<link rel="stylesheet" href="https://cdn.plyr.io/3.7.8/plyr.css" />
ወደ ካታሎግ ተመለስFAአባ አብርሃም
አባ አብርሃም ·Videoከእንግሊዝኛ ተተርጉሟል

FA-02 የአብርሃም ሕይወት፡- የመጀመሪያ ትርጉም

ሙሉውን ጽሑፍ ያንብቡ

እነዚህ ታሪኮች በእስራኤል ሕዝብ ላይ በመጀመሪያ ሊያደርጉት የነበረውን ተጽዕኖ ይዳስሳል። ወደ ተ約 ቦደት ሲሄዱ ከሙሴ ጋር ተከተሉ።


From the transcript

ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ጎብኙ፡፡

የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ቅዱሳት መጻሕፍትን ይወድዳሉ፡፡ በበርካታ የተለያዩና በጣም ግለሰባዊ በሆኑ መንገዶች ለሕይወታችን ሲናገሩን እናገኛቸዋለን፡፡ ይህም ቅዱሳት መጻሕፍትን አስመልክቶ በፍፁም ልንዘነጋው የማይገባን የከበረ እውነት ነው፡፡ ሆኖም ይህ አስደናቂ በሆነ መንገድ ግለሰባዊ ይዘት ያለው የቅዱሳት መጻሕፍት አድማስ ዘወትር ልናስታውስ የሚገባንን አንድ ነገር እንዳናስተውል ያደርገናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለእኔ ወይንም ለእናንተ በቀጥታ አልተፃፈም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ይኖሩ ለነበሩ ሌሎች ሰዎች ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት ዛሬ በእኛ ሕይወት ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ ለመረዳት ስንጥር፣ ዘመነኛው ተዛምዶአችን በቅዱሳት መጻሕፍት ቀደምት ፍቺ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ልናረጋግጥ ይገባል፡፡

ይህ አባታችን አብርሃም የሚል ርዕስ የሰጠነው ተከታታይ ትምህርት ነው፡፡ በዚህም ትምህርት በዘፍጥረት 11፡10 -25፡18 የሚገኘውን የአብርሃምን ሕይወት እንመረምራለን፡፡

ይህኛው ደግሞ ከሦስቱ የመግቢያ ትምህርቶች ሁለተኛው ሲሆን፣ “የአብርሃም ሕይወት፡ ቀደምት ትርጉም” የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ በዚህ ትምህርት የአብርሃምን ሕይወት ሲጻፉ በነበረበት ዘመን እና ከተፃፈላቸው ሰዎች አንፃር መመልከት ምን ያህል አስፈላጊ እደሆነ እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ታሪኮች በሙሴ መሪነት ወደ ተስፋዪቱ ምድር ይጓዙ በነበሩት እስራኤላውያን ላይ ምን ቀደምት ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ታስቦ እንደተፃፉ እንመረምራለን፡፡

የዘፍጥረት 11፡10-25፡18 ቀደምት ትርጉም ሁለት ዐበይት ጉዳዮችን በመዳሰስ እንመለከተዋለን፡፡ በመጀመሪያ፣ በአብርሃም የሕይወት ታሪክና በቀደምት ተደራሲያኑ ልምምዶች መካከል ሙሴ ሊያመለክት የፈለገውን ትስስር እናመለክታለን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ እነዚህ ትስስሮች በቀደምት ተደራሲያኑ ዘንድ የነበራቸውን ጥቂት እንድምታዎች ጠቅለል አድርገን እንመለከታለን፡፡

የአብርሃምን ሕይወት ቀደምት ትርጉም ከመመልከታችን አስቀድሞ፣ ባለፈው ትምህርት የተመለከትነውን ቆም ብለን መከለስ ይገባናል፡፡ እስከዚህች ነጥብ ድረስ፣ በሁለት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አተኩረናል፡፡ በመጀመሪያ፣ ዘፍጥረት 12፡1-3 በአብርሃም ሕይወት ውስጥ የሚገኙ አራት ዐቢይ መሪ ሃሳቦችን እንደሚገልጥ አመልክተናል፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገለጠው በጎነት (እግዚአብሔር ለአባታችን ምህረትን በብዙ መንገድ አሳይቶታል)፣ አብርሃም ለእግዚአብሔር ታማኝ የመሆን ሃላፊነቱ (አብርሃም እርሱን እንዲታዘዝ እግዚአብሔር የሚጠብቅበት መንገዶች)፣ የእግዚአብሔር በረከት ለአብርሃም (ታላቅ ህዝብ፣ ብዙ ልጆች፣ ምድር እና ታላቅ ስም)፣ በአብርሃም አማካይነት የእግዚአብሔር በረከት ለሌሎች (አብርሃም ለምድር ወገኖች ሁሉ በረከት እንደሚሆን የተነገረ ተስፋ)፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ እነዚህ መሪ ሃሳቦች በዘፍጥረት ውስጥ የአብርሃምን ታሪክ ቅርፅ እንዲይዝ ያደረጉበትን መንገድም አይተናል፡፡ የአብርሃም ታሪክ በአምስት ሚዛናዊ ደረጃዎች እንደሚከፈልም አውቀናል፡፡ በመጀመሪያ፣ በ11፡10-12፡9 ውስጥ በሚገኘው በአብርሃም ዳራና ቀደምት ልምድ ጀምረናል፡፡ ሁለተኛ፣ አብርሃም ቀደምት በሆኑት ጊዜያቱ ከተለያዩ የህዝብ ወገኖቸ ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ትዕይንቶችን በዘፍጥረት 12፡10-14፡24፡፡ በዘፍጥረት 15፡1-17፡27 እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ ያተኮረውን ሦስተኛውን ማዕከላዊ ክፍል፡፡ አራተኛውንና አብርሃም ከሌሎች ህዝቦች ተወካዮች ጋር የነበረውን የኋላ ግንኙነት በዘፍጥረት 18፡1-21፡34 ተመልክተናል፡፡ አምስተኛው አንጓ ደግሞ የአብርሃምን ዝርያና ሞት የሚተርከው በዘፍጥረት 22፡1-25፡18 የሚገኘው ነው፡፡

እነዚህ አምስት ደረጃዎች የአባታችንን ሕይወት በሚዛናዊነት ያቀርቡልናል፡፡ ሦስተኛውና በ15፡1-17፡27 የሚገኘው፣ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን የሚናገረው ክፍል፣ የአብርሃም ሕይወት ማዕከላዊ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሁለተኛውና አራተኛው ክፍሎች ደግሞ ሁለቱም አብርሃም ከሌሎች ሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ ስለሚያተኩሩ ተዛማጅነት አላቸው፡፡ የመጀመሪያውና የመጨረሻዎቹ ክፍሎች ደግሞ የአብርሃምን ሕይወት የመጨረሻ ምዕራፍ፣ በማመልከት ያለፈውን የዘር ግንዱን በማመልከት ወደፊት ይስቡናል፡፡

በብዙ ረገድ፣ ይህ ትምህርት በአብርሃም ሕይወትና ውቅርና ይዘት ላይ በሚገኙ መረዳቶች ላይ የተገነባ ነው፡፡ ይህንን ክለሳ በልቡናችን ይዘን፣ ወደዚህ ትምህርት ዐበይት ትኩረት፣ ማለትም በዘፍጥረት መጽሐፍ ወደሚገኘው የአብርሃም ሕይወት ቀደምት ትርጉም እንሸጋገራለን፡፡ በአብርሃም ሕይወት ታሪኮችና እነዚያን ታሪኮች ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀበሉት እስራኤላውያን ልምምዶች መካከል ያለውን ትስስር/ግንኙነት በመመልከት እንጀምር፡፡

ትስስር/ግንኙነት

በእነዚህ ተከታታይ ትምህርቶች የአብርሃምን ሕይወት የምንፈታበትን መንገድ የምንገነባው ታሪኮቹ በቀደምትነት የተፃፉት በሙሴ ዘመን መሆኑን እና በዚያን ዘመን እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም እንደዚያው ብርቱ መሆናቸውን በመረዳት ላይ ይሆናል፡፡ አብዛኞቹ ነቃፊ ምሁራን እነዚህ ታሪኮች በሙሴ ዘመን መጻፋቸውን አያምኑም፣ ሆኖም የብሉይ ኪዳን ሌሎች ክፍሎችና ኢየሱስም ራሱ ዘፍጥረትን ሙሴ እንደጻፈው አመልክተዋል፣ በዚህም ምክንያት የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ሙሴ ስለመሆኑ እውቅና ሊሰጡ ይገባል፡፡ በዚህ ተከታታይ ትምህርት ግን አንድ እርምጃ እልፍ የማለት ዓላማ አንግበናል፡፡ እነዚህን ታሪኮች ሙሴ የመጻፉን እውነታ እንድንጨብጥ ብቻ ሳይሆን፤ ለምን እንደፃፋቸውም ጭምር ማወቅ እንሻለን፡፡ ስለ አብርሃም ሕይወት የነበረው አመለካከት ምን ነበር? የመጻፉ ዓላማ ምን ነበር? የአብርሃምን ሕይወት ቀደምት ትርጉም ለመመርመር የሚያዋጣው አንዱ መንገድ የአብርሃምን ታሪኮች ከቀደምት ተደራሲያኑ ማለትም ከግብፅ ወደ ተስፍዪቱ ምድር በእርሱ መሪነት ከተጓዙት እስራኤላውያን ልምምዶች ጋር ሙሴ ያስተሳሰረበትን መንገድ መመልከት ነው፡፡

ሙሴ ስለ አብርሃም የጻፋቸውን ታሪኮች ከቀደምት ተደራሲያኑ ጋር እንዴት እንዳስተሳሰራቸው ለመመርመር፣ ሦስት ጉደዮችን እንዳስሳለን፡፡ መጀመሪያ፣ ስለ እነዚህ ትስስሮች ስንናገር ምን ማለታችን እንደሆነ እናያለን፡፡ ሁለተኛ፣ በአብርሃም ሕይወት ታሪኮች ውስጥ የሚታዩ ጥቂት የትስስር ዓይነቶችን እንለከታለን፡፡ ሦስተኛ፣ በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ ያሉ ትስስሮችን በአብርሃም ሕይወት ውቅረ ውስጥ ያሉትን አምስት እርከኖች በመመልከት እናጠቃልላቸዋለን፡፡ ትስስር ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ በመመልከት እንጀምር፡፡

ትርጓሜ

በብዙ መንገዶች፣ ሙሴ የአብርሃምን የህይወት ታሪኮች በሚያጠናቅርበት ወቅት፣ ራሱን ያገኘው ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጸሐፈዎች ራሳቸውን ባገኙበት ስፍራ ነበር፡፡ በሁለት ዓለማት መካከል ቆሞ ነበር፡፡ በአንድ በኩል፣ ሙሴ እኛ “ያኛው ዓለም” ብለን የምንጠራውን የአብርሃምን ዓለም ታሪክ ተቀብሎ ነበር፡፡ ከ500 ወይም 600 ዓመታት ቀደም ብሎ በአብርሃም ሕይወት ምን እንደተከናወነ አንድም ከትውፊት አለበለዚያም ከእግዚአብሔር ልዩ መገለጥ አውቆ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ፣ መሴ አስቀድሞ የተገናኘው ከጥንታዊው የአብርሃም የሕይወት ዘመን ጋር ነበር፡፡

በሌላ በኩል ግን፣ ሙሴ የተጋጠመው ራሱ ከኖረበት ዘመን ማለትም የሙሴና እና እርሱን ይከተሉ የነበሩ እስራኤላውያን የኖሩበትን እኛም “የእነርሱ ዓለም” ብለን ከምንጠራው ጋር ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ይኖሩ የነበሩትን የእግዚአብሔር ህዝብ እንደሚመራ መሪ፣ በእነርሱ ዓለም የነበሩዋቸውን መሻቶች ለማሟላት በሚያስችላቸው መንገድ ሙሴ ስለ ጥንታዊው የአብርሃም የሕይወት ዘመን ታሪክ ጽፎላቸዋል፡፡

