ከተመሳሳዩ ተከታታይ ትምህርት 5 ጋር የተያያዘ ቪዲዮ ሲሆን ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ነው፡- የአምላክ መንግስት ምንድን ነው? የአምላክን እንደ ሁሉም ፍጥረት ላይ እንደ ንጉስ የመግዛት መብት የሚሰጠው ምንድን ነው? የድሮው ኪዳን አንዳንድ ጊዜ አምላክን እንደ ተዋጊ ንጉስ የሚያሳይበት ለምን ነው? ጥንታዊ ነገሥታት፣ እንዲሁም አምላክ በፈጣሪነቱ፣ አንዳንድ ጊዜ እንደ አባቶች የሚጠሩት ለምን ነው? የመለኮታዊ ፍትህ አስፈላጊነት ምንድን ነው? የአምላክ መንግስት ከጥንታዊ ሱዘርን-ቫሳል ግንኙነቶች ጋር እንዴት ይመሳሰላል? ኢየሱስ የአምላክ ቫሳል ንጉስ በምን ስሜት ነው? ኢየሱስን የአምላክ መንግስት ላይ ተገቢው ገዥ የሚያደርገው ምንድን ነው? ኢየሱስ ንጉሳችን ነው ስንል ክርስቲያኖች ምን ማለት ናቸው? የኢየሱስ ዘመን አይሁዶች መሲሁስ ምን እንዲያደርግ ይጠብቁ ነበር፣ እናም የሚጠብቁት ነገር የድሮው ኪዳን ትምህርቶችን ያንጸባርቅ ነበር? ክርስቲያኖች የአምላክ መንግስት መጣች ብለው የሚያምኑት ለምን ነው፣ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አልመጣችም? የአምላክ መንግስት እና ቤተክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? የኢየሱስ የንጉስ ቦታችን እንዴት ሊኖረንና እንዴት መሥራት እንዳለብን ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚገባው?
From the transcript
ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡
የሰው ዘር ታሪክ በተደጋጋሚ ጊዜ የተጻፈው ከኃያል ነገሥታት መነሣት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የእስያን፣ የአውሮፓን፣ የአፍሪካንና የላቲን አሜሪካን አብዛኛ ክፍሎች ስለገዙ ነገሥታት ሰምተናል፡፡ ከእነርሱም መካከል አንዳንዶቹ ጠላቶቻቸውን ድል በማድረግ ግዛቶቻቸውን አስከ ሩቅ የዓለም ዳርቻዎች አስፋፍተዋል፡፡ ሁሉም ቢያንስ አንድ የጋራ የሆነ ነገር አላቸው፡፡ ሁሉም አልፈዋል፤ ሁሉም ሞተዋል፤ ሁሉም መልሰው ላይገዙ ተሰናብተዋል፡፡ ኃያል ጦራቸው ተበታትኗል ኃይላቸውም ተንኮታኩቷል፡፡
አንድ ብቻ ለየት ያለ ገዢ አለ፡፡ ኃይሉ የማይደክም፣ መንግሥቱም የማይሻር አንድ ንጉሥ አለ፡፡ ያም ንጉሥ፣ በእርግጥ፣ ኢየሱስ ነው፡፡
በኢየሱስ እናምናለን ከተሰኘው ተከታታይ ትምህርታችን፣ ውስጥ ይህ አምስተኛው ሲሆን፣ “ንጉሥ” የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ በዚህ ትምህርት፣ ኢየሱስ እንዴት አድርጎ በብሉይ ተነግሮ የነበረውን የንጉሥነት አገልግሎት እንደፈፀመ፣ እንደ እግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይና እንደ ልጅ እንዳገለገለ እንመለከታለን፡፡ ቀደም ባሉት ትምህርቶች እንደተመለከትነው፣ በብሉይ ኪዳን ታሪክ በተለያዩ እርከኖች እግዚአብሔር መንግሥቱን ያስተዳደረባቸውን ሦስት ቢሮዎች መመሥረቱን ተመልክተናል፣ እነርሱም፡- የነቢይ፣ የካህንና የንጉሥ ቢሮዎች ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት የመጨረሻ እርከን፣ በተለምዶ አዲስ ኪዳን ብለን በምንጠራው ዘመን፣ ሦስቱም ቢሮዎች በኢየሱስ ላዕላይ ፍፃሜአቸውን አግኝተዋል፡፡ በዚህ ትምህርት፣ በኢየሱስ የንጉሥነት ቢሮ ላይ እናተኩራለን፡፡
ዓላማማችንን ከግብ ለማድረስ፣ ንጉሥን በእግዚአብሔር ምትክ በመሆን በመንግሥቱ ላይ እንዲገዛ በእግዚአብሔር የተሾመ ብለን እንፈታዋለን፡፡ ይህ ፍቺ እንደሚያመለክተው፣ በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ሲገዛ የኖረውና ወደፊትም የሚገዛው እግዚአብሔር ሆኖ ይኖራል፡፡ ሆኖም ሰዎች የእርሱ ወኪሎች ሆነው እንዲገዙ ይሾማል፡፡ እነዚህ ሰብዓዊ ነገሥታት በእርሱ ስር ሆነው ያገለግላሉ፣ የመንግሥቱንም ዓላማዎችና ግቦች ያስፈፅማሉ፡፡ ይህንን ፍቺ በልቡናችን ስንይዝ፣ ስለመጽሐፍ ቅዱሳዊው የንጉሥነት ቢሮ በርካታ ነገሮችን እናስተውላለን፣ ኢየሱስም ይህንን አገልግሎት እንዴት እንደፈፀመ እንረዳለን፡፡
ይህ ትምህርት የኢሱስን የነቢይነትና የካህንነት አገልግሎት የተመለከትንበትን ተመሳሳይ ቅርፅ ይይዛል፡፡ በመጀመሪያ፣ የንጉሥነትን አገልግሎት ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ እንመረምራለን፡፡ ሁለተኛ፣ በኢየሱስ የንጉሥነትን አገልግሎት ሙላት እናያለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ በግል ሕይወታችን የኢየሱስ ንግሥና የሚኖረውን ተዛምዶ እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ የኢየሱስን የንጉሥነት አገልግሎት ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ እንመልከት፡፡
ግሪካዊው ፈላስፋ ፕላቶ The Republic በተሰኘው መጽሐፉ፣ በምድር ከታዩ አገዛዞች ሁሉ ከሁሉ የሚሻለው የፈላስፋ ንጉሥ አገዛዝ ነው ሲል ተሟግቷል፡፡ በእርሱም አመለካከት፣ ከብልጥግናና ከኃይል ይልቅ ጥበብን በእውነት የሚወድዱ ነገሥታት፣ አገራቸውን ወደ ማይቆጠር ትርፋማነት ይመራሉ፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ የእስራኤል ነገሥታት እግዚአብሔርን ሲፈሩ እና ህግጋቱንም ሲከተሉ፣ መንግሥታቸው በእግዚአብሔር በረከት እንደሚጥለቀለቅ ቅዱሳት መጻሕፍት ያሳዩናል፡፡ ሆኖም ደግሞ፣ በእግዚአብሔር ላይ ሲያምፁ፣ ሀገሪቱ በጠቅላላ በእግዚአብሔር ፍርድ ትማቅቃለች፡፡ በዚህ ረገድ፣ በምድር ለምትኖረው የእግዚአብሔር መንግሥት ጤናማነት የእስራኤል ነገሥታት ቁልፍ ናቸው፡፡
የንጉሥነትን ቢሮ ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ በሦስት ርዕሶች እንመረምረዋለን፡ በመጀመሪያ፣ ለንጉሥነት አገልግሎት የሚያበቁ መስፈርቶችን፤ ሁለተኛ፣ የነገሥታትን ተግባር ሦስተኛ ደግሞ፣ ወደፊት ከሚመጣው የእሥራኤል የንጉሥነት አገልግሎት ብሉይ ኪዳን የሚጠብቀውን እንመለከታለን፡፡ አስቀድመን የንጉሥነትን አገልግሎት መመዘኛዎች እንመልከት፡፡
መመዘኛዎች
በብሉይ ኪዳን፣ እግዚአብሔር የነገሥታትን መመዘኛዎች የሰጠው በሁለት እርከኖች ነው፡፡ በመጀመሪያ፣ በሙሴ ሕግ፣ እስራኤል ገና መንግሥት ሳይኖራት እግዚአብሔር የንግሥናን መመሪያ ገለጠ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር በገባው ቃል ኪዳን ወሳኝ ተጨማሪ መመዘኛ ሰጠ፡፡ አስቀድመን፣ በሙሴ ሕግ የተመዘገቡትን የንግሥና መመሪያዎች እንመልከት፡
የሙሴ ሕግ
ብሉይ ኪዳንን፣ በተለይም ፔንታቱክን የመጀመሪያዎቹን አምስት መጻሕፈት ስታነቡ፣ ስለሚጠበቀው ንጉሥ የሚናገሩ ነገሮችን ታገኛላችሁ፡፡ በዚያም ውስጥ ገና ንጉሥ የሚባል ነገር በሌለበት ሩቅ ዘመን ንጉሥ ምን መምሰል እንዳለበትና ምን ማድረግ እንዳለበት ተጽፎ ታገኛላችሁ፡፡ ጉዳዩ ለምን እንዲህ ሆነ? እኔ እንደማስበው፣ ንጉሡ ምን መምሰል እንዳለበትና ምን ሊያደርግ እንደሚገባ በተስፋ የሚናገሩ በተለይ እንደ ዘዳግም ምዕራፍ 17 የመሳሰሉት ምንባቦች፣ ከእግዚአብሔር ዕቅድ አንፃር ልናስቀምጣቸው ይገባል፡፡ ወደ ኋላ ወደ አዳም መመለስ ይኖርብናል፡፡ አዳም ይንቀሳቀስ የነበረው እንደ ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ ነበር፡፡ በዚህ ምድር ላይ የነበረውን የገዢነት ሥልጣን፣ ንጉሥነቱንና የበላይነቱን በአንድ በኩል አጣ፡፡ እንደገና የተነሳው በአብርሃም ቃል ኪዳን ውስጥ በእስራኤል መንግሥት ነው፡፡ ገና በዘፍጥረት ምዕራፍ 17 እንኳን፣ ከአብርሃም ዘር ነገሥታት እንደሚወጡ ተስፋ ተሰጥቷል፡፡ ያም በእስራኤል ውስጥ፣ በተለይም በነገሥታቱ እውን ሆኗል፡፡ የብሉይ ኪዳን ንግሥና ገና በተግባር ከመገለጡ ብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ በዘዳግም ምዕራፍ 17 በሙሴ ውስጥ መታወጁ፣ በዚህ ዓለም ላይ ኃጢአት እንደገና እንደሚያንሠራራ፣ በነገሥታት፣ ከዳዊት ዘር በሆኑት ደግሞ ኅዳሴ እንደሚመጣ ያመለክተናል፡፡ ከዚያም በበለጠ ደግሞ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመምጣቱ እነዚህን ኃላፊነቶች፣ ማለትም፣ የዳዊትን፣ የእስራኤልን፣ በዋናነትም የአዳምን ሃላፊነቶች ተወጣ፣ እኛንም አስቀድመን ወደ ነበርንበት ስፍራችን መለሰን፣ እነዚህ ሁሉ አስቀድመው ተስፋ የተሰጠባቸው ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ ደረጃ በደረጃ ሲገለጡ እኛን ለእግዚአብሔር እቅድ ያዘጋጁናል፣ “የሚመጣው ይህ ነው፡፡ የሚገለጠውም እርሱ ነው፡፡ ንጉሡ እነዚህን ሃላፊነቶች የሚወጣው እንዲህ ነው፡፡” ወደሚለው መሲሃዊ መሪ ሃሳብ ይመሩናል፡፡ [ዶ/ር ስቴፈን ዌሉም]
ሙሴ ህዝበ እስራኤልን ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንዲገባና እንዲወርስ ሲያዘጋጀው፣ እግዚአብሔር በፍጻሜው ንጉሥ እንደሚያነግሥላቸው አብራርቶላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር የሚሾመው ንጉሥ የሚመራባቸውንም አራት መርሆች ዘርዝሯል፡፡ በዘዳግም ምዕራፍ 17 ከቁጥር 14 እስከ 21 ሙሴ ምን እንደጻፈ አድምጡ፡
አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ፥ በወረስሃትም ጊዜ፥ በተቀመጥህባትም ጊዜ። በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ በላዬ ንጉሥ አነግሣለሁ ስትል፥
አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን በላይህ ታነግሣለህ ከወንድሞችህ መካከል የሆነውን በአንተ ላይ ንጉሥ ታነግሣለህ ወንድምህ ያልሆነውን ከሌላ ወገን ሰው በላይህ ንጉሥ ታደርግ ዘንድ አይገባህም።
ነገር ግን ለእርሱ ፈረሶችን አያበዛም እግዚአብሔር፦ በዚያ መንገድ ደግማችሁ አትመለሱም ብሎአችኋልና ፈረሶችን ለማብዛት ሕዝቡን ወደ ግብፅ አይመልስም።
ልቡም እንዳይስት ሚስቶችን ለእርሱ አያበዛም ወርቅና ብርም ለእርሱ እጅግ አያበዛም።
በመንግሥቱም ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ ይህን ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ።
አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፥ ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኰራ ከትእዛዙም ቀኝና ግራ እንዳይል፥ እርሱም ልጆቹም በእስራኤል ልጆች መካከል ረጅም ዘመን ይነግሡ ዘንድ መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፥ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው።
ሙሴ ከንግሥና ጋር የሚዛመዱ አራት መርሆችን ዘርዝሯል፡፡ በመጀመሪያ፣ የእስራኤል ነገሥታት በእግዚአብሔር ሊመረጡ ይገባል፡፡ ህዝቡ እግዚአብሔር በሚጠብቅበት መንገድ የሚመራውን ንጉሥ የመምረጥ ብቃት የለውም፡፡ ከእግዚአብሔር በውክልና የሚገኝን ሥልጣን የመስጠት መብት የላቸውም፡፡ ሥልጣኑን በውክልና ሊሰጥ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ለመረጠው ሰው የሚሰጠው እርሱ ብቻ ነው፡፡
በዘዳግም ምዕራፍ 17 ሙሴ የጠቀሰው ሁለተኛ ነገር ንጉሡ እስራኤላዊ ሊሆን እንደሚገባው ነው፡፡ ያም ማለት፣ እግዚአብሔር የመረጠው መንግሥት ዜጋ ሊሆን ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህም በዘፍጥረት ምዕራፍ 17 ከቁጥር 1 እስከ 8 እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን ከዘሩ በእሥራኤል ላይ ንጉሥ የሚሆን እንደሚያስነሳ የሰጠው ተስፋ ፍፃሜ ነው፡፡
ዘዳግም ምዕራፍ 17 የሚያስቀምጠው ሦስተኛ መመዘኛ ንጉሡ ሰላምንና ብልፅግናን ለማምጣት በሰዎች ስልቶች ከመደገፍ ይልቅ በእግዚአብሔር ሊደገፍ የሚገባው መሆኑ ነው፡፡ ነገሥታት በእግዚአብሔር ከመደገፍ ዘወር ሊሉ የሚችሉባቸውን አራት መንገዶች ሙሴ ዘርዝሯል፡፡
ለጦር ሠራዊቱ አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ፈረሶችን እንዲያከማቹ አይፈቀድላቸውም፡፡ ንጉሡ የምድሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ በሰዎች ጉልበት ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር ሊታመን ይገባል፡፡
ለአስተማማኝ ጥበቃና መግቦት ከእግዚአብሔር ይልቅ ኃያል መንግሥትን ተስፋ ከማድረግ ጋር የተዛመደው ወደ ግብጽ የመመለስ አድማ ሌላው ነው፡፡
ለልዩ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል በጋብቻ መተሳሰርንና በርካታ ሚስቶችን ማግባትን መከልከሉ ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ነገር የሚፈጥረው ችግር እስራኤል ከእግዚአብሔር ይልቅ በውጪ ነገሥታት እንድትታመን በማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ከሌላ አገር የሚመጡ ሚስቶች እንግዳ አማልክትን ማምለካቸው አይቀሬ ስለሆነ፣ ነጉሡንም እንደነርሱ እንዲሆን ሊፈታተኑት ይችላሉ፡፡
በብዙ መጠን ወርቅና ብርን ማከማቸት መከልከሉም ኢ-ፍትሃዊ ቀረጥ ለመሰብሰብ እንዳይፈተኑ ከማገድ ጋር ይዛመዳል፡፡ ንጉሥ ባለጠጋ መሆኑ ስህተት የለበትም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ህዝብ በመበዝበዝ መክበር ወንጀል ነው፡፡
በጠቅላላው፣ እነዚህ ክልከላዎች ንጉሡ ለንግሥናው ፅናት እና ለምድሪቱ ደህንነት በእግዚአብሔር እንዲታመን የሚያደርግ ነው፡፡
ሙሴ በዘዳግም ምዕራፍ 17 ያነሳው አራተኛ ነገር ንጉሡ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ሕግ በመቀበል፣ በመፃፍና በማሰላሰል ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታማኝ ሊሆን እንደሚገባው ነው፡፡ እነዚህ ተግባራት ግላዊ አክብሮትን፣ ተገቢ ትኅትናን ታማኝ ገዢነትን ከማበረታታት አንፃር የተነደፉ ናቸው፡፡
የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ የህዝቡ ወኪሎች ናቸው:: ስለዚህም በብዙ መንገዶች የእግዚአብሔር ወኪል በመሆን በምድር፣ የህዝብ ወኪል በመሆን ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት የመቆም ቅዱስ ተግባር ይፈፅማሉ፡፡ ስለዚህም ይህ ያለባቸው መንታ ደረጃ፣ እግዚአብሔር ለንጉሡ ለራሱ ከዚያም አልፎ ለምድሩ በጠቅላላ ከሚሰጠው ምላሽ አንፃር ወሳኝነት አለው፡፡ እንደማስበውም፣ ጠቅላላ ታሪኩን በእስራኤልና በይሁዳ ውስጥ ታገኙላችሁ፡፡ በእስራኤል ውስጥ አንድም መልካም ንጉሥ አታገኙም፡፡ ሁሉም ብልሹዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህም በ722 ዓ›ዓ. አስቀድመው ወደቁ፡፡ በይሁዳ ውስጥ ግን ነገሩ ወሰድ መለስ ዐይነት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን የሚያደርግ መልካም ንጉሥ ይነሣል፣ ወዲው ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሚያደርግ ንጉሥ ይነሳል፡፡ ክፉዎቹ ነገሥታት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ሲፈፅሙ የከፋ መዘዝ ይከተላል፡፡ ያም “አይሆንልኝም” የሚል የአግዚአብሔር መለኮታዊ ፍርድ በንጉሡና በህዝቡ ላይ ይወድቃል፡፡ እናም በንጉሡ ይዞታና ህዝቡም እርሱን ተከትሎ ከመሄዱ ረገድ መሠረታዊ ግንኙነት ያለ ይመስላል፡፡ ንጉሡ በኮረብታዎች ላይ ጣዖታትን ካመለከ፣ ሕዝቡም ያንኑ ያደርጋል፡፡ ልክ በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን እንደሆነው ዐይነት፣ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ካለ ደግሞ ህዝቡ በጠቅላላ ለእግዚአብሔርና ለህግጋቱ ምላሽ ይሰጣል ስለዚህም ተቃራኒው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ፣ ንጉሡ እግዚአብሔርንም ህዝቡንም ይወክላል ማለት ነው፡፡ [ዶ/ር ማርክ ጊግኒሊአት]
በሙሴ የተገለጠውን የንግሥና መመዘኛ ከተመለከትን፣ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር በቃል ኪዳን ያካተተውን ተጨማሪ መመዘኛ እንመለከታለን፡፡
ከዳዊት ጋር የተደረገ ቃል ኪዳን
በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 7 ከቁጥር 8 እስከ 16 እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳንና በመዝሙር 89 እና 132 ዝርዝሮቹ ተጠቅሰዋል፡፡ ይህ ቃል ኪዳን የዳዊት ዘር የእስራኤል ቋሚ ሥርወ መንግሥት እንዲሆን ይደነግጋል፡፡ እግዚአብሔር የዳዊት ዘር በስርወ መንግሥቱ እንዲጸና በማድረግና እስራኤልም በንጉሣዊ ሥርዓቱ ሰላማዊ ሽግግር እንድትደሰት በማድረግ ለዳዊትና ለእስራኤል ታላቅ ቸርነትን አደረገ፡፡ በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 7 ከቁጥር 8 እስከ 16 እግዚአብሔር ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን አድምጡ፡
አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ
በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ።
ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥ እንደ ቀድሞው ዘመንና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ። ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል።
ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥቱንም አጸናለሁ።
እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።
እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ
ከፊቴም ከጣልሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም።
ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፥ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል።
በዚህ መለኮታዊ ቃል ኪዳን መሠረት፣ በእስራኤል ስለሚነግሠው ንጉሥ እግዚአብሔር አዲስ መመዘኛ ጨመረ፡፡ ከዚህ ጊዜም ጀምሮ፣ የእግዚአብሔር ህዝብ በዳዊት ልጅ ይመራ ጀመር፡፡ በእራኤል ላይ ህጋዊና ዘላቂ የገዢነት ሥልጣን ያለው የእርሱ ቤት ብቻ ነው፡፡
ገና በጠዋቱ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ፣ የይሁዳ ነገድ በእስራኤል ንጉሥነት ተባረከ፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 49 ውስጥ ያዕቆብ “በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም” ሲል ተናገረ፡፡ ዳዊት ከይሁዳ ነገድ እስከሆነ ድረስ፣ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባው ቃል ኪዳን በዘፍጥረት የተነገረው በረከት ሙላት ነው ማለት ነው፡፡ አንድ ቀን ከይሁዳ ነገድ የሆነ ንጉሥ እንደሚነግሥ እግዚአብሔር ላይሻር ወስኗል፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት ካለው መሰጠትና መታዘዝ የተነሳ፣ የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ከዳዊት ዘር እንዲሆኑ በዘላቂነት ተስፋ ሰጠው፡፡ ማንም ሰው ከዳዊት ቤት ካልሆነ በስተቀር በእስራኤል ላይ ንግሥና ይገባኛል ሊል አይችልም፡፡ የወንጌላት ጸሐፍት በእግዚአብሔር የተጠራ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጠው ከዳዊት ዘር የሆነ ብቻ መሆኑንም ማረጋገጥ ያስፈለጋቸው በዚያ ምክንያት ነበር፡፡
የንጉሥነትን መመዘኛዎች ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ በብሉይ ኪዳን የነገሥታትን ተግባር ወደሚዳስሰው ወደ ሁለተኛው ርዕሳችን እንሸጋገር፡፡
ተግባር
