<link rel="stylesheet" href="https://cdn.plyr.io/3.7.8/plyr.css" />
ወደ ካታሎግ ተመለስPENፔንታቴውክ
ፔንታቴውክ ·Videoከእንግሊዝኛ ተተርጉሟል

PEN-04 የአመጽ ዓለም

ሙሉውን ጽሑፍ ያንብቡ

(የመጀመሪያ ታሪክ ትምህርት 3) የዘፍጥረት 4:1-6:8ን ይመረምራል፣ የሰው ልጆች ዓለምን በጥቃት መሙላት እንዴት እንደጀመሩ እና እግዚአብሔር ለእነዚያ ችግሮች እንዴት ምላሽ እንደሰጠ ይገልጻል።


From the transcript

ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡

ትንንሽ ልጆች ያለ ፍርሃት አደገኛ ወደሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሴሄዱ አስተውላችሁ ታውቃላችሁ? ወደ አውራ ጎዳና መሃል ምንም ግድ ሳይሰጣቸው ይሮጣሉ፡፡ በጣም ስለታም ቢላዎ ያለ ጥንቃቄ አፈፍ ያደርጋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወደ እንግዳ ሰዎች እመር ብለው በመሄድ እጃቸውን አፈፍ ያደርጉና አብረዋቸው መሄድ ይጀምራሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች ሊፈጥሩባቸው የሚችሉትን ክፋት በፍፁም ባለማወቅ ማለት ነው፡፡

አዋቂዎች ግን፣ ዓለም በመጠን የለሽ ችግሮች የተሞላች መሆኗን ያውቃሉ፡፡ የተፈጥሮ አደጋዎች ሕይወትንና ንብረትን ያወድማሉ፤ በሽታዎች ስቃይን ያስከትላሉ፤ ማሽኖች ጉዳት ያደርሱብናል፡፡ ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ በሌሎች ሰዎች የሚፈጸምብን መሆኑን እናውቃለን፡፡ ወንዶችና ሴቶች በአምሳያዎቻቸው የሰው ዘሮች ላይ ጥቃትን፣ ግድያንና ጦርነትን ይፈፅማሉ፡፡ ለሰው ዘር ታሪክ ንቁ ከሆንን፣ ወይም አሁን እየተከናወኑ ስላሉት ነገሮች ጆሮ ከሰጠን፣ የሰው ዘር ዓለምን በክፋት ያጥለቀለቃት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡

ይህንን ትምህርት ክፉዋ ዓለም የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ በዚህም ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ድረስ የሰው ዘር በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የመጡትን ችግሮች እና ክፋት ሙሴ የገለጠበትን ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ በእነዚህ ምዕራፎች፣ የሰው ዘር እንዴት ዓለምን በክፋት እንደሞላት፣ እግዚአብሔር ደግሞ ለችግሮቹ እንዴት ምላሽ እንደሰጠ የሙሴን መግለጫ እንመለከታለን፡፡ ይህንን የዘፍጥረትን መጽሐፍ ክፍል በሦስት ገፅታዎች እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ስነ-ጽሑፋዊ አወቃቀሩን እንመለከታለን፤ ሁለተኛ፣ በእነዚህ ምዕራፎች ቀደምት ትርጉም ላይ እናተኩራለን፤ ሦስተኛ፣ እነዚህን ምንባቦች በሕይወታችን እንዴት ማዛመድ እንደሚገባን አዲስ ኪዳን የሚያስተምረንን እንመረምራለን፡፡ አስቀድመን የዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ስነ-ጽሑፋዊ አወቃቀር እንመልከት፡፡

እነዚህ የዘፍጥረት ምዕራፎች በርካታ የተለያዩ ርዕሶችን ይዳስሳሉ፣ ትረካዎችንና የትውልድ ሐረጎችንም ያካትታሉ፡፡ እነዚህ ውስብስቦች ምዕራፎቹ አንዳቸው ከሌላቸው ጋር በአግባቡ ግጥምጥም ባለማለታቸው በግርምታ ውስጥ ይጥሉናል፡፡ ሆኖም ይህንን የዘፍጥረት አንጓ በቅርበት ስንመረምረው፣ በአንድ ወጥ ዓላማ ስር የተቀነባበረ ስነ-ጽሑፋዊ ሥራ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ያለው ክፍል በሁለት ዋና ክፍሎች ተከፍሎ እናገኘዋለን፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ከምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 5 ቁጥር 32 ያለውን ሲይዝ፣ “ቀደምት ክፋትና ተስፋ” የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ ሁለተኛው ክፍል ከምዕራፍ 6 ቁጥር 1 እስከ 8 ያለውን ሲያካትት፣ “የኋለኛው ክፋትና ተስፋ” የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡

በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እና 5 የሚገኘው የቀደምት ክፋትና የአርነት ተስፋ ትዕይንት በአራት ክፍሎች ይከፈላል፣ እነዚህም ክፍሎች በሁለት ጥንድ ተጓዳኝ ትረካዎችና የዘር ሐረጎች ይዋቀራሉ፡፡ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 16 ያለው ክፍል በምዕራፍ 4 ከቁጥር 25 እስከ 26 ካለው ጋር የሚጎዳኝ ትረካ ነው፡፡ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 17 እስከ 24 ያለው የዘር ሐረግ ደግሞ በምዕራፍ 5 ከቁጥር 1 እስከ 32 ከሚገኘው የዘር ሐረግ ጋር ይጎዳኛል፡፡ እነዚህን ምንባቦች በተጓዳኞቹ ትረካዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በመመርመር እናጠናቸዋለን፡፡ ደግሞም በሁለቱ የዘር ሐረግ ጎድኝቶች መካከል ባለው ጉድኝት ላይም እናተኩራለን፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሙሴ ስለ ክፉው ቃየን ታሪክ የሚጽፈው በምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 16 ነው፡፡ ይህ ምንባብ በጣም የታወቀና ቃየን በቅንዓት ቱግ ብሎ ወንድሙን አቤልን የገደለበት ወቅት የተመዘገበበት ነው፡፡ ይህንን ምንባብ በቅርበት ስንመረምረው፣ በአምስት ትዕይንታዊ ክፍሎች እንደሚከፈል ግልፅ ይሆንልናል፡፡ በቁጥር 1 እና 2ሀ ቃየንና አቤል በአንድነትና በመስማማት ሲኖሩ በሚያሳየው ምንባብ ታሪኩ ይጀምራል፡፡ ሆኖም፣ ወደ ትረካው መደምደሚያ ወደ ቁጥር 16 ስንደርስ፣ ለየት ያለ ሁኔታ እናገኛለን፡፡ ቃየን ከእግዚአብሔር ልዩ መገኘት፣ ከቤተሰቡና ከመልካሚቱ ምድር ተወግዶ ብቻውን እናገኘዋለን፡፡

የታሪኩ ሁለተኛ እርከን ደግሞ፣ ከቁጥር 2ለ እስከ 7 ውስጥ ይገኛል፣ ያም እያንዳንዳቸው ለእግዚአብሔር ባቀረቡት መስዋዕት ምክንያት በተፈጠረ ልዩነት ቃየን አቤልን የገደለበትን ክስተት ይዳስሳል፡፡ በቀላሉ ስናስቀምጠው፣ እግዚአብሔር በአቤል መስዋዕት ደስ ተሰኘ፣ የቃየንን መስዋእት ግን አልተቀበለም፡፡ ኃጢአት ልትሰለጥንበት እንደምታደባ እግዚአብሔር ቃየንን ቢያስጠነቅቀውም፣ ቃየን ግን ትኩረት አልሰጠውም፡፡

የዚህ ትረካ ሦስተኛ ክፍል፣ በቁጥር 8 የሚገኝ ሲሆን፣ የታሪኩ አቅጣጫ ይቀየራል፡፡ በዚህ ክፍል፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን ይገድለዋል፡፡ ቃየንና አቤል ከመስዋዕቱ ስፍራ ወደ ሜዳ ይወጣሉ፣ በዚያም፣ ልክ እግዚአብሔር እንዳስጠነቀቀው፣ ኃጢአት በቃየን ላይ ሰለጠነችበት፣ በሰው ልጅ ታሪክም የመጀመሪያውን ግድያ እንዲፈፅም አደረገው፡፡

አራተኛው የዚህ ክፍል ትረካ የሚገኘው ከቁጥር 9 እስከ 15 ነው፣ ያም እግዚአብሔር በቃየን ላይ ያመጣውን እርግማንና የገባለትን የጥበቃ ተስፋ ይገልጣል፡፡ ቃየን ከዔድን ምድር ተወግዶ ተንከራታች እንዲሆን እግዚአብሔር ረገመው፣ ግን ሌሎች ሰዎች እንዳያጠቁት ጥበቃ አደረገለት፡፡

እናም ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እና 5 በቃየን አሳዛኝ የኃጢአት ታሪክ ሲጀምር እንመለከታለን፡፡ በኃጢአት ረከሰ ጻድቅ ወንድሙን አቤልንም ገደለ፣ በውጤቱም፣ ከእግዚአብሔር የበረከት ምድር መባረር ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡

እንግዲህ የዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እና 5 የመክፈቻ ትረካ ውቅር ከተመለከትን፣ በእነዚህ ምዕራፎች ወደሚገኘው ወደ ሁለተኛው ትረካ እንሸጋገር፡፡ ያም በምዕራፍ 4 ቁጥር 25 እና 26 የሚገኘው ተዛማጅ ዘገባ ነው፡፡ ይህ ምንባብ ትኩረታችንን ከኃጢአተኛው ቃየን፣ ወደ ጻድቁ የአዳም ልጅ ወደ ሴት ዘወር ያደርገዋል፡፡

የጻድቁ ሴት ሪፖርት በሦስት አጫጭር እርከኖች ይከፈላል፡፡ በመጀመሪያ፣ በምዕራፍ 4 ቁጥር 25 ውስጥ፣ ሔዋን ሴትን ትወልዳለች፡፡ የዚህ ዘገባ ሁለተኛው እርከን በምዕራፍ 4 ቁጥር 26ሀ የሚገኘውና ሴት ወንድ ልጅ እንደተወለደለት ስሙም ሄኖስ እንደተባለ ሙሴ የጻፈበት ነው፡፡ ስለዚህ ሁኔታ ተጨማሪ ዘገባ አልቀረበበትም፣ ሆኖም ሙሴ በምዕራፍ 4 ቁጥር 26ለ ውስጥ ስለ ሄኖስ አወላለድ ዘገባ ያቀርባል፣ ያም የዚህ ቤተሰብ መንፈሳዊ ባህርይ የተጠቀሰበት ነው፡፡ በምዕራፍ 4 ቁጥር 26ለ ውስጥ ሙሴ እንዲህ ጽፏል፡

በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ፡፡ (ዘፍጥረት 4፡26ለ)

በቀላሉ ስናስቀምጠው፣ ሴትና ሄኖስ ወደ እግዚአብሔር በጸሎት የተጣሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከኃጢአተኛው ቃየን በተቃራኒ፣ እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ ጽድቃቸውም በእውነተኛ አምልኮና ጸሎት ተገልጧል፡፡

