ከተመሳሳይ ተከታታይ ክፍል 4 ጋር የተያያዘ ቪዲዮ ሲሆን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠይቃል፡- የጳውሎስ ደብዳቤ ወደ ፊሌሞን የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ላይ ምንም ዓይነት ትምህርታዊ ሥልጣን አለው? የጳውሎስ ደብዳቤ ወደ ፊሌሞን ለጠቅላላው ቤተ ክርስቲያን ይነበብ ነበር? ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ ወንጌሉን አንድ የተወሰነ ሰው ላይ የሚያሳድረውን አንድምታ ገልጿል? ሁሉም የባሪያነት ዓይነቶች የሰውን ክብር ያበላሻሉ? ቤተ ክርስቲያን ለዘመናዊ የባሪያነት ዓይነቶች እንዴት ምላሽ መስጠት አለባት? የሮማውያን ባሪያነትን መረዳት የጳውሎስን ደብዳቤ ወደ ፊሌሞን ለመረዳት አስፈላጊ ነው? ለምን ጳውሎስ ኦነሲሞስን ነፃ ለማውጣት ፊሌሞንን ከማዘዝ ይልቅ ለማሳመን ሞከረ? ከፊሌሞን ጋር የጳውሎስን የመሳመን ስልቶችን ልንከተል ይገባል? ጳውሎስ ለምን እንዲህ ዓይነቱን አደገኛ ስልት ከፊሌሞን ጋር ለመጠቀም ድፍረትን አገኘ? ኦነሲሞስ ለፊሌሞን ማካካሻ የማድረግ ኃላፊነት ነበረው? ስንታለል ቢሆንም ሁልጊዜ ይቅር ማለት አለብን? ጳውሎስ ኦነሲሞስ ላይ ወንጌሉን እንዴት ያመጣል? የጳውሎስ በባሪያዎችና ጌቶች ላይ ያሉ ትምህርቶች ለሌሎች ዓይነቶች ግንኙነቶች ይተገበራሉ? በፊሌሞን የተብራሩት መርሆዎች ከአላቸው ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ይተገበራሉ? የጳውሎስ መልእክት በአላቸው የተሳደዱ ክርስቲያኖች ላይ እንዴት ይተገበራል? የፊሌሞን መጽሐፍ በጥፋትና በውንጀላ ምን ይላል? በክርስቶስ ውስጥ ያለን ማንነት እንዴት ይቅርናን ለማስታረቅ ያነሳሳናል? ከአላቸው ጋር የመታረቅን ጥረት መገደብ አለብን? ከክርስቲያኖች ጋር የመታረቅን ጥረት መገደብ አለብን? የእግዚአብሔርን መንግስት በትክክል እንዴት መተርጎም እንችላለን?
From the transcript
ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡
አብዛኞቻችን ከወዳጆቻችን በጎ ውለታ የተቀበልንባቸውን ጊዜያት እናስታውሳለን፡፡ ምናልባት ለአንድ ወዳጃችሁ ስጦታ በመስጠት ወይም ለየት ያለ ድጋፍ በማደረግ ግሩም በጎነት ታደርጉ ይሆናል፡፡ እናንተም በተራችሁ ድጋፍ የምትፈልጉበት ጊዜ ሲመጣ ያ ወዳጃችሁ በተራው ለእናንተ መልካም ነገር እንዲያደርግላችሁ ትጠይቃላችሁ፡፡ እነዚህን በመሰሉ ወቅቶች፣ አብዛኛውን ጊዜ የምናደርገው፣ ወደ ወዳጃችን እንሄድና፣ “ይህንን ነገር ማድረግ እንደማትፈልግ አውቃለሁ፣ ሆኖም ግን ያንተ እርዳታ በእውነት ያስፈልገኛል፡፡ እባክህን ቸርነት አድርግልኝ፡፡” በማለት እንጠይቃለን፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስም በብዙ መልኩ ይህንን የሚመስል ችግር ደርሶበታል፡፡ ከወዳጁ ከፊልሞና ይህንን መሳይ በጎነት ማግኘት አስፈለገው፡፡ ስለዚህም ለፊልሞና ደብዳቤ ጻፈለት፣ ጳውሎስ ለእርሱ ምን እንዳደረገለት ካሳሰበው በኋላ እርሱም በተራው ብድሩን እንዲመልስለት ይጠይቀዋል፡፡
“የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች” ከተሰኘው ተከታታይ ትምህርታችን ይህ አራተኛው ነው፡፡ “ጳውሎስ እና ፊልሞና” የሚል ርእስ ሰጥተነዋል፣ ምክንያቱም ጳውሎስ ለወዳጁና የቆላስይስ ቤተክርስቲያን አባል ለሆነው ለፊልሞና የጻፈውን ደብዳቤ በጥልቀት ስለምንመለከት ነው፡፡ ፊልሞና አስቀድሞ ባሪያው ከነበረና በቅርቡ ደግሞ በክርስቶስ ካመነው ከአናሲሞስ ጋር እንዲታረቅ ጳውሎስ እንዴት ልመና እንዳቀረበለት እንመለከታለን፡፡
