ከተመሳሳይ ተከታታይ ትምህርት 1 ጋር የተያያዘ ቪዲዮ ሲሆን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠይቃል: ስለ ጳውሎስ ዳራ ምን ዝርዝሮች እናውቃለን? ጳውሎስ የድሮውን ኪዳን በእምነት በክርስቶስ ተካውታልን? የሪፎርም ወግ ስለ ኦሪት ኪዳን እና አዲስ ኪዳን ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? ጌንታውያን በክርስቶስ ውስጥ እንደ አይሁዶች እና ፍጹም ህግ-አክባሮች ሊቆጠሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ክርስቲያኖች የክርስቶስን ደረጃ እንዴት ይቀበላሉ? ፍጹም በክርስቶስ ውስጥ ከተቆጠሩ፣ ኢየሱስ ፍጹም እንድንሆን የገሠመንት ለምን ነው? ተፈጥሮአዊ እና ከተፈጥሮ በላይ የሆኑ ነገሮች በሯን ውስጥ እንዴት ይገናኛሉ? እግዚአብሔር ምድርን ይመልሳል ወይንስ ያጠፋታል? ክርስቶስ በአከባቢዎቹ ውስጥ እንዴት ይገኛል? የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ስለ ክርስቶስ መመለስ መዘግየት ምን ይ感じ ነበር? የክርስቶስ መመለስ መዘግየት በየቀኑ ክርስቲያዊ ሕይወት ላይ እንዴት ይጎዳል? ሰዎች ሁሉን ለመሆን ስንት መንገድ ልንሄድ ይገባናል? ጳውሎስ ሁሉንም የድሮ ኪዳን ትምህርቶችን ተቀብሏል ወይንስ የተወሰኑትን ብቻ? ዘመናዊ የመልዕክት ስልቶች በጳውሎስ ምሳሌ ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው? ክርስቲያኖች ከሌላው በቅድነት ሊለያዩ ይችላሉ? ቲዮሎጂያችን አካዴሚያዊ ወይንስ ተግባራዊ መሆን አለበት? በመማሪያ ቤት ውስጥ የመንፈሳዊነትን ለመጠበቅ አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች ምንድናቸው? የጳውሎስን ቲዮሎጂ እንደገና መገንባት አደገኛ ነው? ምናብችን Scripture ን እንድንረዳ እንዴት ሊረዳን ይችላል?
From the transcript
ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡
ከዚያ ቀደም አይታችሁት የማታውቁትን አንድ ጎኑን በድንገት አይታችሁ ድንግጥ ያላችሁበት፣ ከዚያ ቀደም ግን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ ብላችሁ የምታስቡት ጓደኛ ኖሯችሁ ያውቃል? ክርስቲያኖች ስለ ሐዋርያው ጳውሎስ ጠለቅ ያለ ጥናት ሲጀምሩ ይህን መሳይ ነገር ደጋግሞ ይገጥማቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ከጳውሎስና ከመልእክቶቹ ጋር ጠንቅቀው ተዋወቃሉ፡፡ በእርሱ ደብዳቤዎች ላይ የተመሠረቱ በርካታ መልእክቶችን ሰምተናል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንንም አዘውትረን የምናተኩረው በእነርሱ ላይ ነው፡፡ በበርካታ መንገዶቻችን፣ ስለ እርሱ የሚሰማን ልክ የቅርብ ወዳጃችን እንደሆነ ዓይነት ነው፡፡ ስለ ጳውሎስ ሕይወትና ስለ ነገረ-መለኮቱ ጠለቅ ያለ ጥናት ያደረጉ በርካታ ክርስቲያኖች ግን በሚያገኙት ነገር ይገረማሉ፡፡
በዚህ ተከታታይ ትምህርታችን፣ የጳውሎስን ነገረ-መለኮት፣ እንመረምራለን፡፡ ይህንን የመጀመሪያውንም ትምህርት፣ “ጳውሎስና ነገረ-መለኮቱ” የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ በነገረ-መለኮቱ ውስጥ የሚገኙትን ወሳኝ ውቅረ-ነገሮች ለማግኘት ያስችለን ዘንድ ይህንን ጥናት የምንጀምረው የጳውሎስን ሕይወትና ጽሑፎቹን በመመልከት ይሆናል፡፡
ሦስት ዋና ጉዳዮችን እንዳስሳለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የእርሱን ክርስቲያናዊ የእምነት አቋም ምንያህል ተፅዕኖ እንዳሳደሩበት ለማየት፣ የጳውሎስን ዳራ ወሳኝ ገፅታዎች እንመረምራለን፡፡ ሁለተኛ፣ የጳውሎስ የእምነት አቋም ከሐዋርያዊ አገልግሎቱ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ እንመለከታለን፡፡ ሦስተኛ፣ ጳውሎስ ሌሎችን በሚያስተምርበት ወቅት አስተምህሮውን የመሠረተባቸውን ወሳኝ ሃሳቦች በመቃኘት የጳውሎስን ማዕከላዊ ነገረ-መለኮታዊ አመለካከት እናያለን፡፡ አስቀድመን የጳውሎስን ባህላዊ ዳራ በመመልከት እንጀምር፡፡
አብዛኞቻችን ከልምዳችን እንደምንገነዘበው ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ራሳችን እና በዙሪያችን ስላለው ዓለም በሚኖረን እምነትና አመለካከት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ነገረ መለኮትን እንዲያው በአየር ላይ የገነባ ማንም የለም፣ ስለዚህም ጉዳዩ ለጳውሎስም እውነትነት አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስን ወደ ትክክለኛው የክርስትና እምነት የመራው ቢሆንም፣ እርሱን ወደ እውነት በመምራቱ ሂደት ውስጥ የጳውሎስን ዳራ ልዩ ልዩ ገፅታዎችን መንፈሱ ተጠቅሞባቸዋል፡፡ እናም እኛ የጳውሎስን ነገረ-መለኮት መረዳት የምንፈልግ ከሆነ፣ ከሕይወቱ ጋር መተዋወቅ ይገባናል፡፡
የሚያሳዝነው፣ ስለ ጳውሎስ አስተዳደግ ብዙ የምናውቀው ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ ሆኖም በሁለት ጠንካራ ባህላዊ ተፅዕኖዎች ስር እንዳደገ ግን እናውቃለን፡፡ በአንድ ወገን፣ የአይሁድ ባህል በእጅጉ ተፅዕኖ አሳድሮበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከአህዛብ ጋር በተለይም ከግሪኮ ሮማዊው ባህል ጋር የነበረው ቀረቤታም እንደዚያው በእጅጉ ተፅዕኖ አድርጎበታል፡፡
ከአይሁድ ወገን መሆኑ በጳውሎስ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ ዝቅተኛ ግምት ከሰጠነው፣ የጳውሎስን ነገረ-መለኮት ማእከላዊ ሃሳብ መሳታችን አይቀሬ ነው፡፡ ለእርሱ የትውልድ ሃረጉ በበርካታ መንገዶች እጅግ ወሳኝ እንደሆነ እናያለን፡፡ በአንድ በኩል፣ ጳውሎስ ወደ ክርስትና ከመምጣቱ አስቀድሞ ከአይሁድ ወገን ስለመሆኑ እጅግ ከፍተኛ ስፍራ ይሰጥ እንደነበረ የአዲስ ኪዳን ዘገባዎች በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡ ከመለወጡ በፊት ስለነበረው የወጣትነት ዘመኑ ራሱ የሰጠው መግለጫ ለይሁዲነት በብርቱ ራሱን የሰጠ እንደነበር ያስረዳናል፡፡ ለምሳሌ፣ በፊልጵስዩስ 3፡5፣ ጳውሎስ እንዲህ ነበርሁ ይላል፡
በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ (ፊልጵስዩስ 3፡5)
ጳውሎስ አክራሪ ሃይማኖተኛ ነበር፣ የእስራኤልንም ትውፊት ጠብቆ ለማቆየት ራሱን የሰጠና በብርቱም የሚከታተል ሰው ነበር፡፡ በገላትያ 1፡14 ራሱን እንዴት እንደገለጠ አድምጡ፡
ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። (ገላትያ 1፡14)
እንዲያውም፣ ጳውሎስ ከመለወጡ አስቀድሞ ለይሁዲነት የነበረው ቀናዒነት እጅግ ብርቱ ስለነበር የክርስቲያኖቹን ቤተክርስቲያን እንደ ስህተት አስተምህሮ በመቁጠር በብርቱ ያሳድድ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ጳውሎስ በይሂዲነት ትውፊት በጣም የተማረ ነበር፡፡ እንደ ሐዋርያት ሥራ 22፡3 አገላለጽ፣ በኢየሩሳሌም ከነበሩ እውቅ መምህራን አንዱ በሆነው፣ በገማልያል እግር ስር ተቀምጦ የተማረ ነበር፡፡ ጳውሎስ ከጭፍን አክራሪነት እጅግ የራቀና በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ፣ በአይሁድ ነገረ-መለኮትና የቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት የመጠቀ ነበር፡፡
የጳውሎስ አይሁዳዊ ባህል ለእርሱ እጅግ ጠቃሚ የነበረው ወደ ክርስትናው ከመምጣቱ አስቀድሞ ብቻ አልነበረም፤ ከመለወጡም በኋላ ለዚያው የባህል በእጅጉ ራሱን የሰጠ ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ ክርስቲያንም ሆኖ እንኳን በርካታ የአይሁድ ወጎችን ይጠብቅ ነበር፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ 9፡20 እንዲህ ብሏል፡
አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ (1ኛ ቆሮንቶስ 9፡20)
ክርስቲያኑ ጳውሎስ የአባቶቹን ወግ በጥንቃቄ ይጠብቅ እንደ ነበር አዲስ ኪዳን በርካታ ስፍራዎች ላይ አስፍሮ እናገኛለን፡፡ ጳውሎስ በክርስቶስ በማመኑ ምክንያት አይሁድ በብርቱ ካሳደዱት በኋላም እንኳን፣ ጳውሎስ ለዘሩ እጅግ ቀናዒ ከመሆኑ የተነሳ እነርሱ ይድኑ ዘንድ ብርቱ ናፍቆት ነበረው፡፡ ለምሳሌ፣ በሮሜ 9፡2-5 እንዲህ ጽፏል፡
ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል።
በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና።
እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤
አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን። (ሮሜ 9፡2-5)
የጳውሎስን አይሁዳዊ ዳራ ወሳኝነት በልቡናችን ይዘን፣ አሁን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፡ የጳውሎስ አይሁዳዊ ዳራ በክርስቲያናዊ ነገረ-መለኮቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው? በበርካታ መንገዶች፣ ይህ ተፅዕኖ በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ በእያንዳንዱ ገጽ ውስጥ በግልጽ የሚታይ ሲሆን፣ ሁለቱን ጉዳዮች ግን ለየት አድርጎ መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
አንደኛ፣ እንደ አይሁድነቱና እንደ አይሁዳዊ ክርስቲያንነቱ፣ ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ያምናል፡፡ ያለ ምንም መቆጠብ ይታመንባቸዋል ራሱንም ይሰጣል፡ ጳውሎስ በምንም መንገድ ከብሉይ ኪዳን አስተምህሮ ጋር በሚቃረን ነገር አያምንም፡፡ የሚያሳዝነው ግን፣ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ደግሞም ዛሬ በእኛ ዘመን፣ አንዳንድ የነገረ-መለኮት ምሁራን ጳውሎስ የብሉይ ኪዳንን አስተምህሮ በክርስቶስ ባገኘው አዲስ እምነት ተክቶታል የሚል ሃሳብ መሰንዘራቸው ነው፡፡ ሆኖም ምንም ነገር ከእውነቱ ሊርቅ አይችልም፡፡ ጳውሎስ እስራኤል ታራምድ በነበረው የብሉይ ኪዳኑ አንድ አምላክ አምላኪነት ስሩን የሰደደ ሲሆን፣ በዕብራውያኑ ቅዱሳት መጻሕፈት በተዘረዘሩት የሞራል ህግጋት በሙሉ ልቡ ያምናል፡፡ ስለ ጳውሎስ ምንም እንበል ምን፣ በእርግጠኝነት የምናውቀው አንድ ነገር ቢኖር፣ የክርስትና እምነቱ ለአንድም ሰከንድ እንኳን ከብሉይ ኪዳን ጋር እንዲያነጣጥለው እንደማይፈቅድ ነው፡፡ ይልቁኑ፣ ለክርስቶስ ያለው መሰጠት ለቅዱሳት መጻሕፍቱ ያለውን ቁርጠኝነት አጠንክሮታል፡፡ በ2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡14 ለእምነት ልጁ ለጢሞቴዎስ ብሉይ ኪዳንን አስመልክቶ የሰጠውን መመሪያ አድምጡ፡
አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤
ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡14)
የእብራውያኑ መጽሐፍ ቅዱስ የጳውሎስም ቅዱስ መጽሐፍ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ፣ ጳውሎስ እግዚአብሔር አንድ ቀን፣ የዳዊት ታላቅ ልጅ የሆነውን እና የእስራኤልን መከራ አስወግዶ የእግዚአብሔርንም መንግሥት በአህዛብ መንግሥታት መካከል የሚያሰፋውን መሲህ እንደሚልክ የሚያስተምረውን የአይሁድን እምነት አጥብቆ ይከተል ነበር፡፡ እንዲያውም፣ ጳውሎስ ወደ ክርስትና የመጣበት ዋናው ምክንያት ኢየሱስ ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የነበረው መሲህ እንደሆነ በማመኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጳውሎ ኢየሱስን ክርስቶስ Christos (Cristo,j) ይህም የዕብራይስጡ መሲህ Meshiach የሚለው ቃል የግሪኩ አቻ ፍቺ ነው፡፡ ጳውሎስ ክርስትናን የይሁዲነት ምትክ አድርጎ አይመለከተውም፡፡ ይልቁኑ፣ ክርስትና ኢየሱስ እውነተኛው መሲህ እንደሆነ እውቅና የሚሰጥ የይሁዲነት ቅርንጫፍ ነው ብሎ ነው የሚያምነው፡፡
ለቅዱሳት መጻሕፍት ፍጹም መሰጠትና በመሲሁ ላይ ተስፋን ማድረግ፣ እነዚህ ሁለት የአይሁድ እምነት ምሰሶዎች ለጳውሎስ ክርስቲያናዊ አመለካከት እጅግ ወሳኝነት ያላቸው አድማሶች ናቸው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም በርካታ መንገዶች፣ የጳውሎስ ማእከላዊ ክርስቲያናዊ እምነቱ በአይሁድነቱ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
ሆኖም ግን ጳውሎስ ተፅዕኖ ያደረበት በአይሁድነቱ ብቻ አልነበረም፡፡ ጳውሎስ ከአህዛብ ባህል ጋር የነበረውን ትስስር ነገረ-መለኮቱን ቅርጽ ለማስያዝ መንፈስ ቅዱስ ተጠቅሞበታል፡፡
የአህዛብ ባህል
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጳውሎስ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በአይሁዶቹ ፓለስታይን ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ የአህዛብ ምድሮችም እንደኖረ ልብ ማለት ይገባናል፡፡ እንደ ሐዋርያት ሥራ 22፡39 አገላለጽ፣ ጳውሎስ በኪልቅያ ከምትገኘው ከጠርሴስ ከአህዛብ ከተማ ነበር፡፡ በሐዋርያት ሥራ 22፡3፣ በኢየሩሳሌም እንዳደገ እናነብባለን፡፡ ሆኖም ሐዋርያት ሥራ 9፡30 እና 11፡25 እንደሚያሳየን ጳውሎስ ካደገ በኋላ በጠርሴስ ኖሯል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ ጳውሎስ ከአህዛብ ዓለም ጋር የነበረው ትስስር ይበልጥ ሰፍቶ የተገለጠው የሮማዊ ዜግነት መብት ተጠቃሚ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲያውም፣ እንደ ሐዋርያት ሥራ 22፡28 አገላለጽ፣ ዜግነቱን ያገኘው በገንዘብ ሳይሆን፣ በመወለድ ነበር፡፡ ጳውሎስ ወንጌልን ከማስፋፋትና ራሱንም ከመመከት አንፃር በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በብዙ ስፍራ ሮማዊ ዜግነቱን በብርቱ ሲጠቀምበት እናገኛለን፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ጳውሎስ ለአህዛብ አብያተክርስቲያናት የጻፋቸው መልእክቶች እንደሚያሳዩን የአህዛብ ልማዶቹን ስለ ክርስቲያኖቹ ወንጌል ጥቅም ሲል ሊጠብቃቸው ፈቃደኛ ነበር፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ 9፡21 ውስጥ፣ ይህንን ተጠቃሽ አዋጅ ያውጃል፡
ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ሕግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ (1ኛ ቆሮንቶስ 9፡21)
ጳውሎስ የክርስቶስን ህግ መጠበቁን ሳይተው፣ ባህርዩ ከአህዛብ ወግ ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ያስችለው ዘንድ የአህዛብን ባህል ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡
በመጨረሻ፣ ጳውሎስ ከዚህም ባሻገር ከአህዛቡ ውስብስብ የስነ-ጽሑፍ ልማድ ጋር ቅርበት እንዳለው አድርጎ ራሱን ያቀርባል፡፡ የሐዋርያት ሥራ 17፡28 እና ቲቶ 1፡12 በመሳሰሉት ክፍሎች፣ ጳውሎስ የአህዛብን ፈላስፎች ያነሳል ከእነርሱም ይጠቅሳል፡፡ በግሪኮ ሮማውያኑ ዓለም ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች የተማረ ነበር፡፡
እንግዲህ አሁን፣ ጳውሎስ ስለ አህዛብ ባህል የነበረው እውቀት ምን ተፅዕኖ አሳደረበት? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ጳውሎስ ለአህዛቡ ባህል የነበረው ተጋላጭነት ተፅዕኖ ያሳደረበት እንዴት ነው? ከሁሉ አስቀድሞ፣ አንዳንዶች እንደሚሉት፣ ጳውሎስ ለአህዛቡ ባህል የነበረው እውቀት ክርስትናን በአህዛቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጎ ለማቅረብና ለማላቅ እንደጠቀመው አድርገን ማሰብ አይገባንም፡፡ በመሠረታዊ ግንዛቤው አይሁድነቱን ጠብቆ ዘልቋል፡፡ ሆኖም፣ ቢያንስ በሁለት መንገዶች ከአህዛቡ ዓለም ጋር የነበረው ትስስር ተፅዕኖ አሳድሮበታል፡፡ በአንድ ወገን፣ ከቤተክርስቲያን ውጪ አህዛብን እንዲያገለግል አስታጥቆታል፡፡ ከብዙዎቹ በተሻለ መንገድ፣ የአህዛብን እሴቶችና ልማዶች ያውቃል፣ ወንጌልንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ለእነርሱ ለማቅረብ ዝግጁ አድርጎታል፡ በሮሜ 11፡13 ጳውሎስ ራሱን፣ “የአህዛብ ሐዋርያ” ብሎ ሲጠራ የምናነብበው ለዚህ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ውስጥም አህዛብን ለማገልገልና ስለ እነርሱም ለመከራከር ዝግጁ ነበር፡፡ እንዲያውም፣ ጳውሎስ የነበረው የአህዛብ አገልግሎቱ፣ በመጀመሪያዪቱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተከስቶ በነበረው አህዛብን እንዲገረዙ እናስገድድ አናስገድድ በሚለው ውዝግብ ውስጥ ከትቶታል፡፡ የሐዋርያት ሥራ 15 እንደሚያሳየን፣ አህዛብ ሊገረዙ እንደማይገባ ሐዋርያቱንና ሽማግሌዎችን ከማሳመን አንፃር ጳውሎስ ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡ እናም በገላትያ መልእክቱ፣ አህዛብ በግርዘት ሥርዓት ውስጥ የማለፍ ግዴታ እንደሌለባቸው በብርቱ ተሟግቶ ጽፏል፡፡ ይህ አንድ ሙግት፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ለነበሩ የአህዛብ አማኞች ጳውሎስ የነበረውን ልብ ሰፋ አድርጎ አሳይቶናል፡፡ በእርሱ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁድ ክርስቲያኖች አህዛብን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲቆጥሩ፣ ጳውሎስ ግን ክርስቶስ በአይሁድና በአህዛብ መካከል የነበረውን ግድግዳ አፍርሶታል በማለት ይሟገታል፡፡ በገላትያ 3፡28-29 እንዲህ ጽፏል፡
አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።
እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ። (ገላትያ 3፡28-29)
ኢየሱስ የድነትን በር ለአህዛብ መንግሥታት ብርግድ አድርጎ ከፍቶታል ስለዚህ በክርስቶስ ያለ የትኛውም አህዛብ በእግዚአብሔር ዐይኖች አይሁዳዊ ደም እንዳለውና ህጉንም ጠንቅቆ እንደሚፈፅም ሰው እንደሚቆጠር የአብዛኞቹ የጳውሎስ መልእክቶች ማዕከላዊ መሪ ሃሳብ ነው፡፡
የጳውሎስ አይሁዳዊና አህዛባዊ ዳራው በበርካታ መንገዶች ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ተመልክተናል፡፡ ይህንን መንታ ዳራ በልቡናችን ይዘን፣ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት እንዴት ከአገልግሎቱ ጋር እንደሚያያዝ እንመለከታለን፡፡
ሐዋርያዊ አገልግሎት
ወደፊት እንደምንማረው፣ ጳውሎስ ለቤተክርስቲያን ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ነገረ-መለኮቱን ደጋግሞ የሚያመለክትና በሚያምንበትም ነገር በጥልቀት የተነካ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ በዚህም ምክንያት፣ የአገልግሎቱን የተለያዩ አድማሶች መመልከት ይገባናል፡፡ በተለይም የጳውሎስን አገልግሎት ሦስት ገጽታዎች እንመለከታለን፡ የሐዋርያነት ቢሮው፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮው እና ሐዋርያዊ ጽሑፎቹ ናቸው፡፡
ቢሮው
ቢያንስ ለሃያ ጊዜያት ያህል፣ ጳውሎስ ራሱን “ሐዋርያ” በማለት የጠቀሰ ሲሆን፣ ያንንም “የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ” በሚል መመዘኛ አስቀምጦታል፡፡ ይህ የሐዋርያነት መግለጫ እጅግ ወሳኝነት አለው ምክንያቱም ኢየሱስ እርሱን ወክለው በሙሉ ሥልጣን ለቤተክርስቲያን እንዲናገሩ ሐዋርያትን ሾሟልና ነው፡፡ ጳውሎስ ኢየሱስ በምድር አገልግሎቱ ዘመን ከመረጣቸው የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት መካከል እንዳልነበረ ሁላችን እናውቃለን፡፡ ሆኖም፣ ጳውሎስ የክርስቶስ ባለሙሉ ሥልጣን ወኪል ነኝ ይላል፡፡ ከቀደሙት ሐዋርያት እኩል የሐዋርያነት ሥልጣን ተቀብያለሁ ይላል ጳውሎስ፡፡ ይህ ግን እንዴት ሊሆን ይችላል? መልሱ የሚያርፈው ጳውሎስ ለሐዋርያነት የተቀመጡትን መመዘኛዎች የሚያሟላ በመሆኑ እውነታ ላይ ነው፡፡
ሐዋርያቱ በበዓለ-ማምሳ ዕለት የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ይጠባበቁ በነበረ ወቅት፣ ይሁዳን የሚተካ አዲስ ሐዋርያ ሊኖር እንደሚገባ ጴጥሮስ ገልጧል፡፡ ስለዚህም ጴጥሮስ የኢየሱስ ሙሉ ሥልጣን ያለው ሐዋርያ ቢያንስ ሦስት መመዘኛዎችን ሊያሟላ ይገባዋል፡፡ አንደኛ፣ እንደ ሐዋርያት ሥራ 1፡21 አገላለጽ፣ በኢየሱስ የምድር አገልግሎት ዘመን በቀጥታ ከኢየሱስ የተማሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ሁለተኛ፣ በሐዋርያት ሥራ 1፡22 እንደምናነብበው፣ የኢየሱስ ትንሣኤ ምስክሮች ሊሆኑ ይገባል፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ በሐዋርያት ሥራ 1፡23-26 እንደምናገኘው፣ አዳዲስ ሐዋርያት ለሐዋርያነት በጌታ በራሱ ሊመረጡ ይገባል፡፡