የዘር ሐረጎች

በእነዚህ ተጓዳኝ ትረካዎች መካከል ያለውን መሠረታዊ ንፅፅር በልቡናችን ይዘን፣ በምዕራፍ 4 እና 5 ወደሚገኘው የዘር ሐረጎች ጉድኝት እንሸጋገር፡፡ በዘፍጥረት 4 እና 5 የሚገኙት የዘር ሐረጎች ከተራ የትውልድ ሰንሰለትነት የዘለለ ፋይዳ አላቸው የሚለው ነገር ለብዙዎች ግልፅ አይደለም፣ ስለዚህ በርካታ ተርጓሚዎች ወሳኝነታቸውን ቸል ይሉታል፡፡ ሆኖም፣ የዘር ሐረጎቹን በቅርበት የሚመለከት ሰው ሙሴ ይህንን የፍጥረተ ዓለም ዘገባ ክፍል የጻፈበትን ዓላማ የሚደግፉ ወሳኝ መረጃዎችን ያገኝባቸዋል፡፡

በአንድ በኩል፣ የመጀመሪያው የዘር ሐረግ በምዕራፍ 4 ከቁጥር 17 እስከ 24 የኃጢአተኛው የቃየን ትውልድ የያዘው ነው፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች፣ በርካታ የቃየንን ዝርያዎች፣ ወደዚህ ቤተሰብ ኃጢአት እንዴት እንደገባ እና ነገዱንም ወደ ትዕቢት፣ ወደ ጉራና ወደ ፈታኝነት እንዳስገባው ሙሴ ይዘረዝራል፡፡ ሁለተኛው ዝርያ ደግሞ በዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ከቁጥር 1 እስከ 32 የሴትን ጻድቅ ትውልድ ይይዛል፡፡ በዚህ ምንባብ፣ በሴት ቤተሰብ ውስጥ ወሳኝ ስፍራ ያላቸውን ስሞች ሙሴ ይዘረዝራል፡፡ ይህ ትውልድ ግን ከቃየን ተቃራኒ በሆነ መንገድ፣ ጻድቅና ታማኝ ሆኖ ይዘልቃል፡፡

ይህንን በዓላማ የተደረገ ዘገባ ልንመለከት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ በሁለቱም ዝርዝሮች ውስጥ ሙሴ የጠቀሳቸውን ሁለት ስሞች ልብ ማለት ነው፡፡ የቃየንም የሴትም የትውልድ ሐረጎች የጠቀሷቸው ስሞች ሔኖክና ላሜህ ናቸው፡፡ ደግሞም ሙሴ በግልፅ እነዚህን ሰዎች እርስ በርስ አነፃፅሯቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ሔኖክ በሚባል ስም ስለ ተጠሩት ሰዎች ሙሴ ምን እንዳለ ልብ በሉ፡፡ በአንድ በኩል፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 17 ውስጥ የቃየን ትውልድ ስለሆነው ሔኖክ እንዲህ እናነብባለን፡

ቃየንም ከተማ ሠራ ፣ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሔኖስ (ሔኖክ) አላት፡፡ (ዘፍጥረት 4 ቁጥር 17)

ቃየንና ልጁ ሔኖስ (ሔኖክ) የከተማዋን ስም በትልቅ ትምክህት ሔኖክ በማለት ራሳቸውን ከፍ አደረጉ፡፡ የዚህን ዘገባ ወሳኝነት የምንመለከተው በምዕራፍ 5 ቁጥር 24 ውስጥ ሙሴ ስለ ሴት ልጅ ስለ ሔኖክ የጻፈውን ልብ ስንል ነው፡፡ በምዕራፍ 5 ቁጥር 24 ውስጥ ሙሴ ስለ ሴት ልጅ ስለ ሔኖክ እንዲህ ፅፏል፡

ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ፣ አልተገኘም፣ እግዚአብሔር ወስዶታልና፡፡ (ዘፍጥረት 5፡24)

በዚህ ስፍራ በሁለቱ ሰዎች በኃጢአተኛው ሄኖክና በጻድቁ ሄኖክ መካከል ለመገመት በሚያዳግት መልክ አስደንጋጭ ተቃርኖ እንመለከታለን፡፡

ሄኖክ በሚባል ስም በሚጠሩት ሁለት ሰዎች መካከል ከሚገኘው ተቃርኖ በተጨማሪ፣ በቃየን ትውልድ ውስጥ የሚገኘውን ላሜህና በሴት ትውልድ ውስጥ የሚገኘውን ላሜህ ሙሴ ይጠቅሳል፡፡ አንድ ጊዜ በድጋሚ፣ በእነዚህም ሰዎች መካከል ጠንካራ ተቃርኖ ይታያል፡፡ በአንድ ወገን፣ የቃየኑ ላሜህ፣ አሰቃቂ ገፅታ ሆኖ ይታያል፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 23 እስከ 24 ላሜህ፣ ነፍሰ ገዳይ እና በግድያ በማረከው ብዝበዛ የሚመካ ሰው እንደሆነ ተዘግቧል፡፡

በተቃራኒው ግን፣ የሴቱን ላሜህ ሙሴ ሲገልጠው፣ በምዕራፍ 5 ቁጥር 29 ውስጥ በልጁ ልደት ላይ የተናገራቸውን ቃላት እንዲህ ያሰፍራቸዋል፡

ስሙንም፣ “እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል ሲል” ኖኅ ብሎ ጠራው፡፡ (ዘፍጥረት 5፡29)

በመጽሐፍ ቅዱሱ የታሪክ ዘመናት ልማድ እንደነበረው ሁሉ፣ የሴት ልጅ ላሜህ የልጁን ስም ለእግዚአብሔር እንደሚቀርብ ፀሎት አወጣ፣ ያም በአዳምና በሔዋን ዘመን እግዚአብሔር ምድርን ሲረግም በምድር ላይ ከተከሰተው አሰቃቂ ሕይወት ኖኅ ድነትን ያመጣልናል የሚል ተስፋን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

እንግዲህ ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እና 5 እንዴት አድርገው የክፋትንና የነፃነትን ተስፋ በንፅፅር እንዳሳዩን ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 8 ወደሚገኘው ወደ ሁለተኛው የክፋትና የተስፋ ትዕይንት እንሸጋገር፡፡

የኋለኛው ክፋትና ተስፋ

እነዚህን ጥቅሶች በቅርበት ከተመለከትናቸው፣ ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 8 በሦስት እርከኖች እንደተከፈለ በግልፅ እናያለን፡፡ አንደኛው፣ ከቁጥር 1 እስከ 3 “የእግዚአብሔር ልጆች” በተባሉ ገፀ-ባህርያት ላይ ያተኩራል፤ ሁለተኛው፣ ከቁጥር 4 እስከ 7 “ኔፍሊም” በመባል በሚታወቁ ሌሎቸ ገፀ-ባህርያት ላይ ያተኩራል፤ እነዚህን ሁለት እርከኖች ተከትሎም፣ ሙሴ ኖህን፣ ተስፋና ነፃነት የተገኘበትን በቁጥር 8 እንደገና ይጠቅሳል፡፡

የእግዚአብሔር ልጆች

የእነዚህ ጥቅሶች ሁለት ዋና እርከኖች በምድር ላይ የተከናወኑ ፈታኝ ክስተቶችን ይገልጣሉ፣ ደግሞም እግዚአብሔር እነዚህን ክስተቶች እንዴት እንደገጠማቸውም ይገልጣሉ፡፡ በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ልጆች የፈጠሩትን ስጋት በምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 3 ያለውን የእግዚአብሔር አፀፋ እንመልከት፡፡ የሚያዛዝነው ግን፣ እነዚህ ጥቅሶች በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ለትርጉም አዳጋች ከሆኑት መካከል የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ችግሩ በተቀዳሚነት የሚያጠነጥነው በቁጥር 2 ላይ ሲሆን እንዲህ እናነብባለን፡

የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ፡፡ (ዘፍጥረት 6፡2)

ሙሴ የእግዚአብሔር ልጆችና የሰው ሴቶች ልጆች እነማን እንደሆኑ በግልፅ አብራርቶ አላስቀመጠም፡፡ ምናልባት ቀደምት ተደራሲያኑ ይረዷቸው ይሆናል፡፡ ለእኛ ዘመን አንባቢዎቸ ግን የእነዚህን ገፀ-ባህርያት ማንነት ከመጠየቅ ባሻገር በትክክል ለማረጋገጥ አዳጋች ነው፡፡

በአተረጓጎም ታሪክ ውስጥ ሦስት ምክንያታዊ ምላሾች ይቀርባሉ፡፡ አንደኛ፣ የእግዚአብሔር ልጆች የሴት ወገን የሆኑት ሲሆኑ ከቃየን ዘር ሴቶች ጋር የተጋቡት ናቸው የሚል ነው፡፡ ይህ አተረጓጎም ጥቂት መሠረት አለው ምክንያቱም በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እና 5 በሴታውያንና በቃየናውያን መካከል የተጠቀሰው ተቃርኖ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ምናልባት መላእክት ይሆናሉ፣ የሰው ሴቶች ልጆች ደግሞ ሰብዓዊ ሰዎች ይሆናሉ የሚል ነው፡፡ ይህኛውም አመለካከት የራሱ መሠረት አለው ምክንያቱም መላእክት ደጋግመው በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ተጠርተዋል፡፡ ለምሳሌ፣ በኢዮብ ምዕራፍ 1 ቁጥር 6 እና በመዝሙር 29 ቁጥር 1 እናገኛለን፡፡ ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ የእግዚአብሔርን ልጆች ነገሥታት ወይም የመሳፍንት ዘር ሆነው ተራ ሴቶችን ያገቡትን ሊወክሉ ይችላሉ፡፡ ይህም አመለካከት የራሱ ዋቤ አለው ምክንያቱም በጥንታዊው የቅርብ ምሥራቅ ነገሥታት በተደጋጋሚ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠሩ ነበር፡፡ ይህም የዳዊት ልጆች በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 7 ቁጥር 14 እና በመዝሙር 2 ቁጥር 7 የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው እንደተጠሩ ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን እኔ ወደዚህ ወደ ሦስተኛው አተረጓጎም ባደላም፣ ሆኖም የእኔ በምለው ላይ ማክረር አልሻም፡፡

ምንም እንኳን በእነዚህ ባህርያት ማንነት ላይ እርግጡን ባናውቅም፣ ስለ ድርጊታቸው ግን እርግጠኛ ነን፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 2 ውስጥ እንዲህ እናነብባለን፡

የእግዚአብሔር ልጆችም … ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ፡፡ (ዘፍጥረት 6፡2)

