<link rel="stylesheet" href="https://cdn.plyr.io/3.7.8/plyr.css" />
ወደ ካታሎግ ተመለስFAአባ አብርሃም
አባ አብርሃም ·Videoከእንግሊዝኛ ተተርጉሟል

FA-01 የአብርሃም ሕይወት: አወቃቀስ እና ይዘት

ሙሉውን ጽሑፍ ያንብቡ

የጥንት እስራኤላውያን ስለ አብርሃም ታላቁ አባታቸው ስለነበሩትเรื่อง የሚ kểዱ ታሪኮችን ይመረምራል።


From the transcript

ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ጎብኙ፡፡

በምድር መንግሥታት መካከል በርካታ ልዩነቶች እንዳሉ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ሁሉም የየራሳቸው መልክዓ-ምድር፣ ተለይተው የሚታወቁ ጎሳዎች እና ለየት ያሉ ትውፊቶች አሏቸው፡፡ ሁሉንም በጋራ የሚያስተሳስራቸው ቢያንስ አንድ ነገር ግን አለ፡ ሁሉም አገሮቻቸው እንዴት እንደተመሠረተች የሚዘግብ ታሪክ አላቸው፡፡ አብዛኞቻችን አገራችንን የቆረቆሯት ሰዎቸ ስለከፈሉት መስዋዕትነትና ስለተቀዳጇቸው ደሎች መስማት እንወዳለን፡፡ ስለ ጀግንነታቸውም እናዜማለን፡፡

እነዚህ የማንነት መገኛ ታሪኮች ለምን እንወዳቸዋለን ለምንስ ስለእነርሱ ማውራት ደስ ይለናል?የእያንዳንዱ ሰብዓዊ ባህል ሁሉ ወሳኝ ክፍልስ ለምን ሆነ?

ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ በአንደ ወገን፣ ስለ አገራችን አቆራቆር የምናወራው ያለፈውን ዘመን ትዝታ ለትውልደ ለማስተላለፍ ነው፡፡ ልጆቻቸን ስረ መሠረታቸውን እንዲያውቁ ማለትም ከየት እንደተገኙ እንዲያውቁ እንፈልጋለን፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ በቀደመው ዘመን መንግሥታችንን አቅጣጫ ያስያዙ ነገሮችን ለማስታወስና ለወደፊቱም ኣርዓያነታቸውን በመከተል አቅጣጫ መያዝም እንፈልጋለን፡፡

በብሉይ ኪዳን ይኖር ለነበረው የእግዚአብሔር ህዝብም ይኸው ተመሳሳየይ ነገር እውነትነት ነበረው፡፡ የቀደሙት እስራኤላውያንም በሁለት ተመሳሳየይ ምክንያቶቸ ስለ አጀማመራቸው ታሪክ ማውራት ደስ ያሰኛቸዋል እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፉታል፡፡ የቀደመው ዘመን ታላቅ ድልና ስኬት እንዳይረሳ በቀደሙት አባቶቻቸው ዘመን የተከናወኑ ክስተቶቸን ለማስታወስ ይዘክሯቸዋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ፣ ታሪካቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፉት ወደፊት ሊጓዙበት የሚገባቸውን አቅጣጫም ለማመልከት ነው፡፡

አባታችን አብርሃም ከተሰኘው ተከታታይ ትምህርታቸን ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህ ተከታታይ ትምህርት የቀደሙት እስራኤላውያን ስለ ታላቁ አባታቸው ስለ አብርሃም የሚናገሩትን እንመረምራለን፡፡ ሙሴ እነዚህን ታሪኮች በዘፍጥረት ታሪክ እንዳሰፈራቸው፣ ይህንንም ያደረገው በእርሱ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ያለፈውን ዘመን እንዲያስታውሱ፣ ደግሞም እግዚአብሔር ለወደፊት ለእነርሱ ጠብቆ ያቆየውን ነገር እንዲረዱም ጭምር ነው፡፡

ይህ ከሦስቱ ተከታታይ ትምህርቶች የመጀመሪያው ሲሆን «የአብርሃም ሕይወት፡ አወቃቀርና ይዘት» የሚል ርዕስም ሰጥተነዋል፡፡ በዚህ ትምህርት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ስለእርሱ በሚተርኩ ምዕራፎች አወቃቀርና ይዘት ላይ በማትኮር የአብርሃምን ሕይወት በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡ ሙሴ የአብርሃምን ሕይወት ታሪክ ያዋቀረው እንዴት ነው? የእነዚህ ምዕራፎቸ ዋና ሃሳብስ ምን ነበር?

የአብርሃምን ሕይወት አወቃቀርና ይዘት በሁለት ክፍሎች እንቃኛለን፡ በመጀመሪያ፣ የታሪኩን ስነ-ጽሁፋዊ ቅርፅ እናያለን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ የእነዚህን ምዕራፎች ዐበይት መሪ ሃሳቦች እንመረምራለን፡፡ አስቀድመን የአብርሃምን ሕይወት ስነ-ጽሁፋዊ ቅርፅ እንመልከት፡፡

የአብርሃምን ሕይወት የመሳሰሉ ታሪኮችን ወይም ትረካዎችን የያዙ ክፍሎች ከቅዱሳት መጻሐሕፍት ውስጠጥ በምናነብበት ወቅት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፍቶቹ ከብዙ ዓመታት በፊት ምን እንደተከናወነ ከመተረክ የዘለለ ነገር እንደሚያስረዱን ልብ ልንል ይገባናል፡፡ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ እንዲሆኑ መነዳትን ስለሰጣቸው፣ የጻፉት ታሪክ ፍፁም እውነት ነው፡፡ ደግሞም መንፈስ ቅዱስ የጻፉላቸውን ሰዎች ፍላጎቶቸም ለማሟላት መነዳትን ሰጥቷቸው ስለነበር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቸ ታሪኩን የሚጽፉት ተደራሲያኖቻቸውን በልናቸወ የይዘው ነበር፡፡ ለሚቀበሉትም ሰዎቸ ትርጉም በሚሰጥና አግባብነት ባለው መንገድ በዓላማ አዋቅረውታል፡፡

በዘፍጥረት መጽሐፍ የተዘገበውን የአብርሃምን ሕይወት ስንመለከት፣ ታሪኮቹ በአብርሃም ሕይወት በእውን ያልሆነን ነገር በተሳሳተ መንገድ ወክለው እንዳልቀረቡ በእርግጠኝነት እናውቃለን፡፡ ሆኖም እነዚህ ታሪኮች በሙሴ ቀደምት ተደራሲያን ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደሚዛመዱ ለመገንዘብ፣ የዘፍጥረት መጽሐፍ የአብርሃምን ሕይወት እንዴት እንደተረከው ማወቅ የይገባናል፡፡ ስለዚህም አብርሃም የተተረከበትን መንገድ ለመረዳት ከሚያግዙን ዋና መንገዶች የመጀመሪያው በዘፍጥረት መጽሐፍ የአብርሃም ሕይወት የተዋቀረበትን ስነ-ጽሁፋዊ ቅርፅ መመርመር ነው፡፡

የአብርሃምን ሕይወት ስነ-ጽሁፋዊ ቅርፅ በሁለት እርከኖች እንቃኛለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የዘፍጥረት መጽሐፍ በጠቅላላ በወፍ በረር እንዳስስና፣ የአብርሃም ታሪክ በዘፍጥረት ዐቢይ ምስል ውስጥ እንዴት እንደሚገጥም እናያለን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ በአብርሃም ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ታሪኮችን አወቃቀር እንመለከታለን፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ አጠቃላየይ ቅኝት እንጀምር፡፡

ዘፍጥረት

በየምዕተ ዓመታቱ፣ ተርጓሚዎች የዘፍጥረትን መጽሐፍ አጠቃላይ አወቃቀር በተለያ መንገድ ሲገነዘቡት ቆይተዋል፡፡ አንደኛው በጠቅላላው የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እዚህም እዚያም ተበታትኖ በተቀመጠው “ትውልድ” ወይም “toledot” በሚለው መሪ ሃሳብ ድግግሞሽ ላይ በመመሥረት ዘፍጥረትን ዐሥር ቦታ መከፋፈል ነው፡፡ በዚህ ዐቢይ የአከፋፈል አተያይ ውስጥ ጥቂት ዋጋ የሚሰጠው ነገር እንዳለ ልንቀበል ይገባናል፡፡ ሆኖም በሌላ ተከታታይ ትምህርት እንዳመለከትነው ዘፍጥረትን በሦስት መክፈሉ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህም ጥንታዊው ታሪክ በዘፍ 1፡1-11፡9፤ የመጀመሪያው የአባቶች ታሪክ ዘፍጥረት 11፡10-37፤ የኋለኛው የአባቶች ታሪክ 37፡2-50፡26 ይሆናል፡፡

