ዘመናዊ ትግበራዎችን ከዘፍጥረት ምዕራፎች ከአብራሃም ጋር በተገናኘ መልኩ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ለመሳል ያተኩራል።
From the transcript
ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ጎብኙ፡፡
የዘመናችን ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚቸገሩበት አንድ ነገር ቢኖር፡- ከሺህ ዓመታት በፊት የተፃፉ ታሪኮች ዛሬ የእኛን ሕይወት የመምራት አቅም አላቸው ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ መሆኑ ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው የአብርሃም ሕይወት ዘገባ ያለ ጥርጥር እውነትነት አለው፡፡ አብርሃም ራሱ የኖረው ከአራት ሺህ ዓመታት በፊት ሲሆን ስለ እርሱ የተጻፉ ታሪኮችም ወደ ከ3600 ዓመታት በፊት ተጽፈዋል፡፡ እንደ ክርስቶስ ተከታዮች ግን፣ እነዚህ ታሪኮች የቅዱሳት መጻሕፍት አካል እንደሆኑ እና ለዘመናችን ሰዎችም ጠቀሜታ እንዳላቸው እናምናለን፡፡
ይህን እያመንንም እንኳን፡ ስለ አብርሃም የተጻፉ እነዚህ ታሪኮች ከዛሬው ከእኛ ሕይወት ጋር እንዴት ይዛመዳሉ? የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም አለ፡፡ እኛንና አብርሃምን ያራራቀንን የ4000 ዓመታት ርቀት እንዴት እናገናኘዋለን፡፡
ይህንን ተከታታይ ትምህርት፣ አባታችን አብርሃም የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፣ ምክንያም የአብርሃምን ሕይወት በዘፍጥረት መጽሐፍ እንደተዘገበው እንመረምራለንና ነው፡፡ ይህ ትምህርት በዚህ ተከታታይ ትምህርት ከሦስቱ የመግቢ ትምህርቶች ሦስተኛው ሲሆን፣ “አባታችን አብርሃም፡ ዘመነኛው ተዛምዶ” የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ በዚህ ትምህርት፣ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ስለ አብርሃም ከሚናገሩት ምዕራፎች ውስጥ ከእኛ ዘመን ጋር የሚዛመዱትን በትክክለኛ መንገድ ለማውጣት በሚያስችል ትኩረት የአብርሃምን ሕይወት ወፍ በረር ዳሰሳችንን እናጠቃልላለን፡፡ ስለ አብርሃም የተጻፉትን ታሪኮች ከእኛ ሕይወት ጋር እንዴት እናዛምዳለን? ዛሬስ በእኛ ሕይወት ምን ዓይነት ተፅዕኖ ያሳድራሉ?
የአብርሃም ሕይወት በእኛ ዓለም እንዴት እንደሚዛመድ ለመረዳት፣ በሁለት መሠረታዊ አቅጣጫዎች ማለትም፡ በመጀመሪያ፣ በኢየሱስና በአብርሃም መካከል ያሉ ትስስሮችን፣ ሁለተኛ፣ በቀደምቷ ተደራሲ በእስራኤልና በዘመኗ ተደራሲ በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ትስስር እንቃኛለን፡፡
የአብርሃም ሕይወት ያለውን ዘመነኛ ተዛምዶ ከመመልከታችን አስቀድሞ ቀደም ባሉት ትምህርቶች የተመለከትናቸውን ለመከለስ ጥቂት ጊዜ እንውሰድ፡፡ የአብርሃም ታሪክ በአምስት ሚዛናዊ ደረጃዎች መከፈሉን ዐይተናል፡፡ በመጀመሪያ፣ የአብርሃም ሕይወት የሚጀምረው በአብርሃም ዳራና በቀደምት ልምምዱ መሆኑን በ11፡10-12፡9 ውስጥ፡፡ ሁለተኛ፣ አብርሃም ከሌሎች ህዝቦች ተወካዮች ጋር የነበረውን ቀደምት ልምምዶች በ12፡10-14፡24 ውስጥ፡፡ ሦስተኛ እና ማዕከላዊው አንጓ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ የሚያተኩረው በ15፡1-17፡27 ውስጥ፡፡ አራተኛ፣ አብርሃም ከሌሎች ህዝቦች ተወካዮች ጋር የነበረው የኋላ ዘመን ግንኙነት በ18፡1-21፡34 ውስጥ፡፡ አምስተኛ በአብርሃም ትውልድና በሞቱ ላይ የሚያተኩረው አንጓ በ22፡1-25፡18 ውስጥ የሚገኙት ይሆናሉ፡፡ እነዚህ አምስት ክፍሎች የአባታችንን ሕይወት በሚዛናዊ አቀራረብ ያቀርቡልናል፡፡ እግዚብሔር ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ የሚያተኩረው ሦስተኛው ክፍል፣ የአብርሃም ሕይወት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሁለተኛውና አራተኛው ክፍሎች ሁለቱም አብርሃም ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ በማትኮር በንፅፅር ይቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያውና አምስተኛው ደግሞ የአብርሃምን ቤተሰባዊ ግንድ ከመጀመሪያው እስከ ወደፈቱ በማመልከት የአብርሃምን ሕይወት ማሰሪያ በተጓዳኝ ያቀርቡልናል፡፡ ከአብርሃም ሕይወት መሠረታዊ ውቅር ባሻገር፣ ሙሴ የአብርሃምን ሕይወት ሲጽፍ ዓላማ እንዳለው ቀደም ባሉት ትምህርቶች ዐይተናል፡፡ ሙሴ የአብርሃምን የሕይወት ታሪኮች የጻፈው ይመራቸው የነበሩ እስራኤላውያን ለምንና እንዴት ግብፅን መልቀቅ እንዳለባቸውና የተስፋይቱን ምድር በድል ለመውረስ መገስገስ እንዳለባቸው ለማስተማር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የሕይወታቸውን ታሪካዊ ዳራ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ በመመልከት፣ ከአብርሃም ታሪኮች ውስጥ ሊከተሏቸውና አሻፈረኝ ሊሏቸው የሚገቧቸውን ተምሳሊቶች በመፈለግ እና የአብርሃም ሕይወት የእነርሱ ሕይወት ጥላ እንዴት ሊሆን እንደሚችል በመለየት፣ ሙሴን የሚከተሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዓላማ መከተል የሚችሉባቸውን መንገዶች ይመለከታሉ፡፡ ይህንን የቀደሙ ትምህርቶች ክለሳ በልቡናችን ይዘን፣ ወደ አብርሃም የሕይወት ታሪክ ዘመነኛ ተዛምዶ እንሸጋገራለን፡፡
አብርሃምና ኢየሱስ
አስቀድመን በአብርሃምና በኢየሱስ መካከል ያሉ ትስስሮችን እንመልከት፡፡ አለመታደል ሆኖ፣ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የአብርሃምን ሕይወት ይብዛም ይነስም በቀጥታ ከዘመኑ ሕይወት ጋር ያዛምዱታል፡፡ የዐብርሃምን ታሪኮች በቀጥታ ለሕይወታችን እንደሚናገሩ ቀላል ግብረገባዊ ታሪኮች አድርገን እንወስዳቸዋለን፡፡ ሆኖም ደግሞ እንደ ክርስቲያኖች፣ ከአብርሃም ጋር ያለን ግንኙነት መካከለኛ ገብቶበታል፤ ማለትም የአብርሃም ሕይወት ለእኛ አግባብነት አለው ምክንያቱም ከአብርሃም ልዩ ዘር ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆነናልና ነው፡፡ ክርስቶስ በእኛና በአብርሃም መካከል ቆሟል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ስለ አብርሃም የተፃፉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች ዘወትር ከክርስቶስና እርሱ ከሠራቸው ሥራዎች አንፃር ልንመለከታቸው ይገባናል፡፡
በአባታችንና በክርስቶስ መካከል ያሉ ትስስሮችን ለመገንዘብ ሁለት ጉዳዮችን እንዳስሳለን፡፡ በአንድ ወገን፣ ክርስቶስ የአብርሃም ዘር መሆኑን አዲስ ኪዳን እንዴት እንደሚያስተምር እንመረምራለን፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ፣ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ያስተዋልናቸው አራት ዐበይት መሪ ሃሳቦች እንደ አብርሃም ዘርነቱ ከክርስቶስ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ እናያለን፡፡ በመጀመሪያ ኢየሱስ የአብርሃም ዘር የመሆኑን ፅንሰ-ሃሳብ እንመልከት፡፡
የአብርሃም ዘር
አብርሃም በታሪክ ዘመናት ሁሉ የሚገኙ ክርስቲያኖች ማለትም ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች አባት የመሆኑ ግንዛቤ አለ፡፡ እኛ ሁላችን የእርሱ ቤተሰብ አካላት ልጆቹና ወገኖቹ ነን፡፡ ይህን ደረጃ ያገኘነው የአብርሃም ልዩ ዘር ከሆነው ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን መሆኑን አዲስ ኪዳን በጣም ግልፅ እንደሚያደርግልን እንመለከታለን፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለዚህ አመለካከት የሚስተምሩንን በውል ለመጨበጥ ሁለት ጉዳዮችን በስሱ እንዳስሳለን፡፡ በመጀመሪያ፣ “ዘር” የተሰኘውን ፅንሰ-ሃሳብ የነጠላ መደብነት እናያለን፡፡ ሁለተኛ፣ ክርስቶስ የአብርሃም ልዩ ዘር የመሆኑን ፅንሰ-ሃሳብ እንዳስሳለን፡፡
