ከተመሳሳይ ተከታታይ ትምህርት 1 ጋር የተያያዘ ቪዲዮ ሲሆን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠይቃል፡- የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የጳውሎስን ሕይወት እውነተኛ ዘገባ ይዟልን? ለምን ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የአይሁድን ሥርዓቶች ተሳትፏል? መጽሐፍ ቅዱስ የማይፈልግባቸውን ወጎች እንዴት መመልከት አለብን? እንደ አድቬንት እና ሊንት ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ወቅቶች ማክበር አለብንን? ለምን ጳውሎስ የሮማዊ ዜጋ እንደመሆኑ መብቱን ለማረጋገጥ ጠበቀ? ለምን ሮም ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ እንዲያስተምር ፈቀደ? ለሁሉም ሰዎች ሁሉ ነገር መሆን ማለት ምን ማለት ነው? የውጭ ባህሎች ጋር መነጋገር አለብን ወይንስ በምናውቀው ባህል ላይ ብቻ መሥራት አለብን? ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች የራሟን ባህል እንዲከተሉ መጠየቅ ያለችበት ጊዜ መቼ ነው? ክርስቲያኖች ለምን መከራ ሊገጥማቸው ይገባል? ለምን ጳውሎስ በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ መከራን ከድል ጋር ማያያዘው? ለጳውሎስ የተሰጡትን የእስራት መልእክቶች ሁሉ ጳውሎስ ራሱ ጽፏቸውን? ለምን የጳውሎስ የፊሌሞን የግል ደብዳቤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ? የእጳውሎስ እስራት የእሱን ክብር አበላሸውም? የጳውሎስ ትምህርት የትኛው ማዕዘን ድንጋይ ዘመናዊው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጣም ይጎድላል? ከክርስቶስ ጋር አንድነት ምንድን ነው እና ለምን አስፈላጊ ነው? የእኛን መልካም ሥራዎች ከማን ሊ উপকር should?
From the transcript
ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1675 ዓ.ም. በቤድፎርድ፣ ኢንግላንድ እውቁ የፒዩሪታን ሰባኪ እና ጸሐፊ ጆን ቡንያን ያለ ፈቃድ በአደባባይ ሲሰብክ በመገኘቱ ተይዞ ለስድስት ወራት በወህኒ ታስሮ ነበር፡፡ ቀደም ብሎም፣ ለዐሥራ ሁለት ዓመታት ታስሮ የነበረ ሲሆን፣ በዚያን ጊዜም በርካታ መጻሕፍትንና በራሪ ጽሑፎችን ጽፎ ነበር፡፡ ስለዚህም ይህኛውን አዲስ እስረኝነት አንደ ታላቅ አሳዛኝ ክስተት ከመቁጠር ይልቅ ብሩኅ ተስፋን ሰንቆ ተተቀበለው፡፡
“ከጽሑፍ ለረጅም ጊዜ ተለያይቼ ነበር፡፡ ምናልባት ይህኛው እስሬ ከእስር ቤትነቱ ይልቅ ዓለምን በክርስቶስ መልእክት የምደርስበት ጽሕፈት ቤቴ ሳይሆንልኝ አይቀርም” ማለቱ ተዘግቧል፡፡
እነዚህ ቃል በቃል የቡንያን ቃሎች ይሁኑም አይሁኑም፣ በዚህች አጭር የእስረኝነት ጊዜው የነበረው አገልግሎት ግን የሚናቅ አልነበረም፡፡ በእንግሊዝኛው የስነ-ጽሁፍ ዓለም አቻ ያልተገኘለትን “የመናኝ ጉዞ” የተሰኘውን በክርስትና ሕይወት ስውር ምስጢራት የታጀበውን መጽሐፍ የጻፈው በእነዚህ ወራት ነበር፡፡
እንግዲህ፣ በእስር ላይ ሆኖ ስለ ክርስቶስ በርካታ ተግባራትን ላከናወነ ሰው ሁላችን አድናቆት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሆኖም ግን የቡንያን ሥራዎች ድንቅ መሆናቸው የመረጋገጡን ያህል፣ የሐዋርያው ጳውሎስ ሥራ ግን እጅግ የላቀ ተግባር ማከናወኑ እርግጥ ነው፡፡ በቂሳርያና በሮም እስር ቤቶች ውስጥ ባሳለፋቸው አራት ዓመታት፣ ከቡንያኑ የመናኝ ጉዞ እጅግ የላቀ ፋይዳ ያላቸውን መልእክቶች ጽፏል፡፡
የጳውሎስ ደብዳቤዎች ከተሰኙት ተከታታይ ትምህርቶቻችን ይህ የመጀመሪያው ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ተከታታይ ትምህርት በተለምዶ “የእስር ቤት ደብዳቤዎች” ተብለው የሚጠሩትን የጳውሎስን ደብዳቤዎች እናጠናለን፡፡ እነዚህም ደብዳቤዎች ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ አገልግሎት ከታሰረባቸው እስር ቤቶች ለተለያዩ አብያተክርስቲያናትና ግለሰቦች የጻፋቸው ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ ይህንን ትምህርት የጳውሎስ መታሰር የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ በዚህ ትምህርት፣ ጳውሎስ ወደ ቆላስይስ፣ ወደ ፊሊሞና፣ ወደ ኤፌሶንና ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ለጻፋቸው ደብዳቤዎች መነሻ የሆኑ ሁኔታዎችን እንዳስሳለን፡፡
በጳውሎስ መታሰር ላይ የሚያጠነጥነው ንግግራችን ሦስት ርዕሰ-ጉዳዮችን ይዳስሳል፡ በመጀመሪያ፣ በቂሳርያ ከዚያም በሮም የጳውሎስን የመታሰር ዳራ እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ፣ በእስረኝነቱ ወቅቶችም ስለነበሩት ተከታታይ የጳውሎስ አገልግሎቶች እንመረምራለን፡፡ በእስር ላይ እያለም አንኳ እንደ ክርስቶስ ሐዋርያ አገልግሎቱን እንዴት እንደቀጠለ እንመለከታለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ በእስር ቤት ደብዳቤዎች መካከል የተገለጠውን ነገረ-መለኮታዊ አንድነት፣ ሁሉም የጋራቸው ባደረጓቸው ዐበይት መሪ ሃሳቦች ላይ በማተኮር እንመለከታለን፡፡
ልናነሳቸው ከምንፈልጋቸው ነገሮች አንዱ ጳውሎስ የቆላስይስን፣ የፊሊሞናን፣ የኤፌሶንን እና የፊልጵስዩስን መልእክቶች ሲጽፍ ታስሮበት ስለነበረው እስር ቤት ምሁራኑ ልዩነቶች ያሉባቸው መሆኑን ነው፡፡ አንዳንዶቹ የጻፈው ከቂሳርያ ነበር ሲሉ፣ ሌሎቹ ግን የጻፈው ከሮም ነበር ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ትምህርት፣ ጳውሎስ የጻፈው ከሮም ሳይሆን አይቀርም የሚለውን መከራከሪያ በመደገፍ እንወያያለን፣ ሆኖም ግን ይህ ጉዳይ ለየትኛዎቹም ትርጓሜዎቻችን ወሳኝነት የለውም፡፡ የሆነ ሆኖ፣ የተከበሩ ምሁራን በዚህ ጉዳይ ስሙም እስካልሆኑ ድረስ፣ በሁለቱም ከተሞች ስላሳለፋቸው ጊዜያት ማብራሪያ እንሰጣለን፡፡
ስለ ጳውሎስ መታሰር የምናደርገው ምርመራ የሚጀምረው ከመታሰሩ ቀደም ብለው የነበሩትን ሁኔታዎች በመዳሰስ ነው፡፡ በመቀጠልም፣ በኢየሩሳሌም በመያዙ ዙሪያ ያሉ ሁኔታዎችን እንመረምራለን፡፡ ከዚያም በቂሳርያ ለመጀመሪያ ጊዜ መታሰሩን እንዳስሳለን፡፡ በመጨረሻም፣ በተከታታይ በሮም የነበረበትን እስር እንመለከታለን፡፡
ከመያዙ አስቀድሞ የነበሩ ሁኔታዎች
በጳውሎስ ሦስተኛ ሚሲዮናዊ ጉዞ ማብቂያ፣ ምናልባትም በ56 ወይም 57 ዓ.ም. አካባቢ፣ ጳውሎስና የጉዞ ባልደረባዎቹ ከትንሿ እስያ ወደ ኢየሩሳሌም አቀኑ፣ መጓጓዣቸውም በቀዳሚነት ጀልባ ነበር፡፡ ዋና ጉዳያቸው በኢየሩሳሌም ለሚገኙና ርሃቡን ተቋቁመው ላለፉ ችግረኛ ክርስቲያኖች እርዳታ ማድረስ ነበር፡፡ በእግረ መንገዳቸውም፣ ወደ ሚሊጢን ጎራ በማለት፣ በአቅራቢያዋ የምትገኘውን የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች አስጠርቶ ጳውሎስ አናግሮ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ወቅት፣ ኢየሩሳሌም ሲደርስ እስራት እንደሚጠብቀው መንፈስ ቅዱስ እንዳስጠነቀቀው ጳውሎስ ገልጦላቸው ነበር፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ከቁጥር 22 እስከ 24 እንዲህ የሚሉ ትንቢታዊ ቃሎቹን እናነባለን፡
አሁንም፣ እነሆ፣ እኔ በመንፈስ ቅዱስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፣ በዚያም የሚገኘኝ ምን እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፣ እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል፡፡ ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ፡፡ (የሐሥ 20፡22-24)
ጳውሎሰ በጎበኛቸው በርካታ ከተሞች ውስጥ፣ ስለ ጳውሎስ እስራት አማኞች ይተነብዩ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን ጳውሎስ ወደዚህ እስራት እንዲሄድ ያደፋፍረው ነበር፡፡ ስለዚህም፣ እነዚህ ትንቢቶች ጳውሎስን ከመንገዱ ሊያስተጓጉሉት ሳይሆን፣ ለሚመጣበት መከራ ዝግጁ ሊያደርጉት የታለሙ ነበሩ፡፡ ጳውሎስ በኢሩሳሌም በርካታ ባላጋራዎች ነበሩት፣ ስለዚህም እዚያ ሲደርስ እንደሚያዝና እንደሚታሰር ያውቅ ነበር፡፡ ሆኖም ደግሞ ይህ መከራ እግዘዚአብሔር ለእርሱ ያዘጋጀው እቅድ አካል እንደሆነም ያውቅ ነበር፡፡
ጳውሎስና ጓደኞቹ፣ ከሚሊጢኒን ተነስተው ወደ ቆስ፣ ከዚያም ወደ ሩድ፣ ከዚያም ወደ ጳጥራ ዘለቁ፡፡ በጳጥራም፣ ቆጵሮስን በስተግራ ትተው ወደ ጢሮስ የሚደርሱበትን መርከብ አገኙ፡፡ በጢሮስም፣ በርካታ አማኞች በኢየሩሳሌም ስለሚጠብቀው መከራ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት ጳውሎስን አስጠንቅቀውት ነበር፡፡ ሆኖም ጳውሎስ አሁንም ወደ ግቡ ለመድረስ ቆርጦ ነበር፡፡
ቡድኑ በጠቅላላ ከጢሮስ ወደ ቶለማይስ፣ ከዚያም የሰማርያ ወደብ ወደሆነችው ወደ ቂሳርያ መጡ፡፡ በጥንታዊው ዓለም ቂሳርያ በሚለው ስም የሚጠሩ በርካታ ከተሞች በመኖራቸው ምክንያት፣ ይህችን ከተማ ከሌሎቹ ለመለየት አንዳንድ ጊዜ “ቂሳርያ ማሪቲማ” ይሏት ነበር፣ ትርጓሜውም “የባህር ዳሯ ቂሳርያ” ማለት ነው፡፡
ጳውሎስ በቂሳርያ ማሪቲማ በነበረ ጊዜም፣ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ማስጠንቀቂያ ደርሶት ነበር፡፡ ሁላችን በምናውቀው ስዕላዊ ድራማ፣ ነቢዩ አጋቦስ የራሱን እጆችና እግሮች እንደትንቢታዊ ምልክትነት በማሰር፣ ጳውሎስ ወደ ኢሩሳሌም ከሄደ እንደሚያዝና እንደሚታሰር ተናግሮ ነበር፡፡ የጳውሎስ ወዳጆች እንዲያዝ ለምን እንዳልፈለጉ መረዳት አያዳግተንም፡፡ የጳውሎስ ደህንነት ጉዳይ አስግቷቸው፣ ደግሞም ክፉ እንዳያገኘው ስለፈለጉ ነበር፡፡ ጳውሎስ ግን ይህን መያዙንና መታሰሩን ወንጌልን ለማስፋት እግዚአብሔር እንዳዘጋጀው ያውቅ ነበር፡፡ የሐዋርያት ሥራ 21 ቁጥር 13 ስናነብብ፣
ጳውሎስ ግን መልሶ፣ … ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቻለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 21፡13)
ጳውሎስ ከፊቱ የሚጠብቀው እስራት “ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም” እንደሆነ አውቋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ የጳውሎስን እስራት ወንጌልን ለማስፋትና ቤተክርስቲያናትን ለማገልገል ይጠቀምበታል ማለት ነው፡፡
እናም ጳውሎስ ከእነዚህ አደጋዎች ጋር በሚጋፈጥበት ወቅት በመንፈስ ቅዱስ እንዲታመን የሚያደርገው በቂ ምክንያት ነበረው፡፡ ቀደም ብሎ፣ በሁለተኛው ሚሲዮናዊ ጉዞው ወቅት፣ መንፈስ ቅዱስ ስለ እርሱ የነበረውን ጥበቃ አስተውሏል፡፡ እንደ ሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 16 ከቁጥር 6 እስከ 10 አገላለጥ፣ ጳውሎስ ወንጌልን በእስያና በቢታኒያ የመስበክ ፍላጎት ነበረው፣ መንፈስ ቅዱስ ግን ከለከለው፡፡ ምንም እንኳን ነገሩ ለጳውሎስ እንግዳ ቢመስልም፣ መንፈስ ቅዱስን ታዝዞ ወደ ትራዖስ ተጓዘ፡፡
በትራዖስም፣ የእግዚአብሔርን እቅድ የሚገልጥለትን ራእይ ጳውሎስ አየ፡ ጳውሎስ ወንጌልን ለመቄዶኒያ ሊሰብክ ይገባው ነበር፡፡ ጳውሎስ በመቄዶኒያ የሰጠው አገልግሎት ፍሬያማ ነበር፡፡ ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስን አልታዘዝ ብሎ በእስያና በቢታኒያ ቢሰብክ ኖሮ በመቄዶኒያ መስበክ ባልቻለም ነበር፡፡ በዚህና በሌሎችም በርካታ ልምዶቹ ምክንያት፣ በኢየሩሳሌም ምንም ይምጣ ምን ጳውሎስ የመንፈስን ምሪት መከተልን ምርጫው አድርጎ ነበር፡፡ ለጳውሎስ እግዚአብሔር እንዲያደርግ የሚፈልገውን ማወቅና መከራውንም አንድ ያልተጠበቀና አስደናቂ ነገር ለማሳካት እንደሚጠቀምበት መታመን በቂው ነበር፡፡
ስለ ወደፊቱ የተገለጠችለት እውቀት ውሱን ብትሆንም፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ላይ ባለው የተደላደለ መተማመን፣ ጳውሎስ ለእስር ራሱን በቁርጠኝነት ሰጥቶ ነበር፡፡ ምናልባትም ወደ 57 ዓ.ም. ገደማ ሦስተኛውን ጉዞውን ወደ ኢየሩሳሌም በማድረግ አጠናቀቀ፡፡ እንደ ሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ቁጥር 16 አገላለጥ፣ በዚያ የደረሰው በበዓለ ሃምሳ ወቅት፣ ማለትም በክረምቱ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡
በኢየሩሳሌም መያዙ
ከጳውሎስ መያዝ አስቀድሞ ስለነበሩት ሁኔታዎች መረጃ አግኝተናል፣ አሁን ደግሞ በኢየሩሳሌም በመያዙ ዙሪያ የነበሩትን ሁኔታዎች መመርመር እንችላለን፡፡ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ከነበሩ ባለሥልጣናት ጋር እንዴት ተጋጨ? ለምንስ ታሰረ?
ጳውሎስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ፣ ምናሶን ከተሰኘ አማኝ ጋር የቆየ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያንም በአግባቡ ተቀብላው ነበር፡፡ በሚቀጥለውም ቀን፣ ጳውሎስ የኢየሱስ ወንድም የሆነውንና በአዲስ ኪዳን የያዕቆብ መልዕክት ተብሎ የተሰየመውን መልእክት የጻፈውን ያዕቆብን ጎበኘ፡፡ የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችም ጳውሎስን ለመገናኘት ተሰበሰቡ፡፡
በሦስተኛው ሚሲዮናዊ ጉዞው የሰበሰበውን ለረሃቡ የተዋጣውን ገንዘብ የሰጣቸውም በዚህ ወቅት ነበር ተብሎ ይገመታል፡፡ ቀደም ካሉት የጳውሎስ መልእክቶች ማለትም ከሮሜ መልእክትና ከ1ኛ እና ከ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክቶቹ እንደምንረዳው የተገኘው ድጋፍ በኢየሩሳሌም የሚገኙ ችግረኞችን ለመርዳት ብቻ ሳይሆን የአይሁድ እና የአህዛብ አማኞችን የማዋሃድ ተልዕኮ እንዲፈጽምም ጳውሎስ ብርቱ ናፍቆት ነበረው፡፡
አይሁድ አማኞች ይህንን ስጦታ ከአህዛብ ሲቀበሉ፣ የሚያቀርቡት ምሥጋና አህዛብን በክርስቶስ እንደ ሙሉ ወንድሞቻቸው እንዲቀበሉ ጉጉት ያሳድርባቸዋል የሚል ተስፋ ጳውሎስ ነበረው፡፡ ሆኖም ግን ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ለድርቁ የተሰበሰበው እርዳታ ስለተሰራጨበት ሁኔታ ምንም ፍንጭ አይሰጠንም፡፡ ይልቁኑ፣ የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ስለ ጳውሎስ አገልግሎት ግድ በተሰኘችባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ አስምሮባቸዋል፡፡ ምናልባትም፣ ይህ የሚያመለክተን ጳውሎስ ተስፋ እንዳደረገው የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ለርሃቡ ስለ ተሰበሰበው መዋጮ ያን ያህልም አድናቆት ያሳየች አትመስልም፡፡
የአህዛብ ክርስቲያኖች ስላሳዩት ልግስና ከመደሰትና የጳውሎስን አገልግሎት ከማመስገን ይልቅ፣ ያዕቆብና ሌሎች ሽማግሌዎች ተረዳድተው ስለ ጳውሎስ ትምህርቶችና ልምምዶች በኢየሩሳሌም ወሬ እንደደረሰ ለጳውሎስ ሲነግሩት እንመለከታለን፡፡ በተለይ ደግሞ፣ አይሁድ ክርስቲያኖች የአይሁድን ወግ ለምሳሌ እንደ መገረዝ ያለውን ጥሰው ከአህዛብ ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት እንዲኖሩ ጳውሎስ አስተምሯል የሚለው ወሬ ተሰምቶ ነበር፡፡ አይሁድ ክርስቲያኖች አይሁዳዊ ወጎችን ሊጠብቁ ይገባቸዋል በማለት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አይሁድ ክርስቲያኖች ያምኑ ነበር፡፡ ከእነዚህም ወሬዎች የተነሳ በአካባቢው ያሉ አይሁድ ክርስቲያኖች ጳውሎስን ይቃወሙት ይሆናል ብለው ያዕቆብና ሽማግሌዎቹ ሰግተው ነበር፡፡
እዚህ ጋ ቆም ብለን ስለ ጳውሎስ ይነገሩ የነበሩ ጉምጉምታዎች የሀሰት ወሬዎች እንደነበሩ ማመልከት ይገባናል፡፡ ጳውሎስ በመልእክቶቹ ሁሉ፣ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት የእግዚአብሔርን የሞራል ህግጋት ዋጋ የሚሰጣቸው መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ አይሁዳውያን በሙሴ ህግጋት ላይ የጨመሩዋቸውን ወጎች እንዲያጣጥሉ አነሳስቶ አያውቅም፡፡ ይልቁኑ፣ እርሱ ራሱም በአይሁዳውያን መካከል በነበረበት ወቅት ትውፊቶቹን ይጠብቅ ነበር፡፡ ሆኖም፣ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ፣ አዲስ ዘመን እንደመጣ አስተምሯል፡፡ በደብዳቤዎቹ ማብራሪያ ሲሰጥም፣ አይሁድም ሆኑ አህዛብ እነዚህን ወጎች የመጠበቅ ግዴታ እንደሌለባቸው አረጋግጧል፡፡ ክርስቲያኖች የአይሁዳውያንን ወጎች በአክብሮት ሊመለከቱ ይገባል፣ ይህንን የሚያደርጉት ግን በማያምኑ አይሁድ መካከል ወንጌልን ለማድረስ በር እንዲያስከፍትላቸው ብቻ ነው፡፡
እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ ያለውን አቋም በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 20 እና 21 ውስጥ እንዴት እንደገለጠው እናዳምጥ፡፡
አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤
ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ሕግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ (1ኛ ቆሮንቶስ 9፡20-21)
ጳውሎስ በአህዛብ መካከል ሲኖር እንደ አህዛብ ለመሆን በፍጹም አያንገራግርም፡፡ ግን ስለ ወንጌል ሲል የአይሁድ ወጎችን መጠበቅም ደስ ያሰኘው ነበር፡፡ እግዚአብሔር በጳውሎስ ላይ በብሉይ ኪዳን የተሰጡትን የአይሁድ ወጎችን የመጠበቅ ግዴታ አልጣለበትም፡፡ በዚህ ስፍራ ጳውሎስ፣ ከእነዚህ ልማዳዊ ድርጊቶች ነፃ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ሆኖም፣ ህጉ በክርስቶስ በኩል ከሚጠብቅበት የሞራል ግዴታዎች ግን ነፃ አልነበረም፡፡ አሁን ክርስቶስ በመምጣቱ የእግዚአብሔር ህግጋት ተግባራዊ ተዛምዶ እንደተለወጠ ጳውሎስ ያምናል፣ ሆኖም ግን አሁንም ስለ ወንጌል ሲባል ትውፊቶቹን መጠበቅ ተቀባይነት አለው፡፡
ይህንን የመሰለው በትልቅ ጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባው አስተምህሮ በቀላሉ በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎም እንደሚችል፣ ወይም አይሁዳውያን እነዚህን ወጎች እንዳይጠብቁ ጳውሎስ እያስተማረ ነው የሚለው ወሬ ለምን እንደተዛመተ መገመት አያስቸግርም፡፡ ያዕቆብና ሽማግሌዎቹ በየትኞቹም ሁኔታዎች ውስጥ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አይሁድ ክርስቲያኖችን ደስ ያሰኛሉ የሚሉዋቸውን የመፍትሄ እርምጃዎች ይወስዱ ነበር፡፡
በተለይ ደግሞ፣ ጳውሎስ ለሙሴ ህግጋት ያለውን ከበሬታ በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ውስጥ በሚፈጸሙት ሥርዓቶች በመሳተፍ አረጋግጧል የሚለውን ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ በተለይ፣ የናዝራዊነትን ቃል ኪዳን የገቡ አራት ሰዎች የመንፃትን ሥርዓት እንዲፈፅሙ እንዲያደርግ በብርቱ አሳስበውታል፡፡ ይህም ጳውሎስ ለህጉ ያለውን ታዛዥነት እና ለአይሁድ ወግ ያለውን መሰጠት ያረጋግጣል፡፡ በተጨማሪም ለአራቱ ናዝራውያን የሚያስፈልገውን ከመንጻት ህግ ጋር የተያያዘ ወጪ እንዲሸፍን ጳውሎስን የጠየቁት ሲሆን፣ ያም የጳውሎስን ጠንካራ ሃይማኖታዊ አቋም ያሳያል፡፡
እንደ አህዛብ ሐዋርያነቱ፣ እነዚህን ተግባራት ሲያከናውን፣ አይሁድ ክርስቲያኖች ስለ እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ አህዛብ ክርስቲያኖችም ያላቸው አመለካከት እንደሚለወጥ ጳውሎስ ያውቃል፡፡ ጳውሎስ ናዝራውያኑን ሲደግፍና ራሱንም ሲያነፃ፣ የአህዛብ ስጦታ ማስገኘት ያልቻለውን በተለይም አህዛብ ክርስቲያኖች በአይሁዳውያኑ ክርስቲያኖች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ይጨምራል የሚል ተስፋም ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ስለዚህ፣ ስለ ክርስቶስ ሲል በተለይ ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ አይሁድና አህዛብ አንድ እንዲሆኑ ያለውን ዓላማ ለማሳካት፣ በዚህ ጉዳይ የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ያስተላለፈችውን ውሳኔ በማክበር የመንፃት ሳምንቱን ጀመረ፡፡
ጳውሎስ የመንፃት ሳምንቱን ሊያጠናቅቅ ሲል፣ በመቅደሱ ውስጠኛ አደባባይ ጊዜ ወስዶ ነበር፡፡ የመቅደሱ አደባባይ የውጪና የውስጠኛ አደባባይ ነበረው፡፡ የውጪው አደባባይ ከውስጠኛው አደባባይ በበር የተለየ ነበር፡፡ የውጪው አደባባይ የአህዛብ አደባባይ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ምክንያቱም ከምድር ሁሉ የተሰበሰቡ ሰዎች ወደዚያ ለመግባት ይፈቀድላቸው ስለነበር ነው፡፡ ሆኖም የውስጠኛው አደባባይ፣ የእስራኤል አደባባይ፣ ለአይሁዳውያን ብቻ የተጠበቀ ነበር፡፡ ወደ እስራኤል አደባባይ የሚገቡ አህዛብ የሞት ፍርድ ይጠብቃቸዋል፡፡
ጳውሎስ በእስራኤላውያን አደባባይ በነበረበት ወቅት፣ በአንዳንድ አይሁዶች ይታይ የነበረው ከትንሿ እስያ እንደመጣ ሰው ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱት የማያምኑ አይሁዳውያን ናቸው እንጂ ከጁዳይዝም ወደ ክርስትና የዞሩት አይደሉም፡፡ ቀደም ብሎም፣ እነዚሁ አይሁዳውያን ጳውሎስን ጥሮፊሞስ ከተባለና ከእርሱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣ ሰው ጋር አይተውት ነበር፡፡ ጥሮፊሞስም ከትንሿ እስያ የሆነ ሰው ነበር፣ እናም በእስያ የሚኖሩ አይሁድ አህዛብ መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስን በእስራኤላውያን አደባባይ ሲመለከቱት፣ ጥሮፊሞስም ወደ አደባባዩ ገብቷል በማለት የተሳሳተ ግምት ገመቱ፣ ታላቅም ቁጣ ተቆጡ፡፡
በዚህም ምክንያት፣ እነዚያ አይሁድ ከተማውን በጠቅላላ በጳውሎስ ላይ አሳደሙ፤ በቁጣ የጦፉ ሰዎችም ሊገድሉት አስበው ከእስራአኤል አደባባይ እየገፈተሩ አስወጡት፡፡ ሆኖም ግን የሮማውያን ጭፍሮች አለቃ ከተማዪቱ በአመፅ እንደጋለች ሲሰማ፣ ረብሻውን ለማረጋጋት ፈጥኖ ሄደ፣ ጳውሎስንም በሰንሰለት አሰረው፣ ወደ ጠባቂዎችም ወሰደው፡፡ ከላውዴዎስ ሊስያስ የተሰኘውም፣ አዛዥ፣ የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ ሲል ጳውሎስን አሳስሮት ነበር፣ ሆኖም ግን ጳውሎስ ሮማዊ መሆኑን ሲረዳ ሊያደርግ ያሰበውን ነገር ተወው፡፡ ጳውሎስ የሮሜ ዜግነት ስላለው፣ በዚህ ዜግነቱ ምክንያት ለየት ያለ የህግ ከለላ የማግኘት መብት ነበረው፣ ይህም መብቱ ያለ ፍርድ በሰንሰለት ያለመታሰርንና ያለመገረፍን መብትም ያካትታል፡፡
በሚቀጥለው ቀን፣ ሊስያስ በእርሱ ላይ የቀረበበትን ክስ ማስረጃ ለማድመጥ፣ ጳውሎስን በአይሁድ ሸንጎ ፊት አቀረበው፡፡ ሆኖም ግን፣ ጥሮፊሞስ ወደ አይሁድ አደባባይ ስለመግባቱ ሊመሰክር የሚችል አንድም ምስክር አለቀረበም፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ በርካታ አይሁዳውያን ለምን የእርሱን አስተምህሮ እንደሚቃወሙ መከላከያውን ለማቅረብ ነፃነት አገኘ፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 23 ከቁጥር 6-8 እንደምናነብበው፡
ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ፦ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ።
ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም ተለያየ።
ሰዱቃውያን፦ ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ። (የሐዋርያት 23፡6-8)
ሰዱቃውያን የሚቃወሙት በፈሪሳዊነቱ እንደሆነ እና የሚሰብከውም ወንጌል ከፈሪሳውያን ትምህርት ጋር በብዙ ነጥቦች እንደሚስማማ ጳውሎስ ተናገረ፡፡ በመሠረቱ፣ ከትንሣኤ አንፃር ስንመለከተው ነገሩ እውነት ነው፡፡ ሰዱቃውያን በሙታን ትንሣኤ አያምኑም፣ ስለዚህም ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚያስተምረውን ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ሊቀበሉት አይችሉም፡፡
ቀደም ባለው ቀን፣ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሣና ለእርሱም በራእይ እንደተገለጠለት ደግሞም የወንጌሉን ምስጢር እንደገለጠለት በቁጣ ግለው ለነበሩት አይሁድ አስረድቶ ነበር፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስ ከሞት የተነሣው ክርስቶስ በገለጠለት ራእይ ላይ ተመስርቶ ለሸንጎው ወንጌልን ሲሰብክ፣ ያነሣው ሃሳብ ከፈሪሳውያን አስተምህሮ ጋር ተጣጥሞለት ነበር፡፡
ጳውሎስ ፈሪሳዊ መሆኑን ሲረዱና፣ ከእነርሱ እምነት ጋር በብዙ መንገዶች የሚስማማ መሆኑን ሲውቁ በሸንጎው ፊት ይሟገቱለት ጀመር፡፡ ሆኖም ግን ሰዱቃውያን ወደ ኋላ አልመለስ በማለታቸው፣ ስብሰባው በእጅጉ ተረበሸ፡፡ ስለዚህም ሉስዮስ ጳውሎስን እንደገና ወደጠባቂዎቹ ወሰደው፡፡
በሚቀጥለውም ቀን፣ ሉስዮስ ጳውሎስን እንደገና ወደ ሸንጎው ለማቅረብና በእርሱ ላይ የሚቀርበውን ክስ ከስረ መሠረቱ ለማጣራት አሰበ፡፡ ሆኖም ግን አርባ የሚሆኑ ቀናተኛ አይሁዶች በመንገድ ላይ አድፍጠው በመጠበቅ ወደ ሸንጎው ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት እንደተማከሩ የጳውሎስ የእህቱ ልጅ ለሉስዮስ አሳሰበው፡፡ ሉስዮስም በብርቱ እንዲጠበቅ አደረገ፡፡ ስለዚህም፣ ወደ ሸንጎው ከመላክ ይልቅ፣ ጳውሎስን ከኢየሩሳሌም አውጥቶ በአቅራቢያዋ ወደምትገኘው ወደ ቂሳርያ ማርቲማ እንዲወሰድ፣ እና በይሁዳ አውራጃ የሮማውያን ገዥ ወደሆነው ወደ ፊሊክስ ዘንድ በደህና እንዲያደርሱት አዘዘ፡፡
ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ከመያዙ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ ትኩረታችንን በቂሳርያ፣ የይሁዳ ገዥ በሆነው በማርቆስ አንቶኒዮስ ፊልክስ ጥበቃ ስር ወደቆየበት እስር እናዞራለን፡፡
በቂሳርያ መታሰሩ
ጳውሎስ በታሰረበት ወቅት፣ በሮማውያን አገዛዝ ስር የነበረው የይሁዳ አውራጃ በደቡብ ይሁዳ ተብሎ የሚጠራውን ክፍል፣ በመካከል ሰማርያን በሰሜን ደግሞ ገሊላን ዋነኞቹ ግዛቶች ያደረገ ነበር፡፡ ቂሳርያ ማርቲማ በሰማርያ ዳርቻ ላይ የምትገኝ እንደነበረች ታስታውሳላችሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሮሜ ግዛት የነበረው የይሁዳ አውራጃ ዋና ከተማም ነበረች፡፡
ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቂሳሪያ ሲደርስ፣ ምናልባት በ57 ዓ.ም. ሊሆን ይችላል፤ ከሳሾቹ ከኢየሩሳሌም እስኪመጡ ድረስ ለአምስት ቀናት በጥበቃ ስር እንዲቆይ ተደረገ፡፡ ከሳሾቹም ሊቀካህኑ ሐናንያ፣ በርካታ የአይሁድ ሽማግሌዎች እና የቡድኑ ጠበቃ የነበረውን ተርቱሊያን የተካተቱበት ነበር፡፡
ከሳሾቹ ሲደርሱም፣ ፊሊክስ ክርክሩን ሊሰማ ተቀመጠ፡፡ በሙግቱም ወቅት፣ ጳውሎስ ብጥብጥ እንዳስነሳና ሰላማቸውን እንዳናጋ መከራከሪያውን አቀረበ፡፡ የእርሱ ሃላፊነት የይሁዳን ሰላም ማስጠበቅ እስከሆነ ድረስ፣ የቀረበው ክስ ለገዢው ለፊሊክስ በጣም ብርቱ ክስ ነበር፡፡ በተለይም ከአይሁዳውያን አመለካከት አንፃር፣ የመቅደሱን ሥርዓት አፍርሷል ብለው በጳውሎስ ላይ ክስ መሥርተው ነበር፡፡ በስፍራው ተገኝተው የነበሩት የአይሁድ ሽማግሌዎች ምንም እንኳን አንዳቸውም ምስክር ነን ብለው ወደፊት ባይቀርቡም ስለ ክሱ ተገቢነት ማረጋገጫ ሰጥተው ነበር፡፡
በግልፅ ይታይ እንደነበረው፣ ስለ ጳውሎስ ይነገር የነበረውን የሐሰት ወሬ በሙሉ ልባቸው አምነው ተቀብለውት ነበር፡፡ ጳውሎስ የጁዳይዝምን ውድቀት ይፈልጋል፣ መቅደሱንም የማርከሱን ተግባር በኩራት እየፈፀመው ነው የሚለውን አቋማቸውን ያጸደቁት ይመስላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት፣ አይሁዳውያን ከሳሾቹ ህጋዊ ምስክር አድርገው ሊጠቅሱ የቻሉት ጳውሎስን ራሱን ነበር!