ጳውሎስ እና ፊልሞና የተሰኘው ትምህርታችን በሦስት ዋና ክፍሎች ይከፈላል፡፡ አንደኛ፣ ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን ደብዳቤ ዳራ እንዳስሳለን፡፡ ሁለተኛ፣ ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን ደብዳቤ አወቃቀርና ይዘት እንመረምራለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ በመልእክቱ ዘመነኛ ተዛምዶ ላይ እናተኩራለን፡፡ አስቀድመን ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን ደብዳቤ ዳራ እንመልከት፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈው ደብዳቤ ቢያንስ በሁለት መንገዶች ከሌሎቹ የእስር ቤት ደብዳቤዎቹ ይለያል፡፡ አንደኛው፣ በእስር ላይ ሆኖ ከጻፋቸው ደብዳቤዎቹ በጣም አጭር መሆኑ ነው፡፡ እንዲያውም፣ የሚዳስሰው አንድን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ፣ ለቤተክርስቲያን ሳይሆን ለአንድ ግለሰብ የተጻፈ ሲሆን፣ ያም የሚያሳየው በጣም የግል ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ማለት ስለ ፊልሞና እና በጉዳዩ ስለተጠቀሱት ሰዎች ይበልጥ ስናውቅ፣ ደግሞም ጳውሎስ የዳሰሳቸውን ሁኔታዎች ይበልጥ ስናውቅ፣ ጳውሎስ በዚህ መልእክት ያስተማረውን ትምህርት በተሻለ መንገድ ለመገንዘብ እና ዛሬ በሕይወታችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁዎች እንሆናለን፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን መልእክት በሦስት መንገዶች እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ በዳሰሰው ጉዳይ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩትን ሰዎች እንለያቸዋለን፡፡ ሁለተኛ፣ ለጳውሎስ ደብዳቤ መንስዔ የሆነውን ችግር እንመለከታለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ የጳውሎስን በአማላጅነት በጉዳዩ ውስጥ መግባትን እንመረምራለን፡፡ አስቀድመን በጉዳዩ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን ሰዎች እንመልከት፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው መልእክት ውስጥ የበርካታ ሰዎቸ ስም ተጠቅሷል፣ ሆኖም ግን ጳውሎስ ፊልሞና እንዲያደርግለት ከለመነው ቸርነት ጋር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ በሚያያዙት ሰዎች ላይ እናተኩራለን፡፡
በመጀመሪያ፣ ራሱን ፊልሞናን እናስተዋውቃለን፡፡ ሁለተኛ፣ ወደ ፊልሞና ባሪያ ወደ አናሲሞስ እንሸጋገራለን፡፡ በመጨረሻም፣ ጳውሎስ ጣልቃ ለሚገባበት ለፊልሞናና ለአናሲሞስ ጉዳይ እንደ ምስክር ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን እንጠቃቅሳለን፡፡ አስቀድመን ጳውሎስ ደብዳቤውን ከጻፈለት፣ ከፊልሞና እንጀምር፡፡