በዘፍጥረት 1፡1-11፡9 የሚገኘው ጥንታዊው ታሪክ ስለ ዓለም መገኛ የእግዚአብሔርን የተገለጠ እውነት ያቀርብልናል፡፡ ስለ አፈጣጠር፣ ስለ ፍጥረት መርከስ እና ምድርን ሁሉ ባጥለቀለቀው የጥፋት ውሃ ፍጥረትን እንደገና ቅርፅ ስለማስያዙ ይናገራል፡፡ ከጥንታዊው የቅርብ ምሥራቅ የታሪክ አወቃቀር ስልት ጋርም በሚጣጣም መንገድ ስነ-ጥሁፋዊ ቅርፁን ጠብቆ ተያይዟል፡፡

በዘፍጥረት 37፡2-50፡26 የሚገኘው የኋለኛው የአባቶች ታሪክ ስለ ዮሴፍ ይተርክልናል፡፡ በዮሴፍና በወንድሞቹ መካከል በተነሳው ጠብ ይጀምርና፣ ዮሴፍ በግብፅ ከፍ ከፍ ወደማለቱና በስተመጨረሻም ዮሴፍ ከወንድሞቹ ጋር ወደመታረቁ ይገሰግሳል፡፡ ተርጓሚዎችም ይህንን ረጅምና የተቀናጀ የታሪክ ፍሰት የዮሴፍ ታሪክ በማለት ይገልጡታል፡፡

በእነዚህ የመጀመሪያና የመጨረሻ ታሪኮች መካከል ዘፍጥረት 11፡10-37፡1 ያለው ክፍል ይመጣል፡፡ እነዚህ ምዕራፎች የመጀመሪያውን የአባቶች ታሪክ፣ ማለትም ስለ እስራኤል የመጀመሪያ አባቶች የተሰባሰበ ታሪክ ይዘዋል፡፡ በዚህ ተከታታይ ትምህርት፣ ከዚህ የመካከለኛ አንጓ ክፍል ውስጥ በአንዱ ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡

በጥቅል አነጋገር፣ የቀደሙት አባቶች ታሪክ በሁለት ይከፈላል፡ የአብርሃመ ሕይወት በ11፡10-25፡18 እና የያዕቆብ ሕይወት 25፡19-37፡1፡፡ ይህ ባለሁለት መንታ ክፍልፋይ ያስገርማችሁ ይሆናል ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ በቅ በዱሳት መጻሕፍት ሲጠቀስ የምንሰማው ስለ ሦስቱ አባቶች ማለትም፡ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የእነዚህ ምዕራፎች ስነ-ጽሁፋዊ አከፋፈል በሦስት ሊሆን እንደሚችልም መጠበቃችን በቂ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ አስቀድሞ ስለ አብርሃም ይነግረናል ከዚያም ስለ ይስሐቅ እና ስለ ያዕቆብ፡፡ እውነታውን ስንነጋገር ግን፣ ከቀደሙት አባቶች ታሪክ ይስሃቅን ዋነኛ ገፀ-ባህርይ አድርጎ የተፃፈ ክፍል አናገኝም፡፡ ይልቁኑ እንደ መሸጋገሪያ ገፀ-ባህርይ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የሕወት ታሪኩ የተነገረን አስቀድሞ የአብርሃም ሕይወት አካል ሆኖ ሲሆን ከዚያ ደግሞ የያዕቆብ ሕይወት ክፍል ሆኖ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ የቀደሙት አባቶች ክፍል በሁለት ዋና ክፍሎች ብቻ ይከፈላል፡፡ እነርሱም፡ የአብርሃም ሕይወትና የያዕቆብ ሕይወት ናቸው፡፡ በዚህ ትምህርት የምናተኩረው ሙሴ አባታችን አብርሃም ብሎ በመዘገበው የመጀመሪያ የታሪኩ አጋማሽ ክፍል ላይ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዘፍጥረት 11፡10-25፡18 የተመዘገበውን የአብርሃምን ሕይወት አወቃቀር ቀረብ ብለን እንመልከተው፡፡

አብርሃም

የአብርሃም ሕይወት በአጠቃላዩ የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ስፍራው የት እንደሆነ ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ በዘፍጥረት 11፡10-25፡18 የተመዘገበውን የአብርሃም ሕይወት አወቃቀር ወደመመልከቱ እንሸጋገራለን፡፡ የአብርሃምን ሕይወት ውቅር ለመመልከት፣ እነዚህን ምዕራፎች በሁለት እርከኖች እንመለከታቸዋለን፡፡ በአንድ ወገን፣ የአብርሃምን ሕይወት መሠረታዊ ክፍልፋዮች ወይም እርከኖችች እንለያቸዋለን በሌላ ጎኑ ደግሞ፣ በዘፍጥረት መጽሐፍ የተገለጠውን የአብርሃምን ቁመና ለመግለጥ እነዚህ የተለያዩ ክፍሎች እንዴት እንደተሰደሩ እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ የአብርሃምን ሕይወት መሠረታዊ ክፍልፋዮች ወይም እርከኖች እንመለክት፡፡

ሙሴ ስለ አብርሃም የጻፈው በዐሥራ-ሰባት ክፍልፋዮች ወይም አንጓዎች ነው፡

የመጀመሪያው፣ ሞገስ ያገኘው የአብርሃም ዝርያ (በ11፡10-26) ሲሆን ይህም የአብርሃምን ትውልድ የሚጠቅስ የትውልድ ሐረግ ነው፡፡

ይህ ምንባብ የአብርሃምን ያልተሳካለት የቀድሞ አባት ታሪክ ያስከትላል ( 11፡27-32)፣ ይህም ሁለተኛው የትውልድ ሐረግ ሲሆን አብርሃም ከአባቱ ከታራ ጋር መጓዙን ይጠቅሳል፡፡

(በ12፡1-9) የአብርሃም ወደ ከነዓን መሰደድ፣ የአብርሃም የመጀመሪያ ጥሪና ወደ ተስፋዪቱ ምድር ጉዞ፡፡

አብርሃም ከግብፅ ነፃ መውጣቱ (በ12፡10-20)፣ ይህም አብርሃም ወደ ግብፅ የወረደበትና እግዚአብሔርም እርሱን ነፃ ያወጣበት ነው፡፡

የአብርሃም ከሎጥ ጋር መጣላት (13፡1-18)፣ በአብርሃም እረኞችና በሎጥ እረኞች መካከል የነበረ ግብግብ፡፡

አብርሃም ሎጥን መታደጉ (14፡1-24)፣ ሎጥን ከማረኩ ነገሥታት እጅ ለመታደግ አብርሃም ወደ ጦርነት የዘመተበትን ታሪክ ይዘግባል፡፡

የአብርሃም ቃል ኪዳን ተስፋዎች (15፡1-21)፣ ዘሩን እንደሚያበዛና ቋሚ ምድር እንደሚሰጠው እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው የቃል ኪዳን ማረጋገጫ፡፡

አብርሃም ወደ አጋር መግባቱ (16፡1-16)፣ ከሣራ ባሪያ ከአጋር እስማኤል የተሰኘ ልጅ ስለማግኘቱ ወቅት ሚተርክ፡፡

የአብርሃም የቃል ኪዳን ግዴታዎች (17፡1-27)፣ እግዚአብሔር ያዘዘውን ትዕዛዝ በታማኝነት ሊፈፅም እንደሚገባው አብርሃምን ያሳሰበበት የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ዘገባ፡፡