ሙሴ “በዚያኛው ዓለም” ማለትም በአብርሃም የሕይወት ዘመንና “በእነርሱ ዓለም” (እርሱ በኖረበት ዘመን) መካከል መካከለኛ በመሆን፣ በአባታችን ሕይወትና በአንባቢዎቹ ሕይወት መካከል ትስስር በመፍጠር የጻፈላቸውን ታሪክ ጠቀሜታ እንዲያስተውሉ ማድረግ ዓላማው ነበር፡፡ ይህም ማለት፣ ሙሴ ታሪኮቹን የመረጠውና ቅርፅ ያስያዛቸው ይከተሉት የነበሩ እስራኤላውያን የአብርሃም ሕይወት ከእነርሱ ህይወት ጋር ትስስር እንዳለው እንዲያስተውሉ ለማድረግ ነበር ማለት ነው፡፡ ከዚህ ላቅ ያለው ደግሞ፣ ሙሴ ይህንን የጻፈው ተደራሲያኑ በአብርሃም ሕይወትና በዛሬው በእነርሱ ልምምዶች መካከል ያለውን ተመሳሳይነትና ተቃርኖ እንዲያስተውሉ ለማድረግ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ንፅፅሮችና ተቃርኖዎች ጨረፍታ ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጣም ጠለቅ ያሉና ዝርዝር ናቸው፣ ሆኖም ሙሴ በሁሉም ምዕራፎች በአብርሃም ሕይወትና በእርሱ ተቀዳሚ ተደራሲያን ሕይወት መካከል ወዳለው ንፅፅርና ተቃርኖ ያመለክታቸዋል፡፡

እንግዲህ የትስስርን መሠረታዊ ሃሳብና ተቀዳሚ ትርጉሙን ከተመለከትን፣ ወደ ሁለተኛው ነገረ ጉዳያችን እንሸጋገር፣ እርሱም በአብርሃም ሕይወትና በተቀዳሚ ተደራሲያኑ በእስራኤላውያን ልምምዶች መካከል ያሉትን የትስስር ዓይነቶች የምንዳስስበት ነው፡፡

ዓይነቶች

ለአንባቢዎቹ አግባብነት ያለው መልዕክት የሚያስተላልፍ የትኛውም ታሪክ፣ አንባቢዎቹ ሊረዱ የሚችሉትን ዓለም ይዞ መቅረብ ይገባዋል፡፡ ታሪኩ የተከናወነበት ዓለም ከገሃዱ ዓለም ፍፁም የተለየ ከሆነና፣ አንባቢዎቹ ከታሪኩ ገፀ-ባህርያትና መሪ ሃሳቦች ጋር ተዛማጅነት ከሌላቸው፣ ታሪኩ ፋይዳቢስ ነው፡፡ ወይም በዚህ ትምህርት ቋንቋ ለማስቀመጥ፣ ያ የአብርሃም ዓለም፣ ከእነርሱ ከሙሴና ከእስራኤላውያን ዓለም ጋር ጨርሶውኑ የተለያየ ከሆነ፣ ስለ አብርሃም የተፃፉት ታሪኮች ለእስራኤላውያን ትርጉም የለሽ ወይም ፋይዳቢስ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ፣ ሙሴ በአብርሃም ዓለምና ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚጓዙት በእስራኤላውያኑ ዓለም መካከል ትስስርን ለመፍጠር ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡

በዚህ ትምህርት ከፊታችን የምንጋፈጠው ጥያቄ ሙሴ እነዚህን ትስስሮች እንዴት ግልጽ አደረጋቸው? የሚለወ ነው፡፡ ስለ አብርሃም የጻፋቸውን ታሪኮች ከአንባቢዎቹ ጋር ሊተሳሰር በሚችል መንገድ እንዴት አዋቀራቸው? በዚህ ትምህርት ወደፊት ስንገፋ፣ ሙሴ ዘገባውን ከእስራኤላውያን ልምምዶች ጋር ያስተሳሰረው በሦስት ዋና መንገዶች መሆኑን እናያለን፡፡ አንደኛ፣ ታሪኮቹን የጻፋቸው እስራኤላውያን እያለፉባቸው ያሉትን ነገሮች ታሪካዊ ዳራ እንዲያመለክቷቸው አድርጎ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ የጻፈው ትረካዎቹ እስራኤላውያን ሊከተሉ የሚገባቸውን ወይም ሊርቁ የሚገባቸውን ነገሮች ተምሳሊት እንዲያሳዋቸው ነው፡፡ ሦስተኛ፣ የጻፈው አብዛኞቹ የአባቶቻቸው ልምምዶች የእስራኤላውያኑን ልምምዶች በጥላነት ወይም በጨረፍታ እንደሚያመለክቱ ለማሳየት ነው፡፡ ወደፊት በዚህ ትምህርታችን እነዚህን የመሳሰሉ ትስስሮችን ደጋግመን ስለምንመለከት፣ ለአሁኑ ሙሴ ለተቀዳሚ ተደራሲያኑ የአብርሃም ሕይወት ምን ያህል ጠቃሚቸው መሆኑን ለማሳየት የተጠቀመባቸውን እነዚህን ሦስት ስልቶች እናስተዋውቃለን፡፡

ዳራዎች

በብዙ መንገዶች፣ ይህኛው ከየትኞቹም ትስስሮች ይልቅ በቀላሉ የሚለየው ዓይነት ነው፡፡ በየትኛውም የሕይወት ጉዞ ላይ ለሚገኙ ሰዎች አሁን እያለፉባቸው ያሉትን ነገሮች ዳራ ማመልከትን ዒላማ አድርጎ ታሪክን መናገር የተለመደ ነው፡፡ ወላጆች ደጋግመው ይህንን ለልጆቻቸው ያደርጋሉ፣ አስተማሪዎች ትምህርታቸውን በዚህ መንገድ ይገልጻሉ፣ መጋቢዎች፣ እና የፖለቲካ መሪዎችም ሳይቀር ተመሳሳዩን ያደርጋሉ፡፡ ለተደራሲያኖቻችን ታሪክ ስንነገር ታሪካዊ ዳራን ሊየገኙበት በሚያስችላቸው መልክ አያይዘን እናቀርብላቸዋለን፡፡

እንግዲህ ከአብርሃም ሕይወት ጋር በተያያዘ፣ ይህንን ትስስር በዚህ መንገድ እንገልፀዋለን፡ እስራኤላውያን አሁን እየተለማመዱት ያለው ነገር ታሪካዊ ስረመሠረቱ በአብርሃም ሕይወት በተከናወኑት ድርጊቶች ውስጥ መሆኑን ሙሴ ሲያመለክተን የታሪካዊ ዳራውን ትስስር እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ፣ ከነዓንን እንደ እስራኤል ምድር አድርጎ የመመልከቱን ታሪካዊ ዳራ ሙሴ ያብራራበትን መንገድ እንውሰድ፡፡ በዘፀአት ወቅት እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ምድር ያንን ያህል ርቀት መጓዝ ለምን አስፈለገ ብለው ብዙ ጊዜ ግራ መጋባታቸውን ታስታውሳላችሁ፡፡ ወደዚያ ምድር ሳይደርሱ እንዳይቆሙ ሙሴ ለምን ከለከላቸው?

በበርካታ ወቅቶች፣ ሙሴ ለዚህ ጉዳይ ምላሽን የሰጠው ስለ አብርሃም ሕይወት ዝርዝር ታሪካዊ ዳራ በማቅረብ ነው፡፡ ቃል በቃል፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም በከነዓን ርስትን እንደሰጠው በመጥቀስ እነርሱም በከነዓን ምድር እንዳላቸው እስራኤላውያን እንዲያስተውሉ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም በዘፍጥረት 15፡18 እንዲህ ተናግሯል፡

“…ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቻለሁ፤” (ዘፍጥረት 15፡18)

ይህ ምንባብ ሙሴ እስራኤል ከነዓንን መውረስ አለባት ብሎ የሚጎተጉትበትን መሠረቱን ወይም ታሪካዊ ዳራውን ያመለክተናል፡፡ እግዚአብሔር ያንን ምድር ለትልቁ አባታቸው ሰጥቷል እና እነርሱ የእርሱ ዝርያዎች በመሆናቸው ተሰጥቷቸዋል፣ ስለዚህ በሌላ ምድር መቀመጥ አግባብነት የለውም፡፡

የአብርሃምን ሕይወት በበለጠ ጥልቀት ስንመረምር ሙሴ ደግሞ ደጋግሞ እነዚህን የመሳሰሉ ታሪካዊ ዳራዎችን ያመለክተናል፡፡ ሙሴ የአብርሃምን ሕይወት በእርሱ ዘመን ከነበረው ከእስራኤል ጋር ያገናኘበት ሁለተኛው መንገድ ተምሳሊቶችን ማሳየት ነው፡፡ በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ ተምሳሊትነት እንዴት እንዳገለገለ እንመልከት፡፡

ተምሳሊቶች

ሙሴ ስለ አብርሃም ሕይወት የጻፋቸውን ታሪኮች ቀደምት ተደራሲያኑ እንደ ተራ ታሪካዊ ዳራ ብቻ እንዲቀበሏቸው አይፈልግም፤ በአብርሃም ሕይወት በነበሩ ሁኔታዎችና በእርሱ ሁኔታዎች መካከል ያሉትን ዐቢይ መመሳሰሎች ያስተውሉ ዘንድ በአባታችን ሕይወት ውስጥ የነበሩትን በርካታ ሁኔታዎች ይገልጥላቸዋል፡፡ እነዚህ መመሳሰሎች ለአብርሃም ተደራሲያን ግብረገባዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ናቸው፡፡ እነዚህ መመሳሰሎች እስራኤል ሊከተል የሚገባውን ተምሳሊት እና አሻፈረኝ ሊል የሚገባውን ለማሳየት ሚያገለግሉ መሆኑን ሙሴ አመልክቷል፡፡

ተምሳሊቶችን ወይም ምሳሌ የሚሆኑ ነገሮችን ማመልከትን ዒላማ አድርጎ ታሪክን መናገር ከአድማጮቻችን ጋር ታሪኮችን ማስተሳሰር የተለመደው መንገድ ነው፡፡ ሁል ጊዜም የሚሆነው እንዲሁ ነው፡፡ በሥራ ቦታ አንድን ሰው ይህን አድርግ ወይም አታድርግ ብለን ስንመክር የምናደርገው ያን በማድረግ ወይም ባለማድረግ ከዚህ ቀደም የሆነን ታሪክ ማንሳት ነው፡፡ ልጆች በትምህርት ቤት በርትተው መሥራት ለምን እንደሚገባቸው ስናስተምር፣ ከዚህ ቀደም በትምህርት ቤት ውስጥ ጠንክረው በመሥራት ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን ታሪክ በምሳሌነት በማንሳት አጠናክረን እናቀርበዋለን፡፡

ሙሴም ስለ አብርሃም ሕይወት የጻፈውን ታሪከ ከተቀዳሚ ተደራሲያኑ ከእስራኤላውያን ጋር ለማስተሳሰር ያደረገው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ የአብርሃምን ታሪክ የሚያቀርብላቸው ገፀ ባህርቱ እስራኤል ሊከተልና ላይከተል የሚገባውን ተምሳሊት እንዲያመለክትለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሙሴ በከነዓን ምድር ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያን ተግዳሮት እንዴት ባለ ልበሙሉነት ሊጋፈጡ እንደሚገባ ያሳሰበበትን እንመልከት፡፡ ኃያል የሆኑት ከነዓናውያን በምድሪቱ ውስጥ ከመኖራቸው የተነሳ ሙሴን ይከተሉ የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ከነዓም ምድር ለመግባት አሻፈረኝ ብለው እንደነበር ከዘኁልቁና ከዘዳግም መጻሕፍት እንረዳለን፡፡ ከነዓናውያን የማይበገሩ ጠላቶች ስለመሰሉዋቸው ልባቸው ፈራ፡፡ በዘዳግም 1፡26-28 ሙሴ ለእስራኤል ነገዶች የተናገረው እንዲህ ይነበባል፡፡

በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ላይ አመፃችሁ እንጂ ወደ እርስዋ መውጣትን እንቢ አላችሁ፤ በድንኳኖቻችሁ ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጉረመረማችሁ፡፡ እግዚአብሔር ስለጠላን እንዲያጠፋን በአሞራውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን፡፡ ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፣ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፣ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፣ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት፡፡ (ዘዳግም 1፡26-28)

ሙሴ ይህንን የከነዓናውያንን ፍራቻ ከተጋፈጠባቸው መንገዶች አንዱ አብርሃም በዘመኑ ከከነዓናውያን ጋር የተጋፈጠበትን ተምሳሊት ማቅረብ ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ በዘፍጥረት 12፡6 ውስጥ በአብርሃም ሕይወት የመጀመሪያውን የከነዓናውያን መረጃ እናገኛለን፡፡

አብራምም … በምድር አለፈ፣ የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በምድር ነበሩ (ዘፍ 12፡6)

በተመሳሳይም መንገድ፣ በዘፍጥረት 13፡7 ውስጥ እንዲህ እናነባለን፡

… በዚያም ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር፡፡ (ዘፍጥረት 13፡7)

ከነዓናውያን በተስፋይቱ ምድር ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ በሁለት አጎራባች ምዕራፎች ሁለት ጊዜ መጥቀስ ሙሴ ለምን አስፈለገው? የመጀመሪያ ዓላማው የአብርሃም ሁኔታ ከእነርሱ ጋር በጣም ተመሳሳይ መሆኑን ለእስራኤል ለማሳየት ነው፡፡ ከነዓናውያን በሙሴ ዘመን እስራኤል ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ሁሉ፣ በአብርሃም ዘመንም በተስፋይቱ ምድር ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ተስፋ በመታመን በከነዓናውያን ወደተያዘችው ምድር ሄደ፡፡ በዚህም መንገድ ምንም እንኳን ዛሬም ከነዓናውያን በምድሪቱ ውስጥ ቢኖሩም በእግዚአብሔር ተስፋዎች በመታመን ልክ እንደ አብርሃም ወደ ተስፋይቱ ምድር በመጓዝ የአብርሃምን ድፍረት የራሳቸው እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ አብርሃም ሊከተሉት የሚገባቸው ተምሳሊት ይሆናቸዋል፡፡

በአብርሃም የሕይወት ጎደና ላይ ስንጓዝ፣ አዎንታዊና አሉታዊ ገፅታዎችን የሚሳዩን በርካታ ምንባቦችን እናገኛለን፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ግን፣ ሙሴ የአብርሃምን ሕይወት ከተደራሲያኑ ሕይወት ጋር ሲያስተሳስረው የአባታችን ሕይወት ዛሬ በእርሱ ዘመን በሚኖሩ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ነገሮችን በጥላነት ወይም በድንግዝግዝ የሚመለክቱ መሆኑን በማሳየት ነበር፡፡

ጥላዎች

በብዙ ገፅታዎች፣ ከታሪካዊ ዳራ ጋር የሚደረግ ትስስር ዓላማውን ለማሳካት በታሪኩና በተደራሲያኑ መካከል እንዲኖር የሚጠብቀው መመሳሰል ጥቂት ነው፤ ምሳሌዎች ወይም ተምሳሊቶች ግን አግባብነት ይኖራቸው ዘንድ ታሪካቸው ከተደራሲያኑ ጋር እንዲመሳሰል በጣም ይፈለጋል፡፡ ጥላነት ሊከሰት የሚችለው ግን በርካታ መመሳሰሎች ሲኖሩ ነው፣ ማለትም ያ የአብርሃም ዓለም ከዛሬው ከእነርሱ ከእስራኤላውያን ዓለም ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው ማለት ነው፡፡ በአብርሃም የሕይወት ታሪኮች ውስጥ እነዚህን የመሰሉ ዝርዝር ትስስሮች ደጋግመው ይታያሉ፣ ሙሴም ደግሞ ደጋግሞ፣ የአብርሃምን ዘመን ከእርሱ ዘመን ክስተቶች ጋር በቅርበት የሚመሳሰሉ መሆኑን ይገልፃል፡፡

ብዙዎቻችን “ታሪክ ራሱን ይደግማል” ስለሚባለወ ብሂል ሰምተናል፡፡ እርግጥ ነው፣ ሁለት ታሪካዊ ክስተቶች ፍፁም ሊመሳሰሉ እንደማይችሉ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ አንዳንድ ክስተቶች ግን ሁለተኛው የመጀመሪያው ድጋሚ እስኪመስል ድረስ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፍትም አንድ ቀደምት ታሪክ በተደራሲያኖቻቸው ሕይወት ውስጥ ከሚከናወነው ነገር ጋር ሲመሳሰል፣ ይህንን ትስስር በግልፅ ያስቀምጡታል፡፡ ይህም ሥነ-ጽሁፋዊ ቴክኒክ ጥላነት ተብሎ ይታወቃል፡፡

አንዱ የጥላነት ምሳሌም እውቅ በሆነውና አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ቃል ኪዳን በሚገልፀው በዘፍጥረት 15፡1-21 ውስጥ ይገኛል፡፡ አብርሃምን ለቃል ኪዳናዊ ትስስር በመጥራት አንድ ቀን ዘሩ የከነዓንን ምድር እንደሚወርስ እግዚአብሔር ለአብርሃም አረጋግጦለታል፡፡ አብርሃም ጥቂት እንስሳትን በማረድና ስጋቸውን በሁለት ከፍሎ በመቆራረጥ በመንገዱ ግራና ቀኝ አድርጎ አዘጋጀ፡፡ አባታችንም እንቅልፍ ሲወስደው፣ ቀደምት ተደራሲያኑ በነበሩበት ዘመን ከነበረው ልምምዳቸው ጋር በቀጥታ የሚመሳሰል ነገር በህልሙ አየ፡፡ በዘፍጥረት 15፡17 እንዲህ እናነብባለን፡፡

ፀሐይም በገባች ጊዜ ታላቅ ጨለማ ሆነ፤ የምድጃ ጢስና የእሳት ነበልባል በዚያ በተከፈለው መካከል አለፈ፡፡ (ዘፍጥረት 15፡17)

በዚህ ምንባብ ሰፊ አውድ ውስጥ የምድጃው ጢስና የእሳት ነበልባሉ የሚወክለው እግዚአብሔር ራሱ ለአብርሃም ዘር የተስፋይቱም ምድር እንደሚያወርሳቸው ለማረጋገጥ ለሁለት በተከፈለው የእንስሳት ስጋ መካከል ማለፉን ነበር፡፡

አሁን ምስሉን ያዙት፡፡ በዘፍጥረት 15፡17 ውስጥ እግዚአብሔር ለዘሩ የተስፋይቱን ምድር እንደሚያወርስ ለማረጋገጥ በአብርሃም ፊት እንደሚነድድ እሳት ሆኖ አለፈ፡፡ ምናልባት ለእኛ፣ ለዘመኑ አንባቢዎች እግዚአብሔር ለአብርሃም ለማረጋገጥ ሲል እንደ እሳትና ጢስ መገለጡ እንግዳ ሊመስለን ይችላል፡፡ ሆኖም ሙሴ ስለ አብርሃም ሕይወት የጻፈው በእርሱ መሪነት ወደ ተስፋይቱ ምድር ለሚጓዙ እስራኤላውያን መሆኑን ስናስታውስ እነዚህን ዝርዝሮች ማካተቱ አያስገርምም፡፡ በእስራኤላውያን ጉዞዎች ሁሉ ውስጥ፣ እግዚአብሔር በእስራኤል ፊት ከሚነድድ እሳትና ጢስ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ተገልጧል፡፡ ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚመራቸው የክብር ደመና ውስጥ፣ እግዚአብሔር እንደሚነድድ እሳትና ጢስ ተገልጦላቸዋል፡፡

ስለዚህ፣ በዚህ መንገድ እግዚአብሔር ለአብርሃም መገለጡ በሙሴ ዘመን ለነበሩ እስራኤላውያን የሚገለጥበትን መንገድ በጥላነት ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር በዚህ መንገድ በአብርሃም ፊት በማለፉ አብርሃም ምድሪቱን እንደሚወርስ ዋስትናን እንዳገኘ ሁሉ፣ ይህንን ታሪክ የሚደምጡ እስራኤላውያንም በራሳቸው ዘመን ምድሪቱን እንደሚወርሱ ዋስትናን ያገኛሉ ማለት ነው፡፡

ሌላውና፣ ምናልባትም የጎላ ተመሳሳይነት ያለው ጥላ የተከሰተው አብርሃም ከግብፅ ነፃ በወጣበት በዘፍጥት 12፡10-20 ምዕራፍ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ምንባብ የተፃፈው እስራኤል ስለ ግብጽ ካላቸው አመለካከት አንፃር ምሪት ለመስጠት ነው፡፡ በዚህ ረገድ፣ ሙሴ ጠቅላላውን ምዕራፍ ያዋቀረው በእርሱ አመራር ስር ካሉት እስራኤላውያን ጋር በቅርበት በሚጎዳኝ መንገድ ነው፡፡ በዘፍጥረት 12፡10-20 በከነዓን ምድር ከነበረው ረሃብ የተነሳ አብርሃም ወደ ግብፅ እንደወረደ፣ በግብፅም ፈርዖን ሚስቱን ሣራን በጉያው እስኪያስገባ ድረስ ቆየ፣ እግዚአብሔር ግን በፈርዖን ቤት ላይ መቅሰፍትን በመላክ አብርሃምን ታደገው፡፡ ከዚያም ፈርዖን አብርሃምን ከግብፅ በሰላም ሰደደው፣ አብርሃምም በታላቅ ብልፅግና ከግብፅ ወጣ፡፡

ስለ አብርሃም የተነገረው ታሪክ በግልፅነት የተቀረፀው ወደፊት የሚመጣው የእስራኤል ትውልድ ልምምድ ጥላ እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡ ልክ እንደ አብርሃም፣ እነርሱም በከነዓን ምድር ከነበረው ረሃብ የተነሳ ወደ ግብፅ ወርደው ነበር፣ በዚያም ፈርዖን አንቆ ይዟቸው ነበር፣ ነፃም የወጡት ከእግዚአብሔር ዘንድ በፈርዖን ቤት ላይ በተላከ ደዌ ምክንያት ነበረ፡፡ በዚያም ምክንያት ፈርዖን እስራኤል ነፃ እንዲለቀቅ ፈቀደ፣ እስራኤልም የግብፃውያንን ሃብት በዝብዞ ወጣ፡፡ ሙሴም የተደራሲያኑን ልምምድ በጥላነት ለማመልከት ሲል ይህንን አገባ በዓላማ አስገብቶታል፡፡ ይህንን የመሰለው ጉልህ ተመሳሳይ የሆነ ጥላ በአብርሃም ሕይወት የሚገለጠው በጥቂቱ ነው፣ ሆኖም ይህንን የመሳሰሉት ትስስሮች በአብርሃም ታሪክ ውስጥ እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡

የአብርሃምን ሕይወት ከዳር እስከዳር ስንመለከት በተለያዩ መንገዶችና በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱንም ትስስሮች እንመለከታለን፡፡ ሙሴ የአብርሃምን ሕይወት ዓለም ከአሁኑ ከቀደምት ተደራሲያኑ የእነርሱ ዓለም ጋር የሚያስተሳስረው፣ የአሁን ልምምዳቸውን ታረካዊ ዳራ በማሳየት፣ ሊከተሉና አሻፈረኝ ሊሉ የሚገባቸውን ተምሳሊት በመግለጥ እና የአብርሃም ሕይወት የእነርሱ በርካታ ልምምድ ጥላ እንዴት ሊሆን እንደቻለ በማመልከት ነው፡፡

ሙሴ በአብርሃምና በእርሱ እስራኤላዊ ተደራሲያን መካከል ያለውን ትስስር የገለጠባቸውን የትስስር ዓይነቶች ተመልክተናል፣ ስለዚህ የአብርሃም ሕይወት ዋና ዋና አንጓዎች እንዴት ከተቀዳሚ ተደራሲያኑ ሕይወት ጋር እንደተሳሰሩ ጠቅለል አድርጎ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡

ጥቅል ሃሳብ

የአብርሃም ሕይወት በአምስት ሚዛናዊ እርከኖች እንደተከፈለ ታስታውሳላችሁ፡፡ ሙሴ በእያንዳንዳቸው ክፍሎች ውስጥ ስለ አብርሃም የተነገሩትን ታሪኮች ከቀደምት ተደራሲያኑ ሁኔታ ጋር የሚያስተሳስርበትን መንገድ ያገኛል፡፡

በመጀመሪያ፣ሙሴ መየአብርሃምን ዳራና ቀደምት ልምምድ በእርሱ መሪነት ከግብፅ ከወጡት ህዝብ ዳራ እና ቀደምት ልምምድ ጋር ሊገናኝ በሚችል መንገድ ይተርከዋል፡፡ አብርሃምና እስራኤል ከአንድ ቤተሰብ ናቸው፡፡ አብርሃምና እስራኤል ሁለቱም የከነዓንን ምድር ለመውረስ በእግዚአብሔር ተጠርተዋል፡፡ ስለዚህ፣ ሙሴ ታሪካዊ ዳራዎችን ይሰጣቸዋል፣ አብርሃምን ተምሳሊት ያደርግላቸዋል ደግሞም የአብርሃም ሕይወት የቀደምት ተደራሲያኑ ልምምድ ጥላ ሊሆን የሚችልባቸውን መንገዶችም ያሳያቸዋል፡፡

ሁለተኛ፣ አብርሃም ከሌሎች ጋር የነበረውን ቀዳሚ ግንኙነት ከእርሱ ተደራሲያን ጋር ሊተሳሰር በሚችል መንገድ ሙሴ ያቀርብላቸዋል፡፡ አብርሃም ከግብፃውያን ጋር እንዴት እንደኖረ ይናገራል ምክንያቱም እስራኤላውያንም በዘመናቸው ከግብፃውያን ጋር ግንኙነት ነበራቸውና ነው፡፡ ስለ አብርሃምና ስለ ሎጥ ተናግሯል ምክንያቱም እስራኤላውያን ከሎጥ ዝርያዎች፣ ከሞዓባውያን እና ከዓሞናውያን ጋር ግንኙነት ነበራቸውና ነው፡፡ ስለ ምሥራቅ ነገሥታት እና ስለ ከነዓናዊው የሰዶም ንጉሥ ጽፏል ምክንያቱም እስራኤልም ከውጪ ነገሥታትና ከከነዓን ከተሞች ጋር ተመሳሳይ ልምምድ ነበራቸው፡፡

ሦስተኛ፣ ሙሴ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ስለ ነበረው ቃል ኪዳን ጽፏል ምክንያቱም እስራኤልም ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ቃል ኪዳናዊ ትስስር ውስጥ ገብቷልና፡፡ አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ቃል ኪዳን በብዙ መንገዶች እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የገባው ቃል ኪዳን ጥላ ነበር፡፡

አራተኛ፣ አብርሃም ከሌሎች ጋር ስለነበረው የኋላ ግንኙነትም ሙሴ ጽፏል፡፡ ስለ ሰዶምና ገሞራ ህዝብ፣ ስለ ሎጥ እና ስለ ፍልስጥኤማዊው አቤሜሌክ ጽፏል ምክንያቱም እስራኤልም በዘመኑ ከተመሳሳይ ሰዎች ማለትም ከከነዓን ከተሞች፣ ከሞዓባውያን፣ ከአሞናውያን እና ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተጋፍጦ ነበር፡፡

አምስተኛ፣ ከእስራኤላውያን አንባቢዎቹ ጋር ሊገናኝ በሚችል መንገድ ስለ አብርሃም ትውልድና ስለ ሞቱም ሙሴ ጽፎ ነበር፡፡ እስራኤላውያን ተደራሲያኑ የይስሐቅ ዝርያዎች ስለነበሩ የእርሱ ልዩ ልጅና ወራሽ በሆነው በይስሐቅ ላይ በማትኮር ጽፏል፡፡ በሣራ የቀብር ስፍራ ላይ አትኩሮት በመሳብ ጽፏል ምክንያቱም ያ መሬት እግዚአብሔር ለእስራኤል ተስፋ የሰጠው ምድር ነበር፡፡ የአብርሃም ወራሾች ስላለነበሩትም ልጆቹ፣ በተለይም ስለ እስማኤል ጽፏል ምክንያቱም እስራኤልም በዘመኑ ከእስማኤላውያን ጋር ግንኙነት ነበረው፡፡

ስለዚህ እንደተመለከትነው ሙሴ ስለ አብርሃም የጻፈው በታሪኮቹና በእርሱ እስራኤላዊ ተደራሲያን ልምምድ መካከል ወዳለው ትስስር ትኩረትን በመሳብ እንደ ነበር ተመልክተናል፡፡ ይህንንም ያደረገው ወደ ተስፋዪቱ ምድር እርሱን ተከትለው በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ የሆኑ መመሪያዎችን ለመስጠት ሲል ነበር፡፡

ሙሴ የአብርሃምን ሕይወት ከተቀዳሚ ተደራሲያኑ ከእስራኤላውያን ጋር ያስተሳሰረባቸውን ዐበይት መንገዶች ከተመለከትን፣ ስለ ተቀዳሚው ትርጉም ሌላ ወሳኝ ጥያቄ ልንጠይቅ ይገባናል፡፡ እነዚህ ትስስሮች ለመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን ምን አንድምታ ነበራቸው? ከአብርሃም የሕይወት ታሪክ ምን ይማራሉ?

እንድምታዎች

በዘፍጥረት መጽሐፍ የምናገኘውን የአብርሃምን ሕይወት የመሰለ ውስብስብ ታሪክ ለመጻፍ ሰዎች ጊዜ ሲወስዱ፣ ሁሉንም ዓይነት መነሳሳትና ግብ በልቡናቸው እንደሚይዙ አጠራጣሪ የመሆኑ ነገር አናሳ ነው፡፡ ታሪኮቻቸው በተደራሲያኑ ሕይወት ውስጥ በርካታ ተፅዕኖዎችን እንዲፈጥሩ ይሻሉ፡፡ ለነገሩ፣ ሙሴ ስለ አብርሃም ሕይወት ሲጽፍ፣ ጉጉቱ ፈርጀ ብዙ ነበር ስለዚህ ታሪኮቹን እንዲያው አድበስብሶ ወይም ቁንፅል አድርጎ ሊጽፋቸው አይችልም፡፡ እንደዚሁም፣ ተደራሲያኑ ከአብርሃም የሕይወት ታሪክ እንዲቀዱለት ተስፋ የሚያደርጋቸውን ዐበይት እንድምታዎች ጠቅለል አድርጎ ማቅረቡም አይቀሬ ነው፡፡

የአብርሃምን ሕይወት ቀደምት እንድምታዎች በሦስት ደረጃዎች እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ እነዚህ ታሪኮች በተቀዳሚዎቹ ተደራሲያን ላይ እንዲያመጡ የሚጠበቀውን መሠረታዊ ተፅዕኖ እንገልፃለን፡፡ ሁለተኛ፣ የእነዚህ ታሪኮች ተፅዕኖ በአብርሃም ሕይወት አራት ዐቢይ መሪ ሃሳቦች ውስጥ እንዴት እንደተብራራ እናያለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ሙሴ ስለ አብርሃም የጻፋቸውን ታሪኮች አምስት ደረጃዎች ቀደምት እንድምታ ጠቅለል አድርገን እናቀርባለን፡፡ እነዚህ ታሪኮች እንዲያመጡ የሚጠበቀውን መሠረታዊ ተፅዕኖ አስቀድመን እንመልከት፡፡

መሠረታዊ ተፅዕኖ

ጠቅለል ባለ አነጋገር፣ የአብርሃምን ታሪክ ዓላማ በዚህ መንገድ ማጠቃለሉ ይጠቅማል፡ ሙሴ ስለ አብርሃም የጻፈላቸው ግብፅን ለቅቀው ተስፋይቱን ምድር ለመውረስ መጓዝ የሚገባቸው ለምንና እንዴት እንደሆነ እስራኤልን ለማስተማር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በአብርሃም ውስጥ የሕይወታቸውን ዳራ በመመልከት፣ በአብርሃም ታሪኮች አማካይነት ሊከተሉ ወይንም አሻፈረኝ ሊሉ የሚገባቸውን ምሳሌዎች በማግኘት እና የእርሱ ሕይወት የእነርሱ ጥላ እንዴት ሊሆን እንደሚችል በመለየት ሙሴን የሚከተሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዓላማ ሊከተሉ የሚችሉበትን መንገድ ያያሉ፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት እና ኢየሱስ ራሱም የዘፍጥረት መጽሐፍ ከሙሴ ዘመን የተገኘ መሆኑን ቢያረጋግጥልንም እንኳን፣ አሁን በእጃችን በሚገኙበት መልክ እነዚህ ታሪኮች መቼ እንደተቀናበሩ በትክክል አናውቅም፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ ሙሴ የአብርሃምን ታሪክ ሲጽፍ ዋነኛ ዓላማው ለሁለቱም ትውልዶች በጣም ተመሳሳይ እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን፡፡ ስለ አብርሃም የጻፈላቸው ልባቸው ወደ ግብፅ መኮብለሉን አቁሞ የተስፋዪቱን ምድር በድል ወደ መውረሱ እንዲገሰግስ ለመመለስ ነበር፡፡

ይህ ለተቀዳሚ ተደራሲያኑ የሚያስተላልፈው ጥቅል እንድምታ እምብዛም ትኩረት አይሰጠውም፡፡ ሙሴ እርሱን የሚከተሉ እስራኤላውያን ወደ ግብፅ መመለስን አሻፈረኝ በማለት የተስፋዪቱን ምድር በድል ለመውረስ እንዲገሰግሱ ለማበረታታት ጽፏል እናም ይህ ጥቅል እንድምታ የአብርሃምን ሕይወት በእኛም ዘመን ማዛመድ እንድንችል ምሪትን ይሰጠናል፡፡ እንደ ክርስቲያን እኛም ተጓዦች ነን፣ ጉዟችንም እስራኤላውያን በሙሴ ዘመን ጀምረውት የነበረውን ወደ ፍጻሜ የሚያመጣ ነው፡፡ ወደ አዲስ ሰማይና ምድር እየተጓዝን ነው፡፡ ስለዚህ የአብርሃምን ታሪኮች በሕይወታችን በአግባቡ ለማዛመድ፣ ቀደምት ተደራሲያኑ ወደ ከነዓን በሚያደርጉት ጉዞ ታሪኮቹ መንገድ ያሳዩዋቸው የነበረበትን ሁኔታ በጥንቃቄ ማስተዋል ይገባናል፡፡

ይህንን ዐቢይ ሃሳብ ይበልጥ ለማብራራት፣ አስቀድመን በዚህ የዘፍጥረት ክፍል ውስጥ ተመልክተናቸው ወደነበሩት አራት ዐበይት መሪ ሃሳቦች በመመለስ የሙሴን ዓላማ በጥልቀት ማየት ይገባናል፡፡

ዐበይት መሪ ሃሳቦች

ዘፍጥረት 12፡1-3 ከዚህ የአባታችን የሕይወት ታሪክ ክፍል ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቢያንስ አራት መሪ ሃሳቦች እንደሚያቀርብልን ማልከታችን ታስታውሳላችሁ፡፡ እነዚህ አራት መሪ ሃሳቦች፣ ሙሴ ታሪኮቹን ሲያዋቅር እንዲያስገኙለት የሚፈልገውን ተፅዕኖ ማዕከላዊ ሃሳብ ይገልፃሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ ለአብርሃም በተሰጠው መለኮታዊ ጸጋ ላይ ያተኩራል፤ ሁለተኛ፣ በአብርሃም ታማኝነት ላይ አፅንዖት ይሰጣል፤ ሦስተኛ፣ ለአብርሃም የተሰጡ በረከቶችን ያመለክታል፤ አራተኛ ደግሞ፣ በአብርሃም አማካይነት በሚሰጡ በረከቶች ላይ ያተኩራል፡፡ ሙሴ ስለ አብርሃም ሕይወት ሲጽፍ የነበረውን ዓላማ በእነዚህ አራት ጭብጦች መመልከቱ ይጠቅማል፡፡