ጳውሎስ በጻፈለት ደብዳቤ ውስጥ የፊልሞና የመኖሪያ ከተማ የት እንደሆነ አልተጠቀሰም፣ ሆኖም ቆላስይስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 9 እንደሚያመለክተን የፊልሞና ባሪያ አናሲሞስ የቆላስይስ ነዋሪ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ጳውሎስ የጠቀሰውን እናድምጥ፡
ቲኪቆስ፤
ከእናንተ ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም ከአናሲሞስ ጋር ወደ እናንተ የምልከው…(ቆላስይስ 4፡9)።
አናሲሞስ የቆላስይስ መልእከት በተጻፈበት ወቅት ከጌታው ከፊልሞና ጋር ይኖር ከነበረ፣ ፊልሞናም የቆላስይስ ነዋሪ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ቆላስይስ በሊከስ ሸለቆ አቅራቢያ ከሚገኙት ከሎዶቂያ እና ከሂራፖሊስ አጠገብ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት፡፡ የሊከስ ሸለቆ የምትገኘው የሮሜ ግዛት በሆነችው በእስያ ጠቅላይ ግዛት፣ በፍርግያ አውራጃ፣ በዘመናችን ትንሿ እስያ ተብላ በምትጠራው አካባቢ ነው፡፡
ፊልሞና በቆላስይስ ይኖሩ የነበሩ አማኞችን በማገልገል ረገድ የነቃ ተሳትፎ ያደርግ የነበረ ሰው ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ በፊልሞና ቁጥር 7 ውስጥ፣ ፊልሞና የሌሎች አማኞችን ልብ እንዴት በፍቅር ያነቃቃ እንደነበር ጳውሎስ ተናግሯል፡፡ ፊልሞና በወንጌል አገልግሎት አብሮኝ የሚጋደል በሚል መግለጫ፣ ጳውሎስ ስለ አናሲሞስ ያለውን ከፍ ያለ ስፍራ በቁጥር 17 ውስጥ በግልጽ አሳይቷል፡፡ እንዲያውም ጳውሎስ በቁጥር 2 ውስጥ ፊልሞናን በቤትህ ያለች ቤተክርስቲያን ብሎ በመጥቀስ አሳይቶታል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ፊልሞና ከጳውሎስ ጋር የጠነከረ ታሪክ ያላቸው መሆኑንና በሰዎቹ መካከል ጠንካራ ቅርርብ መኖሩን እናያለን፡፡ በፊልሞና ቁጥር 19 ውስጥ ጳውሎስ ለፊልሞና የሚሰጠውን ማሳሰቢያ ልብ በሉ፡
ለእኔ የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አልልህም። (ፊልሞና 19)
በዚህም ሆነ በዚያ፣ ጳውሎስ እያለ ያለው ፊልሞናን ወደ እምት ያመጣው ጳውሎስ ነው፣ ወይም ደግሞ ጳውሎስ የፊልሞናን ሕይወት በአንድ በሌላ መንገድ ያዳነውም ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ ፊልሞና የጳውሎስ ታላቀ ባለ ዕዳ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ከእስር እንዲለቀቅ ፊልሞና በጸለየው ጸሎትና ጳውሎስ ከእስር ከተፈታ በኋላ በፊልሞና ቤት ውስጥ ለማረፍ ያወጣውን እቅድ ስንመለከት የግንኙነታቸውን ጠንካራነት መረዳት እንችላለን፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጳውሎስ በፊልሞና ቁጥር 22 ውስጥ የተናገረውን እናድምጥ፡
ደግሞ ከዚህም ጋር የማስተናገጃ ቤት አዘጋጅልኝ፤ በጸሎታችሁ ለእናንተ እንድሰጥ ተስፋ አደርጋለሁና። (ፊልሞና 22)
ጳውሎስ ከፊልሞና ጋር እንዴት እንደተዋወቀ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ማብራሪያ አይሰጠንም፡፡ ቀደም ባሉት ትምህርቶች እንደተመለከትነው ግን፣ ጳውሎስ በሁለተኛው ሚሲዮናዊ ጉዞው በፍርግያ እንዳለፈ ግን ይናገራል፡፡ ሆኖም ደግሞ ጳውሎስ በሊከስ ሸለቆ ከሚገኙ አብያተክርስቲያናት ጋር ቅርርብ እንዳልነበረውም ተመልክተናል፡፡ እውነታው ጳውሎስና ፊልሞና እንዴት ወዳጆች እንደሆኑ አለማወቃችን ነው፡፡ በልበ ሙሉነት መናገር የምንችለው ግን ሁለቱም በሚገባ የሚተዋወቁ መሆኑን ነው፡፡
