ ብቻ ነው፡፡

ከምናስተምራቸው የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ተከታታይ ተምህርቶች ይህኛው ሁለተኛው ትምህርት ሲሆን “እግዚአብሔር አብ” የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ በዚህ ትምህርት፣ በሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ውስጥ የመጀመሪያ በሆነው የእምነት አንቀጽ ላይ እናተኩራለን፡፡ ይህም አንቀጽ የስላሴ የመጀመሪያ አካል በሆነው በእግዚአብሔር አብ ማመንን ይሁንታ የሚሰጥ አንቀጽ ነው፡፡

ቀደም ባለው ትምህርት እንደተመለከትነው፣ የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ በቤተክርስቲያን ቀደምት ምዕተ ዓመታት ውስጥ በተለያየ ቅርጽ ይገለጥ ነበር፡፡ በ700 ዓ.ም. አካባቢ ግን ደረጃውን ጠብቆ በላቲን ቋንቋ ተዘጋጀ፡፡ እውቅ የሆነው ዘመናዊው የእንግሊዝኛ ቅጂ ትርጉም እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

በእነዚህ ትምህርቶች የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫን በአምስት ዋና ክፍሎች መከፋፈላችንን ታስታውሳላችሁ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ክፍሎች ስለ ሦስቱ የእግዚአብሔር አካላት ያወሳሉ እነርሱም ፡ አብ፣ወልድና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ እነዚህንም ትምህርቶች ቤተክርስቲያንንና ድነትን አስመልክቶ የተጻፉትን ክፍሎች አስከትለው ይመጣሉ፡፡ በዚህ ትምህርት፣ በመጀመሪያዎቹ አምስት ክፍሎች ላይ እናተኩራለን፡፡ እነርሱም በአንድ የእምነት አንቀጽ ብቻ ተቀምጠዋል፡

በዚህ የእምነት አንቀጽ ውስጥ የተጠቀሱትን ርዕሶች መከፋፈል የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ በዚህ ትምህርት ግን ለክርስቲያናዊ ነገረ መለኮት ማዕከላዊ በሆኑ ሦስት መሪ ሃሳቦች ላይ እናተኩራለን፡፡ እግዚአብሔር የሚለውን ሃሳብ፣ የሁሉን ቻዩ አብ ስብዕና፣ እንደ ፍጥረት ፈጣሪነቱ ያለውን ድርሻ እንዳስሳለን፡፡

እነዚህን ሦስት መሪ ሃሳቦች ተከትሎ፣ በእግዚአብሔር አብ ላይ የምንማረው ትምህርት በሦስት ክፍሎች ይከፈላል፡፡ በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር የሚለውን ሃሳብ እንዳስሳለን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ኅላዌና ማንነት የሚያስተምራቸውን ጥቂት ጠቅለል ያሉ ነገሮችን እንዳስሳለን፡፡ ሁለተኛ፣ የስላሴ የመጀመሪያ አካል የሆነውንና “ሁሉን ቻዩ አብ” በሚል ሐረግ የተጠቀሰውን የብቻው የሆኑ መለያዎቹን እናተኩርባቸዋለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ነዋሪ የሆነውን ሁሉ የመሥራት ወይም የመፍጠር ድርሻውን እንዳስሳለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርብልንን የእግዚአብሔር ሃሳብ በመመልከት እንጀምር፡፡

በእግዚአብሔር ላይ ያለን የእምነት አቋም ስለተቀረው ማንኛውም ነገር ለሚኖረን የእምነት አቋም መሠረታዊ ነው፡፡ ከንፅረተ ዓለም አንፃር ብናስብ፣ እግዚአብሔር ማዕከላዊ ይሆንና በዙሪያው የሚገኘው የተቀረው ፍጥረት ሁሉ የሆነውን ሁሉ የሆነው ከእርሱ ጋር ባለው ግንኙነት ነው፡፡ ያም አማክሎ-እግዚአብሔራዊ አመለካከቱን በባህላችን በተለምዶ ከምናስበው ራስ-ተኮር፣ እኔ-ተኮር ከሆነውና ሁሉን ነገር፣ እግዚአብሔርን ራሱን ጨምሮ ከእኔ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ከሚያጠነጥነው አስተሳሰባችን አንስቶ በተለያየ መጠን ያስቀምጠዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ነገሮችን ከሚያይበት ዕይታ እጅግ ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡ እኔ እንደማስበው እንዲያውም፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ከሚገልጡት የእግዚአብሔር የብቻው ከሆነው አስተሳሰብም ውጪ ነው ብዬ በድፍረት እናገራለሁ፡፡ እንግዲያው፣ በዚህ ዘመን በምንሰጠው አገልግሎት ውስጥ፣ ለእኛ ተፈጥሮአዊ የሆነውን እኔ-ተኮርነትንና እኔ-ተኮር አስተሳሰብን በእግዚአብሔር-ተኮርነት እና በእግዚአብሔር-ተኮር ንጽረተ-ዓለም መፋለም አስፈላጊ ነው፡፡ [ዶ/ር ጄ.አይ.ፓከር]

ሁለት ትምህርቶችን በመመልከት የእግዚአብሔርን መሠረታዊ ሃሳብ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለጸው እንመለከታለን፡፡ በአንድ በኩል፣ የነገረ መለኮት ምሁራን ደጋግመው “የእግዚአብሔር አሃዳዊነት” ብለው የሚጠሩትን እንዳስሳለን፣ ይህም ያለና የሚኖር ብቸኛ አምላክ የሚል እውነታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በእግዚአብሔር ግልጽነትና ቀሊልነት ላይ ትኩረት እናደርጋለን፣ ሦስት አካላት ያሉት የመሆኑ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እርሱ በእውነት ብቻውን አንድ አምላክ ነው፡፡ አስኪ በእግዚአብሔር አሃዳዊነት እንጀምር፣ ይህም የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር አንዱና ብቸኛ አምላክ ነው የሚል አስተምህሮ ነው፡፡

አሃዳዊነት

የእግዚአብሔርን አሃዳዊነት ስንዳስስ፣ አስቀድመን በቤተክርስቲያን ቀደምት ዘመናት በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ ስለነበረው ብዙ አማልክት አምላኪነት እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ፣ የአንድ አምላክ ማረጋገጫ አድርገንም አንድ አምላክ አምላኪነትን እንዳስሳለን፡፡ ሦስተኛ፣ ስለ ክርስትናና ስለ እግዚአብሔር ስላለው አስተሳሰብ እንመለከታለን፡፡ እስኪ አስቀድመን ወደ ብዙ አማልክት አምላኪነት ትምህርት እንሻገር፡፡

ብዙ አማልክት አምላኪነት

ብዙ አማልክት አምላኪነት ብዙ አማልክት አሉ የሚል የእምነት አቋም ነው፡፡ መላውን ፍጥረተ ዓለም የሚቆጣጠሩ ልዕለ-ተፈጥሮአዊ ኃያል ማንነቶች ማለት ነው፡፡ ከነዚህም አማልክት መካከል ጥቂቶቹ ዘላለማዊ፣ ያልተፈጠሩ ማንነቶች ናቸው ተብሎ ሲታሰብ፣ የተቀሩት ደግሞ የተወለዱ ወይም በአንድ ሁኔታ የተፈጠሩ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በብዙ አማልክት አምላኪነት ስርዓት ውስጥ፣ አማልክቱ አንዳቸው ከሌላቸው የተለዩ ናቸው፣ ስለዚህም በአንድ በኩል የተለዩ ናቸው፣ ልክ ሰብዓዊ ፍጡራን ሁሉም የተለያዩ እንደሆኑት ዓይነት ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን በብዙ አማልክት አምላኪነት ውስጥ፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም የመቆጣጠርን ሥልጣን የሚለማመድና ይገባኛል የሚል ልዕለ-ተፈጥሯዊ ማንነት ያለው አምላክ የለም፡፡

ሄኖቴይዝም በመባል የሚታወቀው፣ እውቅ የብዙ አማልክት አምላኪነት ዓይነት፣ የሌሎችን አማልክት መኖር ሳይክድ ለአንድ አምላክ ቅድሚያን ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ፣ በሮሜ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ጥቂት ሰዎች ዜዮስን ቀዳማይ ሲያደርጉ ለሌሎች አማልክትም እውቅና እየሰጡ ነው፡፡

ቀደምት በሆነችው የቤተክርስቲያን ዓለም ውስጥ፣ ክርስቲያን ያልሆኑ አብዛኞቹ ሰዎች ብዙ አማልክት አምላኪዎች ነበሩ፡፡ በርካቶቹ በግሪክና በሮም የሃሰት አማልክት ሲያምኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ የጥንታዊቷን የቅርብ ምሥራቅ ጣዖታት ያመልካሉ፡፡ የጠፈር ኃይላትን የሚያምኑ እና የተፈጥሮን ውቅረ ነገር ወይም አንድ ነገር የሚያመልኩም ብዙ አማልክት አምላኪዎችም ነበሩ፡፡ ምንም አማልክት የሉም የሚለው የእምነት አቋም ከስንት አንድ ነበር፡፡

በብዙ አማልክት የማምለኩ ነገር የተለመደ ከሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ ብዙ አማልክት አምላኪነት በሕግ ይደነገግ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በሮም ግዛት ውስጥ፣ መንግሥት የሮም ጣዖታት አምልኮን ያስገድድ ነበር፡፡ ሮማውያን ግዛታቸው የአማልክቱን ሞገስና ጥበቃ ያገኝ ዘንድ ይህንን አምልኮ እንዲፈጽሙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሁሉ የሚልቀው የብዙ አማልክት አምላኪነት ምክንያት የሰው ዘር ኃጢአተኝነት ነው፡፡

የሰው ዘር ከእውነተኛው አምላክ ወደ ሃሰት አማልክት ዘወር ማለት እንደሚቀናው መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል፡፡ ይህም በተለይ በመጽሐፍ ቅዱሱ ትምህርተ ኃጢአት ውስጥ ተመልክቷል፡፡ ከታላቁ ፈጣሪ ጋር ግንኙነት ያለን ፍጡራን ከመሆናችን እውነታ አንጻር የሚያሳየንን ያህል ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግንኙነት አንፃር ኃጢአተኛ ፍጡራን መሆናችንን አያመለክተንም፡፡ ስለዚህም ኃጢአት በዚህ መልክ እየሠራ ስለ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ለእኛ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን እውነት እንዳናስተውል ያሳውረናል፡፡ እናም፣ ስለ እግዚአብሔር ጨርሶ እውነት ያልሆኑ ነገሮችን እንደ አምላክ ወይንም መለኮታዊ ብቃት እንዳላቸው አድርገን የመቁጠሩ ነገር ለእኛ የተተወ ይሆናል፡፡ በሌላ አባባል የራሳችንን የፈጠራ አማልክት የእውነተኛው አምላክ ምትኮች አድርገን መፍጠር እንችላለን እንደ ማለት ነው፡፡ [ዶ/ር ዴቪድ ባወር]

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስተምሩን፣ ያለ አንድ መለኮታዊ ፈጣሪ እጅ ፍጥረተ ዓለም ጨርሶ ሊገኝ እንደማይችል ሁሉም ሕዝብ በውስጥ ልቡናው ያውቃል፡፡ ሆኖም በኃጢተኝነታችን ውስጥ፣ ሰብዓዊ ፍጡራን ለእውነተኛው እግዚአብሔር እውቅና መስጠትና እነዚህንም ነገሮች እንደፈጠረ መቁጠር አይቀናቸውም፡፡ በምትኩ ግን፣ የእርሱን ሥራ ለሌሎች ምንጮች እንሰጣለን፡፡ ጳውሎስ ስለዚህ ነገር በሮሜ 1፥20-23 የተናገረውን አድምጡ፡

የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ።

ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥

የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ።

በጳውሎስ አገላለጥ፣ የቅዱሳት መጻሕፍቱ እግዚአብሔር መኖር ለፍጥረት ሁሉ ግልጥ ነው፡፡ ለሁሉ በግልጥ ይታያል ይታወቃልም፡፡ ጳውሎስ እንዲያውም ገፋ አድርጎ የሰው ዘር በፍጥረት ባገኘው መገለጥ በራሱ ውስጥ እግዚአብሔርን ያውቃል በማለት ይገልጣል፡፡ እኛ ግን እርሱን ለማክበርና ለእርሱ ምስጋናን ለማቅረብ አሻፈረኝ የምንል ኃጢአተኞች ነን፡፡ በምትኩ፣ የአርሱን ክብር ለእጅ ሥራዎቻችን ሃሰተኛ ጣዖታት ሰጥተን በእርሱ ምትክ እናመልካቸዋለን፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በውስጣዊ ልቡናቸው፣ በአዕምሯቸው እና በህሊናቸው ያውቃሉ፡፡ ሆኖም ግን ሮሜ ምዕራፍ አንድ እንደሚነግረን አዳምና ሔዋን ኃጢአትን ከሠሩባት ከዚያች ቅጽበት አንስቶ፣ ውስጣዊ የልባችን ጥልቀት እውነተኛውን አምላክ ከማምለክ ተመልሶ በእግዚአብሔር የተፈጠሩ ጣዖታት ወይንም ማንኛውንም ነገር ወደ ማምለክ ዘወር ብሏል፡፡ ስለዚህ የሰው ልብ በተግባር የየትኞቹም ዓይነት ጣዖታት ፋብሪካ፣ ምንጭና ስር ነው፡፡ [ዶ/ር ሳሙኤል ሊንግ]

ይህንን የብዙ አማልክት አምላኪነት ምስል በልባችን ይዘን፣ አንድ አምላክ ብቻ አለ የሚል የእምነት አቋም ወደሚያራምደው የአንድ አምላክ አምላኪነት ዳሰሳ እንገባለን፡፡

አንድ አምላክ አምላኪነት/አማኝነት

ቴክኒካዊ በሆነ አነጋገር፣ አንድ አምላክ አምላኪነት አንድ አምላክ ብቻ አለ ብለው የሚያምኑ የትኞቹንም ሃይማኖቶች ያመለክታል፡፡ ለምሳሌ፣ በዘመነኛው ዓለም ይሁዲነት፣ ክርስትና እና እስልምና ሁሉም አንድ አምላክ አማኝ ሃይማኖቶች ናቸው ምክንያቱም ሁሉም አንድና አንድ ብቻ መለኮታዊ ማንነት አለ ብለው ስለሚያስተምሩ ነው፡፡

በርካታ የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባቦች አንድ አምላክ ብቻ አለ የሚለውን በግልጥ ለይተው በማመልከት የእግዚአብሔርን አሃዳዊነት ያረጋግጣሉ፡፡ ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡ በ 1ነገሥት 8፥60፣ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ያውጃል፡

እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆነና ከእርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ (1ነገሥት 8፥60)

በመዝሙር 86፥10፣ ዳዊት ለእግዚአብሔር እንዲህ ይዘምራል፡

… አንተ ብቻህን አምላክ ነህ

በ2ነገሥት ምዕራፍ 19 ቁጥር 19፣ ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፡

እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፣ … አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን እንዲያውቁ…

በሮሜ ምዕራፍ 3 ቁጥር 30፣ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡

አምላክ አንድ ስለ ሆነ

በያዕቆብ ምዕራፍ 2 ቁጥር 19፣ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፡

እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤

አንድ ብቻ መለኮታዊ ማንነት አለ፡፡ ይህ በብሉይ ኪዳን ዘመንም እውነት ነበር፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመንም እውነት ነበር፡፡ በቤተክርስቲያን ቀደምት ምዕተ ዓመታትም እውነት ነበር፡፡ ዛሬም እውነት ነው፡፡

እንግዲህ አሁን፣ ሁሉም አንድ አምላክ አምላኪ ሃይማኖቶች ተመሳሳይ አምላክ እንደማያመልኩ ማመልከት ያስፈልገናል፡፡ ቀደም ብለን እንደተናገርነው፣ ይሁዲነት፣ ክርስትና እና እስልምና እያንዳንዳቸው አንድ አምላክ ብቻ ያመልካሉ፡፡ ከዚህም በላይ፣ ቢያንስ በመጠሪያ እንኳን ሁሉም ይህን አንድ አምላክ ከአብርሃም አምላክ ጋር ያገናኙታል፡፡ ሆኖም “የአብርሃም አምላክ” ከሚለው ስም ጋር የሚያገናኙዋቸው ጽንሰ ሃሳቦች ግን በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡ በባህርዩ፣ በመለኮታዊ ተግባሩ እና እንዲያውም በማንነቱ ላይ ግን አይስማሙም፡፡

ለምሳሌ ይሁዲነትን እናንሳ፣ ይሁዲነት እምነቱን የሚመሠርተው ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ በብሉይ ኪዳን ላይ ነው፡፡ ሆኖም ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጠውን የስላሴውን እግዚአብሔር ይክዳሉ፡፡ በመሠረቱ፣ የስላሴን እያንዳንዱን አካላት ይክዳሉ፡፡ ኢየሱስ ጌታና ሰው የሆነው አምላክ መሆኑን ይክዳሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ስብዕና ያለው መሆኑን ይክዳሉ፡፡ ኢየሱስንና መንፈስ ቅዱስን ባለመቀበላቸው የላካቸውን አብን ይክዳሉ፡፡ ይህም ኢየሱስ ራሱ በሉቃስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 16 እንደተናገረው ማለት ነው፡