ነጠላ መደብ
መጽሐፍ ቅዱስ የአብርሃምን ዘር በነጠላ መደብ ያስቀመጠባቸውን መንገዶች እናሰላስል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወሳኝ የሆነ ትኩረት ያደረገው ክፍል ገላትያ 3፡16 ነው፡፡ በዚያም እንዲህ ይነበባል፡
“ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ፡፡ ስለ ብዙዎች እንደሚነገር ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን ለዘርህም ይላል፣ እርሱም ክርስቶስ፡፡ ”(ገላትያ 3፡16)
በዚህ ምንባብ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ በዘፍጥረት የሰጠውን ተስፋ ጳውሎስ ያጣቅሳል፡፡ ግን ጳውሎስ በተለይ “ዘር” በሚለው አገላለፅ ላይ የሰጠውን ሃሳብ ልብ በሉ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሮቹ፣ ማለትም ለብዙ ሰዎች ተስፋን አልሰጠም፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ማለትም ለአንዱ ለክርስቶስ ሰጥቷል ነው የሚለው፡፡
ጳውሎስ በዚህ መንገድ ማለትም zera ትርጓሜውም ዘር የሚለውን የእብራይስጥ ቃል በመጥቀስ ይከራከራል፡፡ በግሪኩ sperma ለተሰኘውና በጳውሎስ ዘመን የብሉይ ኪዳን ትርጉም ለሚገኝለት ቃልም ነገሩ እውነትነት አለው፡፡ ጳውሎስ እንደጠቀሰው፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋው ለአብርሃምና ለዘሮችህ (በብዙ ቁጥር) ነው አላለውም፣ ይልቁኑ ለዘርህ (በነጠላ ቁጥር) ነው ያለው፡፡
ለይ ላዩን ሲታይ፣ የጳውሎስ አተያይ ቀጥተኛ መስሎ ይታያል፡፡ የአብርሃም ውርስ ለአንድ ዘር ብቻ መጥቷል፣ ወይም ለአንድ ተወላጁ ብቻ ምክንያቱም ቃሉ በነጠላ ቁጥር ነው፡፡ ጳውሎስ “ዘር” በሚለው ቃል ላይ ያነሳው መከራከሪያ በተርጓሚዎች ዘንድ በርካታ ችግሮችን አስከትሏል፡፡ ችግሩ ግን በዚህ መንገድ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ዘር ወይም zera የሚለው ቃል በቅርፁ የነጠላ መደብ መሆኑ እውነት ነው፣ ሆኖም በብሉይ ኪዳን በበርካታ ጊዜያት፣ የአብርሃምን የሕይወት ታሪኮች ጨምሮ፣ ዘር የሚለው በቅርፁ የነጠላ መደብ የሆነው ቃል ሊወሰድ የሚገባው የወል ነጠላ ትርጓሜ እንዳለው ቃል ነው፣ ያም ማለት በነጠላ መደብ ቡድንን የሚወክል ቃል ማለት ነው፡፡ የዕብራይስጡ ቃል zera ወይም ዘር የሚለው ቃል በእንግሊዝኛው “offspring” ዝርያ ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይህ ቃል በቅርፁ የነጠላ መደብ ቢሆንም፣ አንድን ዘር ወይም ትውልድ ሊወክል ወይም በወል መጠሪያ ብዙ ዝርያዎችን ሊያመለክት ይችላል፡፡
ለምሳሌ፣ ዘር የሚለው ቃል ወይም zera በዘፍጥረት 15፡13 የተቀመጠው ቃል ትርጓሜው የወል ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል፡-
“ዘርህ በባዕድ አገር ስደተኛ እንደሚሆን በእርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል…” (ዘፍጥረት 15፡13)
በዚህ ስፍራ፣ ዘር የሚለው ቃል የነጠላ ቁጥር አመልካች የሆነው zera የተሰኘው የዕብራይስጥ ቃል ፍቺ ነው፣ በግልፅ እንደምናየው ግን ትርጉሙ የወል ነው፡፡ ይህ ጥቅስ ስለ ዘር የሚናገረው የራሳቸው ባልሆነ ምድር በሚል የወል ትርጓሜ ሲሆን፣ በባርነት ተረግጠው የሚገዙ መሆናቸውንም የዕብራይስጡ ግስ በወል ቁጥር ይገልፀዋል፡፡
በእርግጥም፣ ዘር የሚለው የነጠላ መደብ አመልካች ቃል በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ጊዜ ከአንድ ሰው በላይ ወክሎ እንደሚጠቅስ ጳውሎስ ያውቃል፡፡ እንዲያውም፣ በገላትያ 3፡29 ውስጥ ጳውሎስ ራሱ በብዙ ቁጥር አመልካችነት ተጠቅሞበታል፡፡ እንዲህ ይነበባል፡-
“እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ፡፡” (ገላትያ 3፡29)
ይህ ጥቅስ በግሪክኛው፣ እናንተ የሚለው ቃል este (evste) የሚለው የወል ግስ ትርጓሜ ነው፡፡ ደግሞም የአብርሃም “ዘር” የሚለውም “ወራሽ” kleronomoi (Klhrono,moi) ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ሲሆን እርሱም የብዙ ቁጥር ነው፡፡
በዚህ መሠረት አንድ ጥያቄ ልንጠይቅ ይገባናል፡፡ ጳውሎስ “ዘር” የሚለው ቃል የነጠላ መደብ ትርጉም ከአንድ ሰው በላይ የሚወክል መሆኑን ካወቀ፣ ለምን በነጠላ መደብነቱ ላይ ትኩረት አደረገ? የሚመስለው፣ በዘፍጥረት 22፡16-18፣ ከአብርሃም የሕይወት ታሪክ ውስጥ አንድ ምንባብ በልቡናው ይዞ አንደነበር ነው፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ፣ “ዘር” የሚለው ቃል ትርጉም እርግጠኝነት የነጠላ መደብ ነው፡፡ የዚህን ቃል የቁም ትርጉም እስኪ አድምጡ፡-
“እንዲህም አለው፡- እግዚአብሔር በራሴ ማልሁ ይላል ይህን ነገር አድርገሃልና አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፣ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል የምድር አሕዛብ በዘርህ ይባረካሉ፣ ቃሌን ሰምተሃልና፡፡” (ዘፍ 22፡16-18)
የሚያሳዝነው ግን፣ በርካታ የዘመናችን ትርጉሞች በዚህ ምንባብ ውስጥ ዘር የሚለው ቃል የወል ነጠላ አመልካች እንደሆነ አድርገው ይተረጉሙታል፡፡ ይህ ጥቅስ ግን ስለ ይስሐቅ መስዋዕትነት የሚናገረው ታሪክ ክፍል መሆኑን ልናስታውስ ይገባናል፡፡ በዚህ ስፍራ ዘር የሚለው ቃል የሚያመለክተው የአብርሃምን ዘር በጥቅሉ ሳይሆን፣ የአብርሃምን ልጅ ይስሐቅን ነው፡፡ “ይወርሳል” የሚለው ግስ በዕብራይስጡ ነጠላ ነው፣ “የጠላቶችን” የሚለው “ተውላጠ ስምም” ነጠላ መሆኑን ልብ በሉ፡፡
ወደ ኋላ ላይ በሚመጡት ትምህርቶች እንደምናየው፣ ዘፍጥረት ምዕራፍ 22 እና ተከታትለው የሚመጡት ምዕራፎች፣ ይስሐቅን፣ የሳራን ልጅ፣ ከሌሎቹ ልጆቹ፣ ማለትም ከአጋር ልጅና ከኬጡራ ልጆች በመለየት ሰፋ ያለ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ይስሐቅ የአብርሃም ብቸኛው ወራሽ አድርጎ እግዚአብሔር የመረጠው፣ የተስፋው ዘር ነው፡፡ ስለዚህ፣ ይስሐቅ ከመወለዱ አስቀድሞ፣ ዘፍጥረት አዘውትሮ ስለ አብርሃም ዘር የሚናገረው በወል፣ ትርጉሙም ዘሮችህ በሚል በብዙ ቁጥር ነው፣ እዚህ ግን ቃሉ በይስሐቅ ማለትም የአብርሃምን ተስፋዎች ብቸኛ ወራሽ በሆነው ላይ ያተኩራል፡፡
በዚህ መሠረት ጳውሎስ የአብርሃምን ዘር በነጠላ የመጥቀሱን መሠረታዊ ነጥብ እንረዳለን፡፡በዘፍጥረት ምዕራፍ 22 ውስጥ እግዚአብሔር ለአብርሃም እና በቀጥታ ለዘሮቹ ተስፋን እንዳልሰጠ ጳውሎስ ይጠቅሳል፡፡ በዘፍጥረት 22፡16-18 የተጠቀሰው “ዘር” የሚለው ቃል የነጠላ መደብነት የሚያመለክተው ተስፋዎቹ የአብርሃም ልዩ ልጅና ወራሽ ለሆነው ለይስሐቅ የተላለፉ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
ክርስቶስ እንደ ዘር
የአብርሃምን ዘር የነጠላ መደብ አመልካችነት በልቡናችን ይዘን፣ አሁን ደግሞ ክርስቶስ የአብርሃም ዘር ወደ መሆኑ አስተምህሮ እንሸጋገራለን፡፡ ሐዋርያው በገላትያ 3፡16 የተናገረውን አድምጡ፡-
ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ፡፡ ስለ ብዙዎች እንደሚነገር ለዘሮቹም አይልም፣ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን ለዘርህም ይላል፣ እርሱም ክርስቶስ፡፡ (ገላትያ 3፡16)
በዚህ ምንባብ ጳውሎስ ትኩረት የሚያደርገው የአብረሃም ዘር ነጠላ በመሆኑ እውነታ ላይ ብቻ ሳይሆን ያ አንዱ ዘር ክርስቶስ መሆኑን ነው፡፡ እንግዲህ፣ የዘፍጥረትን ቀደምት ትርጉም አስመልክቶ እንደተመለከትነው፣ ሙሴ የጻፈለት የአብርሃም ዘር ይስሐቅ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፣ ያም ከሣራ የተወለደው የተስፋው ልጅ ነው፡፡ እንግዲያው ጳውሎስ የአብርሃም አንድ ዘር ኢየሱስ ስለ መሆኑ የተናገረውን እንዴት ልንረዳው ይገባናል?