አናሲሞስ
ልናስተዋውቀው የሚገባን ሁለተኛው ሰው አናሲሞስ ነው፡፡ እንደ ፊልሞና 16 አገላለጽ፣ አናሲሞስ የፊልሞና ባሪያ ነው፣ ምን ዓይነት ባሪያ እንደነበረ ወይም በምን ዓይነት የተለየ አገልግሎት እንዳገለገለው ግን አናውቅም፡፡
በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በነበረው የሮሜ ግዛት፣ ባርነት በጣም የተለመደ ነገር ነው፡፡ በመንግሥቱ ግዛት ከሚገኙት ግዛቶች አንደ ሦስተኛውን ያህል የተለያዩ ባሮች ይኖሩ ነበር፡፡ ባሮች አብዛኛውን ጊዜ በባለጠጎች የሚገዙ ናቸው ስለዚህም ስፍራቸው የሚወሰነው በባለቤቶቻቸው ደረጃ ነው፡፡
አንዳንድ የሮሜ ባሮች ያልተማሩ ሲሆኑ የተናቁ ስራዎቸን ይሠሩ ነበር፣ ሌሎቹ ደግሞ የተማሩ ነበሩ አንዳንዶቹ በጣም ከፍተኛ ትምህርት ነበራቸው ያገለግሉ የነበረውም በትምህርታቸው ልክ ነበር፡፡ አንዳድ ጊዜ የቤቱ አስተዳዳሪዎች፣ የገንዘብ ነክ ጉዳዮች ሃላፊዎች፣ አስተማሪዎች ወይም ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ የተገኘውን የትኛውንም ነገር የሚሠሩ ይሆናሉ፡፡
ምንም እንኳን በጥቅሉ ከባርነት ይልቅ ነፃነት የሚመረጥ ቢሆንም፣ ጥቂት ድሃ ግለሰቦች የዕለታዊ ምግብና መጠለያ ዋስትና ለማግኘት ሲሉ በፈቃዳቸው ራሳቸውን ለባርነት አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ ከቀደመችው ቤተክርስቲያን የታሪክ መዝገብ እንደምንገነዘበው፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ደሆችን ለመመገብና ለመሳሰሉ አገልግሎቶች ገንዘብ ለማሰባሰብ ሲሉ ራሳቸውን ለባርነት አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡
ጠቅለል ባለ አነጋገር፣ ጌቶች በባሮቻቸው ላይ ያላቸው መብት ፍፁማዊ አይደለም፡፡ ባሮች የራሳቸው ገንዘብ እንዲኖራቸው፣ ንብረትም እንዲያፈሩ ያም ሌሎች ባሮችን መግዛትን ጨምሮ ደግሞም ነፃነታቸውን ከጌቶቻቸው መልሰው መግዛት እንዲችሉ የሮሜ ህግ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ከነዚህ መብቶችም ባሻገር፣ ምንም እንኳን ህጋዊ እውቅና ባይሰጠውም፣ በርካታ ባሮች፣ ዕድሜአቸው ሠላሳ ዓመት ሲሞላ፣ ነጻነታቸውን ያገኛሉ፡፡
አናሲሞስ የፊልሞና ባሪያ ስለሆነ፣ የፊልሞና ቤተሰብ አባል ነበር፡፡ ግን፣ አናሲሞስ፣ መጀመሪያ ላይ እንደጌታው አማኝ አልነበረም፡፡ ሆኖም አናሲሞስ የጳውሎስን እርዳታ ፍለጋ ከፊልሞና ቤት ሲወጣ፣ ሐዋርያው ወደ እምነት አምጥቶታል፣ ለእርሱ ያለውም ፍቅር እጅግ አድጓል፡፡ ጳውሎስ ለአናሲሞስ ያለውን ፍቅር በፊልሞና ቁጥር 10 እስከ 16 እንዲህ ገልፆታል፡
… በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። … አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። … ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ (ፊልሞና 10-16)