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 24 ቁጥር 8 ውስጥ ተርቱልያን ለፊሊክስ ያቀረበውን የመዝጊያ ንግግር እናንብብ፡
ከሳሾቹም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ። (የሐዋርያት ሥራ 24፡8)
እንግዲህ ጳውሎስ፣ ጠበቃ አይደለም፣ ለከሳሾቹ የሰጠው ምላሽ ግን ማራኪ ነበር፡፡ ያቀረበውም ባለ አራት ነጥብ መከላከያ ነበር፡
አንደኛ፣ ተፈጸመ ስለሚሉት ወንጀል አንድም ምስክር በእርሱ ላይ በማስረጃነት አለመቅረቡን አመልክቷል፡፡ ይህም ማለት ክሳቸው መሠረት የለሽ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነጥብ ነው ምክንያቱም ጳውሎስ የተከሰሰበት ወንጀል ህዝብ በተሰበሰበበት ወቅት በቀን የሚፈጸም ስለሆነ ነው፡፡ ወንጀሉን ፈጽሞ ቢሆን ኖሮ፣ በእርግጠንነት አንድ ሰው ያየው ነበር፡፡
ሁለተኛ፣ ሰላም ያናጋው እርሱ ሳይሆን ሌሎች እንደሆኑ ትክክለኛ ሙግት አቅርቦ ነበር፡፡ አመፁን የቀሰቀሱት ከትንሿ እስያ የመጡት አይሁድ ነበሩ፡፡ የሮማውያኑን ሰላም ያናጋው ጳውሎስ ሳይሆን አይሁድ ነበሩ፡፡ ይህም ጭብጥ አይሁድ ጳውሎስን ሊገድሉት አሲረው እንደነበር ሉስዮስ በጻፈው የክስ ደብዳቤ ላይ ተረጋግጧል፡፡
ሦስተኛ፣ ራሳቸውን ከሳሾቹን እንኳን በሚያስገርም መንገድ፣ መቅደሱን የማርከስ ሃሳብ ጨርሶውኑ እንደሌለው ጳውሎስ አስረግጦ መናገሩ ነበር፡፡ ይልቁኑ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተጻፈው ሁሉ የሚያምንና ወደ ቤተመቅደስ የመጣውም ለአምልኮ መሆኑን ተናገረ፡፡
አራተኛ፣ የአይሁድ ሸንጎ ጥፋተኛነቱን ሊያረጋግጥ እንዳልቻለ ጳውሎስ ለሸንጎው ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡ ይህ መከራከሪያ የክሱን ሂደት ጨርሶ የሚያወድም ነበር፡፡ በአይሁድ ዘንድ እውቅና የተሰጠው ሸንጎ፣ ማስረጃ ያልቀረበበትን ክስ ማረጋገጥና ጳውሎስን ወንጀለኛ ማድረግ አልቻለም፡፡ ታዲያ አሁንም ሊገድሉት የሚጥሩት ለምን ነበር?
በጳውሎስ ላይ የቀረበው ክስ ማስረጃ የለሽ ስለነበር፣ ፊሊክስ ጳውሎን በነፃ ሊለቅቀው ይችል ነበር፣ ግን አላደረገውም፡፡ ፊሊክስ ግን ሙሰኛ ገዢ ነበር፡፡ ስለዚህም፣ ጉቦ የሚቀበልበትን መንገድ ይፈልግ ጀመር፡፡ ያንንም ለማሳካት ፍርዱን በማጓተት ጳውሎስን ደጋግሞ እያስመጣ ለብቻ ያነጋግረው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን በረቀቀ አሠራሩ ጉዳዩን በዚያ መንገድ ወደፈቃዱ ይመራው ነበር፡፡
በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 24 ቁጥር 26 ውስጥ፣ ሉቃስ እንዲህ ሲል ያብራራዋል፡
ያን ጊዜም ደግሞ እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ (ፊሊክስ) ተስፋ አደረገ፤ ስለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እያስመጣ ያነጋግረው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 24፡26)
በመጀመሪያ፣ የሮሜው ገዥ ሉስዮስ፣ ቂሳርያ በደረሰ ጊዜ፣ በጳውሎስ ጉዳይ ላይ ፍርድ እንደሚሰጥ ፊሊክስ ተናግሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ፊሊክስ በጳውሎስ ጉዳይ ላይ ምንም ብይን ሳይሰጥ ለሁለት ዓመት አዘገየው፡፡
ሁለቱ ዓመታት ሲገባደዱ ግን፣ ፊሊክስ በፊስጦስ ተተካ፡፡ በ59 ዓ.ም. ፊስጦስ በገዢነት ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ፣ በኢየሩሳሌም የሚኖሩት አይሁድ የጳውሎስ ከሳሾች ጳውሎስን ለመግደል ሌላ አጋጣሚ ይፈልጉ ጀመር፡፡ ከዚያም ሴራ ጠነሰሱና ፊስጦስ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲልክላቸውና ጉዳዩም እንደገና በአጥቢያቸው እንዲታይ እንዲፈቅድላቸው ተፈራርመው ላኩ፡፡ እናም፣ ፊስጦስ ጉባዔ ጠራና ጉዳዩ ከቂሳርያ ይልቅ በኢየሩሳሌም እንዲታይ ጳውሎስ ይፈልግ አይፈልግ እንደሆነ ጠየቀው፡፡
በዚህ ወቅትም. ጉዳዩ በኢየሩሳሌም እንዲታይለት ከመስማማት ይልቅ፣ እንደ ሮማዊ ዜግነቱ ጉዳዩ በኔሮ በቄሳር በራሱ እንዲታይለት ጳውሎስ ይግባኝ አለ፤ ፊስጦስም ጥያቄውን ከማጽደቅ ውጪ ምርጫ አልነበረውም፡፡ ጳውሎስ ለምን ይህን ይግባኝ እንደጠየቀ ቅዱሳት መጻሕፍት ምንም ዘገባ አላቀረቡም፣ ምናልባት ግን ጥቂት ፍንጭ ሊሰጡን የሚችሉ ነገሮችን ማስተዋል እንችላለን፡፡
አንደኛ፣ ጳውሎስ ኢየሩሳሌም ለፍርድ ከቀረበ በኋላ ሊለቀቅ የሚችልበት እድል በጣም ጠባብ እንደሆነ አምኗል፡፡ ፊሊክስ ጉዳዩን በፍትሃዊነት ስላልያዘው ለሁለት ዓመታት ያህል በእስር አሳልፏል፡፡ ስለዚህ ፊስጦስ ጉዳዩን ያለ አድልዎ ፍርድ ሊሰጥ የሚችልበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አምኗል፡፡
ሁለተኛ፣ አይሁድ ሊገድሉት እያሴሩ እንደሆነ ጳውሎስ አስቀድሞውኑ ተረድቶ ሊሆን ይችላል፡፡ የጳውሎስ ባልንጀራ የነበረው የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ ሉቃስ፣ ጳውሎስ ከቂሳርያ ወደ ኢሩሳሌም እንዲዛወር ሲፈቀድ አይሁድ ሊገድሉት አሲረው እንደነበር ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህም ጳውሎስም ስለ ሴራው ሊያውቅ እንደሚችል መገመት እንችላለን፡፡
ሦስተኛና ከሁሉ እጅግ ወሳኝ የሆነው፣ ጳውሎስ በሉስዮስ በተያዘበት ወቅት፣ ጌታ ራሱ ለጳውሎስ በህልም ተገልጦለት፣ ወንጌልን በሮም ሊሰብክ እንደሚገባው ነግሮት ነበር፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 23 ቁጥር 11 እንደምናነብበው፡
በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፦ ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው። (የሐዋርያት ሥራ 23፡11)
ጳውሎስ በተያዘበት ወቅት ያየው ይህ ህልም መታሠሩ ስለ ክርስቶስ በሮም ለመስበክ የሚችልበትን እድል በስተመጨረሻው የሚያስገኝለት እንደሚሆን እንዲያስብ አድርጎታል፡፡ እኛም እንደተመለከትነው፣ ይህ መታሠሩ የወንጌል አገልግሎቱን ድንበር ለማስፋት ጌታ የሚጠቀምበት እንደሆነ ጳውሎስ እንዲያምን መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞውኑ ምሪትን ሰጥቶት ነበር፡፡ በዚህም ወቅት፣ ይህ እስራቱ ወደ ሮም የሚሄድበትን በር እንደሚያስከፍትለት ተረድቶ ነበር፡፡
እነዚህ ማስረጃዎች በአንድነት ጳውሎስ ወደ ቄሳር ይግባኝ ያለበትን ትክክለኛ ተነሳስቶ ለማመልከት ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ ተነሳስቶው ምንም ይሁን ምን አንድ ግልፅ ነገር አለ፣ ይህም ከእስር ቤትም እንኳን ቢሆን ጳውሎስ በስተመጨረሻው ወንጌልን በሮም መስበኩ አይቀሬ ነበር፡፡
ጳውሎስ ወደ ሮም ከመላኩ አስቀድሞ ግን፣ ጉዳዩን በወጣቱ ንጉሥ በዳግማዊ ሄሮድስ በአግሪጳ ፊት ቀርቦ የማስረዳት እድል አግኝቶ ነበር፡፡ አግሪጳም የጳውሎስን መከራከሪያ ካደመጠ በኋላ፣ ይህ ሰው ለቄሳር ይግባኝ ባያቀርብ ኖሮ ሊፈታ እንደሚችል ለፊስጦስ ነገረው፡፡
ጌታ ግን ስለ ጳውሎስ ለየት ያለ ሃሳብ ነበረው፡፡ በዚህ ወቅት ለጳውሎስ ለራሱ እንኳን ግልፅ ባልሆኑ ምክንያቶች፣ ጳውሎስ በሮም የሚጠብቀውን እስር የወንጌል አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት ጌታ አስቀድሞውኑ አቅዶት ነበር፡፡
ጳውሎስ በቂሳርያ ያሳለፈበትን የሁለት ዓመታት የእስር ዘመን መርምረናል፣ አሁን ደግሞ፣ በሮሜ በተከታታይ በእስር ላይ የሰነበተባቸውን ዓመታት እንመረምራለን፡፡
በሮም እስር ቤት
ጳውሎስ የሮሜ እስረኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ በሮሜ ወታደሮች ጥበቃ ስር መሆን ነበረበት፡፡ ስለዚህም፣ ዮሊዮስ በተሰኘ የመቶ አለቃ ሥልጣን ስር እንዲሆን ተደረገና ወደ ትንሿ እስያ በምታቀና መርከብ ተሳፈረ፡፡ የጳውሎስ የጉዞ ባልደረቦች ነበሩት ሉቃስና አርስጥሮኮስ አብረውት እንዲሄዱ ተፈቀደላቸው፡፡
መርከቢቱም ወደ ቂሳርያ ጉዞ የጀመረችው፣ ወደ 59 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በመጀመሪያም ወደ የብስ የደረሱት፣ ጳውሎስ ጥቂት ጓደኞቹን እንዲጎበኝ ፈቃድ ባገኘበት በሲዶና ነው፡፡ ከሲዶናም ተነስተው፣ በቆጵሮስ አልፈው፣ በሴሌውቅያ ወደብ በኩል በፓፍልያ አልፈው በሉቅያ ግዛት ወደምትገኘው ወደ ሙራ መጡ፡፡
በሙራም፣ ወደ ኢጣሊያ የምትሄድ መርከብ ላይ ተሳፈሩ፡፡ ከዚህ በኋላ፣ በጣም አስቸጋሪ የመርከብ ጉዞ ገጠማቸው፡፡ መንገዳቸውንም ወደ ቀኒዶስ በማቅናት፣ የደቡቡን አቅጣጫ በመያዝ፣ የቀርጤስን ደሴት ተተግነው በስተመጨረሻም መልካም ወደሚሉዋት ወደብ ደረሱ፡፡
አሁን ደግሞ የክረምት ወራት በመሆኑ፣ አየሩ ለመርከብ ጉዞ እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በመርከብ መጓዝ አደገኛ በመሆኑ ምክንያት የመቶአለቃው ዩልዮስ ወደ ኢጣሊያ ለመጓዝ እንዳይነሱ እንዲያዝዝ ጳውሎስ ምክር ሰጠው፡፡ ጳውሎስ የዳበረ ልምድ ያላቸውን መርከበኞች ሊመክር መነሳቱ እንግዳ ቢመስልም፣ ነገሩ ትንቢታዊ መረዳት ያለበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡25 ተፅፎ እንደምናነብበው ጳውሎስ ከዚህ ቀደሞም ሦስት ጊዜ የመርከብ አደጋ እንደደረሰበት ማስታወስ ይገባል፡፡ ጳውሎስ በሮም ወንጌልን የመስበክ ብርቱ ፍላጎት ነበረው፡፡ በመርከብ እንዳይጓዙ ምክር የሰጠው በሮም የሚጠብቀውን አደጋ ለመሸሽ አስቦ ሳይሆን፣ ሮም በሰላም ደርሶ ወንጌልን ለመስበክ ከነበረው ጠንካራ ፍላጎት የተነሳ ነበር፡፡
የመርከቢቱ አዛዥና ባለቤት ግን መንገዳቸው ሰላምና የተሳካ እንደሚሆን ዩልዮስን አሳመኑት፣ ስለዚህም መርከቢቱ እንደገና ጉዞ ጀመረች፡፡ ሆኖም ብዙ ርቀው ሳይሄዱ፣ በአደገኛ አውሎ ንፋስ ተመቱና ቄዳ ወደሚሏት ወደሜድትራኒያን በህር በርቀት ተሽቀነጠሩ፡፡ ማዕበሉም ለሁለት ሳምንታት ያህል ቆየ፣ በዚህም ወቅት ጳውሎስ በመርከቢቱ ውስጥ የነበሩትን መንገደኞች አገለገላቸው፣ እግዚአብሔርም ተገልጦለት ማንም እንደማይጠፋ ተስፋን እንደሰጠው በመንገር አበረታታቸው፡፡ በስተመጨረሻም መርከቢቱ በመላጥያ ወደብ አቅራቢያ በሚገኝ ዲብ ላይ በመነዳቷ ከኋላዋም ማዕበሉ ስለበረታ ትሰባበር ጀመር፡፡
መርከቢቱም ስለተሰበረች፣ መርከበኞቹ፣ ወታደሮቹ፣ እስረኞቹና በመርቢቱ ውስጥ የነበሩት ሁሉ በመላጥያ ወደብ መቆየት ግዴታ ሆነባቸው፡፡ ጳውሎስ፣ ጓደኞቹና እና ጠባቂዎቹ በሚሊጢን ለሦስት ወራት ተቀመጡ፣ የደሴቲቱም ነዋሪዎች እዚያ በቆዩበት ወቅት ቸርነትን አደረጉላቸው፡፡
ጳውሎስ በመላጥያ በቆየባቸው ወራቶች፣ አስደናቂ ነገሮች ተከናውነዋል፡፡ በአንድ ወገን፣ ጳውሎስ በመርዛማ እባብ ተነድፏል፡፡ የአካባቢው ተወላጆች በመጀመሪያ ላይ ይህንን ሲመለከቱ ጳውሎስን እንደ ነፍሰ ገዳይ ቆጥረውት ነበርና ሞቱን ይጠብቁ ነበር፡፡ ሆኖም ጳውሎስ በእባቡ በመነደፉ ምክንያት ምንም ህመም አልገጠመውም፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ተወላጆቹ ስለ ጳውሎስ የነበራቸውን አስተሳሰብ በመለወጥ ይህስ ከአማልክት አንዱ ሳይሆን አይቀርም ብለው አሰቡ፡፡
እንግዲህ ከሌሎች ቀደምት አውዶች እንደምነገነዘበው የዚያ አካባቢ ተወላጆች ጳውሎስን እንደ አማልክት በማየታቸው እንዲገፉበት እንደማይፈቅድ እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ፣ ጳውሎስን በልስጥራ ሄርሜን የሚል የአማልክት ስም ሲሰጡት፣ ጳውሎስም ተራ ሰው መሆኑን የገለጠ ሲሆን፣ አጋጣሚውን ግን ወንጌልን ለመስበክ ተጠቅሞበታል፡፡ በመላጥያም ሊያደርግ የሚችለው ይህንኑ ነው ብለን ያለምንም ማንገራገር መናገር እንችላለን፡፡
በተጨማሪም ጳውሎስ በመላጥያ በርካታ ተዓምራዊ የፈውስ አገልግሎቶችን ሰጥቷል፡፡ የፈውስ አገልግሎቱን የጀመረው፣ የፑትልዮስን አባት በመፈወስ ነው፡፡ ፑትልዮስ የመላጥያ አዛዥ ነው፡፡ ጳውሎስ የፑትልዮስን አባት የመፈወሱ ወሬ ሲሰማም፣ በመላጥያ የሚገኙ ህመምተኞች ሁሉ ወደ ጳውሎስ በመምጣት ተፈወሱ፡፡
ከሦስት ወራት በኋላም፣ በ60 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ክረምቱ አለፈ፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስና ባልደረቦቹ ደግሞም ጠባቂዎቹ ወደ ኢጣሊያ በመርከብ ጉዟቸውን ጀመሩ፡፡ መላጥያን ለቅቀው፣ ወደ ሰሜን በማቅናት ወደ ሲሲሊ ደሴት ተጓዙ፣ በሰራኩስም ወደብ አረፉ፡፡ ከሰራኩስም የኢጣሊያ ደቡባዊ ዋና ግዛት ወደምትሆን ወደ ሬጌዩም አቀኑ፡፡ ከሬጌዩም ሲነሱም፣ በብርቱ የደቡብ ንፋስ ተነድተው በቶሎ ወደ ፑቲዩሉስ ደረሱ፣ በዚያም በአካባቢው የሚገኙ አማኞች ጳውሎስን ሊጎበኙ መጡ፡፡ ከሳምንት በኋላም፣ ጳውሎስ በመጨረሻ ወደ ሮም ተጓዘ፡፡ ሮም የደረሰውም በ60 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ነበር በዚያም በግዞት ቤት ውስጥ ተቀመጠ፡፡
ጳውሎስም በሮም በግዞት ቤት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ማለትም ከ60 እስከ 62 ዓ.ም. ተቀመጠ፡፡ በእነዚህ ዓመታት በጥበቃ ስር የቆየ ሲሆን፣ እንግዶችን የመቀበልና በነፃነት የማስተማርም ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር፡፡ በይሁዳ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድ መሪዎች ስለ ጳውሎስ ጉዳይ ምንም አልነገሩዋቸው ስለነበር በሮም ይገኙ የነበሩት አይሁድ ራሳቸው ጳውሎስን ጥያቄ አቀረቡለት፡፡ በስብከቱም፣ ጥቂቶቹ ክርስትናን ተቀበሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግን ከብሉይ ኪዳን እየጠቀሰ ስለ ኢየሱስ ያቀርብ የነበረውን መከራከሪያ አንቀበልም አሉ፡፡
