<link rel="stylesheet" href="https://cdn.plyr.io/3.7.8/plyr.css" />
ወደ ካታሎግ ተመለስPPEየጳውሎስ እስራት ደብዳቤዎች
የጳውሎስ እስራት ደብዳቤዎች ·Videoከእንግሊዝኛ ተተርጉሟል

PPE-03 ጳውሎስና ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ሙሉውን ጽሑፍ ያንብቡ

ከተመሳሳዩ ተከታታይ ትምህርት 3 ጋር የተያያዘ ቪዲዮ ሲሆን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠይቃል: አንዳንድ ሰዎች የኤፌሶን ደብዳቤ ደራሲነትን ለጳውሎስ የሚጠይቁት ለምንድን ነው? ኤፌሶን ከጳውሎስ ሌሎች ጽሑፎች ጋር በሚመሳሰል መልኩ ምን መንገዶች አሉ? የኤፌሶን ደራሲነት ለምን አስፈላጊ ነው? አንድ ሰው ለምን በጳውሎስ ስም ደብዳቤ ይጭናል? ጳውሎስ በእውነት ለኤፌሶን ሰዎች ደብዳቤ ጽፏልን? ካልሆነ ምን ለውጥ ያደርጋል? ይህ ደብዳቤ በአከባቢው ችግሮች ኤፌሰስን ብቻ ይን触ልቅልቅል ወይም ሰፊ ማኅበረሰብ ብቻን ይን触ልቅልቅል? አንድ ግוי ለአይሁድ መሲህ መደሰት ለምን አለበት? የእግዚአብሔር ለአሮጌው ኪዳን እስራኤል ቃልኪዳኖች ለቤተክርስቲያን ይተገበራሉን? በአይሁድና ግዮች መካከል ጉልህ ልዩነቶች ተወግደዋልን? ዘመናዊቺ ቤተክርስቲያን በአንድ አካል ምን መንገድ ናት? እግዚአብሔር ልዩነትን ይወዳልን? ጳውሎስ ለግዮች አንባቢዎች በኤፌሶን የመንግሥት እግዚአብሔር ሀሳብን ዝቅ አድርጎታልን? የመንግሥት እግዚአብሔር ሀሳብ ዘይቤ ብቻ ነውን? ዛሬ እኛን እንዴት ይነካል? በኤፌሶን 4 ውስጥ የመንፈሳዊ ስጦታዎችና የቤተክርስቲያን ቢሮዎች መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? በኤፌሶን 4 የተጠቀሱት የቤተክርስቲያን ቢሮዎች ሁሉ አሁንም ይገኛሉን? የጳውሎስ ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙ መመሪያው በእያንዳንዱ ባህል ላይ ይተገበራልን? የእግዚአብሔር ትጥቅ ሙሉ በሙሉ የመከላከያ ነው ወይንስ ወንጀላዊ ጥራት አለው? በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ የምንገባበት ዋና መንገድ ምንድን ነው? ምስጋናና አምልኮ በአብዛኛው ሙዚቃዊ መሆን አለበትን? በተሰበሰበች ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው አምልኮ ከሌሎች የአምልኮ ዓይነቶች ይለያል እንዴት? የግለሰብና የጋራ ወንጌልን አንኳር እንዴት እናስታረቅ? ወንጌልና የመንግሥት እግዚአብሔር መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? የመንግሥት እግዚአብሔርን ለመገንባት ተግባራዊ መንገዶች ምንድን ናቸው?


From the transcript

ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡

ከአንድ አገር በላይ ለመኖር የተገደዱ ሰዎች ሁለት የተለያዩ ባህሎችን የራስ ማድረግ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ደጋግመው ነግረውኛል፡፡ እያንዳንዱ ሀገር የየራሱ ልማድ፣ ህግና እሴቶች አሉት፡፡ በአንዱ አገር አግባብነት ያለው በሌላው አገር ግን ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል፡፡ ነጋዴዎች፣ ቱሪስቶች እና ሚሲዮናውያንም ሳይቀሩ የሚጎበኟቸውን አገሮች አጠቃላይ አካሄዶች ለማጥናት በርካታ ጊዜዎችን ይወስዳሉ፡፡

በብዙ መንገዶች፣ ለክርስትና ሕይወትም ጉዳዩ ተመሳሳይነት አለው፡፡ እኛ ሁላችን ስንወለድ ያለ ክርስቶስ የነበርን፣ ከመንግሥቱም የተለየን ነበርን፡፡ አብዛኞቻችን የጨለማውን መንግሥት መንገዶች ስንከተልና ስንለማመድ ዓመታትን አሳልፈናል፡፡ ከዚህም የተነሳ አሁን በምንገኝበት በአዲሱ መንግሥት፣ በክርስቶስ ባገኘነው የብርሃን መንግሥት ሥርዓት ለመመላስ ስንሞክር በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥሙናል፡፡

ይህ ተግዳሮት አዲስ አይደለም፡፡ ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን፣ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ መንግሥት የሚገባ ኑሮ እንዴት መኖር እንዳለባቸው መማር አስፈልጓቸው ነበር፡፡ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ከአረማውያን ሃይማኖቶች የመጡ ነበሩ፡፡ በክርስቶስ ከማመናቸው አስቀድሞ፣ የዕድሜያቸውን አብዛኛውን ዘመን የጨረሱት የሰይጣንን መንገዶች በመከተል ነበር፡፡ የቀደመ አስተሳሰባቸውን፣ ስሜቶቻቸውን እና ምግባራቸውን መለወጥ እጅግ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ስለዚህም፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች መልእክቱን ሲጽፍ፣ ለተግዳሮቶቹ ምላሽ የሰጠው በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት ፈለካዊ ገጽታ በዳሰሳ መልክ አሳምሮ በመሳል ነበር፡፡

ይህኛው ትምህርት “የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች” ከተሰኘው ተከታታይ ትምህርታችን “ጳውሎና የኤፌሶን ሰዎች” የሚል ርዕስ የሰጠነው ሦስተኛው ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ እንመረምራለን፣ በተለይ የምናተኩረው ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እንዴት ሊገነቡ፣ ሊጠበቁና እየጎለበቱ ሊሄዱ እንደሚገባቸው ለማስተማር ደብዳቤውን ባዋቀረበት አወቃቀር ላይ ይሆናል፡፡

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን መልእክት በሦስት ክፍሎች እንመረምረዋለን፡፡ አንደኛ፣ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን መልእክት ዳራ እንመረምራለን፡፡ ሁለተኛ፣ የኤፌሶንን አወቃቀርና ይዘት እንመለከታለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ የመልእክቱን ዘመነኛ ተዛምዶ እንወያይበታለን፡፡ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክት ዳራ እንጀምር፡፡

ጳውሎስ እንደ ሐዋርያነቱ የሚጠበቅበት ሃላፊነት ቤተክርስቲያኒቱን በሥልጣን ማስተማርና አመራር መስጠት ነው፡፡ ይህንንም መልእክቶችን በመጻፍ በከፊል ፈጽሞታል፡፡ ጳውሎስ ግን ሚዛኑን የጠበቀ አስተምህሮ በመስጠት ብቻ አላቆመም፣ ወይም ለመጪው ትውልድ ተመዝግቦ እንዲቀመጥ ብቻ አልፈለገም፡፡ እርሱ የፈለገው፣ ከሁሉ አስቀድሞና ከሁሉም በላይ፣ ጤናማውን አስተምህሮ በራሱ ዘመን ተግባራዊ በማድረግ ቤተክርስቲያንን ማገልገል ነበር፡፡ ደብዳቤዎቹ መጋቢያዊ እና ሰለ መንጋው የሚያስቡ፣ ደግሞም በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ቤተክርስቲያንን ይገዳደሩ የነበሩ ችግሮችን የሚዳስሱ ነበሩ፡፡

ይህም ማለት የኤፌሶንን መልእክት ስናጠና፣ ይህ መልእክት ለነማን ተጻፈ? በሕይወታቸው ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመዋቸው ነበር? የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ መጀመር ይረዳል፡፡ እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ማወቃችን ስለ ጳውሎስ አስተምህሮ ትልቅ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስችለናል፡፡

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ ዳራ ስንመለከት፣ ትኩረታችንን በሦስት ጉዳዮች ላይ እናደርጋለን፡፡ አንደኛ፣ ጳውሎስ የደብዳቤው ጸሐፊ ስለመሆኑ እንነጋገራለን፡፡ ሁለተኛ፣ ቀደምት ተደራሲያኑን እንለያለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ጳውሎስ ለእነርሱ የጻፈበትን ዓላማ እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ ጳውሎስ የኤፌሶን መልእክት ጸሐፊ መሆኑን እንመልከት፡፡

ፀሐፊ

በርካታ የዘመኑ ምሁራን ጳውሎስ ደብዳቤውን አልጻፈም በማለት ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ይልቁኑ፣ መልእክቱ የተጻፈው ከጳውሎስ ተማሪዎች አንዱ በሆነ፣ የጳውሎስን አሻራ በታማኝነት ለማስቀጠልና ትምህርቶቹንም በአዲስ መንገድ ለማዛመድ በፈለገ ሰው ነው ይላሉ፡፡ ይህንን ሃሳብ ውድቅ የምናደርግበት ጠንካራ ምክንያት አለን፡፡ አንዱ፣ መልእክቱ ራሱ በጳውሎስ እንደተጻፈ ተገልጧል፡፡ ኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁጥር 1 ምን እንደሚል እናድምጥ፡

በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤ (ኤፌሶን 1፡1)

በቀደመችው ቤተክርስቲያን፣ አንዳንድ የሐሰት መምህራን የሌሎችን ሰዎች ስም በደብዳቤዎቻቸው ላይ በማስመሰል በመጥቀስ ይጽፉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም ቤተክርስቲያኒቱ መልእክቱ የማስመሰል መሆኑን ስትደርስበት ውደቅ ታደርገው ነበር፡፡ ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ በ2ኛ ተሰሎንቄ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 3 የሰጠውን ትምህርት እናድምጥ፡

ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን።

ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና። (2ኛ ተሰ 2፡1-3)

እንግዲህ የጳውሎስ አድናቂ ወይም ተማሪ የሆነ ሰው በደብዳቤው ላይ የእርሱን ስም በማስመሰል በመጥቀስ የጳውሎስን ትምህርት የሚቃረን ነገር ያደርጋል የሚለውን ነገር መቀበል በጣም ከባድ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ የኤፌሶን መልእክት በአስተምህሮም ሆነ በቋንቋ አጠቃቀሙ ከሌሎቹ የጳውሎሰ መልእክቶች ጋር ይስማማል፡፡ ትስስሮቹ በተለይም ከቆላስይስ መልእክት ጋር ይቀራረባሉ፣ እንዲያውም ጳውሎስ ሁለቱንም በአንድ ወቅት ሊጽፋቸው ቢችል ሊያስደንቀን አይገባም፡፡ እነዚህ ትስስሮች እጅግ ብርቱ ከመሆናቸው የተነሳ ጳውሎስ ስሙን ባይጠቅስ እንኳን በግልጽ የሚለዩ ናቸው ስለዚህ ቤተክርስቲያን ጸሐፊነቱን ለሌላ ሰው ሰጥታዋለች ብሎ መገመት አዳጋች ነው፡፡

በመጨረሻ፣ እንደ ሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 19 እስከ 21 አገላለጽ፣ ጳውሎስ በኤፌሶን የምትገኘዋን ቤተክርስቲያን ተክሏል፣ በኤፌሶንም ለሁለት ዓመታት ኖሯል፡፡ ከዚያ በኋላ እንኳን፣ ከሽማግሌዎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በቅርበት እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ ስለዚህ የኤፌሶን ሰዎች ይህንን ደብዳቤ እንደ ሐሰት ሊቆጥሩት አለመቻላቸው ሊታሰብ የማይችል ነው፡፡ በተጨማሪም ደግሞ ይህንን ከመሰለ እውቅ ሐዋርያ ለታወቀች ቤተክርስቲያን የተጻፈን የሐሰት ደብዳቤ ይህንን ያህል ዓመት ሳትለየው ዘለቀ ብሎ ማሰብም ሊታሰብ የማይችል ነው፡፡

ተደራሲያን

የጳውሎስን ጸሐፊነት ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ትኩረታችንን የኤፌሶንን መልእክት ቀደምት ተደራሲያን ወደ መመልከቱ እናሸጋግራለን፡፡

የጳውሎስን ተደራሲያን በሁለት እንከፍላቸዋለን፣ በመጀመሪያ ቀደምት ተደራሲያኑን፣ ማለትም የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን እናያለን፡፡ ከዚያ ደግሞ ወደ ሁለተኛዎቹ ተደራሲያን፣ በተለይም በሌከስ ሸለቆ የሚገኙትን አብያተክርስቲያናት እናያለን፡፡ የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን እንደ ጳውሎስ ቀደምት ተደራሲያን በመመልከት እንጀምር፡፡

ቀደምት ተደራሲያን

ደግመን አንድ ጊዜ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁጥር 1 የተቀመጡትን ቃላት እንመልከት፡

በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤ (ኤፌሶን 1፡1)

በዚህ ደብዳቤ አድራሻ ውስጥ፣ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ቀደምት ተደራሲው መሆኗን ጳውሎስ ጠቅሷል፡፡

ኤፌሶን የሮሜ ግዛት በሆነችው የእስያ አውራጃ ዋና ከተማ ስትሆን፣ በዘመናችን ትንሿ እስያ ተብላ ከምትጠራው ጋር በግርድፉ የምትዛመድ ናት፡፡ በመጀመሪያው ምዕተ-ዓመት፣ ከሮሜ ግዛቶች ሁሉ ብዙ ህዝብ ካለባቸው ከተሞች የምትልቅ ወሳኝ ከተማ ስትሆን፣ በምሥራቁና በምዕራቡ ዓለም መካከል እንደ መገናኛ ድልድይነት ታገለግል ነበር፡፡ በመልክዓ ምድር አቀማመጧም፣ በኤጅያን ባህር ጠረፍ ከሜንዳር ወንዝ ብዙም ሳትርቅ በስተሰሜን ትገኛለች፡፡

እንግዲህ አሁን፣ አንዳንድ ምሁራን ይህ ደብዳቤ በቀደምትነት ለኤፌሶን ሰዎች አልተላከም ብለው እንደሚያምኑ ልንጠቅስ ይገባናል፡፡ ለጥርጣሬያቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ሁሉም ግን ደካማ መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡ አንደኛው፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁጥር 1 የተጠቀሰውና “በኤፌሶን” የሚለው ቃል በጥንታዊው ቅጂ ውስጥ የለም የሚል ነው፡፡ ይህ እውነት ነው ብንል እንኳን፣ አብዛኞቹ ጥንታዊ ቅጂዎች ደግሞ ይህንን ቃል አስፍረዋል፣ እንዲያውም ይህ ደብዳቤ ለሌላ ተደራሲ አድራሻ መደረጉን የጠቀሰ ምንም ቅጂ አልተገኘም፡፡

ከዚህ ባሻገር፣ በደብዳቤው ውስጥ የተጠቀሱት ዝርዝሮች ለኤፌሶን አግባብነት ያላቸው ናቸው፡፡ ሁለቱን እንመልከት፡፡

በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ በኤፌሶን ቆይታ ባደረገበት ወቅት፣ ከጣዖቷ ከአርጤምስ እና ከሌሎችም ክፉ አማልክት አምላኪዎች ጋር መጋጨቱን ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 19 እንገነዘባለን፡፡ በተዛማጅነት፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ቁጥር 11፣ “ፍሬ የሌለውን የጨለማ ሥራ በማውገዝ” ደግሞም በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 11 እና 12 ውስጥ የክርስቲያኖች ውጊያ ከአህዛብ የሐሰት አማልክት ጋር መሆኑን በማሳሰብ ጽፏል፡፡

ሁለተኛ፣ ከከርሰ ምድር ቅርሶች ምርምር እንደምንገነዘበው የኤፌሶን ከተማ “የአርጤምስ ጠባቂ” ተደርጋ እንደምትቆጠር አርጤምስ ደግሞ በእስያ አውራጃዎች ከሚገኙ ከተሞች ሁሉ ኤፌሶን “የተከበረች” እንድትሆን እንዳደረገቻት ይነገራል፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ መንገድ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ከቁጥር 27 እስከ 29 ውስጥ ክርስቶስ የቤተክርስቲያን መጋቢና ተንከባካቢ እንደሆነና ቤተክርስቲያንን የክርስቶስ የ“ክብሩ” ብርሃን አንጸባራቂ ሙሽሪት እንድትሆን እንዴት እንዳደረጋት ጳውሎስ ይናገራል፡፡