ጳውሎስ አናሲሞስን ልጄ ይለዋል ምክንያቱም በክርስቶስ እንዲምን ስላደረገውና ስለ እርሱም አባታዊ የሆነ ፍቅርን እያሳደገ ስለመጣ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁለት ገጸ-ባህርያት በተጨማሪ፣ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ በርካታ የቆላስይስ ቤተክርስቲያን አባሎችን ጠቅሷል፣ እነርሱም፣ አፍብያ፣ አክርጳ እና ኤጳፍራ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከፊልሞና ጋር ወዳጅነት ያላቸው ናቸው፡፡ ምናልባት ጳውሎስ እነርሱን የጠቀሰው በአናሲሞስ ምትክ ሆኖ ለፊልሞና ልመናውን ሲያቀርብ በተለመደው መንገድ ምስክሮች እንዲሆኑት አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡
ምስክሮች
ጳውሎስ አፍብያንና አክርጳን የጠቀሰው በደብዳቤው መግቢያ ላይ ሲሆን በፊልሞና ቁጥር 1 እና 2 ውስጥ ይገኛል፡፡ ጳውሎስ በዚያ ምን አንደጻፈ እናድምጥ፡
የክርስቶስ ኢየሱስ እስር ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ ለተወደደውና አብሮን ለሚሠራ ለፊልሞና፥
ለእኅታችንም ለአፍብያ፥ ከእኛም ጋር አብሮ ወታደር ለሆነ ለአርክጳ፥ በቤትህም ላለች ቤተ ክርስቲያን፤ (ፊልሞና 1-2)
ጳውሎስ አፍብያን እንደ እህቱ መጥቀሱ በቀላሉ አማኝ መሆኗን ለማመልከት ይሆናል፡፡ ከሌሎቹ የቤተክርስቲያን አባላት ለየት ተደርጋ እስከተጠቀሰች ድረስ ግን፣ የፊልሞና ቤተሰብ አካል የመሆኗ ነገር አሳማኝ ይመስላል፡፡ ምናልባትም ሚስቱ ልትሆን ትችላለች፡፡ ምንም እንኳን ቤተክርስቲያኒቱ የምትሰበሰበው በፊልሞና ቤት እንደሆነ ጥቀሱ ቢናገርም፣ አክርጳ የአጥቢያ ቤተክርስቲያኒቱ አስተባባሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ የአጥቢያ ቤተክርስቲያኒቱ መጋቢ ወይም የፊልሞና ቤተሰብ አባል ቢሆንም፣ ሰውየው በፊልሞና ላይ አንድ ዓይነት ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል ዓይነት ሰው አደርጎ ጠቅሶታል፡፡
ኤጳፍራን በተመለከተ፣ ቀደም ባለው ትምህርታችን እንደተመለከትነው እርሱ የቆላስይስን ቤተክርስቲያን የመሰረተ፣ ደግሞም በሊከስ ሸለቆ የሚገኙ አብያተክርስቲያናት ጳውሎስን በእስር ቤት እንዲያግዘው የላኩለት ሰው ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ከጳውሎስ ጋር ስለነበር፣ በቆላስይስ አጥቢያ እንደሚገኝ ምስክር ሊያገለግል አይችልም፡፡ ሆኖም በቤተክርስቲያን የነበረው ስፍራ እርሱ የሚያቀርበው ሃሳብ ከበሬታ እንዲገኝ ያስችለዋል፡፡ ስለዚህ፣ ጳውሎስ ከኤጳፍራ የተላከላቸውን ልዩ ሰላምታ ይጠቅሳል፡፡ በፊልሞና ቁጥር 23 እና 24 የሚገኙትን እነዚህን ቃላት እናድምጥ፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ከእኔ ጋር የታሰረ ኤጳፍራ
አብረውኝም የሚሰሩ ማርቆስና አርስጥሮኮስ ዴማስም ሉቃስም ሰላምታ ያቀርቡልሃል።
(ፊልሞና 23-24)
ከኤጳፍራ የተላከውን ሰላምታ ማስቀደሙን ልብ በሉ፣ ከሌሎቹም ረዘም ያለና ለየት ያለ መግለጫ ያለበትም ነው፡፡ ለኤጳፍራ የተሰጠው ለየት ያለ አጽንዖት ኤጳፍራ ሰላምታ መላክ ብቻ ሳይሆን፣ ፊልሞና ለጳውሎስ ደብዳቤ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ብርቱ ፍላጎትም እንዳለው ፊልሞና እንዲገነዘብ የሚያመለክትም ነው፡፡
ችግር
ከጳውሎስ መልእክት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሰዎች በቅርበት ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ቸግሩን ራሱን እንዳስሳለን፡፡ ጳውሎስ ጣልቃ እስኪገባ ድረስ ያደረሰው ችግር ምንድን ነው?