ግን የጳውሎስስ ነገር? መጀመሪያ ስንመለከተው፣ የመጀመሪያውን የሐዋርያነት መመዘኛ አያሟላም፣ እንዲያውም፣ ኢየሱስን በምድር አገልግሎቱ ዘመን አልተከተለውም፡፡ ግን ረጋ ብለን በጥልቀት ስንመለከት፣ ለሐዋርያነት ብቁ የሚያደርገውን እናገኛለን፡፡ በገላትያ 1፡11-18፣ ጳውሎስ ከመለወጡ በኋላ ወዲያውኑ በዐረብ ምድረ በዳ ሦስት ዓመታትን እንዳሳለፈ ይዘግብልናል፡፡ የጊዜው ርዝማኔ ሌሎቹ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር በምድር ካሳለፉት ዘመን ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።
(ገላትያ 1፡11-12)
ጳውሎስ በተጨማሪም ሁለተኛውንም መመዘኛ ያሟላል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 9፡1-6፣ ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን እንዳየ እናነብባለን፡፡ ከሞት የተነሣውን አዳኝ አይቶታል፡፡ በመጨረሻም፣ እንደ ሐዋርያት 9፡15 አገላለጽ፣ ኢየሱስ ራሱ ጳውሎስን ለቢሮው ሾሞታል፡
ጌታም፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ (የሐዋርያት ሥራ 9፡15)
ምናልባት ስለ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥልጣን ጥርጣሬ ቢኖር፣ ገላትያ 2፡7-8 እንደሚነግረን የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ለሐዋርያነት መጠራቱን አረጋግጠዋል፡፡ ጳውሎስ እንደፃፈው፣
ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤
ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና።
ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ (ገላትያ 2፡7-9)
የተቀሩትም ሐዋርያት የጳውሎስ ሐዋርያነት ከጴጥሮስ ጋር ተስተካካይ እንደሆነ እውቅና ሰጥተዋል፡፡ በ2ኛ ጴጥሮስ 3፡15-16 ጴጥሮስ የተናገረውን አድምጡ፡
የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ።
በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። (2ኛ ጴጥሮስ 3፡15-16)
እንደ ጳውሎስ አገላለጽ፣ የጳውሎስ መልእክቶች “ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት” ጋር በእኩል ይታያሉ፡፡
በመጀመሪያዪቱ ቤተክርስቲያን የጳውሎስን አስተምህሮ ይቃወሙ የነበሩ በርካታ የሐሰት መምህራን ነበሩ፡፡ ስለዚህ፣ እነዚያን የሐሰት አስተምህሮዎች ለማፍረስ አዲስ ኪዳን ጳውሎስ ትክክለኛ ሐዋርያ ለመሆኑ እውቅና ይሰጣል፡፡ ከዚህም በበለጠ፣ ጳውሎስ ለመረዳትና ለመቀበል አዳጋች የሆኑ አመለካከቶችን ለቤተክርስቲያን አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም፣ ጳውሎስ የክርስቶስ አምባሳደርነት ተግባሩን ሲወጣ፣ ለሌሎቹ ሐዋርያት በተሰጠው ሥልጣን ይናገር ደግሞም በቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ይጽፍ ነበር፡፡ ማንም ሰው ምንም ቢል ምን፣ አመለካከቶቻቸው ይዳኙ የነበረው በጳውሎስ ትምህርቶች መሠረት ነበር፡፡ ጽሑፎቹ የክርስቶስን የራሱን ሥልጣን የተሸከሙ ነበሩ፡፡ ጳውሎስን ሳንከተል ኢየሱስን ልንከተል አንችልም፡፡ በዚህም ዘመን እንኳን የታመኑ ክርስቲያኖች ነገረ-መለኮታቸውን ከእርሱ ጋር ያጣጥማሉ፡፡
ተልዕኮ
የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን በልቡናችን ይዘን፣ አሁን ደግሞ ሐዋርያዊ ተልዕኮውን መመልከት ይገባናል፡፡ ጳውሎስ እንደ ሐዋርያ ምን አደረገ? ሥራውስ ምን ነበር? ጳውሎስ ስለሠራው ሥራ ጥሩ መረጃ ለማግኘት ሦስቱን ሚሲዮናዊ ጉዞዎቹን እና ወደ ሮም ያደረገውን ጉዞ መመልከት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አስቀድመን፣ እንደ ክርስቶስ ሐዋርያ ያደረገውን የመጀመሪያ ጉዞ በወፍ በረር እንመልከት፡፡
የመጀመሪያ ጉዞ
ስለ ጳውሎስ የመጀመሪያ ሚሲዮናዊ ጉዞ የምናገኘው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 13 - 14 ውስጥ ነው፡፡ የሚጀምረውም እግዚአብሔር ጳውሎስንና በርናባስን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ ብሎ ለሶርያዋ አንጾኪያ ቤተክርስቲያን ከተናገረ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ወዲያውኑ፣ መንፈስ ቅዱስ በቆጵሮስ በኩል መራቸው፡፡ በዚያም በርካታ አገልግሎቶችን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ትንሿ እስያ የወንጌል ጉዞ አደረጉ፡፡ የጳውሎ የመጀመሪያ ልማዱ የነበረው ወንጌልን በአይሁድ ምኩራቦች መስበክ ነበር፡፡ ሆኖም ከአይሁድ ጠንካራ ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ፣ ለአህዛብም መስበክ ጀመረ፡፡
ጳውሎስ በዚህ ጉዞው በርካታ አብያተክርስቲያናትን በውጤታማነት ተከለ፣ በገላትያ አውራጃም ጥቂቶችን መትከሉን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ጳውሎስና በርናባስ በስተምሥራቅ ወደ ምትገኘው ደርቤ ድረስ በመዝለቅ ከተጓዙ በኋላ፣ ተመለሱ፡፡ ከዚያም በስተመጨረሻ በገላትያ ከተሞች በኩል በማቋረጥ ወደ ባህሩ ደረሱ ከዚያም ወደ ቤታቸው በመርከብ ተመለሱ፡፡
ጳውሎስ እንደ ክርስቶስ ሐዋርያ ያደረገው የመጀመሪያ ጉዞ በንጽጽር አጭርና ያልተወሳሰበ ነበር፡፡ ሁለተኛው ጉዞው ግን ከፓለስታይን ምድር ራቅ ወዳሉ ስፍራዎች ወሰደው፡፡
ሁለተኛው ጉዞ
የጳውሎስ ሁለተኛው ሚሲዮናዊ ጉዞ የሚገኘው በሐዋርያት ሥራ 15፡36-18፡22 ውስጥ ነው፡፡ ይህ ጉዞ የተጀመረው በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትና የቤተክርስቲያን መሪዎች በአንጾኪያ፣ በሶርያ፣ በኪልቅያ እና በገላትያ ለሚገኙ አብያተክርስቲያናት ደብዳቤ እንዲያደርሱ ጳውሎስና በርናባስ ከተመረጡ በኋላ ነበር፡፡ የደብዳቤውም ሃሳብ አህዛብ አማኞች ድነትን ለማግኘት መገረዝም ሆነ የሙሴን ህግ መፈጸም እንደማይገባቸው የሚያብራራ ነበር፡፡
ጉዞው ከመጀመሩ አስቀድሞ ግን፣ ጳውሎስ ከበርናባስ ጋር ሳይስማማ ቀረ፣ ስለዚህ መንገዳቸው ተለያየ እናም ጳውሎስ ከሲላስ ጋር ተቧደነ፡፡ ሁለቱም በሶርያና በኪልቅያ በኩል አድርገው ገላትያ እስኪደርሱ ድረስ ተጓዙ፡፡ ጢሞቴዎስ የጳውሎስን ጉዞ የተቀላቀለው በዚያው አውራጃ በልስጥራን ነበር፡፡
ጳውሎስም በመቀጠል፣ ወንጌልን ለሰሜናዊው እስያና ለቢታንያ ለመስበክ ፈልጎ ነበር፣ መንፈስ ቅዱስ ግን ከለከላቸው፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስ ጢሮአዳ ወደተሰኘችው የወደብ ከተማ ሄደ፡፡ በዚያም መንፈስ ቅዱስ ጳውሎን የከለከለበት ምክንያት ታዋቂ በሆነው የጳውሎስ “የመቄዶኒያ ራእይ” ግልጽ ሆነ፡፡ በዚህ ራእይ፣ አንድ ሰው በሰሜናዊው የግሪክ ግዛት፣ በመቄዶኒያ ወንጌልን እንዲሰብክ ይለምነው ነበር፡፡ ስለዚህም ጳውሎና ቡድኑ ፈጥነው ለራእዩ ምላሽ በመስጠት ወደ ግዛቲቱ በመርከብ ተሳፈሩ፡፡ ጳውሎስ በግሪክ በርካታ አብያተክርስቲያናትን ተክሏል፣ በፊልጵስዩስና በስተሰሜን የምትገኘው ተሰሎንቄም ይካተታሉ፡፡
በመጨረሻም፣ ወደ ደቡብ በማቅናት፣ አቴንስን በመጎብኘት በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ተከለ፡፡ ጳውሎስ ከዚያም ወደ ኤፌሶን አቀና፣ በዚያም ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ወደ ፓለስታይን ምድር ለመመለስ መንገዱን አቀና፡፡
ሦስተኛ ጉዞ
የጳውሎስ ሁለተኛ ጉዞ ብዙም ሳይቆይ፣ ሦስተኛውንና ወደ ሩቅ ምዕራብ በድጋሚ ያደረገውን ጉዞ አስከተለ፡፡ ሦስተኛው የጳውሎስ ሚሲዮናዊ ጉዞ የሚገኘው በሐዋርያት ሥራ 18፡23-21፡17 ውስጥ ነው፡፡ በእነዚህ ጉዞዎች ጳውሎስ ከሶርያዋ አንጾኪያ ተነስቶ በገላትያና በፍርግያ በኩል አልፎ በኤፌሶን የዳበረ አገልግሎትን ሰጠ፡፡ ከዚህም በኋላ፣ ለበርካታ ወራት በግሪክ ከሰሜን ወደ ደቡብ እንደገናም ወደ ሰሜን በመመላለስ አሳለፈ፡፡ በዚያም ወቅት አስቀድሞ በአካባቢው ተክሏቸው የነበራቸውን አብያተክርስቲያናት እየዞረ ጎበኘ፡፡ ከዚያም ሐዋርያው በምድርና በባህር በመጓዝ ወደ ኢሩሳሌም ተመለሰ፡፡
ጳውሎስ ከሦስተኛው ጉዞው በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ፣ አይሁድ ህዝብን አሳምፆአል በማለት በሐሰት ከሰሱትና ሮማውያን አሰሩት፡፡ ሁለት ዓመታትን በእስር ካሳለፈ በኋላ፣ ጳውሎስ ሮማዊ ዜግነቱን በማንሳት ጉዳዩ በቄሳር ፊት እንዲታይለት ይግባኝ አለ፡፡ ይህ ለቄሳር ያቀረበው ይግባኝ እርሱን ወደ ሮም ለወሰደው የአራተኛው ጉዞ መነሻ ሆነ፡፡
አራተኛ ጉዞ
ይህ ጉዞ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 27 እስከ 28 ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ጳውሎስ አብዛኛውን ጉዞውን የተጓዘው በመርከብ ነበር፡፡ በቀርጤስና በመላጥያ ደሴት መካከልም ጳውሎስንና ሌሎች እስረኞችን አሳፍራ የነበረችው መርከብ በማእበል ብትንትኗ ወጣ፡፡ መርከበኞቹ፣ ጠባቂዎቹ፣ ጳውሎስና ጓደኞቹ መርከባቸው ስለተሰበረች ወደ ሮም የምታልፍ መርከብ አስኪያገኙ ድረስ በመላጥያ ደሴት ለሦስት ወራት ተቀመጡ፡፡ ጳውሎስም በ60 እስከ 62 ዓ.ም. ድረስ በቤት እስር ላይ ቆየ፡፡ በዚህ ወቅት በነፃነት ያገለግል ነበር፡፡
ኔሮ ጳውሎስን በነፃ ለቅቆት ስለነበር፣ ወደ ስፔን ተጉዞ ወንጌልን ሰብኮ እንደነበር ትውፊት ይናገራል፡፡ ለጢሞቴዎስና ለቲቶ ከጻፋቸው መልእክቶች የምናገኛቸው አንዳንድ ፍንጮችም ወደ ምሥራቅ በመጓዝ በዚያ አብያተክርስቲያናትን እንደመሠረተና እንዳፀና ያመለክቱናል፡፡ ሆኖም ወደ 65 ዓ.ም. ገደማ ወይም ከዚያ ብዙም ሳይርቅ ኔሮ እንደገና ጳውሎስን አሰረው በመጨረሻም ሐዋርያውን ሰዋው፡፡
በኢየሩሳሌምና በሮም መካከል ያሉትን ግዛቶች ዳስ ስናደርጋቸው ጳውሎስ በርካታ ስፍራዎችን እንደጎበኘ፣ ከሃያ አምስት በላይ በሚሆኑ ከተሞች ከሚገኙ በሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳደረገ ያስረዳናል፡፡ በእነዚህ ተከታታይ ጉዞዎች ጳውሎስ በጽናት ካደረገው ጉዞ እኛ ምን እንማራለን? ስለ ጳውሎስ ነገረ-መለኮትስ ምን የሚነግሩን ነገር አለ?