በብሉይ ኪዳን፣ የእስራኤል ነገሥታት አስቀድመው የእግዚአብሔርን ህግ ተግባር በመግለጥና በማስተዳደር የእግዚአብሔርን ህዝብ በታማኝነት ይገዙ ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ትምህርቶች እንደተመለከትነው፣ በጥንታዊቷ ቅርብ ምሥራቅ ውስጥ የሚገኙ ኃያል ነገሥታት ወይንም ሱዜሪያኖች ደካማ ነገሥታትን ድል በማድረግ አገልጋያቸው ወይንም ቫሳሎቻቸው የማድረጉ ነገር የጠለመደ ነበር፡፡ ሱዜሪያኖቹ ከቫሳሎቻቸው ጋር ያላቸውነ ግንኙነት የሚያስተዳድሩት በውሎች ወይንም በቃል ኪዳኖች አማካይነት ሲሆን፣ ቫሳል መንግሥታቱም የማረካቸው ሱዜሪያን ያወጣውን ህግ በመጠበቅ መገዛት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ እስራኤልም ከእግዚአብሔር ጋር በነበራት ግንኙነት ይኸው ነገር እውነትነት ነበረው፡፡ አገሪቱ በጠቅላላ የእግዚአብሔርን ቃልኪዳን የመጠበቅ ሃላፊነት አለባት፣ ንጉሡም ያንን መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
ነገሥታት ህዝባቸው ለእግዚአብሔር ህግ ተጠያቂ መሆኑን የሚያረጋግጡባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ በዚህ ትምህርት ግን፣ ኢየሱስ ከህጉ ዋና ነገር ብሎ በጠራው ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ያም በማቴዎስ ምዕራፍ 23 ቁጥር 23 ላይ ይገኛል፡
…ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤… (ማቴ 23፥23)
በኢየሱስ አባባል፣ በተለያዩ ስርዓቶችና ወጎች ላይ ከሚያተኩሩት ፈሪሳዊያን በተቃራኒው፣ የህጉ ዋነኛ መለያ ፍርድ፣ ምህረትና ታማኝነት ነው፡፡
የብሉይ ኪዳን ነገሥታት ከእነዚህ ዋነኛ ከሆኑ የህጉ ባህርያት አንፃር የእግዚአብሔርን ህግጋት እንዴት እንዳስፈፀሙ በየተራ እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ነገሥታት ፍርድን ከማድረግ አንፃር የነበረባቸውን ሃላፊነት እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ፣ ንጉሡ ምህረትን በተግባር መግለጥ የሚገባው መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ንጉሡ ታማኝነትን ሊያሳይ እንደሚገባው አንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ በንጉሡ ፍርድ አድራጊነት ላይ እናተኩራለን፡፡
ፍርድ/ፍትህ
ከነገሥታት ሃላፊነት አውድ አንፃር፣ ፍርድ እያንዳንዱን ሰው እንደሚገባው ከእግዚአብሔር ህግጋት አንፃር መዳኘት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡
እንደ ግለሰቦች ወይም ገዢዎች፣ ቀና የሆነውን ወይንም የኃጢአትን ጎዳና የመምረጥ መብቱም ነፃነቱም አለን፡፡ በመጨረሻው ግን በእግዚአብሔር ፍርድ ፊት እንቆማለን፡፡ እነዚህም ነገሥታት ይፈረድባቸዋል፡፡ ኢየሱስ ሲመጣ ነገሮችን ሁሉ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ያደርጋል፡፡ እስከዚያው ግን ተልዕኮ አለን፡፡ ያም እንደ ግለሰቦች ለእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገባና እንደ ሰማያዊ ዜጋ መኖር ይኖርብናል፡፡ ለጊዜው፣ ሌሎችን በማክበር፣ ደካሞችን በማገዝ፣ ፍትህ ለጎደለባቸው በመሟገት፣ ገና ኀጢአት በሞላባት፣ በተሰበረች ዓለም፣ በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ባለች ዓለም፣ ተንኮል፣ ድኅነት፣ ግድየለሽነት እና ሙስና በነገሠባት ዓለም እየኖርን መሆኑን በማሰብ ፍትህን ለማስፈን በብርቱ በመጣር ፍትህንና እኩልነትን ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል፡፡ ልክ ብርሃን እንደሚሰጥ ሻማ፣ ምንም ያህል ክፋት፣ ሙስና እና ጭካኔ በምድር ቢበዛና ዕድሜ የጠገበ ቢሆንም፣ ፍትህ ስለ ጎደለባቸው ግድ የሚለው፣ አፍቃሪ አባት በሰማይ ስላለ፣ ሁሉ ጊዜያዊ ነው፣ በመጨረሻው እግዚአብሔር ሁሉን መልካም ያደርጋል ብለን ልናሳስባቸው ይገባል፡፡ [ዶ/ር ጆናታን ኩታብ]
የእስራኤል ነገሥታት ቢያንስ በሁለት የተለያዩ ደረጃዎች የእግዚአብሔርን ፍትህ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ የእግዚአብሔርን ህግ በእስራኤልና በሌሎች መንግሥታት ውስጥ በማስረፅ የእግዚአብሔርን ዓለም አቀፋዊ ፍትህ ያሳያሉ፡፡
ነገሥታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትህን የሚያሳዩበት መንገድ በ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 5 ከቁጥር 1 እስከ 12 ሰሎሞን እንዳደረገው ከሌሎች መንግሥታት ጋር መደራደር ነው፡፡
ነገሥታት በተጨማሪም ፍትህን አጥብቀው የሚፈልጉበት መንገድ ጦርነት ነው፡፡ ይህንንም የሚያከናውኑት ክፋትን የተሞሉ ነገሥታትን በመቅጣት ሲሆን በ1ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 14 ቁጥር 47 እና 48 ሳዖል እንዳደረገውና በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 8 ከቁጥር 1 እስከ 13 ዳዊት እንዳደረገው ነው፡፡ በተጨማሪም በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 5 ከቁጥር 17 እስከ 25 ዳዊት እንዳደረገው፣ በ2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 19 ሕዝቅያስ እንዳደረገው እስራኤል በሌሎች ስትጠቃ በመከላከል ፍትህን ያሰፍናሉ፡፡ በጌታና በአነርሱ ላይ በሚያምፁ ነገሥታት ላይ የእስራኤል ነገሥታት የሚወስዱትን ፍትሃዊ እርምጃ መዝሙር 2 ጠቅለል አድርጎ አቅርቦታል፡፡ እስኪ ከቁጥር 6 እስከ 12 ያሰፈረውን እንመልከት፡
እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ።
ትእዛዙን እናገራለሁ እግዚአብሔር አለኝ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።
ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ።
በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃዎች ትቀጠቅጣቸዋለህ።
አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ።
ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።
ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው። (መዝ 2፥6-12)
እነዚህ ጥቅሶች በጥንታዊቷ ቅርብ ምሥራቅ ሱዜሪያኖቹ እንደ አባት ቫሳሎቻቸውን እንደ ልጅ የሚቆጥሩበትን ልማድ የሚከተሉ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ፣ እግዚአብሔር ሱዜሪያን ነው ከዳዊት ዘር የሆነው ንጉሥ ደግሞ ቫሳል ነው፡፡ እናም እግዚአብሔር ለመላው ዓለም ያለው እቅድ በመንግሥታት ከዳዊት ዘር ለሆነው ንጉሥ እንዲገዙና እንዳታዘዙት ነው፡፡ እርሱን ሊፈሩትና ሊያከብሩት ይገባል ምክንያቱም እርሱ የእግዚአብሔርን ፍትህ በምድር የሚያመጣ የእግዚአብሔር መሣሪያ ነውና፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ነገሥታት በእስራኤል ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ ፍትህን የማስፈን ሃላፊነት አለባቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ህዝብ ለእርሱ ህግጋት ወደ መገዛት በመምራት ብሔራዊ ፍትህን ያሰፍናሉ፡፡ ይህም ተግባር በምሳሌ ምዕራፍ 29 ቁጥር 14 እንደሰፈረው ደካሞችን በመጠበቅና የሚያስፈልጋቸውን በማዘጋጀት፤ ዳዊት በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 4 ከቁጥር 9 እስከ 12 በተምሳሊትነት እንዳሳየው ክፉዎችን በመመከት፤ በ2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 14 ቁጥር 5 እንደምናገኘው ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ፤ መዝሙር 72 እንደሚያስተምረን ለዜጎች ዕድገትና ብልፅግና መረጋጋትን በማስፈን ይከናወናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ነገሥታት ለባለ ጠጋው ወይንም ለድሃው፣ ለኃያሉ ወይንም ለደካማው በማድላት ፍትህን አያዛቡም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለዚህ ተግባር በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ቁጥር 15 እና ኢሳያስ ምዕራፍ 11 ከቁጥር 1 እስከ 5 ያለውን አካትቶ በበርካታ ቦታዎች ይናገራሉ፡፡
እንደገና አንድ ጊዜ ኢየሱስ ከህጉ ዋነኛ ስለሆነው ነገር ያወሳውን በመጥቀስ፣ ነገሥታት የእግዚአብሔርን ህግ በተግባር ከሚገልጡበት ዋነኛ መንገድ ሁለተኛው ምህረት ነው፡፡
ምህረት
ምህረት እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያለውን ርኅራሄ የሚገልጥበት መንገድ ነው፡፡ የፈጠራቸው ፍጡራን ሲበድሉ፣ እግዚአብሔር ድካማቸውን በመረዳት ይታገሳቸዋል፡፡ ለፍጡሩ በጎነትን ማሳየት ደስ ስለሚያሰኘው፣ በሕይወታቸው መልካሙን ያደርግላቸዋል፣ ከመከራም ያሳርፋቸዋል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር ምህረት በበርካታ ስፍራዎች ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም፣ መዝሙር 40 ቁጥር 11፤ መዝሙር 103 ቁጥር 8 እና ዮናስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 2 ይጠቀሳሉ፡፡
ከፍትህ አንፃር፣ ነገሥታት ቢያንስ በሁለት መንገዶች ምህረትን ያሳያሉ፣ ከዓለማቀፋዊ ግንኙነት ጀምሮ ማለት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ነገሥታት ለእስራኤል አምላክ ራሳቸውን ላስገዙ መንግሥታት ምህረትን ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 10 ቁጥር 19 ላይ ከእስራኤል ጠላቶች መካከል አንዱ ከዳዊት ጋር ሰላምን ባደረገ ጊዜ እርሱም ምህረትን አድርጎለት እንደነበር እንመለከታለን፡፡ በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 10 ቁጥር 1 እና 2 ላይ ደግሞ፣ ዳዊት ለአሞናውያኑ ንጉሥ ሲራራለት እንመለከታለን፡፡
በተጨማሪም፣ በስተመጨረሻው የአህዛብ መንግሥታት ለኢየሩሳሌም እንደሚገዙ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ተንብየዋል፡፡ ለእግዚአብሔር መንግሥት መናገሻ ከተማ ይገብራሉ፣ እግዚአብሔር ከሰየመውም ንጉሥ ምህረትንና ጥበቃን ያገኛሉ፡፡ እነዚህም ትንቢቶች በኢሳያስ ምዕራፍ 60 ከቁጥር 1 እስከ 22፣ ምዕራፍ 66 ከቁጥር 18 እስከ 23፤ ሚክያስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 8 እና ሰፎንያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 11 ውስጥ ተመዝግበዋል፡፡
እርግጥ ነው፣ ስለ ፍትህ በተመለከትነው ርዕሳችን፣ እግዚአብሔር ዘወትር ምህረትን አያደርግም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለክፉ ነገሥታት ንጉሡ ምህረትን እንዳያደርግ እግዚአብሔር ያዛል፡፡ ለምሳሌ፣ በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 5 ከቁጥር 17 እሰከ 25፣ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ጨርሶ እንዲያጠፋ እግዚአብሔር አዘዘው፣ ዳዊትም ያለ አንዳች ምህረት ያንኑ አደረገ፡፡ ክፋታቸው እጅግ በዝቶ ስለነበረ አልተረፉም፡፡ እንግዲያው፣ እግዚአብሔር መቼ ምህረትን ማድረግ እንደሚሻና መቼ ደግሞ እንደማይሻ መለየት የነገሥታት አንዱ ሃላፊነት ነው፡፡
በዓለም አቀፋዊ ደረጃ ምህረትን ከማድረግ ባሻገር፣ ነገሥታት በብሔራዊ ደረጃም ምህረትን በማድረግ የእግዚአብሔርን ህግጋት ሊያስፈፅሙ ይገባል፡፡ ንጉሡ የእግዚአብሔር ቫሳል በመሆኑ ምክንያት፣ እግዚአብሔር ህዝቡን ሊይዝ በሚፈልግበት መንገድ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ያም ማለት በምህረት ሊይዛቸው ይገባል ማለት ነው፡፡ ሆሴዕ ምዕራፍ 6 ቁጥር 6 የመሳሰሉ ክፍሎችን ስናብብ፣ በህጉ ላይ የተደነገጉትን መስዋዕቶች ከማቅረብ ይልቅ ህዝቡ ምህረት እንዲያደርግ እግዚአብሔር እንደሚሻ ተጠቅሷል፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ህግጋት አስፈላጊ ስላልሆኑ ሳይሆን፣ ምህረት ከህጉ ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ምህረትን የሚያደርግ ንጉሥ ተወዳጅ ንጉሥ ነው፣ በዚያም እግዚአብሔር ለህዝቡ ያለውን የክብካቤ አምሳል ያመለክታል፡፡ ዳዊትም ይህንን እንደ 2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 19 ከቁጥር 18 እስከ 23 በመሳሰሉ ስፍራዎች ራሳቸውን ላስገዙለት ነገሥታት ምህረትን በማድረግ ገልጦታል፡፡
ምህረትን በብሉይ ኪዳን ህግጋት ሁሉ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ህጉን እንደ ክፉ የመመልከታችንን ብዥታ ወዲያ ትተን በእውነት ህጉ የእግዚአብሔር ፍቅር የሞላበት በጎነቱ መግለጫ እንደሆነ መመልከት ብንጀምር፣ በሁሉም ስፍራ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ዐሥርቱ ትዕዛዛትን እንደመነሻ ነጥብ ብንወስደው፣ ሰንበትን እንድንቀድስ የተሰጠውን ትዕዛዝ እናገኛለን፡፡ ይህንንም የእግዚአብሔር ትዕዛዛት የመጀመሪያ ክፍል ስናነብብ በሰንበት ቀን እኛ ብቻ እንድናርፍ ሳይሆን፣ በእኛ ስር ያለው ነገር ሁሉ ማለትም፣ ቤታችን፣ አገልጋዮቻችን እና መንጋዎቻችን ሁሉ እንዲያርፉ የሚያዝዝ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በዘመናዊው ዓለማችን፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ወንዶችና ሴቶች ባለሀብቶች ሠራተኞቻቸውን እንደ ጥሪት ጉልበታቸውን ሊያሟጥጡ ሳይሆን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሊመለከቱዋቸውና ሊራሩላቸው ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ለሰጠን ህዝብ ባለአደራ ልንሆን ይገባል፡፡ ያን ጊዜ ምህረት የሞላበት መግቦት ይኖራል፡፡ በብሉይ ኪዳን ህግጋት ውስጥ፣ ምህረትን የሚያመለክቱ ዝርዝር ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡ በዘዳግም በእርሻ ዳር ያለውን ቃርሚያ ስለ መተው በተሰጠው ትዕዛዝ ውስጥ፣ የተቸገሩ ወደዚያ መጥተው የተተወውን እንዲሰበስቡና የሚበሉትን እንዲያገኙ ተደንግጓል፡፡ ከሃገር ሰው አራጣ መቀበልን የሚከለክለውን ህግ የመሳሰሉ ሌሎችም የብሉይ ኪዳን ህግጋት አሉ፡፡ በዚያን ዘመን የነበረው ዓለም ይከተል የነበረው የካፒታሊስቱን የኤኮኖሚ ስርዓት አልነበረም፣ ስለዚህም የወለድ ክፍያው ሰዎችን ለመበዝበዝና ለማንገላታት ነበር፡፡ ያም የለጋስነት ተቃራኒ ነበር፡፡ አንድ ሰው ወገኑ የሆነውን የተቸገረ እስራኤላዊ ለመበዝበዝ ከሞከረ፣ እንደምታውቁት ራሱን ያበለፅጋል፣ ይህንን የሚደርገው ግን ሌሎችን ገፍፎ ነው፡፡ ስለዚህም ህጉ ያንን አታድርጉ ይላል፡፡ በፈንታው፣ ለተቸገሩ በልግስና አበድሩ፣ ወለድንም አትቀበሉ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌም በየሰባት ዓመቱ የሚደረገው በህጋዊ ውል ነፃ የመውጣት ስርዓት፣ ሰዎችን ከገቡበት ያልተጠበቀ መራቆትና ሁኔታ ነፃ የሚያወጣው የኢዮቤልዩ ዓመት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህም የተሃድሶ ህግጋት፣ እግዚአብሔር ለህዝቡ መሃሪ መሆኑንና፣ እነርሱም የእርሱን ባህርያት ያንፀባርቁ ዘንድ በብሉይ ኪዳን ህግጋት የተሰጡ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ [ቄስ ማይክ ግሎዶ]
ከፍትህና ከምህረት ባሻገር፣ ነገሥታት የእግዚአብሔርን ህግ ከመፈፀም አንፃር ሊያሳዩ የሚገባው ሦስተኛ ነገር ለእግዚአብሔር ታማኝነትን መግለጥና ማበረታታት ነው፡፡
ታማኝነት
ታማኝነት ከልብ በሆነ መታመንና መታዘዝ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ተብሎ ሊገለጥ ይችላል፡፡ ታማኝነት እግዚአብሔር ነኝ ያለውን ነው፣ ሌሎች አማልክትን ወዲያ ብሎ እርሱን በታማኝነት ማገልገልን እና ፍቅር በተላበሰ መንገድ እርሱን መታዘዝን ያካትታል፡፡
በፍትህና በምህረት እንዳደረግነው ሁሉ፣ ከዓለም አቀፋዊው መድረክ በመጀመር ንጉሥ ሊያሳይ የሚገባውን ታማኝነት በሁለት መንገዶች እንመለከታለን፡፡ የእስራኤል ነገሥታት የእግዚአብሔር ህዝብ ለአምላኩ ታማኝ ሆኖ እንዲዘልቅ በመምራት በአካባቢያቸው የሚኖሩ መንግሥታት ከጣዖት አምልኮዎቻቸው በመመለስ እግዚአብሔርን ማገልገል እንዲጀምሩ ያደርጋሉ፡፡ ነገሥታትም ይህንን ሃላፊነታቸውን በእስራኤል ውስጥ እውነተኛ አምልኮ እንዲኖር በማድረግ ይወጣሉ፡፡ ይህንንም በ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 8 ከቁጥር 41 እስከ 43 ሰለሞን በጸሎት መቅደሱን ለጌታ አሳልፎ በሰጠበት ጸሎት ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡ ይህንን መንግሥታትን ደቀመዝሙር የማድረግና የመቅጣት ሥልጣን መዝሙር 72 ከቁጥር 8 እስከ 11 እና ዘካርያስ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 20 እስከ 23 በመሳሰሉት ምንባቦች ውስጥም ተገልጧል፡፡
ነገሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለእግዚአብሔር ታማኝነትን ከማሳየት ባሻገር፣ በብሔራዊ ደረጃም ታማኝነት እንዲኖር ያበረታታሉ፡፡ በተለይም ነገሥታት በመንግሥተ እስራኤል ውስጥ ታማኝነትን የሚያበረታቱበት መንገድ የአምልኮ ንፅህና እንዲኖር ማበረታታትና ማረጋገጥ ነው፡፡ መልካም ነገሥታት ለአምልኮ አስፈላጊውን ግብዓት ያቀርባሉ ያቅዳሉ፣ ሰዎችን ያስተባብራሉ፣ ለመቅደሱ መታደስ አስፈላጊውን ፖሊሲ ይቀርፃሉ ደግሞም ህዝባዊ አምልኮ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ዳዊት በ1ኛ ዜና ምዕራፍ 15፣ 16 እና ከ23 እስከ 28 ውስጥ ይህንን አድርጓል፡፡
ንጉሡ እስራኤልን ወደ ታማኝነት ለመምራት የሚያሳየው መሰጠት በምድሪቱ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት የምድሪቱ ተወካይ በመሆኑ ምክንያት፣ ህዝበ እስራኤል፣ ታማኝ በሆኑ መንግሥታት ዘመን የተትረፈረፈ በረከትን፣ ተአማኒነታቸውን ባጓደሉት ዘመን ደግሞ ብርቱ ፍርድን ያስተናግዳል፡፡ ታማኝ የሆኑ ነገሥታት በረከትን በእስራኤል ውስጥ በማምጣትና ደንበሯንም በማስፋት ይባርካቸዋል፡፡ ተአማኒነታቸውን ያጎደሉ ነገሥታት ደግሞ ይቀጣሉ፡፡ እንዲያውም ከፊሉ የነገሥት መጽሐፍ ለይሁዳ መማረክ የእሥራኤልን ነገሥታት ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ እስኪ በ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 9 ቁጥር 6 እና 7 የንጉሥ ሰሎሞንን ቃሎች አድምጡ፡
እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥
እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ። (2ነገሥ9፥6-7)
የሚያሳዝነው ግን፣ ሁሉም የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት ለእግዚአብሔር ታማኞች አልነበሩም፣ በውጤቱም የእስራኤል ህዝብ መከራውን ያይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን መቅደሱ ቸል ሲባልና ህዝበ እስራኤልም በአምልኮተ ጣዖት ውስጥ ሲዘፈቅ፣ ታማኝ የሆኑ ነገሥታት የምድሪቱን አምልኮ ማደስና እንደገና እንዲያንሰራራ ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ይህንንም በ2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 18 ከቁጥር 1 እስከ 8 ሕዝቅያስ፣ በ2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 22 ከቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 23 ቁጥር 25 ደግሞ ኢዮስያስ አከናውነውት እንመለከታለን፡፡ የኅዳሴ ጥረታቸውም በእግዚአብሔር ህዝብ ውስጥ ታማኝት እንዲያንሰራራ አበረታትቷል፣ ያም ክንዋኔ በንግሥናቸው ዘመን እግዚአብሔር ምድሪቷን እንዲባርክ አነሳስቶታል፡፡