እኔን የጣለ የላከኝንም ይጥላል

ይሁዲነት ኢየሱስንና መንፈስ ቅዱስን ጥሏል እናም አብንም ጥሏል፡፡

ይሁዲነት እግዚአብሔርን የማመልከው በብሉይ ኪዳን እንደተገለጠው ነው ብሎ ያምናል፡፡ የሚያመለክተውም ክርስቲያኖች የሚወዱትንና “እኛም ያንኑ እግዚአብሔር እናመልካለን” ብለው የሚናገሩለትን ተመሳሳዩን ብሉይ ኪዳን ነው፡፡ እንግዲያው፣ ላይ ላዩን፣ የምናመልከው አንድ ዓይነት አምላክ ነው ብለን የምንናገርበት አንድ ስሜት አለ፡፡ በሌላ በኩል ግን የእነርሱ አምላክ በጣም የተለየ ነው ምክንያቱም በኢየሱስ የተገለጠውን ምሉዕ የአምላክ መገለጥ ይጥላሉና፡፡

እስልምናን በምንመለከትበት ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ያላቸው ጽንሰ-ሃሳብ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ጋር እንደሚፃረር ግልፅ ነው፡፡

ይህን አስመልክቶ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ፡ ስለ አንዱ አምላክ የእስልምና እምነት የሚያነሳው ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ እኔ እንደማምነው አምላክ አንድ ነው የሚልን ነገር ያነሳል፣ ክርስትና ግን እስልምና የማያነሳቸው የተለያዩ ባህርያትንና የጌታን የባህርይ መገለጫዎች ያነሳል፡፡ እኛ የቤዝዎትና የትስጉት አስተምህሮዎች አሉን፣ እነርሱም በሰዎች ሕይወት ውስጥ የእኛን ጌታ ባህርይ ግልጥ ባለና ወሳኝ በሆነ መንገድ የሚያሳዩ አስተምህሮዎች ናቸው፡፡ ቤዝዎትና ትስጉት ስለ አምላክ አንድነት እስልምና በያዘው መረዳት ውስጥ አይገኙም፡፡ [ዶ/ር ሬይድ ካሲስ፣ የተተረጎመ]

ስለ እግዚአብሔር እስልምና የያዘው አስተሳሰብ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ጋር ይጣረሳል፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከሚጣረስባቸው መንገዶች እጅግ ወሳኙ መንገድ አምላክ ፈጽሞ ሊነጣጠል በማይችል መንገድ አንድ ብቻ ነው የሚለው ድምዳሜያቸው ነው፡፡ እስልምና የያዘውን ይህን ቴክኒካዊ አባባል ላብራራው ብል፣ አምላክ ፍፁም አንድ ብቻ ነው በእርሱም ውስጥ አሃዱ ስሉስነት የለም የሚል ነው፡፡ በክርስቲያናዊ ነገረ-መለኮት ውስጥ ስለ አንድ አምላክ አምላኪነት ፍፁም ታማኝነት አለ፣ ይህም የእምነት አቋም አንድ አምላክ ብቻ አለ የሚል ነው፡፡ ጥንታዊው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሃይማኖት መግለጫ፣ “እስራኤል ሆይ ስማ፣ ጌታ አምላካችን፣ አንድ ጌታ ነው፡፡” እንግዲያው ይህ የአንድ አምላክ አምላኪነት ጉልህ ማረጋገጫ ከዋናው ምንጭ የተቀዳ የይሁዲ-ክርስቲያን ነገረ-መለኮታዊ ትውፊት አካል ነው፡፡ እናም ክርስቲያኖች አንድ አምላክ አምላኪዎች ናቸው፡፡ በርካታ እስላም ጓደኞቻችን ግን እንደዚያ እንደሆንን አያስቡም፡፡ ሦስት-አማልክት አምላኪዎች ያደርጉናል፡፡ እናም በአባት፣ በእናትና በልጅ ታምናላችሁ ብለው ያስባሉ ምክንያቱም መሐመድ ክርስቲያናዊውን የእግዚአብሔር አስተምህሮ አስመልክቶ ተሳስቷልና ነው፡፡ የስላሴ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ይህም አንዱ አምላክ በሦስት አካላት ይኖራል፣ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የአንዱ አምላክ የተለያዩ መግለጫዎች አይደሉም ወይም የአንዱ እግዚአብሔር የተለያዩ ተለዋጭ ዘይቤዎች አይደሉም፣ ነገር ግን በአንዱ እውነተኛ አምላክ ውስጥ ግልጽና ጭብጥ የሆነ አንድነት በአካላቱ መካከል አለ ማለት ነው፡፡ ከእስልምና ፈጽሞ የተለየው አመለካከት ያ ነው ፡፡ [ዶ/ር ጄ ሊጎን ዱንካን ሳልሳዊ]

እንግዲህ፣ ይሁዲነት፣ ክርስትናና እስልምና አንደ አምላክ የሚያመልኩ ሃይማኖቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ከብዙ አማልክት አምላኪነት የተለዩ ናቸው ምክንያቱም ብዙ አማልክት አሉ የሚለውን ይክዳሉና፡፡ ነገር ግን ደግሞ አንዳቸው ከሌላቸው የተለዩ ናቸው የዚህም ምክንያቱ ስለ እግዚአብሔር ማንነት ያላቸው አስተምህሮ ነው፡፡

የብዙ አማልክት አምላኪነትንና የአንድ አምላክ አምላኪነትን ከተመለከትን፣ በክርስትና የተረጋገጠውንና በሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ የተማርነውን የእግዚአብሔር ፅንሰ-ሃሳብ ለመግለጥ እንዘጋጃለን፡፡

ክርስትና

በሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር የተቀመጠው ሃሳብ በጣም ግልጽ ነው፡፡ በቀላሉ

እኔ ሁሉን በሚችል፣ ሰማይንና ምድርን በፈጠረ፣

በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ፡፡

የሃይማኖት መግለጫው አንድ አምላክ ብቻ አለ ብሎ ነጥሎ አይነግረንም፡፡ የዚህን የሃይማኖት መግለጫ ምንጩን ባናውቅ ኖሮ፣ እነዚህን ቃላት ልክ በይሁዲ እምነት ውስጥ ያለውን አምላክ ወይንም የእስልምናውን አምላክ እንደ ማወጅ ዓይነት ሊመስል ይችላል፡፡ ወይንም ከብዙ አማልክት መካከል ለአንዱ እውቅና እንደመስጠትም ሊመስል ይችላል፡፡ እንግዲያው፣ የሃይማኖት መግለጫው ክርስቲያናዊ ካልሆኑት የአንድ አምላክ አምላኪዎች ወይም የብዙ አማልክት አምላኪዎች በተለየ መልኩ ስለ ክስቲያናዊው ስሉስ እግዚአብሔር የሚናገር መሆኑን እንዴት እናውቃለን?

በአንድ በኩል፣ የሃይማኖት መግለጫው ስለ እግዚአብሔር በግልጽ በሚናገራቸው ሌሎች ነገሮች ከክርስትና ውጪ ያለውን አንድ አምላክ አምላኪነት ውድቅ ያደርገዋል፡፡ ቀደም ባለው ትምህርት እንደተመለከትነው፣ የሃይማኖት መግለጫው በስላሴያውያን ቀመር የተዋቀረ ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ፣ አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እና መንፈስ ቅዱስ በአንዱ አምላክ ውስጥ ያሉ ሦስት አካላት ሁሉም እያንዳንዳቸው መለኮታዊነት ያላቸው ስለ መሆናቸው ያለንን የእምነት አቋም ያንጸባርቃል፡፡

እንደገናም፣ የሃይማኖት መግለጫው የእምነት አቋሞች ማጠቃለያ ለመሆን ታስቦ የተዘጋጀ እንጂ ሁሉን ያካተተ ዝርዝር የእምነት አንቀጽ አለመሆኑን እናስታውስ፡፡ በቤተክርስቲያን ስነ-ስርዓት ውስጥ ከጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔርን ሦስቱን አካላት በዚህ መንገድ መግለጥን ሲያውቅ የስላሴን አስተምህሮ ለመግለጥ ያስችላል ተብሎ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሃይማኖት መግለጫው ብዙ አማልክት አምላኪነትን የካደው “አምላክ” የሚለውን ጥቅል ቃል ነጠላ ቅርጹን እንደ መለኮት ስም በመጠቀም ነው፡፡

“አምላክ” የሚለው ቃል ብዙ ፍቺ ሊኖረው ይችላል፡፡ ብዙ ሃይማኖቶች አማልክቶቻቸውን በዚሁ መጠሪያ ይጠሩዋቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይህንኑ “አምላክ” የሚለውን ቃል አጋንንትን፣ ጣዖታትን እና እንዲያውም ሰብዓዊ መሪዎችን ለማመልከትም ሲጠቀምበት እናገኘዋለን፡፡ ነገር ግን አነዚህ “አማልክት” ተብዬዎች በተጨማሪም የራሳቸው ስም አላቸው፡፡ ለምሳሌ፣ በጥንታዊ የሮም ሃይማኖት ውስጥ፣ ማርስ የጦርነት አምላክ፣ ኔፕቲዩን የባሕር አምላክ እና ጁፒተር ደግሞ የጣዖታት መሪ ይባል ነበር፡፡

በተመሳሳይም መንገድ፣ የቅዱሳት መጻሕፍቱ እግዚአብሔር በበርካታ ስሞች ይታወቃል፡፡ አብዛኞቹ ገላጮች ናቸው፣ ለምሳሌ እንደ ኤልሻዳይ፣ አብዛኛውን ጊዜ “ሁሉን ቻይ አምላክ” ተብሎ ይተረጎማል፣ ፍቺውም ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ማለት ነው፤ ኤል ኤሊዮን ደግሞ፣ “ከሁሉ በላይ የሆነው አምላክ” ተብሎ ይተረጎማል፣ማለትም ሁሉን የሚገዛ ማለት ነው፤ አዶናይ ደግሞ፣ በጥቅሉ “ጌታ” ተብሎ ይተረጎማል ማለትም ጌታና ገዢ ማለት ነው፡፡

አንደ እግዚአብሔር ትክክለኛ ስም በጣም የሚቀርበው ስም ያህዌ የሚለው ነው፡፡ በቀደሙት ትርጉሞች ይሆዋ ተብሎ ተገልጧል፡፡ በዘመነኞቹ ትርጉሞች ግን፣ በጥቅሉ “ጌታ” ተብሎ ተተርጉሟል፣ እንግዲያው ፍቺው አዶናይ ከሚለው ይለያል፡፡

እግዚአብሔር ያህዌ በሚለው ስም ራሱን የገለጠው በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ከዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 26 እንደምንማረው ሰዎች ለእግዚአብሔር ይህንን ስም መጠቀም የጀመሩት ከአዳም ልጅ ከሴት ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 9 ቁጥር 26 ደግሞ እግዚአብሔር ለኖህ እንደ ያህዌ ተገልጧል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 12 ቁጥር 8 ደግሞ አብርሃም እግዚአብሔርን በዚሁ ስም ጠርቶታል፡፡

ያህዌ በተጨማሪም በዘፀአት ምዕራፍ 3 ቁጥር 13 እና 14 ተጽፎ እንደምናነብበው እግዚአብሔር ለሙሴ የተገለጠበት ስም ነው፡

ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፥ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ፥ ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው።

እግዚአብሔርም ሙሴን፦ «ያለና የሚኖር» እኔ ነኝ አለው እንዲህ ለእስራኤል ልጆች። «ያለና የሚኖር» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው።

ያህዌ የሚለው ስም ’ehyeh ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ያዛመዳል በዚህ ስፍራም “እኔ ነኝ” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ይህ ስም እግዚአብሔር ለሕዝቡ የተገለጠበት የቅርብ ወዳጅነት ስሙ ሲሆን፣ ከሎሎቹ ስሞች ሁሉ የሚልቅ፣ ከሃሰት አማልክት ሁሉ እርሱን የሚለየው ስም ነው፡፡

በመሠረቱ፣ ጌታ በቅዱሳት መጻሕፍት ከተገለጠባቸው ስሞች ሁሉ፣ “እግዚአብሔር” የሚለው ስም ጥቅል ነው፡፡ በእኛ ዘመን ባለው የብሉይ ኪዳን ቅጂ፣ እግዚአብሔር የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ ኤል ወይም ኤሎሂም ትብሎ ይተረጎማል፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ፣ ቴዎስ በሚለው የግሪክ ቃል ይተረጎማል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ ሌሎች ሃይማኖቶች እነዚህኑ ተመሳሳይ ቃላት የየራሳቸውን ጣዖታት ለማመልከት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ እንግዲያው የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫው ለእግዚአብሔር እንደ ያህዌ የመሰለውን የተለየ ስም ከመጠቀም ይልቅ ለምን ጥቅል የሆነውን መረጠ? ምክንያቱም ይህንን ቀላል “እግዚአብሔር” የሚል ቃል ጌታን ለመግለጥ በመጠቀም፣ የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫው ማመልከት የፈለገው የክርስትናው እግዚአብሔር “አምላክ” ተብሎ መጠራት የሚገባው እርሱ ብቻ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ 1ነገሥት ምዕራፍ 8 ቁጥር 60 ስናነብብ፡

የምድር አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ (በዕብራይስጡ ያህዌ) እንደ ሆነ፥ ከእርሱም በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቅ ዘንድ።

አዎን፣ ሌሎች ሃማኖቶች ትክክለኛ አማልክትን እንደሚያመልኩ ያምናሉ፡፡ ወደ እውነታው ስንመጣ ግን፣ የሚያመልኩት ምናባዊ አካላትን ወይንም ይባስ ብሎ አጋንንቶችንም (በክርስትናው አምላክ የሚመሩ ፍጡራን መናፍስት) ሊሆን ይችላል፡፡ በ1ቆሮንቶስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 20 ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በመጻፍ ነገሩን ግልጽ አድርጓል፡፡

… አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ …

አረመኔዎች (የአምልኮተ ባዕድ ተከታዮች) ለተለያዩ አማልክት እንደሚሰዉ ነው የሚያምኑት እንጂ ለአጋንንቶች እንደሚሰዉ አያምኑም፡፡ ግን ተሳስተዋል፡፡

በአሁኑ ዘመን በዓለም ላይ ከክርስትና ሌላ በርካታ ሃይማኖቶች አሉ፡፡ ሂንዱ፣ ሺንቶ፣ ባዕድ አምልኮ፣ ዊካ፣ እስላም፣ ልማዳዊ ሃይማኖቶች ወ.ዘ.ተ. ፡፡ የእነርሱ አማልክት ግን ስህተት ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ አጋንንቶችን ያመልካሉ፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ ተፈጥሮን ያመልካሉ፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ በምናባቸው የፈጠሩትን ያመልካሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የክርስትናው አምላክ ብቻ እውነተኛ መለኮት እንደሆነ በአጽንዖት ይገልጣል፣ የክርስትናው አምላክ ብቻ በዓለም ላይ ይፈርዳል፣ ደግሞም የክርስትናው አምላክ ብቻ እኛን የማዳን ኃይል አለው፡፡

የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ በመጀመሪያው የእምነት አንቀጹ አዳዲስ ክርስቲያኖች ሲያመልኩዋቸው የኖሩትን አማልክት ወዲያ ብለው፣ የቅዱሳት መጻሕፍቱን አምላክ እንደ አንድ እውነተኛ አምላክ እውቅና እንዲሰጡ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ይህም ጥሪ በቅዱሳት መጻሕፍት እጅግ ወሳኝ የሆነውን ትምህርት ይገልጣል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ዘመን የሚኖር የትኛውም ሰው የብሉይ ኪዳኑና የአዲስ ኪዳኑ እግዚአብሔር ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ እውቅና እንዲሰጥ ግድ ይላል፡፡ እናም እርሱን ብቻ እንዲያመልኩ ያዛል፡፡

ስለ እግዚአብሔር አሃዳዊነት ተነጋግረናል፣ አሁን ደግሞ ቀጥለን ስለ ቀሊልነቱና ግልጽነቱ እንነጋገራለን፡፡

ቀሊልነትና ግልጽነት

እንደምታስታውሱት ቀደም ባለው ትምህርት ትምህርተ ስላሴን ስናብራራ፡ እግዚአብሔር በሦስት አካላት (ስብዕና) የተገለጠ፣ አንድ አምላክ ነው በሚል መንገድ ገልጠነው ነበር፡፡ “ስብዕና” የሚለውም ቃል ራሱን የቻለ፣ ግላዊ ማንነትን እንደሚያመለክት ተናግረናል፡፡ “ማንነት” የሚለውም ቃል ስለ እግዚአብሔር መሠረታዊ ኅላዌ ያመለክታል፣ በልቡናችን የያዝነው የእርሱ ማንነት፣ የእርሱ መሠረታዊ ኅላዌ የእርሱን ማንነት ጭብጥ ያደርገዋል፡፡