ሶዶምና ጎሞራ (18፡1 – 19-38)፣ የሶዶምና የጎሞራ መውደምና ሎጥ ከዚያ ጥፋት የማምለጡ ታሪክ፡፡

አብርሃም ለአቤሜሌክ መማለዱ (20፡1-18)፣ አብርሃም ለአቤሜሌክ የፀለየበት ወቅት፡፡

የአብርሃም ልጆች ይስሐቅና እስማኤል (21፡1-21)፣ የይስሐቅ መወለድና እስማኤል ከአብርሃም ቤተሰብ የመባረሩ ታሪክ፡፡

አብርሃም ከአቤሜሌክ ጋር ያደረገው ስምምነት (21፡22-34)፣ ስለ መሬትና ስለ ውሃ አጠቃቀም አብርሃም ከአቤሜሌክ ጋር ወደ ስምምነት መድረሱ፡፡

የአብርሃም መፈተን (22፡1-24)፣ ልጁን ይስሐቅን እንዲሰዋ ለእግዚአብሔር ጥሪ የቀረበበት ታዋቂ የሆነው ትዕይንት፡፡

የአብርሃም የቀብር ስፍራ ባለቤትነት (23፡1-20)፣ የሳራ መሞትና የቀብር ቦታ ግዢ ታሪክ

የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ሚስት (24፡1-67)፣ ርብቃ የይስሐቅ ሚስት መሆኗ፡፡

በመጨረሻ፣ የብርሃም ሞትና ቅርስ (25፡1-18)፣ የአብርሃም ማለፍና የዝርያዎቹ ታሪክ ዘገባ ይገኙበታል፡፡ታሪ

የአብርሃምን ሕይወት ስንመለከት፣ የሕይወቱ ፍሰት መሠረታዊ የክንዋኔ ቅደም ተከተሎችን ጠብቆ የሚፈስስ ነው፡፡ ታሪኩ የሚጀምረው በዘመኑ ወጣት በሚባልበትና በአባቱ ቁጥጥር ስር ባለበት ወቅት ሲሆን፣ አብርሃም አርጅቶ በመሞቱ ይጠናቀቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግራ መጋባቶች የነበሩበት ሲሆን፣ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ በተከናወኑ የተለያዩ የሕይወት እርከኖች መካከል ግልፅ ያላለ ትስስር አለ፡፡ ሆኖም ከሌሎች የብሉይ ኪዳን ታሪኮች ጋር ስናነፃፅረው፣ የአብርሃም የሕይወት ታሪክ ራሳቸውን የቻሉ ዐሥራ ሰባት ምዕራፎችን የያዘ ነው፡፡ እያንዳንዳቸውም በአብርሃም ሕይወት የተከናወነውን ለመዘገብና ለሙሴ ቀደምት ተደራሲያን ለእስራኤላውያን ግልፅ ትምህርቶችን ለማስተማር ታስበው የተነደፉ ናቸው፡፡ ሙሴ ከግብፅ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሲመራቸው፣ እነዚህ የሕይወት ምዕራፎች በአኗኗራቸው ውስጥ ብዙ የሚያሳያዋቸው ነገር የነበረ ሲሆን፣ ዛሬም እኛ ለምንኖረው ሕይወት ብዙ ነገሮችን ያስተምረናል፡፡

የአብርሃምን ሕይወት መሠረታዊ እርከኖች ከተዋወቅን፣ አሁን ደግሞ እነዚህ ምዕራፎች እርስ በርስ እንዴት እንደተሳሰሩ መመልከት እንችላለን፡፡ የአብርሃም ሕይወት እንዴት ተያያዘ? ያቀናበራቸውስ ምን አመክንዮ ነው? በቀላሉ ለማስቀመጥ፣ የአብርሃም ሕይወት ምዕራፎች ግልፅ በሆኑ መሪ ሃሳቦች ዙሪያ እጅብ ያሉ ሲሆን እነዚህም አምስት ሚዛናቸውን የጠበቁ ዐቢይ እርከኖች አሏቸው፡፡

የመጀመሪያው፣ በአባቶች ሕይወት እንደምንጠብቀው፣ ሙሴ የሚጀምረው በአብርሃም ዳራና ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው የጅማሬ ልምምድ ነው፡፡ ይህም ክፍል፡ የአብርሃምን ሞገስ ያገኘ ዝርያ፣ ያላተሳካለትን አባቱን ወደ ከነዓን መሰደዱን ያካትታል፡፡ እነዚህ ምዕራፎች በአብርሃም ቤተሰባዊ ዳራ እና ወደ ተስፋዪቱ ምድር ባደረገው የመነሻ ጉዞ ላይ በማትኮር አብርሃም እንዴት ከእግዚአብሔር ጋር ወደነበረው ልዩ ግንኙነት ውስጥ እንደገባ ያብራራሉ፡፡

ሁለተኛው የአብርሃም የሕይወት ምዕፎች ዐቢይ ክፍል ከ12፡10 – 14፡24 ተመዝግቦ አብርሃም ከሌሎች ሰዎች ጋር በነበረው ቀዳሚ ግንኙነት ላይ የሚያተኩረው ነው፡፡ ይህም ከግብፅ ነፃ መውጣቱን፣ ከሎጥ ጋር የገጠመውን ጠብ እና ሎጥን መታደጉን ያካትታል፡፡ እነዚህ ሦስት ክፍልፋዮች ተያይዘው የቀረቡት በተቀዳሚነት የሚያተኩሩት አብርሃም ከተለያዩ ህዝቦች ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ ስለሆነ ነው፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች አባታችን በመጀመሪያ ከግብፁ ፈርዖን፣ ከወንድሙ ልጅ ከሎጥ፣ ከወራሪ ነገሥታት፣ ከሰዶም ንጉሥ እና ከሳሌም ንጉሥ ከመልከጼዴቅ ጋር ይገናኛል፡፡

ሦስተኛውና በአብርሃም ሕይወት መካከለኛውን ስፍራ የሚይዘው ክፍል ደግሞ በ15፡1 – 17፡27 የተመዘገበው አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው የቃል ኪዳን ግንኙነት ላይ የሚያተኩረው ነው፡፡ ይህኛው ክፍል ሦስት ምዕራፎች አሉት፡ የአብርሃም የቃል ኪዳን ተስፋዎች፣ አብርሃም ወደ አጋር መግባቱ እና የአብርሃም ቃል ኪዳን ግዴታዎች ናቸው፡፡

አራተኛው ክፍል፣ በ18፡1-21፡34 የሚገኘው እና ወደ ኋላ ላይ አብርሃም ከሌሎች ሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ የሚያተኩረው ነው፡፡ እዚህም ምዕራች በአንድነት የተያያዙት አብርሃም ከሌሎች ሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ የሚያተኩሩ ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህ ምዕራፎች አብርሃምን ከሰዶምና ገሞራ ጋር በተገናኘ መንገድ ያቀርቡታል፡፡ አብርሃም ለአቤሜሌክ መማለዱ፣ አብርሃም ከይስቅና ከእስማኤል ጋር በተገናኘ መንገድ፣ አብርሃም ከአቤሜሌክ ጋር የፈፀመው ውልም ይገኙነበታል፡፡ እነዚህ አራት ምዕራፎች አባታችን ከሎጥና ከቤተሰቡ ጋር፣ ከሰዶምና ከጎሞራ ህዝብ ጋር እና ከፓለስታይኑ አቤሜሌክ ጋር እንዴት እንደተገናኘ ጠለቅ ብው ያብራራሉ፡፡

እንደምንገምተውም፣ አምስተኛው እና የመጨረሻው የአብርሃም ሕይወት ምዕራፍ በ22፡1-25፡18 የሚገኘው ሲሆን፣ በአብርሃም ሕይወት ማብቂያ ላይ ስለተከናወኑት ነገሮች በተለይም ስለ ቀጣይ ዝርያውና እና ስለ ሞቱ ያወሳል፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን እንዴት እደፈተነው ዘግቧል፡፡ አብርሃም የመቃብር ስፍራ መግዛቱን ዘግቧል፡፡ አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት እንዴት እንዳገኘ ዘግቧል፡፡ የአብርሃምንም ሞት ዘግቧል፡፡ እነዚህ ምዕራፎች በአብርሃም ሚስት በሣራና በልጇ በይስሐቅ (በአብርሃም እውነተኛ ወራሽ) ላይ በማተኮር፣ ከአብርሃም ሌሎች ሚስቶችና ልጆች ይልቅ ከበሬታን ይሰጣቸዋል፡፡