የብሉይ ኪዳን ነገሥታትን መመዘኛና ተግባር ከተመለከትን፣ ወደፊት ከሚመጣው የእስራኤል ንጉሥ ብሉይ ኪዳን የሚጠብቀውን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
ጥበቃ / መጠባበቅ
ብሉይ ኪዳን ወደፊት ከሚመጡት ነገሥታት የሚጠበቁ በርካታ ነገሮችን አስቀምጧል፣ በተለይ ደግሞ መንግሥቱን በምድር ላይ የማምጣትን እግዚአብሔራዊ ግብ እንደሚያሳካ በትንቢት የተነገረለትን መሲሃዊ ንጉሥ የሚመለከቱ በርካቶች ናቸው፡፡ እናም አዲስ ኪዳን ይህ መሲሃዊ ንጉሥ ኢየሱስ መሆኑን አስረግጦ ይነግረናል፡፡ ስለዚህም፣ እነዚህን የብሉይ ኪዳን ጥበቃዎች በጥልቀት ልንመለከት ይገባናል፡፡
በእስራኤል ከሚነግሡ የወደፊት ነገሥታት ስለሚጠበቀው ነገር የተነገሩትን ከሁለት ምንጮች እንቃኛለን፡ አንደኛ፣ በብሉይ ኪዳን የነበረውን የንግሥና ታሪካዊ እድገት፤ ሁለተኛ፣ ወደፊት ስለሚመጣው የእስራኤል ንጉሥ የተነገሩ ለየት ያሉ ትንቢቶችን እንመለከታለን፡፡ እስኪ አስቀድመን በታሪካዊው የንግሥና እድገት የተቀመጠውን ጥበቃ እንመልከት፡፡
ታሪካዊ እድገት
በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ ሰብዓዊ ነገሥታት የነበራቸውን ወሳኝ ሚና፣ ከፍጥረት ጅማሬ አንስቶ በእስራኤል ይገዙ እስከነበሩት መሳፍንት ዘመን ድረስ የነበረውን የቅድመ ንግሥና ዘመን በመመልከት እንጀምራለን፡፡
ቅድመ ንግሥና
እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር፣ አዳምና ሔዋን በፍጥረቱ ላይ የእርሱ ረዳት ሆነው ይገዙ ዘንድ በኤድን ገነት አስቀመጣቸው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ዘር የሰጠውን ይህንን ሃላፊነት አዳምንና ሔዋንን በእርሱ አምሳል ለመፍጠር ባቀደበትና በፈጠረበት በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 26 እና 27 ውስጥ እናገኛለን፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ የአምላክ አምሳል፣ የአማልክት ምስያ እና የአምላክ ልጅ የሚባሉት ቃላት በአብዛኛው ለነገሥታትና ለገዢዎች አገልግሎት ላይ ይውሉ ነበር፡፡ ይህም አባባል ነገሥታት የአማልክቶቻቸው ምክትሎች መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ የንጉሡም ድርሻ፣ የአምላኩ ፈቃድ በምድሪቷ ላይ መፈፀሙን ማረጋገጥ ነው፡፡ እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔር አምሳል መሆናቸውን ሲያመለክት፣ የሰው ዘር በሙሉ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ምክትል አስተዳዳሪ እንዲሆን ማመልከቱ ነው፡፡ ሰፋ ባለው አመለካከት፣ የሰው ዘር በሙሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ ነገሥታት ፈቃዱ በምድር ላይ እንድትሆን ራሳቸውን እንደሰጡ ታማኞች እንዲኖሩ ተፈጥረዋል ማለት ነው፡፡ መለኮታዊ አምሳሎች ንጉሣዊ መገለጫዎች ናቸው የሚለው ሃሳብ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን እግዚአብሔር የሰጠው ሥልጣን የተጠቀሰበትን ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 28 ያብራራል፡
እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። (ዘፍ 1፥28)
እግዚአብሔር መላውን ምድር እንደገና ወደ ራሱ መንግሥት መመለስ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህም፣ በእግዚአብሔር ብዙ አምሳሎች ምድርን የሚሞሉትን እና ፍጥረተ ዓለሙን ሁሉ በመግዛት የሚወክሉትን የሰው ልጆች ይሾማል፡፡ ይህም ትዕዛዝ ባህላዊ ሥልጣን ይባላል ምክንያቱም በመላው ዓለም ላይ ባህልን በመቅረፅና ስልጣኔን በማምጣት የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድንመሠርት ያዛልና ነው፡፡
አዳምና ሔዋን በኃጢአት ከወደቁ በኋላ፣ ከቀደመው ሃላፊነታቸው እነርሱና ዝርያዎቻቸው ሁሉ እጅግ ራቁ እግዚአብሔርም የሰውን ዘር በጠቅላላ በኖህ ዘመን በውሃ ማጥለቅለቅ ቀጣ፡፡ ይህም ሆኖ ግን፣ የሰው ዘር በዓለም ላይ ያለውን የንግሥና ሥልጣን አልሰረዘም፡፡ ኖህና ቤተሰቡ ከመርከቡ ከወጡ በኋላ፣ በዓለም ላይ እግዚአብሔርን የሚያከብር ሥልጣኔ እንዲያመጡ ንጉሣዊ አምሳሎቹን በማዘዝ ባህላዊውን ሥልጣን እግዚአብሔር መልሶ አፀናው፡፡
ሆኖም የሰው ዘር የእግዚአብሔር ወኪል የመሆኑ ነገር ግልጥ በሆነ መንገድ በአብርሃም ዘመን ለወጥ ያለ መልክ ያዘ፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን በመቤዠት የመረጠው ህዝቡ የእስራኤል አባት አደረገው፡፡ ጠቅለል ባለው መልክ የሰው ዘር በሙሉ የእግዚአብሔር ወኪል ቢሆንም፣ አብርሃምና ዘሩ በምድር ለሚገኙ ቤተሰቦች ሁሉ የበኩር ልጅ እንዲሆን ተመረጠ፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 15 ቁጥር 17 ላይ፣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መንግሥትን ለመመሥረት እስራኤል ይህ ንጉሣዊ ዕድል የተሰጣት መሆኑን የሚያመለክት ቃል ኪዳን ከአብርሃም ጋር አደረገ፡፡ እናም ይህች መንግሥት የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሌሎቹም መንግሥታት ላይ ለማምጣት መነሻ ሆነች፡፡
ከጥቂት የታሪክ ዘመናት በኋላ፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባውን ይህንን ተስፋ ሙሴና ኢያሱ እስራኤልን እንዲመሩ በማስነሳት ፈፀመው፡፡ በእነርሱም አመራር፣ ህዝቡን ከግብጽ ባርነት አወጣ፣ የተስፋዪቱን ምድር ከነዓንንም ድል በማድረግ የተዋጁ ቅዱስ የእግዚአብሔር አምሳል የሚገለጥባቸው ታላቅ መንግሥት እንዲሆኑ አደረገ፡፡
የሚያሳዝነው ግን፣ እስራኤል ከነዓንን ሙሉ በሙሉ ነፃ ሳታወጣ ቀረች፡፡ ስለዚህም፣ ኢያሱ ከሞተ በኋላ፣ ብሔራዊ አንድነቷ ፈራረሰ በእነዚያ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያትም የተለያዩ መሳፍንቶችና ሌዋውያን የተለያዩ ነገዶችን ይገዙ ጀመር፡፡ ምንም እንኳን በእነዚህ ዓመታትም ውስጥ እግዚአብሔር እስራኤልን የባረካት ቢሆንም፣ የመሳፍንቱና የሌዋውያኑ አመራር እስራኤልን እንደ እግዚአብሔር ንጉሣዊ አምሳልነቷ አመራር ወደ ምትሰጥበት እርከን ለማሳደግ ብቃት የነበረው አልነበረም፡፡ የመሳፍንት መጽሐፍ ጸሐፊ ይህንን ሃሳብ በመጽሐፉ በጠቅላላ በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ በመሳፍንት ምዕራፍ 21 ቁጥር 25 ላይ በመደምደሚያው የሰፈረውን አድምጡ፡
በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር። (መሳ 21፥25)
ተመሳሳይ የሆኑ መግለጫዎች በምዕራፍ 17 ቁጥር 6፤ በምዕራፍ 18 ቁጥር 1 እና በምዕራፍ 19 ቁጥር 1 ላይም ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ድግግሞሾችም አፅንዖት የሚሰጡት እስራኤል እንደተመረጠ መንግሥት የእግዚአብሔር ወኪል ሆና ወደፊት ትገፋ የነበረው ጽድቅን በሚከተሉ ነገሥታት አመራር ዘመን ብቻ እደሆነ ነው፡፡
እንግዲህ፣ የመሳፍንት መጽሐፍ መጪውን ንጉሥ ከማመልከት አንፃር አግባብነት ያለው ነው፡፡ በመሳፍንት መጽሐፍ ውስጥ አንድ የማይቋረጥ ሰንሰለት እንመለከታለን፣ ያም አንድ መስፍን ይነሳል ለጥቂትም ጊዜ መልካም ይሆናል፣ ግን ወዲያው ህዝቡ በኃጢአት ይወድቃል፣ ከዚያም ወደ እግዚብሔር ይጮሃል፣ እግዚአብሔርም ሌላ መስፍን ያስነሳል፡፡ እናም ፀሐፊው አንድ የተረጋጋ፣ አስተማማኝና እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነ ገዢ እና መሪ የሚያስፈልግ የመሆኑን ነገር በግልፅ ያመለክታል፡፡ ይህም ነገር በዳዊት ህይወት በተግባር ተገልጧል፡፡ ዳዊት እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነ፣ ንግሥና ምን እንደሚመስል ያሳየ ተምሳሊት፣ ለእስራኤል ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር በምድር ላለ የሰው ዘር በሙሉ ሊሰጥ የሚሻውን አመራር ያመለከተ ነበር፡፡ ስለዚህም፣ የመሳፍንት መጽሐፍ የንጉሥን አስፈላጊነት፣ ያም ንጉሥ በእግዚአብሔር ስር ሆኖ የሚገዛ፣ እግዚአብሔር ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስካሁን እስከዛሬ ድረስ እንዴት ህዝቡን መምራት እንደሚፈልግ በማመልከት መከራከሪያ የሚያቀርብ መጽሐፍ ነው፡፡ [ዶ/ር ሲሞን ቫይበርት]
የመሳፍንትን መጽሐፍ በእግዚአብሔር የዘላለም ዕቅድ ውስጥ ማለትም ከዘፍጥረት አንስቶ እስከ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ድረስ ባለው የታሪክ መስመር ውስጥ ማስቀመጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የመሳፍንት መጽሐፍ ወደ ቀደመው መገልጥ መለስ ብሎ የሚያስቃኘን ሲሆን፣ ቅኝቱም፣ አዳምን እንደ ንጉሣዊ ተምሳሊት፣ አብርሃምን ደግሞ ከዘሩ ስለሚወጡት ነገሥታት በተገባለት ቃል ኪዳን፣ በብሉይ ኪዳን ተቀባዩ ሙሴ፣ በዘዳግም ምዕራፍ 17፣ ስለሚመጣው ንጉሥ የተተነበየበትን የሚዳስስ ነው፡፡ ሆኖም፣ በዚያች የእግዚአብሔር ዕቅድ ዘመን ውስጥ ነገሥታቶች አልነበሩም፡፡ ስለዚህም መሳፍንቶቹ፣ በአንድ በኩል፣ የመሪዎችን እና የአገዛዝን አስፈላጊነት ያመለክታሉ፡፡ ኢያሱ የሙሴን እግር ተክቶ ተነሣ፣ መሳፍንት ደግሞ በኢያሱ እግር ተተኩ፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር ይመጣል ብሉ የተናገረው ንጉሥ አልመጣም ነበር፡፡ ነገሩ ፍፃሜ አላገኘም ነበር፡፡ መሳፍንቱም እንደ አመራራቸው መጠን፣ መልካም በሆኑ ወቅት ምድሪቱ ከክፋት ትርቃለች፣ ሲከፉ ደግሞ ምድሪቷ ጎስቋላ ትሆናለች፣ እናም ንጉሥ አልነበረም፡፡ ንጉሡ ሲመጣ ግን፣ ነገሮች የተሻሉ እንደሚሆኑ የመሳፍንት መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ [ዶ/ር ስቴፋን ዌሉም]
በእስራኤል ውስጥ ነገሥታት ከመኖራቸው አስቀድሞ በነበረው ዘመን የነበረውን የሰብዓዊ ንግሥና አነሳስ ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ በእስራኤል ነገሥታት በነበሩበት ዘመን የነበረውን ታሪካዊ እድገት እንመለከታለን፡፡
የነገሥታት ዘመን
1ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 8 ከቁጥ 5 እስከ 20 እንደሚነግረን፣ በመሳፍንት ዘመን ማክተሚያ ላይ እስራኤል የአካባቢዎቿ አገሮች በንጉሦቻቸው በመመራት በነበራቸው መረጋጋት ሥርዓት ትቀና እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ የመረጠውን ንጉሥ እስኪያስነሳላቸው መጠበቅ አቃታቸው፡፡ ስለዚህም አሁኑኑ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ጠየቁት፡፡ እግዚአብሔርም የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ አድርጎ ሳዖልን ሰጣቸው፡፡
እስራኤል ንጉሥ የመሻቷ ነገር በራሱ ኃጢአት እንዳልነበረ ልንረዳ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ደጋግሞ እስራኤል በታላላቅ ነገሥታት የምትመራ ታላቅ አገር እንደምትሆን ተስፋ ሰጥቶ ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 17 ቁጥር 6 ላይ፣ ከዘሩ መካከል ነገሥታትም እንደሚኖሩ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ ሰጥቷል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 49 ከቁጥር 8 እስከ 10 ደግሞ፣ ያዕቆብ ልጁን ይሁዳን ሲባርክ ከልጆቹ አንዱ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንደሚሆን ተናግሯል፡፡ በዚህም ትምህርታችን መጀመሪያ አካባቢ እንደተመለከትነው፣ በዘዳግም ምዕራፍ 17 ከቁጥር 14 እስከ 19 ላይ ሙሴ በእስራኤል ለሚነግሡ ነገሥታት መመሪያ አስተላልፎ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ገና እስራኤል እግዚአብሔር ንጉሥን እንዲያነግሥላት ከመጎትጎቷ ቀደም ብሎ፣ ሃና እግዚአብሔር በህዝቡ ላይ ጻድቅ ንጉሥ እንደሚያስነሳ ትንቢታዊ ጸሎት ጸልያ ነበር፡፡
እግዚአብሔር በእስራኤል ስለሚነግሡት ነገሥታት መልካም ዕቅድ ቢኖረውም፣ ምድሪቱ ግን እግዚአብሔርን ባለመታመንና ባለመጠበቅ በደለች፡፡ እናም ሳዖልን በላያቸው እንዲነግሥ ማድረጉ በአንዱ ወገኑ ለዚህ በደላቸው መቀጣጫ የማድረግም ዓላማ ነበረው፡፡ ሳዖል ምንም እንኳን እስራኤልን እልፍ ያደረገ ቢሆንም፣ በእግዚአብሔር ላይ በማመፁ ምክንያት እርሱንና ዘሩን እግዚአብሔር እንዲያጠፋቸው ምክንያት ሆኗል፡፡
ነገር ግን ከሳዖል ውድቀት በኋላ፣ እግዚአብሔር ዳዊትን ንጉሥ ይሆናቸው ዘንድ በማስነሳት በቸርነቱ የሚያስፈልጋትን ዐይነት ንጉሥ ለእስራኤል ሰጠ፡፡ እንደ ሌላው የወደቀ የሰው ዘር ሁሉ ዳዊትም ኃጢአተኛ ነበር፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነም ሰው ነበር፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ምድሪቱን አንድ ያደርግ ዘንድ፣ ጠላቶቻቸውንም ድል ያደርግ ዘንድ፣ ሰላምንና ብልጽግናንም ለእስራኤል ያስገኝ ዘንድ እግዚአብሔር ኃይልን ሰጠው፡፡ ከዚያም በላይ፣ በእስራኤል ላይ የዳዊት ዘር የማይሻር የንግሥና ሐረግ ይኖረው ዘንድ ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፡፡ ስለዚህም ቃል ኪዳን 2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 7፤ 1ኛ ዜና ምዕራፍ 17 እና መዝሙር 89 እና 32 በመሳሰሉ ክፍሎች ውስጥ ተፅፎ እናገኛለን፡፡
ዳዊትም ሲሞት፣ ልጁ ሰሎሞን ከእርሱ ተከትሎ ነገሠ፡፡ በበርካታ መንገዶችም፣ የሰሎሞን ንግሥና በእስራኤል የነገሥታት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዝ ነው፡፡ የእስራኤልን ድንበር አሰፋ ደግሞም መልካም ስም እንዲኖራትና ባለፀጋም እንድትሆን አደረገ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን፣ የባዕዳን ሚስቶቹን ጣዖታት በማምለክ የእግዚአብሔርን ሕግ በእጅጉ ተላለፈ፡፡ ስለዚህም በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ዘመን ጌታ ምድሪቱ እንድትከፈል አደረገ፡፡ ከዚያም በኋላ የመጡት ትውልዶች ለእግዚአብሔር ባለመታመን የከፉ ሆኑ፣ በስተመጨረሻም አስራኤልም ሆነ ይሁዳ ከምድራቸው በመሰደድ በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ወደቁ፡፡ ሰሜናዊቷ እስራኤል በ723 ወይንም በ722 ዓ›ዓ. በአሦራውያን ተማረከች፤ የደቡቡ መንግሥት ደግሞ በ587 ወይንም በ586 ዓ.ዓ. በባቢሎናውያን ተማረከ፡፡ የመጨረሻው ህጋዊ ንጉሥ ዮአኪን፣ በ597 ዓ.ዓ. በምርኮ ተወሰደ፡፡
በንጉሣዊ አገዛዙ ማክተሚያ ላይ፣ ስለ ሰው ዘር ንግሥና እግዚአብሔር ያለውን ታላቅ ምስጢር ገለጠ፡፡ ሰፋ ባለው አተያይ፣ የሰው ዘር በጠቅላላ በምድር ላይ የእግዚአብሔር አምባሳደር ነው፡፡ ጠበብ ባለ ሁኔታ ደግሞ፣ እስራኤል ለተቀሩት መንግሥታት ተምሳሊት በሚሆን መንገድ የእግዚአብሔር የተመረጠች ወኪሉ በመሆን የተቀደሰች ዘር ሆነች፡፡ እጅግ ጠበብ ባለ መንገድ ደግሞ፣ የዳዊት ዘር የእግዚአብሔር ወኪልነት ተቀዳሚ ባለድርሻ ሆነ፡፡ የዳዊት ልጆች የእስራኤል ነገሥታት እንዲሆኑና በተቀረውም ዓለም የሉዓላዊውን ንጉሥ የእግዚአብሔርን የራሱን ፈቃድ በመስፈፀም እንዲያገለግሉ እግዚአብሔር ሾማቸው፡፡
ከእስራኤል የነገሥታ ዘመን አስቀድሞና በነገሥታቱ ዘመን የነበረውን ታሪካዊ እድገት ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ በድኅረ ንግሥና ዘመን እስራኤል በስደት የኖረችበትንና ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ ያልነበረበትን ጊዜ እንመልከት፡፡
ድኅረ ንግሥና
ምንም እንኳን ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በመደምሰስ የዳዊትን ዘር ከዙፋኑ ቢያስወግዱም፣ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ባቢሎንን ድል በማድረግ እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንዲመለሱ አዋጅ አወጣ፡፡ ይህንንም በ2ኛ ዜና ምዕራፍ 36 እና በዕዝራ ምዕራፍ 1 እናነባለን፡፡
ከቂሮስ አዋጅ በኋላ የመጣው ዘመን የተሃድሶ ዘመን በመባል ይታወቃል፡፡ ተመላሾቹም የእግዚአብሔርን መሰዊያ መልሰው ሠሩ፣ አዲስ ቤተመቅደስም ገነቡ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አደሱ፡፡ በሐጌ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 21 እስከ 23 ድረስ ነቢዩ ሐጌ ከምርኮ ለተመለሱት ቅሬታዎች በታማኝነት ከዘለቁ፣ ከዳዊት ዘር የሆነውን ዘሩባቤልን እግዚአብሔር እንደሚያነግሥላቸው ነግሯቸው ነበር፡፡ ህዝቡ ግን ለእግዚአብሔር ታማኝ አልሆነም፡፡ ስለዚህም፣ ብሉይ ኪዳን የሚያበቃው በተስፋዪቱ ምድር ውስጥ ይኖሩ በነበሩ እና ወደፊትም የሚመጣውን የክብር ተስፋ በሚጠብቁ ቅሬታዎች ነው፡፡
በብሉይና በአዲስ ኪዳናት መካከል ባለው ዘመን፣ የእስራኤል አለመታመን የእስራኤልን የንግሥና ኅዳሴ ወደ ኋላ አስቀርቶታል፡፡ የግሪክ መንግሥት የፋርስን መንግሥት ድል በመንሳት በፓለስታይን የሚኖሩትን እስራኤላውያንን በቁጥሩ ስር አደረገ፡፡ በኋላ ደግሞ፣ የሮም መንግሥት ግሪክን ድል በማድረግ የተስፋዪቱን ምድር በቁጥጥሩ ስር አደረገ፡፡ በነዚህ ሁሉ ጊዜያት ውስጥ፣ እስራኤል ከእግዚአብሔር የተሾመ ንጉሥ አልነበራትም፡፡
እስራኤል በአሦራውያን፣ በባቢሎናውያን፣ በምድያማውያን፣ በፋርስ፣ በግሪክና በሮም መንግሥታት ስረ ያሳለፈችው አሰዛኝ ሁኔታ፣ ጻድቅ የሆነው የዳዊት ልጅ ወደፊት ሊነግሥ የሚገባው የመሆኑን አስፈላጊነት በግልፅ ያመለክታል፡፡ እስራኤል እንደ ተመረጠ ህዝብ በዓለም ላይ የሚጠበቅባትን ድርሻ ለመወጣት ትችል ዘንድ ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ ያስፈልጋት ነበር፡፡ እናም ታማኝ የሆኑት የእግዚአብሔር ሰዎች እግዚአብሔር ጻድቅ የሆነውን ንጉሥ ከዳዊት ዘር በማስነሳት ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚፈፅምበትንና ከጨቋኞቻቸውም እጅ እነርሱን ነፃ የሚያወጣበትን የእግዚአብሔርንም ፈቃድ በምድር የሚፈፅምበትን ጊዜ ይጠባበቁ ነበር፡፡
የንጉሥነትን ቢሮ ታሪካዊ ዕድገት ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ በብሉይ ኪዳን ግልፅ ትንቢቶች የተነገሩና ወደፊት ከሚመጣው ንጉሥ የሚጠበቁ ነገሮችን እንመለከታለን፡፡
ውስን ግልፅ ትንቢቶች
ብሉይ ኪዳን ወደፊት በእስራኤል ውስጥ ስለሚኖረው ንግሥና የሚያወሳው በርካታ ነገር ስላለው ሁሉንም መዘርዘር አንችልም፡፡ ስለዚህ፣ ከዚህ ክፍለ ጊዜ ዓላማችን አንፃር፣ አራት ወሳኝ ርዕሰ-ጉዳዮችን ብቻ እናነሳለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የብሉይ ኪዳን ነቢያት እግዚአብሔር የዳዊትን ንጉሣዊ ዘር ያድሳል ብለው ትንቢት መናገራቸው ነው፡፡
ብሉይ ኪዳንን ስንመለከት፣ መሲሁ የዳዊት ልጅ እንደሚሆን በአፅንዖት ይናገራል፡፡ ዳዊት እጅግ ግልፅ በሆነ መንገድ በጌታ የታመነ ታላቅ የእስራኤል ንጉሥ፣ ታላቅ ድሎችን ያስመዘገበ፣ በበርካታ መንገዶችም ጌታን የታዘዘ ነበር፡፡ እርግጥ ነው እጅግ የማይዘነጋ በደልንም ፈፅሟል፣ ሆኖም ዳዊት መሲሁ ምን እንደሚመስል ማሳያ ሆኗል፡፡ በምድሪቷ ሰላምን የሚያሰፍን ገዢ ይሆናል፡፡ ዳዊትም ከሞተ በኋላ በኋላኞቹ የብሉይ ኪዳን ዘመናት የዳዊት ልጅ እንደሚመጣና በዚያም ዘመን ሰላምና ጽድቅ እንደሚኖር ከተነገረው ሃሳብ ጋር የሚጣጣም ተግባር እንደሚከናወን እንመለከታለን፡፡ [ዶ/ር ቶማስ ሽሬነር]
በብሉይ ኪዳን መሲህ ነው ተብሎ የሚታወቀው ሰው ንጉሥ ነው፣ እርሱም ከዳዊት ግንድ የሆነው ነው፡፡ ዳዊት ከእግዚአብሔር የተቀበለው ቃል ኪዳን ነበረው፣ ያም ቃል ኪዳን አንድ ቀን ልዩና ከእግዚአብሔር ጋር የአባትና የልጅ ግንኙነት ያለው ንጉሥ እንደሚመጣ የሚያመለክት ነበር፡፡ እርሱም በዳዊት ዙፋን ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ፍትህንና ፅድቅንም ያሰፍናል፡፡ እንግዲያው በእውነት፣ የብሉይ ኪዳኑን መሲህ የምናጣቅስ ከሆነ፣ የምናመለክተው ንጉሡን ነው፡፡ ያም ንጉሥ ወደር የሌለው፣ የእግዚአብሔርን ማዳንና ነፃ አውጪነት የሚያመጣ ንጉሥ ነው፡፡ [ዶ/ር ማርክ ስትራውስ]