በብሉይ ኪዳን ዘመን ይህ የህጋዊ ጋብቻ ቋንቋ አይደለም፣ ሴቶቹ ወይም ቤተሰባቸው ለዚህ ግንኙነት ያላቸውን ስምምነት እንዲገልጡ ያልተጠበቀ መሆኑን በብርቱ ያሳየናል፡፡ ይልቁኑ፣ የእግዚአብሔር ልጆች፣ ምናልባትም ጉልበታም የሆኑት የመሳፍንት ዘሮች፣ ሴቶቹን ያለ ፈቃዳቸው በጉልበት ወስደዋቸው ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ስፍራ ያለው ቋንቋ ምናልባት የእግዚአብሔር ልጆች እነዚህን ሴቶች ደፍረዋል የሚል ፍቺ ሊይዝ ይችላል፡፡ በሁሉም ወቅቶች፣ ቀደም ብሎ በቃየንና በዘሩ የድፍረት ብዝበዛ የተገለጠው ክፋት ወደ ሌላ የሕይወት ዘርፍ ይሸጋገራል፡፡ ያም በሴቶች ላይ የተፈፀመ ክፋት፡፡

ሙሴ የእግዚአብሔር ልጆች የፈጠሩትን ስጋት ከገለጠ በኋላ፣ ወደ ዋናው ጉዳዩ እግዚአብሐር ለእነዚህ ክስተቶች ወደሰጠው ምላሽ ይሸጋገራል፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 3 እንዲህ እናነባለን፡

እግዚአብሔርም፣ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፣ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሃያ ዓመት ይሆናሉ” አለ፡፡ (ዘፍጥረት 6፡3)

ኃጢአት በሰው ዘር ላይ እያስከተለ ባለው የማይቋረጥ ክፋት እግዚአብሔር አዘነ፣ ስለዚህም ይህንን ክፋት ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ አወጀ፡፡ ሆኖም፣ እግዚአብሔር ፍርዱን ከማምጣቱ በፊት ለሰው ዘር አንድ መቶ ሃያ ዓመታት በቸርነቱ ሰጠ፡፡

ሁለተኛው በምድር የተከናወነ ተግባርና መለኮታዊ ምላሽ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 4 እስከ 7 የሚገኘው የኔፊሊም ታሪክ ነው፡፡

ኔፊሊም

በቁጥር 4 ውስጥ እያደገ ስለመጣው ሌላ የስጋት ድባብ እናብባለን፡

በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፤ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ፡፡ (ዘፍጥረት 6፡4)

አንዳንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ቅዱሶች የሰብዓ ሊቃናትን ቅጂ በመከተል “ኔፊሊም” የተሰኘውን የዕብራይስጥ ቃል “ግዙፎች” ብለው ይተረጉሙታል፡፡ ይህ አተረጓጎም እንደ አለመታደል ሆኖ የቃላቱን ማሳሰቢያ በትክክል አያስተላልፍም፡፡ በቃላቱ ትክክለኛ አተረጓጎም ላይ የምሁራኑ ሃሳብ ይለያያል፣ ሆኖም በአብዛኛው ብርቱ ተዋጊዎችን ወይም የጦር አበጋዞችን ያመለክታል፡፡

በዚህ ምንባብ፣ ሙሴ እነዚህን ኔፊሊም “በዱሮ ዘመን፣ ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ” በማለት ይጠቅሳቸዋል፡፡ ኃያላን ወይም በዕብራይስጡ hagiborim (הַגִּבֹּרִ֛ים), ኃያል ወታደሮችን ወይም ተዋጊዎችን ያመለክታል፡፡ በዚህ አውድ፣ የኔፊሊሞች ዝና በአሉታዊ ጎኑ ተጠቅሷል፡፡ እነዚህ ሰዎች በዙሪያቸው ባሉት ላይ በሚከፍቱት ጦርነት በብዝበዛቸውና በክፋታቸው ይታወቃሉ፡፡ ቃየን ወንድሙን አቤልን ሲገድል የጀመረ ክፋት፣ በቃየን ትውልድ በላሜህ ቀጠለ፣ ከዚያም የኔፊሊም ወታደሮች ያገኙትን ሁሉ ወደሚፈታተኑበት እርከን ተሸጋገረ፡፡ በቁጥር 5 እንዲህ እናነብባለን፡

እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደበዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ፡፡ (ዘፍጥረት 6፡5)

በኔፊሊሞች መገለጥ፣ የሰው ዘር ክፋት ወደዚህ ደረጃ ደረሰ ኃጢአትም የሰውን ዘር ተቆጣጠረ፡፡ በውጤቱም፣ ከቁጥር 6 እስከ 7 እንዲህ እናነብባለን፡

እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፣ በልቡም አዘነ፡፡ እግዚአብሔርም የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፣ ከሰው እስከ እንስሳ እስከተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ፡፡ (ዘፍጥረት 6፡6-7)

ኔፊሊሞች የእርሱን ዓለም እንዴት እንዳሸበሩ እግዚአብሔር አየ፣ ስለዚህም ዓለምንና ሞላዋን በሚያዳርስ ጥፋት የመገለጫው ጊዜ እንደደረሰ ወሰነ፡፡

የኋላ ተስፋ

ደስ የሚያሰኘው፣ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 8 የሚደመደመው በፍርድ ቃል አይደለም፡፡ ይልቁኑ፣ ሙሴ አጠቃላዩን የፍጥረተ ዓለም ዘገባውን ገዢ ፍሰት በዚህ ክፍል በመጠበቅ በቁጥር 8 ላይ የኋላውን ተስፋ ይጠቅሳል፡፡ ምንም እንኳን ከኃጢአት ርኩሰት የተነሳ እግዚአብሔር የሰውን ዘር ሊያጠፋ ቢጨክንም፣ አንድ ተስፋ የተገባለት ሰው ተገኘ፡

ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ፡፡ (ዘፍጥረት 6፡8)

በእነዚህ ጥቂት ቃላት፣ የስጋትንና የነፃነትን ተስፋ ትዕይንት ሙሴ ያጠቃልላል፡፡ በጥፋት ውሃም አማካይነት በክፋት የተሞላውና ኃጢአተኛው የሰው ልጅ ጥፋት ለቀጣዩ ትውልድ ነፃነትን አስገኘ፡፡

በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ድረስ ባለው ክፍል ላይ ካደረግነው ስነ-ጽሑፋዊ አወቃቀር ምርመራ እነዚህ ምዕራፎች በሁለት ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ፡፡ አንደኛ፣ በቃየንና በዘሩ ዘመን በእግዚአብሔር ላይ ባመፁ ሰዎች ምክንያት በተገለጠው ክፋት እና ስጋት ላይ ያተኩራሉ፤ ሁለተኛ፣ በእግዚአብሔር ልጆችና በኔፊሊም ዘመን በተገለጠው የኃጢአተኛ ሰዎች ስጋት ላይ ያተኩራሉ፡፡ በሁሉም ወቅት፣ ሙሴ በአንዱ በሴት ልጅ፣ በኖኅ በኩል እግዚአብሔር ነፃነትን እንደሚያመጣ ያመለክታል፡፡

የዚህን የዘፍጥረትን ክፍል መሠረታዊ አወቃቀርና ማዕከላዊ ትኩረት ከተመለከትን፣ ቀጣዩን ጥያቄ መጠየቅ ይገባናል፡፡ የእነዚህ ምዕራፎች ቀደምት ትርጉም ምን ነበር? ሙሴ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለሚመራቸው እስራኤላውያን የሚያስተላልፈው ምን ነበር?

ቀደምት ትርጉም

የዚህን የፍጥረተ ዓለም ታሪክ ክፍል ቀደምት ትርጉም በአግባቡ ለመጨበጥ፣ ሁለት ጉዳዮችን መመርመር ይጠቅማል፡ በመጀመሪያ፣ ሙሴ የዚህን የፍጥረተ ዓለም ታሪኩን ክፍል ከእስራኤላውያን ልምምድ ጋር እንዴት እንዳገናኘው እንመለከታለን፤ ሁለተኛ፣ ለሙሴ ቀደምት እስራኤላውያን አንባቢዎች እነዚህ ትስስሮች ያላቸውን አንድምታ እንመረምራለን፡፡ እስኪ አስቀድመን ሙሴ እነዚህን ምዕራፎች ከሚመራቸው ከእስራኤላውያን ልምምዶች ጋር እንዴት እንዳገናኛቸው እንመልከት፡፡

ትስስሮች

ሙሴ ይህንን የፍጥረተ ዓለም ዘገባውን ክፍል ከሚኖርበት ዘመን ጋር ያዛመደው በቀደምት የሰው ዘር ውስጥ የነበረው ክፋት እስራኤልን ከገጠመው ክፋት ጋር በቅርበት ከሚመሳሰልበት መንገድ ጋር በማብራራት ነበር፡፡ ይህንንም በማድረግ፣ እስራኤልን የገጠመው ችግር ጥንታዊውን ዓለም ከገጠመው ችግር ጋር በጣም ይመሳሰል እንደነበረ አመልክቷል፡፡

ሙሴ እነዚህን ምሰስሎች እንዴት እንዳዋቀራቸው ለመመርመር፣ እንደገና ዋናዎቹን የዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ሁለት ክፍሎች መለስ ብለን መቃኘት ይገባናል፡፡ አንደኛው፣ በዘፍጥረት ምእራፍ 4 እና 5 የቀደመው ክፋትና የነፃነት ተስፋ ትዕይንት ሲሆን፣ ሁለተኛው ትዕይንት ደግሞ፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 8 የሚገኘው የኋለኛው ክፋትና የነፃነት ተስፋ ነው፡፡ አስቀድመን ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እና 5 ከእስራኤል ልምምድ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ እንመልከት፡፡

ቀደምት ክፋትና ተስፋ

በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እና 5 የሚገኘውን የክፉዎችና የጻድቃን ባሕርይ ስንመለከት፣ ሙሴ መጻሕፍቱን ያቀናበረው አንባቢዎቹ ቃየንና ቤተሰቡን ከግብጻውያን ጋር፣ ጻድቁን አቤልን፣ ሴትንና የሴትን ትውልድ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ህዝብ ከራሳቸው ጋር እንዲያስተያዩ አልሞ እንደነበር ግልፅ ይሆንልናል፡፡ ታዲያ ሙሴ እነዚህን ትስስሮች እንዴት አዋቀራቸው?