እንዲህ አስቡ፡፡ የአብርሃም ውርስ የቤተሰብ ውርስ ማለትም ለዘሮቹ ሁሉ የሆነ ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ታሪክ ውስጥ ግን፣ የአብርሃምን ውርስ ለሌሎች ሁሉ የሚያስተላልፍባቸውን ልዩ የአብርሃም ወራሾች እግዚአብሔር ይመርጣል፡፡ በይስሐቅ ረገድ፣ እርሱ ከአብርሃም ሌሎች ልጆች የተለየ ልዩ ዘር ነው፡፡ ይስሐቅም ሁለት ልጆች ሲወልድ፣ ያዕቆብና ኤሳው፣ እግዚአብሔር ያዕቆብን የይስሐቅ ልዩ ዘር እንዲሆን መርጦ ኤሳውንና ዘሩን ግን አልመረጠም፡፡ ከያዕቆብም ዐሥራሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባቶች ወጡ፡፡ ከእስራኤል ነገዶችም መካከል የተወሰኑና በልዩነት የአብርሃም ዘር ወራሾች የሚሆኑ ይወጣሉ፡፡ ሙሴ፣ ለምሳሌ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከግብፅ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሲጓዙ መሪና መካከለኛ ሆኖ ነበር፡፡ ወደ ኋላ ላይም፣ እስራኤል፣ ጀማሪ መንግሥት ሆና ስትቋቋም፣ ዳዊትና ልጆቹ የአብርሃምን ውርስ የሚያስተላልፉ መካከለኞች ሆነው ነበር፡፡
ክርስቶስ የመጨረሻው የአብርሃም ታላቅ ዘር ነው ብሎ ወደ መጥቀስ ጳውሎስን የመራው ይህ የዳዊትና የልጆቹ ልዩ ሃላፈነት ነው ምክንያቱም ኢየሱስ የዳዊት ዙፋን ህጋዊ ወራሽ ነው፡፡ እርሱ የህዝቡ ዘላቂ ንጉሥ እንዲሆን በእግዚአብሔር ተመርጧል፡፡ እርሱ ታላቅና ዘላለማዊ የአብርሃም ዘር፣ መሲህ ነው፡፡ እናም፣ የሰው ዘር በሙሉ የአብርሃም ወራሽ ሊሆን የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ክርስቶስ ነው፡፡ ከክርስቶስ የተለየ ማንም ሰው የአብርሃምን ተስፋዎች አይቀበልም፡፡ ክርስቶስ የመጨረሻው የአብርሃም ዘር እንዴት እንደሆነ ለመረዳት፣ የእርሱን ሃላፊነት ለዓለም ሁሉ ባመጣው የማዳን መንግሥት ሦስት እርከኖች ረገድ መመልከት ይጠቅማል፡፡
ስለዚህ፣ ኢየሱስን ከአብርሃም ጋር በተገናኘ መንገድ እንዲህ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ ከክርስቲያን አተያይ አንፃር፣ ኢየሱስ ልዩ፣ የመጨረሻ የአብርሃም ዘር ነው፡፡ እናም እንደ ክርስቲያኖች የአብርሃምን ሕይወት በእኛ ዘመን ለማዛመድ ስንፈልግ፣ በአብርሃምና በእኛ ዘመን መካከል ያለው ትስስር የተመሠረተው ክርስቶስ መንግሥቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያመጣ፣ መንግሥቱን አሁንም መገንባቱን ሲቀጥል እና ወደፊትም መንግሥቱን ወደ ፍፃሜ ሲያመጣው የአብርሃም በረከቶቸ ሁሉ ወደ ክርስቶስ የተላለፉ መሆኑን በልቡናችን መያዝ ይኖርብናል፡፡
አዲስ ኪዳን፣ ክርስቶስ የአብርሃምን ውርስ መቀበሉንና ማስተላለፉን የሚያስተምረን በሦስት ዋና እርከኖች ነው፡፡ አንደኛ፣ በመጀመሪያ መምጣቱ ወቅት በተከናወነው በመንግሥቱ መታወጅ፤ ከዳግም ምፅዓቱ አስቀድሞ ባሉት የታሪክ ዘመናት ሁሉ በሚከናወነው የመንግሥቱ መስፋፋት፤ ሦስተኛ ደግሞ በከበረው ዳግም ምፅዓቱ በሚከናወነው በመንግሥቱ ፍፃሜ ነው ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦም ሁሉን ሲገዛም በተትረፈረፈ መጠን የአብርሃምን ውርስ መቀበሉንና ለሁሉ ማካፈሉን ቀጥሏል፡፡ አንድ ቀንም በክብር ሲመለስ የአብርሃምን ውርስ በሙላት ይቀበላል ላመኑትም ሁሉ ይሰጣል፡፡
በገላትያ 3፡16 ውስጥ ጳውሎስ ፈርጀ ብዙ የሆነውን ነገረ-መለኮታዊ አተያይ በጥቂት ቃላት ጠቅለል አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ ተስፋው ለአብርሃምና ለአንዱ ዘሩ ነው በማለት ጳውሎስ ሲናገር እና ያንንም ዘር ከክርስቶስ ጋር ሲያገናኘው፣ በዘፍጥረት “ዘር” በማለት የተጠቀሰው ቃል በቀጥታ ኢየሱስን ያመለክታል ማለቱ አይደለም፡፡ ይልቁኑ፣ በይስሐቅና በክርስቶስ መካከል ያለውን ያለውን ተምሳሊትነት አጠር አድርጎ ማሳየቱ ነው፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ ለመግለጥ፣ በዚህ መንገድ ማስቀመጥ ይኖርብናል፡ ይስሐቅ በዘመኑ የአብርሃም ዋና ወራሽ እንደሆነ ሁሉ፣ ክርስቶስም በአዲሰ ኪዳን ዘመን የአብርሃም ታላቅ ልጅና የአብርሃም ዋና ወራሽ ነው፡፡
ዐበይት መሪ ሃሳቦች
ክርስቶስን እንደ አብርሃም ዘር የመመልከቱን አስፈላጊነት በሙላት ለማየት፣ እነዚህን ጉዳዮች በአብርሃም ታሪኮች ውስጥ በተመለከትናቸው አራት ዐበይት መሪ ሃሳቦች አንፃር መመልከቱ ይጠቅማል፡፡ በእነዚህ የዘፍጥረት ምዕራፎች ውስጥ አራት ዐበይት መሪ ሃሳቦችን መመልከታችንን ታስታውሳላችሁ፡፡ እነርሱም፡- መለኮታዊ ጸጋ፣ የአብርሃም ታማኝነት፣ ለአብርሃም እግዚአብሔር የሰጠው በረከት እና በአብርሃም አማካይነት የተላለፈው የእግዚአብሔር በረከት ናቸው፡፡ እነዚህን ጭብጦች በአብርሃምና በክርስቶስ መካከል ያለውን ትስስር በሚያሳይ መንገድ እንዴት ልንረዳው ይገባናል?