መለኮታዊ ጸጋ

በመጀመሪያ ደረጃ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም ምህረትን ስላሳየባቸው መንገዶች ሙሴ ይጽፋል፡፡ በጥቅሉ ደግሞ፣ አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው የመጀመሪያ ግንኙነት ወቅት እና በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በየዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው እግዚአብሔር ለአብርሃም ብዙ ጸጋን ያሳየው መሆኑን ተመልክተናል፡፡ የመለኮታዊው ጸጋ ጭብጥ በሙሴ ዘመን ለነበሩት እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ብዙ ምህረትን እንዳደረገላቸው ለማሳሰብ ታስቦ የተቀመጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶ ወደ ሲና ሲመጣቸው የመጀመሪያ ጸጋውን አሳይቷቸዋል፡፡ ከዚያም የተስፋዪቱን ምድር ለሚወርሱበት የድል ቀን እያዘጋጃቸው ሳለም ቀን በቀን፣ ምህረቱን ያሳያቸዋል፡፡

በዘፀአት 19፡4 እግዚአብሔር በሲና ከተናገራቸው የታወቁ ንግግሮች ንግግሮች አንዱ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ እንዲህ ይናገራል፡-

“በግብፅ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፡፡” (ዘፀአት 19፡4)

የሚያሳዝነው ግን፣ ሙሴ ይመራቸው የነበሩ እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ምን ያህል ምህረትን እንደተቀበሉ መርሳታቸው ነው፡፡ ገና ከመጀመሪያው እግዚአብሔር እና ሙሴ በምቾት ከተቀመጡበት ከግብፅ በማውጣት እንዳታለሏቸው በማሰብ አጉረምርመዋል፡፡ በምድረ በዳ ስለ ምግብና ውሃ አጉረምርመዋል፡፡ የተስፋዪቱን ምድር በድል ወደ መውረስ እንዲገቡ ሲጠራቸው ፍዳን እንደጠራባቸው አስበዋል፡፡ ስለዚህ፣ ሙሴ እግዚአብሔር ለአብርሃም ምህረትን ባሳየበት መንገድ ላይ ተደጋጋሚ አፅንዖት በመስጠት እግዚአብሔር ለተቀዳሚ ተደራሲያኑ በረከቱን የሰጠባቸውን መንገዶች እና ደግሞ ደጋግሞም ምህረቱን ለእነርሱ ያሳየበትን መንገድ ያሳስባቸዋል፡፡

የአብርሃም ታማኝነት

በሁለተኛ ደረጃ፣ አብርሃም የእርሱን ትዕዛዛት የመፈፀም ሃላፊነት እንዳለበት እግዚአብሔር ያመለከተባቸውን በርካታ መንገዶች በማመልከት ሙሴ በአብርሃም ታማኝነት ላይ አፅንዖት መስጠቱንም ተመልክተናል፡፡ አባታችን ለትዕዛዛቱ ታማኝ እንዲሆን እግዚአብሔር እንደሚጠብቅበት ሙሴ ደጋግሞ አፅንዖት ሰጥቶታል ምክንያቱም እርሱን ይከተሉ ለነበሩት እስራኤላውያንም ይኸው ትኩረት አግባብነት ነበረው፡፡ ይኸው የታማኝነት ግዴታ ጉዳይ በሙሴ ዘመን ለነበሩ እስራኤላውያንም ተነግሯል፡፡ በዘፀአት 19፡4-5 በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር ለእስራኤልም መናገሩን የቀጠለበትን መንገድ አድምጡ፡-

“በግብፅ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፡፡ አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአህዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስት ትሆናላችሁ፤” (ዘፀአት 19፡4-5)

የተወደደ ርስት የመሆኑ በረከት የእስራኤልን ታማኝነት የሚጠይቅ መሆኑን በዚህ ስፍራ እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሔር ለህዝቡ ብዙ ምህረትን ያሳየ ቢሆንም፣ በየትውልዱ የሚገኘው የእያንዳንዱ ሰው አቋም የሚወሰነው ለእግዚአብሔር ትእዛዛት በሚሰጠው ምላሽ ላይ ነው፡፡

እንደተመለከትነው፣ ለአብርሃም የተሰጠው ዋና ሃላፊነት ወደ ከነዓን ምድር መጓዝ ነው፡፡ ሙሴም ይህንን ሃላፊነት ጫን ብሎ የገለፀበት ምክንያት እስራኤላውያንም ወደ ከነዓን የሚያደርጉትን ጉዞ በጽናት እንዲገፉበት ለማድረግ ነው፡፡ ደግሞም፣ ሙሴ ስለ አብርሃም ሌሎች ሃላፊነት ሲጽፍም፣ በእርሱ ዘመን የነበሩት በርካታ የታማኝነት ሃላፊነቶች ቀደምት ተደራሲያኑም ለእግዚአብሔር ትዕዛዛት ታማኝ መሆን የሚጠበቅባቸው የመሆኑን እውነታ በግልፅነት ይናገራሉ፡፡

ለአብርሃም የተሰጡ ሃላፊነቶች

በሦስተኛ ደረጃ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጣቸውን የበረከት ተስፋዎች መሪ ሃሳብ ወሳኝነትም ተመልክተናል፡፡ ሙሴ ስለ አብርሃም በጻፋቸው ታሪኮች ውስጥ፣ አብርሃም ታላቅ ህዝብ ስለመሆኑ፣ ስለ ብልጽግናው እና ለእርሱና ለዘሩ ስለሚሰጠው ታላቅ ስም ትኩረት አድርጓል፡፡ ደግሞም በበርካታ ጊዜያት አብርሃም በሕይወት ዘመኑ የእነዚህን በረከቶች ቅምሻ ያጣጣመ መሆኑንም ተመልክተናል፡፡ በአብርሃም ታሪኮች ውስጥ እነዚህ በረከቶች በሚመጣው ትውልድ ወደ ፍፃሜ እንደሚመጡም በብዙ ትኩረት ተገልጧል፡፡ ሙሴ በአብርሃም በረከቶች ላይ በዚህ መንገድ ትኩረት ያደረገበት ምክንያት እነዚያ በረከቶች እርሱ ለሚመራቸውና የአብርሃም ዝርያ ለሆኑት ለእስራኤላውያንም ስለሆኑም ነበር፡፡ የእስራኤልም ህዝብ ታላላቅ በረከቶችን እንደሚቀበሉ ተስፋ ነበራቸው፡፡ ታላቅ ህዝብ እንደሚሆኑ፣ የተትረፈረፈ ብልጽግና እንደሚያገኙ እና በተስፋዪቱ ምድር ውስጥ ሲገቡ ገናና ስም እንደሚኖራቸው ተስፋ ነበራቸው፡፡

በእርግጥም፣ እንደ አብርሃም ሁሉ፣ እስራኤልም የዘፍጥረት መጽሐፍ በተጻፈበት ወቅት የእነዚህን በረከቶች ቅምሻ አጣጥማ ነበር፡፡ በሕይወት ዘመናቸውም ከተስፋዎቹ መካከል የጥቂቶቹን ፍፃሜ ማየት ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ከገቡ በኋላ ገና ወደ ፍፃሜ የሚመጡ በርካታ በረከቶችም ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤል ስለሚሰጣት የወደፊት በረከቶች በዘፀአት 19፡6 ውስጥ እንዲህ ተናግሯል፡

እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ህዝብ ትሆናላችሁ፤ (ዘፀአት 19፡6)

እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን የበረከት ተስፋ ሙሴ የጻፈው በእርሱ ዘመን የበሩትን የእስራኤላውያንን ተስፋ ለማለምለም ነበር፡፡ ለአባታቸው የተነገረውን የእግዚአብሔር የበረከት ተስፋ ሲያነብቡ፣ እግዚአብሔር ለእነርሱም ምን ያህል ትልቅ ተስፋ እንዳስቀመጠላቸው በግልፅ ይመለከታሉ፡፡

በአብርሃም በኩል የተሰጡ በረከቶች

በአራተኛ ደረጃ፣ የአብርሃም ታሪኮች የእግዚአብሔር በረከቶች በአባታችን አማካይነት ለዓለም ሁሉ የሚመጡ መሆናቸውን ገልጠዋል፡፡ እንደምታስታውሱት፣ በአብርሃም በኩል የሚገኘው በረከት ቀለል ባለ መንገድ የሚመጣ አይደለም፡፡ ከዘፍጥረት 12፡3 እንደምንረዳው እግዚአብሔር ለአብርሃም ስኬትን የሚሰጠው ወዳጆቹን በመባረክና ጠላቶቹን በመርገም ሂደት ነው፡፡ በተለያዩ ምዕራፎችም፣ አብርሃም በሕይወት ዘመኑ ከተለያየ ህዝብ ተወካዮች ጋር ባደረገው ግንኙነት የእዚህን ሂደት ቅምሻ እንዲያጣፊም እግዚአብሔር እንዴት እንዳደረገ ሙሴ አመልክቷል፡፡ ሙሴ ስለ አብርሃም በጻፋቸው ብዙ ወቅቶችም፣ በርካታ ፍፃሜዎች ገና ወደፊት እንደሚመጡም አመልክቷል፡፡

ሙሴ በእነዚህ ጭጦች ላይ ያተኮረበት ምክንያት በዘመኑ እርሱን ለሚከተሉ እስራኤላውያን በጣም አግባብነት ስለነበራቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ወዳጆቻቸውን በመባረክና ጠላቶቻቸውን በመርገም ለሌሎች በረከት የሚሆኑበትን ሂደት አረጋግጦላቸዋል፡፡ እነርሱም በዘመናቸው ከተለያዩ ህዝቦች ጋር ባደረጉት ግንኙነት የእነዚህን በረከቶቸ ቅምሻ አጣጥመዋል፡፡ ብዙ ጊዜም እግዚአብሔር ወዳጆቻቸውን ሲባርክ ጠላቶቻቸውንም ሲረግም አይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ሙሴ የእስራኤላውያንን ዐይን ወደፊት በሚመጣው ፍፃሜ ላይ በማሳረፍ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር ሁሉ እንደሚሰፉ በአትኮሮት ያሳስባል፡፡ እንደተመለከትነው፣ በዘፀአት 19፡6 እግዚአብሔር ለእስራኤል እንዲህ ብሏል፡

እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ህዝብ ትሆናላችሁ፤ (ዘፀአት 19፡6)

ይህ የካህናት መንግሥት የመሆን ራእይ እስራኤል እግዚአብሔርን የሚያገለግል የተቀደሰ ህዝብ የመሆንን ዕድል በማግኘት የምትባረክ መሆኗን የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን፣ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ዓላማ በመላው ዓለም የሚያስፈፅሙ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ ሙሴ እስራኤልን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለመምራት ሲያነሳሳ፣ ስለ አብርሃም የጻፋቸው ታሪኮች የተቀረፁት መንግሥቱን እና በረከቶቹን ወደ መላው ዓለም ለማድረስ እግዚአብሔር እንዴት እስራኤልን እንደሚጠቀም የሚጠቁመውን ራእይ በውስጣቸው ለማተም ነው፡፡

የአብርሃም ሕይወት አራት ዐበይት መሪ ሃሳቦች ለመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን የሚኖራቸውን አንድምታ ከተመለከትን፣ የአባታችን ሕይወት በዘፍጥረት መጽሐፍ በተቀመጠበት መዋቅር ውስጥ የሚገኙትን ዋና ደረጃዎች በመመልከት የአብርሃም ታሪኮች በተቀዳሚ ተደራሲያኑ ላይ የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ በአጭሩ እናጠቃልለው፡፡