ነቢያቱ እግዚአብሔር በመጨረሻው የዳዊትን ንግሥና በእስራኤል ላይ መልሶ የሚያመጣና ፃድቅ የሆነን የዳዊት ልጅ እንደሚልክ ተናግረዋል፡፡ ይህንንም በበርካታ ስፍራዎች የምናኝ ሲሆን፣ መዝሙር 89፤ ኢሳያስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 7 እና ምዕራፍ 16 ቁጥር 5፤ ኤርምያስ ምዕራፍ 23 ቁጥር 5 እና ምዕራፍ 33 ቁጥር 25 እና 26፤ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 34 ቁር 23 እና 24 ይጠቀሳሉ፡፡ አንዱን ለአብነት ለማንሳት ያህል፣ በአሞጽ ምዕራፍ 9 ቁጥር 11 ላይ በነቢዩ አሞጽ በኩል እግዚአብሔር የተናገረውን አድምጡ፡፡
በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፡፡ (አሞጽ 9፥11)
በሁለተኛ ደረጃ፣ ወደፊት የሚመጣው የዳዊት ልጅ የእግዚአብሔርን ህዝብ ከጠላቶቻቸው እንደሚሳርፋቸው ነቢያቱ ተንብየዋል፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ድራማዊ በሆነ መልክ በድንገት ጣልቃ እንደሚገባና ለእርሱ ታማኝ የሆኑ ህዝቡንም ከጠላቶቻቸው እንደሚያሳርፍ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ እግዚአብሔር መንገዱን የተቃወሙትን ሁሉ፣ በእስራኤል ውስጥም ያሉትን ያልታመኑትን ጨምሮ እንደሚፈርድባቸው ተናግሯል፡፡ ነቢያትም በተደጋጋሚ ይህንን ድል ከዳዊት ዙፋን ከሚቀመጠው እና የእግዚአብሔር ወኪል ሆኖ ከሚገለጠው ጋር ያገናኙታል፡፡ እነዚህ ጥበቃዎች በመዝሙር 132 ቁጥር 17 እና 18፤ ኢሳያስ ምዕራፍ 9 ከቁጥር 4 እስከ 7፤ ኤርምያስ ምዕራፍ 30 ከቁጥር 5 እስከ 17፤ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 34 ቁጥር 2 እና ዘካርያስ ምዕራፍ 12 ከቁጥር 1 እስከ 10 በመሳሰሉት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በኤርምያስ ምዕራፍ 30 ከቁጥር 8 እስከ 10 የተነገረውን ትንቢት አዳምጡ፤
በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ለሌላ አትገዛም
ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ እንጂ ሌሎች አሕዛብ እንደ ገና አይገዙአቸውም። (ኤር 30፥8-9)
በሦስተኛ ደረጃ፣ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ይህ ወደፊት የሚመጣው የዳዊት ልጅ የዘላለምን መንግሥት እንደሚመሠርት ተንብየዋል፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ታላቁ የዳዊት ልጅ በእስራኤል ውስጥ ሲገዛ፣ የእግዚአብሔርን በረከት ለዘላለም እንደሚወርሱ ዘወትር ያስተምሩ ነበር፡፡ ከዳዊት ዘር የሆነው ንጉሥ ምድርን እንደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርጋት ሲሆን፣ ህዝቡም በሰላምና በብልፅግና በጽናት ይኖራል፡፡ ይህ ጥበቃ በኢሳያስ ምዕራፍ 55 ከቁጥር 3 እስከ 13 እና በሕዝቅኤል ምዕራፍ 37 ቁጥር 24 እና 25 ውስጥ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በኢሳያስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 7 ላይ ኢሳያስ ስለሚመጣው የዳዊት ልጅ የተናገረውን አድምጡ፡-
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። (ኢሳ 9፥7)
በአራተኛ ደረጃ ደግሞ፣ የሚመጣው የዳዊት ልጅ ዓለም አቀፋዊ መንግሥትን እንደሚመሠርትም ነቢያት አስተምረዋል፡፡ የወደፊቱ የዳዊት ስርወ መንግሥት በጊዜ ብቻ ሳይሆን በመልክዓ-ምድርም ገደብ የለሽ ይሆናል፡፡ የምድርን ሁሉ ፊት ይሸፍን ዘንድ ይሰፋል፡፡ ከኃጢአታቸው በንስሓ የሚመለሱ ሁሉ ዘርና ጎሳ ሳይለያቸው የበረከቱ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡ የዚህንም ነገር ብልጭታ እንደ መዝሙር 2፣ 68፣ 72፣110 እና 122 በመሳሰሉት ውስጥ እንመለከታለን፡፡ እስኪ ዳንኤል በምዕራፍ 7 ቁጥር 13 እና 14 ውስጥ እንዴት እንዳስቀመጠው እንመልከት፡-
በሌሊት ራእይ አየሁ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው። (ዳን 7፥13-14)
የመሲሁን ተግባር ከምንረዳባቸው የብሉይ ኪዳን ክፍሎች መካከል አንዱ መዝሙር 2 ሲሆን፣ እግዚአብሔር አንድ ልዩ ንጉሥ እንደሚያስነሣ፣ በተቀደሰው ተራራው በጽዮንም ላይ ተሾሞ እንደሚነግሥ በግልፅ ይናገራል፡፡ በጥንቃቄ ካነበባችሁትም እግዚአብሔር የሚሾመው ይህ ንጉሥ መንግሥታትን ሁሉ የሚገዛ መሆኑን ትረዳላችሁ፡፡ መንግሥታትም ይገዙለታል፡፡ መንግሥታት እና በምድር ያሉ ገዢዎች ሁሉ በእግሩ ስር የሚሰግዱለትና የሚያመልኩት ባለሥልጣን ሲሆን፣ በመዝሙር 2 ውስጥ “ልጁን ሳሙት” በሚል ሐረግ ተጠቅሷል፡፡ እንግዲያው እርሱ የእስራኤል መሲህ ብቻ ሳይሆን፣ ምንም እንኳን የእስራኤልም ቢሆንም ማለት ነው፣ እርሱ የዓለም ሁሉ ጌታ፣ መላውን ዓለም ሁሉ ይገዛ ዘንድ የተገባው ጌታ ነው፡፡ ስለዚህ ስለመሲሁ ልንረዳው የሚገባን ወሳኝ ነገር፣ መሲሁ ሰብዓዊ መሆኑን እና የዓለም ሁሉ ጌታ እንደሚሆን በትክክል ልንረዳ ይገባል፡፡ [ዶ/ር ፒተር ዎከር]
ብሉይ ኪዳን የሚደመደመው ስለወደፊቱ ንግሥና ታላላቅ ተስፋዎችን በመስጠት ነው፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ ልዩ ወኪል የሆነውን የዳዊት ልጅ ይልካል፡፡ እርሱም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጠላቶች ሁሉ ድል ያደርጋል፡፡ ለእርሱ አገዛዝ ራሳቸውን የሰጡ ሁሉ የሚኖሩበት ዘላላማዊ መንግሥትንም ይመሠርታል፡፡ ይህም መንግሥት፣ የሰው ዘር ሁሉ እንደ እርሱ አምሳል ለመኖር የታቀደለትን የመጀመሪያ ዓላማ ያስፈፅማል፤ ለእስራኤልም እግዚአብሔር የነበረውን የቀደመ ዓላማ ያስፈፅማል፤ የዳዊትንም ዙፋን ሊያፀና ያቀደውን የቀደመ ዓላማ ያስፈፅማል፡፡ ጻድቁ የዳዊት ልጅ ዓለምን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥትነት ይለውጣል፣ ክፋትንም ሁሉ ጠራርጎ ያጠፋል፣ በየዘመናቱ ለኖሩት የእርሱ ሕዝብም ሰላምንና ብልፅግናን ያመጣል፡፡
ምልዓት በኢየሱስ
የንግሥናን አገልግሎት ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ወደ ሁለተኛው ዐቢይ ርዕሳችን፤ የንግሥና አገልግሎት በኢየሱስ ወደ ምልዓት መምጣቱን ወደ መመልከቱ እንሸጋገራለን፡፡ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን የተነገረለት ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ መሆኑን አዲስ ኪዳን በግልፅ ያስተምራል፡፡ ለምሳሌ፣ ሰብዓ-ሰገል በማቴዎስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 2 ላይ የአይሁድ ንጉሥ በማለት ገልጠውታል፡፡ እንደ ማርቆስ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 27 እስከ 29 በመሳሰሉት ስፍራዎች ደግሞ ደቀመዛሙርቱ ኢየሱስን መሲህ ወይንም ክርስቶስ በሚል ንጉሣዊ መጠሪያ ሲጠሩት እንመለከታለን፡፡ በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 49 ላይ ደግሞ የእስራኤል ንጉሥ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ከሁሉ እጅግ ወሳኝ በሆነ ሁኔታ ደግሞ፣ ኢየሱስ ራሱ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በብሉይ ኪዳን ተስፋ የተገባለት መሲህ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 27 ቁጥር 11 ላይ ከጴንጤናዊው ጲላጦስ ጋር ያደረገውን ንግግር አድምጡ፡-
ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም፦ አንተ አልህ አለው። (ማቴ 27፥11)
ተመሳሳይ የሆኑትን ሪፖርቶች በማርቆስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 2፤ ሉቃስ ምዕራፍ 23 ከቁጥር 1 እስከ 3 እና በዮሐንስ ምዕራፍ 18 ከቁጥር 33 እስከ 37 ባሉት ውስጥ እንመለከታለን፡፡ ምንም እንኳን ኢየሱስ በምድር አገልግሎቱ ወደ እስራኤል መንበረ ንግሥና ባይመጣም፣ አዲስ ኪዳን ተስፋ የተገባለት ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ መሆኑን በግልፅ ያስተምራል፡፡ ከዳዊትም ዙፋን ብሉይ ኪዳን የሚጠብቃቸውንም ሁሉ ለማሟላት ተመልሶ ይመጣል፡፡
የንግሥና ቢሮ በኢየሱስ ስብዕና ውስጥ ምልዓትን ያገኘ መሆኑን የዚህን ቢሮ ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ ከተመከትንበት ዳሰሳችን ጋር በሚስማማ መልኩ እንቃኘዋለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ የንጉሥነትን መመዘኛዎች ያሟላ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የንጉሥነትን ተግባር በተምሳሊትነት ያሳየ መሆኑን እናነሳለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ብሉይ ኪዳን ከወደፊቱ የንግሥና አገልግሎት የሚጠብቃቸውን ኢየሱስ ያሟላባቸውን መንገዶች እንዳስሳለን፡፡ ከኢየሱስ ንጉሣዊ መመዘኛዎች አንጀምር፡፡
መመዘኛዎች
በዚህ ትምህርት መጀመሪያ አካባቢ ላይ የሙሴ ህግ ያሰፈራቸውን አራት መመዘኛዎች ተመልክተናል፡፡ አንደኛ፣ ንጉሥ በእግዚአብሔር የተመረጠ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ሁለተኛ፣ እስራኤላዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ሦስተኛ፣ ለስኬትና ለዋስትና በእግዚአብሔር የሚታመን ሊሆን ይገባዋል፡፡ አራተኛ ደግሞ፣ በግል ሕይወቱና በአገዛዙ ቃል ኪዳናዊ ታማኝነት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ ከነዚህም መመዘኛዎች ባሻገር፣ ከዳዊት ጋር የተደረገው ቃል ኪዳን ደግሞ ንጉሡ የዳዊት ልጅ ሊሆን እንደሚገባው ያመለክታል፡፡ በዚህ ትምህርታችን እንግዲህ፣ በእግዚአብሔር ከመመረጥ በመጀመር ኢየሱስ እነዚህን መመዘኛዎች እንዴት እንዳሟላ እንመለከታለን፡፡
በእግዚአብሔር የተመረጠ
ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፣ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ሁሉ ላይ የሚገዛ ታላቁ ሱዜሪያን መሆኑን ተረድተናል፡፡ የእስራኤል ንጉሥ ደግሞ፣ የእግዚአብሔር ምርጥ ህዝብ፣ የተቀደሰው የእስራኤል መንግሥት አገልጋይ ወይንም ቫሳል ንጉሥ ነው ማለት ነው፡፡ ሥልጣንን የሚሰጠው እግዚአብሔር እስከ ሆነ ድረስ፣ በእርሱ መንግሥት ላይ የእርሱን ሥልጣን በተፈቀደላቸው መጠን እንዲጠቀሙ አግባብነት ያላቸውን ነገሥታት የሚመርጠውም እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ኢየሱስ እነዚህን መመዘኛዎች አሟልቷል፣ ምክንያቱም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መርጦታል ሾሞታልም፡፡ ይህንንም በማቴዎስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 1 እስከ 17 በተጠቀሰው የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ውስጥና መልአኩ ገብርኤል ስለ ኢየሱስ ልደት የምሥራቹን ለማርያም በነገረበት ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡ በሉቃስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 31 እስከ 33 ገብርኤል ለማርያም የተናገረውን አድምጡ፡
እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።
እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤
በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።
ኢየሱስ በህዝቡ ሁሉ ላይ ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው መሆኑን እግዚአብሔር በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ ሁለተኛው የንጉሥነት መመዘኛ እስራኤላዊ ሊሆን የተገባው መሆኑ ነው፡፡
እስራኤላዊ
ኢየሱስ እስራኤላዊ ከሆነ ቤተሰብ በመወለዱ ብቻ የእስራኤላዊነትን መመዘኛ ማሟላቱን ባንናገርም ነገሩ መፈፀሙን እንረዳለን፡፡ በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ መፀነሱና ትስጉቱ ልደቱን ያልተለመደ አድርጎታል፡፡ እርሱ ግን አሁንም የዮሴፍና የማርያም ህጋዊ ልጅ ነው፣ እናም የእስራኤል የቃል ኪዳን ማኅበረሰብ አባል ነው፡፡ ይህም በማቴዎስ ምእራፍ 1 እና በሉቃስ ምእራፍ 3 በተመዘገበው የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ውስጥ እና ኢየሱስ እውነተኛ እስራኤላዊ ዝርያ እንዳለው በሚናገረው በሮሜ ምዕራፍ 9 ቁጥር 5 በመሳሰሉት ላይ ይገኛል፡፡
ሦስተኛው የብሉይ ኪዳን መመዘኛ ንጉሡ ሰላምንና ዋስትናን ለማስፈን በሰብዓዊ ስልቶች ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር ሊታመን የሚገባው መሆኑ ነው፡፡
በእግዚአብሔር መታመን
ኢየሱስ ለህዝቡ ዋስትናንና ብልፅግናን ለማምጣት በእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ በመታመን ይህንን መመዘኛ አሟልቷል፡፡ ከሄሮድስ ወይንም ከጲላጦስ ጋር ወይንም ከሌላ ሰብዓዊ መንግሥታት ጋር ወዳጅነትን ለመመስረት አልሞከረም፡፡ በምትኩ ግን፣ ዮሐንስ ምዕራፍ 13 ቁጥር 3 እና ምዕራፍ 19 ቁጥር 10 እና 11 ላይ እንደምንመለከተው መንግሥቱን ለመመሥረትና ለማፅናት ሙሉ በሙሉ ይተማመን የነበረው በእግዚአብሔር ሥልጣንና ኃይል ነበር፡፡
ኢየሱስ ያሟላው አራተኛ የንግሥና ብሉይ ኪዳናዊ መመዘኛ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ለእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕግ ታማኝ በመሆን ቃልኪዳናዊ ታማኝነቱን በመግለጽ ነው፡፡
ቃል ኪዳናዊ ታማኝነት
ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕግ ያለው ታማኝት በብዙ መንገዶች ታይቷል፣ በተለይ ግን ለመሠረታዊ ፍቺው በሚያደርገው ጥንቃቄ እና ሕጉ የሚጠይቀውን ሁሉ ለመፈፀም ባለው መሰጠት ገልጦታል፡፡ ለምሳሌ በማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 በምናገኘው የተራራው ስብከት ውስጥ፣ በዘመኑ በነበረው ትውፊታዊ የሕጉ መምህራን ፍቺና አስተምህሮ ውስጥ ከነበረው በተቃራኒ መንገድ በሕጉ ውስጥ ለተፃፈው የመጀመሪያ ፍቺ ታማኝ መሆኑን ደጋግሞ ገልጧል፡፡ በተጨማሪም፣ እርሱ የመጣው የሕጉን ጥቃቅን ዝርዝሮች እንኳን ሳይቀር ለመፈፀም መሆኑን ተናግሯል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ከቁጥር 17 እስከ 18 ምን እንደተናገረ አድምጡ፡-
እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።
እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። (ማቴ 5፥17-18)
ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን ሃሳብ በሮሜ ምእራፍ 8 ቁጥር 3 እና 4 ላይ ኢየሱስ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለ እኛም ጭምር ሕግን ሙሉ በሙሉ ፈጽሟል በማለት አሰተጋብቶታል፡፡
ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመለክተን፣ ወደ እርሱ የሚያመጣንና ለእርሱም የሚያዘጋጀን መምህራችን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ህግ የእግዚአብሔር ባህርይ ነፀብራቅ ሆኖ ተሰጥቶናል፡፡ እኛ ግን ህጉን መፈፀም ተስኖናል፡፡ ኢየሱስ ሲመጣ ለተፈጠረበት ዓላማ የኖረን እንከን አልባ የሰው ዘር አመልክቶናል፣ ያም የሚገለጠው ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ግንኙነት ለእግዚአብሔር ህግጋት ባለ ታማኝነት ነው፡፡ ኢየሱስ መጣ፣ የሰው ዘር ሊሆን የተገባውንም አሳየን፣ ስለ እኛም ህጉን ፈፀመ፡፡ ኢየሱስ ቃል ኪዳኑን ያለማሰለስ በመጠበቅ እና ከህጉ ጋር የሚጣጣም ባህርይ በማሳየት ህጉን ፈፀመ፡፡ ስለዚህም እርሱ ጽድቃችን ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ፍትሃዊም አጽዳቂም መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ እናም በመጀመሪያ ከህጉ ጋር መጣ ስለ እኛም ህጉን ከሚፈፅመው ከልጁ ጋር ደግሞ መጣ፡፡ ስለዚህ እርሱ ጻድቅ፣ እኛንም በክርስቶስ በኩል የሚያጸድቀን እርሱው ነው፡፡ [ዶ/ር ኬ. ኤሪክ ቶኔስ]
ኢየሱስ እኛን ለመግዛት ባለመብት መሆኑን ለማሳየት ለቃል ኪዳኑ ታማኝ በመሆኑ ላይ አፅንዖት መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም ስል ወደ ኋላ መለስ ብለን አዳም ድረስ የሚወስዱንን በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ማንሳት ይገባናል ለማለት ነው፡፡ አዳም የሁላችን ራስ፣ የሰው ዘር ጠቅላላ ወኪል፣ የእግዚአብሔር ፍጥረት ወኪል እንደመሆኑ መጠን፣ሊታዘዝ እና ታማኝ ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ እኛም ፍጥረቶች ነንና በጠቅላላው ሕይወታችን ፈጣሪያችንን ልንታዘዝ የሚገባን፣ ልናገለግለው፣ ልንታዘዘው እና ልንፈቅረው የሚገባን ነበርን፡፡ ግን አዳም ባለመታዘዙ፣ ኃጢአትን፣ ሞትንና ፍርድን አመጣብን፡፡ ይህ ሁኔታ ይቀለበስ ዘንድ በሌላ አዳም፣ በሌላ የሰው ዘር አማካይነት እግዚአብሔር ራሱ መድሃኒትን ሊያመጣና ሊታደገን ይገባ ነበር፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አዳምን የሚመስል ና በነዚያ ሁሉ ነቢያት፣ ካህናት እና ነገሥታት አማካይነት ጥላውን እያሳየን በመጨረሻም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በወንጌላትም እንደተመለከተው የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈፅም ሊያዘጋጅ ይገባው ነበር፡፡ እርሱ የመጣው ሊታዘዝ ነው፡፡ ገላትያ 4 እንደሚናገረው ከሴት የተወለደው፣ ከሕግ በታች የተወለደው ህጉን ለመታዘዝ ነው፡፡ ግን ይህ ለምን አስፈላጊ ሆነ? ምክንያቱም አዳም ያበላሸውን ማቅናት ስለነበረበት ነው፡፡ በመታዘዙ፣ በዚህም ምድር በመኖሩ ህጉ የሚጠይቀውን ሁሉ አንድ በአንድ ስለ እኛ አሟላልን፡፡ በመታዘዙ ምክንያት፣ ፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 እንደሚነግረንም የእርሱ መታዘዝ እስከ መስቀል ሞት ነበር፡፡ ከዚያም ተግባር የተነሳ፣ እንደ ንጉሣችንና እንደ ካህናችን በፈፀመው ተግባር በእግዚአብሔር ቀኝ በክብር ተቀመጠ፡፡ ከዚህ ቀደም ንጉሥ ወይንም ጌታ ሆኖ እንደማያውቅ ዓይነት ግን አይደለም፡፡ እርሱ ዘወትር እንደ እግዚአብሔር ወልድ በዚያ ነበር፡፡ በሥራው ግን ትስጉተ እግዚአብሔር ወልድ ሆነ፣ በሰውነቱም ታዛዥ ሆነ፣ የታመነ ሆነ፣ ያንንም ስለ እኛ አደረገ በዚያም ድነትን ለእኛ አመጣልን፡፡ ለአብ ፍፁም የሆነ ታማኝነትንና መታዘዝን ባያሳይ ኖሮ፣ በዚያ መሲሃዊና ንጉሣዊ ተግባሩ የነገሥታት ንጉሥ የጌቶችም ጌታ መሆን ባልተሰጠው ነበር፡፡ [ዶ/ር ስቴፈን ዌሉም]
ኢየሱስ ያሟላው አምስተኛው የብሉይ ኪዳን መመዘኛ የዳዊት ልጅ መሆኑ ነው፡፡
የዳዊት ልጅ
እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳን የዳዊት ዘር በእስራኤል ቋሚ ስርወ-መንግሥት እንዲሆን አድርጓል፡፡ ስለዚህ በእስራኤል ውስጥ የንግሥና ህጋዊ መብት ያለው የዳዊት ዘር ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስም ከዳዊት ቤት የመሆኑ ነገር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በበርካታ ስፍራዎች ተቀምጧል፡፡ ጥቂቶቹን ለማስፈር ያህል፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 1 እስከ 25፤ ሮሜ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 1 እስከ 3፤ ራእይ ምዕራፍ 5 ቁር 5 እና ምዕራፍ 22 ቁጥር 16 ይጠቀሳሉ፡፡