ትረካዎች

በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 16 የሚገኘውን የኃጥኡ የቃየንን ታሪክ በመመርመር መጀመር ይገባናል፡፡ በዚህ ታሪክ፣ እስራኤላውያን ይህንን ምንባብ ከራሳቸው ዘመን ጋር ሊያስተሳስሩ በሚችሉባቸው ቢያንስ በአምስት ጉዳዮች ላይ ሙሴ ያተኩራል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሙሴ ትስስሮቹን ለመጥቀስ ይቀናው ዘንድ የቃየንንና የአቤልን ሥራ ይጠቅሳል፡፡

በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 2 ቃየንና አቤል ተለይተው የተገለጡበትን መንገድ አድምጡ፡

አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ፡፡ (ዘፍጥረት 4፡2)

ይህ ምንባብ እንደሚያመለክተን፣ ቃየን የግብርና ባለሙያ ነበር፣ አቤል ደግሞ እረኛ ነበር፡፡ በጥንታዊውም ሆነ በዘመነኛው ዘመን፣ በግብርና ላይ የተመሠረተ ኑሮ በሚኖሩ ህዝቦችና በዘላን እረኞች መካከል የተለመዱ ውጥረቶች ይቀሰቀሳሉ፡፡ የዘፍጥረት መጽሐፍ ራሱም እንደሚያመለክተን፣ ሙሴና እስራኤላውያኑ ይህን ዓይነቱን ውጥረት እንዲገነዘቡትና በግብፅ በነበሩት ወቅት እንዴት ወደ ከባድ ችግር ሊያመራ እንደሚችል ይገነዘባሉ፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 46 ቁጥር 33 እና 34 ውስጥ፣ ወንድሞቹ ወደ ግብፅ በመጡበት ወቅት ዮሴፍ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፡

ፈርዖን ቢጠራችሁ፣ ተግባራችሁስ ምንድን ነው? ቢላችሁ፣ በግ ጠባቂ ሁሉ ለግብፅ ሰዎች ርኩስ ነውና በጌሤም እንድትቀመጡ እንዲህ በሉት፣ እኛ ባሪያዎችህ ከብላቴንነታችን ጀምረን እስከ አሁን ድረስ፣ እኛም አባቶቻችንም እንስሳ አርቢዎች ነን፡፡ (ዘፍጥረት 46፡33-34)

ዮሴፍ በዚህ ስፍራ የሰጠው መመሪያ ሙሴ ለምን ቃየን ገበሬ አቤል ደግሞ በግ ጠባቂ ነበር ብሎ እንደጠቀሰ ጥቂት ነገር ብልጭ ያደርግልናል፡፡ እስራኤላውያን አንባቢዎቹ ገበሬ የሆነውን ቃየንን ከግብፃውያን ጋር፣ የተጠቃውን እረኛ፣ አቤልን ደግሞ ከራሳቸው ጋር እንዲያስተሳስሩ ይፈልግ ነበር፡፡

በዚህ ታሪክና በሙሴ ቀደምት ተደራሲያን መካከል ያለው ትስስር ሁለተኛው ጭብጥ ሆኖ የሚገለጠው በቃየንና በአቤል የቀረበው መስዋዕት ነው፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እንደሚነግረን፣ እግዚአብሔር የቃየንን መስዋዕት አልተቀበለም በአቤል መስዋዕት ግን ደስ ተሰኘ፡፡ እግዚአብሔር በእነዚህ መስዋዕቶች መካከል ያደረገው ልዩነት በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 3 እና 4 ውስጥ በግልጥ ተቀምጦ እንዲህ ይነበባል፡

ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መስዋዕቱ ተመለከተ፤ (ዘፍጥረት 4፡3-4)

ሙሴ መስዋዕቶቹን የገለጠበትን መንገድ ልብ በሉ፡፡ በቁጥር 3 “ቃየን ከምድር ፍሬ” አቀረበ ይልና፣ በቁጥር 4 ግን “አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ” ይላል፡፡ ይህ መለያ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ቃየን ከማሳው ላይ ከሰበሰበው ፍሬ ከየትኛውም ነው ያቀረበው፡፡ አምልኮው ለስም ያህል ነው ምክንያቱም ከምርቱ የተመረጠውን ለእግዚአብሔር አላስቀመጠም፡፡ አቤል ግን ከልቡ በሆነ መስዋዕትነት የሰባውን (በብሉይ ኪዳን መስዋዕት የላቀ ዋጋ ያለውን) እና ከመንጋው በኩሩን (እንደ ሙሴ ህግ በጣም ከፍ ያለ ዋጋ ከሚሰጣቸው እንስሶች መካከል) ለእግዚአብሔር በማቅረብ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ፈፀመ፡፡የቃየን መስዋዕትነት በዘልማድ ከሚቀርቡ መስዋዕቶች እጅግም የማይሻል ነበር፡፡ በንፅፅሩ ግን፣ አቤል ከልብ የሆነ አምልኮን ለእግዚአብሔር አቀረበ፡፡

ሙሴ በቃየንንና በአቤል መስዋዕቶች መካከል ያለውን ልዩነት በግብፃውያንና በእስራኤል መካከል ያለውን ትስስር ለመግለጥም ተጠቅሞበታል፡፡ ይህ ዳራ ግን በጣም አስገራሚ ሆኖ የምናገኘው ሙሴ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፈርዖን ቀርቦ ለአምላኩ እንዲሰዋ እስራኤልን እንዲለቅቅ መጠየቁን ስናስታውስ ነው፡፡ ዘፀአት ምዕራፍ 5 ቁጥር 3 ስናነብብ፣ ሙሴና አሮን ፈርዖንን እንዲህ ብለውታል፡

“የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ … የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፣ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ እንለምንሃለን አሉት፡፡” (ዘፀአት 5፡3)

ፈርዖን ግን ጥያቄያቸውን አልተቀበለም፡፡ ሙሴ በቁጥር 4 እንደዘገበው፣ ፈርዖን እንዲህ አላቸው፡

አንተ ሙሴ፣ አንተም አሮን፣ ሕዝቡን ለምን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ አላቸው፡፡ (ዘፀአት 5፡4)

ልክ ቃየን የይስሙላ መስዋዕት በማቅረብ እግዚአብሔርን እንዳላከበረ ሁሉ፣ ግብፃውያንም ለእግዚአብሔር እውነተኛ አምልኮ አላቀረቡም፡፡ ሆኖም፣ ልክ አቤል ከልብ የሆነና ተቀባይነት ያለው መስዋዕት እንዳቀረበ ሁሉ፣ እስራኤላውያን ለያህዌ የሚቀርበውን እውነተኛ አምልኮ ለማቅረብ ናፍቀዋል፡፡ በዚህ መንገድ፣ ሙሴ ግብፅን ከቃየን ጋር እስራኤልን ደግሞ ከአቤል ጋር የሚያስተያይ ሌላ ትስስር መሥርቷል፡፡

ሙሴ ከእስራኤል ልምምድ ጋር ትስስር የመሠረተበት ሦስተኛው መንገድ የግድያው ጭብጥ ነው፡፡ ቃየን ወንድሙን ገደለ፣ ይህም ሁኔታ በግልፅ ወሳኝነቱ የሚታየው እስራኤላውያን በግብፅ የተገደሉበትን ሁኔታ ስናስታውስ ነው፡፡ በዘፀአት ምዕራፍ 1 እና 2 ግብፃውያን እሥራኤላውያንን ከአቅም በላይ የሆነ ሥራ ማሠራታቸው ሳያንሳቸው፣ ህፃናት ልጆቻቸውን ጨምሮ፣ በርካቶቹን ሆን ብለው ገድለዋቸዋል፡፡ ሙሴ በዚህ መንገድ በቃየንና በግብፃውያን፣ በአቤልና በእስራኤላውያን መካከል የበለጠ ትስስር አመልክቷል፡፡

ሙሴ ትስስር የመሠረተበት አራተኛ መንገድ በምድር ላይ ቃየን የነበረበትን አድራሻ መግለጥ ነው፡፡ ቃየል አቤልን በመግደሉ ምክንያት እግዚአብሔር ሲረግመው፣ ቃየንን ከለሟ ምድር አስወጥቶታል፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 11 እና 12 እንዲህ ይነበባል፡፡

… በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ፡፡ ምድርን ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ፡፡ (ዘፍጥረት 4፡11-12)

ቃየን እርሻው በጣም ጥቂት ምርት በሚያስገኝበት ምድር እንዲኖር ተረገመ፡፡ ይህ የቃየን አድራሻ ሙሴ ስለ ግብፃውያን ምድር ከደረሰበት ምርመራ ጋር በጣም የሚገጥም ነው፡፡ በዘዳግም ምዕራፍ 11 ከቁጥር 10 እስከ 12 ከነዓንንና ግብፅን እንዲህ አነፃፅሯቸዋል ይህም የግብፅን ምድር እስራኤልን ከሚወስድበት ምድር ጋር ያስተያየበት ነው፡፡

ትወርሳት ዘንድ የምትገባባት ምድር፣ በአትክልት ስፍራ እንደሚዘሩ ዘርህን እንደዘራህባት፣ በእግርህም እንዳጠጣሃት፣ እንደ ወጣህባት እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም፡፡ ነገር ግን ትወርሱአት ዘንድ የምትገቡባት ምድር ኮረብታና ሸለቆ ያለባት አገር ናት፤ በሰማይ ዝናብ ውሃ ትረካለች፡፡ አምላክህ እግዚአብሔር የሚጎበኛት አገር ናት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁል ጊዜ በእርስዋ ላይ ነው፡፡ (ዘዳግም 11፡10-12)

እግዚአብሔር ቃየንን ከዔድን በጣም ወደ ራቀ ምድር ሰደደው፣ ያም ምድር እንደ ግብፅ ያለ ምድር ሲሆን፣ በዚያም ግብርና እጅግ አድካሚ ነው፡፡ ይህም እውነታ የሙሴ እስራኤላውያን አንባቢዎች ቃየንን ከግብፃውያን ጋር የሚያስተሳስሩበት ሌላው መንገድ ነው፡፡

ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 እና 5 ቃየንን ከግብፅ ጋር፣ አቤልን ከእስራኤል ጋር የሚያስተሳስርበት አምስተኛው መንገድ ስለ ቃየን ጥበቃ የሚናገረው መሪ ሃሳብ ነው፡፡ ምንም እንኳን ቃየን ወንድሙን አቤልን ቢገድልም፣ ክፉ እንዳይደርስበት እግዚአብሔር ከለላ አድርጎለታል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 15 ውስጥ እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል፡

… እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል፡፡ (ዘፍጥረት 4፡15)

ቃየን ገዳይ ቢሆንም እንኳ ክፉ እንዳያገኘው እግዚአብሔር ከለላ አድርጎለታል፡፡ እስራኤላውያን አንባቢዎቹ ሁኔታዎቹን በግብፅ ከነበሩበት ከራሳቸው ሁኔታ ጋር ሊያስተያዩዋቸው ይችሉ ዘንድ ሙሴ በድጋሚ እነዚህን ሁኔታዎች ይዘግብላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ለግብፅ ታላቅ ጥበቃን አድርጎላት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ገዳዮች ቢሆኑና መለኮታዊ ፍርድ የሚገባቸው ቢሆንም፣ ለረጅም ዘመናት እግዚአብሔር በግብፅ ላይ ልዩ ጥበቃውን አጽንቶአል፡፡

እንግዲህ ቢያንስ በአምስት መንገዶች ሙሴ በእርሱ የፍጥረተ ዓለም ዘመንና በእስራኤል ዘፀአት መካከል ትርጉም የሚሰጥ ትስስርን እንደመሠረተ ዐይተናል፡፡ የተግባር፣ የአምልኮ፣ የግድያ፣ የስፍራ እና የጥበቃ መሪ ሃሳቦች በጠቅላላ የሚያመለክቱት እስራኤላውያን አንባቢዎቹ ቃየንን ከግብፃውያን ጋር፣ አቤልን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ህዝብ ከራሳቸው ጋር በማስተሳሰር ይህንን ታሪክ እንዲያዛምዱት ሙሴ የሚሻ መሆኑን ነው፡፡