አምስቱ ደረጃዎች

የአብርሃም ታሪኮች በአምስት ዋና ደረጃዎች እንደተከፈለ ታስታውሳላችሁ፡፡ በመጀመሪያ፣ በ11፡10-12፡9 የአብሃምን ዳራና ቀደምት ልምምድ፤ ሁለተኛ፣ በ12፡10 -14፡24 አብርሃም ከሌሎች ህቦች ተወካዮች ጋር ያደረጋቸውን ቀደምት ግንኙነቶች፤ ሦስተኛ፣ በ15፡1-17፡27 እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን፤ አራተኛ፣ በ18፡1-21፡34 ከሌሎች ህዝቦች ተወካዮች ጋር ያደረጋቸው የኋላ ግንኙነቶች፤ እና አምስተኛ፣ የአብርሃም ትውልድና ሞት በ22፡1-25፡18 ናቸው፡፡

እነዚህ ዋና ደረጃዎች በተለያዩ ትናንሽ ክፍልፋዮች ወይም ምዕራፎች ይከፈላሉ፡፡ እኛም እነዚህ ምእራፎች ለቀደምት ተደራሲያኑ ያሏቸውን ጥቂት ዐበይት እንድምታዎችና ይዘታቸውን ጠቅለል አድርገን እናቀርባለን፡፡

ዳራና ቀደምት ልምምዶች

የአብርሃም ሕይወት የመጀመሪያ ደረጃ፣ ዳራውና ቀደምት ልምምዶቹ፣ እግዚአብሔር አብርሃምን ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገልግሎት የጠራበትን ጊዜ እና የቤተሰቡን የተለያየ ገፅታ ይዘግቡልናል፡፡ በጥቅል አነጋገር፣ ሙሴ እነዚህን የመጀመሪያ ደረጃዎች የነደፋቸው ቀደምት ተደራሲያኑ እስራኤላውያን ስለ ቤተሰባዊ ዳራቸው እና ከእግዚአብሔር ስለተቀበሉት ጥሪ ከአብርሃም ሕይወት ገፅታዎች እንዴት ሊማሩ እንደሚችሉ ለማሳየት ነው፡፡

ይህ የመጀመሪያ ደረጃ በሦስት ምዕራፎች ወይም ክፍልፋዮች ይከፈላል፡፡ የአብርሃም ሕይወት የሚጀምረው በ11፡10-26 ውስጥ መለኮታዊ ሞገስ ያገኘውን የአብርሃምን የትውልድ ሃረግ በመዘርዘር ነው፡፡ እነዚህ ጥቅሶች አብርሃም በሴም ቤተሰብ ውስጥ ጉልህ ገፀ-ባህርይ እንደሆነ፣ እንደ እግዚአብሔር የተመረጠ ልዩ ህዝብም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘ ቤተሰብ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ይህ ዝርያ በምላሹም የሙሴ ቀደምት ተደራሲያን የሆኑት እስራኤላውያን እንደ አብርሃም ወገንነታቸው ተመሳሳይ ሞገስ እንዳላቸው ያሳስባቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር የተመረጠ ህዝብ ናቸው፡፡

ሁለተኛው የአብርሃም ዳራ ምዕራፍ እና ቀደምት ልምምድ በ11፡27-32 የተመዘገበው የትውልድ ሀረግ፡፡ ይህ ምንባብ በጨረፍታም ቢሆን ወደ ከነዓን ሊጓዝ ሞክሮ ስላልተሳካለት ስለ ጣዖት አምላኪው ታራ ይገልፅልናል፡፡ የሙሴ ቀደምት ተደራሲያን በእነርሱ ሕይወትና በአብርሃም ሁኔታዎች መካከል ያሉ መመሳሰሎችን በቀላሉ ያስተውላሉ፡፡ ወላጆቻቸውም በጣዖት አምልኮ ተሳትፈዋል ወደ ከነዓንም ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ፣ አብርሃም የአባቱን ስህተት ከመድገም ሊጠበቅ እንዳስፈለገው ሁሉ፣ ሙሴን ይከተሉ የነበሩ እስራኤላውያን ማለትም በዘፀአት ዘመን ጣዖትን በማምለክ ከነዓን ሳይገቡ የቀሩትን የአባቶቻቸውንና የእናቶቻቸውን ውድቀት ከመድገም ሊጠበቁ ይገባቸዋል፡፡

የአብርሃም ዳራና ቀደምት ልምምዶች ቀጥለው የሚሸጋገሩት በ12፡1-9 ወደሚገኘው የአብርሃም ወደ ከነዓን የመሰደድ ታሪክ ነው፡፡ አብርሃም ወደ ከነዓን እንዲጓዝ እግዚአብሔር ጠራው፣ አብርሃምም ብዙ ችግሮች ቢኖሩም የእግዚአብሔርን ጥሪ ታዘዘ፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ የሙሴ ቀደምት ተደራሲያን የሆኑትን እስራኤላውያንንም ወደ ከነዓን ምድር እንዲጓዙ እግዚአብሔር ጠርቷቸዋል፡፡ እነርሱም በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ሊታዘዙ ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህ የአብርሃም ወደ ከነዓን የመሄድ ታሪክ በሙሴ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን አብርሃም ወደ ከነዓን የተጓዘበትን ዱካ ተከትለው ወደ ከነዓን ሊጓዙ የሚገባቸው መሆኑን የሚያመለክት ቀደምት እንድምታ አለው፡፡

ሙሴ በእነዚህ ሦስት አንጓዎች፣ ቀደምት ተደራሲያኑ እግዚአብሔርን ለማገልገል በሚያደርጉት ጥረት ለሚገጥማቸው ተግዳሮት ጉልህ ምሪት ያገኙበት ዘንድ የአብርሃምን ሕይወት አስተዋውቋል፡፡

ከሌሎች ጋር የነበረው ቀደምት ግንኙነት

በአብርሃም ሕይወት ዙሪያ ያጠነጠነው የዘፍጥረት ዘገባ ሁለተኛ ዐቢይ እርከን አባታችን ከሌሎች ጋር በነበረው ቀደምት ግንኙነት ላይ ያተኩራል፡፡ እነዚህ ምዕራፎች አባታችን ከተለያዩ ወገኖች ጋር በልዩ ልዩ መንገዶች ያደረገውን ግንኙነት የሚገልፁ ሲሆን ይህም ቀደምት አንባቢዎቹ እስራኤላውያን ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ምሪትን የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ፣ በዘፍጥረት 12፡10-20 ሙሴ የአብርሃምን ከግብፅ ነፃ መውጣት ገልጿል፡፡ እንደምታስታውሱት አባታችን በረሃብ ምክንያት ወደ ግብፅ ቢሰደድም፣ እግዚአብሔር ግን በፈርዖን ቤት ውስጥ በሽታን በመስደድ አባታችንን ከግብፃውያን ባርነት ነፃ አውጥቶታል፡፡ ከእግዚአብሔር ታላቅ ማዳን የተነሳ አብርሃም በብዙ ብልጥግና ከግብፅ ወጣ ዳግመኛም አልተመለሰም፡፡ ግብፅ መኖሪያው እንዳልሆነች አብርሃም በግልፅ ተረድቷል፡፡

የሙሴ ቀደምት ተደራሲያን የሆኑት እስራኤላውያን ልምምዶቻቸው የአብርሃምን ታሪክ በብዙ ገፅታዎቹ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ያስተውላሉ፡፡ በረሃብ ምክንያት ወደ ግብፅ ወርደዋል፣ እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ከላከው መቅሰፍትም የተነሳ ከግብፅ በብዙ ብልጥግና ከባርነት ነፃ ወጥተዋል፡፡ የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን በጉዟቸው ችግር ሲገጥማቸው፣ ብዙዎቹ በግብፅ የነበራቸውን ሕይወት መናፈቅና ወደዚያም ለመመለስ መፈለግ ጀመሩ፡፡ ይህ ምዕራፍ ለቀደምት ተደራሲያኑ ግብፅ መኖሪያቸው እንዳልሆነች በግልፅ ያመለክታቸዋል፡፡ እግዚአብሔር እንዴት በቸርነቱ ነጻ እንዳወጣቸው፣ ግብፅንም እንዲለቅቁ እንደረዳቸውና ግብፃውያንንም ከኋላቸው እንደጣለላቸው ያስታውሳሉ፡፡

አብርሃም ከሌሎች ጋር የነበረው ቀደምት ግንኙነት ሁለተኛ አንጓ በ13፡1-18 የሚገኘውና ከሎጥ ጋር የነበረው ግጭት የተፃፈበት ነው፡፡ ይህ ክፍል የአብርሃም ሰዎችና የሎጥ ሰዎች ለመንጋዎቻቸው አገልግሎት በሚጠቀሙበት የተፈጥሮ ሀብት ምክንያት የተፈጠረ ግጭት የተመዘገበበት ዕውቅ ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ፣ አብርሃም ለሎጥ በጎነትን አድርጎለታል፣ በመረጠውም ምድር በሰላም እንዲኖር ፈቅዶለታል፡፡ የዘፍጥረት ተደራሲያንም ይህ ታሪክ ለእነርሱ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ብዙም አይቸግራቸውም፡፡ እንደ ዘዳግም 2 አገላለጥ፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሲጓዙ የሎጥን ዝርያዎች በበጎነት እንዲመለከቷቸውና በአባቶቻቸው ምድር በሰላም ለመኖር እንዲፈቅዱላቸው ሙሴ አዝዟቸዋል፡፡ በውጤቱም፣ አብርሃም ለሎጥ ደረገው በጎነት እስራኤላውያንም በእነርሱ ዘመን የነበሩ ሞዓባውያንን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው አሳይቷቸዋል፡፡

አብርሃም ከሌሎች ጋር የነበረው ቀደምት ግንኙነት ሦስተኛ ምዕራፍ በ14፡1-24 የሚገኘው አብርሃም ሎጥን የታደገበት ታሪክ ነው፡፡ ይህ ውስብስብ ታሪክ አብርሃም ከረጅም ርቀት የመጡ ኃይለኛ እና ጨካኝ የሆኑ ነገሥታትን ድል በማድረግ ሎጥን እንዴት እንደታደገው የሚገልፅ ሲሆን ለሎጥ ምን ያህል ታላቅ ቸርነትን እንዳደረገለት ያሳያል፡፡ ይህም ታሪክ ሙሴን ይከተሉ ለነበሩ እስራኤላውያንም በግልፅ የሚያስተላልፈው ቀጣይ መልእክት አለው፡፡ እስራኤላውያንም የሎጥ ዝርያ በሆኑት በሞዓባውያንና በአሞናውያም ምድር ሲያልፉም፣ የእስራኤል ሠራዊት የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን እና የባሳንን ንጉሥ አግን ድል አድርጓል፣ ሁለቱም ሞዓባውያንንና አሞናውያንን ያስጨንቁ የነበሩ ናቸው፡፡ እስራኤላውያን በዚህ መንገድ ሞዓባውያንንና አሞናውያንን በመታደግ፣ አብርሃም በፊታቸው ያስቀመጠላቸውን ተምሳሊት ተከትለዋል፡፡

ይህ የአብርሃም የሕይወት ምዕራፍ፣ እራኤላውያን በዘመናቸው ሊከተሉ የሚገባቸውን ተምሳሊት ለማመልከት አብርሃምን እንደ ምሳሌ ያቀርብላቸዋል፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን

አሁን ወደ አብርሃም ሕይወት ሦስተኛ እርከን ላይ ደርሰናል፣ ያም እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ሲሆን በ15፡1-17፡27 ውስጥ ይገኛል፡፡ በጥቅል አነጋገር፣ ይህ እርከን እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖራትን የቃል ኪዳናዊ ግንኙነት ባህርይ በሚገልጥ መንገድ እግዚአብሔር ከአባታችን ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ላይ ያተኩራል፡፡ እነዚህ ምዕራፎች በሦስት ዐቢይ አንጓዎች ይከፈላሉ፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ በተለይ እግዚአብሔር ለአብርሃም በገባው የቃል ኪዳን ተስፋ ላይ የሚያተኩር ይሆንና በ15፡1-21 ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ምዕራፍ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን የገባበትን ጊዜ የሚዘግብ እውቅ ምዕራፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም ዘርንና ምድርን እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለታል፡፡ በተለይም፣ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ዝርያዎች እንደሚሰጠው፣ በባዕድ ምድርም ለተወሰነ ጊዜ በጭቆና ካሳለፉ በኋላ፣ የአብርሃም ወገኖች ወደ ተስፋዪቱ ምድር ተመልሰው ይመጣሉ፡፡ ይህ ምንባብ የተነደፈው እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ከእስራኤል ጋር ተመሳሳይ ቃል ኪዳን እንዳደረገ ለማሳሰብ ነው፡፡ ከዚህም በበለጠ፣ እነርሱ ራሳቸው ለአብርሃም የተሰጡትን ተስፋዎች ፍፃሜ ያጣጣሙ መሆኑን ያሳያቸዋል፡፡ እስራኤላውያን የአብርሃም የተስፋ ዝርያዎች ናቸው፣ እግዚአብሔርም ለአባታቸው ተስፋ ሰጥቶት ወደ ነበረው ምድርም ተመልሰዋል፡፡ እነዚህን እውነታዎች መጠራጠር እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውንና በሙሴም መልሶ የተረጋገጠውን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳናዊ ተስፋዎች መጠራጠር ነው፡፡

እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ሁለተኛ ምዕራፍ በ6፡1-16 የሚገኘው አባታችን ወደ አጋር በመግባት የወደቀው ውድቀት ነው፡፡ ይህ አሳዛኝ ታሪክ አብርሃምና ሣራ እንዴት የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ቸል በማለት ከግብፃዊ ባርያዋ፣ ከአጋር ልጅን ለማግኘት እንደሞከሩ ያሳስባል፡፡ አብርሃምና ሳራ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ተስፋ መጠበቅ አቃታቸው፣ እግዚአብሔር ግን እነርሱ ያመጡትን አማራጭ እቅድ እስማኤልን እንደ አብርሃም እውነተኛ ዘር ባለመቀበል ውድቅ አደረገባቸው፡፡ የሙሴ ቀደምት ተደራሲያንም እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ከሰጣቸው ተስፋ ጀርባቸውን መላልሰው በማዞር የግብፅን ምቾት ይመኛሉ፡፡ የአብርሃም እቅድ ውድቅ እንደተደረገ ሁሉ፣ እነርሱም ለእግዚአብሔር እቅድ የሚያቀርቡት አማራጭ ውድቅ እንደሚደረግባት ይህ የአብርሃም ሕይወት ያስተምራቸዋል፡፡

እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ሦስተኛ ምዕራፍ ከብርሃም በሚጠበቀው የቃል ኪዳን መመዘኛ ላይ የሚያተኩረውና በ17፡1-27 የሚገኘው ነው፡፡ በዚህ ምንባብ፣ አባታችን የእግዚአብሔርን እቅድ ከመከተል ፊቱን ሲያዞር እግዚአብሔር ተጋጥሞታል፡፡ የቃል ኪዳን ታማኝነት ወሳኝ መሆኑን ለማመልከትም በአብርሃምና በወንዶች ልጆቹ ላይ ተፈፃሚ የሚሆን የግርዛት ስርዓት እንዲኖር ደንግጓል፡፡ በዚህ ምልክት፣ የእርሱ የቃል ኪዳን ግንኙነት ታማኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን፣ ያም ታማኝነት ታላቅ በረከትን እንደሚያስገኝ እግዚአብሔር አብርሃምን አሳስቦታል፡፡ ሙሴም ይህንን የአብርሃም ቃል ኪዳን መልሶ ያነሳው እስራኤላውያን ውድቀትን ድል በማድረግ በታማኝት እንዲዘልቁ ለመሞገትና ለቃል ኪዳን ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት ለማመልከት ነው፡፡ እስራኤላውያን ለቃል ኪዳን አመላካቸው ታማኝ ሲሆኑ ብቻ የእግዚአብሔርን ታላቅ በረከት ተስፋ የማድረግ መብት ይኖራቸዋል፡፡

ስለዚህ፣ የአብርሃም ሕይወት ማዕከል የሆነው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ቃል ኪዳን፣ እግዚአብሔር ለእስራኤል ወደ ሰጠው አስደናቂ ተስፋዎች ፀጋ ትኩረትን ይስባል፡፡ በተጨማሪም ተደራሲያኑ የቃል ኪዳን አምላካቸውን በታማኝነት የማገልገል ግዴታ ያለባቸው መሆኑንም በብርቱ ያሳስባቸዋል፡፡

ከሌሎች ጋር የነበረው የኋላ ግንኙነት

አሁን ደግሞ፣ ወደ አብርሃም ሕይወት አራተኛ እርከን ደርሰናል፡፡ ያም በ18፡1-21፡34 የሚገኘው በስተኋላ ከሌሎች ጋር ያደረገው ግንኙነት ነው፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች አብርሃም በሙሴ ዘመን ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ትስስር ካላቸው የተለያዩ ሰዎች ጋር መገናኘቱ ተዘግቧል፡፡ አብርሃም የሰዶምና ገሞራ ዝርያ ከሆኑት ከነዓናውያን፣ ከሎጥ፣ ከአቤሜሌክ እና ከእስማኤል ጋር ተገናኝቷል፡፡ በጥቅል አነጋገር፣ አብርሃም ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያደረገው ግንኙነት እስራኤል ከከነዓናውያን፣ ከሞዓባውያን፣ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጥኤማውያን እና ከእስማኤላውያን ጋር በራሷ ዘመን እንዴት ግንኙነት ማድረግ እንዳለባት ያስተምራታል፡፡

ከአባታችን ሕይወት የዚህኛው አንጓ የመጀመሪያ ታሪክ በ18፡1-19፡38 የሚገኘው የሰዶምና የጎሞራ ታሪክ ነው፡፡ ይህ እውቅ ትረካ በረከሱት የከነዓናውያን ከተሞች ላይ ስለወረደው መለኮታዊ ፍርድ ይናገራል፡፡ በከተሞቹ ውስጥ ስላለው ጻድቅ አብርሃም ግድ መሰኘቱን፣ የከተሞቹን መውደም እና ሎጥ ግን መዳኑን ይነግረናል፡፡ እነዚህ ክስተቶች ስለ ሙሴ ቀደምት ተደራሲያን ሁኔታ በቀጥታ ይናገራሉ፡፡ በእነርሱ ዘመን በሚኖሩ ሰዎች ላይ ምን እንደተከናወነ እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡ ማለትም እግዚአብሔር በከነዓናውያን ላይ የሚያስተላልፈው ፍርድ፣ በከነዓናውያን መካከል ስለሚኖር ፃድቅ ሊቆረቆሩ እንደሚገባ (ለምሳሌ ወደ ኢያሪኮ ሲመጡ ስለ ረዳቻቸው ረዓብ)፣ በከነዓናውያን ከተሞች ላይ ስለማይቀረው ውድመት፣ የሎጥ ዝርያ ከሆኑት ከሞዓባውያን እና ከአሞናውያን ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ ግንኙነት ናቸው፡፡

አብርሃም ከሌሎቸ ጋር የነበረው የኋላ ዘመን ግንኙነት ሁለተኛ ክፍል በ20፡1-18 የሚገኘው ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አብርሃም በድጋሚ በምድሪቱ ነዋሪ ለነበረውና አቤሜሌክ በሚል መጠሪያ ለሚታወቀው ፍልስጥኤማዊ ማልዷል፡፡ ሣራ ሚስቱ መሆኗን ባለማወቅ፣ ከአብርሃም በመውሰድ የአብርሃምን የወደፈት ተስፋ አቤሜሌክ ተፈታትኗል፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር በአቤሜሌክ ላይ ቁጣን ሲያመጣ፣ አቤሜሌክም ከጥፋቱ ንስሓ በመግባት ከክፋት የራቀ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ንስሓ በመግባቱም፣ አብርሃም ስለ አቤሜሌክ ማልዶለታል፣ እናም አብርሃምና አቤሜሌክ ዘላቂ ሰላምንና ባልንጀራነትን አጣጥመዋል፡፡

ይህ ታሪክ እስራኤላውያን በራሳቸው ዘመን ስለሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን ሊኖራቸው ስለሚገባው ዝንባሌ ይናገራቸዋል፡፡ በተለያዩ መንገዶች፣ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ተፈታትነዋል፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር ፍርድ ፍልስጥኤማውያንን ወደ ንስሓ ከመራቸው፣ እስራኤላውያን ሊማልዱላቸውና በሰላም ሊኖሩ ይገባቸዋል፡፡

ሦስተኛው የዚህ ትረካ ክፍል፣ በ21፡1-21 የሚገኘው በይስሐቅ እና በእስማኤል መካከል ባለው አስቸጋሪ ግንኙነት ላይ የሚያተኩረው ነው፡፡ ይስሐቅና እስማኤል ሁለቱም የአብርሃም ልጆች ናቸው፡፡ በመካከላቸው ውጥረት ሲነግሥ ግን፣ እስማኤልን ከቤተሰቡ እንዲያስወጣ እግዚአብሔር አብርሃምን ያዝዘዋል፡፡ እግዚአብሔር እስማኤልን ባርኮታል፣ ሆኖም የአብርሃም ሕጋዊ ወራሹ ግን ይስሐቅ ብቻ ነው፡፡ ሙሴ ስለነዚህ ክስተቶች ለተቀዳሚ ተደራሲያኑ ሲያሳውቅ፣ በዘመናቸው ከእስማኤላውያን ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን የግንኙነት ባህርይ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል፡፡ በእስራኤልና በእስማኤላውያን መካከል ውጥረት ሲነግሥ፣ በመካከላቸው ልዩነት እንዲኖር እግዚአብሔር የደነገገ መሆኑን እስራኤላውያን ሊያስታውሱ ይገባል፡፡ በብዙ መንገዶቸ እግዚአብሔር እስማኤላውያንን ቢባርክም፣ ትክክለኞቹ የአብርሃም ወራሾች እስራኤላውያን ናቸው፡፡

አብርሃም ከሌሎች ጋር የነበረው የኋላ ዘመን ግንኙነት አራተኛ ምዕራፍ በ21፡22-34 የሚገኘው አብርሃም ከአቤሜሌክ ጋር የነበረው የስምምነት ውል ታሪክ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ፍልስጥኤማዊው አቤሜሌክ እግዚአብሔር ለአብርሃም ለሰጠው ሞገስ እንዴት እውቅና እንደሰጠ እና አብርሃምም ከአቤሜሌክና ከዘሩ ጋር እንዴት በሰላም ለመኖር እንደተስማማ ይዘግባል፡፡ ታሪኩ በመቀጠልም የአብርሃም በጎች ውሃ ስለማግኘት መብታቸው እንዴት ክርክር እንደተነሳና አብርሃምና አቤሜሌክም በቤርሳቤህ ወደ ህጋዊ ስምምነት እንደደረሱና እርስ በርስ በመከባበር ለመኖር እንደወሰኑ ይናገራል፡፡

ፍልስጥኤማውያን በእነርሱ ዘመን ምን ያህል ፈተና ሊሆኑባቸው እንደሚችሉ አቤሜሌክና አዛዡ ሙሴንና እስራኤላውያንን ያሳስባሉ፡፡ በዚህ ስፍራ፣ ፍልስጥኤማውያን እግዚአብሔር ለእስራኤል ለሰጠው በረከት እውቅና ከሰጡ፣ እስራኤልም የአብርሃምን ምሳሌነት በመከተል ከእነርሱ ጋር በሰላም ለመኖር መስማማት እንዳላበት ሙሴ ለተከታዮቹ አስተምሯቸል፡፡ ቤርሳቤህ የተሰኘውም ጉድጓድ በሙሴም ዘመን ነበር፣ እርሱም በዚያ ስፍራ የተፈፀመውን ውል እና ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰላምንና መከባበርን እንዴት መሻት እንዳለበት ለእስራኤል ያሳስባል፡፡