አሁን እንግዲህ፣ የነገረ-መለኮት ሊቃውንቱ “ቀላል” እና “ቀሊልነት” የሚሉትን ቃላት ለየት ባለ ቴክኒካዊ መንገድ እንደሚጠቀሙበት እናያለን፡፡ ይህን ስንል እግዚአብሔር በቀላሉ ልንረዳው የምንችል ቀላል ነው ማለታችን አይደለም፡፡ በምትኩ ግን ማንነቱ የተለያዩ ማንነቶች ጥርቅም ሳይሆን አንድ ብቻ የሆነ አንድ ምሉዕ ማንነት ነው ማለታችን ነው፡፡

ይህን የቀሊልነት ሃሳብ ንፁህን ውሃ ከጭቃ ጋር በማነፃፀር ለመግለጥ እንሞክራለን፡፡ በአንድ ወገን ውሃ አንድ ቀላል ነገር እንደሆነ ልንመለከተው እንችላለን፡፡ የየያዘውም ውሃ ብቻ እንጂ ሌላ ምንም ነገር አይደለም፡፡ በንፁሁ ውሃችን ላይ አቧራ ብንጨምር ግን፣ ወደ ጭቃነት ይለወጣል፡፡ ጭቃ ተለያዩ ነገሮች ውሁድ ነው ምክንያቱም ሁለት የተለያዩ አካላትን ውሃና አቧራ በውስጡ ይዟልና፡፡ የእግዚአብሔር ማንነት ልክ እንደ ንፁሁ ውሃ አንድ ማንነት ብቻ ያለው ነው፡፡

ግን ይህ ለምን አስፈላጊ ሆነ? ክርስትና እግዚአብሔር ቀላል ነው በብዙ ማንነቶችም የተሞላ አይደለም ብሎ ትኩረት መስጠት ለምን አስፈለገው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ፣ አንድ ጊዜ መለስ ብለን ትምህርተ ስላሴን እንመልከት፡፡ ትምህርተ ስላሴ፣ እግዚአብሔር ስሉስ አካላት ያሉት አንድ አምላክ ነው በማለት ያስቀምጠዋል፡፡

በትምህርተ ስላሴ ውስጥ ማዕከላዊው ነገር በስብዕናና በማንነት መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡ ከማንነት አንፃር እግዚአብሔር አንድ ነው ከስብዕና አንፃር ሦስት ነው፡፡ በመሠረቱ ለእግዚአብሔር አንድ “ምን” አለ እና ሦስት “እነማን” አሉ ብለን መናገር እንችላለን፡፡ [ዶ/ር ኬት ጆንሰን]

መጽሐፍ ቅዱስ ጠንከር አድርጎ እንደሚያሳስበው እግዚአብሔር ሦስት አካላት አሉት፣ አብ፣ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፡፡ ግን አንድ አምላክ ነው ብሎ ያስተምራል፡፡ በቤተክርስቲያን ቀደምት ዘመን፣ የነገረ-መለኮት ምሁራን ስለ እግዚአብሔር አንድነት ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለመናገር የቆረጡበት ምክንያት ስለ ማንነቱ ለመናገር ሲሉ ነው፡፡ እንግዲያው፣ እግዚአብሔር ቀላል፣ አንድ ማንነት ያለው አምላክ ነው ሲሉ ዓላማቸው አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስት የተለያዩ አማልክት ሆነው በስላሴ ውስጥ ተጣመሩ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ለማድረግ ነው፡፡ በምትኩም ሦስቱ አካላት አንድ አምላክ ብቻ ሆነው ዘወትር ይኖራሉ በማለት አፅንዖት ይሰጣሉ፡፡

በዚህ መንገድ፣ ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖች በተደጋጋሚ በሌሎች ሃይማኖቶች እንደምንነቀፈው በሦስት አማልክት እንደማናመልክ ፍፁም ግልፅ ታደርጋለች፡፡ እኛ የምናመልከው በሦስት አካላት በሚኖረው በአንዱ አምላክ - በአንድ መለኮት ብቻ ነው፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜ ከእስላሞች ጋር ስነጋገር፣ የክርስቲያኖች የስላሴ አተያይ የሦስት አማልክት ወይንም የሦስት አማልክት አምላኪነት ማረጋገጫ ነው ይላሉ፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ግን ይህንን አባባላቸውን ያረጋገጠ አንድም ሰው የለም ምክንያቱም አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው እና መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው የሚለው ማረጋገጫ ከዘፍጥረት አንስቶ እስከ ራእይ ድረስ እግዚአብሔር አንድ መሆኑ የተረጋገጠበት ነው፡፡ እንድ የሚኖርና እውነተኛ አምላክ አለ፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔርን ምሉዕ መገለጥ በትክክል የምንረዳበት ብቸኛ መንገድ፣ ከአንዱ አምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ በዚያው አምላክ ውስጥ አብ፣ወልድና መንፈስ ቅዱስ አሉ ብለን በመናገር ነው፡፡ የቤተክርስቲያንም ቋንቋዋ ሁሉም በአንዱ አምላክ ውስጥ ሦስት አካላት ሆነው ይኖራሉ ለዚህም ነው ሦስት አማልክት አሉ የሚለውን የማንቀበለው የሚል ሆኖ ዘልቋል ይዘልቃልም፡፡ አንድ አምላክ ግን ሦስት አካላት፡፡ እንግዲህ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተማሩት፣ ቤተክርስቲያንም ያረጋገጠችው እና ከዚህም አንጻር ካሉን የሃይማኖት ተፎካካሪዎቻችን በእውነት ልዩ የሚያደርገን ይኸው ነው፡፡ [ዶ/ር ስቴፈን ዌሉም]

ይህ ሃሳብ በሌላው ጥንታዊ የሃይማኖት መግለጫ- በኒቂያው የሃይማኖት መግለጫ በግልጽ ተብራርቷል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ … ከአብ ጋር አንድ ነው፡፡ ይላል፡፡

የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ በአብዛኛው መሠረታዊ ነገር ላይ ስለሚያተኩር እንደ ኒቂያው የሃይማኖት መግለጫ ይህን ጉዳይ ነጥሎ ጥልቅ ማብራሪያ አልሰጠበትም፡፡ ሆኖም ግን፣ እኛ በሦስት አካላት የሚኖር አንድ አምላክ እናመልካለን የሚለውን ሃሳብ ግልጥ ያደርግልናል፡፡

ክርስቲያኖች በሦስት አካላት ውስጥ የሚኖር አንድ አምላክ ያመልካሉ የሚለው እውነታ ለክርስትና ሕይወት ቁጥር ስፍር የሌለው ፋይዳ አለው፡፡ ለምሳሌ ያህል ትውፊታዊው የክርስቲያን አምልኮ ሙሉ ለሙሉ ስላሴያዊ ነው፡ የስላሴን ሦስቱንም አካላት እናመልካለን፣ የምሥጋና ዝማሬዎችንና ልመናዎችን ለእያንዳንዳቸው እናቀርባለን፡፡ ከስላሴ አካላት አንዱን ለሌላው በማድላት ቸል የምንል ከሆነ እግዚአብሔርን ራሱን ቸል ማለታችን ነው፡፡ ለአብ፣ ለወልድ እና ለመንፈስ ቅዱስ ክብርን እናመጣለን ፍቅራችንንም እንገልፃለን ምክንያቱም ሁሉም አንድ አምላክ ናቸውና፡፡

ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔርና ስለ እርሱ ህላዌ ያላቸውን መረዳት ከተመለከትን አሁን ደግሞ፣ ሁሉን ቻዩ አብ በሚለው ሐረግ ላይ ትኩረት በማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ የስላሴ ቀዳሚ አካል ስለሆነው ስለ እግዚአብሔር አብ የሚያስተምረውን በማንሳት እንነጋገራለን፡፡

3. ሁሉን ቻይ አብ (አባት)

ሁሉን ቻይ አብ የሚለው ትምህርታችን በአራት ይከፈላል፡፡ በመጀመሪያ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ “አብ” የሚለው ስም ለእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ የዋለበትን መንገድ እንዳስሳለን፡፡ ሁለተኛ፣ የእግዚአብሔር አብን ስብዕና ከስላሴ አንፃር እንመለከታለን፡፡ ሦስተኛ፣ የእርሱን የአባትነት ኅላዌ፣ ማለትም ነገሮችን በአባትነት ድርሻው የሚያከናውንበትን እንመረምራለን፡፡ አራተኛ ደግሞ፣ ስለ እርሱ ኃይል እንነጋገራለን፡፡ አስቀድመን “አብ” የሚለው ስም በቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅም ላይ የዋለበትን እንመልከት፡፡

ስም

መጽሐፍ ቅዱስ “አብ” የሚለውን ስም ቢያንስ በሦስት ለየት ያሉ ምክንያቶች ተጠቅሞበታል፡፡ በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ለማመልከት ተጠቅሞበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ግሩም የሆነው አዲስ ኪዳናዊ ምሳሌ በ1ቆሮንቶስ ምዕራፍ 8 ቁጥር 6 ላይ ጳውሎስ ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ በማለት በጠቀሰው ውስጥ ይገኛል፡፡ እንግዲህ በዚህ አሁን ባነሳነው ምሳሌ ውስጥ የተቀመጠው መግለጫ ስለ ስላሴ የመጀመሪያ አካል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መግለጫዎችን ሁሉ ያካተተ ነው ማለታችን እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሁለተኛው “አብ” የሚለው ቃል አጠቃቀም የሚያመለክተው አማኞች የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከመሆናቸው (ከመደረጋቸው) የተነሳ ከእግዚአብሔር ጋር ስላላቸው ግንኙነት ነው፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 8፥15 አባ፣ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበልን በማለት “አባት” የሚለውን ቃል ሲጠቀም በዚህ በሁለተኛው መረዳት ነው፡፡ በመጨረሻም፣ ‘አባት’ የሚለው ቃል የሚያመለክተው በኢየሱስ ክርስቶስና በአባቱ መካከል ያለውን ለየት ያለ ግንኙነት ነው፡፡ እነዚህን ሦስት አጠቃቀሞች ስንጠቀልላቸው የመጀመሪያው ስለ እግዚአብሔር የሚናገረው ፈጣሪነቱን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቤዛነቱን ሦስተኛው ደግሞ አብ ከልጁ ጋር ያለውን ግንኙነት ለይቶ የሚያመለክተን ነው በማለት ነው፡፡ [ዶ/ር ኬት ጆንሰን]

ክፋቱ ግን፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ “አባት” የሚለውን ቃል በሚጠቀምበት ጊዜ ሁሉ ስለ ስላሴ የመጀመሪያ አካል መናገሩ ነው ብለው በተሳሳተ መንገድ ማሰባቸው ነው፡፡ ነገር ግን የስላሴ አስተምህሮ እስከ አዲስ ኪዳን ድረስ በግልፅ አልተገለጠም ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ እዚህም እዚያም በእግዚአብሔር ውስጥ የብዙ ቁጥር አመልካች ጠቋሚዎች ብልጭ ይሉ ነበር፡፡ ግን ብሉይ ኪዳን በአስደናቂ ሁኔታ በእግዚአብሔር አንድነት ላይ አጽንዖት ይሰጥ ነበር፡፡

ስለዚህ፣ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር “አባት” ተብሎ ሲጠራ፣ አንድን አካል ብቻ ለማመልከት ሳይሆን ስላሴን ለመግለጥ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በተወሰነ መጠን፣ “አባት” የሚለው ቃል አጠቃቀም የሚያተኩረው በአብ ስብዕና ላይ ነው፡፡ ግን የእግዚአብሔር ሦስት አካላት መገለጥ በአዲስ ኪዳን ግልጽ እስኪሆን ድረስ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ይውሉ የነበሩት መጠሪያዎች “አባት” የሚለውን ስም ጨምሮ ማለት ነው በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተግባራዊ የሆኑት ለስላሴ እንደነበር ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ እንደ ዘዳግም ምዕራፍ 32 ቁጥር 6፤ ኢሳያስ 63 ቁጥር 16 እና ምዕራፍ 64 ቁጥር 8 በመሳሰሉት ምንባቦች “አባት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የእግዚአብሔርን ሁለንተና ነው፡፡ ጉዳዩን በአግባቡ ከመግለጽ አንፃር በብሉይ ኪዳን “አባት” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ የዋለበትን አንድ ምሳሌ እንመልከት፡፡ በሚልክያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 10 ላይ ነቢዩ ይህንን ጥያቄ ይጠይቃል፡

ሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለንምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? (ሚልክ 2፥10)

በዚህ ስፍራ፣ ሁሉም የእግዚአብሔር አካላት-አብ፣ወልድና መንፈስ ቅዱስ-“አባት” ተብለዋል ምክንያቱም ሁሉም የእግዚአብሔር አካላት የሰውን ዘር በመፍጠሩ ሥራ ተሳትፈዋልና፡፡ አዲስ ኪዳን ደግሞ ነገሩን ግልጽ አድርጎታል ይህም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዳቸው የተለያየ ድርሻ አላቸው፡፡ ይህ የብሉይ ኪዳን ምንባብ ግን በእግዚአብሔር አካላት መካከል ይህንን ልዩነት አያሳየንም፡፡ በፋንታው ግን፣ ለሁሉም የስላሴ አካላት “አባት” የሚለውን የጋራ መጠሪያ በፍጥረት ካላቸው ድርሻ የተነሳ ይሰጣቸዋል፡፡

ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችንም ገፋ አድርገን ብንመለከት፣ የአዲስ ኪዳን ጸሐፍት ከብሉይ ኪዳን ወስደው እንደጻፉት፣ ጥቅል በሆነ አተያይ ለስላሴ አባት የሚለውን መጠሪያ ተጠቅመውበታል፡፡ ለምሳሌ፣ ሁሉም የስላሴ አካላት በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 45፤ በምዕራፍ 6 ቁጥር 6 እስከ 18 እና የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 ቁጥር 24 እስከ 29 እንደ አባት ተገልጠዋል፡፡ በእነዚህ ምንባቦች ሁሉም የስላሴ አካላት “አባት” ተብለው የተጠሩት በተለያየ ምክንያት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሁሉም የስላሴ አካላት ዓለምን በመፍጠር ሥራ ውስጥ በመሳተፋቸው ነው፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሁሉም የስላሴ አካላት እኛ ልናከብረው የሚገባ ስነ-ምግባራዊ ደረጃ ያላቸው በመሆኑ ምክንያት ይሆናል፡፡ እስኪ እንደገና፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት አንፃር አንድ ጥቅስ እንመልከት፡፡ በያዕቆብ ምዕራፍ 1 ቁጥር 17 ላይ እንዲህ ተጽፎ እናነባለን፡

በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። (ያዕቆብ 1፥17)

ከዚህ ጥቅስ ቀደም ብሎ፣ የእግዚአብሔር ባሕርይ ስነ-ምግባራዊ ንፅሕና ያለው ስለ መሆኑ መከራከሪያውን አቅርቧል፡፡ እንግዲያው በዚህ ስፍራ ማመልከት የፈለገው ነጥብ ከእግዚአብሔር የሚመጣ ነገር ሁሉ መልካም ነው፣ መልካምም ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው የሚል ነው፡፡ መልካም ነገሮች ሁሉ ከእኛው ስሉስ አምላክ የሚመጡ ከሆነ፣ ክርስቲያን ተርጓሚዎች ይህንን ነገር ለሁሉም የስላሴ አካላት ማገናዘቢያ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ እንደገናም፣ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሁሉ፣ በአብ ስብዕና ላይ ያለውን አጽንዖት መመልከታችን ምክንያታዊ ነው፡፡ ግን ወልድ እና መንፈስ ቅዱስም በጎ ስጦታዎችን እንደሚሰጡን ማረጋገጣችን አስፈላጊ ነው፡፡

ይህም ሆኖ ግን፣ ቅዱሳት መጻሕፍት “አባት” የሚለውን ቃል ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ለተለየ አንድ የስላሴ አካል እንደሚጠቀሙበት ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 14 እና 18፤ ዮሐንስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 17 እስከ 26፤ ገላትያ ምዕራፍ 4 ቁጥር 6፤ 2ጴጥሮስ ምዕራፍ 1ቁጥር 17 ላይ እናየዋለን፡፡ ይህንን ነጥብ ለማብራራት አንድ ጊዜ ሁለት ምሳሌዎችን ጨምረን እንመልከት፡፡ በ2ዮሐንስ ቁጥር 9 ውስጥ፣ ሐዋርያው እንዲህ ሲጽፍ በአብና በወልድ መካከል ለይቷል፡፡

ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። (2ዮሐ 9)

እናም በዮሐንስ ምዕራፍ 14 ቁጥር 16 እና 17፣ ኢየሱስ ይህንን ማረጋገጫ ለሐዋርያት ሲሰጥ በአብና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውን ልዩነት አመልክቷል

እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤

እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። (ዮሐ 14፥16-17)