በኃጢአተኛው የቃየን ታሪክ ውስጥ የተመሠረቱትን ትስስሮች ከተመለከትን፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 25 እና 26 ውስጥ ወደሚገኘውና በጻድቁ ሴት ላይ ወደ ሚያጠነጥነው ተጓዳኝ ምንባብ መሸጋገር ይገባናል፡፡

እንደተመለከትነው፣ ሙሴ ስለ ሴትና ስለ ልጁ፣ ሄኖክ ወሳኝ ሃሳብ ሰንዝሯል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 26 እንዲህ እናነብባለን፡፡

… በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ (ዘፍጥረት 4፡26)

ሙሴ ስለ ሴትና ስለ ልጁ ይህን እውነታ የጠቀሰው አንባቢዎቹ ራሳቸውን ከአቤል ጋር ብቻ ሳይሆን፣ አቤልን ከተካው ከኣዳም ልጅ፣ ከሴት ጋር እንዲያቆራኙ ነበር፡፡

በመጀመሪያ፣ ሴት የተጠራው በመለኮታዊው የያህዊ ስም ሲሆን ይህም መጠሪያ ከእስራኤል ጋር ይገናኛል፡፡ በጣም በሚማርክ መንገድ፣ በሙሴ ዘመን የያህዌ ስም እጅግ ታዋቂ ሆኖ እንደነበር የዘፀአት መጽሐፍ ግልፅ ያደርግልናል፡፡ ለምሳሌ፣ በዘፀአት ምዕራፍ 3 ቁጥር 15 እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ተናግሯል፡

… ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፡፡ የአባቶቻችሁ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፣ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው፡፡ (ዘፀአት 3፡15)

ምንም እንኳን ከሴት ዘመን አንስቶ፣ እስከ ሙሴ ዘመን ድረስ ያህዌ የሚለው ስም በጥቅም ላይ መዋሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘገባዎች ቢያመለክቱም፣ ይህ ስም ግን በዋናነት ለእግዚአብሔር የሚውል ስም እየሆነ መጣ፡፡ በዚህም ምክንያት፣ በሙሴ አመራር ስር የነበሩት ታማኝ እስራኤላውያን ራሳቸውን ከጻድቁ ሴት ጋር ያመሳስላሉ፡፡ ልክ እንደ እርሱ የያህዌን ስም ያገንናሉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ፣ እስራኤላውያን ራሳቸውን ከሴት ጋር በጸሎት መሪ ሃሳብ ሊያስተሳስሩ ይገባል፡፡ ይህም ጭብጥ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 26 ውስጥ “በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ” ብሎ ሙሴ ስለ ሴት ቤተሰብ በጻፈበት ክፍል ውስጥ ይገኛል፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ “በእግዚአብሔር ስም መጠራት” ማለት በጭንቅ ቀን መለኮታዊውን እርዳታ ለማግኘት መጣራት ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሙሴ በራሱ ዘመን ከሚኖሩ እስራኤላውያን ጋር ያደረገውን ሁለተኛ ትስስር እንመለከታለን፡፡ ከተቀረው የሙሴ መጻሕፍት ክፍል እንደምንረዳው፣ እስራኤል ከግብፅ ሲወጡ፣ ልክ ሴትና ሄኖስ እንዳደረጉት ሁሉ፣ በጭንቃቸው ጊዜ ወደ ያህዌ ለእርዳታ ይጣሩ ነበር፡፡

ሙሴ የኃጥኡን ቃየንና የጻድቁን አቤልን ትረካዎች ከራሱ ዓለም ጋር ተጓዳኝ እንዲሆኑ አድርጎ መጻፉን ተመልክተናል፡፡ አንባቢዎቹ ግብፃውያን የቃየን አምሳያዎች መሆናቸውን ልብ እንዲሉ ይፈልጋል፡፡ እነርሱ ራሳቸውን ደግሞ የአቤልና የሴት አምሳያዎች አድርገው እንዲመለከቱ ይፈልጋል፡፡

እነዚህን መሠረታዊ ትስስሮች በልቡናችን ይዘን አሁን ደግሞ ወደ ቃየንና ወደ ሴት የዘር ሐረግ እንሸጋገር፡፡

የትውልድ ሐረግ

ወደፊት እንደምናየው፣ ሙሴ አነዚህን የትውልድ ሐረጎች ያዋቀረው፣ እስራኤላውያን፣ ክፉዎችን ከግብፃውያን ጋር፣ ራሳቸውን ደግሞ ከጻድቃኑ ጋር ማስተሳሰራቸውን እንዲገፉበት ለማድረግ ነው፡፡ ይህንን ዐቢይ ዓላማውን በስፋት ለመግለጥ፣ ዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 17 እስከ 24 የቃየንን ዝርያ ሊካድ በማይቻል መንገድ ከግብፃውያን ጋር አስተሳስሮ ያቀርባቸዋል፡፡ እነዚህ ትስስሮች ቢያንስ በስድስት መንገዶች ይገለጣሉ፡፡

በመጀመሪያ፣ ሙሴ ቃየንን እንደ ከተማ መሥራች ይገልጠዋል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 17 እንደፃፈው፡

ቃየንም … ከተማን ሠራ (ዘፍጥረት 4፡17)

መናገር በማያስፈልግ መንገድ፣ እስራኤላውያን በጠቅላላ በውል እንደሚያውቁት ግብፃውያን ታላላቅ ከተማን በመገንባት ይታወቃሉ፡፡ እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት ውስጥ በነበሩበት ወቅት፣ ለግብፃውያን ከተማን መገንባት አንዱ ተግባራቸው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ስለ ቃየን የተነገሩ ቃላት ከግብፃውያን ጋር ትልቅ ትስስር ይመሠርታሉ፡፡

ሁለተኛ፣ ስለ ቃየን ከተማ ልብ ልንል ይገባናል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 17፣ እንዲህ እናነብባለን፡

ቃየንም … ከተማን ሠራ፣ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሄኖሕ አላት፡፡ (ዘፍጥረት 4፡17)

በሙሴ ዘመን ለነበሩ እስራኤላውያን፣ ይህ ጭብጥ የግብፃውያንን ልምምድ ያስታውሰናል፡፡ በዘፀአት ምዕራፍ 1 ቁጥር 11 ውስጥ ሙሴ እንደዘገበው፡

(ግብፃውያን) በብርቱ ሥራም ያስጨንቋቸው ዘንድ ግብር አስገባሪዎችን ሾሙባቸው፤ ለፈርዖንም (እስራኤላውያን) ፊቶምንና ራምሴን ጽኑ ከተሞች አድርገው ሠሩ፡፡ (ዘፀአት 1፡11)

ራምሴ የተሰኘችው ከተማ ስሟ የተሰጣት ለፈርዖን ራምሴ ክብር (ስም ማስጠሪያ) ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ልክ እንደ ቃየን፣ ግብፃውያን ከተሞችን በራሳቸው ስም ለራሳቸው ክብርና ዝና ይገነቡ ጀመር፡፡ በዚህ መንገድ፣ የቃየን የትውልድ ሐረግ በቃየንና በግብፃውያን መካከል ሌላ ትስስር መሥርቷል፡፡

በቃየን ዝርያና በግብፃውያን መካከል ያለው ሦስተኛ ትስስር የተገለጠው የቃየን ዝርያ የሆነው ላሜህ የእርሱን የግድያ ተግባር በወረሰበት ትዕቢት ውስጥ ነው፡፡ በምዕራፍ 4 ቁጥር 23 ውስጥ ላሜህ ራሱ ለሚስቶቹ ስለ ተግባሩ ዜማ ሲያዜም እንዲህ እናነባለን፡

እናንት የላሜህ ሚስቶች ዓዳና ሴላ፣ ቃሌን ስሙ፣ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጎልማሳውን ለቁስሌ፣ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና፤ (ዘፍጥረት 4፡23)

ላሜህ ስለ ግፉ ያቀረበው የትዕቢት ቀረርቶ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ላሜህን ከግብፃውያን ጋር በልቡናቸው እንዲያስተሳስሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ፈርዖንና ሠራዊቱ በግድያ ስለሚፈፅሟቸው ብዝበዛዎች የጥንት ግብፃውያን እንደሚያሞጋግሱዋቸው እስራኤላውያን በውል ያውቃሉ፡፡

አራተኛው ትስስር የሚገለጠው ሙሴ በልጆች ሞት ላይ ባደረገው ትኩረት ውስጥ ነው፡፡ ላሜህ የተናገረውን እንደገና አድምጡ፡፡ በምዕራፍ 4 ቁጥር 23 እንዲህ እናነብባለን፡

እኔ ጎልማሳውን ለቁስሌ፣ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና፤ (ዘፍጥረት 4፡23)

በዚህ ስፍራ “ጎልማሳው” የሚለው ቃል በእብራይስጡ yeled (יֶלֶד) የሚል ነው፣ አብዛኛውን ጊዜ “ወንድ ልጅ” ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ላሜህ ከገደላቸው ወንድ ልጆች መካከል ገና ታዳጊ ወንዶች ልጆች አይጠፉም፡፡ ሁላችንም በዘፀአት ምዕራፍ እንደምናነበው፣ ፈርዖን የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች እንዲገደሉ አዝዞ ነበር፡፡ ልክ እንደ ቃየኑ ላሜህ ሁሉ፣ ግብፃውያንም ተከላካይ የሌላቸውን እስራኤላውያንን ወንዶች ልጆች አጥቅተዋል፡፡

በቃየን ቤተሰብና በግብፃውያን መካከል የሚታየው አምስተኛው ትስስር የሚገለጠው ቃየን በገለጠው የበለጠ የበቀል ስጋት ውስጥ ነው፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 24 ውስጥ የተጠቀሰው ከቃየን እጅግ የበለጠ ጥበቃ የሚያስፈልገው መሆኑን ያሳያል፡፡

ቃየንን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፡፡ (ዘፍጥረት 4፡24)

ልክ ላሜሕ የእግዚአብሔርን ጥበቃ እንዳሰበ ሁሉ፣ የግብፁም ፈርዖን ከአማልክቶቻቸው ጥበቃን እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነበር፡፡ ግብፃውያን ለዘለቄታው ባይፀናም ለረጅም ዘመናት ያህል ከክፉ ነገር ተጠብቀው ኖረዋል፡፡

በስድስተኛ ደረጃ፣ የቃየንን ሐረግ ባህላዊ ረቂቅነት ልብ ማለት ይገባናል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 20 እስከ 22 ሦስቱ የቃየን ወንድሞች ያባል፣ ዩባል እና ቱባልቃይን የተገለጡበትን ሁኔታ አድምጡ፡

ዓዳም ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ፡፡ የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ፡፡ ሴላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች፡፡ (ዘፍጥረት 4 ፡20-22)