ኢየሱስ ለንግሥና የነበሩትን መመዘኛዎች ከተመለከትን፣ ኢየሱስ የንግሥና አገልግሎት የፈፀመባቸውን መንገዶች ወደመመልከቱ እንሸጋገር፡፡
ተግባር
በዚህ ትምህርት መጀመሪያ አካባቢ፣ የንጉሥ መሠረታዊ ተግባር እርሱ በቫሳልነት በሚያስተዳድረው መንግሥት ውስጥ የእግዚአብሔር ታማኝ ወኪል ገዢ መሆን፣ በተለይም የአግዚአብሔርን ሕግጋት ማስተዳደር መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ዘመን ሁሉንም ሥራውን እንዳልፈፀመ ክርስቲያኖች ሁላችን እናውቃለን፡፡ በመሠረቱ፣ ኢየሱስ አሁንም በሰማያት ተቀምጦ ደግሞም በቤተክርስቲያናት ውስጥ ሥራውን ቀጥሏል፡፡ በመጨረሻውም ሥራውን ወደ ፍፃሜ ለማምጣት ይመለሳል፡፡ እርሱ ክርስቶስ፣ መንግሥቱንም ያድስ ዘንድ የተላከ ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ ለመሆኑ እውቅና እንድንሰጥ ከሚያስችለን በላይ የሆኑ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
እንደ ንጉሥ ኢየሱስ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለአገልግሎቱ ብሉይ ኪዳን ካስቀመጠልን ዳራ አንፃር መመልከት እንችላለን፡ ፍትህን ማስፈን፣ ምህረትን ማድረግ እና ታማኝነትን ማሳየት ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ኢየሱስ ፍትህን የማስፈኑን ነገር እንመለከታለን፡፡
ፍትህ
የብሉይ ኪዳኑን ዳራ በተመለከትንበት ወቅት፣ የፍትህን ጉዳይ በሁለት ጎራዎች ከፍለን ተመልክተነዋል፣ አሁን ከዓለም አቀፋዊው ጎራ አንፃር በመመልከት እንጀምራለን፡፡ በአብዛኛው የምድር አገልግሎቱ ወቅት፣ ኢየሱስ በቀጥታ በሰብዓዊ መንግሥታት ጉዳይ ውስጥ አይገባም ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎችን ከሰይጣን መንግስትና ከአጋንንቶች አስራት ደግሞም ከኃጢአት የጭቆና አገዛዝ በማላቀቅ ፍትህን ሲያሰፍን ነበር፡፡ ቅዱሳት መጻሕፈት ይህንን እንደ ሉቃስ ምዕራፍ 11 ከቁጥር 14 እስከ 20፤ ኤፌሶን ምዕራፍ 2 ቁጥር 2 በመሳሰሉ ስፍራዎች በእግዚአብሔር መንግሥትና በሰይጣን መንግሥት መካከል የተደረገ ጦርነት በማለት አስቀምጠውታል፡፡ እንግዲያው፣ ይህን ተግባር የብሉይ ኪዳን ነገሥታት ዓለምአቀፋዊ ፍትህን በጦርነት ለማምጣት ከሚፈፅሙት ተግባር ጋር ማነፃፀሩ ምክንያታዊ ነው፡፡ ኢየሱስም በማቴዎስ ምዕራፍ 12 ቁጥር 28 ላይ እንዲህ ብሏል፡
እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። (ማቴ 12፥28)
በዚህ ጥቅስ፣ አጋንንትን የማስወጣቱ ተግባር የእግዚአብሔር መንግሥት ከሰይጣን መንግሥት ጋር የመፋለሟ ማረጋገጫ መሆኑን ኢየሱስ አመልክቷል፡፡ የብሉይ ኪዳን ነገሥታትም ከጎረቤት መንግሥታት ጋር ሰላማዊ ድርድር በማድረግም ዓለም አቀፋዊ ፍትህን ያሰፍናሉ፡፡ ምንም እንኳን ኢየሱስ ይህንን ተግባር ደጋግሞ ያልፈፀመው ቢሆንም፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 2 እንደምናነበው፣ ከምሥራቅ ከመጡ ጠቢባን ሰላማዊ እጅ መንሻን ተቀብሏል፡፡ እነዚያ ጠቢባን የውጪ መንግሥታት ወኪሎች ነበሩ፣ ዓላማቸውም በመንግሥታቸውና በእስራኤል በተወለደው ንጉሥ መካከል በጎ ፈቃድን መመሥረት ነበር፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትህን ከማስፈን በተጨማሪ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ፍትህ በእስራኤልም እንዲከበር ያደርግ ነበር፡፡ ልክ እንደሌሎቹ ሰብዓዊ መንግሥታ ሁሉ፣ ኢየሱስ በግለሰባዊ ክርክሮች ውስጥ ጣልቃ አይገባም ነበር፡፡ እነዚያን የመሳሰሉትን ለሌሎች አነስተኛ ሸንጎዎችና ዳኞች ይተወው ነበር፡፡ በህዝቡ መካከል ፍትህ እንዲሰፍን ደግሞ ደጋግሞ ያነሳሳ ነበር፡፡ ይህንንም እንደ ማቴዎስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 25 እና 26 እና ምዕራፍ 12 ከቁጥር 15 እስከ 21፤ እንዲሁም ሉቃስ ምዕራፍ 18 ቁጥር 7 እና 8 በመሳሰሉት ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡ ኢየሱስ በተጨማሪም ተመልሶ በሚመጣበት ቀን ለጎውም ሆነ ለክፉው ብድራት እንደሚመልስና እያንዳንዲቷም ነገር እንደምትመዘገብ ተናግሯል፡፡ ይህም የንጉሣዊ ተግባሩ ገፅታ በማቴዎስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 15፣ ምዕራፍ 11 ከቁጥር 22 እስከ 24 እና ምዕራፍ 12 ቁጥር 36 ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በዚያም ስፍራ ወደፊት የሚመጣ ብርቱ ፍርድ እንደሚኖር ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም ያንን ፍርድ የሚበይነውም እርሱ መሆኑን በዮሐንስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 22 ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡
ፍትህን ከማስፈንም በተጨማሪ፣ የእግዚአብሔርን ህግ በምህረት ተግባራዊ በማድረግ የንጉሥነትን ተግባር ፈፅሟል፡፡
ምህረት
ኢየሱስ ንጉሣዊ ምህረትን የገለጠው እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ባለው ርኅራኄ ልክ ነው፡፡ ሰዎች ሲበድሉ በመታገሥ ታጋሽነቱን አሳይቷል፡፡ ድክመታቸውንም ይረዳል፡፡ ስለዚህም ይራራላቸዋል፡፡ ከመከራቸውም ያሳርፋቸዋል፡፡
ንግሥናን ከሰብዓዊ የንግሥና ታሪካችን አንፃር ስናስበው፣ ዘወትር የምናስበው የምይገሰስ ስልጣን ስላለው ስለ አንድ ሰው ነው፡፡ እነርሱ በአካባቢው ብቅ ሲሉ ሰው ሁሉ ይሰግድላቸዋል፣ ያሻቸውንም ይፈጽምላቸዋል፣ ንጉሥ የተመኘው ሁሉ ይፈፀማል፡፡ የኢየሱስ ንግሥና ግን፣ በሕይወቱ ባከናወናቸው ተግባራት ሁሉ፣ መላውን ዓለም የገለባበጠ ነበር፡፡ ይህንን በማስብበት ወቅት ዓለምን ስለፈጠረው ፈጣሪ የተገለጠበትን የዮሐንስ ወንጌሉን አንደኛ ምዕራፍ አስባለሁ፡፡ ወደ ገዛ ወገኖቹ መጣ የራሱ የሆኑት ግን አልተቀበሉትም ይላል፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው፣ ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ አምናለሁ ብሎ አስረግጦ ቢናገር፣ አስከትሎ ደግሞ አሁን የጠቀስነውን ጥቅስ ቢጠቅስ፣ ራሱ ወደ ፈጠረው ዓለም መጥቶ ቀባይነትን እንዲያጣ የሚፈቅድ ምን ዓይነት ንጉሥ ነው? ብለን መጠየቃችን አይቀሬ ነው፡፡ እንግዲያው እኔ እንደማስበው፣ ምህረት ያደረገልን ጌታ ስለ እኛ በማዘኑ ምክንያት ብቻ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው አዝኗል፣ ግን እኔ እንደማስበው ከዚያ በዘለለ መንገድ የእግዚአብሔርን ውስጣዊ ባህርይ እየገለጠ ነው፡፡ ምህረት ከስላሴ ሕይወት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በእኔ አስተሳሰብ፣ ስላሴ ገና ከጥንት ዘላለም አንስቶ፣ ንጉሡ ራሱ ማለትም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ፣ የፍጥረተ ዓለም ሁሉ ንጉሥ አሃዱ ስሉስ ሆነው አንዱ ለሌላው ራሱን እየሰጠ አብ ለወልድ፣ ወልድ ለአብ፣ መንፈስ ደግሞ ለሁለቱ እርስ በርስ በመሰጣጣት ይኖራሉ፡፡ እንግዲያው ኢየሱስ ለኃጢአተኞች ምህረትን ያደርግ ዘንድ ሲመጣ፣ የንጉሡ ራስን የመስጠት መገለጥ የሆነውን ራስን የመስጠት ፍቅር ለመግለጥ ነው የመጣው ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው ይፈርዳል፡፡ የሚፈርደው ግን እርሱን ለመውደድ ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ ነው፡፡ ወደ ምድር ሲመጣ ግን፣ የሚመጣው ወደተንገላቱት፣ በዲያቢሎስ በራሱና በክፋት ኃይላት የመከራ ድር ወዳደራባቸው ነው፡፡ ንጉሡም ሲመጣ፣ ከእንግዲህ ወዲያ አንዳችም ሸክም አልጭንባችሁም፣ በመጀመሪያ፣ የምመጣው ራሴን ለእናንተ ለመስጠት ነው ይላቸዋል፡፡ ስለዚህ የሚያከናውነው የምህረት ተግባር ሁሉ፣ በስላሴ ውስጥ የነበረውን ራስን ለሌላው አሳልፎ የመስጠት እግዚአብሔራዊ ልብ በዓለም የሚገልጥ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ የእኛ ንጉሥ ተግባሩን የሚያከናውነው አንዲህ ነው፡፡ ራሱን ለመስጠት እንጂ፣ ከሰዎች ያንንና ይህንን እንዲያደርጉ በመጠበቅ አይመጣም፡፡ እኔ እንደማስበው ምህረት አስቀድሞ በእግዚአብሔር ልብ የነበረው ራስን ለሌሎች አሳልፎ የመስጠት አስደናቂ ፍቅር መገለጫ ሲሆን፣ ይህም በኢየሱስ ትስጉትነት እርሱ በደረሰበት ሁሉ ለሰዎች ተገልጧል፡፡ በመሠረቱ የዚህ ምህረትን ለእኛ የመግለጥ ተግባሩ ከፍተኛ እርከን የተገለጠው በመስቀል ላይ ንጉሡ ነፍሱን አሳልፎ በሰጠበት ወቅት ሲሆን፣ ከዚያም የተነሳ ለድነት የሚሆነውን የእግዚአብሔርን ምህረት አገኘን፡፡ ስለዚህ እርሱ በንግሥናው ምህረት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገለጠ ብቸኛና እውነተኛ ምህረትን የተሞላ ንጉሥ ነው፡፡ [ዶ/ር ቢል ዑሪ]
ኢየሱስ ምህረትን የተሞላ ስለሆነ መጥቶ ምህረትን አሳየን፡፡ አሁን እያሰብኩ ያለሁት፣ ስለበረከቶቹ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ እጅግ ያስገርሙኛል፡፡ ሁለተኛው ቡራኬ እንዲህ ይላል፡ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መፅናናትን ያገኛሉና፡፡ ለእኔ ያ ማለት ብፁዓኖቹ የእግዚአብሔርን ልብ የሚሰብር ሁሉ ልባቸውን የሚሰብረው ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ሰው ሲሆንና ወደዚህ ሲመጣ፣ የፈጠረውንም ዓለም ሲመለከት እርሱን የሚያሳዝኑ ነገሮችን ተመለከተ፡፡ ስለዚህ ዝም ብሎ ከማልቀስ ይልቅ፣ ባዶ እንባንም ከማፍሰስም ይልቅ፣ በምህረት ወደ እነዚህ ሁኔታዎች እራመዳለሁ ብሎ ወሰነ፡፡ ምህረት የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳኑ የግሪክ ቃል ሲፈታ በአንድ ሰው ቆዳ ውስጥ አብሮ የመጠረዝ ዓይነት እነደሆነ ባርክሌይ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ ስለዚህ መራራት የሚለው መረዳት ሌሎች ሰዎች የሚሰማቸው ስሜት ልክ እንደነሱ ሆኖ እኔንም ይሰማኛል ማለት ነው፡፡ እዚያ ባለመገኘቴ ደስተኛ ነኝ ከማለት ይልቅ እነርሱ ያሉበትን መከራ ለመካፈል ወደዚያው እሄዳለሁ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ እነርሱ እንቀሳቀሳለሁ፣ እግዚአብሔር አብም ለእነርሱ አሁን በዚህ ሰዓት እንድሆንላቸው የሚፈልገውን እሆንላቸዋለሁ፡፡ [ዶ/ር ማት ፈሬድማን]
ኢየሱስ ምህረትን የገለጠበትን መንገድ በሁለት እርከኖች እንመለከታለን፡፡ አስቀድመንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካከናወነው እንጀምራለን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ንጉሡ ለእግዚአብሔር ራሳቸውን ለሰጡ ህዝቦችና መንግሥታት ምህረትን ያደርጋል፡፡ ኢየሱስም ይህንን በበርካታ መንገዶች አከናውኗል፡፡ አንዱም፣ ከእስራኤል ውጪ ለሚገኙ ለበርካታ አህዛብ ተአምራዊ ፈውስን መስጠቱ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 28 ላይ የከነዓናዊቷን ሴት ልጅ ፈውሷል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 8 ቁጥር 13 ደግሞ የሮሜውን መቶ አለቃ አገልጋይ ፈውሷል፡፡ በማርቆስ ምዕራፍ 5 ከቁጥር 1 እስከ 20 ባለው ክፍል ደግሞ ጌርጌሴኖን በሚባል የአህዛብ ግዛት የሚኖርን አንድ ሰው ሌጌዎን ከሚባል የአጋንንት ጭፍራ ነፃ አውጥቷል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ኢየሱስ ጢሮስን፣ ሲዶናን እና ጌርጌሴኖንን ጨምሮ በበርካታ የአህዛብ አካባቢዎች አገልግሏል፡፡ በሉቃስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 32 ሽማግሌው ስምዖን እንደተነበየውም መልዕክቶቹና ሥራዎቹ ለአህዛብ ብርሃን የሚያወጡ መገለጦች ነበሩ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገለጠው ምህረቱ ንጉሣዊ ከመሆኑ እጅግ በላቀ መንገድ ኢየሱስ በብሔራዊ ደረጃ የገለጠውም እጅግ የጎላ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ህዝቡ እንዲገለገሉለት በሚፈልገው ዓይነት ኢየሱስም እንደ ንጉሥ የእግዚአብሔርን ህዝብ የማገልገል ሃላፊነት ነበረበት፡፡ ያም ማለት ህዝቡን በምህረት ልብ መመልከት ማለት ነው፡፡ እውነተኛው ንጉሥ የእግዚአብሔርን የራሱን ለህዝቡ ግድ የሚሰኝ ልብ የሚገልጥ መሃሪ ነው፡፡ ኢየሱስም እንደ ንጉሥ ለእስራኤል አስደናቂ ምህረትን አሳይቷል፡፡ በትዕግሥትም እያስተማረና እያባበላቸው ለዓመታት አብሯቸው ኖሯል፡፡ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ተዓምራት አድርጓል፡፡ በሽተኞቻቸውን ፈውሷል፣ አጋንንትን አስወጥቷል፣ ለተራቡት ምግብን ሰጥቷል ሙታንንም እንኳን አስነስቷል፡፡
ከነዚህ ሁሉ ግን ንጉሣዊ ምህረቱን አጉልቶ ያሳየው ፈውስ፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 9 ከቁጥር 1 እስከ 7፤ በማርቆስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 11 እና በሉቃስ ምዕራፍ 5 ከቁጥር 17 እስከ 25 የተመዘገበው የሽባው ሰው መፈወስ ነው፡፡ በዚያ ፈውስ ውስጥ ኢየሱስ ሽባውን መፈወስ ብቻ ሳይሆን፣ ኃጢአቱንም ይቅር ብሏል፡፡ በሉቃስ ምዕራፍ 7 ከቁጥር 36 እስከ 50 ባለውም ክፍል እግሩን ሽቱ የቀባችውን ሴት ኃጢአት ይቅር ሲል ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽሟል፡፡
እንግዲህ፣ ኃጢአትን ማስተሰረይ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ለምን ሆነ? ለሚለው ጥያቄ ፈጣን ምለሽ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መልስ፣ የበደልነው እርሱን ስለሆነ ነው የሚል ነው፡፡ እርሱ ጌታ ነው፡፡ እርሱ ፈጣሪ ነው፡፡ እኛን የሠራ እርሱ ነው፡፡ የእኛ ሁለመና እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ ኃጢአታችን ኩሁሉ አስቀድሞ በእርሱ ላይ የተደረገ ነው፡፡ አዎን አንዳችን ሌላችንን እንበድላለን፡፡ በፍጥረተ ዓለሙም ላይ የኃጢአት እንድምታዎች አሉ፡፡ ሆኖም ግን ከሁሉ አስቀድሞ ደግሞም ከሁሉም ይልቅ እኛ የእግዚአብሔር አምሳሎች እንደመሆናችን መጠን የምንሠራው የትኛውም ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ የሚፈፀም አመፅ ነው፡፡ ስለዚህም ይቅር ማለት የሚችል እርሱ ብቻ ነው፡፡ በመዝሙር 51 ዳዊት “አንተን ብቻ በደልሁ” ያለውን ልታስቡ ትችላላችሁ፡፡ የዳዊትን ሕይወት አስቡ፣ ማለቴ፣ እጅግ በርካታ ሰዎችን በድሏል፡፡ ምድሪቷን ጎድቷል፤ ኦርዮንን በድሏል፤ ቤርሳቤህን በድሏል፤ ልጁንም በድሏል፡፡ ዳዊት ግን በቀጥታ ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን እንደ በደለ ተረድቷል፡፡ የእኛ ችግር፣ በአጠቃላይ የሰው ዘር ሁሉ ችግር ይቅር ማለት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ያለማወቅ ችግር ነው፡፡ የኃጢአትን ጣጣ ማቅለል የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ [ዶ/ር ስቴፈን ዌሉም]
እኔ አንድን ሰው ስበድል ወይንም አንድ ሰው ሲበድለኝ፣ የይቅርታ ጥያቄ ይቀርባል ይቅርም እንባባላለን፡፡ በሰዎች መካከል የሚደረገውም እንዲህ ነው፡፡ አንደኛው ወገን “የደረሰብኝ በደል በእኔና በአንተ መካከል ያለንን ግንኙነት የሚያበላሽ የወዳጅነት ደንቃራ እንዲሆን አልፈቅድለትም” ይላል፣ ይህም እጅግ አስፈላጊና በእግዚአብሔር እኛም ይቅር መባላችንን እያሰብን አንዳችን ለሌላችን ልናደርገው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ እግዚአብሔር ይቅር ሲል ግን፣ የበደለኝነት ስሜቴን ሁሉ ጨርሶ በሚያጠፋ መልኩ ሲሆን፣ ያንንም እኔ ለማንም ላደርገው ማንም ደግሞ ለእኔ ሊያደርገው የሚችለው ዓይነት አይደለም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ይቅር ሲል የኃጢአትን ዕዳ ሁሉ ጨርሶ በሚደመስስ መልክ ይቅር ይላል፡፡ ይህም እጅግ አስደናቂው መለኮታዊ ይቅርታ ነው፡፡ ለምሳሌ በማርቆስ ምዕራፍ 2 ኢየሱስ ሽባውን በፈወሰበት ሰዓት “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” አለው፡፡ ነገሩንም በዚያ ተቀምጠው ይከታተሉ የነበሩ ፀሐፍት፣ ክፍሉ እንደሚነግረን “ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ለማለት የደፈረ ይህ ሰው ማነው፣ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ኃጢአትን የሚያስተሰርይ ማነው?” በማለት በልባቸው ያስቡ ነበር፡፡ ነገሩም በትክክል እንደዚያው ነው፡፡ ኢየሱስን ሲናገር የሰሙት ልክ እግዚአብሔር ይቅር በሚልበት መንገድ ልጁን ይቅር ብዬሃለሁ ሲለው ስለነበር እንደ ስድብ ቆጠሩት፡፡ ሲሰሙ በትክክል ሰሙት ምላሽ ሲሰጡ ግን በተሳሳተ መንገድ መለሱለት፡፡ የኢየሱስን አምላክነት ከሚያሳዩን በወንጌላት ከሚገኙ ክፍሎች አንዱ ማስረጃ ይህ ነው፡፡ በራሱ በማንነቱ ውስጥ ባለ መረዳት፣ እሱ ብቻውን በሚያነሳው የማንነት መግለጫ፣ ኃጢአትን ይቅር እንደሚል፣ ይህም ይቅርታ በእርስ በርስ ግንኙነት የሻከረውን የማቃናት ብቻ ሳይሆን፣ በመሠረቱ ኢየሱስ ከዚህ ሽባ ጋር ከዚህ ቀደም የትም ተገናኝቶ አያውቅምና ስለዚህ ይቅርታው የበደልን ስረ መሠረት የመነቃቀል ይቅርታ ሲሆን ይህም እግዚአብሔር ኃጢአትን ይቅር የሚልበት መንገድ ነው፡፡ [ዶ/ር ሮበርት ሊስተር]
ሁሉም ኃጢአት እርሱ ብቻውን የጽድቅ ብቸኛ መለኪያ በሆነው በእግዚአብሔር በራሱ ላይ የሚፈጸም መተላለፍና በደል ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ እግዚአብሔር ብቻ ታላቁ ንጉሥና ዳኛ እስከ ሆነ ድረስ፣ በእርሱ ላይ የተፈፀሙ መተላለፎችን ይቅር ማለት የሚችል እርሱ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ደረጃ ምህረትን የማድረግ ሥልጣን ያለው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ግን ኢየሱስ ፍፁም የሆነ የእግዚአብሔር ቫሳል ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን፣ እግዚአብሔር ኃጢአትን የማስተሰረይ ሥልጣን ሰጥቶታል፣ ስለዚህም ኢየሱስ ለህዝቡ የእግዚአብሔርን ምህረት መስጠት ይችላል፡፡
ኢየሱስ የንጉሥነትን ተግባር የፈፀመበት ሦስተኛ ተግባር ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆንን በሚገልጥ መንገድ ህጉን ተግባራዊ ማድረጉ ነው፡፡
ታማኝነት
በፍትህና በምህረት ላይ እንዳደረግነው ሁሉ፣ የኢየሱስንም ታማኝነት በሁለት ክፍሎች እንመለከተዋለን፡፡ አስቀድመንም በዓለም አቀፉ ደረጃ እንመለከተዋለን፡፡ ኢየሱስ እግዚአብሔርን መታዘዙንና እርሱን ማምለኩን የምንመለከትበት ቀጥተኛ ተግባር ለአህዛብ መንግሥታት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በመስበኩ ነው፡፡ ይህንንም በማቴዎስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 13 እስከ 25፣ ምዕራፍ 24 ቁጥር 14፤ ሉቃስ ምዕራፍ 24 ቁጥር 47 እና በተለይ ደግሞ በማቴዎስ ምዕራፍ 28 ከቁጥር 18 እስከ 20 እና በሐሥ ምዕራፍ 1 ቁጥር 8 ለደቀመዛሙርቱ በሰጠው ተልዕኮ ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡ በእነዚህ በሁለቱም ተልዕኮዎች፣ አህዛብን ሁሉ ደቀመዛሙርት እንዲያደርጉና እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቹ እንዲሆኑ ኢየሱስ ተከታዮቹን አዟቸዋል፡፡