ጳውሎስ በሮም ያደረገውን ቆይታ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ 28 በቁጥር 30 እና 31 ውስጥ ጠቅለል አድርጎ አስቀምጦታል፡
ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤
ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 28፡30-31)
ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የደረሰበት እስራት ኢ-ፍትሃዊ፣ ስቃይ የሞላበትና ሕይወቱንም ለአደጋ ያጋለጠ ነበር፡፡ በቂሳርያም የደረሰበት እስር የፍትህ መጓደል የደረሰበትና ረጅም ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡ ወደ ሮም ያደረገውም ጉዞ በርካታ መከራዎች የተፈራረቁበት ነበር፡፡ በስተመጨረሻው ግን የጳውሎስ ተስፋዎች እውን የሆኑ ሲሆን የእግዚአብሔርም ቃል ተፈጽሟል፡፡ ጳውሎስ በፍጻሜው ሮም ደርሷል፡፡ በእርሱ ዘመን ገናናና ኃያል ከተማ በነበረችው ዋና ከተማ ቢታሰርም፣ ለሁለት ዓመታት፣ ወንጌልን “በድፍረትና ያለእንቅፋት” ሰብኮ ነበር፡፡
ተከታታይ አገልግሎት
እስካሁን ድረስ የጳውሎስን እሥራት ዳራ ስንመረምር ቆይተናል፣ አሁን ደግሞ በእስር ላይ ሆኖ የሠጠውን ተከታታይ አገልግሎት እንመረምራለን፡፡ ወደፊት እንደምንመለከተው፣ ጳውሎስ በእስር ላይ ሆኖም እንኳን ሥራ ፈት አልነበረም፡፡ ይልቁኑም፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል አገልጋይ በንቃትና በትጋት ማገልገሉን ገፍቶበት ነበር፡፡
ጳውሎስ ሐዋርያ ነበር፡፡ ጳውሎስን የጠራው፣ ያሰለጠነው እና እንደ መንግሥቱ ባለ ሙሉ ሥልጣን የቃል ኪዳን አምባሳደር እንዲያገለግል የመረጠው ኢየሱስ ራሱ ነበር፡፡ ዛሬ ለእኛ እንግዳ በሚመስል መንገድ፣ ለጳውሎስ የተሰጠው አደራ ሲታሰር እንኳን አልተገታም፡፡ ይልቁኑ በተቃራኒው፣ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ ጳውሎስ ይህኛውን የሕይወቱን ዘመን በእስር ቤት ውስጥ እንዲያሳልፍ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃዱ ነበር፡፡ ድርጊቶቹን በሙሉ እንደፈቃዱ ይቆጣጠር የነበረው እግዚአብሔር ስለነበር በሮም በእስር ላይ ያሳለፋቸው ዓመታት የክርስቶስን ወንጌል የምዕራቡ ዓለም እምብርት በሆነችው ከተማ ውስጥ እንዲሰብክ ምቹ ዕድል ያገኘባቸው ነበሩ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ በእስር ላይ በነበረባቸው ዓመታት ስለሰጣቸው ተከታታይ አገልግሎቶች መረጃ የምናገኝባቸው ሁለት ዐቢይ ምንጮች አሉ፡፡ አንደኛው፣ በዚያን ወቅት ስለተከናወኑት ተግባራት በርካታ መረጃዎችን የሚሰጠን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ጳውሎስ ከእስር ቤት ለአብያተክርስቲያናት ከጻፋቸው የተለያዩ ደብዳቤዎች የምናገኘው መረጃ ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስለ ጳውሎስ አገልግሎት የሚሰጠንን መረጃ በመመርመር እንጀምር፡፡
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ
ለሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ፣ ለሉቃስ የጳውሎስ የእስር ቤት ቆይታዎች እጅግ ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ከተከሰቱት ከእነዚህ ወቅቶች ጋር ተያያዥ የሆኑ ነገሮችን ለመዘገብ ዘጠኝ ምዕራፎችን ያህል ተጠቅሟል፡፡ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የወሰነበትን ከዘገበበት ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 19 ቁጥር 21 ጀምሮ አስከ ሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 28 ቁጥር 31 እንሰከ መጽሐፉ ማብቂያ ድረስ፣ በኢየሩሳሌም ከመያዙ አንስቶ በተከታታይ ስለገጠሙት እስራቶች ሉቃስ ባስቀመጣቸው ዝርዝር መረጃዎች የጳውሎስ እንቅስቃሴ በዓላማ የተሞላ እንደነበር ዘግቧል፡፡
እነዚህ ምዕራፎች በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዙ ቢሆንም፣ ቢያንስ ሦስት ዋና መሪ ሃሳቦች በበርካታ ወቅቶች ተከስተዋል፡ ጳውሎስ ስለሚጠብቀው መከራ አስቀድሞ ማወቁ፣ ስለሚጠብቀው መከራ የእግዚአብሔርን ዓላማ ስለመረዳቱ እና የእግዚአብሔር በረከት ሊፈስስ የሚችለው በመከራው ውስጥ መሆኑን ስለመረዳቱ የተዘገቡት ይጠቀሳሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ ለክርስቶስ የሚያቀርበው አገልግሎት ብርቱ ፈተናን እንደሚያመጣበትና በሕይወቱም መከራ እንደሚጠብቀው ያውቅ ነበር፡፡
መከራ እንሚገጥመው አስቀድሞውኑ ማወቁ
በሐዋርያት ሥራ ከምዕራፍ 19 እስከ 28 ባሉት ምዕራፎች ውስጥ፣ ሉቃስ ጳውሎስን የገለጠው ስለ ሚገጥመው መከራ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ሰው ነው፡፡ ጳውሎስ እንደሚታሰር፣ ለሞትም አልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ያውቅ ነበር፡፡
ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ከቁጥር 22 እስከ 25 ባለው ክፍል ውስጥ ለኤፌሶን መሪዎች ያቀረባቸውንና ቅድመ እውቀት እንዳለው የሚያመለክቱ ንግግሮቹን እናድምጥ፡
አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፦ እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል።
ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።
አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳታዩ አውቃለሁ። (የሐዋርያት ሥራ 20፡22-25)
ቆየት ብሎ ደግሞ በቂሳርያ ለሚኖሩ አማኞች በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 21 ቁጥር 13 እንዲህ ብሏቸው ነበር፡
እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ። (የሐዋርያት ሥራ 21፡13)
ጳውሎስ ስለ ክርስቶስና ስለ እርሱ ወንጌል በሚሰጠው አገልግሎት ውስጥ ስለሚጠብቁት ፈታኝ ሁኔታዎች አስቀድሞውኑ የሚውቅ ከመሆኑ ባሻገር ሕይወቱን መስዋዕት ለማድረግ እንኳን ዝግጁ ነበር፡፡
ዓላማውን በግልጽ መረዳቱ
በሁለተኛ ደረጃ፣ ጳውሎስ የሚቀበለውን መከራ ዓላማ በግልጽ የተረዳ ሰው ነበር፡፡ እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ እንዲያልፍ ያቀደ ከሆነ፣ ጌታ ያንን መከራ ወንጌልን ለማስፋፋት ሊጠቀምበት በአቅዱ ውስጥ አካትቶት ነበር፡፡
የሚያልፍባቸው መከራዎች የክርስቲያንን ወንጌል ለማስፋፋት እግዚአብሔር እንደሚጠቀምበት ጳውሎስ እምነት ነበረው፡፡ የክርስቶስን የማዳን ወንጌል ለህዝብ ሁሉ ለማብሰር ሲባል የትኛውንም ዓይነት መስዋእትነት መክፈል ተገቢ እንደሆነ እና የእግዚአብሔርም መንገድ እንደሆነ ያውቅ ነበር፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ቁጥር 24 ውስጥ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች የተናገረውን እስኪ እንደገና እናድምጠው፡
ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። (የሐዋርያት ሥራ 20፡24)
ጳውሎስ በእስራቱ ወቅት የሚሰጠው አገልግሎት ስለ ወንጌል ምስክር መሆንንም እንደሚያካትትና ሐዋርያ እንደመሆኑም መጠን በመከራ ውስጥ ማለፍ የሚጠበቅበት መሆኑን ጠንቅቆ ተረድቶ ነበር፡፡ እሥራት ለሐዋርያዊ አገልግሎቱ እንቅፋት ከመሆን ይልቅ፣ ለጳውሎስ አገልግሎት ስኬት ትልቅ አስተዋፅዖ ነበረው፡፡
እንዲያውም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ በሌላ ስፍራ፣ እንደምናነብበው፣ በትክክል ሆኖ የምናየው ይኸው ነበር፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 22 ከቁር 1 እስከ 21 ድረስ፣ ጳውሎስ በኢሩሳሌም ሲያዝ፣ ሞቱን ለሚናፍቁ ሴረኞች የክርስቲያን ምስክርነቱን ማቅረብ ችሎ ነበር፡፡
ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 23 ከቁጥር 1 እስከ 10 እንዳብራራው፣ ጳውሎስ በአይሁድ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን በሸንጎው ፊት ቀርቦ ስለ ወንጌልና ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ መስክሯል፡፡ ጌታ ራሱ ተገልጦለት ሐዋርያዊ ምስክርነቱን በተከታታይ ገና እንደሚሰጥ በመንገር እንዳበረታታውም ሉቃስ ዘግቧል፡፡
ከዚያም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 24 ከቁጥር 14 እስከ 26 ድረስ፣ የጳውሎስ ጉዳይ በቂሳርያ ሸንጎ በሚደመጥበት ወቅት በአደባባይ እና ለአገረ ገዢው ለፊሊክስና ለአይሁዳዊት ሚስቱ ለድሩሲላ በግል ወንጌልን አውጇል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ አገረ ገዢው ፊለሊክስ ደግሞ ደጋግሞ ለሁለት ዓመታት ያህል ከጳውሎስ ጋር እንደተነጋገረ ተረድተናል፡፡
ከዚህም በማስከተል፣ በሐዋርያት ሥራ 25 ከቁጥር 18 እስከ ምዕራፍ 26 ቁጥር 29 ድረስ፣ ሉቃስ እንደሚነግረን ጳውሎስ ለአዲሱ አገረ ገዥ ለፊስጦስ፣ ደግሞም ለአይሁዱ ንጉሥ ለአግሪጳ እና ለሚስቱ ለበርኒቄ ወንጌልን አውጇል፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 28 ከቁጥር 23 እስከ 31 እንደተፃፈውም ጳውሎስ ሮም በነበረበት ወቅት እርሱን ሊጎበኙ ለሚመጡት ሁሉ አዘውትሮ ወንጌልን ይሰብክ እንደነበር ሉቃስ ያብራራል፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 23 ቁጥር 11፣ ክርስቶስ ለጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት የጳውሎስን መከራዎች ዓላማ ጠቅለል አድርገው ያስረዱናል፡
በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፦ ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው። (የሐዋርያት ሥራ 23፡11)
ጳውሎስ የኢሱስ ክርስቶስን የምሥራች ወንጌል ከኢሩሳሌም አንስቶ እስከ ሮም ለማድረስ ሲል መከራን ተቀብሏል፡፡
መለኮታዊ በረከቱን በትክክል መረዳቱ
በሦስተኛ ደረጃ፣ ጳውሎስ በእነዚህ ወቅቶች እግዚአብሔር በአገልግሎቱ የሚያፈስሳቸውን በረከቶች በትክክል ተረድቶ ነበር፡፡ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ከምእራፍ 19 እስከ 28 በግልፅ እንደዘገበው የጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ አስደናቂ ተዓምራዊ በረከቶች የታጀበና በየስፍራው የተሰማ ነበር፡፡
ሉቃስ በተጨማሪም እንደዘገበልን ጳውሎስ የወንጌል አገልግሎቱን ያፋጠኑለትን ሌሎች አገልግሎቶችንም እንደሰጠ እና ያንን በሰዎች ሕይወት ውስጥ በተግባር እንዲገለጥ እንዳደረገ እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ፣ በመርከብ ይጓዙ የነበሩ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ ያየ ሲሆን የራእዩንም ፍቺ በትክክል ገልፆ ነበር፡፡ እንደምናስታውሰውም መርከቢቱ ዐለታማ ከሆነው የባህር ጠረፍ ጋር ተላትማ ነበር፡፡ በመላጥያ በርካታ ህሙማንን ፈውሷል፡፡ እርሱን ለመጎብኘት የሚመጡ አማኞች የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ፍላጎትም ያሟላ ነበር፡፡
በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ተጽፎ ከምናነብበው መረጃ በተጨማሪ፣ በጳውሎስ የእስር ዘመን ስለተከናወኑት ተከታታይ አገልግሎቶች ለአብያተ ክርስቲያናት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ማለትም ከቆላስይስ፣ ከኤፌሶን እና ከፊልጵስዩስ ደብዳቤዎቹ የበለጠ መረጃ ማግኘት እንችላለን፡፡ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ ፊሊሞናን፣ ኤፌሶንን እና ፊልጵስዩስን ጨምሮ እንደሚያስረዱን ጳውሎስ በእስር ላይ እያለ የተዋጣለት አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ በታሰረበት ወህኒ ውስጥ የመውጫውን ቀን እየጠበቀ እንዲያው ዝም ብሎ አልተቀመጠም፣ ይልቁኑ በትልቅ ትጋት ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ይፈፅም ነበር፡፡
ለአብያተክርስቲያናት የተጻፉ ደብዳቤዎች
የጳውሎስን አገልግሎት ጠቅለል አድርገን ማቅረብ የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፣ አራት ጉዳዮች ግን ከሁሉ ቀድመው ፊት ለፊታችን ይመጣሉ፡፡ ጳውሎስ ምንም እንኳን በግዞት ቢቀመጥም፣ ለተለያዩ ባለሥልጣናት፣ ሊጎበኙት ለሚመጡ ሰዎች፣ ወንጌልን በመስበክ ያገለግል የነበረ ሲሆን፣ በመላው ዓለም ለሚገኙ አብያተክርስቲያናትና ለአማኞች ይጸልይ፣ ስለ አብያተክርስቲያናትም ጥቅም ሲል መከራን ይቀበል፣ እንዲያውም በተለያዩ ዓለማት ለሚገኙ አብያተክርስቲያናት እና ግለሰቦች ደብዳቤዎችን ይጽፍ ነበር፡፡ በመጀመሪያ፣ በዚህ ወቅት ጳውሎስ ወንጌልን ይሰብክ እንደነበር እንመልከት፡፡
ስብከት
እንደተመለከትነው፣ ጳውሎስ በእስር ቤት የደረሰበትን መከራ የተቋቋመው ወንጌልን የሚሰብክበትን እድል ለማስፋት ሲል ነበር፡፡ ከእስር ቤት የጻፋቸውም ደብዳቤዎች ይህንን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ይህንንም የምንመለከተው ራሱን በሰንሰለት የታሰረ የክርስቶስ አምባሳደር አድርጎ ዘወትር ከሚቆጥርበት መግለጫው ብቻ ሳይሆን የሚጽፍላቸው አብያተክርስቲያናት እንዲጸልዩለት ከሚያቀርባቸው የጸሎት ጥያቄዎችም ውስጥ ነው፡፡