እነዚህና ሌሎችም ዝርዝሮች በተለይ ከኤፌሶን ቤተክርስቲያን ጋር ትስስር እንዲኖራቸው ተደርገው ተያይዘዋል፡፡

በመጨረሻ፣ በርካታ ቀደምት የቤተክርስቲያን አባቶች ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለኤፌሶን እንደጻፈ መስክረዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የአሌክሳንድሪያው ክሌመንት፣ በሁለተኛው ምዕተ ዓመት ማብቂያ ላይ “The Instructor” በተሰኘው ሥራው ምዕራፍ 5 ውስጥ እንዲህ ጽፏል፡

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍ፣ ከጥያቄ ውስጥ ገብተው የነበሩ ጉዳዮችንና ያስከተሉትን ተፅእኖ ደግሞም ልንሆን የተገባውን ጥርት ባለ መንገድ እንዲህ ተናግሯል፡፡

ክሌመንት ይህንን መግቢያውን አስከትሎ ያስቀመጠው በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁጥር 13 እስከ 15 ያለውን ምንባብ ነው፡፡

በተመሳሳይ መንገድ፣ ተርቱሊያንም፣ በሦስተኛው ምዕተ ዓመት መግቢያ ላይ በጻፈው እና “Against Marcion,” በተሰኘው አምስተኛ መጽሐፉ ምእራፍ 17 ውስጥ እንዲህ ብሏል፡

ይህ መልእክት ለኤፌሶን ሰዎች እንጂ፣ ለሎዶቂያውያን እንዳልተላከ፣ ከቤተክርስቲያን እውነተኛ ትውፊት ውስጥ እናገኛለን፡፡

እንደ ተርቱሊያን አገላለጽ፣ ከዚያን ወቅት ቀደም ብለው የተላለፉ የቤተክርስቲያን ትውፊቶች በጠቅላላ መልእክቱ ለኤፌሶን ሰዎች መላኩን አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን የተርቱሊያንን ሃሳብ የተቃወመ አንድም የቀደመችው ቤተክርስቲያን ምስክርነት አልተገኘም፡፡ በአጭሩ፣ ይህ መልእክት በኤፌሶን በምትገኘው ቤተክርስቲያን እንዲነበብ ዓላማ አድርጎ እንደጻፈው ለማመን የሚስችለን ጠንካራ ማስረጃ አለ፡፡

በኤፌሶን የምትገኘው ቤተክርስቲያን የጳውሎ ተቀዳሚ ተደራሲ የመሆኗን ማስረጃ ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ወደ ሌሎቹ ተደራሲያን፣ በተለይም በሊከስ ሸለቆ ወደነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ትኩረታችንን ዘወር እናደርጋለን፡፡

ሌሎች ተደራሲያን

በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በርካታ አብያተክርስቲያናት በሊከስ ሸለቆ ውስጥ ነበር ያደጉት፡፡ በቆላስይስና በሎዶቅያ ከተሞች አብያተክርስቲያናት እንደነበሩ እናውቃለን፣ እናም በሂሪያፖሊስም ቤተክርስቲያን ልትኖር እንደምትችል መገመት ምክንያታዊ ነው፡፡ ምንም እነዚህ አብያተክርስቲያናት ጳውሎስ ለኤፌሶን በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ ባይጠቀሱም፣ በሚጽፍበት ወቅት እነዚህም አብያክርስቲያናት በልቡናው ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠርጠር ምክንያታዊ ነው፡፡

በሊከስ ሸለቆ ይገኙ የነበሩ አብያተክርስቲያናት የጳውሎስ ሌሎች ተደራሲያን ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክቱንን ሁለት ዓይነት ማስረጃዎችን እንጠቅሳለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ እምብዛም ለማያውቃቸው ተደራሲያን ጽፏል የሚለው ማስረጃ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ በሊከስ ሸለቆ ለሚገኙ አብያተክርስቲያናት ይህ ደብዳቤ የሚኖረው አግባብነት ነው፡፡ አስቀድመን የጳውሎስ ሌሎች ተደራሲያን ከእርሱ ጋር እምብዛም ትውውቅ ያልነበራቸው ናቸው የሚለውን ሃሳብ በመመልከት እንጀምር፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁጥር 15 ጳውሎስ የተናገረውን አስቀድመን እንመልከት፡

ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ (ኤፌሶን 1፡15)

ተደራሲያኑ የነበራቸውን እምነት እርሱ ራሱ በአካል ተገኝቶ ያልተመለከተው መሆኑን የሚያስረዳና በግልጥ የተቀመጠም ክፍል አለ፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ቁጥር 2 እና 3 ተመሳሳይ ሃሳብ እናገኛለን፡፡

ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤

አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ (ኤፌሶን 3፡2-3)

ተደራሲያኑ እርሱ ስለሚሰብከው ወንጌል ያወቁት፣ ቀደም ብሎ ስላስተማራቸው ሳይሆን፣ በዚሁ ደብዳቤው የመጀመሪያ ምዕራፎች ስለ ወንጌሉ ስለጻፈላቸው እንደነበር ጳውሎስ ይገልጣል፡፡ ሆኖም ግን፣ ጳውሎስ የኤፌሶንን ሰዎች በግንባር አስተምሯቸው ነበር፡፡

ጳውሎስ ለበርካታ በአካል ለማያውቃቸውም ሰዎች እንደጻፈ የሚያመለክተን ሌላው አመላካች ሃሳብ በደብዳቤው ውስጥ ምንም ግለሰባዊ ማጣቀሻ አለመኖሩ ነው፡፡ በተቀሩት የእርሱ መልእክቶች ውስጥ፣ በግል የሚያውቃቸውን ተደራሲኑን በመጥቀስ ይጽፍ ነበር፣ ለአብነት ብንጠቅስ፡

ከተደራሲኑ መካከል በአካል የሚያውቃቸውን ግለሰቦች ስም፣

ለተወሰኑ ሰዎች ሰላምታ እንዲቀርብለት፣

ከአንባቢዎቹ ጋር ያሳለፈውን ጊዜ በመጥቀስ፣

የታወቁ የአድራሻ መግለጫዎችን፣ ለምሳሌ፣ “ወንድሞች” የሚለውን ቃል ለአንባቢዎቹ መጥቀሱ፣

ለአንባቢዎቹ ያለውን ፍቅር የሚያንጸባርቅበት መግለጫ፣

የአንባቢዎቹ “መንፈሳዊ አባት” እንደሆነ ራሱን የሚገልጥበት መግለጫዎች ይገኙባቸዋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተካተቱት መልእክቶች መካከል አንድም ግለሰባዊ ማጣቀሻ የሌለው፣ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ ብቻ ነው፡፡ ይህ ግን በኤፌሶን ከምትገኘው ቤተክርስቲያን ጋር እጅግ በጣም ጥብቅ ግንኙት የነበረው መሆኑን ሳይነካ ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተን ደብዳቤው በኤፌሶን ቤተክርስቲያን መጀመሪያ ከተነበበ በኋላ፣ ወደ ተለያዩ አብያተክርስቲያናት እንዲዘዋወር ከዚያም አልፎ ከእርሱ ጋር ትውውቅ ወደሌላቸው አብያተክርስቲያናትም እንዲዘልቅ ጳውሎስ ይፈልግ እንደነበር ነው፡፡

የጳውሎስ ተደራሲያን ከእርሱ ጋር የማይዋወቁትንም እንደሚጨምር ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ በሊከስ ሸለቆ የሚገኙትን አብያተክርስቲያናት ማለትም የቆላስይስን፣ የሎዶቂያንና ኢያራን የሚያካትት የመሆኑን ማስረጃ እንመልከት፡፡

ከሊከስ ሸለቆ ጋር ያለው ግንኙነት የሚገናኘው ከፓውሎስ ወዳጅ ከቲኪቆስ ጋር ነው፡፡ እንደ ኤፌሶን ምዕራፍ 6 ከቁጥር 21 እስከ 22 እና ቆላስይስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 7 እና 8 አገላለጥ፣ ቲኪቆስ ቢያንስ ሁለት ደብዳቤዎችን ለጳውሎስ እንዳደረሰለት እረዳለን፡፡ ማለትም፡ አንዱ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን፣ ሌላው ደግሞ ለቆላስይስ ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ ሁለቱንም በተመሳሳይ ጊዜ እንዳደረሳቸው ሁኔታው ያሳያል፡፡ በተጨማሪም፣ ጳውሎስ ለሎዶቂያ ቤተክርስቲያንም ደብዳቤ ጽፏል፣ ሆኖም ደብዳቤው አልተገኘም፡፡

ጳውሎስ ለሎዶቂያ ቤተክርስቲያን ስለ ጻፈው ደብዳቤ በቆላስይስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 16 እንዲህ ጽፏል፡-

ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ። (ቆላስይስ 4፡16)

ጳውሎስ ለሎዶቂያ የጻፈውን ደብዳቤም ቲኪቆስ ሊያደርሰው እንደሚችል መገመት ምክንያታዊ ነው፡፡ እንግዲህ ሁለቱም አብያተክርስቲያናት ሁለቱንም ደብዳቤዎች እንዳነበቡ ማረጋገጥ የሚቻልበት ተመራጭ መንገድ ይህ ነው፡፡ ደግሞም የኤፌሶንን መልእክት ቅጂ እንዲያነብቡ ይዞላቸው ሊሄድ እንደሚችል ማሰብም ምክንያታዊ ነው፡፡

ጳውሎስ በሊከስ ሸለቆ ይገኙ የነበሩ አብያተክርስቲያናትም የኤፌሶንን መልእክት እንዲያነብቡ ዓላማ እንደነበረው እንድናስብ የሚያደርገን ሌላው ምክንያት እነዚያ አብያተክርስቲያናት በጳውሎስ እሥራት ወቅት በልቡናው ትልቅ ስፍራ የነበራቸው መሆኑ ነው፡፡ በቆላስይስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 1 የጻፈውን እናድምጥ፡

ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ሁሉ እንዴት ያለ ትልቅ መጋደል እንዳለኝ ልታውቁ እወዳለሁና፤ (ቆላስይስ 2፡1)

ጳውሎስ በቆላስይስ ስለነበረው የሐሰት ትምህርት ስጋት ይዞት ነበር፣ ከዚህም የተነሳ በሎዶቂያ፣ ደግሞም በአካባቢው በሚገኙም አብያተክርስቲያናት ተመሳሳይ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉም ያምናል፡፡

ለምሳሌ፣ ጳውሎስ በቆላስይስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 12 እና 13 ውስጥ የኢያራን ቤተክርስቲያን ጠቅሷል፡

ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።

ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና። (ቆላስይስ 4፡12-13)

ጳውሎስ የኢያራን ቤተክርስቲያን መጥቀሱ በዚያ የተደራጀች ቤተክርስቲያን እንደነበረች ያሳያል፡፡ እንድምታውም በሊከስ ሸለቆ የሚገኙ አብያተክርስቲያናት ኤጳፍራ ከጳውሎስ ጋር እንዲቆይ በአንድት ይጸልዩለት የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ ኤጳፍራ አብያተክርስቲያናቱን ወክሎ እንዲገኝ ፈልገው ነው፡፡

ጳውሎስ በሊከስ ሸለቆ ስለነበሩት አብያተክርስቲያናት የነበረው ሸክም እንደሚያሳየን፣ እነርሱን ለማገልገል የሚያስችለውን አጋጣሚ ፍጹም ቸል አይለውም፣ በተለይ ቲኪቆስ ይዞ የሚሄደውን አንድ የደብዳቤ ግልባጭ ማዘጋጀት ብቻ ሲሆንማ እድሉን ፈጽሞ አያሳልፈውም፡፡

የኤፌሶን መልእክት በሊከስ ሸለቆ የነበሩትን አብያተክርስቲያናትንም ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን እንድናስብ የሚስገድደን አንድ ምክንያት የኤፌሶንና የቆላስይስ መልእክቶች የሚዳስሱት ተመሳሳይ ችግሮችን መሆኑ ነው፡፡ እንግዲያው፣ የኤፌሶን መልእክት በሊከስ ሸለቆ ይገኙ ለነበሩ አብያተክርስቲያናትም አግባብነት አለው ብሎ መናገር ሚዛናዊነት ነው፡፡ ማስረጃ እንዲሆነን አንድ ምሳሌ እንጠቅሳለን፡፡

ቀደም ባለው ትምህርታችን እንዳየነው፣ የቆላስይስ ሰዎች አጋንንቶችን ከሚያመልኩና ከሚያከብሩ የሐሰት መምህራን ጋር እየተፋለሙ ነበር፡፡ ጳውሎስ ይህን የስህተት አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጥረታት ሁሉ ደግሞም በተለይም ከአጋንንት ሁሉ እጅግ የሚልቅ መሆኑን በአጽንዖት በመግለጥ ይፋለመው ነበር፡፡

ለምሳሌ፣ በቆላስይስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 16 ውስጥ፣ ጳውሎስ ኢየሱስን እንዲህ ይገልጠዋል፡

እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ (ቆላስይስ 1፡16)

ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 20 እስከ 22 ክርስቶስን ከገለጠበት ጋር አነጻጽሩት፡

ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤

ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።

(ኤፌሶን 1፡20-22)

በዚህ ምንባብ፣ ለቆላስይስ ከተጻፈው እንደምናነብበው፣ ጳውሎስ archē (avrch,), እና exousia (evxousi,a) የተሰኙ የግሪክ ቃሎችን ተጠቅሟል፣ በኤፌሶን ደግሞ አለቅነትና ሥልጣን ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ሁለቱም የሚያመለክቱት መንፈሳዊ አካላትን ነው፡፡ ከዚያም kuriotēs (kurio,thj) የሚለውን ቃል በድጋሚ የተጠቀመ ሲሆን፣ ይህም ለሰብዓዊ መሪዎች ወይም መላእክትን እና አጋንንትን ለመሳሰሉ መንፈሳዊ አካላትም ይጠቀሳል፡፡ በመጨረሻም፣ ጳውሎስ dunamis የተሰኘውን የግሪክ ቃል ሲጠቀም በዚህ ስፍራ የብርታቱ ጉልበት ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ምንም እንኳን dunamis የሚለው ቃል “ብርታት” ወይም “ችሎታ” ለሚለው ቃል ጥቅም ላይ ቢውልም፣ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበረው ጁዳይዝም ይህንን ቃል ራሳቸውን ከሰይጣን ጋር አሰልፈው እግዚአብሔርን ለሚዋጉ አጋንንቶች ተጠቅሞበታል፡፡

ቲኪቆስ እንደ ጳውሎስ መልእክተኛ የነበረው ድርሻ፣ ጳውሎስ በሊከስ ሸለቆ ለሚገኙ አብያተክርስቲያናት የነበረው ሸክም፣ ደግሞም በኤፌሶን እና በቆላስይስ መልእክቶች ውስጥ የሚገኙት ተመሳሳይ መሪ ሃሳቦች ጳውሎስ የኤፌሶንን መልእክት ሲጽፍ በሊከስ ሸለቆ ይገኙ የነበሩ አብያተክርስቲያናትንም በልቡናው አድርጎ ነበር የሚለውን እሳቤ ያጸኑልናል፡፡

የጳውሎስ ቀደምት ተደራሲን የኤፌሶን ሰዎች ደግሞም በሊከስ ሸለቆ የሚገኙ አብያተክርስቲያናት ናቸው የሚለውን ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ የጻፈበትን ዓላማ በጥልቀት ወደ መመልከቱ እንሸጋገራለን፡፡ ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ መላክ ለምን አስፈለገው?