ግን፣ ኢየሱስ በብሔራዊ ደረጃም ታማኝነትን አሳይቷል፡፡ በአህዛብ መካከል እንዳከናወነው ሁሉ፣ በእስራኤልም ውስጥ ወንጌልን በመስበክ ታማኝነቱን አሳይቷል፡፡ ከከተማ ወደ ከተማ እየተዘዋወረ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ፣ ከኃጢአትም በመመለስ ለእግዚአብሔር ተገዙ በማለት ሰዎችን ያዝዝ ነበር፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 17 ላይ የኢየሱስን ስብከት ማቴዎስ እንዴት እንዳጠቃለለው እስኪ አድምጡ፡
ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር። (ማቴ 4፥17)
በማርቆስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 15፤ በሉቃስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 32 እና ምዕራፍ 10 ቁጥር 13 ላይ ተመሳሳይ ማጠቃለያ እናገኛለን፡፡ ይህንን የመሰለውንም ስብከት በወንጌላት ውስጥ በበርካታ ስፍራዎች እናገኛለን፡፡
ኢየሱስ ለእግዚአብሔር መታመንን አስመልክቶ ይህንን የመሰለ ጠንካራ አጽንዖት ሰጥቷል፡፡ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ታማኝነት የመታመን መግለጫ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር በእውነት የእኛን ታማኝነት፣ መታመን፣ መታዘዝ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ አምልኳችን የተገባው የመሆኑ መግለጫ ነው፡፡ የአንድን ሐኪም ትዕዛዝ አልፈፅም በምትሉ ወቅት፣ የምትናገሩት ስለ ትዕዛዙ ብቻ አይደለም፤ ስለ ሐኪሙም የምትናገሩት ነገር ይኖራል፡፡ እናም እግዚአብሔርን በማትታዘዙ ወቅት፣ ከበሬታ ስለነሳችሁት ትዕዛዝ ብቻ ሳይሆን፣ ትዕዛዛቱንም ስለ ሰጠው ስለ እግዚአብሔር የሆነ ነገር መናገራችሁ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህም ታማኝነት የመታመን መግለጫ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በእርሱነቱ ደግሞም የተናገረውን የሚፈፅም ከመሆኑ አንፃር መመልከት ነው፡፡ እንግዲያው፣ ታማኝነትን ለእግዚአብሔር ማሳየት ማለት የመታዘዝ መግለጫ ነው፡፡ ጳውሎስ በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ስለ ክርስትና ሕይወት ሲናገር በሮሜ መጽሐፍ እንደገለጠው ከእምነት የሚነሳ መታዘዝ ብሎታል፡፡ ይህም የክርስትናን ሕይወት እጅግ ውብ በሆነ መንገድ ያጠቃለለ መግለጫ ነው፡፡ እግዚአብሔርን እንደማንነቱ እናየዋለን፣ እምነታችንንም በእርሱ ላይ እናደርጋለን ይህም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ወደ መታዘዝ ያመራል፡፡ የምንታመነውን እግዚአብሔርን እንታዘዘዋለን፡፡ [ዶ/ር ኬ ኤሪክ ቶኔስ]
ታማኝነት እርሱን እጅግ በቅርበት በማወቅ ከእርሱ ጋር እንመላለስ ዘንድ ኢየሱስ ለእኛ የሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ግን በየዕለቱ ለእርሱ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት እንድኖር ይጠብቅብኛል፡፡ እንድታዘዘው አያስገድደኝም፡፡ ህጉንም እንድከተል አይጫነኝም፡፡ ዛሬ የሚሰማህ ስሜት ምንም ይሁን ምን፣ በዓለም ላይ ዛሬ እየሆነ ስላለው ነገር ጥሩም ስሜት ይኑርህ መጥፎ፣ እኔ የምፈልገው ታማኝ የሆነች ሙሽሪትን ነው ይላል፡፡ ታማኝ አገልጋይ እፈልጋለሁ፣ ከልቡ የሚወድደኝን ሰው እፈልጋለሁ፡፡ እንግዲህ እርሱ የሚመለከተው እኔን መሳዩን እና ዓለምን መንፈሳዊ ብዬ ልፈታ በምሞክርበት መንገድ የምመለከተውን ዓይነት ሰው ነው፡፡ ጌታ የሚለው እኔ ከዚያ እጅግ የጠለቀ ነገር እሻለሁ፡፡ ታማኝ ልብ እፈልጋለሁ፡፡ ልክ እንደተጋቡ ጥንዶች፣ የእውነተኛ ፍቅር መሠረት የሆነውን እፈልጋለሁ፡፡ በመንገድ ላይ ምንም ይግጠም ምን ታማኝት በዚያም ውስጥ ይገለጣል፡፡ ጌታ ታማኝነትን ይፈልጋል፣ ግን ታማኝ መሆን የሚያስችለውን መንፈስ ቅዱሱን ሰጥቶ ነው፡፡ [ዶ/ር ቢል ዑሪ]
በንግሥና አገልግሎት ውስጥ የኢየሱስን ንጉሣዊ መመዘኛ እና ተግባር ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ከወደፊቱ መሲሃዊ ንጉሥ ብሉይ ኪዳን የሚጠብቀውን እንመለከታለን፡፡
ጥበቃ
በእስራኤል ታሪክ ውስጥ፣ የነገሥታቶቿ ብልሹነትና ኃጢአት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለችውን ሃላፊነት እንዳትወጣ እንቅፋት ሆኖባት እናያለን፡፡ ሙሴ፣ ኢያሱና ዳዊትን የመሳሰሉት፣ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ሕግ ያስገዙና ለህዝቡ ግድ ይላቸው የነበሩ መሪዎች እንኳን እግዚአብሔር የሚፈልገውን ሁሉ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ድንቅ ሥራ ሠሩ የሚባለው፣ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሰላምንና ፀጥታን ማስፈናቸው ነው፡፡ ህጉ ከእነርሱ የሚጠብቀውን ነገር ሁሉ በየዕለቱ መፈፀም ከአቅማቸው በላይ ነበር፡፡ ለየትኛውም የወደቀ የሰው ዘር በሕግ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት መጣር እጅግ ከባድ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር፣ ምርጥ የተባሉት መሪዎችም እንኳን በዕድሜና በሞት የተገደቡ ነበሩ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉት ችግሮች ዘካርያስ ምእራፍ 4 ቁጥር 6፤ የሐሥ ምዕራፍ 13 ከቁጥር 34 እስከ 39፤ ዕብ ምዕራፍ 4 ቁጥር 8 እና ሮሜ ምዕራፍ 8 ቁጥር 3 እና 4 ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በበርካታ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡
በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን ሕዝብ የመሩ መሪዎች እግዚአብሔር ለሕዝቡ ወዳዘጋጀው ትልቅ በረከት አልደረሱም፡፡ ፈጽሞ አልቻሉም፡፡ የወደቁና ደካማ የሰው ዘሮች ነበሩ፡፡ ውድቀታቸው ግን እግዚአብሔር በመጨረሻው እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በማክበር ሕዝቡን ይታደግለት ዘንድ ጻድቅ የሆነውን የዳዊትን ልጅ እንደሚያስነሳ ተስፋ የተገኘበት ሆነ፡፡ ይህ ንጉሥ በመንፈስ ቅዱስ በኃይል የተሞላ ስለሚሆን የሰው ዘር ድካም የሚገድበው ሊሆን አይችልም፡፡ እርሱ የቀደመውን የዳዊት ዘር ውድቀት፣ የእስራኤልን መንግሥት ውድቀት ባጠቃላይም የሰውን ዘር ሁሉ ውድቀትና ድካም እንደሚቤዥ ታዳጊ የእግዚአብሔርን ህግ በጥንቃቄ የሚጠብቅ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በኢየሱስ በኩል የላከው ንጉሥ ይህንን የሚመስል ንጉሥ ነው፡፡ በኢየሱስ፣ በጻድቁ የዳዊት ልጅ በመሲሁ አማካይነት እግዚአብሔር በመጨረሻው እኛ በራሳችን ልናከናውነው የማንችለውን ነገር ሠራልን፡፡
ኢየሱስ ያሟላቸውን የብሉይ ኪዳን ጥበቃዎች በእርሱ ንግሥና አራት ገፅታዎች ላይ በማተኮር እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ የዳዊትን መንግሥት ያደሰ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ፣ ለህዝቡ የሰጠውን ነፃነትና ድል እንቃኛለን፡፡ ሦስተኛ፣ ኢየሱስ ያመጣውን ዘላለማዊ መንግሥት እናያለን፡፡ አራተኛ ደግሞ፣ በዚያ መንግሥት ዓለም አቀፋዊ ተፈጥሮ ላይ እናተኩራለን፡፡ ኢየሱስ የዳዊትን ስርወ-መንግሥት ያደሰ በመሆኑ እንጀምር፡፡
የዳዊት ስርወ-መንግሥት
በአዲስ ኪዳን በብዙ ሁኔታዎች፣ ኢየሱስ ትንቢት የተነገረለት የዳዊትን ዙፋን የሚያድስ የዳዊት ልጅ ስለመሆኑ ተወስቷል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተመሩ ፀሐፊዎች ይህንን ትስስር በማቴዎስ ምእራፍ 1 ቁጥር 1፤ በሉቃስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 31 እና በሮሜ ምዕራፍ 1 ቁጥር 3 ላይ ጠቅሰውታል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በሐሥ ምዕራፍ 13 ቁጥር 22 እና 23 ላይ አውጆታል፡፡ ኢየሱስ ራሱም ስለ ራሱ መሲሁ የዳዊት ልጅ መሆኑን በማቴዎስ ምዕራፍ 21 ቁጥር 15 እና 16 ደግሞም በራእይ ምዕራፍ 3 ቁጥር 7 እና ምዕራፍ 22 ቁጥር 16 ላይ ተናግሯል፡፡ ይህ መረጃ ኢየሱስ በእውነት በትንቢት የተነገረለት የዳዊት ልጅ፣ በፍጥረተ ዓለሙ ላይ የእግዚአብሔርን መንግሥት ዓላማ የሚያስፈፅም የወደፊቱ መሲሃዊ ንጉሥ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ከዳዊት ዘር እንደወጣ ንጉሥ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ዓላማዎች ማስፈፀም የጀመረው በእስራኤል መንግሥት ውስጥ የነበሩትን ቅሬታዎች ማለትም ታማኝ ደቀመዛሙርትና ሐዋርያት ብለን የምንጠራቸውን ወደ ራሱ በማምጣት ነው፡፡ ከዚያም፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 28 ቁጥር 19 እና 20 ላይ እነዚህ ተከታዮቹ በተሰጣቸው ሥልጣን አይሁድንና አህዛብን ሁሉ ደቀመዝሙር በማድረግ እስከ ምድር ዳር እንዲሄዱ አዘዛቸው፡፡ የእነርሱ ደቀመዛሙርት ደግሞ በዓለም ዙሪያ እጅግ በርካታ ደቀ መዛሙርትን ያፈራሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሂደቱ ቀጥሏል፣ የእግዚአብሔርም መንግሥት በምድር ላይ በርካታውን የህዝብ ቁጥር እየሸፈነ ሲሆን በምድር ላይ በሚገኝ ሀገር ወይንም ጎሳ ውስጥም ይገኛል፡፡
ኢየሱስ በተጨማሪም ለእርሱ ታማኝ ለሆኑት ህዝቡ ነፃነትንና ድልን በመስጠት ብሉይ ኪዳን የሚጠብቅበትን አሟልቷል፡፡
ነፃነትና ድል
ኢየሱስ በምድር በነበረው ሕይወቱ፣ በህዝቡ ላይ ተጭነው በነበሩ መንፈሳዊ ጠላቶች ማለትም ኃጢአት፣ ሞትና አጋንንቶች ላይ ድልን በመቀዳጀት ለህዝቡ ነፃነትን ሰጥቷል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 21 እስከ 23 ያሉትን እነዚህን ቃላት አድምጡ፡-
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።
በነቢይ ከጌታ ዘንድ።
እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።
በዚህ ምንባብ፣ ማቴዎስ፣ የኢሱስን ልደት በኢሳያስ ምዕራፍ 7 ቁጥር 14 ላይ ከተነገረለት አማኑኤል ጋር አያይዞታል፡፡
በኢሳያስ ትንቢት አውድ መሠረት፣ አማኑኤል የተሰኘው ሕፃን ከህዝቡ ጋር በውጊያ አውድማ ውስጥ የሚገኘውን ተዋጊውን ንጉሥ እግዚአብሔርን በምልክትነት የሚያሳይ ነው፡፡ እርሱ ስለእነርሱ ይዋጋል፣ ጠላቶቻቸውንም በውጊያ ድል በማድረግ ከጭቆና አላቆ ነፃነትን ይሰጣቸዋል፡፡ ኢየሱስን ልዩ የሚያደርገው ይኸው ነው፡፡ እርሱ የሰውን ዘር ቀንደኛ ጠላት፣ ኃጢአትን ድል የሚያደርግ ትንቢት የተነገረለት ንጉሥ ነው፡፡ ይህንንም የሚመስል መሪ ቃል በዮሐንስ ምዕራፍ 8 ቁጥር 36 ላይ፣ ኢየሱስ ከኃጢአት የሚያነፃ እርሱ ብቻ መሆኑን በተናገረበት ክፍል ውስጥ ይገኛል፡፡
ኢየሱስ በተጨማሪም ለህዝቡ በሞትም ላይ ድልን ሰጥቷል፡፡ ጳውሎስም ስለዚህ ጉዳይ በሮሜ ምዕራፍ 6 ከቁጥር 4 እስከ 9 እና በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ከቁጥር 54 እስከ 57 የኢየሱስ ትንሣኤ በኃጢአትና በሞት ላይ ድልን እንዳቀዳጀን አረጋግጦልናል፡፡ እንግዲህ በአንድ ወገን ዛሬም ቢሆን ሞትና ኃጢአት ችግሮቻችን ናቸው፣ አሁንም ኃጢአትን እስከሠራን ድረስ ሰውነታችንም ምውት ነው፡፡ ነገር ግን በነዚህ ጠላቶቻችን ላይ ድልን ተቀዳጅተናል ምክንያቱም እኛን ለመቆጣጠር ኃይል የላቸውም፡፡
ከአጋንንትም አንፃር ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢየሱስ ድንቁ ንጉሣችን፣ ድል አድርጓቸዋል፣ እኛንም ባለ ድሎች አድርጎናል፡፡ አሁንም ለእኛ ችግሮች ናቸው ይፈትኑናልም፡፡ አካላዊ ጉዳት እንኳን ያደርሱብናል፡፡ ነገር ግን በእሥራት ሊያቆዩንና ነፍሳችንን ሊያጠፉ አይችሉም፡፡ ጳውሎስ በቆላስይስ ምእራፍ 2 ቁጥር 15 በአጋንንቶች ላይ ስለተቀዳጀው ድል የተናገረውን እስኪ አድምጡ፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። (ቆላስይስ 2፥15)
ኢየሱስ ዳግመኛ ሲመጣ፣ እርሱንና የእርሱን ሕዝብ የሚቃወመውን ጠላት ጨርሶ ያጠፋል፡፡ ሆኖም አሁንም እጅግ የከፋውን ነገር በሚያደርሱብን ላይ ይፈርድባቸዋል፣ ከእነርሱ ተገዢነትም እያላቀቀ ነፃነትን ያጎናፅፈናል፡፡
ሦስተኛው ብሉይ ኪዳ ከንጉሥ የሚጠብቀውና ኢየሱስ የፈፀመው ነገር ዘላለማዊ መንግሥት መመሥረቱ ነው፡፡
ዘላለማዊ መንግሥት
ተስፋ የተገባለት ንጉሥ ዘላለማዊ በሆነው መንግሥት ውስጥ እንደሚያገለግል በብሉይ ኪዳን አስቀድሞ ተነግሯል፡፡ ያም መንግሥተ ሰማያት ሲሆን ከዳዊት ዘር በሆነ ንጉሥ ለዘላለም ይኖራል፡፡ ኢየሱስ እንደ ንጉሥ የመግዛቱ ነገር ለዘላለም የሚፀና እንደሆነ በማቴዎስ ምዕራፍ 19 ቁጥር 28 እና 29፤ ምዕራፍ 25 ቁጥር 34፤ በሉቃስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 33 እና ዕብራውያን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 8 እስከ 13 ባሉት ውስጥ አዲስ ኪዳን ማረጋገጫ ይሰጠናል፡፡ ግን ይህ መንግሥት አሁን የት ነው? ለመሆኑ ኢየሱስ ይህንን ፈፅሞታል? ወይንስ ገና እስኪፈፅመው ድረስ እንጠብቃለን?
ኢየሱስ በምድር አገልግሎቱ ዘመን ካከናወናቸው ነገሮች አንዱ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር መመሥረቱ ነው፡፡ ይህም ማለት፣ በመለኮታዊ ኃይል፣ ኢየሱስ የአመፅን ድንበር እየጣሰ እና ምድርንም ወደ ባለመብቱ ፈጣሪዋ፣ ባለቤቷና ንጉሷ ይመልሳል ማለት ነው፡፡ ይህ በአመፅ ኃይላት ላይ የተወሰደ የመነሻ እርምጃ በተለያዩ ድራማዊ መልኮች ተገልጧል፡ በረቀቀ ተንኮል የሚሠሩትን የክፋት ኃይላት በመገዳደር፣ በብርሃንና በጨለማ መካከል እየተከናወነ ያለውን የማሳት ሥራ በማጋለጥ፣ ዛሬም በመከናወን ላይ ያለ ታላቅ የእግዚአብሔር ሠራዊት እንቅስቃሴ ነው፡፡ እንቅስቃሴያቸውን ጨርሶ የማሽመድመዱ ሥራ፣ ምድርንም ከእነርሱ የማፅዳቱና ለአንዴና ለዘላለም የማሰወገዱ ሥራ ይቀራል፡፡ ሊሸነፍ የሚገባው የመጨረሻውም ጠላት ሞት ነው፡፡ ስለዚህም፣ በዚህ የመንግሥት ፍልሚያ ውስጥ በመንፈሱ አማካይነት ስንሳተፍ፣ መንግሥትህ ትምጣ፣ ፈቃድህም በምድር ትሁን ልንል ይገባናል፡፡ ይህ ተፈፅሞ እናይ ዘንድ መለኮታዊ እርዳታ ያስፈልገናል፡፡ [ዶ/ር ግሌን ስኮርጂ]
የብሉይ ኪዳንን ጥበቃ ለማሟላት፣ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በኢየሱስ አማካይነት በዚህ ዓለም ተገለጠ፣ በሞቱና በትንሣኤውም ተረጋገጠ፡፡ ትንሣኤውም ሞቱ ድል መሆኑን አሳየ፡፡ ኃጢአት መፍትሄ አገኘ፡፡ በኃጢአት ምክንያት የመጣውም ሞት ድል ሆነ፡፡ በትንሣኤውም ብቻ ሳይሆን በእርገቱም ተረጋገጠ፡፡ ዛሬ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጧል፡፡ በበዓለ ሃምሳም ቀን መንፈሱን አፈሰሰው፡፡ ይህ ሁሉ የምትመጣው መንግሥት አካል ነው፡፡ ስለዚህ “የመንግሥቱ ይፋዊ በዓል” አሁን በዚህ አለ፡፡ ሆኖም፣ ኢየሱስ እንደነገረን ደግሞ፣ ወደፊትም የምንጠብቀው አለ፡፡ ስለዚህም እንፀልያለን፡፡ የጌታን ጸሎት አስቡ፣ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለን እንጸልያለን፡፡ አዎን፣ መንግሥቱ መጥታለች፡፡ ድልም ነስቷል፡፡ ሙላቱን ግን ገና እንጠብቃለን፡፡ [ዶ/ር ስቴፋን ዌሉም]
ሰዎች ለመረዳት ከሚቸገሩባቸው ነገሮች አንዶ በተለይም የአይሁድ ህዝብ መረዳት የሚያስቸግራቸው፣ የኢየሱስ የመሲሁ የመጀመሪያና የዳግም ምፅዓት ጉዳይ ነው፡፡ ለመሆኑ ኢየሱስ አንበሶች በእግሮቹ ስር ተቀምጠው ሳናይ፣ ሰዎችም ጦራቸውን ወደ ማረሻነት ሳይለውጡ፣ ሰላምም በምድር ለሰዎችም በጎ ፈቃድ ሆኖ ሳናይ እንዴት መሲህ ሊሆን እና የመሲሁንም ተግባር እንዴት ሊያከናውን ይችላል? መሲሁስ እንዴት መጥቷል ማለት ይቻላል? የተገለጠው መምጣት ብለን የምንጠራው ክስተት በኢየሱስ መምጣት ተከናውኗል፡፡ ለምድር ሁሉ ይፋ ተደርጓል፣ ተግባራቱም እጅግ ወሳኝ በሆነ መንገድ ተጀምረዋል፣ ሆኖም ግን ገና ፍፁም ወደ ሆነው ሙላታቸው ለመድረስ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ ይህም የተፈፀመውና ገና የሚመጣው መንግሥት ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ ኢየሱስ አምጥቶታልና መንግሥቱ መጥቷል፣ ብርቱ ክንዱንም በመሰንዘር የአሳቹን ክንድ ሰብሮ ነፃ ማውጣቱን ጀምሯል፡፡ ወጊያው ግን አሁንም ተፋፍሟል፣ ፍፃሜውም በወደፊት መምጣቱ ይከናወናል፡፡ [ዶ/ር ኤሪክ ቶኔስ]
ኢየሱስ በሰማይ ወዳለው ዙፋኑ ከማረጉ አስቀድሞ መሲሃዊ መንግሥቱን በግልፅ መሥርቷል፡፡ ይህንንም ኢየሱስ አጋንንትን ሲያስወጣ ይህን የሚያደርግበት ኃይል የእግዚአብሔር መንግሥት በዚህ መሆኗን ያረጋግጣል ብሎ በተናገረበት በማቴዎስ ምዕራፍ 12 ቁጥር 28 ላይና በመሳሰሉት ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡ አጋንንትን ማስወጣት መንግሥቱ ገና የምትመጣ መሆኗን ሳይሆን፣ በሙሉ ኃይሏ እዚህ እየሠራች መሆኗንና ንጉሷም ጠላቶቹን እያስለቀቀ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን እንደሚናገሩትና በርካቶችም እንደሚያስቡት መንግሥቱ በይፋ ገና አልታየም ይላሉ፡፡ ኢየሱስ እንደነገረን ግን መንግሥቱን ልክ በምድር እንዳለው ልማዳዊ ፖለቲካዊ ተቋም መጠበቅ አይገባንም፡፡ ለፈሪሳውያን በሉቃስ ምዕራፍ 17 ቁጥር 20 እና 21 ላይ እንዲህ ብሏቸዋል፡
ፈሪሳውያንም። የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤
ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። (ሉቃስ 17፥20-21)
በመጨረሻም፣ ብሉይ ኪዳን ከዳዊት ዘር ከሆነ ንጉሥ የሚጠብቀውና ኢየሱስ የፈፀመው አራተኛ ነገር ዓለም አቀፋዊ መንግሥትን መመሥረቱ ነው፡፡
ዓለም አቀፋዊ መንግሥት
ኢየሱስ ሲመለስ፣ አዲሲቷ ምድር የመንግሥቱ አካል ትሆናለች፡፡ የእርሱ መንግሥትና አገዛዝም በምድር ያሉትን መንግሥታት ሁሉ ትተካለች፡፡ አሁን ግን፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁጥር 21 እና 22 እንደምንመለከተው ዓለም አቀፋዊ ግዛቱ መንፈሳዊ ነው፡፡ ተመልሶ ሲመጣ ግን፣ አካላዊ ይሆናል፡፡ ራእይ ምዕራፍ 21 እና 22 ኢየሱስ በአዲሲቷ ኢየሩሳሌም በንግሥና ተቀምጦ የሚገዛበትን የአዲሲቷን ሰማይና ምድር ድንቅ ገፅታ ያሳየናል፡፡
አዲስ ኪዳን ኢየሱስ ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረው መሲሃዊ ንጉሥ፣ የዳዊት ልጅ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር የሚያመጣ መሆኑን ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በምድር አገልግሎቱ ዘመን ሁሉንም የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችና ጥበቃዎች እንዳላሟላ እርግጥ ነው፡፡ ግን በርካቶቹን ስለፈፀመ እርሱ እውነተኛው ንጉሥ መሆኑን አረጋግጧል፣ አንድ ቀን ተመልሶም የጀመረውን ከፍፃሜ እንደሚያደርሰው ማስተማመኛ ሰጥቶናል፡፡ ያን ቀን፣ መንግሥቱ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያዘጋጀውን ቀደምት ዓላማ ያስፈፅማል፡፡ አዲሲቷም ምድር ከኃጢአት እና ከመከራ የፀዳች፣ አስተማማኝ ሰላም፣ ዋስትናና ብልፅግና የሞላባት፣ በእግዚአብሔር መገኘትና ከእርሱም ጋር በሚኖር ኅብረት የተባረከች ትሆናለች፡፡ የእርሱ መንግሥት ትሆናለች፡፡
ስለ ኢየሱስ ንግሥና እየተነጋገርን ባለንበት ትምህርት እስከ አሁን ድረስ፣ ስለ ኢየሱስ የንግሥና አገልግሎት ብሉይ ኪዳናዊ ዳራና ጥበቃን ደግሞም በክርስቶስ ይህ አገልግሎት መፈፀሙን ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ፣ በዘመናችን የኢየሱስን ድርሻ እንደ ንጉሥ ወደምንቃኝበት የመጨረሻ ዋና ርዕሳችን እንሸጋገራለን፡፡
ዘመናዊ ተዛምዶ
የኢየሱስን ንግሥና ዘመናዊ ተዛምዶ ልንመለከት የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች ቢኖሩም፣ አንዱና ጠቃሚ የሆነው ተምሳሊት በዌስት ሚኒስትሩ አጭር ካቴኪዝም ጥያቄ እና መልስ ቁጥር 26 ላይ የሚገኘው ነው፡፡
ጥ. ኢየሱስ የንግሥናን አገልግሎት ያሳየው እንዴት ነው?