“አባት” የሚለው ስም በቅዱሳት መጻሕፍት የስላሴን አካላት ሁሉ እንዲሁም የስላሴን የመጀመሪያ አካል ለማመልከት በጥቅም ላይ እንደዋለ ተመልክተናል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የእግዚአብሔር አብን ስብዕና ከሌሎቹ የስላሴ አካላት በመለየት እንመለከታለን፡፡

ስብዕና/ማንነት

አብ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለው ግንኙነት በብዙ መንገድ ተገልጦ ሊሆን ይችላል፡፡ በነገረ-መለኮት ታሪክ ግን፣ ሁለት የተለዩ አመለካከቶች ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ በተለይም፣ ስለ ማንነታዊ ስላሴ (ontological Trinity = ontology is a study of being) እና ስለ ቤተሰባዊ ስላሴ (economic Trinity= economic in this sense means relating to household management) መነጋገር የተለመደ ሆኗል፡፡ ሁለቱም ስለ አንዱ ስላሴ ነው የሚናገሩት - አብ፣ወልድና መንፈስ ቅዱስ፡፡ ትኩረታቸው ግን በስላሴ ሦስት አካላት የተለያየ የግንኙነት እሳቤ ላይ ነው፡፡

በሌላ በኩል፣ ስለ ማንነታዊ ስላሴ የምንናገረው በእግዚአብሔር ማንነት ላይ ስናተኩር ነው ብሎ መናገር የተለመደ ነው፡፡ ኦንቶሎጂካል የሚለው ቃል ከማንነት ጋር የተዛመደ ነው፡፡ እንግዲያው ስለ ማንነታዊ ስላሴ ስንነጋገር፣ ስላሴን ከማንነት ወይንም ከመሠረት ጋር አያይዘን መመልከታችን ነው፡፡ ማለትም ሦስቱ የስላሴ አካላት አንዳቸው ከሌላቸው ጋር እንዴት እንደሚዋሃዱ እና አንድ የጋራ ማንነት እንደሚጋሩ እንመለከታለን ማለት ነው፡፡

ከማንነታዊ ስላሴ አመለካከት አንጻር፣ ሦስቱም የስላሴ አካላት መጨረሻ የሌላቸው፣ ዘላለማዊ እና የማይለዋወጡ ናቸው፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ መሠረታዊ መለኮታዊ የባህርይ መገለጫዎች አሏቸው፡፡ እነርሱም፣ ጥበብ፣ ኃይል፣ ቅድስና፣ ፍትህ፣ መልካምነት እና እውነት ናቸው፡፡

በሌላ በኩል፣ የእግዚአብሔር አካላት አንዳቸው ከሌላቸው ጋር እንዴት ግንኙነት እንደሚያደርጉ፣ እንደ ግላዊ ማንነት አንዳቸው ከሌላቸው እንዴት እንደሚዛመዱ ስንመለከት ስለ ቤተሰባዊ ስላሴ ገፅታ መናገራችን ነው፡፡ እንግዲያው፣ ስለ ስላሴ ቤተሰባዊ ገፅታ ስንናገር፣ እግዚአብሔር አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንደልዩ ግላዊ ማንነት እንዴት እርስ በርስ እንደሚዛመዱ መግለጣችን ነው፡፡

ስላሴን ከቤተሰባዊ ማንነት አንፃር ከተመለከትን፣ እያንዳንዱ አካል የተለያየ ኃላፊነት፣ የተለያየ የሥልጣን እርከን እና የተለያየ ተግባር ለመፈጸም የሚያስችል የተለያየ ድርሻ አለው፡፡ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ እርስ በርስ ይነጋገራሉ፡፡ ፍጹምም ይስማማሉ፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ በሌሎችም በበርካታ መንገዶች ይገናኛሉ፡፡

ከማንነታዊ እና ከቤተሰባዊ አመለካከት አንፃር፣ አብ የመጀመሪያ አካል ይባላል፡፡ አብ የማንነታዊ ስላሴ የመጀመሪያ አካል ተብሎ ይጠራል፣ ምክንያቱም ወልድ ከእርሱ የወጣና መንፈስ ቅዱስም ከአብ የሚሰርፅ ነው ስለሚባል ነው፡፡

እስኪ ስለ ወልድ ከአብ መላክ 1ዮሐንስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 9 የሚናገረውን እንስማ፡

በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። (1ዮሐ 4፥9)

“አንድ” የሚለው ቃል ሞኖጂነስ (monogenes) ከሚለው የግሪክ ቃል የወጣ ሲሆን፣ በተደጋጋሚም “አንድያ” ተብሎ ይተረጎማል፡፡ የሚያሳዝነው ግን፣ በቀደመችው ቤተክርስቲያን የነበሩ ጥቂት ሰዎች ይህ ማለት ወልድ ፍጡር ነው ስለዚህም ምሉዕ መለኮትነት የለውም ብለው ማሰባቸው ነው፡፡ ዛሬም እንኳን አንዳንድ የስህተት እምነቶች የወልድን መለኮትነት “አንድያ” ተብሎ በመጠቀሱ ምክንያት ይክዳሉ፡፡

ለዚህ የስህተት አስተምህሮ አፍራሽ ምላሽ ለመስጠት፣ ክርስቲያኖች ወልድ በዘላለም ሃሳብ ከአብ የወጣ ወይም ዘላለማዊ አንድያ ከአብ የሆነ በማለት በትውፊት ይናገራሉ፡፡ እነዚህ አባባሎች ወልድ ያልነበረበት ምንም ጊዜ የለም የሚል ትኩረት ያነገቡ ናቸው፡፡ በዮሐንስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 26 ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ መምጣት የተናገረበትን መንገድ ተመልከቱ፡

ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፣ (ዮሐ 15፥26)

“የሚወጣ” የሚለው ቃል ekporeuomai የሚለው የግሪክ ቃል ትርጉም ነው እናም አብዛኛውን ጊዜ “የሚከተል” ተብሎ ይፈታል፡፡ በትውፊት፣ ይህ ጥቅስ የመንፈስ ቅዱስ ኑባሬ ምንጭ እንደሚያመለክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ይህንን የመሰሉ ምንባቦች አንዳንድ ሰዎችን መንፈስ ቅዱስ ዘላለማዊ እንዳልሆነና ምሉዕ መለኮትነት እንደሌለው አድርገው የተሳሳተ ድምዳሜ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህም፣ ትውፊታዊው ነገረ-መለኮት መንፈስ ቅዱስ የስላሴ ምሉዕ አባል፣ ምሉዕ መለኮት እና እንዲያውም የእርሱ ስብዕና ለዘላለም ከአብ የወጣ መሆኑን በጥንቃቄ ያሳስባል፡፡

አብ የማንነታዊ ስላሴ የመጀመሪያ አካል ከመሆኑ ባሻገር፣ የቤተሰባዊ ስላሴም የመጀመሪያ አካል ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ከቤተሰባዊ አመለካከት አንፃር፣ አብ “የመጀመሪያ አካል” ተብሏል ምክንያቱም እርሱ በሁለቱ አካላት ላይ ሥልጣን አለው፣ ይህም ሰብዓዊ አባት በቤቱ ውስጥ ካለው ሥልጣን ጋር በጣም ይመሳሰላል፡፡

አብ በወልድ ላይ ያለውን ሥልጣን በብዙ መንገዶች እንመለከታለን፡፡ ለአብነት ያህል፣ ከዮሐንስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 40 እንደምንማረው ወልድ የአብን ፈቃድ ይፈፅማል፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁጥር 20 እስከ 22 መሠረት ወልድ ሥልጣንና መንግሥቱን ያገኘው ከአብ ነው፡፡ በመሠረቱ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ደጋግመው እንደሚነግሩን የወልድ ንግሥና ለአብ ንግሥና የሚገዛ ነው፡፡ ይህንንም በተደጋገሙ ሃሳቦች እንመለከተዋለን ኢየሱስ በአብ ቀኝ መቀመጡ፣ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ መቀመጡ በመዝሙር 110 ቁጥር 1 እና በዕብራውያን ምዕራፍ 1 ቁጥር 3 ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ቀኝ የክብርና የኃይል ስፍራ ነው፣ በእርግጠኝነት ግዑዝ ዙፋን ማለት ግን አይደለም፡፡ በመደምደሚያውም ጳውሎስ በ1ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 24 እንዳስተማረው ወልድ መንግሥቱን ለአብ ያስረክባል፡፡ በአጭሩ፣ ቤተሰባዊ ስላሴ፣ አብ በወልድ ላይ ሥልጣን አለው፡፡

በአብና በወልድ መካከል ያለው ግንኙነትና የሥልጣን አጠቃቀም ጥያቄ ውስብስብ ነው፡፡ ግን፣ አብና ወልድ በስላሴ ውስጥ ባላቸው ሃላፊነት ረገድ ልዩነቱን አጉልቶ ለማሳየት የሚጠቅመው ነገር አለው፡፡ ወልድም በገዛ ፈቃዱ ለአብ ራሱን በማስገዛት ድርሻውን ይወጣል፡፡ ወደ ምድርም የመጣው ለአብ ፈቃድ ራሱን ለማስገዛት ሲሆን አብም ሥልጣንን ሁሉ በእጁ ይይዛል፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህ የፍቅር ግንኙነቶች ናቸው፡፡ ማለትም አብ ወልድን ይወዳል ወልድም አብን ይወድዳል እናም አብና ወልድ በስላሴ ውስጥ እርስ በርስ ይከባበራሉ አንዳቸውም ሌላቸውን ደስ ያሰኛሉ፡፡ እንግዲያው፣ እያንዳንዳቸው በሚጫወቱት ሚናና ደስ በሚሰኙበት የእርስ በርስ ፍቅር መካከል ያለውን ምስጢር በጥቂቱም ቢሆን ፈልቀቅ አድርገን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡ [ዶ/ር ሲሞን ቫይበርት]

በተመሳሳይም፣ አብ በመንፈስ ላይ ሥልጣን አለው፡፡ ለምሳሌ፣ በሉቃስ ምዕራፍ 11 ቁጥር 13 እና በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁጥር 17 መሠረት አብ መንፈሱን እንደሚልክ በተደጋጋሚ ተነግሮናል፡፡ በተጨማሪም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 10 ቁጥር 38 አብ ወልድን በመንፈሱ እንዳበረታው እንመለከታለን፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ዳር እስከዳር እንደሚነግሩን፣ መንፈስ ቅዱስ በዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ወኪል ነው፣ ፈቃዱንም ለመፈጸም በአብ ይታዘዛል፡፡ በቤተሰባዊ ስላሴ ውስጥ አብ በወልድ ላይ እንዳለው ሁሉ በመንፈስ ቅዱስም ላይ አለው፡፡

የአብ ሥልጣን ዘወትር የፍቅር ሥልጣን ነው፡፡ የአብ ሥልጣን ወልድን የወደደበት ሥልጣን ሲሆን፣ ወልድም እንዲከብር የሚሻበት ነው፡፡ ይህም ልክ ወልድ አብን ከብሮ ማየት እንደሚሻው ማለት ነው፡፡ በመጨረሻም፣ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የፍቅርን ልብ የሚጋሩ ከሆነ፣ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል አለመስማማት አለ የሚለው ሃሳብ አስቂኝ ነው ምክንያቱም ወልድም ለዘላለም፣ መንፈስ ቅዱስም ለዘላለም የአብን ፈቃድ ለመፈጸም የሚናፍቁ ከሆነ፣አብም ደግሞ ለዘላለም ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሊያከብራቸው የሚሻ ከሆነ፣ በመሠረቱ በእግዚአብሔር ውስጥ የፈቃድ ጠላትነት፣ የፍቅር ጠላትነት ጨርሶ የለም፤ ምክንያቱም በስላሴ ውስጥ ባለው ኅብረት የማንነት ጠብ የለምና፡፡ [ዶ/ር ስቲቭ ብላክሞር]

“አባት” የሚለው ስም በቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት አገልግሎት ላይ እንደዋለ፣ የእግዚአብሔር ስብዕና መገለጫ እንደሆነ ባገኘነው መረዳት መሠረት፣ በፍጥረትና በሰው ዘር ላይ ስላለው የአባትነት ማንነት እንመለከታለን፡፡

አባትነት

የእግዚአብሔርን አባትነት በዝርዝር ከመመልከታችን በፊት፣ ስለ እግዚአብሔር አባትነት የሚናገሩት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን መሆናቸውን ለማመልከት ቆም እንላለን፣ ከዚያን ዘመን ቀደም ብሎ ግን እግዚአብሔር ስሉስ ተፈጥሮውን በግልጽ አሳይቷል፡፡ በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ፣ “አባት” የሚለው ቃል በተቀዳሚነትና በአብዛኛው ለሁሉም ስላሴ እንጂ ለአንዱ የአብ ስብዕና ብቻ አልነበረም፡፡

ሆኖም ግን፣ አዲስ ኪዳን የእግዚአብሔርን አባትነት በተቀዳሚነት ከአብ ጋር ያገናኘዋል፡፡ እንግዲያው፣ እነዚህን የብሉይ ኪዳን ክፍሎች በአብ ስብዕና ላይ በማትኮር መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡

የእግዚአብሔር አባትነት ልንነጋገርበት የሚገባ ብዙ ገጽታ አለው፡፡ ግን ለአሁኑ በጣም ወሳኝ የሆኑ ሃሳቦች በያዙት ሦስት የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ላይ እናተኩራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የአብ የፈጣሪነት ድርሻ እንመለከታለን፣ ሁለተኛ፣ አባትነቱን በፍጥረቱና በሕዝቦች ላይ ካለው ንግሥና አንፃር እንዳስሳለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ አብ በሕዝቡ ላይ እንደ ቤተሰብ ራስ የተገለጠበትን ሃሳብ እናተኩርበታለን፡፡ አስቀድመን የፈጣሪነት ድርሻውን ከአባትነት ገፅታው አንፃር እንመለከታለን፡፡

ፈጣሪ

ሰፋ ባለ እሳቤ፣ አንዳንድ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔርን በፍጡሩ ሁሉ ላይ ካለው አባትነት አንፃር ይገልጡታል፡፡ ለምሳሌ፣ ይህንን ዘዳግም ምዕራፍ 32 ቁጥር 6፣ ኢሳያስ ምዕራፍ 43 ቁጥር 6 እና 7፤ ምዕራፍ 64 ቁጥር 8፤ ሚልክያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 10 እና ሉቃስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 38 በመሳሰሉ ምንባቦች ላይ እናገኘዋለን፡፡

ለምሳሌ አንዱን ለማንሳት ያህል፣ ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 ቁጥር 26 እስከ 28 ለአቴናውያን የተናገራቸውን ቃላት እናድምጥ፡

ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።

ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች፥ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። (ሐሥ 17፥26-28)

ጳውሎስ በዚህ ስፍራ የጠቀሰው ዜየስ የሰው ዘር አባት ነው ምክንያቱም ፈጥሮአቸዋልና በማለት ከተናገሩት የአረማውያን ገጣሚዎች ከሆኑት ክሊንቴስና አራቴስ ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር እንጂ ዜየስ እውነተኛ ፈጣሪ እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡ ግን ጳውሎስ በዚያውም አንድን ነገር መፍጠር ማለት የዚያ ፍጡር አባት መሆን ማለት መሆኑንም አረጋግጧል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ቋንቋ ተጽፏል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር እንደ ፈጣሪ ያለን ሰብዓዊ ግንኙነት ከአባትና ከልጆቹ ጋር ከሚኖረው ግንኙነት አንፃር በተደጋጋሚ ተገልጧል፡፡ በዚህ አውድ፣ የእግዚአብሔር አባትነት የእኛን መገኛና የእርሱን ሥልጣን ይወክላል፡፡ [ዶ/ር ፖል ቻንግ]

ልክ ሰብዓዊ አባቶች ልጆቻቸውን እንደሚታገሡ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር በፍጥረቱ ላይ ያለው አጠቃላይ አባትነትም ይህንን የወደቀ ዓለም በተለይም ኃጢአተኛውን የሰው ዘር በትልቅ ትዕግሥት እንዲሸከመው ግድ ይለዋል፡፡ ይህ ማለት ግን በፍጥረቱ ላይ አይፈርድም ማለት አይደለም፡፡ ግን በመዝሙር 145 ቁጥር 8 እና 9 ለምን ለቁጣ የዘገየ ምህረቱንም ለማሳየት ፈጣን እንደሆነ ለማብራራት ይጠቀማል፡፡

እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፥ ከቍጣ የራቀ፥ ምሕረቱም ብዙ ነው

እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው። (መዝ 145፥8-9)

የእግዚአብሔርን የፈጣሪነት ድርሻ ከተመለከትን፣ የንጉሥነት ድርሻው ከአባትነቱ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ እንመለከታለን፡፡

ንጉሥ

በጥንታዊው የቅርብ ምሥራቅ አገሮች ውስጥ፣ ሕዝቦች ንጉሦቻቸውን እንደ አባት፣ ንጉሦች ደግሞ ሕዝባቸውን እንደ ልጆቻቸው መቁጠር የተለመደ ነበር፡፡ ይህ ቋንቋ በቅዱሳት መጻሕፍትም ተደጋግሞ ይንጸባረቅ ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ እስራኤላውያን ዳዊትን እንደ አባታቸው ይቆጥሩት ነበር ምክንያቱም ንጉሥ ስለነበረ ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ ጥቂት እሥራኤላውያን የዳዊት ዝርያዎች ናቸው፣ ስለዚህም በቀጥታ ቀደምት አባታቸው ይሆናል፡፡ ግን ጠቅላላ አገሪቱ ዳዊትን እንደ አባት ከቆጠረችው፣ ንጉሣቸው ስለሆነ ነው፡፡ በማርቆስ ምዕራፍ 11 ቁጥር 10 ላይ ሕዝቡ በዚህ መንገድ ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲያሰማ አድምጡ፡፡

በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ … (ማር 11፥10)

በዚህ ስፍራ የዳዊት አባትነት ተለይቶ የተያያዘው ከንግሥናው ጋር ነው፡፡ በተመሳሳይም፣ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 4 ቁጥር 25 እና 26 በነዚህ ቃላት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡

በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ። አሕዛብ ለምን አጕረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ?

የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ ብለህ የተናገርህ አምላክ ነህ። (ሐሥ 4፥25-26)

እንደገና፣ ዳዊት የእስራኤል አባት ተብሎ ተጠርቷል ምክንያቱም በጌታ የተቀባ፣ በጌታም ዙፋን ተቀምጦ እስራኤል ከጠላቶቿ መንግሥታት ጋር በምታደርገው ውጊያ የሚመራት ንጉሥ ስለነበር ነው፡፡ ግን የጥንቶቹ ንጉሦቻቸውን እንደ አባቶቻቸው የሚቆጥሩት ለምንድን ነበር?

በጥንታዊው ዓለም የነበሩ ነገሥታት ራሳቸውን “አባት” ብለው ይጠራሉ ምክንያቱም የወላጅነትን ባህርይ ያሳዩ ስለነበር፣ ማለትም ለሕዝባቸው ክብካቤ ያደርጉ፣ መሻቶቻቸውን ያሟሉ፣ ከባላጋራዎቻቸው ይጠብቁዋቸው እና የመሳሰሉ ነገሮችን ያደርጉ ስለ ነበር ነው፡፡ ወደ እውነታው ስንመጣ ግን፣ አብዛኛው ነገር ፕሮፓጋንዳ ብቻ ይሆናል ምክንያቱም በጥንታዊው ዓለም የነበሩ ንጉሦች አብዛኞቹ ከሕዝባቸው ይልቅ ራሳቸውን የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡ ግን በዚያው ዘመን፣ እግዚአብሔር ራሱን ለእስራኤል ሲገልጥ፣ ይህንኑ ነገሥታት እንደ አባት የሚታዩበትን የተለመደ አስተሳሰብ ተጠቀመ፡፡ እናም እግዚአብሔር አባታችን፣ ንጉሣዊ አባታችን፣ ግርማዊ አባታችን፣ የመሆኑን ጉዳይ ስናነሳ ባዶ ፕሮፓጋንዳ አይደለም እውነት ነው! እግዚአብሔር ስለ እኛ ግድ ይለዋል፡፡ ይመግበናል፡፡ ልክ እንደ አባት ይጠብቀናል፡፡ እንግዲያው እርሱ የግዛቱ አባት ነው፣ የመንግሥቱም አባት ነው፡፡ [ዶ/ር ሪቻርድ ፕራት፣ ትንሹ]

ሰብዓዊ ነገሥታት የሕዝቦቻቸው አባቶች ይባሉ እንደነበረው ሁሉ፣ እግዚአብሔርም “አባት” ተብሎ ተጠርቷል ምክንያቱም እርሱ የምድር ነገሥታትን ሁሉ የሚገዛ ንጉሥ ነበርና ደግሞም በእርሱ የተመረጠችውን እስራኤልን በቀጥታ ይመራ ነበርና ነው፡፡

ስለ ጌታ አባትነት በኢሳያስ ምዕራፍ 63 ቁጥር 15 እና 16 የተጻፈውን እናንብብ፡

ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ።

አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።

(ኢሳ 63፥15-16)

በዚህ ስፍራ፣ አእግዚአብሔር እንደ አባት ተጠቅሷል ምክንያቱም ፍጥረትን በጠቅላላ፣ እስራኤልን ደግሞ በተለየ መንገድ እየመራ በሰማያዊ ዙፋን ላይ ተቀምጧልና፡፡ በተለይም፣ መለኮታዊው ንጉሥ በጦርነቱ ውስጥ ሠራዊቱን እንዲመራ፣ ጠላቶቻቸውንም ድል በማድረግ ሕዝቡን እንዲታደግ ልመና ይቀርብለታል፡፡

አባት ልጆቹን እንደሚንከባከብ ሁሉ መለኮታዊ ንጉሣችንም በዚያው ዓይነት (እጅግም በተሻለ መንገድ) ስለ እኛ ግድ የሚለው መሆኑን ማወቃችን ትልቅ መተማመንንና መጽናናትን ይሰጠናል፡፡ በራሳችን አቅም፣ በዚህ ዓለም የክፉ ኃይላት ፊት መቆም የማንችል ነን፡፡ መለኮታዊ ንጉሣችን ግን በእውነት እንደ አባት ስለሚወድደን ሊረዳን ዝግጁ ነው፡፡

በመሠረቱ፣ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ስለ ጌታ ጸሎት ባስተማራቸው ወቅት “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ብለው እንዲጸልዩ ሲያዛቸው አንዱ ሃሳብ ይህንኑ ያዘለ ነው፡፡ በዚህ የጌታ ጸሎት ልመና ውስጥ እግዚአብሔር በሰማያት የሚኖር አባት ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የሰማይ ምስል ከዳር እስከዳር ተመሳሳይ ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር ዙፋን መቀመጫ፣ በዚያም ተቀምጦ መንግሥታትን የሚመራበትም ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ሲነግራቸው፣ እግዚአብሔር ንጉሣዊ አባታችሁ፣ በሰማያት በዙፋኑ ላይ የተቀመጠ መለኮታዊ ንጉሥ እንደሆነ አውቃችሁ ጸልዩ ማለቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር የዕለት እንጀራችንን እንደሚሰጠን፣ በደላችንን ይቅር እንደሚለን፣ ከፈተና እንደሚጠብቀን፣ ከክፉውም እንደሚያድነን የምንተማመነው የሚወድደን ንጉሣችን፣ እነዚህን ነገሮች የመፈፀም መሻትምም ኃይልም ያለው በመሆኑ እውነታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

እግዚአብሔርን በፈጣሪነቱና በንጉሥነቱ እንዲህ ከተረዳን፣ የአባትነቱ ገጽታ አንዱ ክፍል የሆነውን የቤተሰብ ራስነቱን እንመለከታለን፡፡

የቤተሰብ ራስ

እኔን ከሚማርኩኝ ነገሮች አንዱ ነገረ-መለኮት ዘወትር ምጋቤያዊ እንድምታ ያለው መሆኑ ነው፡፡ የምናምነው ነገር ልንሆን በሚገባን ማንነት ላይ የራሱ ተፅዕኖ አለው ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር አባታችን ጋር ካለን ግንኙነት አንፃርም እውነትነት አለው፡፡ እኔ እንደማስበው መልካም አባቶች ለነበሩንም ላልነበሩንም ለሁለቱም ይሠራል፡፡ እኔም መልካም አባት ስለነበረኝ እድለኛ ነኝ፣ ስለዚህም እግዚአብሔርን እንደ ሰማያዊ አባቴ መቁጠር መቼም ቸግሮኝ አያውቅም፡፡ አባቴ የነገረኝ ነገሮች ሁሉ፣ ያደረገልኝ ነገሮች ሁሉ፣ እርስ በርስ የነበረን ቀረቤታ፣ እግዚአብሔር አብን በበጎ ገጽታ ለመመልከት እጅግ፣እጅግ ወሳኝ ነበር፡፡ ግን ከዓመታት በኋላ የአባትነት ቋንቋ እጅግ አፍራሽ፣ መከረኛ፣ አስቸጋሪ ከሆነባቸው ሰዎች ጋር በሥራ ምክንያት ተገናኘሁ፡፡ ከሁሉ ይልቅ ግን ከአንድ ተማሪዬ ጋር ያሳለፍኩትን የሥራ ቀን አስታውሰዋለሁ፣ እርሷም “እግዚአብሔር እስከዛሬ አግኝቼው የማላውቀውን ዓይነት አባት ሆኖልኛል” በማለት አተያዬን በአግባቡ ቀረፀችልኝ፡፡ እናም፣ የእግዚአብሔርን አባትነት ስንደርስበት፣የአባትነት ፍቅርን ካጣንበት ሕይወት ውስጥም ቢሆን እንኳን፣ በምድራዊ አባቶቻችን ያንን አገኘነውም አጣነውም የእግዚአብሔር ልብ ወደ እኛ የሚያዘነብል ልብ መሆኑን እንረዳለን፡፡ [ዶ/ር ስቲቭ ሃርፐር]

እያንዳንዱ ሰው የቤተሰብ ራስ ከሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጋር ይተዋወቃል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወላጅ፣ አያት፣ ወይንም ሌላ ዘመድ ሆኖ ቤተሰብን ወይንም አንድን ቤት የሚመራና ውሳኔ የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት በተደጋጋሚ የሚገልፁት በእነዚህ ተመሳሳይ አባባሎች ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን አንዳንድ ወቅቶች ላይ፣ እግዚአብሔር የሰው ዘር ቤተሰብ ራስ የነበረበትን ብልጭታ እናያለን፡፡ ለምሳሌ፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ቁጥር 1 እስከ 3፣ ሙሴ እግዚአብሔር ከአዳም ጋር የነበረውን ዝምድና አዳም ከልጁ ከሴት ጋር የነበረውን ዝምድና በገለጸበት ተመሳሳይ መንገድ ገልጦታል፡፡

በብሉይ ኪዳን በተደጋጋሚ ጊዜያት፣ የእስራኤል ብሔራዊ ቤተሰብ አባት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይህንንም በዘዳግም ምዕራፍ 1 ቁጥር 31፣ በመዝሙር 103 ቁጥር 13 እና በምሳሌ ምዕራፍ 3 ቁጥር 12 በመሳሰሉት ስፍራዎች ለሕዝቡ በሚያደርገው ክብካቤ ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡ አንድ ምሳሌ ለመጨመር ያህል፣ በሆሴዕ ምዕራፍ 11 ቁጥር 1 የተጻፈውን የጌታን ንግግር አድምጡ፡

እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። (ሆሴዕ 11፥1)

በዚህ ስፍራ ጌታ ራሱን የእስራኤልን መንግሥት ገና ከሕፃንነቷ ጀምሮ እንደሚወድድ ወላጅ ገልጧል፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር በዘኁልቁ ምዕራፍ 12 ቁጥር 7 ላይ፣ ጌታ በዚህ መንገድ የእስራኤል ቤተሰብ ራስ ሆኖ ለሙሴ ተገልጦ እናየዋለን፡

ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። (ዘኁ 12፥7)

“ቤት” የሚለው ቃል ባዪት የሚባለው የዕብራይስጥ ቃል ፍቺ ነው፡፡ ይህ ቃል ህንፃውን ብቻ ሳይሆን በህንጻው ውስጥ የሚኖሩትንም ሁሉ የሚያካትት የተለመደ ቃል ነው፡፡ በዚህ ስፍራ፣ ሙሴ እንደ ልጅ ወይንም በሕዝቡ ላይ እና በቤቱ ላይ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ እንደ ተሾመ ባሪያ የተገለጠ ሲሆን፣ ይህም እግዚአብሔር በእስራኤል መንግሥት ላይ የቤተሰብ ራስ መሆኑን ያመለክታል፡፡

እርግጥ ነው፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንደ ቤተሰብ ራስ የሚገለጥበት መገለጫ በአዲስ ኪዳንም ቀጥሏል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 7 ቁጥር 9 እስከ 11፣ ሉቃስ ምዕራፍ 11 ቁጥር 11 እስከ 13 ላይ ሰብዓዊ አባቶች ልጆቻቸውን እንደሚመግቡ ሁሉ አብም ለጸሎቶቻችን መልስን እንደሚሰጠን ኢየሱስ አስተምሮናል፡፡ በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 12 እና 13፣ እንዲሁም በ1ዮሐንስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 29 እና ምዕራፍ 3 ቁጥር 1 ላይ የእርሱ ቤተሰብ አባላት ሆነን በመወለዳችን እግዚአብሔር እንደሚወደን እናውቃለን፡፡ በዕብራውያን ምዕራፍ 12 ቁጥር 5 እስከ 10 ባለው ክፍል ልክ ምድራዊ አባት ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ እግዚአብሔርም ለጥቅማችን እንደሚቀጣን እናነባለን፡፡ 1ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 15 እና 1 ጴጥሮስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 17 በመሳሰሉ ምንባቦች ቤተክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ ተጠቅሳለች፡፡

በእግዚአብሔር አባትነት ውስጥ ትልልቅ ምጋቤያዊ እንድምታዎች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ ከምናያቸው ነገሮችም መካከል በፍጥነት የምናየው እግዚአብሔር አባት መሆኑን ነው፡፡ ማለቴ አብ ምን እንደሚመስል መመልከት፣ እግዚአብሔርን በቅዱሳት መጻሕፍት መመልከት በጣም ትልቅ የዐይን መገለጥ ነው፡፡ እንግዲያው ገና ከጅማሬው ያ ቤተሰብ ለእግዚአብሔር በጣም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ገና ከዘዳግም ምዕራፍ 6 ጀምሮ ጌታ “ስሙ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ሕጌን አንዲቀጥል የማደርገው በቤተሰብ በኩል ነው” ብሎ ጌታ ተናግሯል፡፡ ይህም ልክ ወላጆች የልጆቻቸውን ትከሻ መታ መታ አሸት አሸት ሲያደርጉ፣ ሕይወታቸውንም ለልጆቻቸው ሲሉ አሳልፈው ሲሰጡ፣ እጅግ ትልቅ ነገር ይሆናል፡፡ ቤተሰብ ለእግዚአብሔር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ እንደማስበውም እናንተም ብትሆኑ አባቶች ለቤተሰብ ወሳኞች መሆናቸውን ትገነዘባላችሁ፡፡ በዚህም ያለውን ምጋቤያዊ እንድምታ እናያለን፡፡ ይህም በመላው ዓለም አባቶች ጠንካራ ሲሆኑ፣ ጠንካራ ባህል ታገኛላችሁ፡፡ አባቶች ደካማ ሲሆኑ፣ ባህልም ደካማ ይሆናል፡፡ ይህም በእናትነት የማይተካ ደካማነት ይከሰታል፡፡ ጠንካራ እናቶች ያስፈልጉናል፣ ስለእርሱ ምንም ጥያቄ የለንም፣ ግን አባቶች ፍፁም ወሳኝ ናቸው፣ እንደማስበውም በእግዚአብሔር አባትነት ውስጥ የምንመለከተውም ይህንኑ ብርቱ ነገር ነው፡፡ አባትነት ሲጎድል፣ በእድገት ወቅት መንገላታት ይኖራል፣ መማር አይቻልም፣ በእድገት ወቅትም ወንጀል ይበረክታል፡፡ እንግዲያው ይህ ሁሉ ምስቅልቅል በየባህሉ የሚከሰተው ስለ አባትነት የተዳከመ አስተሳሰብ ሲኖር እና እግዚአብሔር እንደ አባት የማየቱ እሳቤ ሲዳከም ነው፡፡ [ዶ/ር ማት ፍራይድ ማን]

የሁሉን ቻዩን አባት ስም፣ ስብዕና እና አባትነት ዳስሰናል፣ አሁን ደግሞ ፈቃዱን ለመፈፀም የሚያስችለውን የማይገደብ ኃይሉን ለመመርመር እንዘጋጃለን፡፡

ኃይል

አንድ ጊዜ መለስ እንበልና በሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ውስጥ የተጠቀሰውን የመጀመሪያ የእምነት አንቀጽ እንመልከት፡፡ እንዲህ ይላል፡

እኔ ሁሉን በሚችል ሰማይንና ምድርን በፈጠረ

በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ፡፡

የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫው እግዚአብሔር አብ ሁሉን ቻይ ነው ሲል፣ አቻ የሌለውና የማይገደብ ኃይል አለው ማለት ነው፡፡ በትፊታዊው የነገረ-መለኮት አባባል የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ኃይል ከእርሱ ሁሉን ቻይነት (omnipotence) ጋር ተጠቅሷል፣ ስርወ ቃሉም (omni, meaning all, and the word potency, meaning power.) ነው፡፡

የአብ ኃይል የማይገደብ ነው ምክንያቱም የወደደውን ሁሉ የማድረግ ብቃትና ጥንካሬ አለው፡፡ ይህን መሳይ ኃይል ያለው እርሱ ብቻ ስለሆነ የሚስተካከለው የለም፡፡