ዓላማ

በመደበኛነት ጳውሎስ ይጽፍ የነበረው፣ በአንድ አካባቢ ወይም አጥቢያ የሚገኙና እርሱ በአካል በሚያውቃቸው ሰዎች መካከል ለተከሰቱ ችግሮች መልሰ ለመስጠት ነው፡፡ በኤፌሶን ግን፣ ለየት ያለ ነገር አድርጓል፣ ያም በተለያየ ስፍራ የሚገኙ አብያተክርስቲያናት ለገጠሟቸው ችግሮች ምላሽ ሰጥቷል፣ ከእነዚህም ብዙዎቹን በአካል አያውቃቸውም፡፡

እንግዲህ፣ ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈበት ዓላማ የእነዚያን አብያተክርስቲያናት ችግር ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ የተጠቀመበት ስልት ግን፣ ለእያንዳንዳቸው ጉዳዮች በተናጠል ምላሽ መስጠትን አይደለም፡፡

የጳውሎስን ዓላማ የምንዳስስበት ውይይታችን በሁለት ክፍሎች ይከፈላል፡፡ አንደኛ፣ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ የዳሰሰውን የእግዚአብሔርን መንግሥት መሪ ሃሳብ እንዳስሳለን፡፡ ሁለተኛ፣ ቤተክርስቲያን የገጠሟትን ተግዳሮቶች ከእግዚአብሔር መንግሥት አንጻር ጳውሎስ እንዴት እንደተጋፈጣቸው እንመለከታለን፡፡ አስቀድመን የእግዚአብሔርን መንግሥት መሪ ሃሳብ እንመልከት፡፡

የእግዚአብሔር መንግሥት

አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን መንግሥት በአራቱ ወንጌላት፤ በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ እና በሉቃስ ከተገለጸው ጋር ያዛምዱታል፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር መንግሥት የሚለው ሃሳብ ለጳውሎስም ወሳኝ መሪ ቃል ነው፡፡ በመልእክቶቹ ውስጥ ለዐሥራ ስድስት ጊዜያት በቀጥታ የእግዚአብሔርን መንግሥት የጠቀሰ ሲሆን፣ ሌሎች ንጉሣዊ ቃላትን ደግሞ ደጋግሞ አንስቷል፡፡

ቀደም ባለው ትምህርታችን፣ የጳውሎስ ነገረ-ፍጻሜ ማለትም የመጨረሻው ዘመን አስተምህሮው የአስተሳሰቡ ማዕከል ስለመሆኑ አጽንዖት ሰጥተን ተመልክተናል፡፡ ጳውሎስ፣ ክርስቶስ የታሪክ ሁሉ ፍፃሜ መሆኑን የተረዳ ሲሆን፣ ይህንንም በምድር አገልግሎቱ ጀምሮታል፣ በቤተክርስቲያን ዘመን ቀጥሎታል በዳግመኛ የድል አድራጊነት ምፅአቱ ደግሞ ወደ ፍፃሜ ያመጣዋል ይላል፡፡ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሥራ ሲናገር አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቅሰው አሁን በምንኖርበት የኃጢአትና የሞት ዘመን እና ሊመጣ ባለው እግዚአብሔር በረከትንና መርገምን ወደ ሙላት በሚያመጣበት ዘመን መካከል ያለውን ድርርቦሽ በመጥቀስ ነው፡፡

ኢየሱስና የወንጌላት ጸሐፍት ስለሚመጣው ዘመን ሲናገሩ፣ በጥቅሉ የሚገልፁት ከእግዚአብሔር መንግሥት አንፃር ነው፡፡ የሚመለከቱትም የእግዚአብሔር መንግሥት በሰማይ እንደሆነች በምድር ከምትሆንበት አንፃር ነው፡፡ ጳውሎስም በዚህ ሃሳብ ይስማማል፡፡

ከዚህ አንፃር፣ በጳውሎስ አስተሳሰብ ውስጥ የነበረውን የመንግሥተ እግዚአብሔር አስተሳሰብ የተጋነነ ነው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲያውም፣ የጳውሎስ ወዳጅና የጉዞ ባልደረባ የነበረው ሉቃስ እንደጠቀሰው፣ ስለ እግዚብሔር መንግሥት መስበክ የጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት ማዕከል ነበር፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 28 ቁጥር 30 እና 31 ሉቃስ የጻፈውን እናድምጥ፡

ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤

ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 28፡30-31)

ጊዜውን በጥያቄ ውስጥ እናስቀምጠውና፣ ጳውሎስ በእስር ላይ ነበር፣ ምናልባትም የኤፌሶንን መልእክት የጻፈበት ጊዜና ስፍራ ሳይሆንም አይቀርም፡፡ ሉቃስ በዚህ ስፍራ የጳውሎስን አገልግሎት እንዴት እንዳስቀመጠው ልብ በሉ፡፡ ጳውሎስ “ወንጌልን“ ሰበከ ከማለት ይልቅ፣ ጳውሎስ “ስለ እግዚአብሔር መንግሥት” ሰበከ ይለናል ሉቃስ፡፡

በዘመናችን ቤተክርስቲያን፣ ሰዎች ወንጌልን ወይም የምሥራቹን ቃል የአንድ ሰው ኃጢአት ይቅር ከመባሉ እና ያ ሰው የዘላለም ሕይወት ከማግኘቱ ጋር ያስተሳስሩታል፡፡ አዎን ልክ ነው፣ እነዚህ የተስፋችን ደንቅ ገጽታዎች ናቸው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን፣ ወንጌል ፈለካዊ ድንበር አለው፡፡ መልእክቱም መለኮታዊው ንጉሣችን ኃይሉንና ሥልጣኑን ተጠቅሞ ጠላቶቹን ያንበረክካል ኃጢአትንም ድል ያደርጋል፣ የህዝቡንም ቀንበር ሰብሮ ይዋጃቸዋል በምድርም ላይ እንዲሰለጥኑ ያደርጋል የሚል ነው፡፡ ኢየሱስና የወንጌላት ጸሐፊዎች ደግመው ደጋግመው ስለ “መንግሥቱ ወንጌል” የሚናገሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እናም፣ ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ባህርይ ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍ፣ የወንጌልን ትልቁን ምስል ነው ያሳያቸው ብሎ መናገር አግባብነት አለው፡፡

ምንም እንኳን ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክት ውስጥ የእግዚአብሔርን መንግሥት በቀጥታ የጠቀሰው በጥቂቱ ቢሆንም፣ ደግሞ ደጋግሞ ግን በልዩ ልዩ መንገድ አንስቶታል፡፡ በተጠቀማቸው ቃላቶችም፣ የብሉይ ኪዳኑን መንግሥተ እስራኤልና የዘመኑን የሮሜ መንግሥት ደጋግሞ ጠቅሷል፡፡ እነዚህ ተዛምዶዎች የጳውሎስ ወንጌል የመንግሥቱ ወንጌል፣ በተለይም፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል ስለ መሆኑ የጳውሎስን አንባቢዎች ያሳስባሉ፡፡

በኤፌሶን መልእክት ውስጥ ጳውሎስ የሰዎችን ትኩረት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሳበባቸውን ስድስት መንገዶች እንመልከት፡፡ በመጀመሪያም፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 12 እስከ 19 ጳውሎስ ስለ ዜግነት በጠቀሰው እንጀምር፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ የእግዚአብሔር ህዝብ እንደ መንግሥት የተደራጁ ነበሩ፣ ያም መንግሥት የእስራኤል መንግሥት ነበር፡፡ ንጉሣቸው እግዚአብሔር ሲሆን እነርሱም የመንግሥቱ ዜጎች ነበሩ፡፡ በተመሳሳይም፣ በጳውሎስ ዘመን ከሁሉ የተከበረና እውቅና የተሰጠው ዜግነት የሮሜ ዜግነት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን እንደ “ዜጎች” ሲጠቅሳቸው፣ የአንድ መንግሥት ዜጎች ናችሁ ማለቱ እንደሆነ ተደራሲያኑ ይገነዘባሉ፡፡

ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 14 እስ 18 እና ምዕራፍ 5 ቁጥር 5 ስለ ውርስ ላነሳውም ጽንሰ-ሃሳብ ነገሩ ያው ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ በተስፋዪቱ ምድር የርስት ድርሻ የሚኖራቸው የእስራኤል መንግሥት ዜጎች የሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ በሮሜ ግዛትም፣ የርስት መብት ያላቸው ዜጎቸ ብቻ ናቸው፡፡ በሌላ አባባል፣ የርስት መብቶች የተጠበቁ የሚሆኑት ለመንግሥቱ ዜጎቸ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲያውም፣ ጳውሎስ የእኛን ርስት ከክርስቶስ መንግሥት ጋር በቀጥታ አገናኝቶታል፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ከቁጥር 10 እስከ 18 ጳውሎስ ስለ ውትድርና አገልግሎት የጠቀስነውን ልብ እንበል፡፡ ጦርነት በቀጥታ የሚያያዘው ከመንግሥት ጽንሰ-ሃሳብ ጋር ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ ዕድሜያቸው ለጦርነት የደረሰ ወንዶች ሁሉ በእስራኤል ሠራዊት ውስጥ የማገልገል ግዴታ ነበረባቸው፡፡ በሮሜም ግዛት ውስጥ፣ የውትድርና አገልግሎት የሚሰጡት ዜጎቸ ብቻ ናቸው፡፡ እናም፣ ጳውሎስ የሚያመለክተው፣ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ የመግባታቸው ጉዳይ የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎቸ ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 20 እስከ ምዕራፍ 2 ቁጥር 6 በፍጥረት ላይ ስለመግዛት የተጠቀሰው ሃሳብ ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ ከእስራኤል ላዕላይ ግቦች መካከል አንዱ ግዛቷን በምድር ሁሉ ማስፋፋት ነበር፡፡ በሮሜ ግዛትም ነገሩ እንደዚያው ነበር፡፡ እናም፣ ጳውሎስ አማኞች በፍጥረት ሁሉ ላይ ለመግዛት ከክርስቶስ ጋር ስለመቀመጣቸው ሲያስተምር፣ የሚያመለክተው ክርስቶስ ንጉሥ መሆኑን፣ አማኞች ደግሞ በመንግሥቱ ውስጥ ዜጎችና ባለሥልጣናት መሆናቸውን ነው፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ቁጥር 15 የተጠቀሰው ሃሳብ ስማችን የስርወ ንግሥና ምንጭ እንዳለው ያመለክታል፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ የእግዚአብሔር ህዝብ በእግዚአብሔር ስም ይጠሩ ነበር ምክንያቱም የመንግሥቱ አካላት ነበሩና፡፡

ለምሳሌ፣ በትንቢተ አሞጽ ምዕራፍ 9 ቁጥር 11 እና 12 የተጠቀሰውን እናድምጥ፡

በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤

ይኸውም የኤዶምያስን ቅሬታ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይወርሱ ዘንድ ነው፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር፡፡ (አሞጽ 9፡11-12)

ጌታ የዳዊትን ድንኳ ስለማንሣት ሲናገር፣ የዳዊት ዘር በሆነው ንጉሥ አማካይነት የእስራኤልን መንግሥት እንደገና ሲመሠርት የሰብዓዊ ታሪክ ፍፃሜ እንደሚመጣ መናገሩ ነው፡፡ እንደገና የሚመሠረተው የዚህ መንግሥት ዜጎች ሆነው የሚጨመሩትም በእግዚአብሔር ስም ይጠራሉ ማለት ነው፡፡

ስያሜ በሮሜ መንግሥት ውስጥም ከመንግሥት ጋር ትስስር አለው፡፡ በተለይም፣ በግዛቱ ውስጥ የዜግነት መብት ያገኙ የዜግነት መብት እንዲኖራቸው በደገፋቸው ሰው ስም ወይም ዜግነቱን ባጸደቀላቸው በንጉሡ ስም የመጠራታቸው ነገር በይፋ ይታወቃል፡፡ በሁለቱም መንገዶች፣ በሌላው ስም መጠራት መንግሥቱን የመቀላቀል ጽንሰ-ሃሳብ ነው፡፡

በመጨረሻም፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 20፣ ጳውሎስ ራሱን እንደ እግዚአብሔር አምባሳደር ይጠቅሳል፡፡ በብሉይም ሆነ በሮሜ መቼቶች ውስጥ፣ አምባሳደር የንጉሡ ወይም የአፄው ኦፊሴላዊ ወኪል ነው፡፡

በእነዚህና በሌሎችም በርካታ መንገዶች፣ በዚህ ደብዳቤው የሚዳስሰው ሰፊው ሃሳብ ከመንግሥተ-እግዚአብሔር ጽንሰ-ሃሳቡ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑን ጳውሎስ ገልጧል፡፡

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው ደብዳቤው የዳሰሰውን የመንግሥተ-እግዚአብሔር ጽንሰ-ሃሳብ ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ጳውሎስ የዳሰሳቸውን የመንግሥቱን ተግዳሮቶች ወደ መመልከቱ እንሸጋገራለን፡፡

ተግዳሮቶች

በኤፌሶን እና በሊከስ ሸለቆ የምትገኘውን ቤተክርስቲያን የሚገዳደሩትን በርካታ ፈተናዎች ጳውሎስ የዳሰሰ ቢሆንም፣ ካለን ጊዜ አንጻር ሦስቱን ብቻ እንጠቅሳለን፡፡ እነርሱም፣ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ ሆኖ ኃጢአትን እንድናደርግ የሚገፋፋን እና ከ“አዲሱ ሰው” ጋር የሚፋለመው “አሮጌው ሰው”፤ በአይሁድና በአህዛብ ክርስቲያኖች መካከል ያለው የዘር ውጥረት እና አጋንንታዊ ኃይላት ናቸው፡፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ ስለ ኃጢአተኛ ተፈጥሯችንና ኃጢአት ስለ ነገሠበት ልማዳችን ሲጽፍ፣ ያቀረበው በመንግሥታዊ ቋንቋ ሲሆን፣ ትምህርቱም ኃጢአት የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች መለያ አይሆንም የሚል ነው፡፡

ለምሳሌ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ቁጥር 5 ውስጥ፣ ጳውሎስ እንዲህ ጽፏል፡

ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። (ኤፌሶን 5፡5)

የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች ክርስቶስን ሊታዘዙ አሊያም ላይታዘዙ ይችላሉ፡፡ ቢታዘዙ፣ ለንጉሣቸው ታማኝ ቢሆኑ፣ የቃል ኪዳኑን በረከቶች ማለትም የኃጢአትን ይቅርታ እና የዘላለምን ሕይወት ይቀበላሉ፡፡ ዜጋው ክርስቶስን ቢክድ፣ በንጉሡና እርሱ በሰጠው የድነት ስጦታ ቢያምፅ ግን፣ ያ ሰው በክርስቶስ መንግሥት ምንም ድርሻ አይኖረውም፡፡

ሁለተኛ፣ ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ውስጥ በአይሁድና በአህዛብ ክርስቲያኖች መካከል የነገሠውን የዘር ውጥረት ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠት የተጠቀመው የእግዚአብሔርን መንግሥት መግለጫ ነው፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 11 እስከ 13 የተናገረውን አድምጡ፡

ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤

በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።

አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። (ኤፌሶን 2፡11-13)

በዚህ ስፍራ፣ ጳውሎስ “ያልተገረዙ” አህዛብ አንባቢዎቹን በክርስቶስ ከማመናቸው በፊት የነበሩበትን ሁኔታ ክርስቶስን ካመኑ በኋላ ካላቸው ሁኔታ ጋር ያነጻጽረዋል፡፡ ወደ እምነት ከመምጣታቸው አስቀድሞ፣ የእስራኤል ማለትም በምድር የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች ሳይሆኑ እንግዶች ነበሩ፡፡ አህዛብ ወደ እምነት ሲመጡ ግን፣ የመንግሥቱ ሙሉ ዜጎች ይሆናሉ፡፡

ጳውሎስ በተጨማሪም የሚጠቅሰው አህዛብ ከተስፋው ቃል ኪዳን ውጪ ነበሩ ብሎ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ቃልኪዳኖች፣ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የተፈፀሙ ብሔራዊና አምላካዊ የቃል ኪዳን ትስስሮች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በምድር የምትገኘውን መንግሥቱን የሚያስተዳድርባቸው ህጋዊ ድንጋጌዎች ነበሩ፡፡ አህዛብ በክርስቶስ አማካይነት ወደ መንግሥቱ ሲጨመሩ ግን፣ ከእነዚህ ብሔራዊ የቃል ኪዳን ውሎች ሥልጣን ስር ይሆናሉ፡፡ በውጤቱም፣ የቃል ኪዳኑ በረከቶች ተካፋዮች ይሆናሉ፡፡