እነዚህን ቃላት ስንመለከት፣ የቃየን ቤተሰብ የረቀቀ መልክ እንዳለው ሙሴ ይገልጥልናል፡፡ ያባል ተራ እረኛ ብቻ አልነበረም፣ የከብት አርቢዎች አባት ነበረ እንጂ፡፡ ዮባል የሙዚቃ ፈልሳፊ ነበር፣ ቱባል ቃይን ደግሞ አንቱ የተባለ የብረታ ብረት ሥራ ባለሙያ ነበር፡፡ ስለዚህ በሙሴ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ይህንን ትስስር ሊዘነጉት አይችሉም፡፡ ከእስራኤል አባቶች ቀላል የከብት አርቢነት ሕይወት ጋር ሲነፃፀር፣ የግብፃውያን ባሕል እጅግ የተወሳሰበ ነው፡፡ ሙሴ የቃየንን ኃጥእ የትውልድ ሐረግ በዚህ መንገድ በመግለጥ አንባቢዎቹ በቃየን ዝርያና በግብፃውያን መካከል ያለውን ትስስር እንዲያረጋግጡ ያደርጋል፡፡

እንግዲህ ሙሴ በቃየን ትውልድና በእስራኤላውያን መካከል ቢያንስ ስድስት ዓይነት ትስስሮችን እንደመሠረተ አስተውለናል፡፡ የከተማ ግንባታው፣ ለከተሞች ስም አወጣጡ፣ በግድያው መኩራራቱ፣ በልጆች ላይ ክፋትን መፈፀሙ፣ መለኮታዊ ጥበቃ የተደረገለት መሆኑ እና የቃየን ቤተሰብ ባህላዊ ረቂቅነት እነዚህን ትስስሮች ለመግለጥ በዓላማ ተነድፈዋል፡፡

አሁን ደግሞ በዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ከቁጥር 1 እስከ 32 ወደተገለፀው ወደ ሴት የትውልድ ሐረግ መሸጋገር ይገባናል፡፡ ምናልባት እንደምንገምተው፣ እስራኤላውያን አንባቢዎቹ ራሳቸውን ከሴት የትውልድ ሐረግ ጋር ያመሳስሉ ዘንድ ሙሴ የሴትን የትውልድ ሐረግ ይዘረዝራል፡፡ ይህ ትስስር ቢያንስ በአራት ምክንያቶች ይገነባል፡፡ በመጀመሪያ፣ በስነ-ሕይወታዊ ደረጃ፣ እስራኤል ከሴት ዘር የተገኘች መሆኗን እንመለከታለን፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ቁጥር 32 የኖህን ሦስት ልጆች ስሞች እናገኛለን፡

ኖኅም የአምስት መቶ ዓመት ሰው ነበረ ኖኅም ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ። (ዘፍጥረት 5፡32)

በተለይ ሴም የሚለው ስም ለሙሴ እጅግ ወሳኝ ነው ምክንያቱም ሴም የእስራኤል ግንድ ነው፡፡ በዘመናችን ቋንቋ ከሴም የተገኙ መሆኑን ለማሳየት “ሴማውያን” እንላቸዋለን፡፡ ምንም እንኳን ሌሎችም ህዝቦች ከሴም ዘር የተገኙ ቢሆንም፣ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጡ ከሴም ዘር የወጡ ልዩ ዘሮች ናቸው፡፡ በዚህ ቀላል ስነ-ሕይወታዊ መረዳት፣ ሙሴ እስራኤላውያን አንባቢዎቹን ከሴት የትውልድ ሐረግ ጋር ያያይዛቸዋል፡፡

በሴት ዘርና በእስራኤላውያን መካከል ያለው ሁለተኛው ትስስር የሚታየው በሴት ዝርያ ጽድቅ ላይ የተደረገው ተደጋጋሚ ትኩረት ነው፡፡ የሴት ዝርያ ታማኝና ጻድቅ መሆኑ ተገልጧል፡፡ ለምሳሌ፣ ዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ቁጥር 24 እንዲህ ይላል፡

ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም እግዚአብሔር ወስዶታልና። (ዘፍጥረት 5፡24)

በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” ተብሎ የተተረጎመው መግለጫ ሄኖክንና ኖህን ለመግለጥ ብቻ ውሏል፡፡ ሆኖም፣ በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ፣ እስራኤላውያን በያህዌ መንገድ ላይ ልክ እንደ ሄኖክ ሊጓዙ እንደሚገባ ሙሴ እዚህም እዚያም ሲያሳስባቸው እናገኛለን፡፡ በዚህ መንገድ፣ ሙሴን ይከተሉ የነበሩ ታማኝ እስራኤላውያን ከሴት ዘር ጋር የሚቆራኙበትን ሌላ ነጥብ ያሳያቸዋል፡፡ ሄኖክን መምሰል ግባቸው ነበር፡፡

በሴት ዝርያና በእስራኤል መካከል ያለው ሦስተኛው ትስስር የተገለጠው በሴታውያን ቁጥር ላይ ሙሴ በሰጠው አፅንዖት ውስጥ ነው፡፡ ከሴት የትውልድ ሐረግ የምንገነዘበው ቁጥራቸው እጅግ የበዛ መሆኑን ነው፡፡ ሙሴ የሴትን ትውልድ መብዛት የገለጠው “ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ” በሚል ቃል ነው፡፡ እንዲያውም በዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ውስጥ ይህንን ሃሳብ 9 ጊዜ ደጋግሞታል፡፡ ይህ በሴት ትውልድ በቁጥር መብዛት የተሰጠ አፅንዖት ለሙሴ እስራኤላውያን አንባቢዎች ወሳኝ ነው ምክንያቱም በግብፅ ውስጥ ሲኖሩና ሊወጡ ሲሉ እግዚአብሔር በቁጥር እጅግ አብዝቷቸው እንደ ነበር ያውቃሉ፡፡

በአራተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ሙሴ እስራኤልን ከሴት ወገን ጋር ለማስተሳሰር ሲል የሴት ትውልድ ረጃጅም ዕድሜ የኖረ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ፣ የሴት ወገን የሆነው ማቱሳላ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ከተጠቀሱት ሁሉ ረጅሙን ዕድሜ ኖሯል፡፡ በዘፍጥረት 5 ቁጥር 27 እንደተጠቀሰው 969 ዓመታት ኖሯል፡፡ ሌሎችም የሴት ወገኖች እንዲሁ ረጃጅም ዓመታት ኖረዋል፡፡ ሙሴ በሴት ወገን ረጃጅም ዕድሜ ላይ ማትኮሩ አግባብነት አለው ምክንያቱም፣ የሙሴ ህግ እንደሚያመለክተው፣ በተስፋዪቱ ምድር ረጅም ዕድሜ መኖር በእስራኤል ውስጥ ለሚኖሩ ታማኞች ግባቸው ነበርና ነው፡፡ ሙሴ የሴትን ትውልድ ረጃጅም ዕድሜ በመጥቀስ፣ በሴት ትውልድና በእስራኤል መካከል በዚህም ረገድ ትስስር እንዳለ አመልክቷል፡፡

ስለዚህ ሙሴ በፍጥረተ ዓለም ታሪኩ ውስጥ ስለቀደምት ክፋትና የነፃነት ተስፋ የጻፈው ከእርሱ ዘመን ጋር ያለውን ፅኑ ትስስር ለማመልከት ሲል ነው፡፡ ቃየንና የእርሱ ዝርያ በእስራኤል ላይ ክፋትን ካደረጉት ከግብጻውያን ጋር ይያያዛሉ፡፡ አቤል፣ ሴትና የሴት ዝርያ ደግሞ፣ ለግብፃውያን ጥቃት ተጋላጭ ከነበሩት ከእስራኤላውያን ጋር ይገናኛሉ፡፡ እነዚህ ትስስሮች በእርሱ የታሪክ ዘገባ በዚህኛው አንጓ ውስጥ የሙሴ ማእከላዊ ስልቶች ናቸው፡፡

ሙሴ ቀደምት ክፋትንና ተስፋን እንዴት እንደገለጠ ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 8 ወደ ተገለጠው የኋላ ክፋትና የነጻነት ተስፋ እንሸጋገራለን፡፡

የኋላ ክፋትና ተስፋ

በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 4 ሙሴ እነዚህን ሰዎች የገለጠበትን ሁኔታ እንመልከት፡

በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ። (ዘፍጥረት 6፡4)

ኔፍሊሞች ኃያላንና ባስገባሪነታቸው የታወቁ እንደነበሩ አስቀድመን አይተናል፡፡ ሙሴ ግን ስለ ኔፍሊሞች ወሳኝ ሃሳብ እንደሰነዘረ ልብ በሉ፡፡ ኔፍሊሞች በጥንታዊው ዓለም ደግሞም “ከዚያ በኋላም” በምድር ይኖሩ እንደነበር ተናግሯል፡፡

የኔፍሊም ተዋጊዎች፣ ከጥፋት ውሃም በኋላ እንደገና መኖራቸውን በተዘዋዋሪ በመግለጥ፣ እስራኤላውያን አንባቢዎቹ በእነርሱም ዘመን ከኔፍሊሞች ጋር እንደሚጋጠሙ ሙሴ አሳስቧቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኔፍሊም የሚለው ቃል በድጋሚ የሚገኘው በዘኁልቁ ምዕራፍ 13 ቁጥር 32 እና 33 ውስጥ ነው፡፡ በዚያም፣ ሙሴ ወደ ከነዓን ምድር የላካቸው ሰላዮች ኔፍሊሞችን ካዩ በኋላ እንዲህ ብለዋል፡

እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው።

በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ።

የከነዓን ምድር በክፋት የተሞላችና ፈታኝ ምድር እንደሆነች፣ በከነዓን ዘሮችም ውስጥ ከኔፊሊም ወገን የሆኑት፣ ኃያል ጦረኞች እንደነበሩ እና በልባቸው ፍርሃት እንደለቀቁባቸው ታማኝ ያልሆኑት ሰላዮች ተናገሩ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ፣ ይህ ዘገባ ሙሴን የተከተለው የመጀመሪያው ትውልድ ለድል እግዚአብሔር ካቀረበለት ጥሪ ፊቱን እንዲመልስ አድርጎታል፡፡ ይህም የእምነት ማነስ እግዚአብሔርን እጅግ ስላሳዘነው የመጀመሪያው ትውልድ ጨርሶ እስኪያልቅና አዲሱ ትውልድ ለመውረስ እስኪዘጋጅ ድረስ እስራኤል በምድረ-በዳ ይንከራተት ዘንድ ወደ ምድረ-በዳ ሰደዳቸው፡፡

በዚህም መሠረት ሙሴ በዚህ የፍጥረተ ዓለም ታሪኩ አንጓና በእስራኤል ልምምድ መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንደመሠረተ እንገነዘባለን፡፡ እስራኤላውያን አንባቢዎቹ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 የሚገኙትን ጥንታዊ ኔፍሊሞች በከነዓን ከነበሩት አሸባሪ የኔፍሊም ተዋጊዎች ጋር እንዲያነፃፅሩ ይፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 8 የሚገኘው ክፋትና የነፃነት ተስፋ ከነዓንን ሊወርሱ ሲሉ ስለሚጠብቃቸው የክፉ ተግዳሮት በቀጥታ ይናገራል፡፡

በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 የሚገኘውን ክፍል ቀደምት ትርጓሜ ለማግኘት ባደረግነው ምርመራ ከእስራኤል የወቅቱ ልምምድ ጋር ትስስር ያላቸውን ጥንታዊ ገጸ-ባሕርያት ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ ሁለተኛውን ጥያቄ ልናነሳ ይገባናል፡፡ እነዚህ ትስስሮች ወደ ተስፋዪቱ ምድር በሙሴ መሪነት ለሚጓዙት እስራኤላውያን የሚኖራቸው እንድምታ ምን ነበር?