መለኮታዊ ጸጋ
በመጀመሪያ ደረጃ፣ እግዚአብሔር በአብርሃም ሕይወት ውስጥ የተትረፈረፈ ጸጋን መግለጡን ተመልክተናል፡፡ እርግጥ ነው፣ አብርሃምም ኃጢአተኛ ስለሆነ ለራሱም ጸጋ ያስፈልገዋል፣ ከዚህ ባሻገር ግን፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገለጠው ምህረት እግዚአብሔር ለአብርሃም ያሳየው በጎነት ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ ከአብርሃም ጋር ግንኙነትን በማጠንከር፣ እግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ ያዘጋጀውን ቤዛነት በስፋት ገልጦታል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔር በአብርሃም ሕይወት መልካነቱን ባሳየበት መጠን፣ እግዚአብሔር ለአባታችን የገለጠው ፀጋ ለእኛም እንደ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በክርስቶስ የገለጠው ምህረት ጥላ ከመሆንም ዘለል ያለ መሆኑን እናምናለን፡፡ እርግጥ ነው፣ ክርስቶስ ያለ ኃጢአት በመሆኑ ለራሱ የድነት ጸጋን አልተቀበለም፣ ሆኖም ግን ክርስቶስ እንደ አብርሃም ዘር የመምጣቱ ነገር እግዚአብሔር ለዓለም ሁሉ የገለጠው ምህረት ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡
እግዚአብሔር በክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት፣ ባወጀው መንግሥቱ ብዙ ምህረትን ገልጧል፡፡ ሕይወቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱ እና የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ የእግዚአብሔር ጸጋ አስደናቂ መገለጫዎች ናቸው፡፡ አሁንም ክርስቶስ በሰማይ በመንበረ ንግሥናው ላይሆኖ፣ መንግሥቱን ሲያሰፋ፣ እግዚአብሔር የበለጠውን ምህረቱ እየገለጠ ነው፡፡ ድነትም ለዓለም ሁሉ ሲደርስ፣ በየታሪክ ዘመናቱ ዓለምን ማንም ሊክደው በማይችለው ለውጥ ውስጥ በማሳለፍ እግዚአብሔር በክርስቶስ የገለጠውን በጎነቱን እያሳየ ነው፡፡ ክርስቶስም ሲመለስ፣ በመንግሥቱ ፍፃሜ የማይለካ ምህረትን ይዞ ይመጣል፡፡ ክርስቶስ ይመጣል አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም ያመጣል፡፡ እንደ ክርስቶስ ተከታዮች፣ በአብርሃም ታሪኮች ውስጥ እግዚአብሔር አዘውትሮ በጎነቱን ያሳየናል፣ ስለዚህ ልባችን እና አዕምሯችን በክርስቶስ ውስጥ በመንግሥቱ ሦስት እርከኖች ወደተገለጠው የእግዚአብሔር ምህረት ሊመለስ ይገባዋል፡፡
የአብርሃም ታማኝነት
በሁለተኛ ደረጃ፣ ሙሴ ስለ አብርሃም ሕይወት በሰጠን ዘገባ ውስጥ የምናገኘው ወሳኝ መሪ ሃሳብ አብርሃም ለእግዚአብሔር የነበረው ታማኝነት ነው፡፡ ገና ከመነሻው፣ አብርሃም ወደ ተስፋይቱ ምድር የመሄድ ሃላፊነት እንዳለበት እግዚአብሔር አመልክቶታል፡፡ ደግሞም በሕይወቱ ዘመንም ሁሉ በርካታ ነገሮችን እንደሚጠብቅበትም አሳይቶታል፡፡ እንደ ክርስቲያኖች አብርሃም ይጠበቁበት ስለነበሩት ሃላፊነቶች ስናነብብ፣ ክርስቶስ እንደ አብርሃም ዘርነቱ ለሰማያዊ አባቱ ወደነበረው ታማኝነት ልባችንና አዕምሯችን ሊሳብ ይገባዋል፡፡
በእርግጥም፣ ክርስቶስ በሦስቱ የመንግሥቱ እርከኖች ውስጥ ለአባቱ የታመነ ነበር፡፡ በመንግሥቱ መታወጅ ወቅት፣ እግዚአብሔር አስቀምጦለት ለነበረው መመዘኛ ፍፁም ታዛዥ መሆኑን አሳይቷል፡፡ አብርሃም ጭብጥ በሆነ መንገድ በሕይወቱ ሁሉ ለእግዚአብሔር ታማኝ የነበረ ቢሆንም፣ ክርስቶስ ግን በሕይወቱ በእያንዳንዲቷ ደቂቃ ውስጥ ለእግዚአብሔር ፍፁም ታማኝ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ በሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ በመንግሥቱ ውስጥ ሲገዛም ክርስቶስ ለአባቱ እውነተኛና ታማኝ ሆኖ ይዘልቃል፡፡ ወንጌልን በማስፋትና ለህዝቡም ቤዛነትን በማምጣት የእግዚአብሔርን ዓላማዎች በፍፁምነት በማገልገል በሁሉ ላይ ይገዛል፡፡
በመጨረሻ፣ ክርስቶስ በመንግሥቱ ፍፃሜ ሲመለስ በምድር በነበረበት ወቅት የጀመራቸውን የጽድቅ ሥራዎች ያጠናቅቃል፡፡ ለአብም ክብር ጠላቶቹን ሁሉ ያጠፋል ሁሉንም አዲስ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ፣ አብርሃም ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነባቸውን መሪ ሃሳቦች በምናነብበት ጊዜ ሁሉ እንደ ክርስቲያኖች እነዚህን ጉዳዮች በእኛ ዘመን በትክክል ልናዛምድ የምንችለው ከክርስቶስ፣ ከአብርሃም ዘር ጋር በትክክል ስናገናዝባቸው መሆኑን እንረዳለን፡፡
የአብርሃም በረከቶቸ
በሦስተኛ ደረጃ፣ እንደ ክርስቲያኖች መለኮታዊ ጸጋና ሰብዓዊ ሃላፊነት በእኛ ዘመን በክርስቶስ አማካይነት እንዴት ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ብቻ መመልከት ብቻ አንፈልግም፣ ሦስተኛውንም የአብርሃም ሕይወት መሪ ሃሳብ ማወቅ እንሻለን፡፡ ያም እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው በረከት ነው፡፡ እስራኤል ታላቅ መንግሥት እንደምትሆን፣ በተስፋዪቱ ምድርም ብልፅግና እንደምታገኝ እና አብርሃምና እና እስራኤልም ስማቸው ገናና፣ ዓለም አቀፋዊ ዝና እንደሚኖራቸው እግዚአብሔር ለአብርሃም ነግሮታልእግዚአብሔር ለአብርሃም ነገረው፡፡
አሁንም፣ እንደገና እንደ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለአብርሃም ዘር ለክርስቶስ ወደሰጣቸው በረከቶች ልቦናችን ሊያቀና ይገባል፡፡ በመጀመሪያ መምጣቱ፣ ክርስቶስ ከሞት ተነሥቷል በሰማይና በምድርም ሥልጣን ሁሉ ተሰጥቶታል፤ በሰማይና በምድርም ከኢየሱስ ስም ሚበልጥ ስም የለም፡፡ አሁንም መንግሥቱ እየሰፋ ባለበት ዘመንም ኢየሱስ በተተትረፈረፉ በረከቶቹ ደስ እያሰኘን ነው፡፡ ዓለምን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲገዛ፣ እጅግ የላቀ ክብርን ለራሱ ተቀብሏል፡፡ በፍፃሜው ቀን ክርስቶስ ሲመለስ ግን እነዚህን በረከቶች ከልክ ባለፈ መጠን እንደሰትባቸዋለን፡፡ ይህ ታላቁ የአብርሃም ልጅ፣ እጅግ ከፍ ይላል ጉልበትም ሁሉ ይንበረከክለታል፡፡ ስለዚህ አብርሃም ከእግዚአብሔር የተቀበላቸውን በረከቶች በምንመለከትበት ጊዜ ሁሉ፣ ዐይኖቻችን የአብርሃምን በረከቶች ሁሉ ወደ ወረሰው እና የእግዚአብሔርንም በረከቶች እጅግ በተትረፈረፈ መጠን ወዳገኘው ወደ ክርስቶስ ሊያቀኑ ይገባል፡፡
በአብርሃም አማካይነት የተገኙ በረከቶቸ
በመጨረሻም፣ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ አራተኛው መሪ ሃሳብ በአብርሃም አማካይነት ለሌሎች የተላለፈው በረከት ነው፡፡ በበረከትና በመርገም ሂደት ውስጥ የምድር ወገኖች ሁሉ በአብርሃም አማካይነት እንደሚባረኩ እግዚአብሔር ተናገረ፡፡ ይህ ትልቅ ተስፋ በአዲስ ኪዳን ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡ በሮሜ 4፡13 ውስጥ ጳውሎስ ለአብርሃም የተሰጠውን ይህንን በረከት የጠቀሰበትን መንገድ አድምጡ፡-
የዓለምም ወራሽ እንዲሆን ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው የተስፋ ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ አይደለም፡፡ (ሮሜ 4፡13)
በዚህ ስፍራ እግዚአብሔር የምድርን ወገኖች ሁሉ እንደሚባርክ ለአብርሃም ተስፋን ሲሰጠው፣ ተስፋው ሊፈፀም የሚችለው ለአብርሃም የምድርን ወገኖች ሁሉ ርስት አድርጎ በመስጠትና የእግዚአብሔርንም መንግሥት በዓለም ሁሉ በማድረስ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ አብርሃምና ዘሩ ዓለምን ሁሉ ይወርሳሉ፣ መንግሥታትም ሁሉ በእነርሱ መሪነት ስር ይሆናሉ፡፡ አዳምና ሔዋን አስቀድሞውኑ ምድርን ሁሉ እንዲገዙ እንደተነገራቸው ሁሉ፣ አብርሃምና ዘሩም የእግዚአብሔርን በረከቶች ለአህዛብ ሁሉ በማድረስ ምድርን እንዲወርሱ እግዚአብሔር ተስፋን ሰጥቷቸዋል፡፡