ለሚለው ጥያቄ ካቴኪዝሙ የሰጠው መልስ፣
መ. ክርስቶስ የንግሥናን አገልግሎት የገለጠው፣ እኛን ለእርሱ በማስገዛት፣ እኛን በመምራትና በመጠበቅ፣ የእኛንና የእርሱን ጠላቶች በመዋጋትና ድል በመንሳት ነው፡፡
ይህ መልስ የኢየሱስ ንግሥና በሕይወታችን ላይ ተፅዕኖ ያሳደረባቸውን ሦስት ጎራዎች ከትውፊታዊው ሲስተማቲክ ቲዮሎጂ አንፃር ይዳስሳል፡፡ አንደኛ፣ ኢየሱስ እኛን ለእርሱ አስገዛን፣ ያም ማለት፣ እኛን ወደ መንግሥቱ አመጣን፣ ስለዚህም እኛ ጠላቶቹ ሳንሆን የተወደዱ ዜጋዎቹ ሆንን፡፡ ሁለተኛ፣ እኛን በመምራትና በመጠበቅ መንግሥቱን ያስተዳድራል፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ የእኛንና የእርሱን ጠላቶች ይዋጋል ደግሞም ድል ያደርጋል፡፡
ይህንን የዌስት ሚኒስቴር አጭር ካቴኪዝም አትኩሮት በመከተል፣ የኢየሱስን ንግሥና ዘመናዊ ተዛምዶ በሦስት ክፍሎች ከፍለን እንወያይበታለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ መንግሥቱን የሚመሠረት መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ፣ ህዝቡን የሚገዛ የመሆኑን እውነታ እንዳስሳለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ጠላቶቹን ድል የሚነሳበትን መንገድ እንመለከታለን፡፡
መንግሥቱን ይመሠርታል
ኢየሱስ መንግሥቱን እንዴት እንደሚመሠርት ከሦስት አመለካከቶች አንፃር እንቃኛለን፡ አንደኛ፣ የሥራውን ግብ፤ ሁለተኛ፣ የመንግሥቱን መገለጫ በዓለም ውስጥ፤ ሦስተኛ ደግሞ፣ መንግሥቱን ለመመሥረት ኢየሱስ የተጠቀመበትን ዘዴ እንቃኛለን፡፡ እስኪ በኢየሱስ ሥራ ግብ እንጀምር፡፡
ግብ
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር ዓለምን በጠቅላላ ወደ እርሱ መንግሥት ማምጣት እንደሚሻ ያስተምሩናል፣ ስለዚህም በምድር ያለው አገዛዙ በሰማይ ያለውን ነፀብራቅ ያሳየናል፡፡ ይህንንም ኢየሱስ በማቴዎስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 10 ላይ መንግሥቱ እንድትመጣና ፈቃዱም ልክ በሰማይ እንደሆነችው ሁሉ በምድርም እንድትሆን እንድንጸልይ ባስተማረበት ክፍል ውስጥ እናየዋለን፡፡ ደግሞም የአዲሱ ሰማይና ምድር ስዕላዊ መግለጫ በሆነው በራዕይ ምዕራፍ 21 እና 22 ውስጥም እናየዋለን፡፡ እንግዲያው ሰፋ ባለ መንገድ ስንገልጠው፣ የኢየሱስ መንግሥትን በምድር የመመሥረቱ ግብ ዓለምን በጠቅላላ ወደ እርሱ መንግሥት ማፍለስ፣ ለእርሱ አገዛዝ የሚመች ማድረግ እና ለእርሱም ፍፁም በታማኝነት በሚገዙ ሰዎች መሙላት ነው፡፡ ግን የእግዚአብሔር ዓላማ መንግሥቱን በምድር መመሥረት ከሆነ፣ ኢየሱስ የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው? ምንም እንኳን በፍጥረቱ ላይ የበላይ ሆነው ንጉሥ እግዚአብሔር ቢሆንም፣ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ይመራ ዘንድ ኢየሱስን ሾሞታል፣ ስለዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት በቀጥታ የኢየሱስ መንግሥት ተብሎ ሊጠራ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ፣ እግዚአብሔር ልክ እንደ ጥንታዊው የቅርብ ምሥራቅ ሱዜሪያዊ ሲሆን፣ ኢየሱስ ደግሞ የእርሱ ቫሳል ንጉሥ ነው፡፡ ኢየሱስም ሱዜሪያኑን ለማስደሰት በመሻቱ ምክንያት፣ የእግዚአብሔርን ግብ ለማሳካት ራሱን ይሰጣል፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ከቁጥር 24 እስከ 28 ኢየሱስ ለእግዚአብሔር አብ ራሱን እንዴት እንዳስገዛ ጳውሎስ የገለጠበትን መንገድ አድምጡ፡
በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።
ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።
የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤
ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው።
ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል። (1ቆሮ 15፥24-28)
ልክ እንደ እግዚአብሔር ቫሳል ንጉሥ፣ ኢየሱስ በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ ሥልጣን አለው፣ ደግሞም በፍጥረቱ ላይም እንዲሁ፡፡ ያንንም ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚቃወመውን ሁሉ ድል ለመንሳት፣ ሁሉን ለእግዚአብሔር ለማስገዛት እና እግዚአብሔር ለፍጥረተ ዓለሙ ያለውን ዓላማ ለማሳካት ይጠቀምበታል፡፡ ግን ይህ ግብ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? የኢየሱስ ግቡ ዓለምን በሙሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ማፍለስ ነው ለሚለው ሃሳብ ዘመናዊያኑ ክርስቲያኖች ምላሽ መስጠት የሚገባቸው እንዴት ነው? ቀላሉ መልስ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት የእኛም ሕይወት ግብ ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ግቦች ቢኖሩንም፣ ማለትም፣ የኑሮ ጉዳይ፣ ለቤተሰብ የሚያስፈልገውን ማቅረብ፣ በጤና መቆየት እና መማር እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከማስፋት አንፃር የተቃኙ ሊሆኑ ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህም ኢየሱስ በማቴዎስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 33 እንዳስተማረው ማለት ነው፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። (ማቴ 6፥33)
ቀጥሎ የምንመለከተውና ሁለተኛው ኢየሱስ መንግሥቱን የሚመሠርትበት መንገድ ገፅታ የመንግሥቱ መገለጫ በዓለም ውስጥ ነው፡፡
መገለጫ
አዲስ ኪዳን ስለ ኢየሱስ መንግሥት መገለጫ በሚናገርበት ጊዜ ሁሉ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ መንግሥቱን ከቤተክርስቲያን ጋር እንደሚያያይዘው በየዘመናቱ የኖሩ በርካታ የነገረ-መለኮት ምሁራን ተረድተዋል፡፡ በመንግሥቱና በቤተክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት በበርካታ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ውስጥ ተገልጧል፡፡ እነርሱም ኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 19 እስከ ምዕራፍ 2 ቁጥር 20 ድረስ፤ ራዕይ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 4 እስከ 6 ያሉትን ያካትታል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 16 ከቁጥር 16 እስከ 19 በኢየሱስና በጴጥሮስ መካከል የተደረገውን ውይይት እናድምጥ፡
ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።
እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።
የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። (ማቴ 16፥16-19)
ይህ ምንባብ መንግሥቱን ከቤተክርስቲያን ጋር የሚያያይዙ ቢያንስ ሦስት ነገሮችን ይናገራል፡፡ አንደኛ፣ ኢየሱስ “ቤተ ክርስቲያኔን እመሠርታለሁ” ብሏል፡፡ ከዚያም ለጴጥሮስ “የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ” ያለበትን ሐረግ አስከተለ፡፡ በዚህ ስፍራ ያለውን ግንኙነት ልብ በሉ፡ ሐዋርያና የቤተክርስቲያን ምሥረታ አካል የሆነው ጴጥሮስ በመንግሥተ ሰማያት ላይ ኃይል አለው፡፡
በመንግሥቱና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት አጉልቶ የሚያሳየን ሁለተኛ እውነታ ክርስቶስ የተሰኘውን ማዕረግ ጴጥሮስ ለኢየሱስ መስጠቱ ነው፡፡ “ክርስቶስ” የሚለው ቃል “የተቀባ” ማለት ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ነገሥታት ለዙፋናቸው ሲታጩ የሚቀቡበትን ዘይት ነው፡፡ ስለዚህ፣ ጴጥሮስ ኢየሱስን ክርስቶስ ብሎ ሲጠራ፣ ኢየሱስ በትንቢት የተነገረለት ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ መሆኑን ማመልከቱ ነው፡፡ እንደ ንጉሥም በሚኖረው ተግባር ኢየሱስ ቤተክርስቲያንን ይመሠርታል ማለት ነው፡፡
ሦስተኛውና በማቴዎስ ምዕራፍ 16 ከቁጥር 16 እስከ 19 የተመዘገበው በቤተክርስቲያንና በመንግሥቱ መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት የሚያመለክተው ነጥብ፣ ቤተክርስቲያን በገሃነም ደጆች እና በመንግሥተ ሰማይ መካከል በሚደረገው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ትሆን ዘንድ ኢየሱስ የሚሻ መሆኑን የሚያመለክተው ነው፡፡
እነዚህ ዝርዝሮች በጠቅላላ የሚያመለክቱት ኢየሱስም ሆነ ጴጥሮስ ያስተማሩት ቤተክርስቲያንና መንግሥቱ የሚሉት ፅንሰ ሃሳቦች የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ ምንም እንኳን የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ቢሆንም አዲስ ኪዳን እንደሚያመለክተን ግን ፍፁም አንድ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ከምሁራኑ አብዛኞቹ እንደሚስማሙት መንግሥቱ ከቤተክርስቲያን እጅግ ላቅ የሚል ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡
በቤተክርስቲያንና በእግዚአብሔር መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ ማራኪ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ሁሉን ፍፁም ለሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ወድዶ የማስገዛት ኅዳሴ ዐቢይ ራእይ ነው፡፡ ራእዩም መላውን ፍጥረተ ዓለም፣ በተለይም የምንኖርባትን ፕላኔትና የሰው ሕይወት የሚያካትት፣ ለንጉሡም በመገዛት ሰላም የሞላበትን፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ለእኛም ደስታ አስቀድሞ የታቀደውን አስደናቂ ሕይወት መፍጠር ነው፡፡ ይህንንም ዐቢይ ራእይ ለማስፈፀም እግዚአብሔር የመረጣት መሣሪያው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያንን፣ በተለይም ሃይማኖታዊ መዋቅሯን ከመንግሥቱ ጋር ማምታታት ተገቢ አይደለም፤ ከዚያ አንፃር አንድ ልናደርጋቸው አንችልም፣ አንድ የሚሆነው ፍፃሜው ነው፡፡ በተጨማሪም ደግሞ፣ ቤተክርስቲያን በተራራ ላይ እንዳለች ከተማ፣ በውስጥዋ በሚኖራት ሕይወትና በማኅበራዊ ተሳትፎዋ፣ ያም አንድ ቀን የእግዚአብሔር ፍጥረት በጠቅላላ ከባህር ጫፍ እስከ ባህር ጫፍ ያለው ሁሉ የሚገለጥበት ዓይነት ባሕርይ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የመንግሥቱ ዓይነታዎች ደግሞም የመንግሥቱ አምባሳደሮች ነን፡፡ [ዶ/ር ግሌን ስኮርጂ]
የእግዚአብሔር መንግሥትና ቤተክርስቲያን የሚሉት ፅንሰ-ሃሰቦች ሁለቱም ሁሉም ክርስቲያኖች በእያንዳንዱ ሕይወታቸው እንዴት መኖር እንደሚገባቸው የሚያመለክቱ የማይነጣጠሉ ሃሳቦች ናቸው፡፡ ግን በሁለቱ መካከል ልዩነትም እንዳለ መረዳቱ አስፈላጊ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ እንደማስበው እኔን ጨምሮ በርካታ ክርስቲያኖች ለዓመታት ያህል የምናስበው፣ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት ቁንጮ እንደሆነች አድርገን ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ስንመለከት ግን መንግሥተ እግዚአብሔር ከቤተክርስቲያን እጅግ የሚበልጥ መሆኑን ያሳዩናል፡፡ እናም እኔ የማስበውን መጽሐፍ ቅዱስም ያፀናልኛል፣ ማለትም ቤተክርስቲያን ጨርሶ የማትቀለበስ የመንግሥቱ አካል ናት፣ ግን ከመንግሥቱ ዐቢይ ሥራ አንዷ ክፍል ናት፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የእርሱ አገዛዝ፣ ዘወትር የእውነታው መሠረት ነው፡፡ እርሱ የፍጥረተ ዓለሙ፣ የሰማይና የምድሩ ደግሞም የእኛም ገዢ ነው፡፡ እርሱ የህዝቦች፣ የመንግሥታት፣ የነገሥታት እና የሁሉም ነገዶች ጌታ ነው፡፡ አሁን ብዙዎቹ አያውቁትም፣ እርሱ ግን ገዢ ነው፡፡ እንግዲያው የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የእግዚአብሔር ንግሥና፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ገዢ ሃሳብ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን፣ ራሳቸውን ለኢየሱስ ጌትነት ያስገዙ፣ ለእርሱ ንግሥናና ጌትነት እውቅና የሰጡ እና በዓለምም ላይ የእርሱ አምባሳደሮች ለመሆን ራሳቸውን ያስገዙ ሰዎች ናት ማለት ነው፡፡ [ዶ/ር ቢል ዑሪ]
አዲስ ኪዳን እንደሚያስተምረን የእግዚአብሔር ንግሥና የመጨረሻው እርከን የተጀመረው በክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ እያደገችና የሰውን ልጅ በርካታ ባህላዊ ገፅታዎች በእግዚአብሔር አገዛዝ ስር እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ማንም የማይጋፋት እና በፍጥረትና በሰው ዘር ባህላዊ ገፅታዎችም ላይ የምትገለጥ ትሆናለች፡፡
ታዲያ ቤተክርስቲያን በዚህ የታሪክ ውቅር ውስጥ ያላት ድርሻ ምንድን ነው? በመሠረቱ፣ ቤተክርስቲያን በዚህ ዘመን የእግዚአብሔር መንግሥት ማዕከል ናት፡፡ እኛም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋት ራሳችንን ልናስገዛ ይገባናል፡፡ ክርስቶስ ሲመለስም፣ የመንግሥቱን ሙሉ በረከት እንወርሳለን፡፡ እሰከዚያው ግን፣ እርሱ ያዘዘንን ሁሉ በማስተማር ክርስቶስ ዳግም ከመምጣቱ አስቀድሞ የክርስቶስን ወንጌል ልናስፋፋ፣ የእግዚአብሔርም ንግሥና በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ላይ እንዲገለጥ ልንተጋ ይገባናል፡፡
ቤተክርስቲያን በመንግሥቱ ውስጥ ያላትን ስፍራ ማወቋ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ወደ ፊት ከእርሱ ጋር ስንሆን፣ እርሱ ተመልሶ ሲመጣ፣ ቤተክርስቲያን ተብለን እንጠራለን ብዬ አላስብም፡፡ ያን ጊዜ መንግሥት እንሆናለን፡፡ ሙሽሪትም ለሙሽራው ትዘጋጃለች፣ ያም ቅዱሳት መጻሕፍት የሚገልጡት ሌላው ምስል ነው፡፡ ይህንን ለምን ትናገራለህ ብትሉኝ፣ አንዳንድ ጊዜ እኛ ስለራሳችን እንደ ቤተክርስቲያን ያለን አመለካከት የላቀ ስለሆነ ነው፡፡ እኛ ብቸኞቹ መልሶች እንደሆንን እናስባለን፣ ወይንስ የእግዚአብሔር ብቸኛው ዓላማ እኛ ብቻ ነን? አዎን እኛ በጣም በጣም አስፈላጊዎች ነን፡፡ እርሱ ለቤተክርስቲያን ሞቷል፡፡ ራሱንም መስዋዕት ለማድረግ ሞቷል፡፡ ልንዘነጋው የማይገባን ግን እርሱ ለመላው ዓለምም መሞቱን ነው፡፡ ስለዚህ ራሴን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባልነቴ ልመለከት የሚገባኝ፣ አንድ ግብ ያለኝ ያም የአካሏ ብልት መሆን መሆኑን ነው፡፡ የተጠራሁት ልክ እርሱ በምድር እዚህ እንዳለ ዓይነት እጁ ልሆን፣ እግሩ ልሆን፣ እና ክንዱ ልሆን ነው፡፡ ለእኔና ለሁላችን እንደ ቤተክርስቲያን የእኔ ንጉሥ የሰጠን ትዕዛዝ ያ ነው፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ግን እኛ ማለትም ቤተክርስቲያን የመንግሥቱ ቁንጮዎች እንደሆንን፣ እርሱ ሊያከናውን የመጣው ሥራም በእኛ እንዳበቃና ከእኛም የሚጠበቀው እርሱ እስኪመጣ ድረስ ተቀምጦ መጠበቅ ወይንም በመካከላችን በሚገለጠው ህልውናው መደሰት ብቻ እንደሆነ ማሰባችን ነው፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ አስተሳሰብ እንደሆነ አስባለሁ ስለዚህም ይህንን አመለካከት ልናርምና ብድግ ብለንም የቤተክርስቲያንን ዓላማ ከጌታችንና ከአዳኛችን ንጉሣዊ ዓላማ ጋር ወደሚያቀናጀው ተልዕኮ ልንገባ ይገባናል፡፡ [ዶ/ር ቢል ዑሪ]
ኢየሱስ መንግሥቱን የሚገነባበትን ግብና የመንግሥቱን መገለጫዎች ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ ኢየሱስ መንግሥቱን ለመመሥረት የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች እንመለከታለን፡፡
ዘዴዎች
ኢየሱስ መንግሥቱን የመሠረተው በሁለት ተቀዳሚ መንገዶች ነው፣ ሁለቱም በቀጥታ ቤተክርስቲያንን ያካትታሉ፡ ወደ ቤተክርስቲያን ሰዎችን ይጨምራል፣ መልክዓ ምድራዊ ድንበሯንም ያሰፋል፡፡ በአዲስ ኪዳን ጅማሬ፣ ኢየሱስ ህዝቦችን መሰብሰብ የጀመረው አስቀድሞ ከእስራኤል ነው፡፡ ነገር ግን በሐሥ ምእራፍ 1 ከቁጥር 6 እስከ 8 እንደተጻፈው ወደ ሰማይ ሲያርግ ቤተክርስቲያን መንግሥቱን በይሁዳ፣ በሰማርያ እና እስከ ምድርዳር ድረስ እንድታሰፋ አዝዟታል፡፡ ኢየሱስ መንግሥቱን የሚመሠርተው ቤተክርስቲያን የሰውን ዘር ሁሉ እንደትደርስና መላውን ዓለም እንድትሸፍን በማድረግ ነው፡፡ እኛ ግን፣ አሁን ያለነው ቤተክርስቲያን በዚህ ሥራ እንዴት ልንሳተፍና ምላሽ ልንሰጥ ይገባናል? በጥቅል አባባል፣ መልሱ በማቴዎስ ምዕራፍ 28 ከቁጥር 19 እስከ 20 ባሉት ቃላት ውስጥ ተቀምጧል፡፡
እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። (ማቴ 28፥19-20)
በዚህ ስፍራ እንደምንመለከተው፣ ኢየሱስ መንግሥቱን ለመመስረት የሚጠቀምባቸው ተቀዳሚ ዘዴዎች ወንጌል ማድረስ፣ ጥምቀትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ናቸው፡፡ እነዚህንም ዘዴዎች ብቻውን ከማከናወን ይልቅ፣ ቤተክርስቲያን በእርሱ ምትክ ሆና እንድትፈፅማቸው ኢየሱስ አዘዛት፡፡ ወንጌልን ማድረስ ሰዎችን ወደ እምነት ያመጣል፡፡ ጥምቀት ደግሞ ወደ ቤተክርስቲያን ኅብረት ይቀላቅላቸዋል፡፡ ማስተማር ደግሞ ቤተክርስቲያንን ከማጠንከርና ወደ ላቀ መስፋፋት ለማምጣት በሚያስችል መልኩ እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል፡፡
በየወንጌላቱ መጨረሻ የምናገኘው ሞጋች ሃሳብ ወደ ዓለም ሁሉ እንድንሄድና የምሥራቹን በመስበክ ሰዎችን ሁሉ ደቀመዛሙርት እንድናደርግ መታዘዛችን ነው፡፡ ደቀመዝሙርነት የሚለው ቋንቋ እንዲያው ተማሪ መሆን ከሚለው የዘለለ አንድምታ ያለው ነው፡፡ አማኝ ብቻ ከመሆንም የዘለለ ነው፡፡ በፋንታው ከእግዚአብሔር ጋር ብርቱ ቁርኝት ያለው መሆን ነው፡፡ አዎን፣ እግዚአብሔር ያስተምረናል፡፡ አዎን፣ እግዚአብሔር ይመራናል፣ ግን ደቀመዛሙርት ማድረግ የሚለው ጥሪ ከእግዚአብሔር ጋር በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ አብረው በመማርና በጥብቅ ግንኙነት የሚዘልቁ ሰዎችን ማፍራት ነው፡፡ እናም፣ ስለዚህ ጉዳዩ ብርቱ ተምሳሊት የሚሻ፣ እኔ እንደማስበውም ሰዎች የክርስትናን ሕይወት በአግባቡ መኖር የሚቻልባቸውን መንገዶች ከሚያሳዩዋቸው ሌሎች አማኞች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው፡፡ አዎን፣ በተጨማሪ ማስተማርም ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ከተከታዮቹና ከደቀመዛሙርቱ ምን እንደሚጠብቅ ሰዎች ሊያውቁ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ የተካተተ ሊሆን ይገባዋል፣ ምክንያቱም ሰዎች እንደ ክርስቲያን ያድጉና የዕድሜ ዘመን ሁሉ ተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ፣ በቀጥታ ሐረጉን መጠቀም ካስፈለገም፣ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸውና እርሱን በእምነት የሚከተሉት ሰዎች ይሆኑ ዘንድ የሚረዳ መዋቅር በዚያ አለና ነው፡፡ [ዶ/ር ሲሞን ቫይበርት]