ለምሳሌ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ከቁጥር 19 እስከ 20 ያቀረበውን ልመና አድምጡ፡
ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤
ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ። (ኤፌሶን 6፡19-20)
ጳውሎስ በእስር ላይም እንኳን፣ ተቀዳሚ ሃላፊነቱ ወንጌልን መስበክ እንደሆነ ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህም፣ ሐዋርያዊ ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚችልበትን ብርታት እንዲያገኝ እንዲጸልዩለት ለኤፌሶን ሰዎች ጥያቄውን ያቀርባል፡፡
በተመሳሳይም፣ በቆላስይስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 3 እና 4 ውስጥ እንዲህ ሲል ጽፏል፡
በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤
ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ። (ቆላስይስ 4፡3-4)
ጳውሎስ ዘወትር ከፊት ለፊቱ በሚጠብቁት አጋጣሚዎች ወንጌልን መስበክ ይችል ዘንድ ዘወትር የጸሎት ድጋፍ እንዲደረግለት ይጠይቅ ነበር፡፡
ጸሎት
ሁለተኛ፣ ጳውሎስ ለአብያተክርስቲያናት አዘውትሮ ይጸልይ ነበር፡፡ ከጳውሎስ ደብዳቤዎች እንደምንረዳው፣ አገልግሎቱ ለማያምኑ ሰዎች ወንጌልን ከማድረስም የዘለለ ነበር፡፡ በመላው ዓለም ለሚገኙ አብያተክርስቲያናትና ግለሰቦች በቋሚነት መጸለይንም ያካተተ ነበር፡፡
ተግባራዊ በሆነ መንገድ ስንናገርም፣ የጳውሎስ መታሰር ለጸሎት በርካታ ጊዜ እንዲያገኝ እንዳስቻለው አያጠራጥርም፡፡ ሚሲዮናዊ ጉዞ ያደርግ በነበረበት ወቅት በጉዞ ብዙ ጊዜውን ያሳልፍ ነበር፣ እንዲያውም ለራሱ የሚያስፈልገውን ለማዘጋጀት በትጋት ይሠራ ነበር፡፡ በእስር ቤት ግን፣ ምንም የሚሠራው ሥራ የለውም፣ ወደየትም መጓዝ አይችልም ጣልቃ የሚገቡበትም ነገሮች ውሱን ነበሩ፡፡ ይህም ሁኔታ ለጸሎት ብዙ ጊዜ እንዲኖረው አስችሎታል፡፡ ደብዳቤዎቹ ከሚያቀርቡልን ምስክርነቶች መረዳት እንደምንችለው፣ ለሌሎች ሰዎች የመጸለይን እድል በማግኘቱ ጳውሎስ ራሱን እንደታደለና ትልቅ ክብርን እንዳገኘ አድርጎ ይቆጥራል፡፡
በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 16 እስከ 18 ውስጥ ለሌሎች አማኞች ለመጸለይ ስላገኘው እድል ጳውሎስ የተናገረውን እናዳምጥ፡
ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ።
ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ (ኤፌሶን 1፡16-19)
ጳውሎስ በየቀኑ ሳያቋርጥ ለኤፌሶን ሰዎች ይጸልይ ነበር፡፡ ጸሎት ብርቱ ጉልበት እንዳለው ያምን ነበር፣ ደግሞም እግዚአብሔር ጸሎቱን እንደሚሰማና የኤፌሶንን ሰዎች በመባረክ ለጸሎቱ መልስን እንደሚሰጥ ተስፋ ያደርግ ነበር፡፡ ጳውሎስ በጸሎት ያደርግ የነበረው ተጋድሎ በአጠገቡ በሌሉች ሰዎች ሕይወት ውስጥ ትልቅ መቀጣጠልንና ትጋት ያለበትን አገልግሎት እንዲሰጡ ያነሳሳቸው ነበር፡፡
ተመሳሳይ በሆነ መንገድ፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 3 እስከ 9 ባለው ውስጥ፣ በፊልጵስዩስ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን አዘውትሮ እንደሚጸልይ ገልጧል፡
ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ። … ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። (ፊልጰጵስዩስ 1፡3-9)
በቆላስይስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 9 ላይም በቆላስይስ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን ስላለው መሰጠት እናነብባለን፡
ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ (ቆላስይስ 1፡9)
በተጨማሪም በቆላስይስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ ለአንዳንድ ግለሰቦች ማለትም ለፊሊሞና፣ ለአፊያ እና ለአርቺፐስ ይጸልይ ነበር፡፡ ለምሳሌ በፊልሞና ቁጥር 6 እንዲህ ጽፏል፡
የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ (ፊልሞና 6)
በእነዚህ ሁሉ ምንባቦች እንደተመለከትነው፣ ጳውሎስ ለአማኞች አብዝቶ ይጸልይና በእነርሱም ምትክ ሆኖ የእግዚአብሔር በረከት እንዲፈስላቸው ይናፍቅ ነበር፡፡
መከራ
በሦስተኛ ደረጃ፣ ከመስበክና ከመጸለይ ባሻገር፣ ጳውሎስ በእስር ቤት የነበረው አገልግሎት ስለሌሎች መከራ መቀበልንም ያካትት ነበር፡፡ መከራን በራሱ ከተመለከትነው፣ ፈተና እንጂ አገልግሎት አይደለም፡፡ ሆኖም የመከራው ውጤትና ግብ በወንጌል ስብከት አማካይነት የእግዚአብሔርን መንግሥት ማስፋት እስከ ሆነ ድረስ ግን፣ መከራ እንደ ክርስቲያናዊ አገልግሎት አንዱ ገፅታ ቢወሰድ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው፡፡
ክርስቲያኖች አዘውትረው በመከራ ውስጥ አልፈዋል፣ ኢየሱስ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስም መከራ ይቀበላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን አስረግጦ ይነግረናል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም ክርስቲያኖች አንድ ዓይነት መከራ ይደርስባቸዋል ወይም በጳውሎስ ላይ የደረሰው ሁሉ ይደርስባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ ሥራውን እስኪፈጽም ድረስ፣ መንግሥቱንም በሙላት በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣ ጠላቶቹ አሁንም እርሱን ከመዋጋት አይታቀቡም ስለዚህ እግዚአብሔር ያ እንዲሆን ፈቅዷል፡፡ ይህም ማለት የኢየሱስ ተከታዮች መከራ መቀበላቸው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
የምንቀበለው መከራ በከንቱ እንዳልሆነ ግን፣ የጳውሎስ ሕይወት አንድ ማረጋገጫ ይሰጠናል፡፡ የምንቀበለው መከራ ለቤተክርስቲያን በረከት ነው፡፡ መከራችን የወንጌል ምስክር ነው፣ መከራችን ቤተክርስቲያንን ከክብር ወደ ክብር ያሸጋግራታል፡፡
ስለ ወንጌል መከራን መቀበል ዓላማ ያለውና ጉልበታም አገልግሎት ነው፡፡ አንዱ ነገር፣ ስለ ወንጌል እውነት መከራከሪያ የማይቀርብበት ምስክርነት ነው፡፡ ስለ እምነታቸው ሲሉ የሞቱትን ክርስቲያኖች “ሰማዕታት”ወይም “ምስክሮች” ብለን የምንጠራቸው ለዚህ ነው፡፡ ጳውሎስ የተቀበለው መከራ ወንጌልን የሚሰብክበትን በር እንደከፈተለት በበርካታ መንገዶች ተመልክተናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ሌሎችም ሰዎች ወንጌልን እንዲሰብኩ አበረታትቷቸዋል፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 14 ውስጥ ይህንን ስለመሰለው በጎ ተፅዕኖ ጳውሎስ የጻፈውን እናንብብ፡
በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። (ፊልጵስዩስ 1፡14)
ከዚህም በተጨማሪ፣ መከራን እንደ አገልግሎት መውሰድ ትክክለኛ አስተሳሰብ የሚሆነው ለሌሎች ጥቅምን የሚሰጥ ስለሆነ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው ስለኃጢአተኞች ሲሆን የሞተውም እኛን ለማዳን ነው፡፡ ስለዚህ ስለሌሎች ስንል መከራን በመቀበል የክርስቶስን ፈለግ እንድንከተል ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ እንደ አማኝነታችን፣ ስለሌሎች ጥቅም ስንል መከራን መቀበልን እንዲያውም እስከሞት ድረስ መጽናትን ወድደን ለመቀበል ፈቃደኞች ልንሆን ይገባናል፣ ደግሞም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በመከራ ውስጥ ስላለፉት ቅዱሳን ጌታን ልናመሰግን ይገባናል፡፡
ሐዋርያው ዮሐንስ በ1ኛ ዮሐንስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 16 እንደጻፈው፡
እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። (1ኛ ዮሐንስ 3፡16)
ጳውሎስ በዚህ ያምን ነበር፡፡ እንደተመለከትነውም፣ ወደ እስር ቤት ለመግባት፣ ከዚያም አልፎ ለመሞት እንኳን ፈቃደኛ ነበር፡፡ እኛም እንዲሁ ብናደርግ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ እናደርሳለን፡፡
ስለሌሎች ሲል መከራን ለመቀበል ፈቃደኛ እንደነበር በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ቁጥር 13 ውስጥ እናነብባለን፡
ስለዚህ ስለ እናንተ ስላለ መከራዬ እንዳትታክቱ እለምናችኋለሁ፥ ክብራችሁ ነውና። (ኤፌሶን 3፡13)
ጳውሎስ በዚህ ስፍራ እያመለከተ ያለው እስራቱ ወንጌልን ወደ አዳዲስ ስፍራዎችና ወደ አዳዲስ ህዝቦች ለመውሰድ የሚችልበትን እድል እንዳስገኘለትና ከዚያም የነተሳ በርካታ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለማምጣት እንደረዳው ነው፡፡ ወንጌል ሲስፋፋና ቤተክርስቲያን ስታድግ፣ ቅዱሳን ሊቀበሉት ያለውን ክብር እጅግ ያበዛዋል፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 14፣ ጳውሎስ እንደሚያመለክተውም በመከራ ውስጥ በማለፍ ለሌሎች ያስቀመጠው ምሳሌነት ሌሎችም በምስክርነታቸው እንዲገፉ አበረታትቷቸዋል፡፡
በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። (ፊልጵስዩስ 1፡14)
በሦስተኛ ደረጃ፣ የእርሱ መከራ የክርስቶስ መከራ ቀጣይ ክፍል እንደሆነ የጳውሎስ ደብዳቤዎች ያመለክቱናል፡፡ በቆላስይስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 24 ውስጥ፣ ጳውሎስ መከራዎቹን አስመልክቶ ያለውን ልባዊ ደስታና አቋም ይገልጣል፡
አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። (ቆላስይስ 1፡24)
በቆላስይስ ምዕራፍ 1 ውስጥ ጳውሎስ ክርስቶስ ለሁሉ ነገር ብቁ ስለመሆኑ አስረግጦ ይናገራል፡፡ ስለዚህ፣ በክርስቶስ መከራ “የጎደለውን” ብሎ ሲናገር፣ እኛን ለማዳን የክርስቶስ ሞት ብቁ አይደለም ወይም አማኞች በክርስቶስ ሞት ላይ የራሳቸውን የጽድቅ ሥራ ይጨምሩበታል ማለቱ አይደለም፡፡
ይልቁኑ፣ ጳውሎስ እያለ ያለው፣ የክርስቶስ ሥራ ገና አልተፈፀመም ነው፡፡ ኢየሱስ ሲሞትና ከሞትም ተነሥቶ ወደ ሰማይ ሲያርግ፣ የክፉውን ጭንቅላት ፈርክሶታል፣ በእርሱም አጋንንታዊ ኃይላት ላይ ድልን ተቀዳጅቷል፡፡ ሆኖም ግን ሰይጣንና ጭፍሮቹ በክርስቶስና በመንግሥቱ ላይ ግብግብ መግጠማቸውን እንዳላቆሙ ጳውሎስ ያውቃል፡፡ ኢየሱስ ዳግመኛ በክብር ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ማለትም አሁን ጠላቶቹን ገና ጨርሶ አላጠፋቸውም፡፡
እስከዚያች ቀን ድረስ፣ እግዚአብሔር እንድንቀበል የፈቀደውን መከራ ቤተክርስቲያን ለመቀበል ዝግጁ መሆንና መጽናት ይገባታል፡፡ ኢየሱስ እጅግ አብዝቶ ስለሚወድደን፣ ከአማኞችም ጋር ራሱን ስላስተሳሰረ፣ እኛ መከራ ስንቀበል አብሮን ይቀበላል፡፡ በውልና ተጨባጭ በሆነ መንገድ፣ የቤተክርስቲያን መከራ የክርስቶስ መከራ ነው፡፡
ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ በተለወጠበት ወቅት ኢየሱስ ለጳውሎስ በግልፅ ያስቀመጠለት ነጥብ ይኸው ነበር፡፡ ሳውል በመባል ይታወቅ የነበረው፣ ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖችን አጥብቆ ያሳድድ፣ ወደ ወህኒም ይጥላቸውና ለሞትም አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ሆኖም በደማስቆ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ለማሳሰር ሲሄድ ሳለ ግን፣ ኢየሱስ በመንገዱ ላይ ተገናኘው፣ በመሬትም ላይ ጣለው፣ እውነትንም ገለጠለት፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 9 ቁጥር 5 ላይ በኢየሱስና በጳውሎስ መካከል ከተደረጉት ንግግሮች መሃል ከፊሉ ተዘግቧል፡
ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ (የሐዋርያት ሥራ 9፡5)
አማኞችን ማሳደድ ማለት ኢየሱስን ራሱን ማሳደድ ማለት እንደሆነ ኢየሱስ ለጳውሎስ በግልጽ አስቀምጦለታል፡፡ ስለዚህም፣ አማኞች መከራ ሲቀበሉ፣ ኢየሱስም አብሮ መከራ ይቀበላል፡፡
ስናጠቃልለውም፣ ክርስቶስ ዳግመኛ እስኪመለስ ድረስ መከራን ሊቀበል ይገባዋል፣ መከራውንም የሚቀበለው አካሉ በሆነችው፣ በቤተክርስቲያን በኩል ነው፡፡ የመከራው ዘመን ሲፈጸም ግን፣ ጠላቶቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድል ያደርጋል፣ ቤተክርስቲያኑንም ያከብራል፡፡ ጳውሎስም ክርስቶስ መከራውን በእርሱ አማካይነት እንዲፈፅም የሚያደርግበትን እድል አግኝቷል፡፡
የጳውሎስ ደብዳቤዎች፣ ጳውሎስ እንደ ሐዋርያነቱ በእስር ላይ በነበረባቸው ዓመታት ወንጌልን ስለመስበኩ፣ ስለመጸለዩና መከራን ስለመቀበሉ ከማመልከታቸውም በተጨማሪ በጽሑፍ አገልግሎት በጣም የተወጠረ እንደነበርም ያስረዱናል፡፡
ደብዳቤ