ጳውሎስ ቤተክርስቲያንን ከዜግነትና ከቃል ኪዳን አንጻር ሲገልጽ ቤተክርስቲያንን እንደ እግዚአብሔር መንግሥት እየገለጸ ነው ማለት ነው፡፡ በአጭሩ፣ ጳውሎስ እያስተማረ ያለው፣ አይሁድና አህዛብ እርሰ በርሳቸው ታርቀዋል ምክንያቱም አሁን ሁለቱም የአንድ መንግሥት ዜጎች ናቸውና፡፡

በመጨረሻ፣ ጳውሎስ የመንግሥቱን ቋንቋ የተጠቀመው ቤተክርስቲያንን እየተገዳደሩ ያሉትን አጋንንታዊ ኃይላት ጉዳይ ለመዳሰስ ነው፡፡

ቀደም ባለው ትምህርት እንዳየነው፣ በሊከስ ሸለቆ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሐሰት አስተማሪዎች እየታወኩ ነበር፡፡ የሐሰት መምህራኑ የግሪክን ሃይማኖትና የአይሁድን ህግጋት የተሳሳተ ፍቺ በመዋስ ክርስቲያኖች የተለያዩ መንፈሳዊ ኃይላትን፣ አጋንንቶችንና የፍጥረተ-ዓለሙን ቁሳዊ ነገሮች ማለትም፤ ምድርን፣ አየርን፣ ውሃን እና እሳትን ጨምሮ እንዲያመልኩ ያበረታቱ ነበር፡፡ ጳውሎስ እነዚህን አጋንንቶችና መሠረታዊ ቁሶችን ከእግዚአብሔር መንግሥት ነገረ-መለኮቱ አንጻር በተለያዩ መንገዶች ዳስሷቸዋል፡፡ ከሁሉ ግልጽ የሆነው ግን በኤፌሶን 2 ቁጥር 1 እና 2 የሚገኘው ነው፡፡

በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። (ኤፌሶን 2፡1-2)

አጋንንቶች የራሳቸው መንግሥት አላቸው ይላል ጳውሎስ፣ ያንንም የአየር ላይ መንግሥት ይለዋል፡፡ ይህ መንግሥት የሚያስተዳድረው ገዢ ወይም ንጉሥ አለው፡፡ ከተቀሩት ቅዱሳት መጻሕፍት እንደምንረዳው፣ ክፉው መንፈስ ሰይጣን ነው፡፡ የጳውሎስ ደብዳቤ በቤተክርስቲያንና በሰይጣን መንግሥት መካከል ያለውን ፍልሚያ በሁለት መንግሥታት መካከል እንደሚካሄድ ጦርነት መግለጡ አያስደንቅም፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 12 የተናገረውን አድምጡ፡

መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። (ኤፌሶን 6፡12)

ቤተክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር መንግሥትነቷ በሰይጣንና በአጋንንቶቹ ከሚመራው ከጨለማው መንግሥት ጋር ፈለካዊ ውጊያ ላይ ናት፡፡

የጳውሎስ ቀደምት ተደራሲያን ከግለሰብ ኃጢአት አንስቶ እስከ ዘር ውጥረት፣ ከዚያም እስከ ጣዖት እና አጋንንት አምላኪነት የሚዘልቅ እጅግ በርካታ እና መጠነ ሰፊ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ጳውሎስ እነዚህን ፈርጀ ብዙ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የመረጠው ፍቱን መንገድ ሁሉንም ከአንድ መሪ ሃሳብ ጋር በማዛመድ ማፈራረስን ነው፡፡ ስለዚህ፣ ሁሉንም ሁሉን በሚዳስሰው እና ፈለካዊ እውነታ ባለው በክርስቶስ በተገኘው የእግዚአብሔር መንግሥት ብርሃን በመዳሰስ፣ ተደራሲያኑ እግዚአብሔር ያጠናቀቀውን ትልቁን ምስል እንዲያዩ ያደርጋል፡፡

ጌታ ህዝቡን አዲስ አድርጎ ፈጥሯል፣ የመንግሥቱን ዜግነት ሰጥቷቸዋል፣ ስለዚህም እነርሱ ዳግመኛ የኃጢአተኛ ተፈጥሯቸው ወይም የሰይጣን መንግሥት ተገዢዎች አይሆኑም፡፡ እርስ በርሳቸው ተዋህደውና ተቀባብለው እንዲኖሩ፣ የመንግሥቱ በረከቶች ተካፋዮች እንዲሆኑ ጠርቷቸዋል አስችሏቸዋልም፡፡ ደግሞም አጋንንታዊ ባላጋራዎቻቸውን እንዲዋጉም አስታጥቋቸዋል፡፡

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን መንግሥት መሪ ሃሳብ በእነዚህ ጉዳዮች አንጻር በማንሳት፣ የመጀመሪያዎቹ አብያተክርስቲያናት የክርስትናን ሕይወት በጥቅሉ እንዴት እንደሚቀበሉ እና በፍቅርና በመሰጠት እንዴት እንደሚኖሩበት መንገዱን አሳይቷቸዋል፡፡

አወቃቀርና ይዘት

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን መልእክት ዳራ ስንመረምር ቆተናል፣ አሁን ደግሞ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን መልእክት አወቃቀርና ይዘት ወደ መዳሰሱ እንሸጋገራለን፡፡

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈው መልእክት በአምስት ዋና ክፍሎች ይከፈላል፡ በምዕራፍ 1 ቁር 1 እና 2 የሚገኘው ሰላምታ፤ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 3 እስከ 14 የሚገኘው ለእግዚአብሔር የቀረበ ምሥጋና፤ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 15 እስከ 23 ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የሚጸልየው የዘወትር ጸሎት ማብራሪያ፤ በምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 20 የሚዘልቀው የብርሃንን እና የጨለማን መንግሥታት ያነጻጸረበት ዋናው አካል፤ በምዕራፍ 6 ከቁጥር 21 እስከ 24 የሚገኘው የመጨረሻ ሰላምታ ናቸው፡፡

ሰላምታ

ሰላምታው የሚገኘው በምዕራፍ 1 ቁጥር 1 እና 2 ላይ ነው፡፡ ደብዳቤው ከጳውሎስ የተላከ መሆኑን እና የሐዋርያነትን አገልግሎት የተቀበለውም “በእግዚአብሔር ፈቃድ” መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚለው መግለጫ ጳውሎስን የእግዚአብሔር ህጋዊ ወኪል ያደርገዋል፣ ስለዚህም ጳውሎስ የሚጽፋቸው ቃላት መለኮታዊ ሥልጣን የተሸከሙ ናቸው ማለት ነው፡፡ ሰላምታው የሚጠናቀቀው በተለመደው የሰላምታ አዘጋግ በአጭር ቡራኬ መልክ ነው፡፡

ምሥጋና

ለአግዚአብሔር የሚቀርበው ምሥጋና ቀጥሎ የሚመጣ ሲሆን፣ የሚገኘውም በምዕራፍ 1 ከቁጥር 3 እስከ 14 ውስጥ ነው፡፡ ከጳውሎስ መልእክቶች መካከል ሰላምታውን ተከትሎ ለእግዚአብሔር ምስጋና የቀረበበት መልእክት ይህኛው ብቻ ነው፡፡ በተለመደው መንገድ፣ ጳውሎስ ሰላምታውን አስከትሎ ይጽፍ የነበረው አንዳንድ ግለሰቦችን ወይም ለሰዎች ሰላምታን ነበር፡፡ እንደተመለከትነው በኤፌሶን መልእክት ግን ስለማንም ወይም ስለምንም የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

ጳውሎስ ለምን ግላዊ ሰላምታን እንዳላካተተ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ምናልባት በየስፍራው እየተዘዋወረ ለሚነበብ ደብዳቤ የምሥጋናው ክፍል ይበልጥ አስፈላጊ ይሆን ይሆናል፡፡ ምናልባትም ደግሞ ቀጥሎ ለሚያነሳው አስትምህሮአዊ ጉዳይ ምቹ መደላድል ሊያስቀምጥ ፈልጎ ይሆናል፡፡ አንዳንዶች ይህንን ክፍል በተከታታይ በሚመጡት ሦስት ምዕራፎች የሚያነሳው የጸሎት ሃሳብ መነሻ ነው ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በጥንታዊው ዓለም በመደበኛ ኢፊሴላዊ ደብዳቤዎች ለንጉሡ ውዳሴ ማቅረብ የተለመደ ከመሆኑ ጋር ያያይዙታል፡፡ በየትኛውም መንገድ፣ ጳውሎስ ደብዳቤውን በዚህ መንገድ ያቀናበረበት ምክንያት ውስብስብ ነው፡፡ ምናልባት ይህንን ያደረገባቸው በርካታ ምክንያቶቸ ቢኖሩም፣ ከላይ የጠቀስናቸውም የዚያው አካል ናቸው፡፡

ምናልባት ጳውሎስ ይህንን የምሥጋና ክፍል ማካተት የፈለገበትን ምክንያት መረዳት አዳጋች ሊሆን ይችላል፣ ይዘቱን መረዳት ግን ቀላል ነው፡፡ ምናልባትም በሚከተሉት ነጥቦች ላይ በማትኮር መመርመር መልካም ይሆናል፡ በጥቅሶቹ የምናገኘው ጠንካራ ነገረ-ስላሴ፣ ማለትም የአብን፣ የወልድን፣ እና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ በግልጽ ማስቀመጡ፤ በቁጥር ሰባት አፅንዖት የሰጠበት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የተገኘው መዳን፤ በቁጥር 9 የተጠቀሰው የወንጌሉ ምስጢር መገለጥ፤ ከቁጥር 11 እስ 14 የሚገኘው በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታ አማካይነት የተረጋገጠው የወደፊቱ የክብር ተስፋ ናቸው፡፡ እነዚህ ሃሳቦች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

ሆኖም እነዚህን የጳውሎስን የምሥጋና ሃሳቦች የሚያካትት ብቻ ሳይሆን፣ በጳውሎስ ደብዳቤ በዚህኛው ምንባብ ውስጥ የተጠቀሰውን ሃሳብ በበለጠ ጥልቀት የሚያብራራ ሌላ የላቀ ሃሳብ አለ፡፡ ያም ሃሳብ የእግዚአብሔር መንግሥት ሃሳብ ነው፡፡

ለምሳሌ፣ በቁጥር 4 እና 5 ውስጥ፣ ጳውሎስ እግዚአብሔርን ስለ ሉዓላዊ አገዛዙ ያከብረዋል፣ አንዳንድ ሰዎችን ለእርሱ የተለዩ ህዝቦች እንዲሆኑ አስቀድሞ ስለመወሰኑ ያመሰግነዋል፡፡ በቁጥር 9 እና 10 እግዚአብሔር በፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ገዢ ስለመሆኑና በመጨረሻም ሁሉን በክርስቶስ ራስነት ስለመጠቅለሉ ጳውሎስ ምሥጋናውን ያቀርባል፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ ከቁጥር 5 እስከ 7 ውስጥ፣ ለህዝቡ ስላሳየው በጎነት ጳውሎስ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፡፡ እግዚአብሔር ህዝቡን ልጆቹ በማድረግ፣ በመዋጀት እና ይቅር በማለት ምህረቱን ገልጧል፡፡ የጥንት ነገሥታትም ለህዝባቸው ታታላቅ በጎነቶችን ያሳያሉ፣ የእግዚአብሔር በጎነት ግን በምድር ገዢዎች ከሚሰጠው ልግስና እጅግ የላቀ ነው፡፡

በቁጥር 14 ደግሞ፣ በክርስቶስ ስለተገኘው ውርስ ጳውሎስ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፡፡ ይህም አግባብነት የሚኖረው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ነው፣ ምክንያቱም ጳውሎስ በምዕራፍ 5 ቁጥር 5 ውስጥ ውርሳችንን “በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ከሚገኝ ውርስ” ጋር አዛምዶታል፣ የውርስ መብት ያላቸው ደግሞ የመንግሥቱ ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡

ጸሎት

ከመግቢያው ምሥጋና በኋላ፣ የሚቀጥለው ክፍል ጳውሎስ ለአንባቢዎቹ የጸለየው ጸሎት ሲሆን፣ የሚገኘውም በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 15 እስከ 23 ውስጥ ነው፡፡

የጳውሎስ ጸሎት በዋናነት ሦስት ክፍሎች አሉት፡ ስለሚጽፍላቸው ሰዎች ያቀረበው ምሥጋና፣ መንፈስ ቅዱስ አብርሆትን እንዲሰጣቸው ያቀረበው መንታ ልመና፤ ስለሚለምነው አብርሆት ተጨማሪ ማብራሪያ ናቸው፡፡

የጰውሎስ ጸሎት፣ ቀደም ብለን በተመለከትነው የምሥጋና ክፍል ውስጥ የተነሱ ሃሳቦችን ደግሞ ያነሳል፡፡ በቁጥር 17 ያነሳው ጠንካራ ነገረ-ስላሴ፣ ማለትም የአብን፣ የወልድን፣ እና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ በግልጽ ማስቀመጡ፤ በቁጥር 19 እና 20 አፅንዖት የሰጠበት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የተገኘው መዳን፤ ከቁጥር 17 እስከ 19 የሚገኘው የወንጌሉ ምስጢር ይበልጥ እንዲገለጥላቸው የለመነበት ዋነኛ የልመናው ክፍል ሲሆን ያም አብርሆት አማኞች የሚቀበሉትን በረከት በትክክል እንዲገነዘቡ የሚያስችላቸው ብርሃን ነው፡፡ በቁጥር 18 ደግሞ ወደፊት ስለሚጠብቀን የክብር ተስፋ ይናገራል፡፡

ልክ እንደ ምሥጋናው ክፍል ሁሉ፣ በስፋት የተቀመጠው የእግዚአብሔር መንግሥት ሃሳብ የጠቀስናቸው ሌሎች ሃሳቦች የተቀመጡበትን አውድ ያመለክተናል፡፡

በጳውሎስ ምሥጋና ውስጥ የተጠቀሰውን የእግዚአብሔርን መንግሥት መሪ ሃሳብ ስንመረምር፣ በሦስት ዝርዝሮች ላይ እናተኩራለን፣ እርሱም፣ ኃይሉንና ሥልጣኑን አጣምሮ የያዘውን፣ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ አገዛዝ፤ ለእኛ እንዲያው የሰጠንን መልካም ነገሮች ሁሉ ያካተተውን፣ የእግዚአብሔርን ደግነት፤ እግዚአብሔር ለህዝቡ የሰጣቸውን የቃል ኪዳን በረከቶች የያዘውን፣ በክርስቶስ ያገኘነው ውርስ ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት የመንግሥቱ ውቅረ-ነገሮች በጸሎቱም ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት የጠቀሰው በቁጥር 19 ውስጥ ስለ አብ “ወደር የማይገኝለት ታላቅ ኃይል” እና “ታላቅ ብርታት” ሲናገር፣ ደግሞም በቁጥር 21 ውስጥ ክርስቶስ ከአለቆችና ከሥልጣናት ሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ባለ ዙፋን ስለመቀመጡ ሲናገር ነው፡፡

ጳውሎስ በቁጥር 19 ውስጥ የእግዚአብሔር ኃይል “ለእኛ ለምናምን” መሆኑን ሲጠቅስ ስለ በጎነቱ ተናግሯል፣ ደግሞም በቁጥር 22 እና 23 ውስጥ ክርስቶስ በንግሥና የሚገዛው ስለ ቤተክርስቲያን ጥቅም መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

በመጨረሻም፣ በቁጥር 18 ውስጥ፣ ጳውሎስ ቅዱሳን ስለተጠሩበት ተስፋ ማለትም ክርስቶስ “በቅዱሳኑ ውስጥ ስላለው የርስት ክብር ባለጠግነት” በቀጥታ ተናግሯል፡፡ የክርስቶስ ርስት ተስፋችን መሆኑን ጳውሎስ ሊናገር የቻለበት ምክንያት፣ በደብዳቤው ዋና አካል ውስጥ እንደሚያስተምረው፣ ክርስቶስ እኛን የርስቱ ተካፋዮች አድርጎናል፣ ስለዚህ የእርሱ ርስት የእኛም ርስት ስለሆነ ነው፡፡ በተጓዳኝም ይህ ሃሳብ፣ በዘዳግም ምዕራፍ 9 ከቁጥር 26 እስከ 29 ከሚገኘው የብሉይ ኪዳን የታወቀ ሃሳብ ጋርም ይስማማል፣ ያም የእስራኤል መንግሥት የእግዚአብሔር ርስት ነው፣ እናም የመንግሥቱ ዜጎች በዚህ ምክንያት የዚህ ታላቅ በረከት ተካፋዮች ይሆናሉ የሚለው ነው፡፡