ከእርሱ ሚሲዮናዊ ጉዞ ስለ ጳውሎስ ነገረ-መለኮት የምንማራቸው በርካታ ነገሮች እንደሚኖሩ ምንም መናገር አያስፈልግም፡፡ አንድ የምንማረው ወሳኝ ነገር ግን የጳውሎስ ነገረ-መለኮት የተሽከርካሪ ወንበር የነገረ-መለኮት ሰውነት እንዳልነበረ ነው፡፡ በእርግጠኝነት፣ ጳውሎስ ጠንቅቆ የተማረና አምሮ ብሩህ ሰው ነበር፡፡ ሆኖም ነገረ-መለኮቱ ሕይወቱን ወደሚሰዋበት አገልግሎት መርቶታል፡፡ ስለዚህ፣ የጳውሎስን ነገረ-መለኮት ስንመለከት፣ ከተግባራዊ አኗኗር በተፋቱ የሃሳብ ጥርቅሞችና እምነቶች ላይ ተረጋግተን አንቀመጥም፡፡ አንድ ሕይወት ለዋጭና ድንቅ ነገርን እስክናገኝ መግፋት ይገባናል፡፡ የጳውሎስን ነገረ-መለኮት በትክክል ስንረዳ፣ እርሱን ለክርስቶስ፣ ለቤተክርስቲያን እና ለዓለም ሁሉ እረፍት የለሽ አገልግሎት ወደ መስጠት እንደመራው ሁሉ እኛንም አቅጣጫ ያስይዘናል፡፡
እንግዲህ አሁን የእርሱን አገልግሎት ሦስተኛ ገፅታ የምንመለከትበት እርከን ላይ ደርሰናል፡፡ እነዚያም የእርሱ ሐዋርያዊ ጽሑፎች ወይም የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ናቸው፡፡
ጽሑፎች
ጳውሎስ የኖረው ባልተቋረጠ የአገልግሎት ሰንሰለት ውስጥ በመሆኑ ምክንያት፣ የሚጎበኛቸውን አብያተክርስቲያናት የሚፈታተኑ ጉዳዮችን ያውቃቸዋል፡፡ እንግዲህ በገላትያ የሚኖረው ጉዳይ ከኤፌሶኑ የተለየ እንደሚሆን ትገምታላችሁ፡፡ በኤፌሶን ያሉ ችግሮች በቆሮንቶስ ካሉ ተግዳሮቶች የተለዩ ናቸው፡፡ የሚሄድበት ስፍራ ሁሉ የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስ መልእክቶቹን ሲጽፍ እነዚያን ሁኔታዎች ሊዳስሱ በሚችሉ መጠን መቀረፃቸ ያሳስበዋል፡፡
በአዲሰ ኪዳን ውስጥ ጳውሎስ ባሳለፋቸው የአገልግሎት ዓመታቶች በተለያዩ ጊዜያት የተፃፉ ዐሥራሦስት የጳውሎ ደብዳቤዎች ይገኛሉ፡፡ የጳውሎስ ደብዳቤዎች ወቅታዊ በመሆናቸው ምክንያት፣ ያም ማለት፣ የተወሰኑ ችግሮችን ለመፍታት በመጻፋቸው፣ የትኞቹም መልእክቶቹ በቅደም ተከተል ወይም በስልታዊ ነገረ-መለኮት መንገድ የተሟላውን ነገረ-መለኮቱን አያሰፍሩልንም፡፡ ይልቁኑ፣ መልእክቶቹ የእርሱን ነገረ-መለኮት መጋቢያዊ አንድምታ ይዘዋል፡፡ በአብዛኛዎቹ መልእክቶቹ በግልጽ እንደምናየው ጳውሎስ የጻፈው በቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረን አንድ ጉዳይ ለመዳሰስ ነበር፣ ይህንንም እውነታ በወደፊት ትምህርቶቻችን በጥልቀት እናየዋለን፡፡
ይህ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ለማሳየት ግን፣ ስለ ሮሜ መልእክት ጥቂት ጊዜ ወስደን እናስብ፡፡ በርካታ ክርስቲያኖች የሮሜን መጽሐፍ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት ስልታዊ ስውር አስተዋፅዖ እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ያዩታል፡፡ ስለዚህም በመጽሐፉ ላይ በግልጽ የሚታዩት መሪሃሳቦች የጳውሎስን ነገረ-መለኮታዊ ስልት ቅርፁን ያሳዩናል ብለው ይደመድማሉ፡፡ ሆኖም የሮሜን መጽሐፍ በጥልቀት ስንመለከት የሚገለጥልን ጳውሎስ ይህንንም መልእክት የጻፈው አንድን ጉዳይ ለመዳሰስ እንደሆነ ነው፡፡ ጳውሎስ ለእነርሱ ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ በሮም የሚገኙትን የአይሁድና የአህዛብ አማኞች ግንኙነት ለማጠናከር ነው፡፡
የሮሜን መጽሐፍ አወቃቀር በወፍ በረር መዳሰስ ይህንን ምጋቤያዊ ትኩረት ይፋ ያደርገዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች፣ አይሁዶችም ሆኑ አህዛቦች ኃጢአተኞች መሆናቸውን በማረጋገጡ ላይ ጳውሎስ በማተኮር፣ ማናቸውም የበላይ ነኝ የማለት መብት እንደሌላቸው ግልጽ ያደርጋል፡፡ ከምዕራፍ 4-8 እግዚአብሔር ለአይሁድም ለአህዛብም ተመሳሳይ የድነት መንገድ እንዴት እንዳዘጋጀ አፅንኦት ሰጥቶ ይጽፋል፡፡ አይሁድም ሆኑ አህዛብ በእግዚአብሔር ፊት ያው ናቸው፡፡ ከምዕራፍ 9-11 ጳውሎስ እግዚአብሔር በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ባለው እቅዱ ውስጥ ባላቸው ሚና ላይ ያተኩራል፡፡ ከዚያም፣ በእነዚህ አስተምህሮአዊ መሪ ሃሳቦች ላይ አፅንዖት ከሰጠ በኋላ፣ ከምዕራፍ 12 - 16 ውስጥ በተግባራዊ የክርስቲያን አኗኗር ረገድ በአይሁድና በአህዛብ መካከል ካለው ግጭት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ይዳስሳል፡፡
ለምሳሌ፣ በምዕራፍ 12 ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው፣ ክርስቲያኖች እንደ አንድ አካል ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ በምዕራፍ 13 ክርስቲያኖች ለአህዛብ መንግሥታትም ሳይቀር ራሳቸውን በማስገዛት ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ያሳስባል፡፡ ከምዕራፍ 14-16 መልዕክቱን ከመደምደሙ አስቀድሞ ደግሞ፣ የአይሁድንና የአህዛብን ወጎች በማክበር በአይሁድና በአህዛብ መካከል የእርስ በርስ መከባበርና መረዳዳት ሊኖር እንደሚገባ ጳውሎስ አትኩሮት ያደርጋል፡፡
ይህ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች የጻፈው መልእክት አጭር አስተዋፅዖ የሮሜ መጽሐፍ የጳውሎስ እምነቶች ምስጢራዊ መግለጫ እንዳልሆነ ለማየት ያስችለናል፡፡ ይልቁኑ፣ ይህ መጽሐፍ በክርስቲያኗ ቤተክርስቲያን ውስጥ በአይሁድና በአህዛብ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት የሚነሱ መግቦታዊ ጉዳዮችን መመለስ ተቀዳሚ ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ የሮሜ መጽሐፍ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት በተግባር የተገለጠባቸውን ውሱን ጉዳዮች ተዛምዶ የሚያሳየን ነው፡፡
ጳውሎስ በአግባቡ የተደራጀ፣ አመክኖአዊ ነገረ-መለኮታዊ የእምነት አቋሞች ወይም ስልታዊ ነገረ-መለኮት እንዳለው ማመናችን ትክክል ነው፡፡ ሆኖም የጳውሎስ የነገረ-መለኮት ስልት፣ ምንም እንኳን መልእክቶቹን አቅፎ የያዘ ቢሆንም፣ በቀጥታ በጽሑፍ ግን አልሰፈረም፡፡ እስከምናውቀው ድረስ፣ የጳውሎስ የነገረ-መለኮት ስልት በሙላት በጽሑፍ ተጠቃልሎ አልሰፈረም፡፡ ሆኖም፣ የጻፋቸውን መልእክቶች መሠረት አድርገን በትልቅ ደረጃ እንደገና ልናዋቅራቸው እንችላለን፡፡
የጳውሎስን ነገረ-መለኮታዊ ስልት እንደገና ለማዋቀር፣ ደጋግሞ ያነሳቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት መመልከት የለብንም፡፡ ምክንያቱም እርሱ በዘመኑ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በእርሱ ዘመን ለቤተክርስቲያን ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመጻፍ ስለሆነ ነው፡፡ ይልቁኑ፣ እንዲህ ብለን መጠየቅ ይገባናል፡ ጳውሎስ የጻፈባቸውን ውሱን ነገሮች የሚደግፉ ምን መርሆዎች አሉ? የእርሱን ውሱን አስተምህሮ በተሻለ መንገድ የሚያብራራ ምን የእምነት ልምምድ አለ? ለተለያዩ አብያተክርስቲያናት ከጻፈባቸው ጉዳዮች ጋር የሚያያዙ ምን አስምህሮዎች አሉ? እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት፣ የጳውሎስን ነገረ-መለኮት እንደገና ማዋቀር እንችላለን፡፡ እናም የጳውሎስ ደብዳቤዎች የመጀመሪያውን ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያን በምን ዓይነት ሊመሯት ዒላማ አድርገው እንደነበርና ዛሬም እኛን እንዴት ሊመሩን እንደሚገባ በግልጽና በተሻለ መንገድ እንገነዘባለን፡፡
ስለ ጳውሎስ ዳራና አገልግሎት ጥቂት መሠረታዊ የሆኑ ግንዛቤዎችን ጨብጠናል፣ አሁን ደግሞ የጳውሎስን ነገረ-መለኮታዊ አመለካከት በቀጥታ መመልከት እንጀምራለን፡፡
ማእከላዊ አመለካከቶች
በዚህ ነጥብ ላይ ጥቂት ወሳኝ ጥያቄዎችን ልንጠይቅ ይገባናል፡ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት አወቃቀሩ ምንድን ነው? በመልእክቶቹ ውስጥ ያስተማራቸው ትምህርቶች ያረፉት በምን ዓይነት እምነቶች ላይ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡ ምላሾች ጳውሎስን በትክክል ለመረዳት ወሳኞች ናቸው፡፡
ጳውሎስ በበርካታ ክርስቲያናዊ ትውፊቶች ውስጥ ታላቅ ተፅዕኖ ያለው ሰው መሆኑን እያወቅን የእርሱን ነገረ-መለኮት በሁሉ ረገድ ጠንቅቀን ለማወቅ መሞከር የሚቻል አይደለም፡፡ ስለዚህ ተርጓሚዎች የተጓዙባቸውን ሁለት መሠረታዊ አቅጣጫዎች ለመመልከት ራሳችንን እንገድባለን፡፡ እነርሱም፡ በጳውሎስ ነገረ-መለኮት ላይ ያለውን የተሃድሶ አስተሳሰብ እና ነገረ-ፍፃሜያዊ አመለካከት ብለን የምንጠራውንና በቅርብ ዐሥርት ዓመታት ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆነ የመጣው አመለካከት ናቸው፡፡ አስቀድመን በጳውሎስ ላይ ያጠነጠነውን የተሃድሶ አመለካከት እንመልከት፡፡