ጳውሎስ በእስር ላይ በነበረባቸው ዓመታት የነበረው የጽሁፍ አገልግሎቱ ለቆላስይስ፣ ለኤፌሶን፣ እና ለፊልጵስዩስ አብያተክርስቲያናትና ከቆላስይስ ለነበረው ለፊልሞና በጻፋቸው ደብዳቤዎች አማካይነት በአዲስ ኪዳን ተቀምጦልናል፡፡ ጳውሎስ በእነዚህ ደብዳቤዎቹ አማካይነት ለአብያተክርስቲያናትና ለግለሰቦች አግባብነት ያለውን የመጋቢነት አገልግሎት መስጠት ችሎ ነበር፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተመዝግበው ለእኛ ተጠብቀው እስከዘለቁ ድረስ፣ የጳውሎስም አገልግሎት ላለፉት ሁለት ዓመታት በመላው ዓለም በስፋት ተዳርሷል ማለት ነው፡፡
የጳውሎስ ደብዳቤዎች ከእርሱ ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነትና ትስስር ለነበራቸው አብያተክርስቲያናትና ግለሰቦች የበለጸገ አገልግሎት ስለመስጠቱ ያወሱናል፡፡ በእነርሱ ዙሪያ እየተከናወኑ ስላሉት በርካታ ጉዳዮች እና ስለ ግለሰቦቹም በግል ያውቅ ነበር፡፡ ይህም እውቀቱ፣ ተደራሲያኑን በግል ይፈታተኑዋቸው ለነበሩ ጉዳዮችና ነገረ-መለኮታዊ ግንዛቤዎች ትምህርት መስጠት እንዲችል ረድቶታል፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ባይችልም፣ ጳውሎስ ለሚጽፍላቸው ሰዎች ይሰጥ የነበረው አገልግሎት በበቂ መረጃ የተደገፈና ለአብያተክርስቲያናቱና ለግለሰቦቹ ወቅታዊ ሁኔታዎች መፍትሄ በሚሰጥ መንገድ የተቀነባበረና የተዋጣለት ነበር፡፡
ለምሳሌ፣ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ውስጥ፣ ሲንጤኪንና ኤዎድያን እርስ በርስ እንዲስማሙ በመምከር የእረኝነት አገልግሎት በመስጠቱ ውስጥ በቀጥታ ይሳተፍ እንደነበር መመልከት እንችላለን፡፡ እነዚህ ሴቶች፣ ጳውሎስ ያውቃቸው የነበሩ፣ ከእርሱም ጋር በአገልግሎት ተጠምደው የነበሩ፣ አሁን ግን እርስ በርስ መስማማት ያቃታቸው ነበሩ፡፡ ለጳውሎስ የእነዚህ ሴቶች ጉዳይ በግሉ ያሳስበው የነበረ፣ ከፍቅር የመነጨ እና ለችግራቸው ያቀረበው መፍትሄ እጅግ የሚወደድ ነበር፡፡
ስለ እነርሱ የጻፈውን በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 2 ውስጥ እንዲህ እናነብበዋለን፡
በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። (ፊልጵስዩስ 4፡2)
ተመሳሳይ በሆነ መንገድም፣ በፊልሞና መጽሐፍ ውስጥ እንደምናነብበው፣ በአማኞች መካከል እርቅ እንዲወርድ ጳውሎስ ሲመክር እናገኘዋለን፡፡ አናሲሞስ ስለሚባልና ከቆላስይሱ ጌታው ከፊልሞና በኮበለለው ባሪያ ምትክ አማላጅ ሆኖ ሲለምን እናገኘዋለን፡፡ እንዲያውም፣ የፊልሞና መጽሐፍ ፊልሞና ለአናሲሞስ ደግነትን እንዲያሳየው በመማጸን ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ነው፡፡
አናሲሞስ በግልጽ ከጌታው ከኮበለለ በኋላ፣ የአናሲሞስ ወዳጅ የሆነውን ጳውሎስን ይልግ ጀመር፡፡ እናም በጳውሎስ አገልግሎት፣ አናሲሞስ ክርስቲያን ሆነ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ አናሲሞስ ከጳውሎስ ጋር በመቀመጥ ጳውሎስን በእስር ዘመኑ ያገለግለው ነበር፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስ ለአናሲሞስና ለፊልሞና የሰጠው አገልግሎት በቅርብ ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ እንደ መጋቢያቸውና እንደ ወዳጃቸው፣ እንቅፋት ገጥሞት የነበረው ግንኙነታቸው እንዲስተካከል በብርቱ ይጥር ነበር፡፡
ጳውሎስ በተጨማሪም ቤተክርስቲያን በጠቅላላው ይገጥሟት የነበሩትን ነገረ-መለኮታዊ ጉዳዮች አስመልክቶ በደብዳቤዎቹ አማካይነት በሐዋርያዊ ሥልጣኑና በእረኝነት በትሩ መመሪያዎችን ይሰጥ ነበር፡፡ እንደ ክርስቶስ ባለሙሉሥልጣን ወኪል በመታሰሩ ምክንያት የማስተማር አገልግሎቱ አልተደናቀፈም ነበር፡፡ ይልቁኑ፣ ጳውሎስ በዚህን ወቅት በደብዳቤዎቹ አማካይነት የማይሻሩ እውነቶችን ይገልጥ ደግሞም እውነቶቹ በቤተክርስቲያን ውስጥ በተግባር እንዲገለጡ ያደርግ ነበር፡፡
የሐዋርያት ሥራንና የጳውሎስን የአዲስ ኪዳን ደብዳቤዎች እንደተመለከትናቸው፣ ጳውሎስ በእስር ላይ በነበረባቸው ዓመታት በአገልግሎት በብርቱ ተጠምዶ እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ እስራቱ ለአገልግሎቱ እንቅፋት እንደሚሆንበት በማሰብ ተስፋ በመቁረጥ አገልግሎቱን እርግፍ አድርጎ አልተወም፡፡ ይልቁኑ፣ በእሥራቱ እግዚአብሔር ወንጌልን መስበክ የሚችልበትን ግሩም በር እንደሚከፍትለት ደግሞም ለቅዱሳን ጽኑ ተምሳሊት እንደሚሆንበት ያምን ነበር፡፡ በዚህ እውቀቱም በመነቃቃት፣ የስብከት፣ የጸሎት፣ የመከራና የጽሑፍ አገልግሎቱን እጅግ ወደላቀ ደረጃ በማሳደግ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሚጠበቅበትን አደራ ሁሉ በታማኝነት ተወጥቷል፡፡
ነገረ-መለኮታዊ አንድነት
እስካሁን በተመለከትናቸው ክፍሎች ስለ ጳውሎስ እስራትና በእስር ላይ እያለ ስለሰጣቸው ተከታታይ አገልግሎቶች ተረድተናል፣ አሁን ደግሞ እስር ቤት ሆኖ ስለጻፋቸው ደብዳቤዎች መለኮታዊ አንድነት እንመለከታለን፡፡ በዚህ ክፍል፣ የእስር ቤት ደብዳቤዎቹ የሚጋሩዋቸውን አስተምህሮአዊ መሪ ሃሳቦች እንመረምራለን ደግሞም ከጳውሎስ ሰፋ ያለ ነገረ-መለኮታዊ አወቃቀር ጋር እንዴት እንደሚጣጣሙም እናብራራለን፡፡
የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች የሚጋሩዋቸው ወሳኝ አስትምህሮአዊ መሠረቶች አሉዋቸው፡፡ ከሁሉ የሚቀድመው ደግሞ፣ ሁሉም አንዱን ወንጌል የሚያጸኑ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ግን፣ ሁሉም ወንጌሉን የጋራቸው በሆነ መንገድ ያቀርባሉ ደግሞም ተመሳሳይ በሆኑ የወንጌል ገጽታዎች ላይ አጽንዖት ወደ መስጠቱ ያደላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም ፍፁም አንድ ዓይነቶች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሁሉን የሚያያይዛቸው አንድ ትልቅ ምስል፣ ሁሉም የሚታመኑበት አንድ የወል መሠረት አለ ለማለት ነው፡፡ ያም የጋራ መሠረታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ድል የነሣና የፍጥረታት ሁሉ ገዢ ነው የሚለው እውነታ ነው፡፡
በጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች ነገረ-መለኮታዊ አንድነት ላይ የምናደርገው ውይይት በሦስት ዋና አስተምህሮዎች ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ አንደኛ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ንጉሥ ነው የሚለውን አስተምህሮ እንመለከታለን፡ ሁለተኛ፣ በኢየሱስ የፍጥረት ንጉሥነት አንፃር ትኩረት ሰጥተን የምንመለከተው አንድ መገለጫ አለ ይህም በክርስቶስ ንግሥና ውስጥ አማኞች ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን አንድነት የምንመለከትበት ነው፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ከላይ የተመለከትናቸው ሁለቱ አስተምህሮዎች እንድንኖር በሚጠይቁት ሥነ-ምግባራዊ አኗኗር ላይ እናተኩራለን፡፡ እስኪ አስቀድመን ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ንጉሥ በሚለው አስተምህሮ እንጀምር፡፡
የፍጥረት ንጉሥ
ጳውሎስ በክርስቶስ የፍጥረት ንጉሥነት አንፃር የሰጠው አፅንኦት ከሌሎቹ ጽሑፎቹ ይልቅ ይበልጥ የተንጸባረቀው በእስር ቤት ደብዳቤዎቹ ውስጥ ነው፡፡ ስለ ክርስቶስ ንግሥና በእስር ቤት ደብዳቤዎቹ ውስጥ በተደጋጋሚ በተገለጡት ሦስት ዋና ዋና ገፅታዎች ላይ እናተኩራለን፡፡ እነርሱም፣ ኃይሉንና ሥልጣኑን አካትቶ የያዘው ሉዓላዊነቱ፤ ግርማዊነትን የተላበሰው ክብሩ እና ሊከበር፣ ሊልቅና ሊገንን ደግሞም ሊከበር የተገባው መሆኑ፤ መንግሥቱንም በምድር ላይ ለማምጣት ዳግመኛ ተመልሶ ለመምጣት ያለው ቁርጠኝነት ናቸው፡፡ አስቀድመን የክርስቶስን ንጉሣዊ ሉዓላዊነት በመመልከት እንጀምር፡፡
ሉዓላዊነት
ክርስቶስ ሉዓላዊ ነው ስንል፣ እርሱ ፈቃዱን ለመፈፀም የሚያስችል ብርታትና ኃይል አለው፣ ያንንም ለማድረግ ህጋዊ ሥልጣንና መብት አለው ማለታችን ነው፡፡ በጥንታዊው ዓለም፣ ነገሥታት በአገራቸው የሚገኙትን የጦር ሠራዊቶች ያዝዛሉ፣ የፈለጉትን ነገር የሚያስፈፅሙበትንም ኃይል ያስታጥቃሉ፡፡ በየአገሮቻቸው የሚወጡ ህግጋትም ለእነርሱ የመግዛትና የማስተዳደር ሥልጣን እውቅና ይሰጣሉ፣ ማለትም እነርሱም የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉበት ሥልጣን አላቸው ማለት ነው፡፡ በርካታ በዘመናችን ያሉ መንግሥታትም ተመሳሳይ ኃይልና ሥልጣን አላቸው፡፡
እንደ ጳውሎስ አገላለጥ፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ፣ እግዚአብሔር አብ በፍጥረታት ሁሉ ላይ ሉዓላዊ የሚሆንበትን ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ አሁን ኢየሱስ፣ ፍፁም ኃያል እና ፍፁም ባለሥልጣን ነው፡፡ ሉዓላዊነቱም በምድርም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም በሚገኙ በሌሎች ነገሥታትና ገዢዎችም ላይ ይሠራል፡፡
በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 20 እስከ 22 ውስጥ፣ አብ ለክርስቶስ የሰጠውን ሉዓላዊነት ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይገልጠዋል፡
ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤
ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።
(ኤፌሶን 1፡20-22)
አሁን በዚህ ጊዜ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍፁም ኃይል ፍጥረታትን በጠቅላላ እየገዛ ነው፡፡ ሉዓላዊነቱም በሰማያዊ ስፍራ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ምድርንም ይገዛል፡፡
በማቴዎስ 28 ቁጥር 18 ውስጥ ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ሲል አውጇል፡፡
ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፡፡ (ማቴዎስ 28፡18)
ጌታችንና አዳኛችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ፍጥረታትን ሁሉ ይገዛል፣ አገዛዙም እጅግ ሩቅ ከሆነው ጋላክሲ አንስቶ በምድር ውስጥ እስከሚገኙት ደቂቃን ድረስ ባሉት ላይ ይገለጣል፡፡ በምድር ገዢዎችና ነገሥታት፣ በመላእክትና በአጋንንት ሁሉ ላይ ገዢ ነው፡፡ በፍጥረት ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ግን በሚፈለገው መጠን እርሱን አይታዘዝም፡፡ ይህም ሆኖ ግን፣ እንዲታዘዙት የማዘዝ እና የማስፈፀም መብትና ኃይልም አለው፡፡ የሚቀበሉትን ሁሉ ለመባረክ ደግሞም ጠላቶቹን ለመደምሰስ የሚያስችል ማለቂያ የሌለው ኃይልና መብት አለው፡፡
ጳውሎስ በክርስቶስ ሉዓላዊነት ላይ አፅንኦት ከመስጠቱ ባሻገር፣ ግርማውንና እሴቶቹን ወዳካተተው ወደ ክርስቶስ ክብር የሰዎችን ትኩረት ይስባል ለዚያም ተገቢ የሆነው አክብሮት፣ ገናንነትና አምልኮ እንዲቀርብለት ያሳስባል፡፡
ክብር
ክርስቶስ ፍፁም፣ ቅዱስና ጻድቅ ስለሆነ የከበረ ነው፡፡ ደግሞም እርሱ ከሥልጣን ሁሉ በላይ የሆነውን ሥልጣን ስለያዘና ያንንም ሥልጣን ያለ አድልዎና በጽድቅ ስለሚጠቀምበት የከበረ ነው፡፡ እርሱ በተጨማሪም ከፍጥረታት ሁሉ እጅግ የሚልቅ ደግሞም እግዚአብሔር ከሁሉ ይልቅ እጅግ ከፍ ከፍ ያደረገው አምላክ ስለሆነ እጅግ የከበረ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር እርሱ የፍጥረተ-ዓለሙ ሁሉ ፈጣሪና ጠባቂ ስለሆነም ክቡር ነው፡፡ ኢየሱስ ክብር የሚገባው መሆኑን የሚያረጋግጡልንን በመቶዎች የሚቆጠሩ ምክንያቶችን በቀላሉ መዘርዘር እንችላለን፡፡ ኢየሱስ ክብርንና ምሥጋናን ሊቀበል የተገባው የሚሆንበት ከሁሉ የላቀው ምክንያት ግን እርሱ መለኮት ደግሞም አምላክ ስለሆነ ከሁሉ የላቀውን ክብር ሊቀበል የተገባው መሆኑ ነው፡፡
ጳውሎስ የኢየሱስን ክብር እጅግ ከፍ አድርጎ የገለጠበት አንዱ ምክንያት በቤተክርስቲያን ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ምን ያህል የተለየ አምላክ እንደሆነ በማሰብ እምብዛም አክብሮት ስለማይሰጡት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የስህተት አስተማሪዎች የመላእክትን እና የመናፍስትን አምልኮ በቤተክርስቲያን ውስጥ በግልፅ እያስፋፉ ስነበረ እና ኢየሱስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነው የሚል አስተምህሮ እያዛመቱ ነበር፡፡ ጳውሎስ ይህንን የስህተት አስተምህሮ ከተጋፈጠበት አንዱ መንገድ የክርስቶስን እጅግ የተለየና አስገራሚ ታላቅነት አፅንዖት መስጠት ነው፡፡
እስኪ በቆላስይስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 16 እስከ 17 የክርስቶስን ማንነት ከመንፈሳዊ ኃላት ጋር ያነጻጸረበትን መንገድ እናዳምጥ፡
እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤
እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። (ቆላስይስ 1፡16-17)
ኢየሱስ እርሱ አምሳያ የሌለው ነው ምክንያቱም መላእክትን እና የሐሰት አስተማሪዎች የሚያመልኳቸውን መናፍስት ሳይቀር የፈጠራቸው እርሱ በመሆኑ ነው፡፡ ኢየሱስ በፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ ካሉት ገዚዎች የሚልቅ ገዢ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም ባሻገር በመንፈሳዊው ዓለምም ሆነ በምድር ላይ ያሉትን ዝቅተኞቹን የሥልጣን መዋቅሮች ሁሉ የዘረጋቸው እርሱ ነው፡፡ በተጨማሪም ሌሎችንም ግዛቶች ማለትም ምድርን የሚገዙትንም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም የሚገዙትን መላእክትንና አጋንንቶችንም የፈጠራቸው እርሱ ነው፡፡