የአብርሃም ሕይወት ምዕራፎች አንዳቸው ከሌላቸው ሲነፃፀሩ የራሳቸው የተለየ ነገር ያላቸው በመሆናቸው ምክንያት፣ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አብርሃም ሲያነብቡ፣ ትርጉም በሌለው መንገድ ከአንዱ ሁኔታ ወደ ሌላው የሚንከራተቱ ይመስላቸዋል፡፡ ሙሴ እነዚህን ክስተቶች የዘገበው በጣም ጥቂት ድኅረ ሃሳብ ወይም ዕቅድ በልቡናው ይዞ እንደሆነ በማሰብ የአብርሃምን ታሪክ ያነብባሉ፡፡ ከዚህ የመነሻ ግንዛቤ ባሻገር ግን፣ የአብርሃም ሕይወት ታሪኮች ማዕከላዊ ሃሳቦችን ሊያቀርብልን በሚችል መንገድ ትርጉም በሚሰጡ ምዕራፎች የተቀናበሩ ናቸው፡፡ ቀላሏ ባለ አምስት እርከን አስተዋፅዖአችን ሙሴ በአብርሃም ሕይወት ምን እየተከናወነ እንደሆነ ሊያሳየን እንደጻፈው ይገልጣሉ፡፡ ከፍ ባለው ደረጃ ስንመለከተው የአብርሃም ሕይወት ዘገባ ሚዛናዊነት ያለውን ድራማ ቅርፅ ይይዛል፡፡ እያንዳንዱ ክፍል በድራማው ውስጥ ካሉት ተስተያይ ክፍሎች ጋር ሚዛናዊ ነው፡፡

በ11፡10–12፡9፣ በአብርሃም ቤተሰባዊ ዳራና ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው የመጀመሪያ ግንኙነት ላይ ትኩረት ተደርጎ ታገኛላችሁ፡፡ እነዚህን ቀዳሚ ትኩረቶች በሚዛናዊነት በማነፃፀር፣ የመዝጊያው ክፍል 22፡1-25፡18 ለአብርሃም የፍፃሜ ዓመታት እና ለቀጣይ ዘሩ ትኩረት ይሰጣል፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ የአብርሃም ሕይወት ሁለተኛው ክፍል አብርሃም ከሌሎች ነገዶችና መንግሥታት ጋር ያደረገውን ግንኙነት በጥንቃቄ በማዋቀር በምዕራፎች ያቀርብልናል፡፡ በሚዛናዊ ቀለበትም፣ በሁለተኛው ክፍል ወደተጠቀሱ ተመሳሳይ መሪ ሃሳቦች ይመለሳል፣ የአብርሃም ሕይወት አራተኛ ክፍል አብርሃም ከሌሎች ጋር የነበረውን ግንኙነት የሚያመለክቱ ተጨማሪ ምሳሌዎችን ወደ መጥቀሱ ይመለሳል፡፡

በመጨረሻ፣ በአብርሃም መካከለኛ ሕይወት ዘመን፣ አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው የቃል ኪዳን ግንኙነት ላይ ያተኮሩ ሦስት ማዕከላዊ መዘውርነት የሚታይባቸው ሦስት ምዕራፎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምዕራፎች የአብርሃምን ሕይወት ማዕከላዊ መዘውር የሚያዋቅሩ ሲሆን አብርሃምና ዘሩ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የቃል ኪዳን ግንኙነት ወሳኝ ኃይል ያብራራሉ፡፡

የእነዚህ ምዕራፎች ቅርፅ ሙሴ ዘገባውን በጥንቃቄ እንዳዋቀረው ይገልጣል፡፡ የእስራኤልን የመጀመሪ አባት ስነ-ጽሁፋዊ ቁመና ግልፅ ወደ ሆኑት የሕይወቱ ገፅታዎች ትኩረትን ለመሳብ ሲል አዋቅሮታል፡፡ እነርሱም፡- አብርሃም ለበረከትና ለባለመብት ወራሽነት መመረጡ፣ የአብርሃም ቀደምትና የኋላ ግንኙነቶች እና አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን የቃል ኪዳን ግንኙነት ናቸው፡፡ ወደፊት እንደምንመለከተው፣ ይህ ስነ-ፅሁፋዊ ትኩረት የሙሴ ቀደምት ተደራሲያን የነበሩትን የእስራኤላውያንን መሻት ለማሟላት ታቅዶ የተነደፈ ነው፡፡ እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ወደ ተስፋዪቱ ምድር በሚጓዙበት ወቅት እንዴት የእርሱን ፈለግ ሊከተሉ እንደሚገባ የአብርሃም ሕይወት ያስተምራቸዋል፡፡ እናም እነዚህን የአብርሃም ሕይወት ክፍልፋዮች ስንቀርባቸው፣ የእነዚህን በዓላማ የተነደፉ ቅርፆች አስፈላጊነት መልሰን መላልሰን እንመለከታለን፡፡

የአብርሃምን ሕይወት አጠቃላይ ስነ-ጽሑፋዊ ቅርፅ ከተመለከትን፣ በአብርሃም ሕይወት ውቅርና ይዘት ላይ ወደሚያጠነጥነው ወደ ሁለተኛው ርዕሳችን እንሸጋገር፡፡ ይህም በዘፍጥረት 11፡10 – 25፡18 የሚገኘው መሪ ሃሳብ ነው፡፡ የእነዚህን ምዕራፎች ይዘት ልንገልፅ የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች ቢኖሩም፣ በግርድፉ ያሳየናችሁ መዋቅር በእነዚህ ምዕራፎች ከተጠቀሱት ወሳኝ መሪ ሃሳቦች ጋር የሚዛመዱ መሆኑን እንመለከታለን፡፡

ዐቢይ መሪ ሃሳቦች

እንደ አብርሃም ዐይነት ረጅምና የተወሳሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ዐቢይ መሪ ሃሳቦች መግለጥ አስቸጋሪ ስለ መሆኑ መናገር አስፈላጊ አይመስልም፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች የሚከሰቱትን እያንዳቸውን ጭብጦች መዘርዘርና በዐቢይ መሪ ሃሳብነት መዋቀር አይቻልም፡፡ ሆኖም ከሌሎቹ ይልቅ ጎልተው የሚወጡትን ጭብጦች ለያይቶ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ እንደምንመለከተውም፣ በእነዚህ ምዕራፎች የምናገኛቸው መሪ ሃሳቦች የአብርሃምን ሕይወት አንድ ያደርጉልናል ደግሞም የሙሴ ቀደምት ተደራሲያን የሆኑት እስራኤላውያን ከአብርሃም ሕይወት እንዲቀስሙለት የሚፈልገውን ዋና ሃሳብ እንድንረዳ ይረዱናል፡፡ ከዚህም በበለጠ፣ ከዚህ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል እኛ ምን እንድንማር እግዚአብሔር እንደሚፈልግም እንመለከታለን፡፡

የአብርሃምን ሕይወት ዐበይት መሪ ሃሳቦች በሁለት መንገዶች እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የአብርሃምን ሕይወት አራት መሪ ሃሳቦች የሚስተዋውቀንን ቁልፍ ምንባብ እንመረምራለን፡፡ ሁለተኛ፣ እነዚህ መሪ ሃሳቦች በአብርሃም የሕይወት ምዕራፎች እንዴት እንደተገለጡ እንዳስሳለን፡፡ አስቀድመን የአብርሃምን ታሪክ መሪ ሃሳቦች የሚያስተዋውቀንንቁልፍ ምንባብ እንመልከት፡፡

ቁልፍ ምንባብ

በአብርሃም የሕይወት ታሪክ መክፈቻ ላይ፣ በዘፍጥረት 12፡1-3 እግዚአብሔር ለአብርሃም ያቀረበውን ጥሪ እንደሚገኝ በቀላሉ እንደምታስታውሱት እርግጠኛ ነኝ፡፡ አብርሃም ገና በከለዳውያን ዑር ሲኖር ሳለ፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንዲሄድ እግዚአብሔር ጥሪ አቀረበለት፡፡ እስከአሁን ድረስ ለበርካታ ዓመታት፣ እነዚህ ጥቅሶች በአብርሃም ሕይወት ትልቅ ታሪክ ውስጥ የሚገኙትን ጥቂት ወሳኝ ጉዳዮች እንደሚያስተዋውቁ ተርጓሚዎች ተረድተዋል፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ሙሴ ምን እንደጻፈ አድምጡ፡-