ዋናው አካል

በጳውሎስ ምሥጋናና ጸሎት ውስጥ ተቀመጠውን የመንግሥቱን ትኩረት ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ከምዕራፍ 2 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 20 ወደሚገኘው የመልእክቱ ዋና አካል እንሸጋገራለን፡፡ አካሉ የሚያተኩረው ጽድቅ የነገሠበትን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድ ወገን በማድረግና ኃጢአት የነገሠበትን የአጋንንቶችና የወደቀውን የሰውን ዘር መንግሥት በሌላ ወገን አድርጎ በማነፃፀሩ ላይ ነው፡፡

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን መልእክት ዋና አካል በበርካታ መንገዶች ማዋቀር ይቻላል፡፡ በዚህ ትምህርታችን ልንዳስሰው ካሰብነው ትኩረት አንፃር ግን፣ አወቃቀራችን አጽንዖት የሚሰጠው የዋናው አካል መሪ ሃሳቦች ከእግዚአብሔር መንግሥት ርዕሰ-ጉዳይ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ በማሳየቱ ላይ ነው፡፡ ዋናውን አካል በሦስት ተቀዳሚ ክፍሎች እንከፋፍለዋለን፡፡ አንደኛ፣ በምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 22 የሚገኘውንና ጳውሎስ በመንግሥቱ ውስጥ ስለሚገኘው ዜግነት ያስተማረውን ትምህርት፤ ሁለተኛ፣ በምዕራፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ 21 የሚገኘውንና ስለ መንግሥቱ አስተዳደር የሰጠውን ማብራሪያ፤ ሦስተኛ ደግሞ፣ ከምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 20 የሚገኘውንና በመንግሥቱ ውስጥ ስለሚኖረው የአኗኗር ዘይቤ የገለጸበትን ክፍል ይሆናል፡፡ ሁሉንም ነጥቦች ዘርዘር አድርገን የምንመለከት ሲሆን፣ በመጀመሪያ በምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 22 የሚገኘውን በመንግሥቱ ውስጥ የሚገኘውን ዜግነት እንመልከት፡፡

ዜግነት

ጳውሎስ በእግዚአብሔር የብርሃን መንግሥት ውስጥ ስለሚገኘው ዜግነት ያስተማረው ትምህርት በሦስት ክፍሎች ይከፈላል፡፡ አንደኛ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 3 የወደቁት የሰው ልጆች በጨለማው መንግሥት ውስጥ የተወለዱ እና ከፍጥረታቸውም የእግዚአብሔር ጠላቶች በመሆናቸው ላይ ያተኩራል፡፡ ሁለተኛ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 4 እስከ 10 እግዚአብሔር እኛን ከጨለማው መንግሥት ወደ ብርሃን መንግሥት በማፍለስ የመንግሥቱን የዜግነት መብት የሰጠባቸውን መንገዶች ያብራራል፡፡ ሦስተኛ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 11 እስከ 22 በብርሃን መንግሥት ውስጥ የተቀበልነው ዜግነት ያሉትን ባህርያት ያወሳል፡፡

በመጀመሪያ፣ የሰው ዘር ኃጢአተኛና የወደቀ እንደሆነ ጳውሎስ ለተደራሲያኑ ማሳሰቢያ ይሰጣል፡፡ በመንፈስ ሙታን ነበርን፤ ፍጥረታችን የጥፋት ልጅነት ነበር፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች አገልጋዮች ነበርን፤ ስለዚህም በፍርድ ቀን ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች እንሆናለን፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 3 የወደቀውን የሰው ዘር የገለጸበትን መንገድ እስኪ እናድምጥ፡

በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።

በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። (ኤፌሶን 2፡1-3)

የወደቀው የሰው ዘር የእግዚአብሔር ጠላቶች ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ሳያድነን በፊት፣ ኃጢአተኛ ተፈጥሯችንን በፈቃዳችን እንከተል ነበር፣ ደግሞም የአየሩን መንግሥት አለቃ፣ ሰይጣንን እናገለግል ነበር፡፡

በዚህ ትምህርት ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ግን፣ እግዚአብሔር በሉዓላዊ ሥልጣኑ አንዳንዶች ድነትን እንዲቀበሉ ወሰነ፡፡ እናም፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 4 እስከ 10፣ እግዚአብሔር ንጉሣዊ ሥልጣኑን በመጠቀም ከጨለማው መንግሥት ወደ ብርሃን መንግሥት እንዳሸጋራቸው ወደሚያስረዳው ጭብጥ ጳውሎስ ትኩረቱን ዘወር ያደርጋል፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ፣ መንፈሳችንን አደሰ፣ ስለዚህም እኛ በመንፈስ ሕያዋን ሆንን፡፡ በክርስቶስም ዳግመኛ ወለደን፣ ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔርን የሚወድድ አዲስ ማንነት አገኘን፡፡ ልናደርግ የተገባንን መልካም ሥራ አስቀድሞ ወሰነ፣ በመሆኑም እኛ የእግዚአብሔርን ጠላቶች ማገልገላችንን አቁመን እግዚአብሔርን እናገለግላለን፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ ከእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ይልቅ በሚመጣው ዘመን የምንቀበለውን ወደር የማይገኝለትን ባለጠግነት እንጠባበቃለን፡፡

ጳውሎስ በዚህ ክፍል ያነሳው የመጨረሻ ርዕስ አይሁድንና አህዛብን በአንድ የእግዚአብሔር ሉዓላዊ አገዛዝ ስር ለማድረግ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን አቅዶት የነበረውን ሃሳብ እንዴት እንደፈጸመው ማመለክት ነው፡፡ ይህ ሃሳብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከጫፍ እስ ጫፍ ተገልጧል፡፡

ለምሳሌ፣ በመዝሙር 22 ቁጥር 27 እና 28 ውስጥ፣ ወደፊት የምትመጣውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ራእይ ዳዊት እንዲህ አስቀምጦታል፡

የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሱ፤ የአሕዛብ ነገዶች ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ።

መንግሥት ለእግዚአብሔር ነውና፥ እርሱም አሕዛብን ይገዛል። (መዝሙር 22፡27-28)

ሆኖም ግን፣ በጳውሎስ ዘመን፣ የአህዛብ ክርስቲያኖች ቁመና ጉዳይ እጅጉን አወዛጋቢ ነበር፡፡ ሁሉም አይሁድ ክርስቲያኖች በጥቅሉ አህዛብ መለወጣቸውን አይቃወሙም፡፡ አንዳንዶቹ ግን አህዛብ ሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች ናቸው የሚል ስሜት አላቸው፡፡

ክርስቶስ ከመምጣቱ አስቀድሞ፣ አይሁዳውያን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለየት ያለ ስፍራ ነበራቸው፡፡ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ህዝብ የነበረው የእስራኤል ህዝብ ነበር፣ የቃል ኪዳኑን የተሟላ በረከት የሚቀበሉትም ነፃ የሆኑት አይሁዳዊ ወንዶች ናቸው፡፡ ይህንን የብሉይ ኪዳንን እምነት ጳውሎስ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በአዲስ ኪዳን፣ በሐዋርያት ዘመን ግን፣ ሁሉም አማኞች አይሁድም ሆኑ አህዛብ፣ ወንድም ሆኑ ሴት፣ ባሪያም ሆኑ ጨዋ ከክርስቶስ ጋር በመተባበራቸው ብቻ የቃል ኪዳኑን ዘላለማዊ በረከቶች ይቀበላሉ፡፡ በክርስቶስ፣ እያንዳንዱ አማኝ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ጠንቅቆ እንደጠበቀ፣ የቃል ኪዳኑንም በረከቶች ሙሉ በሙሉ እንደወረሰው እንደ ኢየሱስ ይቆጠራል፡፡

በውጤቱም፣ በአይድና በአህዛብ መካከል የነበረው አሮጌ የጥል ግድግዳ ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ እያንዳዱ ሰው ድነትን በተመሳሳይ መንገድ በመቀበሉ ምክንያት፣ አዲሱ ስርዓት ለእያንዳንዱ ዜጋ፣ ዘሩ ምንም ይሁን ምን የሚሰጠው ስፍራና መብት እኩል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ የብርሃኑ መንግሥት ዜጎቸ በጠቅላላ ወደ እግዚአብሔር የመግባትን መብት ጨምሮ የሁሉም መብቶችና ትሩፋቶች እኩል ተካፋይ ሆናሉ፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 13 እስከ 19 እንዲህ ጽፏል፡

አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል።

እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥

ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።

መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤

በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።

እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። (ኤፌሶን 2፡17-19)

በእግዚአብሔር የብርሃን መንንግሥት ውስጥ ዜጋ የመሆንን ሃሳብ ስንመለከት ቆይተናል፣ አሁን ደግሞ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ 21 ውስጥ ስለ መንግሥቱ አስተዳደር ወደሰጠው ትምህርት እንሸጋገራለን፡፡

አስተዳደር

አንድ መንግሥት አንድ ዓይነት የአስተዳደር አወቃቀር እንደሚኖረው ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ መንግሥታት ንጉሥና የዜግነት ጉዳይ ብቻ ቢኖራቸው ተግባራቸውን በአግባቡ ሊወጡ አይችሉም፡፡ ንጉሡ መንግሥቱን የሚያስተዳድርባቸው ሌሎች መንግሥታዊ ቢሮዎች ያስፈልጉታል፡፡ በተለይም በሰብዓዊ መንግሥታት ውስጥ፣ እነዚህ ቢሮዎች በተለያዩ የአመራር መዋቅሮች ይደራጃሉ፡፡ ለምሳሌ ህግ አውጪዎች፣ ህግ አስፈጻሚዎችና በህግ ተላላፊዎች ላይ ፍርድ የሚበይኑትን ያካትታል፡፡ በእግዚአብሔር የብርሃን መንግሥትም ነገሩ እንደዚያው ነው፣ ይህም በቤተክርስቲያን ውስጥ በተግባር ተገልጦ የምናየው ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በሽማግሌዎች እንድትመራ፣ ሽማግሌዎቹም እርስ በርስና ለእግዚአብሔር ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡

በጳውሎስ ዘመን፣ የሐሰት መምህራን የቤተክርስቲያንን የሥልጣን አወቃቀር እጅግ ይፈታተኑ ነበር፡፡ እንዲያውም፣ ጳውሎስ በኢሩሳሌም ከመያዙ አስቀደሞ፣ ከመካከላቸው የሐሰት መምህራን እንደሚነሱ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች አስጠንቅቆ ነበር፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 20 ከቁጥር 28 እስከ 30 ጳውሎስ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች የተናገረውን ሉቃስ እንዲህ ዘግቦታል፡

በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ። (ኤፌሶን 20፡28-30)

የሐሰት መምህራን እንደሚነሱና ቤተክርስቲያንን እንደሚያውኩ፣ ጳውሎስ ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ፣ ሽማግሌዎች መንጋውን ከእነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች እንዲጠብቁ ያዝዛቸዋል፡፡

ጳውሎስ ይህንን አደራ ለሽማግሌዎች የመስጠት እና የሐሰት መምህራንን የማውገዝ ሥልጣን ማን ሰጠው? በጳውሎስ ዘመን፣ እግዚአብሔር መንግሥቱን ያስተዳድርበት የነበረ የቤተክርስቲያን ቢሮ ነበር፣ ያም ቢሮ መሠረታዊ ቢሮ ነበር፣ ያ ቢሮ ግን ዛሬ የለም፡፡ ያም ቢሮ የሐዋርያ ቢሮ ነው፡፡ እነዚያም ሰዎች በእግዚአብሔር በራሱ በቀጥታ የተመረጡና የተጠሩ ደግሞም ከሞት የተነሣውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የተገናኙ፣ እንደ ጳውሎስ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያት ሽማግሌዎችንም ጨምሮ በቤተክርስቲያን ውስጥ የማይሻር የእግዚአብሔር ሥልጣን ነበራቸው፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ከቁጥር 2 እስከ 7 ድረስ፣ ጳውሎስ የሐዋርያነት ሥልጣኑን ከእግዚአብሔር መንግሥት አስተዳደር ጋር በተዛመደ መንገድ ገልጾታል፡፡ እስኪ የተናገረውን እናድምጥ፡

ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤

አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤

ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤

ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም።

እንደ ኃይሉ ሥራ እንደ ተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን የወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት። (ኤፌሶን 3፡2-7)

ሐዋርያት በአገልግሎታቸው የሚያስታጥቃቸው ልዩ ጸጋ ከእግዚአብሔር የተቀበሉ ሲሆን፣ ሊሻር የማይችልንም እውነት ከእግዚአብሔር በልዩ መገለጥ ተቀብለዋል፡፡ ከእርሱ ያገኙትንም መገለጥ ለቤተክርስቲያን እንዲያስተምሩ ከእግዚአብሔር አደራ ተቀብለዋል፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስ እንደ ሐዋርያ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ህግጋት ለዜጎቹ የማብራራት እና ከዚያ በተቃራኒው የሚቆሙትን የማውገዝ ግዴታም መብትም ነበረው፡፡

እግዚአብሔር ጳውሎስን በምድር የእርሱ ህጋዊ ወኪል፣ ሐዋርያ እንዲሆን ሾሞታል፡፡ ይህም የሐዋርያነት ሥልጣኑ የጳውሎስ ቃል ልክ በእግዚአብሔር እንደተነገረ ያህል ሥልጣን እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ግን የጳውሎስ የሐዋርያነት ሥልጣን ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ለምን ወሳኝ ሆነ? በቀላሉ ለማስቀመጥ፣ ቤተክርስቲያን ማንን ልታምን እንደሚገባ ማወቅ ስለሚገባት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ልናሰኘው ከፈለግን፣ ልናውቅ የተገባንን ማወቅ ደግሞም እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ በጳውሎስ ዘመን ግን፣ በእርግጥ የእግዚአብሔር መመዘኛዎች የትኞቹ ናቸው ብሎ ለመለየት በሚያዳግት መጠን በርካታ የሐሰት አስተምህሮዎች ተስፋፍተው ነበር፡፡ የሐሰት መምህራኑ አንድ ነገር ይናገራሉ፣ በቤተክርስቲያን የተደራጀው አመራር ደግሞ ሌላ ነገር ይናገራል፡፡

ጳውሎስ ይህንን ችግር የፈታው ሐዋርያዊ ሥልጣኑን በመጠቀም ነው፡፡ ሐዋርያ በመሆኑ፣ የእርሱ ሥልጣንና የሚያነሳቸው ሃሳቦች ከሌሎቹ ሁሉ የበላይ እንደሆነ አንባቢዎቹን ያሳስባቸዋል፡፡ ማንም የሐሰት አስተማሪ ሐዋርያ ነኝ ሊል አይችልም፡፡ እናም የትኛውም የሐሰት አስተማሪ የጳውሎስን ዓይት መገለጥ ሊኖረው ወይም በመለኮታዊ ሥልጣን ሊናገር አይችልም፡፡ በሌላ ጎን ጳውሎስ ግን፣ የእግዚአብሔርን ህዝብ ወደ እውነት ለመምራት፣ የእግዚአብሔርን ቃል፣ ለእግዚአብሔር ህዝብ ይናገራል፡፡

ጳውሎስ ስለ መንግሥቱ አስተዳደር ያቀረበው ትምህርት የሚጠናቀቀው ሥልጣኑን በማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ጥበብ በተሞላበት መንገድ በጸሎት ነበር፡፡ ይህም በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ከቁጥር 14 እስከ 21 ይገኛል፡፡ ጳውሎስ ለረጅም ዘመን ሚሲዮናዊ፣ መጋቢ እና ሐዋርያ ሆኖ ያገለግል ነበር፣ ምክንያቱም ሰዎች ወንጌልን ስለሰሙ ብቻ ሊያውቁትና ሊቀበሉት እንደማይችሉ ስለሚረዳ ነው፡፡ የሕይወት ቃል በእጁ እንዳለ ያውቃል፣ ሆኖም የወደቀው የሰው ዘር እንዲያምንበት የማድረግ አቅም በራሱ እንደሌለውም ያውቅ ነበር፡፡ እናም ስለዚህ፣ መንፈሰ ቅዱስ አዕምሯቸውን እንዲያበራ፣ የእርሱን ሥልጣንና ትምህርት እንዲቀበሉ እንዲረዳቸው ይጸልይ ነበር፡፡ አከታትሎም፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት በሚገነባ መንገድ እንዲኖሩ ይጸልይላቸውና ዜጎቹንም ይባርክ ነበር፡፡