ጳውሎስ የክርስቶስን ንግሥና ከሉዓላዊነቱና ከክብሩ አንፃር ከማመልከቱም ባሻገር፣ መንግሥቱን በሙላት ለመግለጥ ዳግመኛ ተመልሶ ለመምጣት ስላለውም ቁርጠኝነት ያወሳል፡፡
ቁርጠኝነት
ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት ያለውን አመለካከት በትክክል ለመረዳት፣ ስለ ነገረ ፍፃሜ (eschatology) ያለው አስተምህሮ የመነጨው አይሁድ ከሚያራምዱት የነገረ ፍፃሜ ትውፊት እንደሆነ ማስታወስ ይገባናል፡፡ በጳውሎስ ዘመን ይቀነቀን በነበረው የአይሁድ ትውፊታዊ ነገረ-መለኮት ውስጥ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት የሰውን ዘር ዕድሜ በሁለት ዋና ክፍሎች ይከፍሉታል የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ ክርስቶስ ከመምጣቱ አስቀድሞ፣ ዓለም የአሁኑ ዘመን ተብሎ በሚጠራውና መለያውም ኃጢአት፣ ሞትና ርኩሰት በሆነው ዘመን ውስጥ ነበረች፡፡
የአሁኑ ዘመን የሚመጣውን ዘመን ያስከትላል፣ መጽሐፍ ቅዱስም ያንን ዘመን የእግዚአብሔር መንግሥት እና መንግሥተ ሰማያት በማለት ይጠራዋል፡፡ ይህም መተካካት መሲሁ ወይም ክርስቶስ ሲመጣ በአንድ ጊዜ ይከናወናል ይላሉ፡፡
ሆኖም እንደ ጳውሎስን እንደተቀሩትም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች አገላለጥ ግን፣ ይህ የአይሁዳውያን ትውፊታዊ አመለካከት ሙሉ በሙሉ ትክክል አለመሆኑን ክርስቶስ ገልጦአል፡፡ አዎን የሚመጣው ዘመን የአሁኑን ዘመን ይተካል፣ ሆኖም ግን ሁሉም በአንድ ጊዜ አይከናወንም፡፡ ይልቁኑ ሁለቱም ዘመናት፣ የተራራቁ የዘመን ልዩነቶች አሉዋቸው፡፡ ይህም በክርስቶስ ምድራዊ የአገልግሎት ዘመን ጅማሬው ይሆንና፣ እኛ የእግዚአብሔር መንግሥት በይፋ የታወጀበት ብለን ከምንጠራው ጊዜ አንስቶ እስከ ክርስቶስ ዳግመኛ መመለስ ማለትም እስከ እግዚአብሔር መንግሥት ሙላት ድረስ ያለውን ዘመን በማካተት ይከናወናሉ፡፡ መንግሥቱ በይፋ በታወጀበትና ወደሙላት በሚመጣበት ዘመን መካከል ያለውን ጊዜ የእግዚአብሔር መንግሥት የመስፋፋት ዘመን እንለዋለን፡፡ መካከለኛውም ዘመን ቤተክርስቲያን በጳውሎስም ዘመን የኖረችበትን ደግሞም እስከዚህ እስከኛ ዘመን ድረስ የዘለቀችበትን የሚያካትት ነው፡፡
ጳውሎስ ለተደራሲያኑ ሊያመለክታቸው የፈለገው ወሳኝ ሃሳብ ይህ ነው፣ ምክንያቱም ይህ ሃሳብ ለበርካታ ችግሮቻቸው ማብራሪያን ስለሚሰጣቸው ነው፡፡ ኃጢአት፣ ሞትና ርኩሰት መታወቂያው የሆነው የአሁኑ ዘመን ገና አልተፈፀመም፣ አማኞች በመከራ ውስጥ ማለፍ የሚገባቸውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ኢየሱስ አንድ ቀን ተመልሶ ይመጣና ለአማኖች ሁሉ የተሟላ በረከቱን ያወርሳቸዋል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖችም በዚህ ጊዜ፣ ኢየሱስ እንደሚመለስ በማመን ሊጠባበቁ ይገባል፡፡ ክርስቶስ የጀመረውን ወደ ፍፃሜ ለማምጣት ቁርጠኛ ስለሆነ ይህ እንደሚሆን ጽኑ ተስፋ አለን፡፡
አሁን በዚህ ጊዜ፣ ኢየሱስ በሰማይ በንግሥና መንበሩ ላይ ተቀምጧል፡፡ በዚያ ብቻ ግን አያበቃም፡፡ ልክ አሁን በሰማያት ላይ እንደነገሠ ሁሉ፣ በእያንዳንዲቷ ፍጥረት ላይ በሙላትና በክብር ሊገዛ ይፈልጋል ደግሞም አቅዷል፡፡ ጠላቶቹን ፈፅሞ እስኪያጠፋና ለዘላለም እስኪቀጣቸው ደግሞም የእርሱን ታማኝ አገልጋዮች በሙላት እስኪባርክ ድረስ አሁን በሆነው ነገር ረክቶ አይቀመጥም፡፡ ይህንንም ለማከናወን ያቀደው መንግሥቱን በዓለም ሁሉ በማስፋት ነው፡፡
ጳውሎስ ክርስቶስ በዓለም ሁሉ ላይ ለመግዛት ያለውን ዕቅድ ስለሚያውቅ፣ ክርስቶስ መንግሥቱን ወደሙላት ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኑን አስረግጦ ይናገራል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በደብዳቤዎቹ ውስጥ አማኞች ወደፊት ስለሚወርሱት ነገር የሚጽፈውና ክርስቶስ ዳግመኛ ሲመለስ በሚጠብቀው ብድራት ላይ ጽኑ ተስፋውን ያሳረፈው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ለምሳሌ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 13 እስከ 14 የተናገራቸውን ቃላት ልብ በሉ፡
እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤
እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል። (ኤፌሶን 1፡13-14)
እግዚአብሔር የገባውን የተስፋ ቃል ስለማይለውጥ፣ ወደፊት የሚጠብቀን ውርስ የተረጋገጠ መሆኑን ጳውሎስ አስረግጦ ይናገራል፡፡ ስለዚህም፣ በመንግሥቱ ፍፃሜ ውርሳችንን ሊያስረክበን ኢየሱስ ዳግመኛ ሊመጣ ይገባዋል፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 20 እስከ 21 ድረስ፣ ጳውሎስ የክርስቶስን ዳግመኛ መመለስ እንዲህ ይገልጸዋል፡
እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤
እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል። (ፊልጵስዩስ 3፡20-21)
ክርስቶስ መንግሥቱን በምድር ላይ ወደ ፍፅምና ሲያመጣ፣ እኛ የምንቀበለው ውርስ አዲስና ክቡር ሰውነት መልበስን ያካትታል፡፡ ጳውሎስ ስለዚህ ውርስ የሚናገረው በፍፁም እርግጠኝነት ነው ምክንያቱም ኢየሱስ እንደሚመለስ ተስፋን ሰጥቷል ደግሞም የገባውን ተስፋ ለመፈፀም ኢየሱስ ቁርጠኛ እንደሆነ ያውቃልና ነው፡፡
ጳውሎስ በእስር ቤት ደብዳቤዎቹ ከዳር እስከዳር፣ በክርስቶስ ንጉሣዊ ሉዓላዊነት፣ በክብሩና በቁርጠኝነቱ ላይ በመተማመን የአስተምህሮዎቹ የማእዘን ድንጋይ አድርጎ ያስቀምጣቸዋል፡፡ እነዚህ መሪ ሃሳቦች በደብዳቤዎቹ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሱ ሲሆን፣ በቆላስይስ፣ በኤፌሶንና በፊልጵስዩስ መልእክቶቹ ላስተላለፋቸው ትምህርቶቹ መሠረት አድርጓቸዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ንጉሥ ነው የሚለውን አስተምህሮ ስንመለከት ቆይተናል፣ አሁን ደግሞ በእስር ቤት ደብዳቤዎቹ ውስጥ ከምናገኛቸው አስተምህሮዎች ወደ ሁለተኛው እና በእርሱ ንግሥና ውስጥ አማኞች ከእርሱ ጋር ስላላቸው አንድነት ማለትም ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት የእርሱ በረከቶች ተካፋይ ስለመሆናችን ወደ ሚዘረዝረው አስተምህሮ ትኩረታችንን እናዞራለን፡፡
ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት
እንደ ጳውሎስ አገላለጥ፣ በኢየሱስ ስናምን፣ ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ፣ ከእርሱ ጋር አንድ ሆነናል፡፡ እናም ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን ምክንያት፣ ከእርሱ ጋር አንድ እንደሆንን ተደርጎ ተቆጥሮልናል፡፡ ለምሳሌ፣ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ፊት አንዳችም ነውር የለበትም፣ እኛም ከእርሱ ጋር ከመተባበራችን የተነሳ፣ በእግዚአብሔር እንከን የሌለን ተደርገን ተቆጥረናል፣ ኃጢአታችንም በጠቅላላ ይቅር ተብሎልናል፡፡
ጳውሎስ በእስር ቤት ደብዳቤዎቹ ደጋግሞ ወደሚያነሳው ነጥቡ ማለትም አንባቢዎቹ የክርስቶስ ንግሥና ተካፋዮች መሆናቸውን በማሳሰብ ወደሚበረታታበት ነጥቡ ይመለሳል፡፡ ደጋግሞ የሚነሳውም አማኞች የክርስቶስ ንግሥና ተካፋዮች በመሆናቸው ምክንያት፣ በአሁን ዘመን ማለትም በክርስቶስ መንግሥት መስፋፋት ወቅት በረከትን ይቀበላሉ፣ ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ በመንግሥቱ ፍፃሜ ወቅት እጅግ የሚበልጥ በረከትን ይጠባበቃሉ፡፡
ለምሳሌ፣ በቆላስይስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ 4 ጳውሎስ እንዲህ ጽፏል፡
እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ እሹ፤
በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።
ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና፤
ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። (ቆላስይስ 3፡1-4)
ከክርስቶስ ጋር አንድ ስንሆን፣ ከክርስቶስ ሞትም ጋር እንተባበራለን፣ ስለዚህም እኛም ከእርሱ ጋር እንሞታለን፡፡ ደግሞም የክርስቶስ ትንሣኤና ሕይወት ተካፋዮችም ስለምንሆን ከእርሱ ጋር ደግሞ ከሞት እንነሣለን፡፡ በተጨማሪም ከክርስቶስ እርገትና ትንሣኤም ጋር እንተባበራለን፣ ስለዚህም እርሱ በክብር ሲመለስ፣ ከእርሱ ጋር እንገዛለን፡፡
ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 6 እስከ 7 እንዲህ ጽፏል፡
በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። (ኤፌሶን 2፡6-7)
እንደ ጳውሎስ አገላለጥ፣ አሁን እኛ እርሱ በፍጥረት ሁሉ ላይ ያለው ንግሥና ተካፋዮች እንሆን ዘንድ፣ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጠናል፡፡ ምንም እንኳን የእኛ ምድራዊ ሁኔታ ያንን በሙላት ሊያንጸባርቀው ባይችልም፣ እኛ አሁን በመንፈሳዊ ሚዛን የእርሱ ክብርና በረከት ተካፋዮች ነን፡፡ እናም ኢየሱስ ሲመለስ መንፈሳዊ በረከቶቻችን እጅግ የተትረፈረፉ ይሆናሉ፣ ምድራዊ በረከትንም እንቀበላለን፡፡
ጳውሎስ ግን በሌላው ጎኑ የክርስቶስ ንግሥና ተካፋዮች ከመሆናችን አንፃር በብርቱ ሊያሳስብ የሚፈልገው እኛ እንዲሆኑብን ስለማንፈልጋቸውና ደስ ስለማያሰኙን ማለትም የመከራውም ተካፋዮች ስለመሆናችን ነው፡፡ የመከራው ተካፋይ ከመሆን አንፃር ጳውሎስ አማኞችን የሚበረታታው መከራን የሚቀበሉት ብቻቸውን እንዳልሆነና መከራቸውም በከንቱ እንዳልሆነ በማሳሰብ ነው፡፡ ይህ ነገር በጳውሎስ በራሱም ሕይወት ውስጥ እውነትነት እንዳለው ተመልክተናል፡፡ ጳውሎስ ግን የጻፈው በአንባቢዎቹም ሕይወት ውስጥ ይህ እውነት ተፈፃሚ እንደሚሆን በማሳሰብ ነው፡፡
እስኪ በቆላስይስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 24 የተቀመጡትን ቃላት እናዳምጥ፡
አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። (ቆላስይስ 1፡24)
የክርስትና ሕይወት ከባድ ሕይወት ነው፣ ያም በታላቅ መከራ ማለፍን ያካትታል፡፡
ንጉሣችን አሁን በሰማያት የነገሠ ቢሆንም፣ ጠላቶቹን ግን ገና ጨርሶ አላጠፋቸውም፣ እናም እነዚህ ጠላቶች ደግመው ደጋግመው ያላቸውን ኃይል በእኛ ላይ ያዘምቱብናል፡፡ ስለ ወንጌል መከራን ስንቀበል፣ ከክርስቶስ ጋር አንድ ከመሆናችን የተነሳ ክርስቶስም አብሮን መከራን ይቀበላል በማለት ጳውሎስ ይህንን ሃሳብ መጽናኛው ያደርገዋል፡፡ ከንጉሡ ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን፣ የምናልፍበት መከራ በክርስቶስ መንግሥት፣ ማለትም በቤተክርስቲያን ውስጥ ላሉ ለሌሎች ጥቅም በመሆኑም ጳውሎስ ይጽናናል፡፡ በመጨረሻም፣ የእኛ መከራ አስቀድሞ የተነገረውን የክርስቶስን መከራ ወደሙላት የሚያመጣ ሲሆን፣ ለንጉሣችን ዳግመኛ በድል መመለስም መንገድ ጠራጊ ነው፡፡
እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች፣ የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች እኛ ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን መሪ ሃሳቦች ላይ ይመሠረታሉ፡፡ በጳውሎስ አስተሳሰብ፣ ከፍጥረታት ንጉሥ ጋር ያለን አንድነት መዳናችን የተረጋገጠ መሆኑን በልበ ሙሉነት እንድናውቅ፣ በመከራችንም ወቅት ታላቅ ብርታት እንዲሆነን እና ስለ ወደፊቱም ታላቅ ተስፋ እንዲኖረን ያደርገናል፡፡
እስካሁን ድረስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ንጉሥ ነው፣ ደግሞም አማኞች የንግሥናው ተካፋዮች ናቸው የሚለውን ሃሳብ ጳውሎስ እንዴት በጥቅም ላይ እንዳዋለው መርምረናል፣ አሁን ደግሞ የእስር ቤት ደብዳቤዎቹ ያነገቡትን ነገረ-መለኮታዊ ስምምነት ወደምንመለከትበት ወደ መጨረሻው ነጥብ በመሸጋገር፣ በክርስቶስ ንግሥና እና እኛ ከእርሱ ጋር ባለን አንድነት በተግባር ሊገለጡ በሚገባቸው የአኗኗር ሥነ-ምግባሮች ላይ እንነጋገራለን፡፡
የአኗኗር ሥነ-ምግባር
የጳውሎስን ደብዳቤዎች ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች ሐዋርያው አስተምህሮአዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የጻፈውን ያህል ስለ ክርስቲያኖች ስነ-ምግባራዊ አኗኗርም በርካታ ትምህርቶችን እንዳስተላለፈ ያውቃሉ፡፡ እንዲያውም፣ ዘወትር አንድ አስተምህሮአዊ ጉዳይ ሲያነሳ፣ በዚውም አያይዞ አማኞች ያንን አስተምህሮ እንዴት በሕይወታቸው ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ ይህም ተዛምዶ በትክክለኛ አስተሳሰብና የእምት አቋም ላይ ብቻ አያቆምም፡፡ የአማኞችን ስሜትና ባሕርይም የሚገዛ ይሆናል፡፡ እንዲያውም ጳውሎስ ከዚያ በጣም በጠለቀ መንገድ፣ አስተምህሮ ስሜታችንንና ባህርያችንን በሚለውጥ መንገድ ካልተዛመደ በስተቀር ፋይዳ ቢስ ነው በማለት ይገልጻል፡፡
በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ቁጥር 2 ጳውሎስ የተናገራቸውን ቃላት እናድምጥ፡
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። (1ኛ ቆሮንቶስ 13፡2)