ይህ የአብርሃምን በረከቶች ለምድር ሁሉ የማድረሱ የመጨረሻ መሪ ሃሳብ ለክርስቶስም ተግባራዊ ይሆናል ምክንያቱም እርሱ የአብርሃም ዘርና የአብርሃም ተስፋዎች ወራሽ ስለሆነ ነው፡፡ መንግሥቱ ሲታወጅ፣ ክርስቶስ ከእስራኤል ህዝብ መካከል የታመኑትን ጠራ፡፡ ከሞት ሲነሣና በሰማይ ወዳለው ዙፋኑ ሲያርግ ግን፣ የምድር ሁሉ ንጉሥ ሆኖ ተነሣ እናም ታማኝ ቅሬታዎቹ የእስራኤልን በረከት ለምድር ህዝቦች ሁሉ እንዲያደርሱ ነገራቸው፡፡ መንግሥቱም በአሁን ዘመን ሲቀጥል፣ በወንጌል አማካይነት የክርስቶስ ንግሥና በምድር ህዝቦች ሁሉ መስፋፋቱም ምድርን ሁሉ በእርሱ አማካይነት እንደሚባርክ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ፍፃሜ ነው፡፡ በመንግሥቱ ፍፃሜ ወቅት ክርስቶስ ሲመለስም ፣ ለምድር ወገኖች ሁሉ የእግዚአብሔርን በረከቶች ይሰጣል፡፡ በራእይ 22፡1-2 እንዲህ ይነበባል፡-
በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውሃ ወንዝ አሳየኝ፡፡ በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ-ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፣ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ፡፡ (ራእይ 22፡1-2)
አብርሃም ለአህዛብ ሁሉ በረከት የመሆኑ ተስፋ በሙላት የተፈፀመው በክርስቶስ መንግሥት መታወጅ፣ መስፋፋትና ፍፃሜ ውስጥ ነው፡፡
ስለዚህ፣ ጉዳዩን እንዲህ ጠቅለል ማድረግ እንችላለን፡፡ የአብርሃምን ሕይወት ከእኛ ዘመን ጋር የምናዛምድበት ትክክለኛው መንገድ ክርስቶስ እንደ አብርሃም ዘርነቱ ላለው ሃላፊነት እውቅና መስጠትን ሊያካትት ይገባዋል፡፡ እንደ አብርሃም ልዩ ዘር፣ ክርስቶስ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ የምንመለከታቸውን መሪ ሃሳቦች ወደ ፍፃሜ አምጥቶአል፡፡ የእግዚአብሔር ምህረት በክርስቶስ ተገልጧል፤ እውነተኛና ፍፁም ታማኝነት በክርስቶስ ውስጥ ይገኛል፤ ክርስቶስ ለአብርሃም ተስፋ የተሰጡትን በረከቶች ሁሉ ተቀብሏል ደግሞም በክርስቶስ ውስጥ የአብርሃም በረከቶች እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሲዳረሱ አይተናል፡፡ ስለ ዘመነኛው ተዛምዶ የትኛውንም ነገር ብንናገር፣ በአብርሃምና በኢየሱስ መካከል ያሉትን ትስስሮች ማስታወሳችን ወሳኝነት አለው፡፡
በአብርሃምና በኢየሱስ መካከል ያሉት ግንኙነቶች በአብርሃም ታሪኮችና እኛ በምንኖርበት ዓለም መካከል የማያወላዳ ትስስር እንዳለው ከተመለከትን፣ ወደ ሁለተኛው የዘመናችን ተዛምዶ ማለትም በእስራኤልና በቤተክርስቲያን መካከል ወዳለው ግንኙነት ልንሸጋገር ይገባናል፡፡
እስራኤልና ቤተክስቲያን
ሙሴ በመጀመሪያ ጊዜ የአብርሃምን ሕይወት ሲያጠናቅር፣ ስለ እነዚህ ነገሮች የጻፈው የእስራኤል ህዝብ ግብፅን ወደ ኋላ ጥለው የተስፋይቱን ምድር በድል ለመውረስ በሚያደርጉት ጉዞ ሊያበረታታቸው እንደነበር ዘወትር ማስታወስ ይገባናል፡፡ በአብሀርሃም ሕይወት ውስጥ የዚህን ራእይ ታሪካዊ ዳራ ሊያገኙ፤ ደግሞም ሊከተሉትና አሻፈረኝ ሊሉ የሚገባቸውንም ነገር ተምሳሊት በማግኘት ራእዩን ሊያሳኩ፤ ደግሞም በአብርሃም ሕይወት ውስጥ የሕይወታቸውን ጥላ ሊመለከቱ ይገባቸው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት፣ የአብርሃም ሕይወት ከዘመኑ ዓለም ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ለመመልከት፣ በእስራኤል ህዝብና በዛሬዋ የክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን መካከል ስላለው ትስስር አዲስ ኪዳን የሚያስተምረውን መመርመር ይገባናል፡፡
በእስራኤልና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ይህንን ግንኙነት ለመመርመር፣ ቀደም ካለው ትምህርታችን ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ሁለት ርእሶችን እንዳስሳለን፡፡ አንደኛ፣ የአብርሃም ዘር የተሰኘውን መሪ ሃሳብ ከእስራኤል መንግሥትና ከክርስቶስ ቤተክርስቲያን ጋር የሚዛመድበትን መንገድ ገፋ አድርገን እንመረምራለን፡፡ ሁለተኛ፣ የአብርሃም ዘር የተሰኘው መሪ ሃሳብ በአብርሃም ሕይወት አራት ዐቢይ መሪሃሳቦች ውስጥ እንዴት አንደተንፀባረቀ እናያለን፡፡ አስቀድመን እስራኤልንና ቤተክርስቲያንን እንደ አብርሃም ዘር እንመልከታቸው፡፡
የአብርሃም ዘር
እንደ አብርሃም ዘር በእስራኤልና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት ለመመልከት አራት ጉዳዮችን በስሱ እንዳስሳለን፡፡ አንደኛ፣ የአብሃምን ዘር አሃዛዊ እድገት እናያለን፡፡ ሁለተኛ፣ የዘሩን የነገድ መለያ ልብ እንላለን፡፡ ሦስተኛ፣ በአብርሃም ዘር መንፈሳዊ ባህርይ ላይ እናተኩራለን፡፡ አራተኛ፣ የአብርሃምን ዘር ታሪካዊ ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ አስቀድመን የአብርሃምን ዘር አሃዛዊ እድገት እንመልከት፡፡
አሃዛዊ እድገት
እንደተመለከትነው፣ የዘፍጥረት መጽሐፍ የአብርሃም ዘር የሚለውን ቃል፣ ከአንድ ከተለየ ሰው፣ ከይስሐቅ ጋር በማጣቀስ በግልፅ አስቀምጦታል፣ አዲስ ኪዳንም ይህንኑ በማንገብ በአብርሃምና በክርስቶስ መካከል ትስስር ይፈጥርበታል፡፡ አሁን ደግሞ ጥቂት እይታችን ሰፋ አድርገን የአብርሃምን ዘር ሌላኛ ገፅታ እናያለን፡፡ ይስሐቅ በአብርሃም ታሪኮች ውስጥ የአብርሃም ዘር ወይም ትውልድ ተብሎ የተጠራ ብቸኛ ሰው አይደለም፡፡ ይስሐቅ የአብርሃምን ቅርስ ለራሱ ብቻ አልተቀበለም፡፡ ብዙዎች በእርሱ አማካይነት የአብርሃም ዝርያዎች ይሆኑ ዘንድ ማስተላለፊያ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ሙሴ ደግሞ ደጋግሞ እስራኤልን እንደ አብርሃም ዘር ጠቅሷታል፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ የአብርሃምን ታሪኮች ከእኛ ዘመን ጋር ስናዛምድ፣ በአዲስ ኪዳን ዋነኛው የአብርሃም ዘር ክርስቶስ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፣ የክርስቲያኗ ቤተክርስቲያንም የአብርሃም ዘር መሆኗንም ማስታወስ ይገባል፡፡ ጳውሎስ በገላትያ 3፡29 እንዲህ አስቀምጦታል፡
እናንተም… የአብርሃም ዘር፣ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ፡፡ (ገላትያ 3፡29)
በዚህ ምንባብ ጳውሎስ በግልፅ እንዳስቀመጠው፣ ከክርስቶስ ጋር በመተባበራችን የተነሳ ከአብርሃም ጋር ተያይዘናል፡፡ እኛ፣ ልክ እንደ ብሉይ ኪዳኗ እስራኤል፣ የአብርሃም ዘር ነን፡፡ በዚህ ምክንያት፣ የአብርሃም ታሪኮች የሚዛመዱት ከክርስቶስ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ከእርሱ ጋር ለተቆራኙ ለበርካታ የአብርሃም ልጆች ሁሉ ነው፡፡
የነገድ መለያ
በብሉይ ኪዳን እስራኤል ዛሬ በእኛ ዘመን ደግሞ ቤተክርስቲያን የአብርሃም ዘር ከመሆናቸው እውነታ ባሻገር፣ በሁለቱም ኪዳናት ስለ አብርሃም ዘር የነገድ መለያ ጥቂት ማለት እንወዳለን፡፡ እንደተመለከትነው፣ በመጀመሪያ ደረጃ የአብርሃም ታሪኮች የተፃፉት ሙሴን ይከተሉ ለነበሩት እስራኤላውያን ነበር፡፡ ከቀደምቱ ተደራሲያን አብዛኛውን የሚይዙት የአይሁድ ነገዶች ማለትም የአብርሃም ሥጋዊ ወገኖች ቢሆኑም፣ ቀደምት ተደራሲያኑ አይሁድ ብቻ ነበሩ ማለት ግን ስህተት ነው፡፡ ሙሴን ይከተሉ የነበሩ በርካታ ህዝቦች የአይሁድና ወደ እስራኤል ወገንነት የጠጨመሩ አህዛብም ነበሩበት፡፡ በውጤቱም፣ በበርካታ ወቅቶች፣ የዘፍጥረት መጽሐፍ ቀደምት ተደራሲያ አይሁድ ብቻ እንዳልነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍት ግልፅ ያደርጉልናል፡፡
ለአብነት ያህል፣ በዘፀአት 12፡38 ሙሴን ይከተሉ የነበሩ ሰዎች የተገለጡበትን መንገድ አድምጡ፣
ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ህዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ፡፡ (ዘፀአት 12፡38)