እግዚአብሔርም አብራምን አለው፡- “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ፡፡ ታላቅ ህዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ ስምህንም አከብረዋለሁ ለበረከትም ሁን የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፡፡” (ዘፍጥረት 12፡1-3)

እነዚህ ሦስት ጥቅሶቸ በቁም ነገር የተሞሉ ሲሆን በበርካታ መንገዶች ጠቅለል ተደርገው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ በሰዋሰዋዊ ደረጃ፣ በቁጥር 1 የመጀመሪያ ክፍል በሚገኘው መግቢያ ይጀምራሉ፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር ለአብርሃም በተናገራቸው እና ለሁለት በሚከፈሉት ቃላት ይቀጥላሉ፡፡ ክፍል አንድ፣ ከቁጥር 1 ሁለተኛ አጋማሽ አንስቶ እስከ ቁጥር 2 አብዛኛ ክፍል ድረስ ሦስተ የተለያዩ ግሦችን ያስከተለ ትዕዛዛዊ ቅፅል ይዟል፡፡ ክፍል ሁለት እግዚአብሔር ለአብርሃም የተናገረው ነገር የሚመጣው በቁጥር 2 መጨረሻና በቁጥር 3 ውስጥ ነው፡፡ በትዕዛዛዊ ቅፅል ይጀምርና ሦስት ግሣዊ መግለጫዎችን ያስከትላል፡፡ የዘፍጥረት 12፡1-3 ሦስት ክፍሎች በመመልከት ስለዚህ ምንባብ ወሳኝነት ጥቂት ወሳኝ መረዳቶችን እናገኛለን፡፡ በመጀመሪያ በቁጥር 1 ውስጥ እግዚአብሔር ለአብርሃም የተናገራቸውን ቃላት ሙሴ እንዴት በቀላሉ እንዳስተዋወቀ አድምጡ፡

እግዚአብሔር አብራምን አለው፣ (ዘፍ 12፡1)

በርካታ የዘመናችን ትርጉሞች በዚህ መስመር ላይ የተቀመጠው ግስ “እግዚአብሔር አለው” ከሚባል ይልቅ “እግዚአብሔር ብሎት ነበር” ሊባል እንደሚገባ በትክክል ተረድተዋል፡፡ ይህ አተረጓጎም በጣም ወሳኝ ነው ምክንያቱም በሐሥ 7፡2-4 የተጻፈውን የእስጢፋኖስን ንግግር ስንመለከት፣ አብርሃም ጥሪውን የተቀበለው አባቱ፣ ታራ፣ ከመሞቱ አስቀድሞ፣ በካራን ነበር፡፡ በዘፍጥረት ስነ-ጽሑፋዊ አቀራረብ ግን ታራ መሞቱን በመጀመሪያ የምናገኘው በ11፡32 ውስጥ ሲሆን ከዚያም በ12፡1 እግዚአብሔር አብርሃምን ጠራው የሚለውን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ዘፍጥረት 12፡1 ወደ ኋላ ተመልሶ ያለፈውን ታሪክ ነው የሚያሳየን፣ እናም ሊተረጎም የሚገባው “እግዚአብሔር ብሎት” ተብሎ ነው፡፡ ይህ ጥቅስ የሚያመለክተው አብርሃም ገና ለእግዚአብሔር ምላሽ ከመስጠት አንፃር ምንም ማድረግ ሳይጀምር፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ከመንቀሳቀሱ ረጅም ዘመናት በፊት የነበረውን ነው፡፡

ይህንን መግቢያ በመከተል፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የተናገረውን የመጀመሪያ አጋማሽ እናገኛለን፡፡ ይህ የመጀመሪያ አጋማሽ በትዕዛዛዊ ግስ ይጀምራል፡፡ በዘፍጥረት 12፡1 እነዚህን ቃላት እናነባለን፡

“ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ፡፡” (ዘፍጥረት 12፡1)

እንደምንመለከተው፣ ይህ ክፍል የሚከፈተው “ውጣ” (ወይም አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንደሚፈታው “ውጣና … ሂድ”) በሚለው ትእዛዝ ነው፡፡ አብርሃም አንድ ነገር እንዲያደርግ፡ ወደ ከነዓን ምድር እንዲሄድ እግዚአብሔር ያዝዘዋል፡፡ እግዚአብሔር ለአባታችን የሰጠው ቀዳሚ ትዕዛዝ ይህ ነው፡፡

ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንዲሄድ ከተሰጠው ትዕዛዝ ቀጥሎ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የተናገረው ንግግር በቁጥር 2 የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ በተገለጡት ሦስት የተለያዩ ግሳዊ መግለጫዎች ለሦስት ተከፍሎ የቀረበ ነው፡፡ ዘፍ 12፡2 እንደገና ተመልከቱ፡

“ታላቅ ህዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ ስምህንም አከብረዋለሁ” (ዘፍ 12፡2)

እነዚህ ቃላት እግዚአብሔር አብርሃምን ሲጠራው ባዘጋጀለት በረከቶች ላይ ያተኩራሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ አብርሃምን ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርገው እግዚአብሔር ይናገራል፡፡ ሁለተኛ፣ አብርሃምን በሀብት እንደሚባርከው ይገልጣል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ የከበረ ስም ወይም ዝና እንደሚሰጣቸው ይናገራል፡፡

አሁን ደግሞ እግዚአብሔር ለአብርሃም ወደ ተናገራቸው ቃላት ሁለተኛ አጋማሽ እንመጣለን፡፡ አብዛኞቹ የዘመናችን ትርጉሞች እንድናየው ባያስችሉንም፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የተናገራቸው ቃሎች ሁለተኛ አጋማሽ የመጀመሪያው አጋማሽ ሰዋሰዋዊ አወቃቀር ተጓዳኝ ነው፡፡ በትዕዛዝ ይጀምርና ሦስት በራሳቸው የሚቆሙ ግሳዊ መግለጫዎችን ያስከትላል፡፡ በዘፍጥረት 12፡2-3 እንዲህ እናብባለን፡፡

“…ለበረከትም ሁን የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፡፡” (ዘፍጥረት 12፡2-3)

“ለበረከትም ሁን” ተብሎ የተተረጎመው፣ የዕብራይስጡ ቃል፣ በቅርፁ ትዕዛዛዊ ነው ደግሞም በቁጥር 1 “ውጣ” ተብሎ የተሰጠው ትዕዛዝ ተጓዳኝ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረፀ ነው፡፡ ግን ይህ ቅፅል እንደ ትዕዛዝ አያገለግልም፡፡ በብዙ መንገዶች ሊተረጎምም ይችላል፡፡ለምሳሌ፡- “ለበረከት ትሆናለህ”ወይም “ለበረከት ሁን” ወይም “በእርግጥ ለበረከት ትሆናለህ” ሊባል ይችላል፡፡ በሁሉም ወቅቶች፣ ይህ ቅፅል ወሳኝ የሃሳብ ሽግግርን ያመለክታል፡፡ ትኩረቱንም አብርሃም በረከትን ይቀበላል ከማለት ዘወር ያደርገውና (በቁጥር 2 የመጀመሪያ ክፍል እንዳየነው) አብርሃም ለሌሎች በረከት መተላላፊያ ይሆናል ወደሚለው ይወስደዋል፡፡