የዜግነትንና የአስተዳደርን ሃሳብ ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር በተያያዘ መንገድ ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ በብርሃኑ መንግሥት ውስጥ ሊኖርበት የሚገባውን የአኗኗር ዘይቤ ወደ መመልከቱ እንሸጋገራለን፣ የሚገኘውም በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 20 ድረስ ነው፡፡

የአኗኗር ዘይቤ

በመንግሥቱ ውስጥ የሚኖረው ይህ የአኗኗር ዘይቤ ስለ ክርስቲያናዊ ባህርይ የሚናገሩ በርካታ መመሪያዎችን ያካተተ ነው፡፡ ሆኖም ግን በሚከተለው መንገድ ጠቅለል ብሎ ይቀርባል፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 16 ስለ መንግሥቱ ቤተክርስቲያናዊ አስተዳደር፤ በምዕራፍ 4 ከቁጥር 17 እስከ ምዕራፍ 5 ቁጥር 20 ስለ መንግሥቱ መንፃት፤ በምዕራፍ 5 ከቁጥር 21 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 9 ስለ ቤተሰባዊ አስተዳደር እና በመጨረሻ፣ በምዕራፍ 6 ከቁጥር 10 እስከ 20 ስለ መንግሥቱ ውጊያ ተጽፎ እናብባለን፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 16 የሚገኘው የመንግሥቱ አስተዳደር ክፍል፣ በተቀዳሚነት የሚያተኩረው በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኘው የአመራር ተዋረድ፣ ተጽዕኖና ሥልጣን ላይ ነው፡፡ የጳውሎስ አስተምህሮም አጽንዖት የሚሰጠው እነዚህ ሃላፊነቶች ለሁሉ ጥቅም ተቀናጅተው ሥራ ላይ በሚውሉባቸው መንገዶች ላይ ነው፡፡ ዜጎች አርስ በርሰ መቀናናት የለባቸውም፣ ይልቁኑ ወንደሞቻቸውና እህቶቻቸው ስለሚያበረክቱት አስተዋፅዖ አድናቆት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የተሰጠውን ሃላፊነት ሲወጣ፣ ለክርስቶስ ጥቅም ይሆናል፡፡ ለክርስቶስ ጥቅም ስለሚሆንም፣ መንግሥቱን በጠቅላላ ይጠቅማል፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ቁጥር 8 ጳውሎስ በዚህ ረገድ የተናገረውን እንመልከት፡

ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። (ኤፌሶን 4፡8)

በዚህ ምንባብ፣ ጳውሎስ ያጣቀሰው በመዝሙር 68 ቁጥር 18፣ ጌታ ከውጊያ በድል እንደሚመለስ ንጉሥ የተገለጸበትን ክፍል ነው፡፡ በመዝሙር 68፣ ጌታ ድል ካደረጋቸው ጠላቶቹ ምርኮን እንደሚቀበል ተልጧል፡፡ ሆኖም፣ ጳውሎስ የሚያተኩረው ጌታ እነዚህን ስጦታዎች አስመልክቶ ባደረገው ነገር ላይ ነው፡፡ ልክ እንደ ጥንት ነገሥታት፣ ለሠራዊቱ ያካፍላል፡፡ እናም፣ በእውነተኛው መረዳት፣ እነዚህ ስጦታዎች የሚጠቅሙት ክርስቶስን ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥቱ ያለውን ህዝብ በጠቅላላ ነው፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁር 7 እስከ 12 ጳውሎስ ከእነዚህ ስጦታዎች ጥቂቶቹን ይጠቅሳል፡

ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን።

ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።

ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው?

ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።

እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤

ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። (ኤፌሶን 4፡7-12)

ክርስቶስ ስጦታዎቹን ያከፋፈለው የመንግሥቱ ዜጎች አንዳቸው ሌላቸውን ለማገልግል እንዲያስችላቸው አድርጎ ነው፡፡ እናም በዚህ አገልግሎት የክርስቶስ መንግሥት ትበዛለች ትጠነክርማለች፡፡

ምዕራፍ 4 ቁጥር 17 እስከ ምዕራፍ 5 ቁጥር 20 የሚያብራራው የብርሃኑን መንግሥት በውስጡ ቅሪት ሆኖ ከተቀመጠው ርኩሰት ስለሚያነፃበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ርኩሰት ወይም ኃጢአት፣ እኛ አስቀድሞ በሰይጣን የጨለማ መንግሥት ውሰጥ በነበርንበት ወቅት በውስጣችን ይሰፋና ያድግ የነበረ ነው፡፡ ይህም አሁን የብርሃኑ መንግሥት ዜጎች ሆነንም እንኳን በውስጣችን ብቅ የሚል የአሮጌው፣ ኃጢአተኛ ተፈጥሯችን ውጤት ነው፡፡ ሆኖም በእምነት በብርሃኑ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩ ግን ኃጢአትን ድል ማድረግ የሚችሉበት አዲስ ተፈጥሮ ተቀብለዋል፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁጥር 22 እስከ 24 ጳውሎስ እንዲህ ጽፏል፡

ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥

በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥

ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። (ኤፌሶን 4፡22-24)

በተቻለ መጠን የእግዚአብሔር መንግሥት ንጽህናው የተጠበቀ ሊሆን ይገባል፤ ማለትም የንጉሡን ባህርይ ሊያንጸባርቅ ግድ ነው፡፡ ይህም ለጠቅላላው ለመንግሥቱ ጥቅም ነው፡፡ እግዚአብሔር ግብረገባዊ ንጽሕናን ይባርካል ይሸልማልም፡፡ ስለዚህም፣ ከኃጢአት በመራቅ፣ መልካሙንም ሥራ በመሥራት፣ ዜጎቹ የመንግሥቱን ብሩክነት ማብዛት ደግሞም ውርሳቸውን ማጽናት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በብርሃኑ መንግሥት ውስጥ የቤተሰባዊ አስተዳደር ጉዳይ የተዳሰሰው በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ከቁጥር 21 እስከ ምዕራፍ 6 ቁጥር 9 በሚገኘው ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ይህ ክፍል በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የሥልጣን አወቃቀር እና እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ባለው የሥልጣን አወቃቀር መሠረት እርስ በርስ እንዴት ግንኙነት ሊያደርግ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡

ይህ ክፍል በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 16 ከተጠቀሰው ከጳውሎስ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ትምህርት ጋር ይስማማል፡፡ በዚህ ክፍል፣ ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ውስጥ በአመራር ስፍራ ላይ የተቀመጡትን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን እያንዳንዱ ሰው ሊያከብራቸውና ሊታዘዛቸው እንደሚገባ ያስተማረ ሲሆን፣ በሥልጣን ላይ ያሉትም ሥልጣናቸውን ለሁሉ ጥቅም እንዲያውሉትም አስተምሯል፡፡

ቤተሰባዊ አስተዳደር በሚዳሰስበት በዚህ ክፍል፣ በባልና በሚስት፣ በወላጆችና በልጆች፣ በጌቶችና በባሮች መካከል ላለው የሥልጣን አወቃቀር ጳውሎስ እውቅና ይሰጣል፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥ ያለ እያንዳንዱ አባል ሁሉንም አካላት በሚያከብርና ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ያስተምራል፡፡ በድጋሚ፣ የዚህ ምክንያቱ እነዚህ ተዋረዶች በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሕይወት እንዲትረፈረፍ ስለሚያደርጉ ነው፡፡

በመጨረሻ፣ በምዕራፍ 6 ከቁጥር 10 እስከ 20 ጳውሎስ በበብርሃን መንግሥትና በጨለማው መንግሥት መካከል ስለሚካሄደው ውጊያ ይናገራል፡፡ በዚህ ስፍራ ጳውሎስ፣ በብርሃኑ መንግሥት ውስጥ ተካፋይ የሆነ የትኛውም ሰው በእግዚአብሔር ሠራዊት ውስጥ እንዲያገለግል እና ከጨለማው መንግሥት ጋር በሚካሄደው መንፈሳዊ ውጊያ ተሳታፊ እንዲሆን መጠራቱን ያመለክታል፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 11 እና 12 ውስጥ የሚገኘውን የመልእክቱን ዋና አካል፣ ጳውሎስ ያጠቃለለው እንዲህ ብሎ ነው፡

የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።

መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።

ዲያቢሎስና የእርሱ መንግሥት በቤተክርስቲያንና በብርሃኑ መንግሥት ላይ ጦርነት ከፍተዋል፣ መለኮታዊ ንጉሣችንም በውጊያው ውስጥ በታማኝነት እንድንሳተፍ ይጠብቅብናል፡፡ ጠላቶቻችንን በጽናት በመቆም እንድንፋለም ሊያስችለንም፣ የእርሱን የጦር እቃ አስታጥቆናል ቃሉንም የማጥቂያ ሰይፍ አደርጎ ሰጥቶናል፡፡

የመጨረሻ ሰላምታ

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ የመጨረሻ ክፍል ስንብት ሲሆን፣ የሚገኘውም በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ከቁጥር 21 እስከ 24 ውስጥ ነው፡፡ በአጭሩ በዚህ ምንባብ ውስጥ፣ ጳውሎስ የመዝጊያ ቡራኬውን ያቀርባል፣ ደብዳቤውንም ቲኪቆስ እንደሚያመጣላቸው ይናገራል፡፡

ዘመነኛው ተዛምዶ

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ ዳራ መርምረናል፣ አወቃቀሩንና ይዘቱን ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ ጳውሎስ አስቀድሞ ለኤፌሶን ሰዎች ልኮት የነበረውን ትምህርት ዘመነኛ ተዛምዶ ወደመመልከቱ እንሸጋገራለን፡፡

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ ተዛምዶአችን በሦስት ክፍሎች ይከፈላል፡፡ ይህም ጠበብ ካለው ሰፋ ወዳለው የእግዚአብሔር መንግሥት ጽንሰ-ሃሳብ ይዘልቃል፡፡ በመጀመሪያ፣ ንጉሡን ስለማክበር እንነጋገራለን፡፡ ሁለተኛ፣ መንግሥቱን ስለ መገንባት እንወያያለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ፍጥረተ ዓለምን ድል የመንሣትን ርዕሰ-ጉዳይ እንዳስሳለን፡፡ አስቀድመን ንጉሡን የማክበርን ርዕስ በመመልከት እንጀምር፡፡

ንጉሡን ማክበር

እንደተመለከትነው፣ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ እግዚአብሔር በፍጥረት ሁሉ በተለይም በመንግሥቱ ህዝብ ላይ መለኮታዊ ንጉሥ የመሆኑን ሃሳብ በጽኑ ያነሳል፡፡ መለኮታዊ ንጉሣችንም ለእኛ እጅግ ብዙ አስደናቂ ነገሮችን አደርጎልናል ስለዚህ እኛም እርሱን በምሥጋና፣ በመታዘዝና በታማኝነት በማክበር ምላሽ ልንሰጠው ይገባል፡፡

እንግዲህ አሁን፣ ጥንታዊው ማኅበረሰብ ስለ ነገሥታትና ስለ ህዝባቸው የሚነጋገሩትን በልቡናው በመያዝ፣ ጳውሎስ እግዚአብሔር “ከፍቅር” አንፃር ለእኛ ያደረገውን ንጉሣዊ በጎነት ይገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ፣ ከእኛ የሚጠበቀውንም ግዴታ ይገልፃል፡፡ ለምሳሌ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 4 እስከ 7 ጳውሎስ የተናገረውን እናድምጥ፡

ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥

ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥

በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። (ኤፌሶን 2፡4-7)

ይህ ክፍል እግዚአብሔር እኛን እንዴት የመንግሥቱ ዜጎች እንዳደረገን ጳውሎስ ያቀረበው ረዘም ያለ የመከራከሪያ ሃሳብ አንጓ ነው፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ያነሳው ነጥብ እግዚአብሔር ዳግም ልደት ሲሰጠን፣ ወደ መንግሥቱ ሲያፈልሰን፣ የሥልጣንና የክብር ስፍራን ሲሰጠን የርስቱም ተካፋይ ሲያደርገን ፍቅሩን ገልጦልናል የሚል ነው፡፡

በጥንታዊው ዓለም፣ ነገሥታት በግዛቶቻቸው ስር ላሉ ፍቅራቸውን ይገልጣሉ፣ ተገዦዎቻቸውም በምላሹ እንዲወድዷቸው ይጠብቃሉ፡፡ በዚህ ብሔራዊነት በሚንጸባረቅበት አውድ ውስጥ፣ “ፍቅር” የሚለው ቃል ዛሬ በዚህ ዘመን እኛ አገራችንን እንወድዳደለን ብለን እንደምንናገረው ዓይነት የታማኝነትና የመሰጠት መግለጫ ነው፡፡ በተጨማሪም ንጉሡ በበኩሉ በጎነቱንና ጥበቃውን ሲገልጽ፣ በግዛቱ ስር የሚገኙት ደግሞ በመታዘዝና በታማኝነት የድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡

ጳውሎስ እግዚአብሔር ለህዝቡ ያለውን ፍቅር የገለጠው ልክ ይህንን በሚመስል አገላለጽ ነው፡፡ የወንጌል ታሪካዊ እውነታዎች እንደሚያረጋግጡት እግዚአብሔር በመንግሥቱ ውስጥ ለሚገኙት ህዝቡ ራሱን ሰጥቷል፣ ደግሞም ለእኛ ከፍ ያለ ዋጋ ሰጥቶናል፡፡ እርሱ ለእኛ ያለው ታማኝነት በቸርነቱ እና በጥበቃው የተገለጠ ሲሆን ይህም አስቀድሞ በመወሰናችን፣ ክርስቶስ ስለ እኛ በመሞቱ፣ ለመንፈሳችን ዳግመኛ ልደትን በመስጠቱ፣ በመንግሥቱ ዜጎች በማድረጉ፣ ከሰማያዊ ንጉሣችን ከክርስቶስ ጋር እኛን ተካፋይ በማድረጉ እና ወደፊት ክብርን እንድንለብስ በማድረጉ ውስጥ ታይቷል፡፡ እናም እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ አስደናቂ ነገሮች ለእኛ በማድረጉ፣ እኛም በምላሹ እርሱን ልናከብረው ግድ ይለናል፡፡

ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ከቁጥር 17 እስከ ምዕራፍ 4፡1 የተናገረውን እናድምጥ፡

በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥

ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ።

እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥

ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ (ኤፌሶን 3፡17-4፡1)

ጳውሎስ በዚህ ምንባብ ውስጥ ከእግዚአብሔር ፍቅር አንጻር ሁለት የተዛምዶ ሃሳቦችን አውጥቷል፡፡ በመጀመሪያ፣ ለእግዚአብሔር ልባዊ አድናቆት የሞላበት ምሥጋና በማቅረብ ለእርሱ ክብርን ይሰጣል፡፡ ሁለተኛ፣ አንባቢዎቹ ደግሞ ተገቢ በሆነ ኑሮ እና በመታዘዝ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ ጳውሎስ ያሳስባል፡፡

እግዚአብሔርን ልናከብርባቸው የሚገቡንን እነዚህን ሁለት መንገዶች በጥልቀት የምንመለከት ሲሆን፣ ለእርሱ ልናቀርብ በሚገባን ምሥጋናና አምልኮ እንጀምራለን፣ ከዚያም ለእርሱ ልናሳይ ወደሚገባን የመታዘዝ ሕይወት እንሸጋገራለን፡፡ አስቀድመን ምሥጋናና አምልኮን እንመልከት፡፡

ምሥጋናና አምልኮ

ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ቁጥር 19 እና 20 ውስጥ፣ አንባቢዎቹ እግዚአብሔርን በምስጋናና በአምልኮ እንዲያከብሩት እንዲህ በመጻፍ በቀጥታ ያዝዛቸዋል፡፡

በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤

ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ። (ኤፌሶን 5፡19-20)