ከላይ የገለጥናቸውን የአብን ኃይል ገጽታዎች ተመልክተናል፡፡ እነርሱም የማይገደብ እና የሚስተካከለው የሌለ የመሆኑ እውነታ ናቸው፡፡ እስኪ በማይገደበው የኃይሉ ተፈጥሮ እንጀምር፡

የማይወሰን

ቅዱሳት መጻሕፍት አብ የወደደውን ማድረግ የሚችልበት ኃይል እንዳለው ይገልጡልናል፡፡ ይህንንም የማይወሰን ኃይል በተለያየ መንገድ ይገልጠዋል፡፡ ዓለምን ለመፍጠር እና ለማጥፋትም የሚያስችለው ኃይል አለው፡፡ አየሩን የሚቆጣጠርበት፣ ጠላቶቹን በጦርነት የሚረታበት፣ ሰብዓዊ መንግሥታትን የሚገዛበትና የሚቆጣጠርበት፣ ታላላቅ ተዓምራትን የሚገልጥበት እና ህዝቡን የሚያድንበት ኃይል አለው፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ በኤርምያስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 10 እስከ 16 ስለ ጌታ የተናገረውን አዳምጡ፡

እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፥ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች አሕዛብም መዓቱን አይችሉም።

እናንተም፥ ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ ትሉአቸዋላችሁ።

ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።

ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይሰበሰባሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል።

ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና።

እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ።

የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። (ኤር 10፥10-16)

እግዚአብሔር የፈጠረውን ዓለም ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ይቆጣጠራል፡፡ ደስ ያሰኘውን ለማድረግ ኃይል አለው፡፡ በኢሳያስ ምዕራፍ 46 ቁጥር 10 እና 11 ላይ፣ ጌታ ራሱ የእርሱን ኃይል እንዲህ አስቀምጦታል፡

በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።

ከምሥራቅ ነጣቂ ወፍን፥ ከሩቅም አገር ምክሬን የሚያደርገውን ሰው እጠራዋለሁ። ተናግሬአለሁ እፈጽማለሁ አስቤአለሁ አደርግማለሁ።

(ኢሳ 46፥10-11)

ዓለም ከቁጥጥር ውጪ በመሆን ማብቂያ ወደ ሌለው ቀውስ በመገስገስ የምትጦዝ ስትመስል የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት (omnipotence) እንደ ታደገን ለእኛ እንደ ክርስቲያኖች ትልቅ ማሳሰቢያ ነው፡፡ እግዚአብሔር መቼም ቢሆን ከእርሱ በላይ በሆነ ኃይል ወይንም ምንጭ ሊገደብ ጨርሶ አይችልም፡፡ ዓለም፣ ምንም ትምሰል ምንም፣ ዓለም በፍፁም ከቁጥጥር ውጪ ልትጦዝ አትችልም፣ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው፣ ከእርሱ በላይ የሆነ ኃይል ሊጫነው አይችልም ስለዚህም በእርሱ እንተማመናለን፣ ለዚህች ውሱን ለሆነች አስተሳሰባችን ምስጢራዊ የሚመስሉ ነገሮች ቢከሰቱም በእርሱ ሉዓላዊነት በመበርታት በእምነት እንራመዳለን፡፡ እግዚአብሔር የሚያየውን ማየት ሲሳነን፣ የእርሱ ኃይል ከፈቃዱ ውጪ እንዲፈፅም አንድ ታጋይ ከእጁ እንደወሰደበት እና ነገሩን መቆጣጠር እንደተሳነው ልናስብ አይገባም፡፡ ወደ እኔ ምንም ነገር ይምጣ፣ በሕይወቴ ምንም ይከሰት ምንም፣ ሁሉ የሆነው በእግዚአብሔር አፍቃሪ እጅ ሥልጣን ስር ነው፡፡ ምንም እንኳን ያለሁበትን ሁኔታ በውል መግለጥ የማልችልበት ሁኔታ ውስጥ ብሆንም፣ የሚያፀናኝና አብሮኝ በነገሮቹ ውስጥ የሚጓዝ አምላክ እንዳለኝ ስለማውቅ በእርሱ እተማመናለሁ፡፡ (ዶ/ር ሮበርት ጂ. ሊስተር)

በመላው መጽሐፍ ቅዱሳችን፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በውል እንደሚያመለክቱት እግዚአብሔር ህዝቡን የተቤዠበት ሥራው የኃይሉ እንከን የለሽ መግለጫ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ በዘፀአት ግብፃውያንን በወረርሽኝ ሲመታ፣ እስራኤልንም ከባርነት ነፃ ሲያወጣ፣ ለአርባ ዓመታትም ሕዝቡን በምድረበዳ ሲመግብ፣ የተስፋይቱንም ምድር በድል ሲያወርሳቸው ኃይሉን ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸ ተጽፎ እናነባለን፡፡ በጥንታዊቷ እስራኤል ልቡና ውስጥ፣ ዘፀአት ጨርሶ የማይዘነጉት የእግዚአብሔር ቤዛዊ ኃይል ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡

በእስራኤል መውጣትና በጠቅላላው የሕግ መጻሕፍት እንደ ዘፀአት ምዕራፍ 14 ቁጥር 31፤ ዘኁልቁ ምዕራፍ 14 ቁጥር 31 እና ዘዳግም ምዕራፍ 9 ቁጥር 26 እስከ 29 በመሳሰሉት ምንባቦች ውስጥ የእግዚአብሔርን ኃይል ማስረጃዎች እናገኛለን፡፡ በተቀሩትም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ይህንን መሪ ሃሳብ እናገኛለን፡፡ በታሪክ መጻሕፍት 2ነገሥት ምዕራፍ 17 ቁጥር 36፤ በግጥም መጻሕፍት መዝሙር 66 ቁጥር 3 እስከ 6 በመሳሰሉ ስፍራዎች፤ በትንቢት መጻሕፍት ደግሞ እንደ ኢሳያስ 63 ቁጥር 12 በመሳሰሉ ስፍራዎችም እናገኘዋለን፡፡

ይህ ማለት ግን ጥንታዊቷ እስራኤል ይህንን መሳይ ከአዕምሮ በላይ የሆነ ታላቅ የመንፈሳዊ መቤዠት ከጌታ በጸጋ በእምነት መቀበሏን ቸል አለችው ማለታችን አይደለም፡፡ “በእግዚአብሔር ኃይል አምናለሁ” የሚሉና የመሳሰሉ ነገሮችን ሲናገሩ ለእነርሱ ትልቅ የከበረ ዋጋ እንዳለው ያመለክታል፡፡ የብሉይ ኪዳን በርካታ ጸሐፍት ግን “በእርሱ ክንድ ብቻ መንግሥታችንን ከባርነት ነጻ በማውጣት እግዚአብሔር ኃያልነቱን አረጋግጧል” ብሎ መጻፍ የተሻለ ማራኪ እንደሚሆን በማመን እንደዚያው ጽፈዋል፡፡ ይህ አስገራሚ ሊሆንብን አይገባም፡፡ እንዲያውም፣ በዘፀአት የታየው የእግዚአብሔር ኃያልነት ውጫዊ መገለጫ የማይካድና የማያምኑት ግብፃውያን እንኳን ሳይቀሩ ያመኑበት ነው፡፡

ይህንን የእግዚአብሔር የማይወሰን ኃይል መረዳት በአዕምሯችን እንደያዝን፣ ምንም እንኳን እግዚአብሔር የማይገደብ ኃይል ቢኖረውም ፈጽሞ ግን ሊያደርግ የማይችላቸው የተወሰኑ ነገሮች እንደሚኖሩ ለማንሳት ቆም ማለት ይገባናል፡፡ በተለይም፣ የአብ ማንነት የሚያደርገውን ሁሉ ይቆጣጠራል የሚለውን አፅንዖት በመስጠት ከማንቱ ጋር የሚፃረሩ የትኞቹንም ነገሮች ጨርሶውኑ ሊያከናውን እንደማይችል ልንረዳ ይገባል፡፡

ማንነት (ኅላዌ) የሚለው ቃል በጣም አስፈላጊና ግላዊ የባህርይ መገለጫን አጣምሮ የሚይዝ ሰፊ ቃል ነው፡፡ ምናልባትም እንደ አንድ ማንነት መሠረታዊ ባህርይ፤ ወይም እንደ አንድ ማንነት ማዕከላዊ ገፅታ ልንገልፀው እንችል ይሆናል፡፡ ጉዳዩን ከአብ አንፃር ስንመለከተው፣ የእርሱ ኅላዌ ማንነቱንና ባህርዩን ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች የስላሴ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነትም የሚያካትት ነው፡፡ የአብ ኅላዌ ኢ-መዋቲ፣ የማይለወጥና ፍፁማዊ ነው፣ ስለዚህም ኃይሉን በተመሳሳይ መንገድ ሳይለዋወጥ እንዲገልጥ ያስችለዋል፡፡ ያእቆብ ምዕራፍ 1 ቁጥር 17 በዚህ መንገድ ይህንን የማይለዋወጥ የእግዚአብሔር ተፈጥሮ ይገልጥልናል፡፡

… መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። (ያዕ 1፥17)

የአብ ኅላዌ ከማንነቱ ጋር የሚጣጣሙ ነገሮችን ከማድረግ አይገድበውም፡፡ ግን የእርሱን ሁሉን ቻይ ኃይል በተግባር የሚገልጠው ከባህርዩ ጋር በማይጣረስ መንገድ መሆኑን በዋስትና አስረግጦ ያሳየናል፡፡ ለምሳሌ፣ በምንም መንገድ ዘላላማዊነቱን ሊቀይረው አይችልም፡፡ በምንም መንገድ ሥልጣኑን ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስም ሊሰርዝ አይችልም፡፡ ኃጢአትንም ጨርሶ አያደርግም፡፡ ተስፋውንም ዘወትር ይጠብቃል፡፡

በዘመናዊው ሳይንስ አድገት ውስጥ የጎላ ድርሻ ያለው ነገር እግዚአብሔር የሚሠራው ትናንት ያደርግ እንደነበረው መሆኑን መረዳት ወይንም እውቅና መስጠት መሆኑን ማሰብ እኔን ይማርከኛል፡፡ አኒሚዝም (ፍጡር ሁሉ ነፍስ አለው ድንጋዩንና ተራራውንም ጨምሮ፣ ሰዎች ከአካላቸው ውጪ የሚሠራ መንፈስ አላቸው ወ.ዘ.ተ. የሚል ፍልስፍናዊ እምነት) በዓለማችን ብዙዎችን እየማረከ ቢሆንም፣ ብዙ አማልክት አሉ እነዚያም አማልክት በዚህ ዓለም ውቅረ ነገሮች ውስጥ ይኖራሉ፣ እግዚአብሔር ጨርሶውኑ እንዲህ ነው ተብሎ ሊነገር አይችልም (ይለዋወጣል ለማለት ነው)፣ እግዚአብሔር ጨርሶውኑ የማይታወቅ ከሆነ ደግሞ ይህንን ዓለም ማጥናት አይቻልም ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ ነው ያላችሁት ነገ ተለውጦ በሌላ መንገድ ሊጓዝ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን የማይለዋወጥ ከሆነ፣ ወጣ ብላችሁ ዓለምን ልትመረምሩ እና እግዚአብሔር እንዴት እንደሠራትና እንዴትም ተግባሯን እንደምታከናውን ልትረዱ ትችላላችሁ፡፡ በዚህም ምክንያት በእግዚአብሔር አለመለዋወጥ ላይ ያለው የእምነት አቋም ዘመነኛው የሳይንስ ምርምር እንዲነሳ አስችሎታል፡፡ ለዘመነኛው ሳይንስ ማቆጥቆጥ እገዛ እንዳደረገ ሁሉ፣ ክርስቲያኖችም ሁሉን በግልጽ አጥርተው መመልከት ባልቻሉባቸው አጠራጣሪ በሆኑ ነገሮች ላይ ዋስትናና ምቾት እንዲሰማቸው አስችሏቸዋል፡፡ ከዕይታችን ከተሰወረ ሰዋራ ስፍራ ምን ሊመጣ እንደሚችል ማወቅ ግዴታ አይሆንብንም፡፡ ልናውቅ የሚገባን ነገር የእኛ እግዚአብሔር የሚያጋጥመንን የትኛውንም ተግዳሮትና መሻት ሊጋጠምና ሊያሟላ ብቃት ያለው መሆኑን እና ልክ ለዳዊት፣ ለአብርሃም፣ ለአዳም፣ ለኢየሱስና ለጳውሎስ ተስፋ እንደሰጠው፣ ሁሉ የእኛንም ሁኔታ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ እንደሚጋጠመው በውል መረዳት ነው፡፡ እርሱ ሊታመኑት የተገባ፣ ታማኝ፣ የማይለዋወጥ፣ ከዕለት ወደ ዕለት የማይቀያየር፣ እኛ የምንገኝበትን የትኛውንም ሁኔታ መልስ ሊሰጠው የሚያስችለው ኃይል አለው፡፡ [ዶ/ር ጄ. ሊጎን ዱንካን ሣልሳዊ]

የማይወሰነውን የአብን ጉልበት ከተወያየንበት፣ አሁን ደግሞ እግዚአብሔር ብቻውን ሁሉን ቻይ ነው የሚለውን አቻ የለሽነቱን እንመለከታለን፡፡

አቻ የሌለው/አምሳያ የለሽ

በኢሳያስ ምዕራፍ 14 ቁጥር 24 እስከ 27 የእግዚአብሔር አቻ የሌለው ኃይል የተገለጠበትን መንገድ አድምጡ፡

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል። እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፥ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል።

አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፥ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሣል፥ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል።

በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ ይህ ነው፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት።

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች የሚመልሳትስ ማን ነው? (ኢሳ 14፥24-27)

በዚህ ምንባብ፣ የጌታ የማይወሰን ኃይል በተገለጠበት መግለጫ ውስጥ እርሱ ብቻ ሁሉን ቻይ የመሆኑ ማረጋገጫም መከተሉን ልብ ማለት ይገባል፡፡ እርሱን ሊያጨናግፈው የሚችል፣ እጁንም መመለስ የሚችል ማንም የለም፡፡

የአብ ኃይል ወደር የሌለው የመሆኑ እውነታ እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ ነው ከሚለው ጭብጥ የሚፈልቅ ነው፡፡ የማይገደብ ኃይል ያለው ሌላ ማንነት ቢኖር ኖሮ፣ የእግዚአብሔር ብቸኛ አምላክነት ያለጥርጥር በጥያቄ ውስጥ ይወድቅ ነበር፡፡ በመሠረቱ፣ የማይገደብ ኃይል ያለው ማንነት አንድም መለኮታዊ፣ አሊያም በእርሱ በራሱ ኃይል መለኮትነትን የተላበሰ ሊሆን ግድ ነው፡፡

እግዚአብሔር ለኢዮብ በምዕራፍ 38 የነገረው ፍሬ ነገር ይኸው ነበር፣ ኢዮብ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ማቅረብ የሚችለው እግዚአብሔር በኃይሉ ያከናወናቸውን ተግባራት የሚስተካከሉ ተግባራት ማለትም መፍጠር፣ ፍጥረተ ዓለምን ስርዓት ማስያዝና መግቦታዊ ቁጥጥር ማድረግ የመሳሰሉትን ሊፈጽም እንደሚገባው የሚያሳስብ ነበር፡፡

እውነታው ግን እግዚአብሔር ብቻውን መለኮታዊ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም የማይገደብ ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

አሳዛኝ በሆነ መንገድ ግን፣ ጥሩ አቋም አላቸው የሚባሉ በርካታ ክርስቲያኖች በእኛ ዘመን እግዚአብሔር ኃያል መሆኑን ይክዳሉ፡፡ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ላይ ያሻውን እንደሚያደርግ ቅዱሳት የሚያስተምሩትን በትክክል አይረዱም፡፡ የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት አስደናቂ በሆነ መንገድ የቅዱሳት መጻሕፍት ተግባራዊ ትምህርት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ህዝብ በችግር ውስጥ ሲወድቅ፣ እንደሚያድናቸው በማመን ለእርዳታ ወደ እግዚአብሔር ይጮሃሉ፡፡ ክፉ ዓለምን በቁጥጥሩ ስር ያደረገ ሲመስል፣ እግዚአብሔር በክፉ ላይ የበላይነት እንዳለው በማመን በእረፍት በአስተማማኝ ዋስትና ውስጥ እንሆናለን፡፡ በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ካላመንን፣ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ድል እንደሚነሳ የምንተማመንበት መሠረት የለንም ልጆቹም የገባላቸውን የዘላለማዊ በረከት ተስፋ እንደሚቀበሉ እርግጠኛ መሆን አንችልም፡፡