ሁለተኛውም የትዕዛዛዊ ቅፅል ቅርፅ ሦስት ራሳቸውን የቻሉ ግሣዊ መግለጫዎችን ያስከትላል፡፡ እነዚህ ሦስት ግሦች አብርሃም ለሌሎች በረከት የሚሆንበን ሂደት ያመለክታሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር “የሚባርኩህን እባርካለሁ አለው”፡፡ ያም ማለት፣ ከአብርሃም ጋር በመልካም የሚጓዙትን መልካም ነገርን ይሰጣቸዋል ማለት ነው፡፡ ሰዎች አብርሃምን በበጎ ከተመለከቱት እግዚአብሔርም በበጎነት ይመለከታቸዋል፡፡ ሁለተኛ፣ “የሚረግሙህንም እረግማለሁ” በማለት እግዚአብሔር ተስፋን ሰጠው፡፡ ያም ማለት፣ አብርሃምን የሚያቃልሉትን እግዚአብሔር ይረግማቸዋል፡፡ ራሳቸውን የአብርሃም ጠላት አድርገው የሚያሰልፉትን በከፋ ሁኔታ አፀፋ በመስጠት አብርሃምን እንደሚጠብቀው እግዚአብሔር ተስፋን ሰጠው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ግን፣ እግዚአብሔር “የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” አለው፡፡ መጀመሪያ ስትመለከቱት፣ ሦስተኛው ትኩረት የአብርሃምን ጠላቶች ከመርገሙ መሪ ሃሳብ ጋር የሚቃረን ይመስላል፣ እግዚአብሔር ግን በመንታ የበረከት ሂደቶች ማለትም ወዳጆቹን በመባረክ እና ጠላቶቹን በመርገም የምድርን ወገኖች ሁሉ እንደሚባርክ ለአብርሃም ተስፋን ሰጠው፡፡ የምዕራፍ 12 የመክፈቻ ሰዋሰው በሦስት ዋና ክፍሎች እንደሚከፈል አይተናል፡፡ ማለትም፡- መግቢያ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም በሚሰጣቸው በረከቶች ላይ ያተኮረ እና በአብርሃም አማካይነት እግዚአብሔር ለምድር ህዝቦች ሁሉ ስለሚሰጠው በረከት የሚናገሩ ናቸው፡፡

ዝርዝር መግለጫ

በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ አራት ዐቢይ መሪ ሃሳቦች እንደሚታዩ ልብ ብለናል፡፡ ለአብርሃም በተገለጠው መለኮታዊ ጸጋ እንጀምራለን፣ ከዚያም ከአብርሃም የሚጠበቀውን ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ የመዝለቅ ግዴታ እንመለከታለን፣ ከዚያም ለአብርሃም የእግዚአብሔርን በረከት በመጨረሻም በአብርሃም በኩል የሚገለጠውን የእግዚአብሔርን በረከት እናያለን፡፡

መለኮታዊ ጸጋ

የመጀመሪያው ጭብጥ፣ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ በተደጋጋሚ ሲከሰት የምናየው፣ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የነበረው ግንኙነት በእርሱ ጸጋ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው፡፡ መለኮታዊው ጸጋ በዘፍጥረት 12፡1 የመግቢያ ቃላት ውስጥ ሰወር ብሎ ተቀምጧል፡፡ እንደተመለከትነው፣ በዚያ ስፍራ እንዲህ እናነብባለን፡

እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ ብሎት ነበር፡፡ (ዘፍጥረት 12፡1)

አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት እውን የሆነው አብርሃና ገና እግዚአብሔርን በማገልገል ረገድ ምንም ከማድረጉ በፊት እግዚአብሔር ወደ አብርሃም ሕይወት በመምጣቱ መሆኑን እነዚህ ቀላል ቃላት የሙሴን ቀደምት ተደራሲያን ያሳስባሉ፡፡

አብርሃም የተጠራው ገና በወጣትነት ዕድሜው ነበር፡፡ ገና ወደ ከነዓን አልሄደም፤ ጠላቶቹን ገና ድል አላደረገም፤ ለቃል ኪዳን ታማኝነት ገና ራሱን አልሰጠም ነበር በሰዶምና ጎሞራ ስለሚኖሩት ጻድቃንም ገና አልማለደም፤ የቱንም ዓይነት የእምነት ፈተና ገና አላለፈም፡፡ በተቃራኒው፣ እግዚአብሔር አብርሃምን እንደ ልዩ አገልጋዩ የጠራው ለአብርሃም ደግነቱን ለማሳየት ስለ ወደደ ብቻ ነው፡፡

እርግጥ ነው፣ የእግዚአብሔር ጸጋ የተገለጠው አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው የመጀመሪያ ጉዞ ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ በአብርሃም የታሪክ ሂደቶች ሁሉ ይገለጥ የነበረ መሪ ሃሳብ ነው ምክንያቱም እግዚአብሔር በአባታችን ሕይወት በእያንዳንዱ ክፍልፋይ ውስጥ ሁሉ ምህረቱን ስላሳየ ነው፡፡ ምክንያቱም አብርሃም ኃጢአተኛ ስለሆነ፣ ዘወትር የእግዚአብሔር ምህረት የሚያስፈልገው ሰው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በ15፡6 ከሚገኘው ዕውቅ ጥቅስ የምንረዳው አብርሃም የዳነበት ጽድቅ እንኳን የተገኘው የምህረት ስጦታ ሆኖ ነው፡፡ በዚያም እንዲህ ይነበባል፡

አብርሃምም በእግዚአብሔር አመነ፣ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት፡፡ (ዘፍጥረት 15፡6)

ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 4፡3 እና በገላትያ 3፡6 እንዳመለከተው እግዚአብሔር ለአብርሃም ጽድቅ እንዲቆጠርለት የማድረጉ እውነታ የሚያመለክተው የምህረት መገለጫ መሆኑን እንጂ የመልካም ሥራዎች ሽልማት ሆኖ አይደለም፡፡ አብርሃም ይህንንና ሌሎችንም በረከቶች ከእግዚአብሔር የተቀበለው በዚህ መለኮታዊ ጸጋና ምህረት አማካይነት ነው፡፡

እንደ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ጸጋ ጠቀሜታ ሁላችን እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት የጀመረው በጸጋው ሲሆን፣ ከእርሱ ጋር ያለንንም ግንኙነት የሚጠብቀው በእርሱ ጸጋ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ከእግዚአብሔር ምህረት ውጪ አድራሻችን የት ነበር? እንግዲህ ነገሩ ለአብርሃምም እንዲሁ እውነትነት ነበረው፡፡ ከዚህም በላይ፣ ሙሴ ስለ አብርሃም ለጻፈላቸው ለእስራኤላውያንም ሕይወት የእግዚአብሔር ጸጋ ወሳኝ ነበር፡፡ እነርሱም በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው የእግዚአብሔር ምህረት የሚያስፈልጋቸው ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ሙሴ የአብርሃምን የሕይወት ታሪክ ሲያቀናብር፣ ደግሞ ደጋግሞ ትኩረታቸውን ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ይስብ ነበር፡፡

የአብርሃም ታማኝነት

ከእግዚአብሔር ጸጋ መሪ ሃሳብ በተጨማሪ፣ ዘፍጥረት 12፡1-3 የአብርሃምን ታማኝነት እንደሚገልፅ ልብ ልንል ይገባናል፡፡ አብርሃም ምህረቱን እንዲቀበል እግዚአብሔር ዝም ብሎ አልመረጠውም፤ ለአባታችን ምህረቱን ያሳየው አብርሃም መታዘዝ በሞላበት ታማኝነት ምላሽ እንዲሰጠው ነበር፡፡ እንደተመለከትነው፣ በዘፍጥረት 12፡1 የተጠቀሰው ትዕዛዝ አብርሃም በተለየ መንገድ ለእግዚአብሔር ታማኝ የመሆን ሃላፊነት እንዳለበት አፅንዖት ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ነበር ያዘዘው፡

ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደ ማሳይህ ምድር ውጣ፡፡ (ዘፍጥረት 12፡1)

ይህ መለኮታዊ ጥሪ ከአብርሃም በርካታ ታማኝነትን እንደሚጠይቅ ለማየት ብዙ መላ መምታት አይጠይቅም፡፡ አገሩንና የአባቱን ቤት በመተው ገና ወደማያውቀው ምድር መጓዝ ነበረበት፡፡ አዎን፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም ምህረቱን አሳይቶታል፣ ሆኖም አብርሃምም ከውስጣዊ ማንነቱ ለእግዚአብሔር የታመነ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበት ነበር፡፡