እግዚአብሔር ስለሚሰጠን በረከቶች ክርስቲያኖች ዘወትር አመስጋኞች ሊሆኑ ይገባል፡፡ ልባዊ ምሥጋናችንንም፣ በመዝሙር፣ በቅኔ፣ በመንፈሳዊ ዝማሬዎች፣ እና በሙዚቃ ልናቀርብ ይገባናል፡፡ ሌሎች እየሰሙም በከፍተኛ ድምጽ ብናቀርባቸው፣ ወይም በልባችን ለጌታ ብቻ ብናቀርባቸው ሁሉም ምሥጋናና አምልኳችን የሚቀርብባቸው መንገዶች ናቸው፡፡

ጳውሎስ እግዚአብሔርን እንድናመሰግን ከማዘዝም ባሻገር፣ የተለያዩ የምስጋና አቀራረብ ምሳሌዎችንም አቅርቦልናል፡፡ ለምሳሌ፣ በምእራፍ 1 ከቁጥር 3 እስከ 14 ያቀረበው የመግቢያ ምሥጋና እና በምዕራፍ 3 ከቁጥር 14 እስከ 21 ያቀረበው የውዳሴ ጸሎት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱም ምንባቦች በተመሳሳይ ምሥጋናና አደናቆት እግዘአብሔርን እንዴት ልናከብር እንደምንችል ያሳዩናል፡፡

እንደተመለከትነው፣ በሁለቱም ክፍሎች ውስጥ፣ ጳውሎስ በእያንዳንዳቸው የስላሴ አካላት ሥራ ላይ አተኩሯል፡፡ ማለትም፣ የኢየሱስን ቤዛነት፣ ለእኛ የእግዚአብሔር መገለጥ እና እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀው የወደፊት ክብር ናቸው፡፡ እነዚህንም ነገሮች የጠቀሳቸው በእኛ ላይ ስለተገለጠው ንግሥናው እግዚአብሔርን ልናከብረው እንደሚገባ በገለጸበት አውድ ውስጥ ሲሆን፣ ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊ አገዛዝ፣ ለእኛ ስላለው በጎነት እና በክርስቶስ ስምንቀበለው ርስትም በመዘርዘር ነው፡፡

እግዚአብሔርን ስለ ንጉሥነቱ የምናመሰግንባቸው ተቀባይነት ያላቸው መንገዶች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁኑ፣ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ከቁጥር 19 እስከ 20 እንዳስተማረው፣ በእነዚህ ጥቂት ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር እግዚአብሔርን ልናከብር ይገባናል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን፣ እግዚአብሔርን በምስጋናና በአምልኮ ስናከብር፣ እርሱ ያደረገልንን አንዳንድ ነገሮች መጠቃቀስ ትክክል ነው፡፡

ከምስጋናና ከአምልኮ ባሻገር፣ መለኮታዊ ንጉሣችንን ለማክበር መታዘዝን አንዱ መገለጫ መንገድ ስለማድረግም ጳውሎስ አስተምሮናል፡፡

መታዘዝ

ለእግዚአብሔር ታዛዥ መሆናችንን የምንገልጽበት አንዱ መንገድ ለእርሱ በቁርጠኝትና በጽናት ታማኝነታችንን በመግለጽ መዝለቅ እና አለቆችንና ሥልጣናትን መካድ ነው፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ከቁጥር 8 እስከ 10 እንዲህ ጽፏል፡

ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤

የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ (ኤፌሶን 5፡8,10)

እኛ አስቀድመን የጨለማው የሰይጣን መንግሥት ዜጎች ነበርን፡፡ አሁን ግን ተገዢነታችን ተለውጧል፡፡ እግዚአብሔር አድኖናል፣ እኛም እንታዘዘዋለን፤ የምንታዘዘውም የጨለማውን መንግሥት የኃጢአት መንገዶች ወዲያ ለመጣልና አዲሱን ጌታችንንና ንጉሣችንን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ለመኖር ነው፡፡

ጳውሎስ በድጋሚ በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 24 በፍቅር ላይ ስለተመሠረተው የተገዢነት በረከት ሲናገር እንዲህ አስቀምጦታል፡

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን። (ኤፌሶን 6፡24)

ለጌታ ያለን ፍቅር “የማይጠፋ” ማለትም፣ ማለቂያ የሌለው፣ የማይዋዥቅ፣ የተሰጠ እና ጽኑ ሊሆን ይገባዋል፡፡

እግዚአብሔር የእኛን ፍፁም የሆነ አምልኮና መሰጠት ይፈልገዋል፡፡ እርሱን ከምናመልካቸው ከዕልፍ አማልክት ጋር ልንደባልቀው አንችልም፤ እርሱ የእኛን ለማንም የማያጋሩት ተገዢነት ይፈልገዋል፡፡ እንደ ነገሩ የሆነ መገዛትን፣ ማለትም ከሐሰት አማልክት ዞር በማለት ወዲያውኑ የእርሱን መንግሥት በረከቶች እንድናፍስ ብቻ አይፈልግም፡፡ እርሱ የሚፈልገው ትዕዛዛቱን እንድናከብር፣ ሌሎች አማልክቶችን ወግዱ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ ለእኛ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ሁሉ ለማድረግ ራሳችንን እንድንሰጥ ነው፡፡

ይህንን አስመልክቶ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 8 እስከ 10 የተናገረው ፍንጭ ይሰጠናል፡

ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤

ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።

እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። (ኤፌሶን 2፡8-10)

እግዚአብሔር ከጥፋት ሊያድነን ብቻ፣ ወይም በእርሱ መንግሥት ውስጥ ተመችቶን እንድንኖር ብቻ አላዳነንም፡፡ ይልቁኑ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት አድርጎናል፣ ስለዚህም በመንግሥቱ ውስጥ ፍሬያማ ዜጎች እንሆናለን፣ እርሱ ለእኛ ያዘጋጀውን መልካሙንም ሥራ እንሠራለን፡፡

በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፣ መልካም ሥራዎች የራሳቸው ድርሻ አላቸው፣ እግዚአብሔር መንግሥቱን የሚያነጻባቸው፣ የሚያሰፋባቸው፣ ክብርን የሚቀበልባቸው እና ለህዝቡ አገልግሎትን የምንሰጥባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ እንደ ጳውሎስ አገላለጽ፣ እግዚአብሔር እኛን ያዳናበት ዓላማ እነዚህን መልካም ሥራዎች ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ለእግዚአብሔር ጸጋ ትክክለኛው ምላሽ እንደ እርሱ ባሪያዎችና አገልጋዮች የተሰጠንን ሃላፊነት መወጣት ነው፡፡ ማለትም፣ የእርሱን ግብ ግባችን ማድረግ እና የእርሱን ዓላማ ዓላማችን ማድረግ ነው፡፡ ተደራሲኑ የተገባ ኑሮ ይህም የንጉሡንና የመንግሥቱን ባህርያት በሚያንጸባርቅ ሕይወት እንዲኖሩ ጳውሎስ ደጋግሞ የሚያሳስበው በዚህ ምንክያት ነው፡፡

ንጉሡን የምናከብርባቸውን ጥቂት መንገዶች ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ፣ መንግሥቱን ለመገንባት ጳውሎስ ወዳመለከተው ስልት እንሸጋገራለን፡፡ እግዚአብሔር ከፍቅር የመነጨ ምስጋናና መታዘዝ እንደሚጠብቅብን ሁሉ፣ ምድራዊ መንግሥቱን ለማስፋትና ለማሳደግ አብረነው እንድንሰለፍም ይጠብቅብናል፡፡

መንግሥቱን መገንባት

የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር እንዴት ልንገነባ እንደምንችል እኛን ለማገዝ፣ ጳውሎስ በርካታ ተለዋጭ ዘይቤዎችን ይጠቀማል፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች እርሰ በርስና ከክርስቶስ ጋር እንዴት ሊገናኙና በመንግሥቱ ውስጥ ለማደግ እንዴት ሊተባበሩ እንደሚገባ እያንዳንዳቸው ትምህርቶችን ያስተምራሉ፡፡ ከእነዚህ ተለዋጭ ዘይቤዎች ሁለቱን እንጠቅሳለን፣ ጳውሎስ መንግሥቱን ከእግዚአብሔር መቅደስ ጋር ባነፃፀረበት እንጀምራለን፡፡

ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 19 እስከ 22 ለአህዛብ ክርስቲያኖች የተናገራቸውን ቃላት እናድምጥ፡

እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም።

በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤

በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤

በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ። (ኤፌሶን 2፡19-22)

አህዛብ ክርስቲያኖች ከአይሁድ ክርስቲያኖች ጋር በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እኩል የዜግነት መብት እንዳላቸው ጳውሎስ ያስተምራል፡፡ ይህንንም እውነታ አጽንዖት ለመስጠት፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከህንፃ ጋር፣ ማለትም እያንዳንዱን ክርስቲያን በህንጻው መዋቅር ውስጥ ከሚገባ ድንጋይ ጋር ያነጻጽረዋል፡፡

በዚህ ተተለዋጭ ዘይቤ፣ ክርስቶስ ከሁሉ የላቀ፣ ሌሎቹ ድንጋዮች ሁሉ የሚገጣጠሙበት የማዕዘን ራስ፣ በእርሱም ህንፃው ሁሉ የተጋጠመበት ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ሐዋርያትና ነቢያት ደግሞ በክርስቶስ ስር ከፍ ያለውን ሥልጣን በመያዝ፣ የእርሱ ወኪሎች ሆነዋል፡፡ ሌሎቹ ክርስቲያኖች በጠቅላላ በመካከላቸው መለያየት ሳይኖር በአወቃቀሩ ውስጥ ድንጋዮች ሆነዋል፡፡

እንግዲህ፣ የዚህ ህንፃ ግቡ የእግዚአብሔር ማደሪያ መሆን ሲሆን፣ ከዚያም የተነሳ እግዚአብሔር በህዝቡ መካከል ይኖራል፡፡ በብሉይ ኪዳን የእስራኤል መንግሥት ይህንን የመሰለውን በረከት ያጣጥሙ ነበር፣ በተለይም ሰሎሞን በ2ኛ ዜና ምዕራፍ 6 እንዳወጀው በኢየሩሳሌም በሚገኘው መቅደስ በሙላት ይገለጥ ነበር፡፡ ብሉይ ኪዳን በተጨማሪም አህዛብም በስተመጨረሻው የእግዚአብሔርን የመገኘቱን በረከት እንደሚካፈሉም ያስተምራል፡፡

ለምሳሌ፣ በኢሳያስ ምዕራፍ 66 ቁጥር 19 እና 20 የእግዚአብሔር ቃል የሚናገረውን እናድምጥ፡

…. በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ። ….

ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ … ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ (ኢሳይያስ 66፡19-20)

በዚህ ምንባብ፣ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት እንደገና ሲመሠርት፣ ያንንም በኢየሱስ አማካይነት በኢየሱስ ጀምሮታል፣ እስራኤላውያን ጌታን ለማምለክ እንደገና ወደ መቅደስ እንደሚመጡ ይናገራል፡፡ አስደንጋጩ ነገር ግን፣ አህዛብም ከእነርሱ ጋር በአንድነት ይመጣሉ፣ እንዲያውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቁርባን ይሆኑ ከመንግሥታት ሁሉ እስራኤላውያንን ወደ እግዚአብሔር ይመልሳሉ፡፡

ስለዚህ ጳውሎስ፣ አህዛብ እና እስራኤል ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ ሆነው በእግዚአብሔር መገኘት ውስጥ ይኖራሉ ብሎ ሲያስተምር፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ መጨረሻው ግቡ እየገሰገሰ ነው ማለቱ ነው፡፡ ይህም ማለት የእግዚአብሔር መንግሥት በረከቶች ወደ ሁሉም የሰው ዘር ይደርሳሉ ማለት ነው፡፡ ጳውሎስ ግን ይህንን ግልጽ ተለዋጭ ዘይቤ ለምን ተጠቀመ? ይህን ያደረገው፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በአይሁድና በአህዛብ መካከል እርቅ መውረዱን በትክክል ለማስተላለፍ ነው፡፡

በጳውሎስ ዘመን፣ አንዳንድ አይሁድ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች ከአህዛብ ይበልጣሉ ምክንያቱም እነርሱ ለእግዚአብሔር የተመረጡ ህዝቦች ናቸው የሚል አስተሳሰብ ያራምዱ ነበር፡፡ ለረጅም ዘመናት ከእግዚአብሔር ዘንድ ለየት ያለ በጎነት ሲቀበሉ ኖረዋል ስለዚህም አሁንም በዚያው መልክ ሊቀበሉ ይገባቸዋል በማለት ማሰብ ጀምረው ነበር፡፡

እውነቱ ግን የሰው ዘር በሙሉ፣ አይሁድም ሆነ አህዛብ፣ ያለ ክርስቶስ ሁሉም የጠፉ መሆናቸው ነው፡፡ ማናችንም ቢሆን የበረከቱን ጥቂት ቁራሽ ማግኘት የሚገባን አይደለንም፤ ሁላችን እርግማን የሚገባን ነን፡፡ በረከቶቹን ሊቀበል የተገባው ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ምሥጋና ይግባውና፣ እኛ ከእርሱ ጋር በመተባበራችን፣ እኛም በረከቱ የሚገባን ሆኖ ተቆጠረልን፡፡ በውጤቱም፣ በክርስቶስ አማካይት፣ አይሁድ በእግዚአብሔር ፊት ለየት ያለ ስፍራ የማግኘታቸው ነገር አበቃ፡፡

ስለዚህ፣ በእኛም ዘመን የእግዚአብሔርን መንግሥት ስለመገንባት ስናስብ፣ እግዚአብሔርን የማክበርን እና በእርሱ መገኘት ውስጥ የመኖርን ደግሞም የራሳችንን ሳይሆን የክርስቶስን ክብር የማስፋትን ትልቅ ምስል ልንጨብጥ ይገባናል፡፡ አንዳችን ለሌላችንም ትኁታን ልንሆንና አንዱ ከሌላው በተሻለ መጠን በረከት ሊቀበል እንደሚገባው ላለማሰብ መጨከን ይገባናል፡፡

ይህም ማለት በቤተክርስቲያን ውስጥ በዘር ምክንያት የሚታየው የዘር እንቅፋት ጨርሶ ሊወገድ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተሳሳተ መንገድ እርስ በርስ ስለመከፋፈላችን ወይም በተሳሳተ መንገድ ራሳቸንን ከፍ በማድረግ ሌሎችን ስለመጉዳታችን ንስሓ ልንገባ ያስፈልገናል፡፡ ምናልባትም የቤተክርስቲያን መሪዎች ከምዕመናኑ ይልቅ ራሳቸውን ከፍ ያደርጉ ወይም ባለጠጋ ክርስቲያኖችን ከድሆቹ ይልቅ የከበሬታ ስፍራ እንሰጣቸው ይሆናል፡፡ ምናልባትም ደግሞ፣ የእኛን አጥቢያ ወይም ቤተእምነታችንን በጣም ከፍያለ ስፍራ በመስጠት በሌላ ቤተክርስቲያን ያሉትን ክርስቲያኖች ዝቅ አድርገን ልንመለከት እና መንግሥቱንም ለመገንባት ከእነርሱ ተገንጥለን ለመገንባት እንሞክር ይሆናል፡፡ ጳውሎስ እንደሚያስተምረን ግን፣ በምንም ይሁን በምን ምክንያት እብሪታችንን እና ትምክህታችንን ወዲያ ጥለን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሁሉን ክርስቲያኖች በእኩልነት ልናቅፍ ይገባናል፡፡

እንግዲህ፣ ስለ መቅደሱ የቀረበው ተለዋጭ ዘይቤ ጠቃሚ የመሆኑን ያህል፣ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከመገንባት አንጻር ደጋግሞ የጠቀሰው ተለዋጭ ዘይቤ አካል ነው፡፡ በተለይም የክርስቶስን አካል፣ ማለትም ክርስቶስ ራስ የሆነበት፣ አባላት ሁሉ ደግሞ በአንድነት የክርስቶስ አካል ክፍል የሚሆኑበት ማለት ነው፡፡ ጳውሎስ ይህንን ተለዋጭ ዘይቤ በምዕራፍ 1፣ 3፣ 4 እና 5 ውስጥ በመጥቀስ የተለያዩ የተዛምዶ ነጥቦችን ከውስጡ ለማውጣት ተጠቅሞበታል፡፡

በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ከቁጥር 20 እስከ 23 ድረስ ይህንን ተለዋጭ ዘይቤ ያስተዋውቃል፡

ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤

ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።

እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት። (ኤፌሶን 1፡20-23)

ልክ እንደ ቤተመቅደሱ ተለዋጭ ዘይቤ ዓይነት፣ ይህኛውም የእግዚአብሔርን መንግሥት ይገልጻል፤ ክርስቶስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ተቀምጧል ደግሞም ስለ ህዝቡ፣ ስለ ቤተክርስቲያን ጥቅም ሁሉን ይገዛል፡፡

ጳውሎስ ይህንን ተምሳሊታዊ መግለጫ በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ቁጥር 6 ውስጥ እንዲህ በማለት በተጨማሪ መረጃ ያቀርበዋል፡

አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ (ኤፌሶን 3፡6)

ጳውሎስ በዘር መካከል ስላለው እርቅ የሰጠው አጽንዖት በዚህም ስፍራ በግልጽ ይታያል፡፡ አይሁድም ሆኑ አህዛብ ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆነዋል፣ በክርስቶስም እርስ በርስ ተባብረዋል ደግሞም በክርቶስ የተሰጠው ተስፋ ተካፋዮች በመሆናቸው ብቻ በረከቶቹን ይቀበላሉ፡፡

ጳውሎስ የክርስቶስን አካል በሙላት የገለጠበት መግለጫ የሚገኘው ግን በምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 16 ባለው ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ በዚያም በመንግሥቱ ውስጥ ያለውን ቤተክርስቲያናዊ የመንግሥቱን አስተዳደር አቅርቧል፡፡ በዚያ ስፍራ ያተኮረው በቤተክርስቲያን የአመራር ተዋረድ፣ ተጽዕኖና ሥልጣን ላይ ሲሆን፣ ያም የሚያገለግለው ጠቅላላዋን ቤተክርስቲያን ለአገልግሎት ለማስታጠቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀው መልካሙ ሥራ አንዳችን ለአንዳችን የምንሰጠውን አገልግሎት በስፋት ያካተተ ሲሆን፣ ያም ቤተክርስቲያንን ለማነጽና ቤተክርስቲያንም የፍጥረተ ዓለሙ ጌታ መላውን ዓለም የሚገዛባት መንግሥት እንድትሆን ለማድረግ ነው፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁጥር 11 እስከ 13 የተናገረውን እናድምጥ፡

እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤

ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። (ኤፌሶን 4፡11-13)

እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ውስጥ መሪዎችን የሰጠው አንዳችን ለሌላችን አገልግሎት መስጠት እንድንችል እንዲያዘጋጁን ነው፡፡

እነዚህ መሪዎች ቤተክርስቲያንን ወደ ሁለት ግቦች ይመራሉ፡፡ የመጀመሪያው ወደ “እምነት አንድነት” ማድረስ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ፣ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮ አንድ ልትሆን ይገባል የሚል ሃሳብ በልቡናው ይዟል፡፡ ያም ማለት የወንጌል የመጀመሪያ ነገር በመረዳት ብቻ ረክቶ መቀመጥ ሳይሆን የበሰለና ያልተዛነፈ እውቀት መጨበጥ ማለት ነው፡፡ ይህም ጳውሎስ አስቀድሞ ባቀረባቸው ጸሎቶቹ የገለጣቸውን እና በክርስቶስ የተገኙትን በረከቶች የጳውሎስ አንባቢዎች በሙላት እንዲቀበሏቸው እግዚአብሔር እንዲረዳቸው የቀረበውን ልመና ማጽናት ነው፡፡

ሁለተኛው ግብ፣ “ወደ ክርስቶስ ፍጹም ሙላት ደርሶ መሞላት” ነው፡፡ የዚህ ግብ አድማስ አፅናፈ ዓለሙ ሲሆን፤ ይህም ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁጥር 10 እንዳስተማረው፣ ፍጥረትን ሁሉ በክርስቶስ አገዛዝ ስር ማድረግ ነው፡፡ ጉዳዩ ሁላችንን እስኪያስደንቀን ደረስ፣ በተስተካከለ የቤተክርስቲያን አመራር እና በክርስቲያኖች መካከል በሚከናወን መሰጠት የሞላበት አገልግሎት፣ ፍጥረተ ዓለሙ በጠቅላላ በክርስቶስ ጌትነት ስር ይሆናል፡፡

በመቀጠልም ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ከቁጥር 15 እስከ 16 የቤተክርስቲያን መሪዎች ህዝቡን ሊያስተምሩ የሚገባቸውን ጥቂት ነገሮች ሲዳስስ ይህንን ተለዋጭ ዘይቤ እንዲህ አስቀምጦታል፡፡

ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤

ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። (ኤፌሶን 4፡15-16)

መሪዎች ለቤተክርስቲያን፣ ለአካሏ፣ እውትን በፍቅር ሲናገሩ፣ አካሏ ያንን እውነት ትረዳለች፡፡ በውጤቱም፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን ለሌሎች ትርጉም ያለው አገልግሎት መስጠትን፣ በልዩ ልዩ መስክ መሠማራትንና መበረታታትን ይማራል፡፡ አንድ ሌላ ነገርም ልብ ማለት ይገባል፡ ፍቅር የመሪዎች አስተምህሮና በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚከናወኑ አገልግሎቶች መለያ ሊሆን ይገባዋል፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅርና እኛ ለእርሱ ያለን ፍቅር በመንግሥቱ ውስጥ ከሚገለጥ ታማኝነትና መሰጠት አንፃር ቀደም ሲል እንደተገለጠ ሁሉ፣ እኛ ለክርስቲያኖች ያለን ፍቅርም በዚሁ መንገድ ሊገለጥ ይገባዋል፡፡ ለባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር የስሜትና የግለሰባዊ ትውውቅ ውጤት ሳይሆን፣ በአካል ባናውቃቸውም እንኳን የእነርሱን ጥቅም በሚናፍቅ መንገድ ከታማኝነትና ከመሰጠት የሚመነጭ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ይህ ፍቅር የትብብር ወይም የአንድ ጎራነት ፍቅር ሊሆንም አይገባውም፡፡ ይልቁኑ፣ ክርስቲያናዊ ፍቅር አማኝ ወንድሞቻችን በጠቅላላ የክርስቶስ ርስት ተካፋዮች እንደሆኑ በመረዳት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ክርስቶስ እነርሱን የራሱ ለማድረግ ሊሞት ፈቅዷል፣ እነርሱ የእርሱ በመሆናቸውም ክብርንና ምሥጋናን ይቀበላል፡፡ ይህ መረዳት ለእነርሱ ከፍ ያለ ዋጋ እንድንሰጥ እና እነርሱን ለማገልገል የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል እንድንፈቅድ ያነሳሳናል፡፡

እስካሁን ድረስ፣ ንጉሡን የማክበርንና መንግሥቱን የመገንባትን ርዕሶች ስንዳስስ ቆተናል፣ አሁን ደግሞ ወደ መጨረሻው ርዕሳችን፣ ማለትም ፍጥረተ-ዓለሙን ድል ማድረግ ወደተሰኘው መሸጋገር ይገባናል፡፡ ኢየሱስ አሁን የቤተክርስቲያን ንጉሥ ነው፣ ሆኖም ጠላቶቹን ድል የሚያደርግበትና በፍጥረተ-ዓለሙ ሁሉ ላይ ገዢ የሚሆንበት ቀን ግን ይመጣል፡፡

ፍጥረተ-ዓለሙን ድል ማድረግ

እንደተመለከትነው፣ በአሁኑ ወቅት የእግዚአብሔር መንግሥት የምትገዛው በአሁኑ የኃጢአትና የሞት ዘመን መካከል ነው፡፡ በዚህ ዘመን፣ የእግዚአብሔር ሠራዊት፣ ቤተክርስቲያኑን ጨምሮ ከአጋንንት እና ከወደቀው የሰው ዘር መንግሥት ጋር እየተዋጋ ነው፡፡ በስተመጨረሻ ግን ኢየሱስ ይመለሳል፡፡ ዳግመኛ ሲመጣም በጠላቶቹ ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ይበይናል፣ እርሱንም የሚቋቋሙበትን ኃይል ለዘለዓለም ይሰብራል፡፡ በስተመጨረሻው በጨለማው ኃይላት ላይ ድልን መቀዳጀት የተረገገጠ ነው፡፡ እስከዚያች ቀን ድረስ ግን፣ በጽናት እነርሱን መፋለም ይጠበቅብናል፡፡

ሆኖም በዚህ በኃጢአትና በሞት ዘመንም እንኳን፣ ከአጋንንት ኃይላት ጋር በምናደርገው ውጊያ አሸናፊዎቹ እኛው ነን፡፡ እንደተመለከትነው፣ ንጉሣችን ሥልጣንንና ኃይልን ለብሶ እነርሱን በሚገዛበት ዙፋን ላይ ተቀምጧል፣ እኛም ከእርሱ ጋር ተቀምጠናል፡፡ ከእርሱ የክፋት አገዛዝ እግዚአብሔር ነፃ አውጥቶናል በመንግሥቱ ውስጥ ወደሚገኘው በረከትም አፍልሶናል፡፡ ጠላቶቻችን የሚሰነዝሩብንን የክፉ ጥቃት መቋቋም የምንችልበትን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አልብሶናል፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 6 በቁጥር 13 እና 16 የተናገረውን ልብ እንበል፡

ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ (ኤፌሶን 6፡13፣16)

እግዚአብሔር በጸጋውና በመንፈሱ፣ የአጋንንትን ፍላፃዎች የምንቋቋምበትን ኃይል አስታጥቆናል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ቤተክርስቲያን የተቀበለቻቸው በርካታ በረከቶች፣ ለአጋንንቱ መሸነፋቸው አይቀሬ መሆኑን ያረጋግጡላቸዋል፡፡ እንዲያውም፣ ጳውሎስ በመቀጠል የቤተክርስቲያን በምድር መኖር የእግዚአብሔር ጠላቶች ማብቂያ ቀን እየተፋጠነ የመሆኑ አመልካች ነው ይላል፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ከቁጥር 8 እስከ 11 ጳውሎስ የተናገረውን እናድምጥ፡

ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ፤

ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤

ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥ (ኤፌሶን 3፡8-11)

እንዲያውም የሰው ዘር ከመፈጠሩም አስቀድሞ፣ በቤተክርስቲያን አማካይነት ክብሩን ለአጋንንታዊ ጠላቶቹ ለመግለጥ እግዚአብሔር አቅዷል፡፡ አስከ ክርስቶስ ዘመን ድረሰ ግን ጉዳዩ ምሥጢር ሆኖ እንዲቆይ አድርጓል፡፡ አሁን ግን ክርስቶስ መጥቷል፣ እግዚአብሔርም ጥበቡንና ኃይሉን ለጠላቶቹ ለመግለጥ ቤተክርስቲያንን እየተጠቀመ ነው፡፡ የአጋንንትን ከፍተኛ ኃይል እንኳን መደምሰስ እንደሚችል ለማሳየት ቤተክርስቲያንን ከፍ አድርጓታል፣ በዚህም ሁሉን ከራሱ ጋር የማስታረቅ አቅም እንዳለው አሳይቷል፡፡ የሰውን ዘር ሁሉ ከኃጢአት ባርነት ከተቤዠ፣ እርስ በርሳችን ደግሞም ከእርሱ ጋር ካስታረቀን እርሱ ለማድረግ የሚሳነው ምንም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡

እኛ ዝም ብለን የናሙና ማሳያዎች አይደለንም፡፡ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ስጦታ ናት፡፡ ከጠላቶቹ መንግሥት ነጥቆ ለማውጣት የተዋጋላቸውና ድል አድርጎ ያስለቀቃቸው በረከቶቹ ነን፡፡ እኛ እግዚአብሔር ለማዳን ሲል ታሪክን የሚቆጣጠርበት፣ ሊጠብቃትና ሚስቱ ሊያደርጋት ክርስቶስ ሕይወቱን የሰጠላት ህዝቡ ነን፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ከቁጥር 23 እስ 27 ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተክርስቲያን የሰጠውን መግለጫ እናድምጥ፡

ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። …

… ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት … ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤

እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። (ኤፌሶን 5፡23-27)

እግዚአብሔር ይወድደናል የከበረ ዋጋም ይሰጠናል፡፡ ሁሉን ከራሱ ጋር የማስታረቁን፣ ፍጥረተ-ዓለሙን የማደስና የማንፃት ሥራውን በሚሠራበት ሂደት ውስጥም ሥራውን የሚጀምረው ከእኛ ነው፡፡ ስለዚህም፣ የቤተክርስቲያን መኖርና፣ የቤተክርስቲያን ይቅር መባል፣ ደግሞም የቤተክርስቲያን መቀደስ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት የመጀመሯ ማረጋገጫ ነው፡፡ ከተጀመረች ደግሞ መጠናቀቋ የተረጋገጠ ነው፡፡ ያ ሲሆን ግን፣ አጋንንቶች ጨርሶውኑ ይደመሰሳሉ፣ የክርስቶስ ንግሥናም ፍፁም ይሆናል፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 1 ቁር 22 እና 23 እንዳፃፈው፡

ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።

እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት። (ኤፌሶን 1፡22-23)

ጳውሎስ በዚህ ስፍራ የተናገራቸው ቃላት አስደንጋጮች ናቸው፤ ክርስቶስ የፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ንጉሥ የሆነው ለቤተክርስቲያን በረከት ነው፡፡ እኛ የእርሱ ሙላቱ፣ አካሉ ነን፡፡ እርሱን ፍፁም እናደርገዋለን፡፡

ከማንነቱና ከመታዘዙ የተነሣ፣ ክርስቶስ ሊገዛ እንደተገባው ሁሉ፣ የመግዛቱ ዓላማ በእውነት እኛን መባረክ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ቤተክርስቲያን የመባረኳ እውነታ፣ አይሁድና አህዛብ፣ ባሎችና ሚስቶች፣ ወላጆችና ልጆች፣ ጌቶችና ባሮች እርስ በርስና ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቃቸው እውነታ እግዚአብሔር መልካም እና ጥበበኛ እንደ ሆነ ደግሞም ፍጥረተ-ዓለሙን ሊያድስ መጀመሩን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ይህ ከሆነ፣ እኛ ለዚህ በረከት ምላሽ መስጠት የሚገባን እንዴት ነው? መንግሥቱስ በክርስቶስ አድጋ ጠላቶቿን ድል እንድታደርግ የምንደግፋት እንዴት ነው? ለንጉሣችን የሚገባውን ክብርና ምሥጋና በማቅረብ፤ በታማኝነትና በመታዘዝ ለእርሱ በመገዛት፤ ቤተክርስቲያኑን በማገልገልና በመገንባት፤ የመንግሥቱን ጠላቶች በጽናት በመቋቋም ምላሽ መስጠትና መደገፍ እንችላለን፡፡

ማጠቃለያ

በዚህ ትምህርት ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን ተዘዋዋሪ ደብዳቤ መርምረናል፡፡ ለመልእክቱ መቼት የምናገኝበትን ዳራ ተመልክተናል፣ የመልእክቱንም አወቃቀርና ይዘት ዳስሰናል፡፡ በመጨረሻም፣ ጳውሎስ በዚህ መልእክት ትምህርት የሰጠበትን ዘመነኛ ተዛምዶ በአንክሮ አይተናል፡፡

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈው መልእክት ዛሬም በእኛ ዘመን ትልቅ ትምህርት የምናገኝበት መልእክት ነው፡፡ ድነት ሰዎች ከኃጢአት መቤዠትን የሚያገኙበት ግለሰባዊ በረከት ብቻ አለመሆኑን ያስተምረናል፡፡ ይልቁኑ፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ አብሮ መገንባትን፣ መታደስንና እየተሠሩ በናፍቆት ማደግን ያካተተ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያለን መረዳት ሲጨምር፣ ጠላቶቻችንን ለመቋቋም ይበልጥ ዝግጁዎች እንሆናለን፣ እግዚአብሔርንም ደስ በሚያሰኝ መንገድ እንኖራለን ደግሞም የእርሱን በረከት እኛም ሆንን ወንድሞቻችን በሙላት እንቀበላለን፡፡

Continue reading the full transcript