ኢየሱስ መንግሥቱን ይመሰርታል የሚለውን ሃሳብ ዘመናዊ ተዛምዶውን ከተመለከትን፣ በዚያ መንግሥት ውስጥ የእርሱን ህዝብ ይገዛል የሚለውን ሃሳብ ደግሞ እንመልከት፡፡
የራሱን ህዝብ ይገዛል
ኢየሱስ የራሱን ህዝብ የሚገዛበትን መንገድ ሁለት ገፅታዎች እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የሚገዛቸው ለእነርሱ ጥቅም ሲባል ነው በሚለው እውነታ ላይ እናተኩራለን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ ከጠላቶቻቸው ይጠብቃቸዋል የሚለውን እንመለከታለን፡፡ እስኪ አስቀድመን ኢየሱስ እንዴት የራሱን ህዝብ እንደሚገዛ እንመልከት፡፡
መግዛት
የኢየሱስ አገዛዝ የእኛን ዘላለማዊ በጎ ከማስጠበቅ አንፃር ሲሆን፣ እነዚያም ከእርሱ ጋር ለዘላለም የምንካፈላቸው በረከቶች ናቸው፡፡ እንደ ዮሐንስ ምዕራፍ 6 ከቁጥር 35 እስከ 37፣ ምዕራፍ 7 ቁጥር 37፣ ምእራፍ 10 ቁጥር 28 እና 29፤ የሐሥ ምእራፍ 5 ቁጥር 31 የመሳሰሉት ክፍሎች እንደሚያሳዩን ወደ እርሱ የሚመጣ ሁሉ ምህረትንና ይቅርታን ይቀበላል፡፡ እርሱ እንደ እግዚአብሔር ወራሾች ይቀበለናል ፍፁም በመታዘዙም ያገኛቸውን የቃል ኪዳን በረከቶች ተካፋዮች እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ይህን መሳዩን የኢየሱስ አገዛዝ በሐሥ ምእራፍ 13 ከቁጥር 34 እስከ 39፤ ሮሜ ምዕራፍ 8 ቁጥር 17 እና 32 እና ዕብራውያን ምዕራፍ 2 ቁጥር 13 ላይ እንመለከታለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 16 እና በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ቁጥር 8 እና 9 ላይ ደግሞም በሌሎች በርካታ ስፍራዎች እንደምናነብበው እነዚህን በረከቶች ሁሉ የሚሰጠን በፀጋው ነው፡፡
የክርስቶስ ፍቅር የተሞላው አገዛዙ በዚህም ዓለም ጊዜያዊ መልካም ነገሮችን እንድናገኝ ያደርገናል፡፡ በሐሥ ምእራፍ 2 ቁጥር 33፤ በገላትያ ምዕራፍ 4 ቁጥር 6 እና በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 19 እንደምንመለከተው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በእርሱ ኅላዌ ባርኮናል፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 21፤ ገላትያ ምዕራፍ 6 ቁጥር 2 እና ቆላስይስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 16 ውስጥ እንደምንመለከተው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ግልፅ የሆነ አመራርን ይሰጠናል፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12 ቁጥር 28 እና ኤፌሶን ምዕራፍ 4 ቁጥር 11 እና 12 እንደምናነብበው ለቤተክርስቲያን አመራርን ይሰጣል፣ ሕዝቡንም ያገለግሉ ዘንድ ሥልጣንን ይሰጣል፡፡
ኢየሱስ ጨካኝና አምባገነን ንጉሥ አይደለም፤ እርሱ አፍቃሪና ለእኛ የሚያስፈልገንን ሁሉ የሚያዘጋጅ ስለእኛም ግድ የሚለው ንጉሥ ነው፡፡ የእርሱ አገዛዝ የችግር ምንጭ ከመሆን እጅግ የራቀ ከመሆኑ ባሻገር፣ ገደብ የለሽ በረከቶቹ ደግሞ ለአሁንና ለዘላለምም ትርፎቻችን ናቸው፡፡ እናም ለዚህ አገዛዝ ሊኖረን የሚገባው ምላሽ ግልፅ ነው፡፡ ንጉሣችን ለእኛ ያለውን በረከት ለመቀበል፣ ለአገዛዙ ራሳችንን ማስገዛት ይገባናል፡፡ ህግጋቱንም ልንታዘዝ ውድቀቶቻችንንና ችግሮቻችንንም ድል ለመንሳት በምህረቱ ልንታመን ይገባናል፡፡ እናም፣ ለአመራሩ አድናቆት ሊኖረን፣ ለእኛም ስላለው መልካምነት ልናመሰግነው ይገባናል፡፡
ኢየሱስ የራሱ የሆኑትን ይገዛል የሚለውን እውነታ ከተነጋገርንበት፣ እኛንም ይጠብቃል ወደሚለው ሃሳብ ደግሞ እንሸጋገር፡፡
ይጠብቀናል
ኢየሱስ አማኞችን የሚጠብቅባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፣ ለአሁኑ የትምህርታችን ግብ በሦስቱ ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ኃጢአትን እንድናደርግ ከሚገጥመን ፈተና ይጠብቀናል፡፡
ኢየሱስ እንደንጉሣችን፣ ከፈተና የሚጠብቀን በብዙ መንገዶች ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 13 ላይ እንደምናነብበው ወደ ፈተና እንዳንገባ አስቀድሞ ያስጠነቅቀናል፡፡ በዕብራውያን ምዕራፍ 2 ቁጥር 16 እንደምናነብበው ደግሞ ኃጢአትን እንድንቋቋም ያበረታናል፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 13 እና 2ኛጢሞቴዎስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 18 እንደምንመለከተው ከሚያጓጓንና ወደ ወጥመድ ከሚጥለን ነገር እየጠበቀ ከኃጢአት ዘወር የምንልበት መንገድ እንዳለ ያመለክተናል፡፡
ሁለተኛ፣ በፈተና ውስጥ ስንወድቅ ደግሞ፣ በኃጢአት ከመርከስ ይጠብቀናል፡፡ በኃጢአት እርኩሰት ከመጠመድ ኢየሱስ እኛን ከሚያድንበት መንገዶች አንዱ፣ ስንበድል በመቅጣት የኃጢአት ባሪያዎች እንዳንሆን ማድረጉ ነው፡፡ ይህንንም በኤርምያስ ምዕራፍ 46 ቁጥር 28፤ ዕብራውያን ምዕራፍ 12 ከቁር 5 እስከ 11፤ ራዕይ ምዕራፍ 3 ቁጥር 19 እና በሌሎችም በርካታ ምንባቦች ውስጥ እናያለን፡፡ በ1ኛ ዮሐንስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 9 ላይ እንደምንመለከተው ደግሞ ከእርኩሰት እኛን የሚጠብቅበት ሌላው መንገድ ደግሞ ንስሓ ስንገባ ይቅር በማለትና ከኃጢአታችን በማንፃት ነው፡፡
ሦስተኛ፣ በኃጢአት ከመከሰስ ኢየሱስ ይጠብቀናል፡፡ ሁሉም ክርስቲያኖች ለኃጢአት የተጋለጡ ናቸው፡፡ ራዕይ ምዕራፍ 12 ቁጥር 10 በምናነብበት ወቅት፣ ኃጢአትን ስናደርግ፣ ሰይጣን እኛን ለመክሰስ በእግዚአብሔርን እንደሚጠይቅ እንረዳለን፡፡ ኢየሱስ ግን ይሟገትልናል፣ ስለዚህም እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ ይቆጥረናል፡፡ ምንም እንኳን ቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ የኢየሱስን ምልጃ ከካህንነት አገልግሎት ጋር ቢያገናኙትም፣ ሮሜ ምዕራፍ 8 ቁጥር 34 እንደሚያመለክተን ግን ጥበቃው የንጉሥነት አገልግሎቱም ክፍል ነው፡፡ እንደ ታላቁ ቫሳል ንጉሥ፣ በህዝቡ ላይ ስሚከፈተው ክስ በታላቁ ሱዜሪያን ፊት በመማለድ ይሟገታል፡፡
ኢየሱስ በብርቱ የሚጠብቀን ስለሆነ፣ ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ጦርነት ብርቱ መተማመኛ አለን፡፡ ፈተናን ለመቋቋም፣ በኃጢአት ምክንያት ከሚመጣብንም መዘዝ ለማምለጥ፣ በምልጃው፣ በጠበቃነቱና በይቅርታው ከተደገፍን አንዳችም የሚጎዳን ነገር የለም፡፡ ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ጦርነት የሚመራን ታላቁና ብርቱ ተዋጊ የሆነው ንጉሥ ኢየሱስ ነው፡፡ ምንም እንኳን እኛ በአግባቡ ባንዋጋም እርሱ አይተወንምና አንሸነፍም፡፡ እርሱ ዘወትር ይከላከልልናል፣ ይጠብቀናልም፣ ይቅር ይለናል ያነፃናልም፣ ይከራከርልናል ከፍርድም ነፃ ያደርገናል፡፡ በስተመጨረሻውም፣ ወደ እርሱ የማይሻር ዘላለማዊ መንግሥት ያመጣናል፡፡
ኢየሱስ ህዝቡን የሚገዛበትን መንገዶች ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ጠላቶቹን ድል የሚነሳ የመሆኑን ሃሳብ ወደ መመልከቱ እንሻገራለን፡፡
ጠላቶቹን ድል ያደርጋል
የእግዚአብሔር ህግ ሲጣስ፣ ብዙ ጊዜ በርካታ ሰዎች ይጎዳሉ፡፡ ይህንንም በዙሪያችን በሚከናወኑ ወንጀሎች በየዕለቱ እናስተውላለን፡፡ የዘረፋ፣ የማጭበርበር፣ የድብደባ፣ የመከዳት ይባስም ብሎ የሞት ሰለባ የሆኑ በርካቶች አሉ፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ቋንቋም፣ እነዚህን ወንጀሎች የፈፀሙ ወንጀለኞች የሰለባዎቻቸውና የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነዋል፡፡ ለዚህም ወንጀል ትክክለኛው የመንግሥት ምላሽ ወንጀለኞቹን መያዝና መቅጣት ነው፡፡ ፍርዳቸውም ለፈፀሙት ወንጀል የሚመጥን እና ሰለባዎቻቸውንና የተቀረውንም የኅብረተሰብ ክፍል ከቀጣይ ወንጀል የሚታደግ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ስለዚህም ነገር በምሳሌ ምዕራፍ 20 ቁጥር 8 እና ምዕራፍ 25 ቁጥር 5 ላይ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡
ኢየሱስ ስለሚፈርደው ፍርድ አንድ ተመሳሳይ የሆነ እውነት አለ፡፡ የእርሱንና የእኛን ጠላቶች የሚቀጣው ከፍትህ አንፃር ሲሆን ያም ለወንጀላቸው ተገቢው ቅጣት ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሚቀጣቸው እኛን ለመባረክ፣ ከኃጢአትና ከአመፃቸው እኛን ለመጠበቅ፣ ለእኛም ያዘጋጃትን ዓለም ከማንፃትና ከመከላከል አንፃር ቸርነቱን ያሳየን ዘንድ ነው፡፡
በኢየሱስ ዓለምን የእግዚአብሔር ምድራዊ መንግሥት ማዕከል በማድረጉ ተልዕኮ ውስጥ በበደለኞች ላይ የመፍረዱና እነርሱን የማጥፋቱ ሥራ ወሳኝ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ዓለም እግዚአብሔርን ደስ የምታሰኝ፣ ለእርሱም አገዛዝ የምትመች ትሆን ዘንድ፣ እኛም የእርሱን ዘላለማዊ በረከት እንደሰትበት ዘንድ፣ የኃጢአት ርኩሰት ከውስጧ ጨርሶ ሊወገድ ይገባል፡፡
በዚህ ትምህርት ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፣ ኢየሱስ በእርሱና በእኛ ጠላቶች ላይ መፍረድ የጀመረው በምድራዊ አገልግሎቱ ዘመን ነው፡፡ እነዚህም ጠላቶች ኃጢአትን፣ ሞትንና አጋንንቶችን ያካትታሉ፡፡ በእነዚህ ጠላቶች ላይ ኢየሱስ ድልን ተቀዳጅቷል፣ ሆኖም ቅጣቱ ገና አልተጠናቀቀም፡፡ ስለዚህም፣ በዚህም ዘመን፣ ኢየሱስ በእነርሱ ላይ መፍረዱን ቀጥሏል፣ ፍርዱም የሚጠናቀቀው ተመልሶ ሲመጣ ነው፡፡ ይህም እውነታ በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4፤ በይሁዳ ቁጥር 6 እና በራእይ ምዕራፍ 20 ቁጥር 10 እና 14 ላይ ተቀምጧል፡፡
ኢየሱስና ቤተክርስቲያን ግን ሌሎችም ጠላቶች አሏቸው፡፡ ራሱን ለክርስቶስ ገና ያላስገዛ ኃጢአተኛ የሰይጣን መንግሥት ዜጋ ነው እናም የእግዚአብሔር ጠላት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን በማቴዎስ ምዕራፍ 13 ከቁጥር 37 እስከ 43፣ ሉቃስ ምዕራፍ 19 ቁጥር 27 እና ኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁር 1 እስከ 3 ውስጥ በግልፅ አስቀምጠውታል፡፡
በአሁኑ ዘመን፣ ኢየሱስ ከፊል ፍርዱን ከእነዚህ ጠላቶች በአንዳንዶቹ ላይ በምድር ሕይወታቸውም እየፈፀመው ነው፡፡ ለምሳሌ ሄሮድስ ሰዎች እንደ አምላክ እንዲቆጥረው በፈቀደ ወቅት በሞት እንዲቀሰፍ እንዳደረገው ማለት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን፣ ኢየሱስ በጠላቶቹ ላይ ከመፍረድ በመታገሥ፣ ፍርዱን እስከ ዳግም ምፅዓቱ ድረስ ጠብቆታል፡፡
ወደፊት የሚገለጠው ፍርድ በአዲስ ኪዳን በተደጋጋሚ ጊዜ የወንጌሉ አካል ሆኖ መገለጡ አስገራሚ ነው፡፡ ይህም ነገር የመልካሙ የምሥራች ተፃራሪ ወገን እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ እውነታው ግን ጉዳዩ የምሥራቹ አካል መሆኑ ነው፡፡ የምሥራቹ አካል የሚሆንበትም ምክንያት፣ መከራ ለዘላለም የማይቀጥል መሆኑና በፈንታው ግን ፈውስ እንደሚሆን፣ ኢፍትሃዊነትም እንደማይቀጥል፣ በፈንታው ግን ክፉ ወደ በጎ እንደሚለወጥ እግዚአብሔር የሰጠው ዋስትና ማረጋገጫ በመሆኑ ነው፡፡ በየሰዉ ልብ ውስጥ ኢ-ፍትሃዊነት እንዳይቀጥል መጓጓቱ ወይንም እንደማያስፈልግ ታውቆ ጨርሶ መወገዱን የመፈለግ ጥልቅ መሻት አለ፡፡ ይህም የሆነው ወደዚያው እየገሰገስን ስለሆነ ነው፡፡ አሁን በመከራ ውስጥ እያለፉ ላሉት እግዚአብሔር ሊታገሰው እንደማይችል የሰጠው ብርቱ ተስፋ አካል ነው፡፡ በእርሱ የሚታመኑት ጠበቃ እንዳላቸው በማወቅ፣ በበቀል ተሞልተው ፍትህን በራሳቸው ጥረት ከማምጣት በመቆጠብ ራሳቸውን ለታመነውና ሁሉን ለሚያስተካክለው ዳኛ ሊሰጡ ይገባቸዋል፡፡ [ዶ/ር ግሌን ስኮርጂ]
ሐዋርያት የኢየሱስ ንጉሣዊ አገዛዝ የወደፊቱን ፍርድ፣ ማለትም ሁሉም ሰው ለህጉና ለአገዛዙ መልስ የሚሰጥበት መሆኑን በግልፅ ተረድተውታል፡፡ ይህም የመጨረሻው ዘመን ፍርድ በሐሥ ምዕራፍ 17 ቁጥር 31፤ በሮሜ ምእራፍ 14 ከቁጥር 10 እስ 12 እና በእብራውያን ምእራፍ 10 ከቁጥር 26 እስከ 31 ውስጥ ተገልጧል፡፡ የሚመጣው ፍርድ የክርስቶስ ንጉሣዊ ሥራ ማዕከላዊ ክፍል ነው ምክንያቱም በኃጢአተኞች ላይ ፍትሁን ለመግለፅ፣ ለሚያምኑት ምህረቱን ለማሳየት፣ መንግሥቱንም ሲያፀዳ ታማኝነቱን ለአብ የሚያሳይበት ነውና፡፡
የመጨረሻው ፍርድ አስተምህሮ ክርስቶስን እንደ ጌታቸው ገና ላልተቀበሉት አሸባሪ ቢመስልም፣ ያ መሆኑ ግን ክፉ ነገር አይደለም፡፡ ማስጠንቀቂያዎቹ ታማኝ ላልሆኑት ከኃጢአታቸው ንስሓ ይገቡ ዘንድ፣ ይቅርታን፣ ምህረትንና ጸጋን ከንጉሣችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የመቀበል ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ አዎን፣ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል፡፡ ንስሓ ለሚገቡ ግን በረከት ይጠብቃቸዋል፡፡ በመሠረቱ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው የወንጌል መልእክት ስለ ወደፊቱ ፍርድ የሚናገረው ለዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ይህንን በማቴዎስ ምዕራፍ 21 ከቁጥር 32 እስከ 44 እና የሐሥ ምዕራፍ 17 ቁጥር 30 እና 31 ላይ እንመለከተዋለን፡፡
እንደማስበው ንስሓ በማይገቡት ላይ ማለትም በክርስቶስ ባልሆኑት፣ ከነኃጢአታቸው በሞቱት ላይ ስለሚፈፀመው ዘላለማዊ ቅጣት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የወንጌል መልዕክት አካል ሆኖ በግልፅ መግለጫ የመቅረቡ ጉዳይ በርካታ ክርስቲያኖችን ግር የሚያሰኝ ነው፡፡ ታውቃላችሁ እኔ ግን ነገሩን ከዚህም በመረረ መንገድ ነው የምመለከተው፡፡ አያችሁ ነገሩ እንዲህ ነው፡- በሐኪሜ ፊት ለፊት ሆኜ እርሱም ዐይን ዐይኔን እያየ “ዕጢ ተገኝቶብሃል” ብሎ ሲነግረኝ የሚሰማኝ ስሜት መልካም ዜና ሊባል የሚችል ይመስላችኋል? ግን ታውቃላችሁ፣ ነገሩ እኮ እውነትም መልካም ዜና ነው፡፡ መልካም ዜና የሚሆነው ሐኪሙ ችግሩን ማግኘቱ ነው፡፡ ሲቀጥል ደግሞ ስለ ሁኔታው ለእኔ መንገሩ ነው፡፡ አስኪ አስቡ ዕጢ እንዳለብኝ መንገር መልካም መስሎ ባይታየውስ? ያን ቢያደርግ ኖሮ፣ አይወደኝም ማለት ነው፣ እንዲያውም ጭካኔ የሞላበት ነው የሚሆነው፡፡ በጥቅሉ መልካም አይደለም፡፡ ዕጢውን ካገኘ በኋላ “አየህ ዕጢ አለብህ፣ ለሕይወትህም አስጊ ነው፣ እውነታው ይህ ነው፣ እኛ ግን አንድ ነገር እናደርጋለን፡፡ ” እንግዲያው፣ መልካም ዜና የሚሆነው ይህ ነው፡፡ አያችሁ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለሚመጣው ፍርድ እና ኃጢአትም ስለሚያስከትለው ፍዳ በግልፅ ይናገራሉ፡፡ ያንንም ማወቃችን መልካም ዜና ነው፡፡ የእግዚአብሔርንም ክብር የሚገልጥ መሆኑ ሌላው የምሥራች ነው፡፡ ይህ የመጪው ፍርድ ጉዳይ ጨርሶውኑ እንዳይከናወን እግዚአብሔር የማይከለክለው ጉዳይ ነው፡፡ የእግዚአብሔር የጽድቁ፣ የፍትሃዊነቱና የቅድስናው ሙላት ነው፡፡ እንግዲያው፣ ሊመጣ ካለው ጥፋትና ፍርድ ለማምለጥ ወደ ክርስቶስ እንድንሸሽ ስለሚያደርገን መልካም ዜና ነው ማለት ነው፡፡ ግን ወደ አዲስ ኪዳኑ መደምደሚያ የራእይ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ስትመጡ መጽሐፍ ቅዱስ፡ የእግዚአብሔር ክብሩ በተዋጁት መዳንና ንስሓ ለመግባት አሻፈረኝ ባሉት ላይ በሚያፈስሰው ፍርድም ነው በማለት በፍፁም ግልፅነት ይነግረናል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር የሚከብረው በክርስቶስ ውስጥ ባሉትና ኃጢአታቸው በራሳቸው በጎ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ ይቅር በተባለላቸው ላይና እስከ ፍፃሜው ድረስ ልባቸውን እልከኛ በማድረግ በተቃወሙት ላይ ጽድቁን ሲገልጥ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ እውነታው ይህ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ወንጌል የምስራች ነው ምክንያቱም ከሁሉ አስቀድሞ ከሚመጣው ጥፋት እናመልጥ ዘንድ የሚነግረን በመሆኑና በክርስቶስ እንድንታመንና በእርሱም በመሆን የዘላለምን ሕይወት እንድንወርስ ማስቻሉ ነው፡፡ ስለ ተቀረውም ታሪክ እንድናውቅ በማድረጉም ወንጌል የምሥራች ነው፣ ሌላውም ታሪክ የወንጌሉ አካል ነውና፡፡ [ዶ/ር አር. አልበርት ሞህለር]
መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጨረሻው ፍርድ የሚስተምረው ትምህርት አማኞችን የሚበረታታ ነው፡፡ አሁን የምናልፍበት መከራ በከንቱ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል፡፡ ያዕቆብ ምዕራፍ 5 ቁጥር 7 እና 8፤ 2ኛ ተሰሎንቄ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 4 እስከ 10 ያለውን ስናነብብ ሁሉ ለመልካም ይለወጥልናል፡፡ የክርስቶስ ፍርድ ለእኛ የምስጋና ምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱም የትኛውንም ዓይነት የክፋት ሥራ ተፅዕኖና እርኩሰትን ሁሉ የሚያስወግድ እና የምንወርሳትንና ለዘላለም የምንኖርባትን ፍፁም ውብና ድንቅ ዓለም የሚስገኝልን ስለሆነ ነው፡፡ ነገሩ መልአኩ በራእይ ምዕራፍ 14 ቁጥር 7 ላይ እንዳወጀው ነው፡፡
በታላቅ ድምፅም። የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ። (ራእይ 14፥7)
ማጠቃለያ
በዚህ ትምህርታችን፣ የኢየሱስን የንግሥና አገልግሎት ተመልክተናል፡፡ የአገልግሎቱንም ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ ከመመዘኛዎቹ፣ ከተግባራቱና ወደፊትም ስለሚጠበቅበት ነገር ተመልክተናል፡፡ እነዚህም የንጉሥነት አገልግሎት ገፅታዎች በኢየሱስ ያገኙትን ፍፃሜ ተመልክተናል፡፡ የኢሱስንም የንግሥና አገልግሎት ዘመናዊ ተዛምዶ መንግሥቱን ከመገንባት፣ የራሱን ሕዝብ ከመግዛትና ጠላቶቹን ድል ከማድረግ አንፃር ተመልክተናል፡፡
በዚህ ተከታታይ ትምህርት፣ የትምህርተ ክርስቶስን የዳበረ እውቀት ዳስሰናል፡፡ ኢየሱስንም በታሪክ ዘመናት ሁሉ ቤዛ መሆኑን፤ ህይወቱንና አገልግሎቱን፤ እንደ ነቢይ፣ እንደ ካህንና እንደ ንጉሥ የሰጣቸውንም አገልግሎቶች ተመልክተናል፡፡ ስለ ኢሱስ ያወቅነው ዕውቀት ግን አዕምሮአዊ ብቻ ሊሆን አይገባውም፡፡ እርሱ ማን መሆኑን ስናውቅ፣ ስለራሱም የገለጠውን በውል ስንረዳ፣ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፣ በምንሠራው ሥራ ሁሉ፣ በቤታችን፣ በሥራዎቻችን እና በቤተክርስቲያናችንም እንወደዋለን እንከተለዋለንም፡፡
Continue reading the full transcript