የሚያሳዝነው ግን፣ በርካታ ክርስቲያኖች አብርሃም ዝም ብሎ የእምነትና በእግዚአብሔር የመታመን ተምሳሊት ብቻ እንደሆነ ወደማሰብ ያጋድላሉ፡፡ ይህ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ወሳኝ የሆነ መሪ ሃሳብ ሲሆን በአዲስ ኪዳን የተለያዩ ምንባቦች ውስጥም ተሰምሮበታል፡፡ ሆኖም አብርሃም ታማኝ እንዲሆን እና የታመነ አገልግሎትም እንዲሰጥ እግዚአብሔር እንዳዘዘውም ቸል ልንል አይገባም፡፡ እግዚአብሔር ታማኝነትን ከአባታችን ብዙ ጊዜ ጠይቆ ነበር፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ሊዘልቅ ይገባው ነበር፡፡

በጣም ድራማዊ ምሳሌነት ያለውና ለእግዚአብሔር ታማኝነቱን እንዲያሳይ የተጠየቀበት ወቅትም የሚገኘው በዘፍጥረት 22 ውስጥ ሲሆን፣ በዚያም አባታችን ልጁን ይስሐቅን ከሚወድድበት ፍቅር በበለጠ እግዚአብሔርን የሚወድድ መሆኑን ለማረጋገጥ ልጁን ይስሐቅን እንዲሰዋ እግዚአብሔር አዝዞታል፡፡ ከእግዚአብሔር ከፍተኛ መታዘዝን የሚጠይቅ ነገር ሲመጣ ነገሩ ምን ያህል እንደሚከብድ መገመት ያዳግታል፡፡

አብርሃም በዚህና በሌሎችም መንገዶች ታማኝነቱን እንዲገልጥ ቢጠየቅም፣ ዘፍጥረት 12፡1 አብርሃም የተቀበለውን ወሳኝ ሃላፊነቶች ግልፅ ያደርጋል፡፡ በዚያም እግዚአብሔር፡

“እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ፡፡” (ዘፍጥረት 12፡1) ይለዋል፡፡

ይህ ምንባብ፣ አብርሃም እግዚአብሔር ወደ ሚያሳየው ምድር እንዲሄድ የሚጠበቅበት መሆኑን ይገልፃል፡፡ አብርሃም የተስፋውን ምድር ሊወርስ ይገባዋል፣ ይህም መሪ ሃሳብ ስለ አባታችን በተፃፈው ታሪክ ውስጥ በርካታ ጊዜያት ተገልጧል፡፡ አባታችን ወደ ተስፋዪቱ ምድር መሄዱ ለእግዚአብሔር ትልቅ ዕቅድ ማለትም ለአብርሃምም ሆነ ለእርሱ ታማኝ ዝርያዎች በጣም ወሳኝነት ነበረው፡፡ ሙሴ እነዚህን ታሪኮች ስለ አብርሃም የጻፈው እርሱ ራሱ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለሚመራቸው ለእስራኤላውያን መሆኑን ስናስታውስ፣ ይህንን አፅናዖት ማየታችን አያስገርመንም፡፡

እንደ ክርስቶስ ተከታዮች፣ ምንም እንኳን ድነት የእግዚአብሔር ጸጋ ነፃ ስጦታ መሆኑን ብንረዳም፣ ትዕዛዛቱን ለመታዘዝ የቻልነውን ሁሉ በማድረግ ለእርሱ ያለንን አድናቆት እንድናሳይ እግዚአብሔር ይጠብቅብናል፡፡ ሙሴም እነዚህን መርሆች ያውቃቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ጸጋ አብርሃም ለእግዚአብሔር ታማኝ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ የታማኝት አስፈላጊነት ጉዳይ የአብርሃምን ሕይወት በምናጠናበት ወቅት በርካታ ጊዜ ተደጋግሞ የሚገለጥ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ሙሴ ስለ ተቀዳሚ ተደራሲያኑ ስለ እስራኤላውያን አንድ ነገር ያውቃል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ታማኝ ሆኖ የመኖርን አስፈላጊነት ወደ መርሳቱ ያዘነብላሉ፡፡ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር ሲያስወጣቸው ብዙ ምህረቱን ቢያሳያቸውም፣ በምድረ በዳም ቢጠብቃቸውም፣ እነርሱ ግን ከትዕዛዛቱ ፈቀቅ ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ከአብርሃም ታሪኮች ውስጥ አንዱ አብርሃም ለእግዚአብሔር የነበረው ታማኝነት የተገለጠበት መሪ ሃሳበ ሆኗል፡፡ ይህም መሪ ሃሳብ የሙሴ ቀደምት ተደራሲያን እና እኛም ዛሬ፣ ታማኝነት በሞላበት መንገድ እግዚአብሔርን እንድንታዘዝ ይቀሰቅሰናል፡፡

የአብርሃም በረከቶች

እንደተመለከትነው፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም ብዙ ጸጋን ሰጥቶታል፣ ከእርሱም ታማኝነት ያለበትን መሰጠት ጠይቆታል፡፡ በዘፍጥረት 12፡1-3 ውስጥ ልብ ልንለው የሚገባን ሦስተኛው መሪ ሃሳብ ለአብርሃም የተሰጡት በረከቶች ናቸው፡፡ በዘፍጥረት 12፡2 ውስጥ እግዚአብሔር ለአብርሃም ይህንኑ መናገሩን ማስታወስ ትችላላችሁ፡

“ታላቅ ህዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ ስምህንም አከብረዋለሁ” (ዘፍ 12፡2)

እግዚአብሔር ለአባታችን ሦስት በረከቶችን ሰጥቶታል፡፡ በመጀመሪያ፣ አብርሃም ታላቅ ህዝብ ይሆናል፡፡ ዝርያውም ከቁጥር ያለፈ ይሆናል፡፡ ዘሩም መንግሥት፣ ታላቅ ህዝብ ይሆናል፡፡ በዚያን ወቅት አብርሃምና ከእርሱ ጋር የነበሩት በቁጥር አነስተኛ ነበሩ፡፡ አብርሃምም የራሱ ልጅ አልነበረውም፡፡ ሆኖም፣ አንድ ቀን የአብርሃም ዝርያ ከሰማይ ከዋክብት በቁጥር እንደሚበልጥ እግዚአብሔር ተስፋን ሰጠው፡፡

ሁለተኛ፣ እግዚአብሔር አብርሃምን እንደሚባርከው ነገረው፡፡ በየትኛውም መንገድ፣ ይህ መግለጫ አብርሃምና ዘሩ ከልክ የተረፈ በረከትን ይቀበላል ማለት ነው፡፡ አብርሃምና ዘሩ በተትረፈረፈ ብልጽግና ይኖራል፡፡ በምድር የሚንከራተቱ አይሆኖም፣ ወይም ጊዜያዊ ሰፋሪዎች አይሆኖም፡፡ አብርሃምና ልጆቹ ታማኝ መሆናቸው ከተረጋገጠ፣ በብልፅግና ይኖራሉ፡፡

ሦስተኛ፣ የእግዚአብሔር በረከት ለአብርሃም ታላቅ ስምን ያስገኝታል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አብርሃም ወደ ተስፋዪቱ ምድር ቢሄድና እግዚአብሔርን በታማኝነት ቢያገለግል፣ የቁጥሩ መብዛትና የዘሩ መበልጸግ እርሱንና ዘሩን በመላው ዓለም የተከበሩ ያደርጋቸዋል ማለት ነው፡፡ታላቅ ክብር ወደ አባታችንና ታማኝ ወደሆኑት ዘሮቹ ይመጣል፡፡

እንዲያውም፣ በአብርሃም ታሪኮች ውስጥ፣ እነዚህን የመሳሰሉ በረከቶች ደግመው ደጋግመው ለአብርሃም የፈሰሱለት መሆኑን ሙሴ አመልክቷል፡፡ አብርሃም ልጆች ነበሩት፤ ከአንዱ ልምምዱ ወደ ሌላው ሲሸጋገር እየበለጸገ ሄዷል፡፡ በአካባቢውም ታዋቂ ሰው ሆኗል፡፡ እነዚህን ታሪኮች ለሚያደምጡ እስራኤላውያንም፣ የአብርሃም በረከቶች እነርሱን ስለሚጠብቋቸው በረከቶች ታላቅ ተስፋን ይሰጧቸዋል፡፡ ዘሩን ማብዛቱ፣ ለአባታችን የተሰጡት ብልፅግናዎችና ዝና እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ ገና የሚሰጠው ታላቅ ስጦታ ጥላ ብቻ ነበሩ፡፡