በዚህ ስፍራ በእስራኤላውያን መካከል “ድብልቅ ህዝቦች” መኖራቸውን ልብ በሉ፡፡ ይህም ህዝብ ከእስራኤል ጋር የተደባለቁና ከግብፅ አብረዋቸው የወጡ አህዛቦችን ያካተተ ነው፡፡ ይህ ቡድን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ በኋለኞቹ የበሉይ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ ዕውቅ የሆኑት አህዛብ ረዓብና ሩት በኋለኞቹ ትውልዶች ወደ እስራኤል ዘር ውስጥ መግባታቸው ተገልጧል፡፡ ይህም በ1ኛ ዜና 1-9 የትውልድ ሐረግ ውስጥ በእግዚአብሔር ህዝቦች መካከል የአህዛብ ስሞችም ተካትተዋል፡፡
ስለዚህ ሙሴ ስለ አብርሃም ታሪኮች ስቀድሞ የጻፈላቸው የአብርሃም ዘሮች ድብልቅ ነገዶች ነበሩ ማለት ነው፡፡ የአብርሃምን የሥጋ ወገኖችና ወደ እስራኤል ቤተሰብ ውስጥ የተጨመሩትን አህዛብም ያካትታል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በተስፋይቱ ምድር ስለሚኖራቸው የወደፊት ሕይወት በአብርሃም ታሪኮች አማካይነት ይገነዘባሉ፡፡
በተመሳሳይ መንገድ፣ የዘመናችን ቤተክርስቲያንም ድብልቅ ነገዶች አሉባት፡፡ ክርስቶስን ጌታ ያደረጉ አይሁድና ክርስቶስን ጌታቸው በማድረግ ወደ አብርሃም ቤተሰብነት የተቀላቀሉ አህዛብን ይዛለች፡፡ እንግዲህ፣ ይበልጥ እርግጠኛ ለመሆን፣ ታሪክ ይፋ እንዳደረገው የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ከአይሁድ ይልቅ ወደ ቤተሰቡ በተቀላቀሉ አህዛብ በጣም ብትበዛም ዛሬም ቢሆን የአብርሃም ዘር እውነታ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሁሉ ድብልቅ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የአብርሃም ታሪኮች ለመጀመሪያ ጊዜ የአብርሃም ዘር ተብለው ለተቆጠሩት አይሁድና አህዛብ እንደተሰጡ ሁሉ፣ እኛም የአብርሃምን ታሪኮች ዛሬም የአብርሃም ዘር ተብለው ለተቆጠሩ ለአይሁድና ለአህዛብ ለማዛመድ ዝግጁ መሆን ይገባናል፣ ምክንያቱም በመላው ዓለም ሁለቱም ወገኖች በቤተክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉና፡፡
ይህ ነገር ከዘመነኛው ተዛምዶ አንፃር ወሳኝ ጉዳይ ነው ምክንያቱም በርካታ ክርስቲያኖች ለአብርሃም የተሰጡት ተስፋዎቸ ሊፈፀሙ የሚችሉት ለአይሁድ ነገዶች ብቻ ነው የሚለውን የተሳሳተ አስተምህሮ ተቀብለውታልና ነው፡፡ በዚህ አመለካከት፣ እግዚአብሔር ለአህብ ሌላ ፕሮግራም አለው፡፡ እዚህም እዚያም ከሚገኙ መንፈሳዊ መርሆች በስተቀር፣ አህዛብ አማኞች የአብርሃም ተስፋዎች ወራሾች አይደሉም ይባላል፡፡ እንግዲህ ይህ አመለካከት ታዋቂ እየሆነ ቢመስልም፣ በሙሴ ዘመን የነበረው የአብርሃም ዘር ድብልቅ ነገዶችን ያካተተ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም የአብርሃም ዘር ድብልቅ ነገዶችን እንዳካተተ ይቀጥላል፡፡ ሙሴ ይከተሉት ለነበረ ህዝብ ያስተማረው ትምህርት፣ ዛሬም ለቀጠለው ህዝብ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንም ይሠራል፡፡
መንፈሳዊ ባህርይ/ገፅታ
በሦስተኛ ደረጃ፣ የአብርሃም ሕይወት ዘመነኛው ተዛምዶ የእስራኤልን እና የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ ባህርይ እንደ አብርሃም ዘርነታቸው ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡ እንደመለከትነው፣ ብሉይ ኪዳን የምትታየዋን የእስራኤልን መንግሥት በአብርሃም ዘር፣ የወል የአብርሃም ዘር ብሏታል፣ ሆኖም ግን በምትታየዋም የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የተለያየ መንፈሳዊ ገፅታ እንደነበር ልናስተውል ይገባል፡፡ የማያምኑና እውነተኛ አማኞች ነበሩባቸው፡፡ በእስራኤል መንግሥት ውስጥ በርካታ ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች እውነተኛ አማኞች እንዳልነበሩ፣ ሆኖም ደግሞ በእግዚአብሔር ተስፋዎች የሚታመኑ እውነተኛ አማኞችም እንደነበሩ ብሉይ ኪዳን በጣም ግልፅ ያደርግልናል፡፡ በእርግጠኝነት፣ በእስራኤል ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ፣ የሚያምነውም የማያምነውም፣ በርካታ ልዩ ወቅታዊ በረከቶችን ከእግዚአብሔር ይቀበል ነበር፡፡ ሁሉም ከግብፅ ባርነት ነፃ ወጥተዋል፤ በሲና ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ቃል ኪዳናዊ ግንኙነት ውስጥ ገብተዋል፤ ለማመን በርካታ እድሎች ተሰጥቷቸዋል ሁሉም ወደ ተስፋዪቱ ምድር እድል ተሰጥቶዋቸው ነበር፡፡ ሆኖም በርካታ ልዩነቶችም ነበሩዋቸው፡፡ በአንድ ወገን፣ በእስራኤል መካከል ያሉት የማያመኑ ሰዎች ህጉን በመተላለፍ የልባቸውን እውነተኛ ገፅታ አሳይተዋል፡፡ እናም የአብርሃም ታሪኮች እነርሱን ወደ እውነተኛ ንስሓና ለመዳን ወደሚያበቃው እምነት ለመጥራት የተቀረፁ ነበሩ፡፡
በሌላ በኩል፣ በእስራኤል መካከል የነበሩት እውነተኛ አማኞች ደግሞ በእግዚአብሔር ተስፋዎች በመታመንና ህጉን በመጠበቅ የልባቸውን እውነተኛ ገፅታ አሳይተዋል፡፡ እነዚህን እውነተኛ አማኞች በእምነታቸው እንዲያድጉ ለማበረታታት የአብርሃም ታሪኮች ተዘግበዋል፡፡ በእስራኤል መካከል የሚገኙት የማያምኑ ሰዎች ህጉን በመተላለፋቸው ምክንያት፣ ጊዜያዊ በረከቶችን ብቻ ተቀብለዋል፡፡ ለዘላለም ግን የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ፍርድ ይቀበላሉ፡፡ እውነተኛዎቹ አማኞች፣ የአብርሃም እውነተኛ ዘር የሆኑቱ፣ መንፈሳዊ ልጆቹ ግን፣ አላፊ የሆኑትን በረከቶች ብቻ ሳይሆን አንድ ቀን በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር ውስጥ፣ የአብርሃምን ዘላለማዊ በረከቶች ይወርሳሉ፡፡ በሮሜ 9፡6-8 ጳውሎስ ይህን አመለካከት ጫን ብሎ ይሟገትለታል፡፡ በዚያ የተናገረውን አድምጡ፡-
ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤል አይደለምና፡፡ ከአብርሃም ዘርም ስለሆኑ፣ ሁሉም ልጆቹ አይደሉም፤ ይልቁንስ፣ ትውልድህ በይስሐቅ በኩል ይጠራልሃል እደተባለው ነው፡፡ ይህም ማለት የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የሥጋ ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን የአብርሃም ልጆች የተባሉት የተስፋው ልጆች ናቸው፡፡ (ሮሜ 9፡6-8)
እንግዲህ፣ በክርስቶስ ቤተክርስቲያንም ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያየ መንፈሳዊ ገፅታ መኖሩን መመልከት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በአዲስ ኪዳን በመጠመቅ የምትታየዋ ቤተክርስቲያን አባል የሆኑ ሰዎች ሁለት ዓይነት ናቸው፡ የሚያምኑና የማያምኑ፡፡ እርግጥ ነው፣ በብሉይ ኪዳን ሰዎች ከእግዚአብሔርና ከህዝቡ ጋር ከመቀየጣቸው የተነሳ በርካታ አላፊ በረከቶችን እንደ ተቀበሉ ሁሉ፣ በክርስቶሰ ቤተክርስቲያንም ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች በርካታ አላፊ በረከቶችን ይቀበላሉ፡፡ ፍቅርን የሚካፈሉበትን ማኅበረሰብ ያገኛሉ፤ የእግዚአብሔር ቃልና ሥርዓቶቹ አሏቸው፤ ወንጌል ተብራርቶ ይሰበክላቸዋል፡፡ ሆኖም ደግሞ፣ በዚችው በምትታየዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ ህጉን በመተላለፍ የልባቸውን እውነተኛ ገፅታ የሚያሳዩ ሰዎችም አሉ፡፡ እናም የአብርሃም ታሪኮች በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ ለማያምኑ ሰዎችም ተግባራዊ በመሆን ወደ እውነተኛ ንስሓና ለመዳን ወደሚያበቃው እምነት ይጠራቸዋል፡፡
ግን አሁንም በዚያችው በምትታየዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ በእግዚአብሔር ተስፋዎች የሚታመኑ እና ህጉን በመጠበቅ እውነተኛውን የልባቸውን ገፅታ የሚያሳዩ እውነተኛ አማኞችም አሉ፡፡ እነዚህም ክርስቲያኖች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በእምነታቸው እንዲያደጉ ለማበረታታት የአብርሃም ታሪኮች ለእነርሱም ተፈፃሚነት አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የማያምኑ ሰዎች፣ ባለማመናቸው ምክንያት፣ አላፊ በረከቶችን ብቻ ይቀበላሉ፡፡ ለዘላለሙ ግን፣ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ፍርድ ይቀበላሉ፡፡ የአብርሃም እውነተኛ ዘሮች፣ የአብርሃም እውነተኛ ልጆች፣ በክርስቶስ የሚታመኑት ግን በርካታ አላፈ በረከቶችን ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ቀን በአዲስ ሰማይና ምድር የአብርሃም ውርስ የሆነውን ዘላላማዊ ብድራታቸውን ይቀበላሉ፡፡