ሁሉን ቻዩ አባታችን በሚለው ሃረግ ውስጥ ስለተካተተው የበለፀገ ነገረ መለኮት ማሰብ አስደናቂ ነው፡፡ አስገራሚ በሆነ መንገድ የሚንከባከበንን፣ የሚወድደንን፣ ኃያል፣ በግል ማንነታችንን የሚረዳ አባታዊ አምላክ እናገለግላለን፡፡ እርሱ ራሱ የማይወድቅ ስለ ሆነ ጥበቃው እንደማይለየን በማወቅ በፍፁም ዋስትና እንኖራለን፡፡ እርሱ ዘወትር ፈጣሪያችን፣ ንጉሣችንና የቤተሰባችን ራስ ሆኖ ይኖራል፡፡ እርሱ ዘወትር ወሰንና አቻ የሌለው ኃይል አለው፡፡ ፈጽሞም አይለዋወጥም፡፡ እርሱ ዘላለማዊ ስለሆነ ከእርሱ የምንቀበለውም መዳን እንዲሁ ይኖራል ሊያድነንም በዚያ ዘወትር ይኖራል፡፡

በዚህ ትምህርት የስሉስ አምላካችንን ማንነት እና ሁሉን ቻዩ አባታችን ተብሎ የተጠራውን መለኮታዊ አካል ባህርይ ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ አሁን ደግሞ፣ ወደ ቀጣዩ ነጥባችን ለመሸጋገር እንዘጋጃለን፡፡ ይህም ሰማያንና ምድርን የመፍጠር የአብ ድርሻ ነው፡፡

4. ሠሪ

ሰማይንና ምድርን የመፍጠር የአብን ድርሻ በምንዳስስበት በዚህ ትምህርታችን በሦስቱ የፍጥረት ሥራ ገፅታዎቹ ላይ እናተኩራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የአብን የፍጥረት ሥራ እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ፣ በፍጥረት መልካምነት ላይ እናተኩራለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ በፍጥረት ላይ የአብን ሥልጣን እንመለከታለን፡፡ እስኪ አብ በፍጥረት ላይ የገለጠውን ሥራውን እንመልከት፡፡

የፍጥረት ሥራ

የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ለአብ በተለይ ከሰጣቸው ሥራዎች አንዱ ነው፡፡ ፍጥረት ይህንንም በመጀመሪያው የእምነት አንቀጽ እንዲህ ተጠቅሶ ታገኛላችሁ፡

እኔ ሁሉን በሚችል፣ ሰማይንና ምድርን በፈጠረ፣

በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት አብ ያከናውናቸዋል ተብለው ከተጠቀሱት በርካታ ተግባራት መካከል፣ ታሪካዊ ክርስትና የሚያነሳውና ክርስቲያኖች በጠቅላላ ያረጋገጡት አንዱ ሥራ ይህ ነው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ስለሚጠቅሱት፣ እግዚአብሔር የፍጥረተ ዓለም ሁሉ ፈጣሪና ጠባቂ ነው ከሚለው ሃሳብ ጋር አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ይተዋወቃሉ፡፡ በመሠረቱ የመጽሐፍ ቅዱሳችንን የመጀመሪያ ገጽ ገልጠን ስናነብብ፣ የምናገኘው የመጀመሪያ ነገር እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ፈጣሪ መሆኑን ነው፡፡ ከዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 1 እንደምንረዳው፡

በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። (ዘፍ 1፥1)

ከዚህ የመግቢያ ጥቅስ በኋላ፣ የተቀረው የዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ክፍል የሚያወሳው በስድስት ቀናት ውስጥ እግዚአብሔር ፍጥረተ ዓለምን እንደፈጠረና ሥርዓት እንዳስያዘ ነው፡፡

በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ስለፍጥረት የተጻፈውን ቃል አፈታት አስመልክቶ በርካታ የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች ተስተናግደዋል፡፡ በቅርቡ ግን ሁሉም የነገረ መለኮት ምሁራን እግዚአብሔር ፍጥረተ ዓለምን ከሌለ ነገር ፈጠረ (ex nihilo or out of nothing) በሚለው ተስማምተዋል፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ከመፍጠሩ አስቀድሞ፣ ከራሱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ ማንም አልነበረም ለማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረተ ዓለምን የፈጠረበት ቅድመ ነዋሪ ቁስ አልነበረም፡፡ ብዙዎችም እንደሚሉት ጊዜንና ስፍራን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፡፡

ሆኖም ግን የነገረ - መለኮት ምሁራኑ አብ ፍጥረተ ዓለምን የፈጠረበትን የጊዜ ቀመር፣ በተለይም በስድስት ቀናት ውስጥ በሚለው ጉዳይ በተደጋጋሚ ጊዜ አለመስማማቶችን አስተናግደዋል፡፡ በርካታ የቤተክርስቲያን አባቶች፣ እንደ ክሌመንት፣ ኦሪገን እና አውጉስቲን የመሳሰሉት እንደሚያምኑት፣ ቀናቱ በአንድ ወቅት የተከናወኑ የመፍጠር ተግባራት ዘይቤያዊ መግለጫዎች ናቸው ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ግን፣ እንደ ኢራኒየስ እና ተርቱሊያን የመሳሰሉት ሃያ አራት ሰዓታት ያሉዋቸው ቀናት ናቸው ይላሉ፡፡ ቆይቶ ግን፣ ሳይንስ ፍጥረተ ዓለም ረጅም ዕድሜ አስቆጥሯል የሚል ሃሳብ ሲያቀርብ፣ በርካታ የነገረ መለኮት ምሁራን የፍጥረትን ታሪክ በአዲስ መንገድ ማንበብ ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹም፣ ቀኖቹ ሃያ አራት ሰዓታት ናቸው፣ እግዚአብሔር በፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል ግን ረጅም ጊዜ አልፏል የሚል ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ቀናቶቹ የታሪክ ዘመናት ጅማሮዎችንና ዘመናቱን የሚወክሉ ዘይቤያዊ ንግግሮች ናቸው ብለው ፍቺ ይሰጣሉ፡፡

በእርግጠኝነት በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ የተጠቀሰው የፍጥረታት ቀናት ጉዳይ በጣም የጋለና ለበርካታ ሙግቶች መነሻ ነው፡፡ እንደማስበው ከጉዳዮቹ አንዱ፡ ምን ዓይነት ስነ-ጽሑፍ ነው? የሚለው ነው፡፡ ይህ ስነ-ጽሁፍ ስሜትን እንዲቀሰቅስ ተደርጎ የተቀረፀ ነው፣ ወይስ መንፈሳዊ ጭብጥን ለማስተማር የተቀረፀ ነው? በነዚህ በሁለቱ መካከል ልዩነትን ለመፍጠር መሞከር አይገባንም፡፡ እግዚአብሔር የዚህ ዓለም ፈጣሪ ስለሆነ ሁለቱ በጋራ መጣጣም ይኖርባቸዋል፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድን እንደ ሳይንሳዊ ጽሑፍ ከተመለከትነው፣ ከፍጥረት ባህርይና ትርጉም አንፃር ከምናደርገው ውይይት የተለየ ትርጉም እንይዛለን፡፡ [ዶ/ር ጆን ኦስዋልት]

ለቀደምቷ ቤተክርስቲያንና ከሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ አጠቃቀም አንፃር፣ በጣም ወሳኙና አስፈላጊው ነገር እግዚአብሔርና እግዚአብሔር ብቻ፣ በአብ በመመራት ፍጥረተ ዓለምን፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ግዛቶችን ሁሉ፣ በውስጣቸው ካሉ ነገሮችና ጥቃቅን ፍጥረታት ጭምር ፈጥሯል ያፀናልም የሚለውን አማኞች እውቅና እንዲሰጡት ማድረግ ነው፡፡

በነህምያ ምዕራፍ 9 ቁጥር 6 ሌዋውያን ትኩረት ያደረጉበት ሃሳብ ይኸው ነበር፡፡ አስኪ ቃሎቻቸውን አድምጡ፡

አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። (ነህ 9፥6)

በዚህ ስፍራ እንደምናነብበው ፍጥረተ ዓለምን የፈጠረ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እናም አሁንም በውስጥዋ ለሚኖረው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ፣ የፈጠረውንም ዓለም የሚያፀና እርሱ ብቻ ነው፡፡

ምድርንና ሰማይን በመፍጠርና በማፅናቱ ተግባር ውስጥ አብ የመሪነቱን ሚና ቢጫወትም እነዚህ ተግባራት ግን ጠቅላላውን የስላሴ አካላት ያሳተፉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፣ ወልድ አብ ዓለምን የፈጠረበት መሣሪያው ነበር አሁንም በእርሱው ያፀናታል፡፡

እስኪ ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 8 ቁጥር 6 የፍጥረትን ሥራ የገለጠበትን መንገድ እናድምጥ፡

ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን። (1ቆሮ 8፥6)

በዚህ ስፍራ፣ ጳውሎስ አብ የፍጥረት ምንጭ መሆኑን ይገልጣል፡፡ ፍጥረት የተገኘው ከእርሱ ነው፡፡ የመጣው ግን በልጁ በኩል ነው፡፡ ዛሬም በሕይወት እንኖራለን ምክንያቱም አብ በልጁ በኩል ሕይወታችንን ያፀናልና፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት የመንፈስ ቅዱስ ድርሻ ተለይቶ የተቀመጠው በስሱ ነው፡፡ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን ምንባቦች የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ስብዕና አካል ሆኖ በገሃድ አልተገለጠም ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ አዲስ ኪዳን በዓለም ላይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም በሥራ ላይ እንደነበር ያስተምራል፡፡ ይህንንም የብሉይ ኪዳን ጸሐፍት ይነዱ የነበሩት በመንፈስ ቅዱስ እንደ ነበረ እንደሚናገረው እንደ ማርቆስ ምዕራፍ 12 ቁጥር 36 ያሉ ምንባቦች እና መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ዘመንም እንኳን የትንቢትና የመንፈሳዊ ስጦታዎች ምንጭ እንደነበረ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 2 እስከ 17 ጴጥሮስ ባስተማረው ትምህርት ውስጥ ተገልጦ እናነበዋለን፡፡

እንግዲያው፣ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር መንፈስ ተብለው የተጻፉትን ስናነብብ፣ ወደፊት የሚመጣውንና ራሱን የቻለ መለኮት የሆነውን መንፈስ ቅዱስን የሚያመለክት ጥላ እንደሆነ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው፡፡ ለአብነት ያህል፣ በዘፍጥረት 1 ቁጥር 2 እና 3 ላይ እንዲህ ተጽፎ እናነባለን፡

ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።

እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ። (ዘፍ 1፥2-3)

“የእግዚአብሔር መንፈስ” የሚሉት ቃላት ቃል በቃል ሲፈቱ የሚያመለክቱት የእግዚአብሔር አካላት ሁሉ ነው፡፡ ከእኛ የአዲስ ኪዳን አመለካከት አንፃር ግን፣ በመንፈስ ቅዱስ ስብዕና ላይ የሚያተኩሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

በፍጥረት ስራ ውስጥ የአብን ድርሻ ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ አብ በፈጠረው ፍጥረት ውስጥ ያለውን መልካምነት እንመለከታለን፡፡

የፍጥረት መልካምነት

በርካታ ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች ቁሳዊው ዓለም ከግብረገብ ውጪ ነው፣ ብለው ያስተምራሉ፡፡ ማለትም መልካምም ክፉም አይደለም ማለት ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ዓለም ራሷ ክፉ ናት ይላሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የጥንቷ ቤተክርስቲያን የተጋፈጠቻቸው የባህላዊ እምነት ፈላስፎች ቁሳዊው ዓለም ርኩስ ነው፣ በእውነት የሰውን ዘር ለማዳን ከተፈለገ ከአካሎቻቸው እሥራት መፈታት አለባቸው ብለው ያስተምሩ ነበር፡፡ የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው የሚለውን ትኩረት እንዲያደርግበት ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ይህን የመሰለው ስለ ዓለም በሰዎች ዘንድ ያለ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አተያይ፣ ፍጥረተ ዓለም የእግዚአብሔርን መልካምነት የሚያሳይ መልካም ተፈጥሮ ነው፡፡

በዘፍጥረት ምዕራፍ 1፣ የፍጥረት መልካምነት በቁጥር 4፣ 10፣ 12፣ 18፣ 21፣ 25 እና 31 ላይ በድምሩ ሰባት ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ የሁሉም መደምደሚያ በሆነው በቁጥር 31 ላይ ሙሴ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደመዘገበው መላው ፍጥረተ ዓለም “መልካም” ብቻ ሳይሆን “እጅግ መልካም” ነበር፡፡

እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። (ዘፍ 1፥31)

እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን፣ እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ አዳምና ሄዋን መልካምንና ክፉን ከምታስታውቀው ዛፍ በመብላት በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት አደረጉ፡፡ በሰው ዘር ኃጢአትም ምክንያት እግዚአብሔር መላውን ዓለም ረገመ፡፡ ስለዚህም ነገር የሚናገረውና እግዚአብሔር ለአዳም ስለ መርገሙ የተናገረበት ክፍል ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ቁጥር 17-19 ያለው ነው፡፡

አዳምንም አለው፥ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤

እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።

ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና። (ዘፍ 3፥17-19)

በአዳም ኃጢአት ምክንያት፣ እግዚአብሔር ምድርን ረገማት ስለዚህም እርሻ እጅግ አስቸጋሪ ሆነ፣ አዳምና የተቀረው የሰው ዘር በሙሉ ምግቡን ለማግኘት ጥረት አይቀሬ ሆነ፡፡ ይህ የምድር መረገም ግን በእርሻ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ መላውን ዓለም በሁለንተናዊ መልኩ አናጋ፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 8 ላይ ስለ አማኞች በክርስቶስ መቤዠት መከራከሪያውን ሲያቀርብ ይህ መቤዠት የፍጥረት ኅዳሴም እንደሚካተትበት በተናገረው ውስጥ ይህንን ችግር ጠቅሶ ጽፏል፡፡ በሮሜ ምዕራፍ 8 ቁጥር 20 እስከ 22 ጳውሎስ የጻፈውን አድምጡ፡

ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤

ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።

ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና። (ሮሜ 8፥20-22)

የምድር መረገም የፍጥረትን ውቅረ ነገር ሁሉ እንዳናጋ ጳውሎስ ይገልጻል፡፡

የእግዚአብሔር መርገም እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ ፍጥረት ከዚህ በኋላ መልካም ሊሆን አይችልም ብለን ልንሳሳት አይገባም፡፡ አዎን፣ የሰው ዘር በኃጢአት መዘፈቅ የፍጥረትን ውድመት አስከትሏል፡፡ ግን አሁንም የእግዚአብሔር ዓለም ስለሆነ፣ አሁንም በመሠረቱ መልካም ነው፡፡ ጳውሎስ ስለ ጋብቻ ጠቃሚነት በተናገረበትና ክርስቲያኖች ሁሉን አይነት ምግብ የመመገብ ነፃነት እንዳላቸው በጻፈው ውስጥ ይህንን ነጥብ ግልጽ አድርጎታል፡፡ በ1 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 4 ቁጥር4 የተናገረውን አድምጡ፡

እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ (1ጢሞ 4፥4)

በዚህ ስፍራ ጳውሎስ የተናገረውን ልብ በሉ፡፡ የተፈጠረ ነገር ሁሉ “መልካም” ነው አላለም፣ ያለው እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም “ነው” ነው፡፡

እግዚአብሔር መልካም ነው ያለው ቁሳዊው ዓለም መልካም ነው የሚለው እውነታ ለእኛ በርካታ ተግባራዊ እንድምታዎች አሉት፡፡ አንደኛው አካባቢያችንን መጠበቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ የፍጥረቱ ባለ አደራዎች ነን፡፡ ሌላኛው ደግሞ፣ እግዚአብሔር ፍጥረትን የሚጠብቅ መሆኑ ነው፡፡ እንደገና መልሶ ይፈጥራል፡፡ ማለትም የፍጥረት ውድመት ሳይሆን የፍጥረት ተሃድሶ ይኖራል፡፡ በአዲስ ሰማይና ምድር ለዘላለም እንኖራለን፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ገሃዱ ዓለም መልካም ነው፡፡ አካላችን፣ ህልውናችን ሁሉም መልካሞች ናቸው፡፡ [ዶ/ር ማርክ ስትራውስ]

እንግዲያው፣ ስለጋብቻም ሆነ ስለ ምግብ ወይንም ስለማንኛውም በእግዚአብሔር ስለተፈጠረ ነገር እንነጋገር፣ ሁሉም መልካም መሆናቸውን በእርግጠኝነት እንናገራለን ምክንያቱም ፈጣሪያቸው መልካም ነውና፡፡ ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 1፣ የእግዚአብሔር መልካምነት ለሰው ዘር በሙሉ በፍጥረት በኩል ግልጽ ሆኖ የሚታይ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ለዚህም ነው መዝሙር 19 ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ በማለት የሚያውጀው፡፡

ጆን ዌስሊ በዐሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ሥራው (A Survey of the Wisdom of God in the Creation, part 3, chapter 2) እስኪ ምን እንደጻፈ አድምጡ፡