ስለዚህ፣ አብርሃም ከሌሎች ጋር ያደረገው የኋላ ዘመን ግንኙነት ታሪክ ሙሴና እስራኤል በዘመናቸው ከተገናኙዋቸው ሰዎች ባሕርይ ጋር የሚጎዳኝ መሆኑን አይተናል፡፡ አብርሃም የወሰዳቸውን እርምጃዎች በመመልከት እስራኤላውያን ለዘመናቸው የሚጠቅም ብዙ ትምህርት ያገኛሉ፡፡

ትውልድና ሞት

ሙሴ ስለ አብርሃም ሕይወት የዘገበው ዘገባ የመጨረሻ እርከን ላይ ደርሰናል፣ እርሱም በ22፡1-25፡18 የሚገኘው ትውልዱና ሞቱ ነው፡፡ እነዚህ ምዕራፎች በአብርሃም ቅርስ፣ ማለትም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን የቃል ኪዳን ግንኙነት ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፉ ላይ ያተኩራሉ፡፡ በጥቅል አነጋገር፣ እነዚህን ታሪኮች ለመጀመሪያ ጊዜ ከሙሴ የሚቀበሉ እስራኤላውያን እንደ አብርሃም ዘርነታቸው ሊኖራቸው ስለሚገባው አቋም እና ለእነርሱም ትውልድ ስላለው ተስፋ ብዙ ሊማሩ ይገባል፡፡

በዚህኛው የአብርሃም ሕይወት ምዕራፍ የመጀመሪያ ክፍል እውቁና አብርሃም የተፈተነበት ታሪክ በ22፡1-24 የሚገኘው ነው፡፡ ይህ ፈተና የተነደፈው አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ከሚወድድበት መውደድ ይልቅ እግዚአብሔርን ይወድድ እንደሆነ ለመፈተሽ ነው፡፡ እግዚአብሔር አስቸጋሪ ፈተና አዘጋጀ፣ አብርሃምም ልጁን እንዲሰዋ ጠራው፡፡ አብርሃምም ታዘዘ፣ በመታዘዙም ምክንያት የልጁ የይስሐቅ ነገው ብሩኅ እንደሚሆን እግዚአብሔር ለአብርሃም ዋስትናን ሰጠው፡፡

ይህ ታሪክ ሙሴን ለሚከተሉ እስራኤላውያን በርካታ እንድምታዎች ቢኖሩትም፣ የዚህ ምንባብ ወሳኝ ገፅታ ግን እስራኤል ለእግዚአብሔር ያላትን ታማኝነት ጥልቀት ለመለካት እስራኤልን እንደሚፈትን ማሳሰብ ነው፡፡ እግዚአብሔር በሙሴ ዘመን ለነበሩት እስራኤላውያን በርካታ ፈተና አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ አብርሃም ለፈተናው ታዛዥ መሆኑ እስራኤላውያንም ፈተናዎቻቸው የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆኑም ፈተናዎቹን በመታዘዝ መልስ ሊሰጡ እንደሚገባ ያስታውሳቸዋል፡፡ የአብርሃም ዘር በመሆኑ ለይስሐቅ የተሰጠው የወደፊት ብሩህ ተስፋ እስራኤላውያንም ፈተናዎቹን ካለፉ እነርሱም ስለሚያገኙት ብሩህ ተስፋ ያስታውሳቸዋል፡፡

በአብርሃም ሕይወት የመጨረሻ እርከን ውስጥ ሁለተኛው ምዕራፍ በ23፡1-20 የሚገኘው አባታችን የገዛው የመቃብር ስፍራ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ሚስቱ ሣራ ስትሞት አብርሃም በሄብሮን ስለ ገዛው የቤተሰብ የመቃብር ስፍራ ይገልፃል፡፡ ይህ ትረካ አባታችን ያንን ንብረት እንደ ስጦታ አለመቀበሉን ይልቁኑ ዋጋ ከፍሎ መግዛቱን በአፅንዖት ያመለክታል፡፡ ይህ የንብረት አያያዝ ሥርዓት ቤተሰቡ የከነዓንን ምድር ህጋዊ ርስታቸው የማድረጋቸውን ባለመብትነት እንድናይ ያስችለናል፡፡

ሙሴን የሚከተሉ እስራኤላውያንም በግዢ የተያዘው የመቃብር ስፍራ በሕይወታቸው ያለው አንድምታና አስፈላጊነት ምን ያህል እንደሆነ እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡ ቦታው የዘራቸው የመቃብር ስፍራ ነው፡፡ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ የተቀበሩት በዚያ ነው፡፡ ምድሪቱን ድል አድርገው ከመያዛቸው በፊትም ይህ ስፍራ በምድሪቱ ውስጥ ያለ ሕጋዊ ርስታቸው እንደነበር ይረዳሉ፡፡ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ አብዛኛውን ዘመናቸውን በሔብሮንና በአካባቢዋ አሳልፈዋል፡፡ እስራኤላውያን ሔብሮንን የዘራቸው የመቃብር ስፍራ አድርገው ከመያዛቸው የተነሳ የአባታቸውን የያዕቆብን አፅም እንኳን ወደ ሔብሮን ይዘው ተጉዘዋል፡፡ አብርሃም የመቃብር ስፍራን የመግዛቱ ታሪክ የእርሱ ዘር ህጋዊ ርስቱ ከከነዓን ሌላ የትኛውም ምድር ሊሆን እንደማይችል የሚያመለክት ነው፡፡

የአብርሃም ትውልድና ሞት ሦስተኛው ልብን የሚነካ ምዕራፍ ስለ አብርሃም ምራት፣ የልጁ የይስሐቅ ሚስት ስለሆነችው ስለ ርብቃ የሚናገረው በ24፡1-67 የሚገኘው ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ፣ ይስሐቅ ከከነዓናውያን ጋር በመዳቀል እንዳይረክስ ለመከላከል፣ የከነዓንን ሴቶች እንዳያገባ አብርሃም የወሰደው እርምጃ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን ይስሐቅ በተስፋይቱ ምድር በከነዓን የመቀመጡም ነገር የተረጋገጠ እንዲሆን አብርሃም ባሪያውን በመላክ ለልጁ ሚስትን እንዲያመጣለት እርምጃ ወስዷል፡፡ አብርሃም በዚህ መንገድ ለይስሐቅ ሚስትን በመፈለግ፣ የይስሐቅና የዘሩ የወደፊት በረከት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተረጋገጠ እንዲሆን አድርጓል፡፡

ሙሴን የሚከተሉ እስራኤላውያን ከዚህ የይስሐቅ ታሪክ፣ ከአብርሃም ጋር ያላቸውን የዘር ትስስር እንዲረዱ፣ ምንም እንኳን በከነዓን ምድር ቢቀመጥም ከከነዓናውያን ርኩሰት ራሱን ከመጠበቁ ትምህርትን ሊቀስሙ ይገባል፡፡ የይስሐቅ የወደፊት ብሩኅ የበረከት ተስፋ የእነርሱም እንዲሆን በተስፋይቱ ምድር ውስጥ ከሚኖሩ ከነዓናውያን ርኩሰት ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባቸዋል፡፡

የአብርሃም ሕይወት የመጨረሻ ምዕራፍ የአባታችን ሞትና ትውልድ የተመዘገበበት በ25፡1-18 የሚገኘው ታሪክ ነው፡፡ ይህ አጫጭር ትረካዎችን ያዘለ ክፍል አብርሃም ከሳራ ውጪ ስለወለዳቸው ልጆቹ የሚተርክ ነው፡፡ ከዚያም ስለ አባታችን ሞትና ይስሐቅ እንደ ህጋዊ ወራሽነቱ የአብርሃምን የፍፃሜ በረከት ስለ መቀበሉ ይናገራል፡፡ በመጨረሻም፣ የእስማኤልን ዝርያዎች በንፅፅር በሚዘረዝረው ክፍል ይደመደማል፡፡

ይህ የአብርሃም ታሪክ መደምደሚያ ለቀደምት ተደራሲያኑ ብዙ እንድምታዎች አሉት፡፡ የተቀሩትን የአብርሃም ልጆች ከእስራኤላውያን ለመለየት ይዘረዝራቸዋል፡፡ ሙሴን ይከተሉ የነበሩ እስራኤላውያን የአብርሃምተስፋዎች ትክክለኛ ወራሽ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አብርሃም ለይስሐቅ የፍፃሜ በረከት ያሰምርበታል፡፡ የእስማኤል ዝርያዎች ከአብርሃም በረከት ለመካፈል የሚያነሱትን የትኛውንም የይገባኛል ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ይጠቅሳል፡፡ የአብርሃምን ሕይወት ዘገባ በዚህ መንገድ በመደምደም፣ ሙሴ በእርሱ መሪነት ወደ ተስፋዪቱ ምድር የተጓዙት እስራኤላውያን የአብርሃም እውነተኛ ወራሽ የመሆናቸውን መለያ፣ መብትና ሃላፊነት ይገልፃል፡፡

ስለዚህ ሙሴ የአብርሃምን የሕይወት ታሪኮች የጻፈው ይመራቸው የነበሩ እስራኤላውያን ለምንና እንዴት ግብፅን መልቀቅ እንዳለባቸውና የተስፋይቱን ምድር በድል ለመውረስ መገስገስ እንዳለባቸው ለማስተማር ነው፡፡ ይህንንም ግብ ለማሳካት፣ ለአባታችን የተሰጠው ፀጋ ተካፋዮች እንዴት እንደሆኑ፣ አባታችን ታማኝ እንደነበረው ሁሉ እነርሱም እንዴት ታማኝ የመሆን ሃላፊነት እንዳለባቸው፣ አብርሃምም እንደተቀበለው የእግዚአብሔርን በረከት እንዴት ሊቀበሉ እንደሚችሉ፣ አንድ ቀንም ለምድር ህዝቦች ሁሉ እንዴት በረከት ሊሆኑ እንደሚችሉ ሙሴ በአባታችን የህይወት ታሪክ ምዕራፎች ውስጥ የተለያዩ አፅንዖቶችን በመስጠት አመልክቷቸዋል፡፡ ስለ አብርሃም ሕይወት ሙሴ ያቀረበው ዘገባ ወደ ተስፋይቱ ምድር እርሱን ተከትለው ለተጓዙ እስራኤላውያን ሊለካ የማይችል እንድምታዎች አሉት፡፡

ማጠቃለያ

በዚህ ትምህርት በዘፍጥረት መጽሐፍ የተዘረዘረውን የአብርሃም ሕይወት ዘገባ ቀደምት ትርጉም ተመልክተናል፡፡ ተቀዳሚ ትርጉሙንም ለመመርመር በሁለት ዋና አቅጣጫዎች ተጉዘናል፡፡ በአንድ ወገን በእነዚህ ታሪኮችና በጻፈላቸው እስራኤላውያን ልምምዶች መካከል ሙሴ ያመለከተውን ትስስር መርምረናል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ፣ ተቀዳሚ ተደራሲያኑ ግብፅን ወደ ኋላቸው በመተው የተስፋይቱን ምድር ከነዓንን ለመውረስ በሚገሰግሱበት ወቅት እነዚህ ታሪኮች ተፅዕኖ እንዲያሳድሩባቸው አድርጎ ሙሴ እንዳቀናበራቸው ዐይተናል፡፡

በአብርሃምና በቀደምት ተደራሲያኑ በእስራኤላውያን መካከል ሙሴ ሊያመለክት የሚፈልገውን ትስስር፣ በተደራሲያኑም ላይ ታሪኮቹ ሊያመጡ የሚፈልገውን ተፅዕኖ ይበልጥ በተረዳን ቁጥር፣ የአብርሃም ሕይወት እያንዳንዱ ምዕራፍ እንዴት እስራኤልን የመምራት ዓላማ እንዳነገበ እንደርስበታለን፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ታሪኮች በዛሬውም በእኛ ሕይወት እንዴት ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚቸሉ ይበልጥ መገንዘብ እንችላለን፡፡

Continue reading the full transcript