ለዚህም ነው ያዕቆብ በያዕቆብ 2፡21-22 ውስጥ ስለ አብርሃም የጻፈው፡፡ በውስጥዋ የሚያምኑና የማያምኑ ላሉባት ለክርስቲያኗ ቤተክርስቲያን ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፡-
አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? በዚህም እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበር ታያለህ፤ እምነትም በሥራ ፍጹም ሆነ፡፡ (ያዕቆብ 2፡21-22)
በዚህ ስፍራ የያዕቆብ ዋና ሃሳብ የአብርሃም ታሪኮች በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን የማያምኑ ሰዎች ከግብዝነታቸው እንዲመለሱ ይሞግታሉ፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን እውነተኛ አማኞች ደግሞ በታመነ አኗኗር እምነታቸውን መግለጣቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታቷቸዋል የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ የአብርሃምን ታሪኮቸ ከእኛ ዘመን ጋር ስናዛምድ በቤ ተክርስቲያን ውስጥ ያለውን የተለያየ መንፈሳዊ ገፅታ በመረዳቱ ረገድ የያዕቆብን ምሳሌነት ልንከተል ይገባናል፡፡
ታሪካዊ ሁኔታ
በአራተኛ ደረጃ፣ የአብርሃምን ሕይወት ከዘመናችን ጋር ለማዛመድ፣ በዛሬዋ ቤተክርስቲያንና ሙሴን ይከተሉ በነበሩ እስራኤላውያን ታሪካዊ ሁኔታ መካከል ጉልህ የሆነ ተመሳሳይነት መኖሩን ማስታወስ ይገባናል፡፡ ሙሴ ስለ አብርሃም ሕይወት የጻፈላቸው በጉዞ ላይ ለነበሩ እስራኤላውያን እንደነበር ታስታውሳላችሁ፡፡ ለመጀመሪያዎቹ ወይም ለቀጣዮቹ የዘፀአት ተጓዞች ቢጽፍም ቀደምት ተደራሲያኑ በሁለት ዓለማት መካከል ተጉዘዋል፡፡ በአንድ በኩል፣ ከግብፅ ባርነት ወጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ ገና ወደ ተስፋዪቱ ምድር ወደ ከነዓን አልገቡም፡፡ ወይም በሌላ መንገድ ብናስቀምጠው፣ የእስራኤል ህዝብ ከአሮጌው ዓለማቸው የመጀመሪያውን ነፃነት አግኝተዋል፣ ሆኖም ወደ አዲሱ ዓለማቸው ገና አልገቡም፡፡ በውጤቱም፣ እስራኤላውያን ከግብፅ ጋር ከነበራቸው ቁርኝት ፈፅመው እንዲላቀቁና ወደፊት በመጓዝ ምድሪቱን በድል እንዲወርሱ ሊያበረታታቸው ሙሴ ጽፈፎላቸዋል፡፡
የቀደምት ተደራሲያኑ ታሪካዊ ሁኔታ ለዘመነኛው ተዛምዶ ወሳኝነት አለው ምክንያቱም የዛሬዋም የክርስቲያን ቤተክርስቲያን ተጓዳኝ በሆነ ታሪካዊ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነፃ እንደ ወጣች እና በተስፋይቱ ምድር ወደሚጠብቃት የከበረ ሕይወት እየተጓዘች እንደነበረ ሁሉ፣ የክርስቶስ ቤተክርስቲያንም ክርስቶስ በምድር በነበረበት ዘመን ባከናወነው ሥራ ከኃጢአት ተገዢነት ነፃ ወጥታለች፣ ሆኖም ክርስቶስ ዳግመኛ ሲመጣ ወደምትቀበለው የከበረ አዲስ ፍጥረት ገና በመገስገስ ላይ ትገኛለች፡፡ እነዚህ ተጓዳኝ ሁኔታዎች የአብርሃምን ሕይወት ከዘመናችን ጋር የምናዛምድበትን የማገናዘቢያ ማዕቀፍ ይለግሱናል፡፡ እስራኤል ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላው በምታደርገው ጉዞ ሊያበረታታትና ሊመራት የአብርሃምን ታሪክ ሙሴ እንደጻፈላት ሁሉ፣ እኛም ዛሬ ሞት ከነገሠበት ዓለም ወደ የዘላለም ሕይወት ወደሚገኝበት አዲስ ዓለም በምናደርገው ጉዞ የእርሱ ታሪኮች ያበረታቱናል ይመሩናልም፡፡
ከተዛምዶ አንፃር እነዚህ ታሪካዊ ጉድኝቶች እነዚህን መሳይ መረዳቶች እንደሚያስጨብጡን እርግጠኛ መሆን እንችላለን ምክንያቱም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ብሉይ ኪዳንን ሲያዛምድላቸው እነርሱኑ ጠቅሶ ነበር፡፡ በ1ኛ ቆሮ 10፡1-6 በሙሴ ተደራሲያንና በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን መካከል ስላለው ታሪካዊ ጉድኝት የጻፈበትን መንገድ አድምጡ፡፡
ወንድሞች ሆይ፣ ይህንን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባህር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባህር ተጠመቁ፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፣ በምድረ በዳ ወድቀዋልና፡፡ እነዚህም ክፉ ነገር እንደተመኙ እኛ ደግመ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን፡፡ (1ኛ ቆሮ 10፡1-6)
በቀላሉ ስናስቀምጠው፣ በምድረ በዳ ሙሴን ይከተሉ የነበሩ እስራኤላውያን ያለፉባቸው ልምምዶች ከክርስቲያኖቹ ልምምዶች ጋር ተጓዳኝነት እንዳላቸው ጳውሎስ ይጠቅሳል፡፡ እኛ በክርስቶስ ነፃ እንደወጣን ሁሉ እነርሱም በሙሴ ነፃ ወጥተው ነበር፡፡ ክርስቲያኖች በክርስቶስ እንደተጠመቁ ሁሉ እነርሱም በሙሴ ተጠምቀው ነበር፡፡ ክርስቲያኖች የጌታን እራት እንደሚካፈሉ ሁሉ እነርሱም ከእግዚአብሔር ዘምንደ መና በልተዋል ውሃም ጠጥተዋል፡፡ ሆኖም፣ እነዚህ ቀደምት የጸጋ ልምምዶች እስራኤልን ወደ ሙከራ ጊዜ ውስጥ አስገብተዋታል፣ ማለትም ወደ ተስፋዪቱ ምድር በሚጓዙበት ወቅት የሚፈተኑበት ጊዜ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ግን፣ በሙሴ ዘመን እግዚአብሔር በሚበዙት ደስ አልተሰኘም ስለዚህ በምድረ በዳ ውስጥ አለቁ፡፡ ስስዚህ ክርስቲያኖች እንደ ቤተክርስቲያን ሲጓዙ የጉዟቸውን ሁኔታ ከእስራኤል ሊማሩ እንደሚገባ ጳውሎስ ጠቅለል አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ የአብርሃምን ሕይወት ከክርስቲያኖቹ ቤተክርስቲያን ጋር እንዴት ማዛመድ እንዳለብን ጳውሎስ ካቀረበው ምሳሌ ብዙ እንማራለን፡፡
ስለ አብርሃም ሕይወት ሙሴ የጻፈው ታሪክ እግዚአብሔር እነርሱን ከግብፅ ባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው መለስ ብለው እንዲመለከቱና ወደ ተስፋዪቱም ምድር ሲጓዙ በታማኝነት እንዲፀኑ ያበረታታቸዋል፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ በዚህ ዘመን ለምትገኘውም ቤተክርስቲያን የአብርሃም ሕይወት ከጉዟችን ጋር በተገናኘ መንገድ ይሠራል፡፡ መንግሥቱን ወደ ምድር ባመጣበት ወቅት ስለ ሠራልን ሥራ ለክርስቶስ ታማኞች ልንሆን ይገባናል፡፡ በእኛም ዘመን መንግሥቱ እየሰፋች ስትሄድም በታማኝነታችን ልንፀና፣ ደግሞም አንድ ቀን ወደ አዲሲቷ ምድርና ሰማይ ስንገባም መንፈሳዊ ጉዟችን የሚጠናቀቅበትን ቀን በናፍቆት ልንጠብቅ ይገባናል፡፡
ስለዚህ የአብርሃም ሕይወት ከዘመናችን ጋር የሚዛመድበትን መንገድ ስንመለከት፣ በአብርሃምና በኢየሱስ መካከል ስላሉት ትስስሮች ብቻ ማሰብ የለብንም፡፡ ይልቁኑ የአብርሃምን ታሪኮች ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀበሉትና በክርስቲያኗ ቤተክርስቲያን መካከል ስላለውም ትስስር ልናስብ ይገባናል፡፡ የብሉይ ኪዳኗ እስራኤልና የአዲሰ ኪዳኗ ቤተክርስቲያን የአብርሃም ዘር ናቸው፤ ሁለታችንም ድብልቅ ነገድ አለን፤ ሁለታችንም የተለያዩ መንፈሳዊ ገፅታዎች አሉን ደግሞም ሁለታችንም ወደ ከበረው የእግዚአብሔር መንግሥት ግብ በመጓዝ ላይ እንገኛለን፡፡
ዐበይት መሪ ሃሳቦች
በአሁኑ ዓለም የአብርሃም ዘር ቀጣይ ትውልድ እንደመሆናቸው የአብርሃም ሕይወት ለክርስቲያኖቹ ቤተክርስቲያንም ሊዛመድ እንደሚችል ከተመለከትን፣ ይህ የማዛመድ ሂደት ለአብርሃም ሕይወት የተሰጡትን አራት ዐበይት መሪ ሃሳቦች እንዴት እንደሚነካ ልንመለከትም ይገባናል፡፡ እነዚህ ጭብጦች ዛሬ በክርስቶስ ለምንኖረው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ምን የሚናገሩት ነገር አለ?