ተሃድሶ
የፕሮቴስታንቱ የተሃድሶ አራማጆች የጳውሎስን ነገረ-መለኮት አወቃቀር የተረዱት እንዴት ነው? ከተሃድሶው ንቅናቄ አስቀድሞ በነበሩት ምዕተ-ዓመታት፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ድነት የእግዚአብሔርን ጸጋና የሰዎችንም ጥረት እንደሚፈልግ ታስተምር ነበር፡፡ በዚህ አስተምህሮ መሠረት፣ ጽድቅ ረጅም ሂደት ሲሆን ያም እግዚአብሔር ጸጋውን በአማኝ ውስጥ ጊዜ ወስዶ የሚያሰርጽበትና አማኙም መልካምን ሥራ በማድረግ እንዲጸድቅ ጸጋ ያግዘዋል የሚል ዓይነት ነው፡፡ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የሚጸድቁት እና የሚድኑት በእግዚአብሔር ህግ ስታንዳርድ መሠረት ጸድቀዋል ሊባሉ የሚያስችላቸውን ሥራ ከሠሩ ብቻ ነው የሚል ነው፡፡
ማርቲን ሉተር፣ ዑልሪች ዝዊነግሊ እና ጆን ካልቪንን የመሳሰሉ መሪ የተሃድሶ አራማጆች የጳውሎስን መልእክቶች በማንበብ፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳውሎስን አስተምህሮ በሕገኝነት ቃና መተርጎሟ ትክክል አለመሆኑን ድምዳሜ ሰጡበት፡፡ ጽድቅ የተገኘው አንድ ጊዜ ነው፣ ያም ከሰው ሥራ ፈፅሞ የተለየ ነው እንጂ፣ ከሰው ጥረት ጋር ተቀይጦ በረጅም ሂደት የሚከናወን ተግባር አይደለም የሚለውን የአውጉስቲንን ትምህርት ተከተሉ፡፡ የክርስትና ሕይወት የረጅም ጊዜ ሂደት የሆነው ቅድስና፣ ጽድቅን ተከትሎ የሚመጣ ሲሆን በአማኙ የሕይወት ዘመን ሁሉ አብሮ የሚዘልቅ ነው፡፡ ጽድቅ ግን እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ለዘላለም ያወጀው፣ አማኙም ከኃጢአት ዕዳ ነፃ የሚወጣበት የክርስቶስንም ጽድቅ የሚቀበልበት አዋጅ ነው፡፡
ይህ የእምነት አቋም sola fide ወይም በእምነት ብቻ በመባል እየታወቀ መጣ፡፡ ምክንያቱም እኛ የጸደቅነው በክርስቶስ በማመናችን ብቻ እንጂ እምነት ሲደመር የእኛ መልካም ሥራ አላጸደቀንም የሚል ግንዛቤ ስለጨበጠ ነው፡፡ ያለምንም ጥርጥር፣ የተሃድሶ አራማጆቹ በጳውሎስ ጽሑፎች ውስጥ ይህንን አስተምህሮ ማግኘታቸው ትክክል ነው፡፡ በቀደመችው ቤተክርስቲያን፣ ከአይሁድ አማኞች መካከል የሆኑና ጁዳይዘርስ ተብለው የሚጠሩ ቡድኖች፣ ድነት በመለኮታዊ ጸጋና በሰው ሥራ የሚገኝ ነው በማለት ይከራከሩ ነበር፡፡ ጳውሎስ ግን በቀደመችው ቤተክርስቲያን የነበረውን ይህንን ሕገኝነት ይቃወማል እናም ጽድቅ ሕግን በመፈፀም በሥራ የማይገኝ ልዩ ሁነት ነው በማለት ይከራከራል፡፡ የተሃድሶ አራማጆቹን የገጠማቸው ውዝግብና ጳውሎስን የገጠመው ውዝግብ ግልጽ ጉድኝት አላቸው፡፡ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሕገኝነት በግርድፉ ከጁዳይዘሮቹ ጋር ይዛመዳል፡፡ እኛም የተሃድሶው sola fide ከጳውሎስ አስተምህሮ ጋር ይጎዳኛል፡፡
በውጤቱም፣ ጳውሎስ ነገረ መለኮቱን የገነባው ድነት በአማኙ የግል ሕይወት ላይ እንዴት ሊዛመድ እንደሚችል በሚያጠነጥኑ መሪ ሃሳቦች ላይ ነው የሚለውን አቋም አብዛኞቹ ፕሮቴስታንቶች አነገቡ፡፡ በትውፊታዊው ነገረ-መለኮታዊ አባባል፣ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት የተዋቀረው የድነት ሂደት ወይም ordo salutis በሚለው ላይ ነው የሚል ትምህርት አለ፣ ይህም ሂደት ድነት በክርስቶስ በእኔና በእናንተ ሕይወት የተዛመደበት ማለት ነው፡፡ በተሃድሶው ትውፊት፣ አብዛኞቹ ፕሮቴስታንቶች ordo salutis በተለይም ጽድቅ በእምነት ብቻ፣ የሚለው ሃሳብ በጳውሎስ ነገረ-መለኮት ውስጥ ማእከላዊ መሪ ሃሳብ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ይህም የእርሱ ነገረ-መለኮት ማዕከላዊ ሃሳብ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
በእርግጥም፣ ባላፉት ምዕተ-ዓመታት ጳውሎስ ጽድቅ በእምነት ብቻ ነው ከሚለው ሌላ በርካታ ነገሮችን ያምን እንደነበር ደርሰውበታል፡፡ ያም ማለት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጫፉ ላይ የደረሰው ድነት የእግዚአብሔር የረጅም ዘመናት የመቤዠት ታሪክ አካል ነው የሚለውም ጉዳይ ያሳስበው ነበር ለማለት ነው፡፡ በነገረ-መለኮታዊ አባባል፣ ይህንን የእርሱን አስተምህሮ historia salutis የድነት ታሪክ ብለን እንጠራዋለን፡፡ በአብዛኛው ክፍል ግን፣ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት ትውፊታዊ ግንዛቤ እንደሚያስረዳው የድነት ታሪክ ከድነት ሂደት ጠቀሜታው አነስ ያለ ነው፡፡ አሁንም እንኳን፣ አብዛኞቹ ፕሮቴስታንቶች የድነትን ታሪክ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት ማእከል አድርገው አይመለከቱትም፡፡
ነገረ-ፍፃሜያዊ
የጳውሎስን ነገር ከመፍታት አንፃር የቀደመው የፕሮቴስታንት አመለካከት ተፅዕኖ ፈጣሪ የመሆኑን ያህል፣ ያለ ተግዳሮት ግን አልዘለቀም፡፡ በቅርብ ዐሥርት ዓመታት፣ ሌላ አመለካከት ወደ ፊት ለፊት እየወጣ መጥቷል፣ ያም በጳውሎስ ነገረ-መለኮት ላይ የቀረበ ነገረ-ፍፃሜያዊ አስተሳሰብ የምንለው ነው፡፡ ይህ አመለካከት የድነት ሂደት ከድነት ታሪክ ይልቅ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት ማዕከላዊ ሃሳብ ነው የሚለውን የሚያጸና ነው፡፡
እንግዲህ፣ በቅርብ ዐሥርት ዓመታት በጳውሎስ ነገረ-መለኮት ላይ የተሰነዘሩ ሌሎች አመለካከቶች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ አንዳንድ እውቅ የነገረ-መለኮት ምሁራን የጳውሎስ ነገረ-መለኮት በተቀዳሚነት የሚያተኩረው አይሁዳዊ ዳራውን ከግሪክ ፍልስፍና ጋር በማጣጣሙ ላይ ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ጳውሎስ ተቀዳሚ የሚያደርገው በሥጋ ፍላጎት ላይ ቁርጠኛ የሆነ ክርስቲያናዊ አኗኗር ገዢ ይሁን የሚለውን ነው ይላሉ፡፡ ሌሎቹም ደግሞ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት በሄለኒስቶቹ ምሥጢራዊ ሃይማኖት ወይም በአይሁዳውያኑ አቡቀለምሲስ ብርቱ ተፅዕኖ አርፎበታል ብለው ይከራከራሉ፡፡ እነዚህ አመለካከቶች በጳውሎስ ነገረ-መለኮት ላይ አንዳንድ ግንዛቤ ቢያስጨብጡንም፣ በእርሱ ነገረ-መለኮት ላይ የተሰነዘረው ነገረ-ፍፃሜያዊ አመለካከት ያህል ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ሊያረጋግጡ አልቻሉም፡፡
በጳውሎስ ነገረ-መለኮት ላይ የቀረበውን ነገረ-መለኮታዊ አስተሳሰብ በሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማትኮር እንመረምረዋለን፡፡ አንደኛ፣ ነገረ-ፍፃሜ የሚለውን ቃል እናያለን፤ ሁለተኛ፣ የጳውሎስን ነገረ-ፍፃሜ ውቅር እናያለን፤ ሦስተኛ ደግሞ፣ የጳውሎስን ነገረ-ፍፃሜ አንድምታ እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ ነገረ-ፍፃሜ የሚለውን ቃል እንመልከት፡፡
ቃሉ
“ነገረ-ፍፃሜ” “eschatology” የሚለው ቃል eschatos (e,;scatoj) ከተሰኘው የግሪክ ቃል የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጓሜውም “ፍፃሜ” ወይም “መጨረሻ” ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነገረ-ፍፃሜ ማለት በፍፃሜ ወይም በመጨረሻ ነገሮች ላይ የሚቀርብ ትምህርት ማለት ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ይህንን ቃል “የመጨረሻ ዘመን” ወይም “የፍጻሜው ቀናት” በማለት ደጋግሞ ይጠቅሰዋል፡፡ ያም የሚያመለክተው መሲሁ በመጨረሻ ወደ ምድር በመመለስ የድነትን ታሪክ የሚያጠናቅቅበትን ጊዜ ነው፡፡ በበርካታ ወቅቶችም አዲሰ ኪዳን፣ እነዚህ “የመጨረሻ ዘመን” ወይም “የፍጻሜው ቀናት” የተሰኙ የብሉይ ኪዳን ቃላት በኢየሱስ በመሲሁ መፈጸማቸውን ለማመልከት ይጠቅሳቸዋል፡፡ እኛም ነገረ-ፍፃሜ “eschatology” የተሰኘውን ነገረ-መለኮታዊ ቃል የወሰድነው eschatos ከተሰኘው ከግሪኩ ቃል ሲሆን፣ ፍቺውም የነገረ-ፍፃሜ አስተምህሮ ማለት ነው፡፡
በትውፊታዊው ስልታዊ ነገረ-መለኮት፣ ነገረ-ፍፃሜ የሚለው ቃል የሚያመለክተው በተቀዳሚነት ስለ ክርስቶስ ዳግመኛ መመለስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ነው፡፡ እኛ ግን ስለ ጳውሎስ ነገረ-ፍፃሜያዊ አቀራረብ ስንነጋገር፣ ቃሉ ከክርስቶስ ዳግመኛ መመለስ ባሻገር ያሉ ጉዳዮችን እንዲዳስስ አድርገን እናቀርበዋለን፡ ወደፊት እንደምናየው፣ ጳውሎስ ስለ ክርሰቶስ ሁሉንም ነገር ተረድቷል፣ ማለትም ከነገረ-ፍፃሜ አንፃር ከመጀመሪያው እስከ ሁለተኛው መምጣቱ ድረስ ያሉትን የመጨረሻ ዘመን ክንውኖች ሁሉ ማለታችን ነው፡፡