እንድምታዎች

ሙሴ ለእስራኤል ያስተላለፈውን መልዕክት ማዕከላዊ ሃሳብ ለመረዳት፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መሠረታዊ የሆነውን ትዕይንት ማስታወስ ይገባናል፡፡ ከዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ያለው ክፍል ሁለት የክፋትና የነፃነት ተስፋ ትዕይንቶችን ያዘለ መሆኑን ታስታውሳላችሁ፡፡ ከምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 5 ቁጥር 32 ድረስ ያለው በቃየንና በዘሩ ክፋት ላይ ያተኩራል፡፡ ሆኖም፣ ምዕራፍ 5 ቁጥር 29 እና 32 ድነት በእርሱ በኩል እንደሚመጣ ለማመልከት ኖህን ይጠቅሳል፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ ልክ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1 እስከ 8 ያለው ክፍል የኔፍሊምን ዘሮች ክፋት እንደሚዘግበው ሁሉ፣ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ደግሞ እግዚአብሔር ከእነዚህ ፈተናዎች የሚታደግ መሆኑን ለማሳየት ኖህን እንደገና ይጠቅሳል፡፡

ሙሴን ለሚከተሉ እስራኤላውያን፣ እነዚህ ትዕይንቶች የምሥራቾች መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእነርሱ አስቀድሞውኑ ምን እንዳደረገላቸው፣ ደግሞም ምን ሊያደርግላቸው እንደተዘጋጀ ይገልጣሉ፡፡ በአንድ በኩል፣ የእስራኤልን የቀድሞ አባቶች ከከነዓናውያን ለመታደግ እግዚአብሔር ኖህን እንደተጠቀመ ሁሉ፣ እስራኤላውያንን ከግብፅ ለመታደግ ሙሴን ተጠቅሟል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ፣ ከጥንታውያኑ ኔፍሊሞች ነፃ ለማውጣት ኖህን እንደተጠቀመ ሁሉ፣ አሁን ደግሞ እስራኤላውያንን ወደ ከነዓን ሲገቡ ከሚጠብቃቸው ፈተና ለመታደግ ሙሴን ሊጠቀምበት ነው፡፡

እንግዲህ፣ የዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ድረስ ያለውን ክፍል አወቃቀርና ቀደምት ትርጉም ከተመለከትን፣ ወደ መጨረሻው ርእሳችን፣ ዘመነኛው ተዛምዶ መሸጋገር ይገባናል፡፡ ይህ የሙሴ የፍጥረተ-ዓለም ዘገባ አንጓ ከእኛ የአሁን ሕይወት ጋር እንዴት እደሚዛመድ አዲስ ኪዳን የሚያስተምረን ምንድን ነው?

ዘመነኛው ተዛምዶ

በተለመደው አካሄዳችን፣ አዲስ ኪዳን በክርስቶስ መንግሥት ሦስት እርከኖች መሠረት እነዚህን መሪ ሃሳቦች እንዴት እንደሚያብራራቸው እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ ክርስቶስ ወደ ምድር ሲመጣ በተከናወነው የመንግሥቱ ምሥረታ፤ ሁለተኛ በቤተክርስቲያን የታሪክ ዘመናት ሁሉ በቀጠለው የመንግሥቱ መስፋፋት (ዕድገት)፤ ሦስተኛ፣ ክርስቶስ በክብር ሲመለስና አዲስ ሰማይና ምድር ሲያመጣ በሚከናወነው የመንግሥቱ ፍፃሜ ላይ ይሆናል፡፡ እነዚህ የክርስቶስ መንግሥት እርከኖች ሊመረመሩ የሚባቸው ክፋትና ነፃነት በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉባቸውን ምሉዕ ግንዛቤዎች ሊያስጨብጡን በሚችሉ መንገዶች ሊሆን ይገባዋል፡፡ እስኪ አስቀድመን በመንግሥቱ ምሥረታ ወቅት የተከናወነውን ክፋትና የነፃነት ተስፋ እንመልከት፡፡

ምሥረታ

በክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት የተከናወነው የመንግሥቱ ምሥረታ ቢያንስ በሁለት መንዶች በፍጥረተ ዓለም ታሪክ የነበረውን ክፉ ዓለም ያሳስበናል፡፡ በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ በምድር ሲኖር የገጠመውን ክፋት፤ ሁለተኛ፣ ክርስቶስ ለራሱ ሕዝብ ካመጣው ነፃነት ጋር ያለውን ትስስር እናያለን፡፡ አስቀድመን ኢየሱስ በመጀመሪያ መምጣቱ ያለፈበትን መከራ እንመልከት፡፡

ክፋት

ስለ ኢየሱስ ሕይወት እንግዳ ያልሆነ ሰው ኢየሱስ በበርካታ መንዶች ከዓለም መከራን እንደተቀበለ ያውቃል፡፡ የተናቁና የተገፉትን ሲያገለግል፣ ስቃይና ህማማቸውን ይካፈል ነበር፡፡ ሆኖም፣ እንደ አዲስ ኪዳን ዘገባ በክርስቶስ ላይ የተፈፀመው የክፋት ቁንጮ በመስቀል ላይ ሲሞት የተፈፀመበት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በእርሱ ዘመን በውል በሚታወቀው እጅግ የከፋ አሰቃቂ የሞት ፍርድ ውስጥ በማለፍ፣ በጥንታዊው ዓለም ፃድቅ ከሚያልፍበት እግጅ በከፋ ስቃይ ውስጥ ኢየሱስ አልፏል፡፡

በዚህ መሠረት አዲስ ኪዳን የኢየሱስን መከራ ሲገልፅ የእርሱን በመስቀል ላይ መሞት በጥንታዊው ዓለም ከነበረው ክፋት ጋር፣ በተለይም ከአቤል ሞት ጋር ለማነፃፀር መሆኑ አያስገርመንም፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ ክርስቶስ በክፉዎች እጅ ያለ በደሉ መከራን እንደተቀበለ ያውቃል፣ በዚህም ምክንያት፣ በመልዕክቱ በምዕራፍ 12 ከቁጥር 23 እስከ 24 ውስጥ የክርስቶስን ሞት ከአቤል ሞት ጋር ያነፃፅረዋል፡

በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥

የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል። (ዕብ 12፡23-14)

ይህ የሙሴ የፍጥረተ ዓለም ታሪክ ተዘዋዋሪ ዘገባ ግልፅ ነው፡፡ የፈሰሰው የክርስቶስ ደም ከአቤል ደም ይልቅ ትልቅ ቋንቋ አለው፡፡ ይህም ማለት፣ በእግዚአብሔር አይኖች ፊት የክርስቶስ ሞት ከአቤል ሞት ይልቅ እጅግ የከበረ ነው ማለት ነው፡፡ የክርስቶስ ሞት ተራ ክስተት አይደለም፡፡ የእርሱ ሞት የህዝቡን ኃጢአት አስተሰርዮአል ምክንያቱም በእርሱ ያመኑ አማኞች ሁሉ ምትክ ሆኖ ተሰቃይቷልና ነው፡፡ ከዚህም ባሻር ግን፣ የክርስቶስ ሞት የእግዚአብሔርን የጽድቅ ቁጣ ከአቤል ደም ይልቅ አነሳስቶታል፡፡

በዚህ መሠረት፣ በፍጥረተ ዓለም ታሪክ ውስጥ ሙሴ ያሰፈረውን የክፋት ዘገባ ስናነብብ፣ ሙሴ ለእስራኤላውያን ቀደምት ተደራሲያኑ እነዚህን ምዕራፎች ለምን እንደፃፈ ብቻ ማሰብ የለብንም፡፡ ከአዲስ ኪዳናዊው አስተሳሰብ አንፃር፣ በጥንታዊው ዓለም በጻድቃን ላይ የደረሰው ክፋት በመንግሥቱ ምሥረታ ወቅት በክርስቶስ ላይ የሚደርሰውንም መከራ ከርቀት ያመለክታል፡፡

አዲስ ኪዳን በጥንታዊው ዓለም ክፋትና በክርስቶስ መከራ መካከል ያለውን ትስስር እንዴት እንደገለጠው ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ ይህንን የዘፍጥረት ክፍል የመንግሥቱ ምሥረታ የዳሰሰበትን ሁለተኛ መንድ እንመለከታለን፡፡ ነፃ በማውጣቱ ተስፋም ውስጥ ክርስቶስ ለዓለም ካስገኘው ነፃነት ጋር ወሳኝ ትስስር አለ፡፡

ነፃ ማውጣት

ኢየሱስ የአደባባይ አልግሎቱን አብዛኛ ጊዜ ያሳለፈው የተስፋን መልእክት በማወጅ ነው፡፡ ያም ወንጌል ነው፡፡ መልዕክቱም እርሱን ለሚከተሉ ሁሉ አንድ ቀን የመከራ ሕይወት የሚያበቃ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ወንጌል ኢየሱስ የነበረው ቁርጠኝነት በትምህርቶቹ ሁሉ ውስጥ ይገለጣል፡፡ በተራራው ስብከት የመክፈቻ የበረከት ንግግር ውስጥ፣ የነጻ ማውጣቱ መልእክት በብፅዕና መልእክቶችም ውስጥ እንዴት እንደተገለጠ ልብ በሉ፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ከቁጥር 10 እስከ 12 ባለው ክፍል ውስጥ፣ ይህንን ታዋቂ ክፍል ኢየሱስ እንዲህ ሲል ከፍቶታል፡

ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።

ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።

ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። (ማቴዎስ 5፡10-12)

እነዚህ የብፅዕና መልእክቶች እንደሚገልጡት የኢየሱስ የማስተማር አገልግሎት ማዕከላዊ ትኩረቶች ከሆኑት መካከል አንዱ እግዚአብሔር ሕዝቡን የማይጥል የመሆኑን ተስፋ የተሞላ መልእክት ማምጣት ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ቀን ከመከራዎቻቸው ሁሉ ነፃ እንደሚያወጣቸው ተስፋ እንዲያደርጉ ኢየሱስ ተከታዮቹን ያበረታታል፡፡

ኢየሱስ ነጻ የማውጣትን ተስፋ ብቻ አላወጀም ይልቁኑ በሞቱና በትንሣኤው አስቀድሞ ያወጀውን ነፃ የማውጣት ተስፋ ፈፅሞታል፡፡ ኢየሱስ ፍፁም የሆነው የዳዊት ልጅ በመሆኑ ምክንያት፣ ሞቱ የእግዚአብሔርን ህዝብ ኃጢአት አስተሰርዮአል፡፡ የእርሱ ሞት የኃጢአትን ዕዳ ከፍሏል ስለዚህም የእርሱ ተከታዮች ከእንግዲህ ወዲያ የሞት ፍርሃት አይኖርባቸውም፡፡ በዕብራውያን ምዕራፍ 2 ቁጥር 14 አና 15 እንደምናነብበው፣ ኢየሱስ በመሞቱ፡

እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። (ዕብራውያን 2፡14-15)

ስለዚህ የክፋትና የነፃነት ተስፋ መሪ ሃሳቦች በክርስቶስ መንግሥት ምሥረታ ውስጥም ሊዛመዱ እንደሚችሉ አይተናል፡፡ ሙሴ በእስራኤል ላይ የተሰነዘሩ የክፋት ጥቃቶችን እውቅና በመስጠት እግዚአብሔር ግን ከዚያ የማዳን ኃይል እንዳለው ለማስተማር እንደፃፈ ሁሉ፣ አዲስ ኪዳንም ክርስቶስ የመጣው መከራን ሊቀበልና በዓለም ካለው ክፋት ህዝቡን ነፃ ለማውጣት እንደሆነ ይልፃል፡፡

አዲስ ኪዳን የክርስቶስን የመጀመሪያ መምጣት ከፍጥረተ ዓለም ታሪክ ጋር የሚያያይዝባቸውን ጥቂት መንገዶች አይተናል፣ አሁን ደግሞ አዲስ ኪዳን ይህንኑ የፍጥረተ ዓለም ታሪክ ክፍል ከመንግሥቱ እድገት ማለትም በመጀመሪያውና በሁለተኛው የክርስቶስ መምጣት መካከል ካለው ጊዜ ጋር እንዴት እንደሚያዛምደው እንመለከታለን፡፡

እድገት

አዲስ ኪዳን የመንግሥቱ እድገት እንዴት የዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 የተጠቀሱትን መሪ ሃሳቦች እንደሚዳስስ የሚያብራራባቸው ቢያንስ ሁለት መንገዶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህም ማጣቀሻዎች ይህንን የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ከዛሬዋ ቤተክርስቲያን ጋር በምናዛምድበት ወቅት ጠቃሚ መሠረታዊ መርሆ ያስቀምጡልናል፡፡ በአንድ በኩል፣ በእዚአብሔር ህዝብ ላይ ዛሬም ክፋቱ እየቀጠለ እንደሚሄድ እንድንነዘብ አዲስ ኪዳን ያስተምረናል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ፣ ክርስቶስ ከዚያ እንደሚያድነን በማመን በመከራ ውስጥ እንድንፀና ያበረታታናል፡፡ በመጀመሪያ፣ በክርስቶስ ተከታዮች ላይ ክፋት ሊፈፀምባቸው የሚችል የመሆኑን እውነታ መጠበቅ እንደሚገባን እንመልከት፡፡

የክፋት መባባስ

የእርሱ ተከታዮች ከዓለም መከራና ጥላቻ እንደሚመጣባቸው ኢየሱስ ደግሞ ደጋግሞ አስተምሯል፡፡ ሆኖም በማቴዎስ ምዕራፍ 23 ከቁጥር 34 እስከ 35 ውስጥ ግን፣ ኢየሱስ ራሱ የሚደርስበት መከራ በፍጥረተ ዓለም ዘመን ጻድቃን ይደርስባቸው ከነበረው መከራ ጋር ትስስር ያለው የመሆኑን እውነታ አፅንዖት ሰጥቶበታል፡፡ ኢየሱስ ፈሪሳውያንን እንዲህ አላቸው፡

ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤

ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ። (ማቴ 23፡34-35)

የእርሱን ተከታዮች ወደ ዓለም ሲልክ፣ ብርቱ መከራ እንደሚደርስባቸው ኢየሱሱ ተንብዮአል፡፡ ግን ደግሞ ኢየሱስ ይህንን ትንበያውን ከፍጥረተ ዓለም ታሪክ ጋር እንዴት እንዳገናኘው ተመልከቱ፡፡ በእርሱ ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ክፉ ድርጊት ያኔ ቀድሞ ወንድሙ ቃየን ከገደለው ከጻድቁ ከአቤል ደም ጋር ተያያዥነት እንደሚኖረውና ክፋቱም የዚያው ቅጥያ መሆኑን ተናሯል፡፡

የእምነት ማደግ

በመንግሥቱ እድገት ወቅት የክርስቶስ ተከታዮች በመከራ ውስጥ በጽናት ያልፉ እንደነበር ስንገነዘብ፣ እኛም በክርስቶስ ያለንን እምነት የማፅናትን አስፈላጊነትም እንመለከታለን፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንን ጉዳይ በመልእክቱ በምዕራፍ 11 ውስጥ ዳስሶታል፡፡ በምዕራፍ 11 ቁጥር 4 ውስጥ እንዲህ እናነብባለን፡

አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። (ዕብራውያን 11፡4)

የዚህ ምንባብ ዋና መልእክት በየዘመናቱ የሚመጡ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ፣ የአቤልን ተምሳሊት ሊከተሉ ይገባል የሚል ነው፡፡ ምንም እንኳን የአቤል ጽድቅ ከክፉ ወንድሙ መከራ ቢያመጣበትም፣ የአቤል በታማኝነት መፅናት በእኛ ዘመን የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ሊከተሉት የሚገባ ተምሳሊት ይሆንላቸዋል፡፡

በፍጥረተ ዓለም ታሪክ ውስጥ የታዩት የክፋትና የነፃነት መሪ ሃሳቦች በመንግሥቱ እድገትም ወቅት በክርስቶስ ተከታዮች ሕይወትም ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆኑ አይተናል፡፡ በአንድ ወገን፣ በዘመናችን የሚደርስብንን መከራና ተቃውሞ ለመቀበል ዝግጁ ልንሆን ይባናል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ፣ በእነዚህ ፈታኝ ወቅቶች ውስጥ ስናልፍ፣ ክርስቶስ አንድ ቀን ነፃ እንደሚያወጣን በማመን በመፅናት ድል ልናደርግ ይገባናል፡፡

የክፋትና የነፃነት መሪ ሃሳቦች በመንግሥቱ ምሥረታና እድገት ውስጥ እንዴት እንደሚዛመዱ ካየን፣ አሁን ደግሞ ወደ ክርስቶስ መንግሥት የመጨረሻ እርከን፣ ወደ ዳግም ምፅዓቱ እንሸጋገር፡፡

ፍፃሜ

በቀላሉ ለማስቀመጥ፣ ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ በእግዚአብሔር ህዝብ ላይ የሚፈፀመው ክፋት እንደሚያበቃ እና ከዚያም ዘላለማዊ በረከት ወደሚኝባት ዓለም በነፃነት እንደምንባ አዲስ ኪዳን ያስተምረናል፡፡

የክፋት ፍፃሜ

የክፋት ፍፃሜ የአዲስ ኪዳን የነገረ ፍፃሜ ትምህርት ማዕከላዊ መሪ ሃሳብ ነው፡፡ ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ፣ ፍጥረትን እንደና በሙላት ያድሳል፣ ከክፋትም ያነፃዋል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ምዕራፍ 21 ከቁጥር 1 እስከ 5 ውስጥ የክርስቶስን መመለስ የገለጠበትን መንገድ አድምጡ፡

አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም።

ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።

ታላቅም ድምፅ ከሰማይ። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤

እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።

በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም። እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ። (ራእይ 21፡1-5)

የፍፃሜው ነፃነት

የክርስቶስ መንግሥት በፍፃሜው ክፋትን ወደ ፍፃሜ በማምጣት ብቻ አያቆምም፡፡ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ፣ ለህዝቡ ማለቂያ የሌለው ሕይወትንና ሰላምን ያመጣል፡፡ ነፃነታችንም ምሉዕና ፍፁም ይሆናል፡፡ በራእይ ምዕራፍ 22 ቁጥር 1 እና 2 ውስጥ ስለ ፍፃሜ ነጻነታችን እንዲህ ተፅፎ እናነብባለን፡

በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ።

በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ። (ራእይ 22፡1-2)

በክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ወቅት የምናገኘው ይህ የፍፃሜ ነፃነት ተስፋ በጠቅላላው አዲስ ኪዳን ውስጥ ተገልጦ እናገኘዋለን፡፡ የክርስቲያኖችን እምነት የመደምደሚያ እውነታ ይገልጣል፡፡ የአሁኗ ዓለም መከራና ችግር ማለቂያ በሌለው ሕይወት ሰጪ ድንቃ ድንቅ በተሞላች ዓለም የሚለወጥባትን ያቺን ቀን በናፍቆት እንጠባበቃለን፡፡ ስቃይ በደስታ ይተካል፡፡ ትግልም በድል ይዋጣል፡፡ ሞትም በዘላለም ሕይወት ይለወጣል፡፡

ልክ ሙሴ እስራኤልን ለማበረታታትና ወደ ተስፋዪቱ ምድር በፅናት እንዲገስሱ ለማሳሰብ የፍጥረተ ዓለምን ዘመን ክፋት እንደ ጻፈ ሁሉ፣ አዲስ ኪዳንም በፍፃሜው የምናገኛትን ዓለም እንድንናፍቅ ያስተምረናል፡፡ ክርስቶስ ሲመጣ፣ በእርሱ ያመኑ ሁሉ የክፋትን ፍፃሜ ያያሉ፣ በዘላለም የመዳን ምድርም ውስጥ ምሉዕና የከበረ ነፃነትን ይቀዳጃሉ፡፡

ማጠቃለያ

በዚህ ትምህርት በዘፍጥረት ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ድረስ በሚኘው የፍጥረተ ዓለም ዘገባ ውስጥ የተገለጡትን ልዩ ልዩ የጥንታዊ ዓለም የክፋት ገፅታዎች ተመልክተናል፡፡ የዚህን የዘፍጥረት መጽሐፍ ክፍል አወቃቀር እና በእርሱ መሪነት ወደ ከነዓን እየተጓዙ የነበሩ እስራኤላውያንን ለማበረታታ ሙሴ ይህንን እንዴት እንደፃፈም ተመልክተናል፡፡ እኛም እንደ ክርስቲያኖች ይህንን የፍጥረተ ዓለም ታሪክ ክፍል በአዲስ ኪዳናዊ እምነታችን ልናዛምደው እንደሚገባም ተምረናል፡፡

ይህንን የዘፍጥረት መጽሐፍ ክፍል ሙሴ አስቀድሞ ለእስራኤል በምን ዓላማ እንደ ፃፈው ስንመለከት፣ ይህ ክፍል ያለፈ ታሪክ ዘገባ ብቻ ከመሆን የዘለለ ነገር እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ እግዚአብሔር በጥንታዊው ዓለም ነፃ እንዳወጣ፣ ኋላም በሙሴ ዘመን እስራኤልን ነፃ እንዳወጣ ሁሉ፣ እኛንም ክርስቶስ አንድ ቀን ከዚህ ክፉ ዓለም ነፃ እንደሚያወጣን በማመን ተስፋችን ሊለመልም ይገባል፡፡

Continue reading the full transcript