እንደምታስታውሱት የአብርሃም ታሪኮች አራት ዐቢይ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ፡ መለኮታዊ ጸጋ፣ የአብርሃም ታማኝነት፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው በረከት እና በአብርሃም አማካይነት የእግዚአብሔር በረከት ለሌሎች፡፡ በሚከተለው ትምህርታችን፣ እነዚህ መሪ ሃሳቦች እንደ አብርሃም ዘርነታችን ለሕይወታችን ምን እንደሚናገሩ ደጋግመን እናመለክታለን፡፡ ለአሁኑ ግን፣ ልንከተላቸው የሚገቡንን አጠቃላይ መመሪያዎች በአጭሩ እናቀርባለን፡፡ አስቀድመን መለኮታዊ ጸጋን እንመልከት፡፡
መለኮታዊ ጸጋ
እግዚአብሔር ለአብርሃም ብዙ ምህረትን አድርጎለታል፣ ይህም በሕይወቱ ጅማሬ ላይ ብቻ ሳይሆን በምድር በኖረባት በእያንዳንዲቷ ቀን ሁሉ ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት በግልፅ እንደሚያስተምሩት፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም ምህረቱን እንዳሳየ፣ ዛሬም እኛን ወደ ክርስቶስ ለማምጣትና ለማፅናት እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች ጸጋን ይሰጣል፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን 2፡8-9 እንዲህ ጽፏል፡-
ጸጋው በእምነት አድኗችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም፡፡ (ኤፌሶን 2፡8-9)
በክርስቶስ መዳን የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ነው፤ እምነትም እንኳን የሚገኘው ከእርሱ ነው፡፡ በዚያው ምህረት መኖራችንን ለመቀጠል በየዕለት ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በእግዚአብሔር ምህረት አብዝተን ልንደገፍ ይገባናል፡፡ ከሚያጸናው ከእግዚአብሔር ጸጋ በስተቀር ታማኝ ለመሆን የምንጥረው ጥረት ሁሉ ከንቱ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት፣ ሙሴን ይከተሉ የነበሩ እስራኤላውያን የአብርሃምን የሕይወት ታሪኮች በሚያደምጡበት ወቅት በሕይወታቸው የእግዚአብሔርን አስደናቂ ጸጋ እንደተረዱ ሁሉ፣ እኛም እግዚአብሔር ለአብርሃም ያሳየውን ምህረት በምናነብበት በየትኛውም ወቅት፣ በግልም ሆነ በጋራ እግዚአብሔር ለእኛ ስላደረጋቸው ነገሮች የምንደነቅበትን ዕድል እናገኛለን፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ብዙ ምህረቱን ገልጦልናል እናም የእርሱ ምህረት እንዴት ልንናቀውና ልንደገፍበት እንደምንችል ልንማር ይገባናል፡፡
የአብርሃም ታማኝነት
በተመሳሳይ መንገድ፣ የአብርሃም ታማኝነት መሪ ሃሳብ በብዙ መልኩ ከክርስቶስ ተከታዮች ጋር ይዛመዳል፡፡ ስለ አብርሃም ሕይወት ስናነብብ፣ አብርሃም እግዚአብሔርን በመታዘዝ እንዲያገለግል የታዘዘባቸውን በርካታ ወቅቶች አይተናል፡፡ እርግጥ ነው፣ ወደ ሕይወት ፍፅምና አልደረሰም፣ ሆኖም የእውነተኛ እምነት ፍሬዎች ግን ይታዩበታል፡፡ እግዲህ፣ በብሉይ ኪዳንም እንኳን፣ ከእምነት የሚነሳ መታዘዝ ዘወትር በእግዚአብሔር ምህረትና ጸጋ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ይህንን አፅንዖት የሕገኝነት አንዱ ቅርፅ አድርገን በመቁጠር መሳሳት አይገባንም፡፡ የሆነ ሆኖ፣ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሁሉ፣ ዛሬም እውነተኛ አማኞች ከእምነት በሚነሳ መታዘዝ ለእግዚአብሔር ጸጋ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲስ ኪዳን በክርስቶስ ተከታዮች ሃላፊነት ላይ ደግሞ ደጋግሞ አፅንዖት የሚያደርገው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን 2፡8-10 ውስጥ ጸጋንና ታማኝነትን ያገናኘበትን መንገድ አድምጡ፡፡
ጸጋው በእምነት አድኗችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም፡፡ እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን (ርኤፌሶን 2፡8-10)
ቁጥር 10 በግልፅ እንዳስቀመጠው፣ ክርስቲያኖች ዛሬም ቢሆን መልካም ሥራን የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ እግዚአብሔር ለድነት የሚያበቃውን እምነት ስለሰጠን ለእርሱ ታማኝ መሆን እንችላለን፡፡ ስለዚህ፣ የአብርሃም ሕይወት ከሰው የሚጠበቅን ታማኝነት አስመልክቶ የሚነሳቸውን ነገሮች በምናይበት ወቅት ሁሉ፣ እነዚያን ከሕይወታችን ጋር የማዛመድ ሃላፊነት እንዳለብን ልናውቅ ይገባናል፡፡
ለአብርሃም የተሰጡ በረከቶች
በሦስተኛ ደረጃ፣ ለአብርሃም የተሰጡት በረከቶች ከክርስቲያኖች ህይወት ጋር ሊዛመዱ የሚችሉባቸውን መንገዶች የምንገነዘብ ልንሆን ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ ታላቅ የበረከት ተስፋን እንደሰጠው ታስታውሳላችሁ፡፡ በስተመጨረሻም፣ ታላቅ፣ ባለፀጋና ዝናቸው በምድር ሁሉ የወጣ ይሆናሉ፡፡ በአብርሃም ታሪኮችም ወስጥ እግዚአብሔር አባታችንን ሲባርከው የእነዚህን በረከቶች ፍጻሜ አስቀድሞ በቅምሻ ሲያሳየው ታገኛላችሁ፡፡
ቀደምት ተደራሲያኑ እስራኤላውያን የተስፋቸውን ፍፃሜ እየተጠባበቁ ሳሉ ለአብርሃም የተሰጡት በረከቶች በሕይወታቸው ሲፈፀሙ ያዩ እንደነበረ ሁሉ፣ እኛም ደግሞ ዛሬ እንደ ክርስቲያኖች ሁሉም በሙላት የሚገለጡበት አንድ ቀን እንደሚመጣ በተስፋ እየተጠባበቅን ሳለ፣ የእነዚህን ተመሳሳይ በረከቶች ቅምሻ በእጅጉ አሁን በዚህ እናጣጥማለን፡፡ አሁን በምንኖረው ሕይወት የምናያቸው በረከቶች ክርስቶስ ሲመለስ የእኛ የሚሆኑትን የፍጻሜ በረከቶች በተስፋ እየጠበቅን የየዕለት ሕይወታችንን እንድንመራ በብዙ ያበረታቱናል፡፡
በአብርሃም አማካይነት ለሌሎች የተሰጡ በረከቶች
በመጨረሻ፣ የአብርሃም ታሪኮች እግዚአብሔር በአብርሃም አማካይነት ለዓለም ሁሉ በሚሰጣቸው በረከቶችም ላይ እንደሚያተኩሩ ሁሉ፣ ክርስቲያኖችም በእኛ አማካይነት ለዓለም ሁሉ የተሰጡ በረከቶችን የምናንፀባርቅበት ዕድል ተሰጥቶናል፡፡ አብርሃም ከጠላቶቹ እንደሚጠበቅ እና ለወዳጆቹም በረከት እንደሚሆን እና አንድ ቀንም ለምድር ወገኖቸ ሁሉ የእግዚአብሔርን በረከት እንደሚያስተላልፍ ተስፋ እንደተሰጠው ታስታውሳላችሁ፡፡ ከዚህም በበለጠ፣ በአብርሃም ታሪኮች ውስጥ፣ በረከቱን ለሁሉም የሰው ዘር የሚያስተላልፍበት መሣሪያው አድርጎ እዚህም እዚያም እንደተጠቀመበት እናያለን፡፡
የዘፍጥረት ቀደምት ተደሲያን ስለ እነዚህ ሁኔታዎች ሲረዱ፣ በእነርሱ ዘመን በሚገጥሟቸው ሁኔታዎች ውስጥ የሚያንጸባርቁባቸውን ዕድሎች ያገኛሉ፡፡ ከተለያዩ የአህዛብ ወገኖች ጋር በሚገናኙበት ወቅት ለዓለም ሁሉ የእግዚአብሔር በረከት መተላለፊያ መንገድ ሆነው ስለሚያገለግሉባቸው መንገዶች ምሪትን ያገኛሉ፡፡ በእርግጠኝነትም ከጠላቶቻቸው ይጠበቃሉ ደግሞም ለጎረቤቶቻቸው የእግዚአብሔርን መንግሥት በረከቶች ለማዳረስ ወደፊት ይገሰግሳሉ፡፡
በተመሳሳይም መንገድ፣ ዛሬም እኛ ክርስቲያኖች እነዚህን ጭብጦቸ በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል፡፡ እኛም የእግዚአብሔር ጥበቃ በዙሪያችን አለ ደግሞም የእግዚአብሔርን መንግሥት እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ በማድረስ ለምድር ወገኖች ሁሉ በረከት ለመሆን ብርታትን እናገኛለን፡፡
ማጠቃለያ
በአብርሃም ሕይወት ዘመነኛ ተዛምዶ ላይ በሚያተኩረው በዚህ ትምህርት፣ በአባታችን ሕይወት ላይ የሚያጠነጥኑት የዘፍጥረት ምዕራፎች ለዛሬው የእኛ ዓለም እንዴት አግባብነት እንዳላቸው መርምረናል፡፡ በመጀመሪያ፣ ክርስቲያኖች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መቅረብ ያለባቸው ወደ አብርሃም ታላቅ ዘር ወደ ክርስቶስ በማትኮር መሆኑን አስምረንበታል፡፡ በአብርሃም ሕይወት የምናያቸውን ጭብጦች ክርስቶስ የፈፀመባቸውን መንገዶች ይመለከታል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ የአብርሃም ሕይወት እንዴት በቤተክርስቲያንም፣ በአብርሃም የወል ዘር ተግባራዊ እንደሚሆንም አይተናል፡፡ በክርስቶስ ውስጥ ያሉ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በእነዚህ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች አስተምህሮ መሠረት እንዴት መኖር እንዳለባቸው ተመልክተናል፡፡
በዘፍጥረት ውስጥ የሚገኘውን የአብርሃምን ሕይወት በበለጠ ቅርበት ስንመለከት፣ የአባታችንን ሕይወት በዛሬው ሕይወታችን የምናዛምድባቸውን በርካታ እድሎች እናገኛለን፡፡ ሙሴ ስለ አባታችን አብርሃም የጻፈው ታሪክ ልባችንን የሚስበው ወደ አባታችን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ አብርሃም ዘር ወደ ክርስቶስም፣ ደግሞም እኛም በክርስቶስ የአብርሃም ልጆች ለአብርሃም የተሰጡ ተስፋዎች ወራሾች ወደሆንንበት አስደናቂ ማንትነም ጭምር ነው፡፡
Continue reading the full transcript