እንደ ክርስቲያኖች፣ ሁሉን ተናግረን ልንጨርሳቸው አዳጋች የሆኑ በረከቶችን ከእግዚአብሔር ቀብለናል፡፡ በእርግጥም፣ በሙሴ መሪነት ወደ ተስፋዪቱ ምድር የተጓዙትም እስራኤላውያን ቁጥር ስፍር የሌላቸውን በረከቶች ተቀብለዋል፡፡ ከባርነት ነፃ ወጥተዋል፤ በቁጥር በዝተዋል፤ በጉዞአቸው ሁሉ ከክፉ ተጠብቀው ወደ ተስፋዪቱና የወደፊት ታላቅ በረከታቸውን ወደሚቀበሉበት ምድር ተጉዘዋል፡፡ እስራኤላውያን ግን ልክ እንደኛ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያደረገላቸውንና ገና ወደፊት ያዘጋጀላቸውን ቸል በማለት ወደ መርሳቱ ያጋድላሉ፡፡ ስለዚህ ሙሴ እስራኤላውያን አድማጮቹን እግዚአብሔር የሰጣቸውን በረከት እንዲያስቡ እና ልባቸውም ለእርሱ ባላቸው አድናቆት እንዲሞላ ለማድረግ ስለ አብርሃም በረከት ይጽፍላቸዋል፡፡

በአብርሃም አማካይነት የተሰጡ በረከቶች

ዘፍጥረት 12፡1-3 ከእግዚአብሔር ምህረት፣ ከአብርሃም ታማኝነት እና እግዚአብሔር ለአብርሃም ከሰጣቸው በረከቶች በተጨማሪ፣ በረከቶቹ በአብርሃም በኩል ለሌሎች ህዝቦች የተሰጡ ወደ መሆኑ እውነታ ትኩረታችንን ይስበዋል፡፡ እግዚአብሔር በዘፍጥረት 12፡2-3 የተናገረውን አስታውሱ፡

“…ለበረከትም ሁን የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፡፡” (ዘፍጥረት 12፡2-3)

እነዚህ ቃላት አብርሃም በረከትን እንደሚቀበል ብቻ ሳይሆን የምድር ነገዶች ሁሉ በእርሱ አማካይነት እንደሚባረኩ ያብራራሉ፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንዲሄድ የጠራው የእርሱና የዘሩን ሕይወት ለማበልፀግ ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን የጠራው ለምድር ህዝቦች ሁሉ የመለኮታዊ በረከት ማስተላለፈያ ቧንቧ እንዲሆን ነው፡፡ የአብርሃም ዓለም አቀፋዊ በረከት በሁለት መንገዶች እንደሚገለጥ ይህ ምንባብ የሚያስተምር መሆኑን ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ በዘፍጥረት 12፡3 እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል፡

“የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ” (ዘፍጥረት 12፡3)

በዚህ ምንባብ መሠረት፣ በሰው ዘር መካከል አብርሃም ልክ እንደ ባለ ሁለት አፍ ሰይፍ ያገለግላል ማለት ነው፡፡ አብርሃም ከእግዚአብሔር ሞገስን በማግኘቱ ምክንያት፣ የሌሎች መንግሥታት ህዝብ አብርሃምን ሲባርክ፣ እርሱን ሲያከብሩት በዚያም እርሱ የሚያገለግለውን እግዚአብሔርን ይባርካል ከዚያም እግዚአብሔር እነርሱን ይባርካቸዋል፡፡ ግን የሌሎች መንግሥታት ህዝቦች አብርሃምን ሲያጠቁ እና በዚም የአብርሃምን አምላክ ሲያቃልሉ፣ እግዚአብሔር ይቀጣቸዋል፡፡ የሌሎች ህዝቦች ዕጣፈንታ ከአብርሃም ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡

በሕይወት ዘመኑ ሁሉ፣ ሌሎች መንግሥታትን ከሚወክሉ ሰዎቸ ጋር ማለትም ከፍልስጥኤማውያን፣ ከከነዓናውያን፣ ከግብጻውያን እና የሞዓባውያንና የአሞናውያን አባት ከሆነው ከወንድሙ ልጅ ከሎጥ ጋር ግንኙነት ነበረው፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች ወሳኝ ነበሩ ምክንያቱም ሌሎች ሰዎች ከአብርሃም ጋር እንደነበራቸው ግንኙነት በመባረክም ሆነ በመርገም ቃሉን ሚጠብቅ መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ በተጨማም አብርሃም በሕይወት ዘመኑ የምድር ሁሉ በረከት መሆን መጀመሩን ያመለክታሉ፡፡

ደግሞ ደጋግሞ ግን የእግዚአብሔር ህዝብ እነዚህን ወሳኝ ትምህርቶች መርሳት ይቀልለው ነበር፡፡ በሙሴ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን በዚህ ዘመን ከሚኖሩ በርካታ ክርስቲያኖች ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ ከእግዚአብሔር በተቀበልነው ድነትና ሕይወት ደስ እንሰኛለን፣ ሆኖም እነዚህ በረከቶች ለእኛ ለምን እንደተሰጡ እንረሳለን፡፡ በሙሴ መሪነት እግዚአብሔር ለእስራኤል ሰጥቷቸው የነበሩ እያንዳንዳቸው በረከቶች እና ለዛሬዋም ቤተክርስቲያን የተሰጡ እያንዳንዳቸው በረከቶች ላቅ ላለ ዓላማ የተቀረፁ ነበሩ፡፡ እኛ የተባረክነው የእግዚአብሔርን በረከቶች ለዓለም ሁሉ ለማድረስ ነው፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን ወደ ራሱ ጠራው ስለዚህም አብርሃም የዓለምን መንግሥታት ወደ እግዚአብሔር በረከቶች ይመራቸዋል ማለት ነው፡፡ በሙሴም ዘመን እግዚአብሔር እስራኤልን ወደ ራሱ ጠራ እስራኤል ደግሞ ህዝቦችን ወደ እግዚአብሔር በረከቶች ያመጣሉ ማለት ነው፡፡ በዚህም ዘመን እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ጠራ ስለዚም እኛ የዓለምን መንግሥታት ወደ እግዚአብሔር በረከቶች እናመጣለን፡፡ የአብርሃምን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተቀበሉት እስራኤላውያን ይህ መሪ ሃሳብ ወሳኝ ነው፡፡ በእኛም ዘመን ክርስቶስን ስንከተል ለእኛም ወሳኝት አለው፡፡

ማጠቃለያ

በዚህ ትምህርት የአብርሃምን ሕይወት በወፍ በረር ለመዳሰስ የመጀመሪያ ምልከታችንን አድርገናል፡፡ ትኩረታችንንም በዚህ የዘፍጥረት መጽሐፍ ክፍል መዋቅር ወይም ዲዛይን ላይ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም ሙሴ በስነጽሁፋዊ አወቃቀሩ አውድ መሠረት ያቀረበውን ዐበይት መሪ ሃሳቦችን ወይም ይዘቶችን መርምረናል፡፡

በዚህ ትምህርት ወደ ፊት ስንገፋ፣ የዚህን ትምህርት ርዕሶች መላልሰን እናያለን፡፡ የአብርሃም ሕይወት ባለ አምስት አቻ እርከን መሆኑንም ተመልክተናል፡፡ በተጨማሪም በአብርሃም ሕይወት አራት ዐቢይ መሪ ሃሳቦች መኖራቸውን ዐይተናል፡፡ የእግዚአብሔር ደግነት ለአብርሃም፣ የአብርሃም ታማኝነት፣ የእግዚአብሔር በረከቶች ለአብርሃም እና የእግዚአብሔር በረከቶች በአብርሃም በኩል ናቸው፡፡ እነዚህም መሪ ሃሳቦች የአብርሃም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተጻፈለት ለእስራኤል ህዝብ ምን ትርጉም እንዳለው መረዳትን የሚሰጡን ብቻ ሳይሆኑ፣ ይህን የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል በሕይወታችን ማዛመድ የምንችልበትን መንገድም ያመለክቱናል፡፡

Continue reading the full transcript