ምሥጢርን ሁሉ ካወቅን እና እውቀትን ሁሉ ካወቅን፣ እግዚአብሔር ስለነገሮች ያለውን ራእይ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በሌላ አባባል፣ ፍፁም የሆነ አስተምህሮ ይኖረናል፡፡ መልካም አስተምህሮ አለን ማለት እንዲያውም እንከን የለሽ አስተምህሮም ቢሆን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ያ አስተምህሮ ሕይወታችንን ካልለወጠ፣ በፍቅር የተቃኘ ካልሆነ፣ ሌሎችን በጨዋነትና በገርነት ወደምናስተናግድበትና ክርስቶስንም በአክብሮት ወደመታዘዝ ካልወሰደን፣ ለእኛ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡
ስለዚህ፣ የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች በአኗኗር ሥነ-ምግባር ላይ ደጋግመው አጽንዖት ቢሰጡ አይገርመንም፡፡ በአንድ በኩል፣ ክርስቶስ ንጉሥ የመሆኑ እውነታ እንድንታዘዘው ግድ ይለናል፡፡ በሌላ ጎን ደግሞ፣ እኛ ከክርስቶስ ጋር አንድ የመሆናችን እውነታ ከእርሱ ባህርይ ጋር በተጣጣመ መንገድ እንድንኖር ግድ ይለናል፡፡ አስኪ አስቀድመን ከክርስቶስ ንግሥና ስለሚመነጨውና እኛንም በተቀደሰ አኗኗር እንድንኖር ግድ ስለሚለን እውነታ እንመልከት፡፡
ክርስቶስ ንጉሥ
አስቀድመን እንዳልነው፣ ክርስቶስ ንጉሥ ስለሆነ፣ ሉዓላዊ ነው፡፡ ይህም ማለት እኛ እንድንታዘዘው የማድረግ ህጋዊ መብት አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ፣ እኛም እርሱን የመታዘዝ ህጋዊ ግዴታ አለብን ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም እንደተነጋገርነው፣ ክርስቶስ ፍፁምና ፍትሃዊ ንጉሥም ነው፡፡ ይህም ማለት የእርሱ ፍርዶችና ትዕዛዛት ሁሉ ሥነ-ስርዓትን የጠበቁ ናቸው፣ ስለዚህ እኛም እርሱን የመታዘዝ ሥነ-ምግባራዊ ግዴታ አለብን ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ሉዓላዊና ፍትሃዊ በመሆኑ ምክንያት፣ እኛም እርሱ ያዘዘንን ሁሉ የመፈጸም ህጋዊና ሥነ-ምግባራዊ ግዴታ አለብን ማለት ነው፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 9 እስከ 12 ውስጥ ጳውሎስ ያቀረበው ሙግት የዚህ ዓይነት መልክ አለው፤ የተጻፈውም እንዲህ ይላል፡
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤
ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥
መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ (ፊልጵስዩስ 2፡9-12)
ኢየሱስ በሰማይ፣ በምድር እና ከምድርም በታች ያሉትን ሁሉ የሚገዛ ጌታ ነው፡፡ በሌላ አባባል፣ እርሱ የፍጥረት ንጉሥ ነው፡፡ ጳውሎስም የክርስቶስን ንግሥና መሠረት በማድረግ፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች ክርስቶስን እንዲታዘዙ ያሳስባቸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ቀደም ብለን እንዳየነው፣ የክርስቶስ ንግሥና ክብሩንም ያካትታል፡፡ በዚያም አግባብ፣ ክርስቲያኖችም ለንጉሣቸው ክብር በሚመጥን መንገድ የተቀደሰ ሕይወት ሊኖሩና ሊያከብሩት ይገባል በማለት ጳውሎስ ሙግቱን ያቀርባል፡፡ አንዱ ነገር፣ ክርስቶስን መታዘዝ በእኛ ዘንድ የስሙ ዝና ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋል፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ክርስቶስ ቅዱስ፣ ጻድቅና የከበረ ነው፣ ስለዚህ ልንታዘዘው ይገባል፡፡
ጳውሎስ ይህንን በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 27 ውስጥ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፡
…ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። (ፊልጵስዩስ 1፡27)
በቆላስይስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 10 ውስጥ ደግሞ ተደራሲያኑን እንዲህ በማለት ያበረታታቸዋል፡
በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፥
በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን።
(ቆላስይስ 1፡10)
የክርስቶስ ክብርና ዝና ሊከበርና ሊጠበቅ የሚገባው የመሆኑ ጉዳይ የጳውሎስ ዋና ጉዳዩ ነው፣ አማኖችም ይህንን ሊያሳኩ የሚችሉት መልካም ሥራን ሲሠሩ መሆኑን፣ ያም ማለት የጌታን ትዕዛዛት ሲፈፅሙ መሆኑን ያመለክታቸዋል፡፡
ጳውሎስ በእስር ቤት ደብዳቤዎቹ በጠቅላላ፣ አንባቢዎቹ የጌታን ትዕዛዛት በአግባቡ በመመላለስ እንዲጠብቁ፣ በሃሳባቸው፣ በስሜታቸውና በትክክለኛ ሥነ-ምግባራቸው ክርስቶስን እንዲታዘዙ ያሳስባቸዋል፡፡ ምንም አንኳን በሁሉ ነገር ውስጥ ጉዳዩን ከክርስቶስ ንግሥና ጋር ባያያይዘውም፣ የክርስቶስ ንግሥና በበጎ ሥነ-ምግባር የታነጸ ሕይወት እንድንኖር የሚያነሳሳን መሠረታዊ እውነት ሊሆን እንደሚገባው ግን እየደጋገመ ይገልጻል፡፡
ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ንጉሥ ስለሆነ ክርስቲያኖችም ለዚያ የተገባ ኑሮ ሊኖሩ እንደሚገባ ከማስተማሩ ባሻገር፣ እኛ ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን ምክንያት፣ ከእርሱ ባህርይ እና ትዕዛዛት ጋር የተጣጣመ ኑሮ የመኖር ግዴታ አለብን አቅምም ተሰጥቶናል በማለት ያብራራል፡፡
ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት
እኛ ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት፣ ለዚያ የተገባ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል አቅም እንደተሰጠንና ግዴታም እንዳለብን የሚያሳዩ ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛ፣ ክርስቶስ በመንፈሱ አማካይነት በውስጣችን አድሯል፣ አዲስ ፍጥረትም አድርጎናል መልካሙንም ሥራ እንድናደርግ አስችሎናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን የመኖሩ አንዱ ውጤት፣ ማንነታችንን ወደ ክርስቶስ ማንነት መለወጡ ነው፡፡ በውጤቱም፣ እኛ ተለውጠናል፣ ክርስቶስንም መታዘዝ የምንችልበት መነሳሳት በውስጣችን አለ፡፡ በእነዚህ ሁሉ፣ እግዚአብሔር በውስጣችን ይሠራል እኛንም ወደ ራሱ ያቀርበናል ደግሞም ክርስቶስ እንደተወልን ምሳሌ እንድንኖር ያስችለናል፡፡
ስለዚህ ጉዳይ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁር 12 እና 13 ውስጥ የተናገረበትን መንገድ አድምጡ፡
ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤
ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። (ፊልጵስዩስ 2፡12-13)
ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት እግዚአብሔር በመንፈሱ በእኛ ውስጥ ከማደሩ ጋር የተያያዘ ነገር አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ትክክለኛውንና በሥነ-ምግባር የታነፀውን ኑሮ መኖር የሚያስችለንን እግዚአብሔርን የመታዘዝ ሕይወት እንድንመራ ስሜታችንንና ፈቃዳችንን ያነሳሳል፡፡
ጳውሎስ በቆላስይስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 5 እስከ 10 ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሙግት ያቀርባል፡
እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ … አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥
የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ (ቆላስይስ 3፡5-10)
ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን ምክንያት፣ አዲስ ፍጥረት ነን፡፡ እግዚአብሔርም አዲስ ፍጥረት ሲያደርገን፣ ግዴታ ብቻ ሳይሆን የሰጠን፣ ኃጢአትን እንድናደርግ የሚጎተጉተንን ፈተና በመቋቋም መልካሙን ሥራ ለመሥራት የሚያስችለንንም አቅም ጭምር ነው፡፡
ሁለተኛ፣ ከልጁ ጋር አንድ የሆኑ ሁሉ የተቀደሰ ኑሮ ሊኖሩ እንደሚገባቸው እግዚአብሔር አዟል፡፡ እንዲያውም፣ እግዚአብሔር ትዕዛዝ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ አስቀድሞውኑ የፈጠረን መልካሙን ሥራ እንድንሠራ አድርጎ ነው፡፡
ጳውሎስ ይህንን በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ቁጥር 10 ውስጥ ጽፎታል፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። (ኤፌሶን 2፡10)
እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጥረናል፣ ያም ማለት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አማካይነት እግዚአብሔር ያድነናል፡፡ ይህንን ካደረገበት ምክንያት አንዱ እኛ መልካሙን ሥራ እንድናደርግ ለማስቻል ነው፡፡
ሦስተኛ፣ እኛ ሁላችን ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን ምክንያት፣ እርስ በርሳችንም በክርስቶስ አንድ ሆነናል፡፡ ይህም ለክርስቶስ ባለን ከበሬታ ልክ እርስ በርሳችን እንድንከባበር ግድ ይለናል መከባበሩም እኛን ሌሎች እንዲያከብሩን በምንፈልግበት ልክ ነው፡፡
ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ቁጥር 25 እንደጻፈው፡
ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። (ኤፌሶን 4፡25)
“እኛ ሁላችን የአካሉ ብልቶች ነን” የሚለው ሐረግ አብዛኛውን ጊዜ በቁሙ ሲፈታ “እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናል” የሚል ፍቺ ይይዛል፡፡ ጳውሎስም ሊያስጨብጥ የፈለገው ነጥብ፣ እርስ በርሳችን በክርስቶስ አንድ ከመሆናችን የተነሳ፣ ይህ አንድነት እርስ በርስ እንድንከባበር፣ አንዳችን በሌላችን ላይ በደልን እንዳንፈጽም፣ ይልቁኑ አንዳችን ለሌላችን ጥቅም እንድንኖር ግድ ይለናል፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 3 እንደጻፈው፡
በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ …
ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ (ፊልጵስዩስ 2፡1-3)
አዲስ ፍጥረት በመሆናችን፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝ እና እርስ በርስ ባለን አንድነት፣ ቢያንስ በእነዚህ ሦስት ምክንያቶች፣ እግዚአብሔርም በቅዱሳት መጻሕፍት ባስቀመጠልን ደረጃና ልክ የተቀደሰ ሕይወት ልንኖር እንደሚገባን ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት ግድ ይለናል፡፡
የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች ነገረ-መለኮታዊ አንድነት የላቸው ሲሆኑ ይህም አንድነታቸው፣ በጳውሎስ የበለጸጉና በርካታ ገፅታ ባላቸው በክርስቶስ የፍጥረት ሁሉ ንጉሥነት፣ አማኞች ከክርስቶስ ጋር ባላቸው አንድነት እና ከዚያም በሚመነጨው የተቀደሰና ተገቢ የሆነ ኑሮ የመኖር እውነታ ላይ የተገነባ መሆኑን አይተናል፡፡
ወደፊት በምንመለከታቸው ትምህርቶችም፣ የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች በጋራ የሚስተላልፏቸውን በርካታ መሪ ሃሳቦች እንዳስሳለን፡፡ እነዚህን እውቅ መሪ ሃሳቦች እርስ በርስ የሚያስተሳስራቸው ዋና ሃሳብ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ሁሉ ንጉሥ ነው የሚለው አስተምህሮ ነው፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ ትምህርት የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች እንዲጻፉ ምክንያት የሆኑ ነገሮችን እና ጳውሎስ በእነዚህ ደብዳቤዎች የተጠቀመባቸውን ነገረ-መለኮታዊ አቀራረቦች ዳስሰናል፡፡ እንዲያዝ ያደረጉትን ሁኔታዎች እና ከዚያም ተከትሎ የመጣውን እሥራቱን ደግሞም ጳውሎስ በእስር ቤት የሰጣቸውን ተከታታይ አገልግሎቶች መርምረናል፡፡ በመጨረሻም፣ የጳውሎስን የእስር ቤት ደብዳቤዎች የሚያስተሳስራቸውን ዋና ነገረ-መለኮታዊ መሪ ሃሳብ አስተዋውቀናል፡፡ ያም ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ንጉሥ ነው የሚለው ነው፡፡
የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች በነገረ- መለኮት የበለጸጉ ናቸው፣ ደግሞም የዛሬይቱን ቤተክርስቲያን ለማስተማርና ለማበረታታት አግባብነት ያላቸው ናቸው፡፡ ወደፊት በምንመለከታቸው ትምህርቶች፣ እነዚህን ደብዳቤዎች በበለጠ ጥልቀት እንዳስሳቸዋለን፡፡ ይህንንም ስናደርግ፣ በዚህ ትምህርት የዳሰስናቸውን ነጥቦች በአዕምሯችን በመያዝ እንደ ዳራ እንጠቀምባቸዋለን፡፡
ጳውሎስ ያለፈበትን መከራ እና በእስር ቤት በጽናት የሰጠውን አገልግሎት ማወቃችን ጳውሎስ ለቆላስይስ፣ ለኤፌሶን እና ለፊልጵስዩስ አብያተክርስቲያናት ደብዳቤዎቹን እንዲጽፍ ያነሳሳውን ነገርና ግቡን እንድነገነዘብ ያስችለናል፡፡ እነዚህን ደብዳቤዎች የሚያስተሳስሩትን ነገረ-መለኮታዊ አንድነቶች መረዳታችን ደግሞ ጳውሎስ ለእነዚህ አብያተክርስቲያናት የሰጣቸውን በርካታ መመሪያዎች እንድንረዳ ያስችለናል፡፡ እነዚህን ነገሮች በልቡናችን ስናስቀምጥ፣ የጳውሎስን ትምህርቶች በትክክል በመረዳት፣ በግል ሕይወታችንና በቤተክርስቲያኖቻችን ተግባራዊ እንድናደርጋቸው ይበልጥ ዝግጁዎች እንሆናለን፡፡
Continue reading the full transcript