መላው ፍጥረተ ዓለም፣ የፈጣሪው እንከን አልባነት በግልጽ የተንፀባረቀበት ስዕል ነው፡፡ የእርሱን መኖር ብቻ ሳይሆን፣ አንድነቱን፣ ኃይሉን፣ ጥበቡን፣ የማንም ጥገኛ አለመሆኑን እና መልካምነቱንም ያሳያል፡፡

ፍጥረተ ዓለም በተፈጥሮ በተጎናፀፈው መልካምነት የእግዚአብሔርን መልካምነት ያንፀባርቃል፡፡ ይህም መልካምነት ከሌላ ያገኘው መልካምነት ነው ምክንያቱም በመልካሙ እግዚአብሔር ተፈጥሯልና፡፡

የእግዚአብሔር ፍጥረት የእርሱን መልካምነት ያንፀባርቃል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ፍጥረት በራሱ ክፉ አይደለም፣ ስለዚህም ክፋት በቁስ ውስጥ ከጅማሬው ጀምሮ አልነበረም ብሎ ይነግረናል፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር፣ ሁሉን እጅግ መልካም አድርጎ ፈጥሯል፡፡ ስለዚህም በፍጥረት ውስጥ ውበት አለ፡፡ በውድቀት መዘዝ ግን ይህ ውበት ተበላሸ፡፡ እሾህ፣ አሜኬላ እና በላብ መጠመቅ፣ የእግዚአብሔርን ፍጥረት አበላሸው፣ እኛ ግን እንደ ክርስቲያኖች አዲስ ሂደት ጀምረናል ማለትም እግዚአብሔር አዲሱን ፍጥረት የመሥራቱን ሂደት ጀምሯል፡፡ እኛ በኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ነን እናም አንድ የመዝሙር ጸሐፊ እንደተናገረው፣ እንደ ክርስቲያኖች፣ ክርስቶስ የሌላቸው የማያዩትን እንድ ነገር እኛ እናያለን፡፡ ፍጥረትን እንደ እግዚአብሔር የእጅ ሥራ ማየት ጀምረናል፡፡ ስለዚህ እንደ ክርስቲያኖች ጥበብን፣ ውበትን፣ ውቅርን፣ ቅንብርን፣ በፍጥረት በራሱ ውስጥ ቅንጅትን እንመለከታለን፡፡ በአዲሱ ሰማይና ምድር የምንጠብቀውም ይህንኑ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍጥረት አዲስ ሲሆን እግዚአብሔር በፍጥረት እንድናገኝ አቅዶ የነበረውን ደስታ መቋደስ እንጀምራለን፡፡ [ዶ/ር ዴሬክ ደብሊዩ. ኤች. ቶማስ]

ይህንን የፍጥረት ሥራና የፍጥረት መልካምነት መረዳት በልቡናችን ይዘን፣ አብ በፍጥረት ላይ እንደ ሠሪ ያለውን ሥልጣን ለመመልከት እንዘጋጃለን፡፡

በፍጥረት ላይ ያለው ሥልጣን

እግዚአብሔር አብ እንደ ፈጣሪ ስላለው ሥልጣን የምንላቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ግን በሦስቱ መሠረታዊ ባህርያቱ ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ እነርሱም፡- ሥልጣኑ ፍጹም ነው፣ የእርሱ ብቻ ነው፣ በሁሉ ላይ የሚገለጥ ነው፡፡ አብ እንደ ፈጣሪ ባለው ሥልጣን በመጀመር፣ ሁሉንም ሃሳቦች በቅርበት እንመለከታቸዋለን፡፡

ፍፁም

የአብ ሥልጣን ፍፁም ነው ስንል በፈጠረው ፍጡሩ ላይ የወደደውን የማድረግ ምሉዕ ነፃነት አለው ማለታችን ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የእርሱን ፍፁም ሥልጣን ሸክላ ሠሪ በሸክላው ላይ ካለው ሥልጣን ጋር በማነፃፀር ደጋግመው ይገልፁታል፡፡ ይህንን መግለጫ እንደ ኢሳያስ ምዕራፍ 29 ቁጥር 16፣ ኢሳያስ ምዕራፍ 45 ቁጥር 9፣ ኤርምያስ ምዕራፍ 18 ቁጥር 1 እስከ 10 እና ሮሜ ምዕራፍ 9 ቁጥር 18 እስከ 24 በመሳሰሉት ቦታዎች እናገኘዋለን፡፡ በሮሜ ምዕራፍ 9 ቁጥር 20 እና 21 ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ሥልጣን የተናገረውን አድምጡ፡

ነገር ግን፥ አንተ ሰው ሆይ፥ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን፥ ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን?

ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን? (ሮሜ 9፥20-21)

ጳውሎስ ላነሳቸው ዝም የሚያሰኙ ጥያቄዎች መልሱ ግልጽ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ ስለሆነ፣ በፈጠረው ፍጡር ላይ ያሻውን የማድረግ መብቱም ነፃነቱም አለው፡፡

አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር በዓለም ላይ በሚከናወን ድርጊት ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ሥልጣን አለው በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ሲሰሙ ይፈተናሉ፤ ቅርም ይሰኛሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ግን፣ የእግዚአብሔርን ማንነት ስናስብ በአስደናቂ ሁኔታ በምሥጋና እንሞላለን፡፡ ይህም ማለት ሕይወታችን በሁሉ ጥበበኛ በሆነ፣ በሁሉን ቻዩ፣ ሁሉን አፍቃሪ በሆነና ስለ እኛም በመስቀል ላይ አንድያ ልጁን በሰጠን አባት እጅ እንዳለ እንረዳለን ማለት ነው፡፡ በተለይም በመከራ ወቅት፣ በሕይወታችን ምን እየሆነ እንዳለ በውል መለየት በሚሳነንና ግር በሚለን ወቅት ይህ መረዳት ትልቅ መጽናናትን ይሰጠናል፡፡ [ዶ/ር ዴኒስ ጆንሰን]

ምንም እንኳን በዙሪያችን ምን እየተከናወነ እንደሆነ በውል ባናውቅም፣ የኢየሱስ እስከሆንን ድረስ፣ እግዚአብሔር አባታችን ነው እርሱም ይወድደናል፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብናልፍም፣ እርሱ ዐይኖቹን በእኛ ላይ ያደርጋል ይጠብቀናልም፡፡ በዚህች ዘመን ሕይወታችን የምናልፍባቸው አንዳንድ ነገሮች በእውነት ስቃይ የሞላባቸው ናቸው፡፡ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብታልፉም እርሱ ሁሉን ይቆጣጠራል፡፡ የምታልፉበትን ሁኔታ ለእናንተው መልካምና ለመቀደሳችሁ ይሆን ዘንድ እንዳደረገው አሁን የምታልፉበትን ትቀበሉታላችሁን? እግዚአብሔር ጠላቶቻችንን ወዳጆቻችን ያደርጋቸዋል ስለዚህም በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ አሸናፊዎች ብቻ አይደለንም፤ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ፈተናና መከራዎቻችንን እኛን ለመቀደስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንድንመስል የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ያደርጋቸዋል፡፡ እርሱ በሕይወታችን በሚያመጣቸው ነገሮች ሁሉ ክርስቶስን እየመሰልን እንሠራባቸዋለን፡፡ ዕብራውያን 12 እንደሚነግረን፣ እርሱ እንደ ቸር፣ ጥበበኛና መልካም አባት ለጥቅማችን ይቀጣናል፡፡ እኔ እንደማስበው የእምነት ተጋድሎ የሚካሄደው በዚህ ስፍራ ነው፡፡ ምንም እንኳን በሕይወቴ የሚያመጣቸውን ነገሮች ለእኔ ለመልካም፣ ለእኔ ቅድስና እና ፍፅምና እንዳመጣቸው ባልረዳም እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር ስለ እኔ ግድ ይለዋል ብለን አሁንም አሁንም ለራሳችን ልንነግረው ያስፈልጋል፡፡ [ዶ/ር ቶም ሽሪነር]

የእርሱ ብቻ

የአብ ሥልጣን ፍፁም ከመሆኑ ባሻገር፣ በፈጠረው ፍጡር ሁሉ ላይ የእርሱ ብቻ የሆነ ሥልጣን አለው፡፡ አብ እንደ ፈጣሪ ያለው ሥልጣን ከፍጡር ማንም የእርሱን የሚመስል ፍፁም ሥልጣን ያለው የሌለ መሆኑን በሚገልጥ መንገድ የብቻው ሥልጣን አለው፡፡ ፍፁም ሥልጣን የፈጣሪ ብቻ ነው፣ ፈጣሪ ደግሞ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ስላሴን ከቤተሰባዊነት አንፃር ስንመለከተው፣ አብ በሌሎቹ የሥላሴ አካላትም ላይ ሥልጣን አለው፡፡ ለምሳሌ፣ በዮሐንስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 26 እና 27 ኢየሱስ የተናገረውን እናድምጥ፡

አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።

የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። (ዮሐ 5፥26-27)

ኢየሱስ በዓለም ላይ እንዲፈርድ ሥልጣን የተሰጠው ከአብ እንደሆነ አስተምሯል፡፡ ይህ ሥልጣን በዋናነት በአብ ውስጥ ነው ያለው፣ የእርሱ የብቻው ነው፡፡ አብ ግን ወልድ በእርሱ ምትክ ሆኖ እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጠው፡፡ በ1ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 24 ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ እናገኛለን፣ ይህም በፍጥረተ ዓለም ላይ ወልድ ያለው ንግሥና ለአብ ትልቅ ንግሥና የሚገዛ መሆኑ የተጠቀሰበት ነው፡፡

ከመንፈስ ቅዱስም አንጻር ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ እንደ ዮሐንስ ምዕራፍ 16 ቁጥር 13፣ ሮሜ 8 ቁጥር 11 እና 1ጴጥሮስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 2 እንደሚያስተምሩን መንፈስ ቅዱስም የሚፈፅመው የአብን ፈቃድ ነው፡፡

የወልድ ሥልጣንና የመንፈስ ሥልጣን ከአብ እንደሚሰጥ ሁሉ የፍጡራን ሁሉ ሥልጣንም እንዲሁ ከአብ የተሰጠ ነው፡፡ መላዕክት፣ ምድራዊ ገዢዎች፣ አብላጫው የሰው ዘር የተወሰነ ሥልጣን አላቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሥልጣኖች ግን ከአብ የሚሰጡ ናቸው፣ ስለዚህ የአብ ሥልጣን ከፍጡር ሥልጣን ሁሉ የበላይ ነው፡፡

በሁሉ የሚገለጥ

ፍፁምና የእርሱ ብቻ የሆነ ሥልጣን ከመኖሩ በተጨማሪ፣ አብ በፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ላይ የሚገለጥ ሥልጣንም አለው፡፡ የእግዚአብሔር ሥልጣን በሁሉ ላይ የሚገለጥ ነው ስንል፣ በፈጠረው ፍጡር ሁሉ ላይ በዝርዝርና በጥልቀት ሥልጣን አለው ማለታችን ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ይህ እውነታ ሁለት ወሳኝ እንድምታዎች አሉት፡፡ በመጀመሪያ፣ ሁሉ በእግዚአብሔር ሥልጣን ስር ነው፡፡ ማለትም እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ግዴታ ነፃ የሆነ ሰው ወይም ፍጡር የለም፡፡

ለአብ የታመኑ መላእክትና የሰው ልጆች ለእርሱ በፍፁም ፈቃዳቸው እውቅና ይሰጣሉ ይገዙለትማል፡፡ አጋንንቶችና ያልታመኑ ሰዎች ግን በእርሱ ላይ ያምፃሉ ለእርሱም ትዕዛዛት አይገዙም፡፡ ይህም ሆኖ፣ የአብ ሞራላዊ ፍርድ ግን በሁሉ ላይ ይፈፀማል፡፡ ማንም እንሁን ወይም የትም እንኑር፣ ምንም ዓይነት ባህል ወይም ሃይማኖት ይኑረን፣ ሁላችን ለእግዚአብሔር ተጠያቂ ነን፡፡

ሁለተኛ፣ ሁሉ ነገር በእግዚአብሔር ሥልጣን ስር ነው፡፡ የእርሱ ሥልጣን በፈጠረው ፍጥረት ጥቃቅን ጉዳዮች ሁሉ ላይ ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር የሁሉም ፈጣሪ ስለሆነ፣ የትኛውም ፍጥረት ከሞራላዊ ግዴታ ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡ እያንዳንዱን ነገር የፈጠረው በዓላማ ነው፣ ለእያንዳንዱም ሞራላዊ ባህርይ መድቦለታል፡፡ ይህም ማለት ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን፣ የትኛውም ዓይነት ፍጥረት ይከሰት፣ የሞራል አይነኬነት ጨርሶ የለም፡፡ የትኛውም ፍጥረት እግዚአብሔር እንደሚሻው የሚሠራ፣ መልካም ነው፣ እግዚአብሔር ከሚሻው በተቃራኒ ያለው ደግሞ ክፉ ነው፡፡

በዘመነኛው ዓለም ብዙ ክርስቲኖች ሕይወትን የተቀደሰና ዓለማዊ ብሎ በመንታ ወደ መክፈል እያዘነበሉ ነው፡፡ ብዙዎቻችን እንደ ቤተክርስቲያን፣ አምልኮ፣ የወንጌል አገልግሎት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመሳሰሉት “የተቀደሱ”ና በእግዚአብሔር ሥልጣን ስር ያሉ ናቸው ብለን እውቅና ለመስጠት እንሞክራለን፡፡ በተጨማሪም ደግሞ ለቤተሰባችን እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ትዕዛዛት እና ስነ-ምግባራዊ ምርጫዎቻችንን የተቀደሱ አድርገን እውቅና ለመስጠት እንጥራለን፡፡ አብዛኛዎቹ ክርስቲኖች ግን “ዓለማዊ” ብለው የፈረጇቸውን ማለትም እንደ ፖለቲካ፣ ትምህርት እና ሥራ የመሳሰሉትን የእግዚአብሔር ትዕዛዛት አይገዙዋቸውም ብለው ወደ ማሰቡ ያዘነብላሉ፡፡ ይህ ዘመነኛው የተቀደሰና ዓለማዊ የሚለው ክፍፍል ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም፡፡ ምሳሌ ምዕራፍ 3 ቁጥር 6፣ መክብብ ምዕራፍ 12 ቁጥር 14 እና 2 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 16 እስከ 17 ያሉት ምንባቦች እግዚአብሔር ስለ የትኛውም ዓይነት የሕይወት ፈርጅ እንደተናገረና የእርሱም ሥልጣን በምናደርገው በየትኛውም ነገር ላይ እንደሚገለጥ ያመለክታል፡፡

ሥልጣን በአሉታዊ መልኩ ብቻ በሚታወቅበት ዓለም ውስጥ፣ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ሥልጣን የማመናቸው ነገር ትልቅ ነገር ነው ምክንያቱም እግዚአብሔር ዓለምን ዛሬም ይወዳልና፣ እግዚአብሔር አሁንም ሁሉን ይቆጣጠራልና፣ ገና ከጅማሬው ፍፃሜውን ያውቃልና፣ እግዚአብሔር የአህዛብ ሁሉ ፈራጅ ነውና፡፡ ይህም እኛ ሰላም እንዲሰማን ያደርገናል ምክንያቱም እንድ የሚሠራውን የሚያውቅ አካል እንዳለ ስለምናውቅ ወስትናችን የፀና ነው ለወደፊቱም ትምክህት የሚሆነን እርሱ ነው፡፡ [ዶ/ር ሲሞን ቫይበርት]

5. ማጠቃለያ

ስለ እግዚአብሔር አብ በተነጋገርንበት በዚህ ትምህርት፣ በሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ የተጠቀሰውን የመጀመሪያ የእምነት አንቀፅ በጥልቀት ተመልክተናል፡፡ በዚህ የእምነት አንቀፅ ስለ እግዚአብሔር የተወሳውን ሃሳብ ተወያይተንበታል፡፡ ሁሉን ቻዩን አብን የስላሴ የመጀመሪያ አካል አድርገን ተነጋግረንበታል፡፡ ሰማይንና ምድርን በመፍጠር ረገድ የአብን ድርሻም ቃኝተናል፡፡

የእግዚአብሔር አብን ስብዕና መረዳት ለሁሉም ክርስቲያናዊ ነገረ-መለኮት መሠረት ነው፡፡ እውነተኛውንና የቅዱሳት መጻሕፍቱን ስሉስ-አሃዱ አምላክ የማናውቅና የማናመልክ ከሆነ፣ የምናመልከው የተሳሳተ አምላክ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት አብ ብለው የሚጠሩትን ማንነት ማወቅና ማክበር የእውነተኛ አምልኮ ለድርድር የማይቀርብ ክፍል ነው፡፡ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የሚታዘዙትና የሚያከብሩት፣ የሚያደርጉትም ሁሉ ክብሩን የሚያበዛና የሚደምቅ ነው፡፡ እንግዲያው እኛም የምንታዘዘው፣ የምናከብረውና የምናነግሠው እርሱን ሊሆን ይገባል፡፡

Continue reading the full transcript