አወቃቀር
ነገረ-ፍፃሜ የሚለው ቃል ከክርስቶስ ዳግመኛ መመለስ ባሻገር ያሉ ነገሮችን ሁሉ በሚያካትት መልኩ ሰፋ አድርገን ለመመልከት፣ ትኩረታችንን ወደ ጳውሎስ ነገረ-ፍፃሜ አወቃቀር ዘወር ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ ጳውሎስ የመጨረሻውን ዘመን ወይም የፍፃሜውን ቀናት በውስጡ ያኖረው እንዴት ነው? የዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጥናታችን በሦስት ክፍሎች ይከፈላል፡ ምንጮቹ፣ ዕድገቱ እና የጳውሎስ ነገረ-ፍፃሜ መሪ ሃሳቦች ናቸው፡፡ አስቀድመን የጳውሎስን ነገረ-ፍፃሜ ምንጮች እንመልከት፡፡
በጳውሎስ ዘመን፣ የአይሁድ የነገረ-መለኮት ምሁራን ብሉይ ኪዳን የዓለምን ታሪክ በሁለት ዘመናት ይከፍለዋል ብለው ያስተምራሉ፡፡ ከእነዚህም የመጀመሪያው አሁን ያለንበት የኃጢአትና የመከራ ዘመን ሲሆን፣ ያንንም “የአሁን ዘመን” ይሉታል፣ ወይም በዕብራይስጡ፣ olam hazeh ማለት ነው፡፡ የአሁን ዘመን ወደ ዝቅተኛው እርከን የደረሰው እስራኤል በመለኮት እርግማን ከተስፋዪቱ ምድር በተሰደደችበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህም፣ የአይሁድ የነገረ-መለኮት ምሁራን ስለ አሁኑ ዘመን በአሉታዊ ቃላት ቢናገሩ ሊያስገርመን አይገባም፡፡
ሆኖም መምህራኖቻቸው በተጨማሪም ይህንን የመከራ ዘመን ተከትሎ የሚመጣ የወደፊት የበረከት ዘመን አለ ብለው ያምናሉ፡፡ ይህንንም የወደፊት ዘመን “መጪው ዘመን” ወይም በዕብራይስጡ olam haba ይሉታል፡፡ በሚመጣው ዘመን፣ እግዚአብሔር በስተመጨረሻ ለእስራኤል የገባውን ተስፋ ሁሉ ይፈፅማል፡፡
በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ አይሁዶች፣ የመሲሁ መገለጥ በእነዚህ ሁለት ዘመናት መካከል ወሳኝ የአቅጣጫ ለውጥ የሚያመጣ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ መሲሁ ሲመጣ፣ የጌታን ቀን የሚያመጣ ሲሆን፣ ያም ቀን እግዚአብሔር ህዝቡን የሚባርክበት እና ጠላቶቹንም የሚያጠፋበት ነው፡፡ የሚመጣው ዘመን ይዞልን የሚመጣው ይህንን የመሰለውን ቀን ነው፡፡
የጳውሎስን መልእክቶች ስናነብብ፣ እርሱም ስለ ታሪክ እነዚህን ሁለት መሠረታዊ መንታ አመለካከቶች እንዳነገበ በግልጽ እናያለን፡፡ እንዲያውም፣ እርሱ እየኖረበት ያለውን ዘመን በቀጥታ የአሁን ዘመን በማለት ቢያንስ ዐሥራ ሁለት ያህል ጊዜያት ጠቅሶታል፡፡ ለምሳሌ፣ ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፡4 ሰይጣንን “የዚህ ዓለም አምላክ” ይለዋል፡፡ ደግሞም ስለ አህዛብ ፈላስፎች ሲናገር በ1ኛ ቆሮንቶስ 1፡20 “የዘመኑ ፈላስፋ” ይላል፡፡
በተመሳሳይ መንገድም፣ በሰው ዘር ሁሉ ላይ ፍርድና በረከት የሚመጣበትን የወደፊት ዘመን ለማመልከት ጳውሎስ “የሚመጣው ዘመን” የሚለውን መግለጫ ይጠቀማል፡፡ ለምሳሌ፣ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡19 ላይ ጳውሎስ “ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን…” በማለት አማኞች በታማኝነት እንዲዘልቁ ያበረታታል፡፡ በኤፌሶን 2፡7 ደግሞ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው “በሚመጣው ዘመን … የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው” ይላል፡፡
ከሁሉ በበለጠ የጳውሎስን መንታ አስተሳሰብ የሚገልጸው ሃሳብ የሚገኘው በኤፌሶን 1፡21 ውስጥ ነው፡፡ በዚያም ክርስቶስ የተቀመጠበትን ስፍራ ሲጠቅስ በግልጽ ሁለቱን ዘመናት አመልክቷል፡፡
… ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው… (ኤፌሶን 1፡21)
እነዚህን የሁለት ዘመናት መሠረታዊ እሳቤ በልቡናችን ይዘን፣ ጳውሎስ ክርስቲያናዊ ነገረ-ፍፃሜን ለየት አድርጎ የገነባበትን መንገድ መመልከት እንጀምር፡፡ በትውፊታዊው የአይሁድ ነገረ-ፍፃሜ በዚህ ዘመንና በሚመጣው ዘመን መካከል የመሲሁ መምጣት የአቅጣጫ ለውጥ ተደርጎ እንደሚወሰድም ታስታውሳላችሁ፡፡ መሲሁ ሲመጣ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር ህዝብ የእርሱን ሙሉ በረከት ይቀበላል፣ ጠላቶቹ ደግሞ ወዲያውኑ ጥፋት ያገኛቸዋል በማለት አይሁዶች ለበርካታ ምዕተ-ዓመታት ያምኑ ነበር፡፡ ሆኖም፣ ጳውሎስ፣ እንደ ኢየሱስ ተከታይነቱ፣ ከዚህ ለረጅም ዘመናት ከዘለቀ የእምነት አቋም ብርቱ ተግዳሮት ገጥሞታል፡፡ ኢየሱስ የእስራኤሉ መሲህ መሆኑን ያውቃል ሆኖም ደግሞ እስራኤል እንደጠበቀችው ኢየሱስ ዓለምን ወደ መጨረሻው ፍፃሜ እንዳላመጣም ያውቃል፡፡ እንደ ራሱ እንደ ኢየሱስ፣ እንደተቀሩት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት፣ ጳውሎስም ለዚህ ችግር መፍትሄ የሰጠው ትውፊታዊውን የአይሁድ ነገረ-ፍፃሜ በማሻሻል ነው፡፡
እንደ ጳውሎስ ማብራሪያ፣ ከአሁኑ ዓለም ወደ መጪው ዓለም የሚደረገው ሽግግር ከአንድ ዘመን ወደሌላው የሚደረግ ተራ ሽግግር አይደለም፡፡ ይልቁኑ፣ አንዱ ዘመን ሳይጠናቀቅ ሌላው ዘመን የሚጀምርበትን የሽግግር ሂደት ያካትታል፡፡ በዚህ እሳቤው መሠረት፣ መጪው ዘመን በክርስቶስ ሞት፣ ትንሣኤና ዕርገት በተግባር መገለጥ ጀምሯል ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ በክብር ዳግመኛ ሲመለስ፣ ይህ ክፉ ዘመን ያበቃል መጪውም ዘመን ከነሙላቱ ይጀምራል፣ ያም የእግዚአብሔርን ሕዝብ የፍፃሜ በረከት እና የጠላቶቹንም የፍፃሜ ፍርድ ይዞ እንደሚመጣ ጳውሎስ እርግጠኛ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ያ ሙላት እስኪመጣ ድረስ፣ ሁለቱም ዘመናት ማለትም የአሁኑ ዘመንና መጪው ዘመን ጎን ለጎን አብረው ይጓዛሉ፡፡
የጳውሎስን ነገረ-ፍፃሜ ምንጭ፣ ዕድገት እና አወቃቀር በልቡናችን ይዘን፣ በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ መሪ ሃሳቦች እርስ በእርስ ተደራርበው የሚመጡ የዘመናት ታሪኮች ከመረዳት አንፃር ማብራራቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ የጳውሎስን ነገረ-ፍፃሜያዊ አመለካከት “የተፈፀመና ሊሆን ያለ” ብሎ መግለጥ የተለመደ ሆኗል፣ ምክንያቱም የመጨረሻው ዘመን አንዳንድ ገፅታዎች በክርስቶስ ውስጥ ተገልጠዋል፣ አንዳንዶቹ ግን ገና አልተገለጡም በማለት ጳውሎስ ስለሚያምን ነው፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጥቂት ፈታ አድርገን እንመልከተው፡፡
በአንድ በኩል፣ እንደ ጳውሎስ አገላለጥ፣ የሚመጣው ዘመን በብዙ መንገዶች በእኛ መካከል እየተፈፀመ ነው፡፡ በጳውሎስ ጽሑፎች ውስጥ ይህ መሪ ሃሳብ የተገለጸባቸውን ሦስት መንገዶች እንጠቅሳለን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት የመጨረሻው ደረጃ ኢየሱስ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ ሲያርግ ተጀምሯል ብሎ ጳውሎስ ያስተምራል፡፡ ለምሳሌ፣ በኤፌሶን 1፡20-21 አብ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው ለዚህ ነው ብሎ ጳውሎስ ጽፏል፡፡
ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ (ኤፌሶን 1፡20-21)
ምንም እንኳን በአሁን ዘመን የክርስቶስ ንግሥና በተቀዳሚነት እየተገለጠ ያለው ከምድር ይልቅ በሰማያዊ ስፍራ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን ክርስቶስ በአለቆችና በሥልጣናት ላይ ገዢ መሆኑ እውነት ነው፡፡ በዚህ ግንዛቤ መሠረት፣ በሚመጣው ዘመን የእግዚአብሔር ገዢነት የዚህ ዘመንም እውነታ ነው ማለት ነው፡፡
አሁን በእኛ መካከል እየሆነ ያለው የሚመጣው ዘመን ሁለተኛው ገጽታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ የተቀበልነው ዘላለማዊ ውርሳችን ቅምሻ ነው፡፡ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ዙፋኑ ሲያርግ፣ ክርስቶስ ዳግመኛ ሲመለስ የምናገኘውን የተሟላ ውርስ ከወዲሁ በቅምሻ እናጣጥመው ዘንድ መንፈስ ቅዱሱን በቤተክርስቲያን ላይ እንዳፈሰሰ ጳውሎስ ያስተምራል፡፡ ጳውሎስ ይህንን በሮሜ 8፡23 ውስጥ “የመንፈስ በኩራት ያለን እኛ” በማለት ያብራራዋል፡፡ “በኩራት” የሚለው ቃል aparche (avparch) የተሰኘው የግሪክ ቃል ትርጓሜ ሲሆን፣ በብሉይ ኪዳን የመከርን የመጀመሪያ ፍሬ ለይቶ ለማስቀመጥ ይውል የነበረው ቃል ፍቺ ነው፡፡ በኩራት የሚለው ቃል የተትረፈረፈ ፍሬ ወደፊት እንደሚመጣ አመልካች ነው፡፡ ስለዚህ ለጳውሎስ፣ በአማኞች ሕይወት ውስት የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ማለት የሚመጣው ዘመን የተትረፈረፈ በረከት ቅምሻ ነው ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ መንገድ፣ እንደ ኤፌሶን 1፡14 አገላለጥ፣ መንፈስ ቅዱስ ራሱ፡
የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል። (ኤፌሶን 1፡14)
መያዣ ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል arrabon (avrrabw,n) ነው፡፡ ይህ ቃል የሚያመለክተው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠው ቀብዱ ወይም መያዣ ሲሆን፣ ይህም ወደፊት ከእግዚአብሔር ዘንድ ብዙ እንደምንቀበል የሚያረጋግጥልን ነው፡፡ አሁንም በድጋሚ፣ መንፈስ ቅዱስ የመጪው ዘመን በረከት ሲሆን አሁንም ለእኛ ተሰጥቶ ከእኛ ጋር አለ፡፡
በመጨረሻም፣ ጳውሎስ ከሚመጣው ዘመን ጋር ግንኙነት ያለውን አዲስ ፍጥረት ክርስቶስ የመግለጡን እውነታ ያመለክታል፡፡ ክርስቶስ በሠራው ሥራ ምክንያት፣ ክርስቲያኖች አሁን፣ በከፊልም ቢሆን፣ የዓለምን ዳግመኛ የመፈጠር በረከት በማጣጣም ላይ ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ፣ በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር ዓለምን እንደገና ፈፅሞ አዲስ እንደሚያደርጋት ማለትም የሰው ልጅ በኃጢአት ከመውደቁ አስቀድሞ እንደነበረችው ገነት ያደርጋታል፡፡ በኢሳያስ 65፡17 ጌታ መጪውን ዘመን ለኢሳያስ እንዴት እንደገለጠለት እናድምጥ፡
እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ወደ ልብም አይገቡም። (ኢሳያስ 65፡17)
በጳውሎስ ልቡና ውስጥ ክርስቶስ አሁን ሰውን የማዳኑ ሥራ የዓለም እንደገና መፈጠር የጀመረ መሆኑን ያረጋግጣል የሚል እውነታ አለ፡፡ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17 ይህንን ሃሳብ በደንብ ይገልጸዋል፡፡
ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። (2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17)
ምንም እንኳን ጳውሎስ ክርስቶስ መጀመሪያ ሲመጣ የመጪው ዘመን በርካታ ገፅታዎች የተገለጡ መሆናቸውን ቢያስተምርም፣ ሆኖም የመጨረሻው ዘመን በረከቶች በሙላት ገና ያልተገለጡ መሆናቸውንም ጳውሎስ ያምናል፡፡ ስለዚህም፣ ክርስቶስ የመጨረሻውን ፍርድና በረከት የሚያፈስስበትን የክርስቶስን ዳግመኛ መመለስ በናፍቆት ይጠባበቃል፡፡ አንድ ጊዜ እንደገና፣ የጳውሎስ አመለካከት ገሃድ የሆነባቸውን ሦስት መንገዶች እናነሳለን፡፡
በመጀመሪያ፣ አስቀድመን እንዳየነው፣ ንጉሡ ክርስቶስ በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ሆኖ አሁን ይገዛል በማለት ጳውሎስ ያስተምራል፡፡ ግን ደግሞም ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ሲመለስ የእግዚአብሔርን መንግሥት በሙላት ያመጣታል ብሎ ያምናል፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፡24-26 ይህንን ያስቀመጠበትን መንገድ እናድምጥ፡
በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።
ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።
የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ (1ኛ ቆሮንቶስ 15፡24-26)
ጳውሎስ ክርስቶስ አሁን ከሚገዛበት ዘመን ባሻገር መጪውንና አለቅነትን፣ ሥልጣናትንና ኃይላትን ሁሉ ማለትም የእግዚአብሔርን ዓላማ የሚጋፉትን ሁሉ የሚያጠፋበትን የወደፊት ዘመን እንደሚያይ ይህ ምንባብ ግልፅ ያደርግልናል፡፡ ሞትን ጨምሮ፣ ጠላቶቹ ሁሉ አስኪወገዱ ድረስ ክርስቶስ በሰማያዊ ዙፋኑ ላይ ይቆያል፡፡ ስለዚህ በአንደ በኩል፣ የክርስቶስ መንግሥት አሁን እዚህ እንዳለች፣ ግን በሌላ በኩል ደግሞ ገና በሙላት እዚህ እንዳልተገለጠችም ጳውሎስ ያምናል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ እንዳየነው፣ መንፈስ ቅዱስ የወደፊቱ የድነት መከር በኩራት እንደሆነ እና የወደፊት ውርሳችን መያዣ እንደሆነ ጳውሎስ ያምናል፡፡ በኩራት እና መያዣ የተሰኙት ቃሎች የውርሱ ሙላት ገና ወደፊት እንደሚመጣ ያመለክታሉ፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 8፡23 ውስጥ እንዴት እንዳስቀመጠው እናድምጥ፡
እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። (ሮሜ 8፡23)
ጳውሎስ በዚህ ስፍራ በዘመናችን መንፈስ ቅዱስ ለእኛ የተሰጠበትን የአሁን እውነታ ከወደፊቱ ጋር በቀጥታ ያዛምደዋል፡፡ ምክንያቱም፣ መንፈሱን አሁን እዚህ ስለተቀበልን፣ መጪውም ዘመን አሁን እዚህ ስላለ ነው፡፡ ሆኖም ግን አሁንም በውስጣችን እንቃትታለን ምክንያቱም የሰውነታችንን መቤዠት ገና እየተጠባበቅን ስለሆነ ነው፡፡
ተመሳሳይ በሆኑ በብዙ መንገዶች፣ በኤፌሶን 1፡14 ውስጥ ጳውሎስ ስለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡
እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ (ኤፌሶን 1፡14)
መንፈሱ አስደናቂ ቅምሻ ነው፣ ግን የታላቁ ድነታችን፡ የሙሉ ውርሳችን ቅምሻ ብቻ ነው፡፡
በመጨረሻም፣ ምንም እንኳን አዲስ ሰውነት በአማኞች ሕይወት ውስጥ የተገለጠ መንፈሳዊ እውነታ ቢሆንም፣ የፍጥረትን ፍፁም ተሃድሶና በአዲሲቷ ምድር ለዘላለም ገዢ የምንሆንበትን እውነታም እንጠባበቃለን፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 8፡21 እንደ ጻፈው፣ በዚያውም አዲሱን ሰውነታችንን እንለብሳለን፡
ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። (ሮሜ 8፡21)
ጳውሎስ አዲሱ ፍጥረት ወደ ሙላት የሚደርስበትን፣ የክርስቶስን ዳግመኛ መመለስ በናፍቆት ይጠባበቃል፡፡
ጳውሎስ ስለ አሁኑና ስለሚመጣው ዘመን ወሳኝ የሆኑ መሪ ሃሳቦችን ካነሳባቸው መንገዶች መካከል እስካሁን ያየነው ጥቂቶቹን ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የእርሱን አመለካከት ሊያሳየን የሚችል አጠቃላይ ንድፍ ግን ለማሳየት ጥረናል፡፡ የሚመጣው ዘመን በርካታ በረከቶችን ለአማኞች ይዞ የመጣ የዚህ ዘመንም እውነታ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ዘመን ገና አልተፈፀመም፣ እና የሚመጣው ዘመን ክርስቶስ ዳግመኛ በክብር እስኪመጣ ድረስ ገና ወደ ሙላቱ አይደርስም፡፡ በዚህም መካከል፣ የዚህ ዘመን ፈተናና የቀጣዩ ዘመን ድንቅ ነገሮች በተጓዳኝ ይጓዛሉ፡፡
የጳውሎስን ነገረ-ፍፃሜ ከተመለከትን፣ ከእርሱ አመለካከቶች ወሳኝ አንድምታዎች መካከል ጥቂቶቹን ወደ መመልከቱ እንሸጋገራለን፡፡
አንድምታዎች
እንደተመለከትነው፣ ጳውሎስ ነገረ-መለኮቱን በስፋት ያንጸባረቀው በመጋቢያዊ አገልግሎት አውድ ውስጥ ነው፡፡ በስውር ነገረ-መለኮት ላይ አላተኮረም፣ ያተኮረው ገሃድ በሆኑት ሰብዓዊ ልምምዶች ላይ ነው፡፡ ነገረ-ፍፃሜው እንኳን ስውርነት የለበትም፡፡ ይልቁኑ፣ ቤተክርስቲያንን አሁን እየተፈታተኗት ያሉ በርካታ ችግሮች ምንጫቸው በአሁኑ ዘመንና በሚመጣው ዘመን መካከል ባለው ቅይይጦሽ ውስጥ ለመኖር የሚደረግ ውጥረት ነው፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ በጽሑፎቹ ውስጥ፣ በመጀመሪያው መምጣት ውስጥ እግዚአብሔር ለአማኞች ምን እንዳደረገ እና ክርስቲያኖች የክርስቶስን ዳግመኛ መመለስ ሲጠባበቁ ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸው አብራርቷል፡፡
የዚህን የጳውሎስን ነገረ-ፍፃሜ ተግባራዊ ትኩረት ገላልጦ ለመመልከት፣ ሦስት ርዕሶችን እንመለከታለን፡ አንደኛ፣ ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን፤ ሁለተኛ፣ መለኮታዊ ዓላማ፤ እና ሦስተኛ፣ የክርስቲያን ተስፋ ናቸው፡፡ አስቀድመን ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር አንድ ስለመሆን ያስተማረውን እንመልከት፡፡
ጳውሎስ በሮሜ 6፡3-4 ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት እኛን ከአሁን ዘመን ወደሚቀጥለው ዘመን አሸጋግሮናል በማለት ያመለክታል፡፡ ጳውሎስ በድጋሚ ከክርስቶስ ጋር አንድ ስለመሆናችን ከጥምቀት አንፃር ሲጽፍ አንዲህ ይጠይቃል፡
ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?
እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። (ሮሜ 6፡3-4)
በቀላሉ ስናስቀምጠው፣ ከአሁን ዘመን ወደመጪው ዘመን ያደረግነው ሽግግር በተጨባጭ የተፈፀመው በክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ ውስጥ ነው፡፡ ሆኖም ወንዶችና ሴቶች በሚያድን እምነት ወደ ክርስቶስ በሚመጡበት ጊዜ ሁሉ፣ ከእርሱ ትንሣዔ ጋር ይተባበራሉ፡፡ በውጤቱም፣ እኛ ዳግመኛ በኃጢአት ባርነትና እርሱንም ተከትሎ በሚመጣው በእግዚአብሔር ፍርድ ስር መኖራችን አብቅቷል፡፡ እኛ አዲስ ሕይወት፣ የትንሣዔ ሕይወት ተቀብለናል፣ ስለዚህ ክርስቶስን ለማገልገል በነፃነት እንኖራለን፡፡ ጳውሎስ በመቀጠልም በሮሜ 6፡10 እና 11 ማብራሪያውን እንዲህ ይቀጥላል፡
መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል።
እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ። (ሮሜ 6፡10-11)
እኛ ከክርስቶስ ጋር ስላለን አንድነት ጳውሎስ ያስተማረው ትምህርት የአማኞች ተግባራዊ ሕይወት የነገረ-ፍፃሜ ተዛምዶ መሆኑን ያሳያል፡፡ ልክ ኢየሱስ ይህንን ዘመንና ፍርዱን ወደ ኋላው እንደጣለው ሁሉ፣ እኛ ከኃጢአትና ከፍርድ ነፃ ወጥተናል፡፡ ደግሞም አሁን ኢየሱስ በሚመጣው ዘመን ኃይል እንደሚኖር ሁሉ፣ እኛም በዚው ኃይል እንኖራለን፡፡
ከክርስቶስ ጋር በእምነት አንድ መሆናችን አዲስን ሕይወት እንዴት እንዳስገኘልን አንድ ጊዜ ከተረዳን፣ ፈታኝ ጥያቄ ይጠብቀናል፡ በአሁን ዘመንና በሚመጣው ዘመን መካከል ሁለቱ በተጓዳኝ የሚኖሩበትን ዘመን እግዚአብሔር ለምን አመጣ? የእግዚአብሔር ዓላማ ምንድን ነው? ጳውሎስ ለአህዛብ ያበረከተው ሚሲዮናዊ አገልግሎት ለዚህ አመለካከቱ ዋቤ ይሆናል፡፡ ያም እግዚአብሔር በእነዚህ ዘመናት መካከል የሁለቱን አብሮ የመጓዝ ዘመን ያመጣው አይሁድ አማኞችንና አህዛብን አንድ የእግዚአብሔር ህዝብ ለማድረግ ነው የሚል ነው፡፡
ጳውሎስ በተጨማሪም በአሁን ዘመንና በመጪው ዘመን መካከል ያለው በጉድኝት የመጓዝ ዘመን ዓላማው ቤተክርስቲያንን ወደ መንፈሳዊ ብስለት ለማምጣት ነው ብሎ ያምናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህንን ሃሳቡን፣ ኤፌሶን 2፡19-22 በመሳሰሉት ስፍራዎች የእግዚአብሔርን መቅደስ ከመገንባት አንፃር ያስቀምጠዋል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ በሰብዓዊ አካል ዕድገት አንፃርም ያቀርበዋል፣ በኤፌሶን 4፡15-16 እንደጠቀሰው ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ዘመንና በመጪው ዘመን መካከል ያለው የሁለቱም ቅይጥ ዘመን አንዱ የእግዚአብሔር ማዕከላዊ ዓላማ የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ብስለት እንደሆነ ጳውሎስ ተረድቷል፡፡
ከታሪክ ረገድ ይህን የመሰለው አመለካከት የተለመደ እንዳልሆነ ጳውሎስ ተገንዝቧል፡፡ ከዚያ ቀደም አልተገለጠም፡፡ ይህ ነገር እግዚአብሔር ለሌሎች እንዳስረዳው የገለጠልኝ ምሥጢር ነው በማለት የሚጠቅሰው ለዚህ ነው፡፡ በሮሜ 11፡25፣ ጳውሎስ እንዲህ ጽፏል፡
ወንድሞች ሆይ፥ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ምሥጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ ድንዛዜ በእስራኤል በአንዳንድ በኩል ሆነባቸው፤ (ሮሜ 11፡25)
በዚህ ምንባብ ጳውሎስ ያመለከተው እግዚአብሔር ይህንን ዘመን የተጠቀመው በርካታ አይሁዶች ልባቸውን ለወንጌል ዝግ ሲያደርጉ አህዛብን በሙላት ለማዳን ነው የሚለውን ነው፡፡ በኤፌሶን 3፡4-6 እንዳመለከተው፡
ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤
ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም። (ኤፌሶን 3፡4-6)
ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ዓላማዎች ያለው አመለካከት በአሁኑ ዘመንና ሚመጣው ዘመን መካከል ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ፍንጭ ሰጪ ነው፡፡ በሕብረትም ሆነ በግል፣ ክርስቲያኖች ይህንን ዘመን የሚመጣውን ዘመን ሙላት እጃቸውን አጣጥፈው የሚጠባበቁበት ዘመን አይደለም፡፡ ይልቁኑ፣ እግዚአብሔር ይህንን ዘመን ያዘጋጀው፣ ለትልቅ ሥራ ነው፡፡ ያም ሥራ ከመላው ዓለም በርካቶችን የማዳን እና ቤተክርስቲያንንም ወደ መንፈሳዊ ብስለት ማምጣት ነው፡፡ ጳውሎስ ሕይወቱን ወንጌልን ለማዳረስና ቤተክርስቲያንን ለመገንባት አሳልፎ የሰጠው ደግሞም ሌሎችም የዚህ ሥራ አጋር እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረበው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በአሁኑ ዘመንና በሚመጣው ዘመን መካከል እኛ ከክርስቶስ ጋር ስላለን አንድነት ጳውሎስ ያስተማረው ትምህርት፣ ክርስቲያኖች በሕይወት ዘመናቸው በሚኖራቸው ትግል ውስጥ ታላቅ ተስፋን የሚያገኙበት የተስፋ ምንጫቸው መሆኑንም ያመለክታል፡፡ ጳውሎስም እንደ ሐዋርያ በሕይወቱና በአገልግሎቱ በርካታ ፈተናዎች ገጥመውታል፣ እናም ክርስቲያኖች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ መከራ እንደሚቀበሉ ያውቃል፡፡ የጳውሎስ ነገረ-ፍፃሜ ግን ቢያንስ በሁለት መንገዶች ተስፋን ይፈነጥቅላቸዋል፡፡
በአንድ በኩል፣ ወደፊት ስለሚጠብቀን ተስፋ የጳውሎስ ነገረ-መለኮት የሚያሳየን የሚመጣውን ዘመን በረከት አሁን በዚህ ዘመን ማጣጣም መጀመራችንን በማወጅ ነው፡፡ ሕይወታችንን ስንመለከትና የመጪውን ዘመን በረከቶች በአሁኑ ዘመን ሕይወታችን እየቀመስን መሆኑን ስናስተውል በመጪው ዘመን የምንቀበለውን እጅግ የሚልቅ ሙላት በተስፋ እንጠባበቃለን፡፡ ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፡16-18 እንዲህ ጽፏል፡
ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። (2ኛ ቆሮንቶስ 4፡16-18)
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከፊታችን የሚጠብቁን በረከቶች እጅግ አስደናቂ ከመሆናቸው የተነሳ በአሁኑ ዘመን የሚገጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ እንደምንም እንድንቆጥራቸው ያስችሉናል፡፡ ጳውሎስ በሮሜ 8፡18 የጠቀሰውን እንዲጽፍ ምክንያት የሆነው ይህ እምነቱ ነው፡
ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ። (ሮሜ 8፡18)
የአሁን ዘመን ስቃያችን ጊዜያዊ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ በመጨረሻ ይህንን ክፉ ዘመን ወደ ፍፃሜ ያመጣውና ለልጆቹ ያዘጋጀውን የከበረ ስጦታ አዲስ ዓለም ይፈጥራል፡፡
በዚህ ዘመን ሕይወታችን ከሚገጥመን ፈተና የተነሳ በውጫችን እጅግ ድቅቅ እንደምንል ጳውሎስ እውቅና ቢሰጥም፣ ሆኖም ደግሞ አሁን በተቀበልናቸውና በሚመጣውም ዘመን በምንቀበላቸው በረከቶች ምክንያት ውስጣችን ዕለት ዕለት እንደሚታደስ ያውጃል፡፡ ከኃጢአት ነፃ መውጣትና የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በዕለት ከዕለት ውስጣዊ የመታደስ ልምምዳችን ደስ እንድንሰኝ ያስችሉናል ስለዚህም ዐይኖቻችን በክርስቶስ በገኘነው ዘላለማዊ ተስፋ ላይ ያርፋሉ፡፡ በሚመጣው ዘመን የሚጠብቀንን የበረከት ሙላት አሁን በቅምሻ መቀበላችን ክርስቶስ ዳግመኛ ሲመለስ የሚጠብቀንን የተሟላ ድግስ በናፍቆት እንድንጠባበቅ ያስችለናል፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ ትምህርት ስለ ጳውሎስና ስለ ነገረ-መለኮቱ አጭር ዳሰሳ አድርገናል፡፡ የጳውሎስ ዳራ ነገረ-መለኮቱን እንዴት እንደቀረፀው፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቱ ደግሞ ከክርስቲያናዊ እምነቱ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ዐይተናል፡፡ የእርሱን ነገረ-ፍፃሜ በመመርመር ስለ ጳውሎስ ነገረ-መለኮት ማዕከላዊ ትኩረት ወሳኝ የሆኑ ግንዛቤዎችንም ጨብጠናል፡፡ እነዚህን አመለካከቶች በልቡናችን በመያዝ፣ ወደፊት በምንመለከታቸው ትምህርቶች የጳውሎስን ሕይወትና መልእክቶች በጥልቀት መመልከት የምንችልበትን አቅም አግኝተናል፡፡ ጳውሎስ በቀደመችው ቤተክርስቲያን ያስተማረውን ትምህርት በተሻለ መንገድ መገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱ ትምህርቶች ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም ይሰጡናል የሚለውንም በተሻለ መንገድ እንገነዘባለን፡፡
Continue reading the full transcript