አንዳንድ ሠራተኞች መልካም ሠራተኞች ያለመሆናቸው፣ አንዳንድ አገልጋዮችም ጥሩ አገልጋዮች አለመሆናቸው እና አንዳንድ ሰዎችም ሃላፊነትን እንደማይቀበሉና ግዴታቸውንም እንደማይወጡ ነገር ለማንም ምስጢር አይደለም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖም፣ አናሲሞስም ከእነዚያ ሰዎች እንደ አንዱ የሆነ ይመስላል፡፡ እናም ውድቀቶቹ ማለትም፣ ሐኬተኝነት፣ ዝርክርክነት፣ ወይም ተንኮለኝነት ጌታውን ፊልሞናን አስቆጥጦታል፡፡ ስለዚህም አናሲሞስ ከፊልሞን የሚጠብቀውን ቅጣት እጅግ ፈርቶታል፡፡ እናም፣ ከዚህ ቅጣት ለማምለጥ፣ አናሲሞስ ከፊልሞና ቤተሰብ ጠፍቶ ሄደ፡፡ በፊልሞና 11 ጳውሎስ ለፊልሞና የተናገረውን ልብ እንበል፡
አስቀድሞ ስላልጠቀመህ (ፊልሞና 11)
እዚች ጋ የቃላት ጨዋታ የምትመስል ነገር አለች፡፡ “አናሲሞስ” የሚለው ስም የተወሰደው ከግሪክ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም “ጠቃሚ” ወይም “አትራፊ” ማለት ነው፡፡ ጳውሎስ ግን በዚህ ስፍራ አናሲሞስ የማይጠቅም እንደነበረ ይናገራል፡፡ ጳውሎስ በዚህ የቃላት ጨዋታ አናሲሞስ አስቀድሞ የማይጠቅም ባሪያ እንደነበረ ለፊልሞና ያረጋግጥለታል፡፡
ከዚህም የከፋው፣ እንደ ፊልሞና 19 አገላለጽ፣ አናሲሞስ ፊልሞናን በጣም ኪሳራ ውስጥ ያስገባው ይመስላል፡፡ ጳውሎስ በዚህ ስፍራ የተናገረውን እናድምጥ፡
በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቍጠር፤ (ፊልሞና 18)
አብዛኞቹ ተርጓሚዎች ይህንን ጥቅስ የሚረዱት በዚያን ዘመን የቤት ውስጥ ባሮች እንደሚያደርጉት ዓይነት፣ አናሲሞስ ከፊልሞና እንደሰረቀ አድርገው ነው፡፡ አናሲሞስ ግን በፊልሞና ላይ ሌላ ኪሳራ ማለትም፣ ቤቱን በሚገባ ባለማስተዳደር ወይም ውድመት ወይም የንብረት ብክነት ሊሆን ይችላል፡፡
በየትኛውም ምክንያት፣ ፊልሞና ሊቆጣ ይገባዋል ደግሞም አናሲሞስ ፊልሞናን ሊፈራ የሚችልበት በቂ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ በሮሜ ህግ፣ ጌቶች ባሮቻቸውን ብርቱ ቅጣት የመቅጣት፣ ቅጣቱም ብርቱ በትር መምታትን ሊጨምር የሚችለበት መብት ይሰጣቸዋል፡፡ አናሲሞስም የፊልሞናን ቁጣ ስለፈራ ሸሸ፡፡
ጳውሎም ይህንን ሁኔታ በፊልሞና 15 ላይ እንዲህ በማለት ይጠቅሰዋል፡
ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤ (ፊልሞና 15)
ፊልሞና አናሲሞስ ቤቱን ለቅቆ እንዲሄድ ዓላማ አልነበረውም እንዲውያም ከቤት የመሸሹን ነገር የፈቀደ አይመስልም፡፡ ጳውሎስ እያለ ያለው ግን ይህንን ሁኔታ እግዚአብሔር ለመልካም ተጠቅሞበታል ነው፡፡ በዚህ በተለያዩበት ወቅት፣ እግዚአብሔር አናሲሞስን ለወጠው፣ ስለዚህ ለፊልሞና አሁን እጅግ የሚጠቅም ይሆናል፡፡
በሮሜ ግዛት ውስጥ፣ የጌቶቻቸውን ቤት በዚህ መንገድ ለጊዜው የተለዩ ሰዎች እንደ ኮብላዮች አይቆጠሩም፡፡ ኮብላዮች የሚባሉት ወደ ጌታቸው የመመለስ ሃሳብ የሌላቸውና በዓላማ የሚያደርጉት ናቸው፡፡ ህባሮች ከጌቶቻቸው ጋር የሚያስታርቃቸውና አማላጅ ሚሆናቸው ሰው ፍለጋ ለጥቂት ጊዜ ከጌቶቻቸው ቤት መራቅ እንደሚችሉ ህጉ ይደነግግላቸዋል፡፡ በርካታ የሮም ህግ አዋቂዎች ይህንን እውነታ በመዝገብ አስፍረውታል፡፡ ለምሳሌ፣ ከ 98 ዓ.ም. እስከ 117 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደጻፈው የሚነገርለት፣ ቪቪያነስ የተሰኘው ሰው፣ በዚህ መንገድ አቅርቦታል፡
አንድ ባሪያ ከጌታው ኮብልሎ ወደ እናቱ ቢመለስ፣ ኮብላይ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከግምት ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው ሁለት ነገሮች አሉ፤ ወደ ጌታው ላለመመለስ አቅዶ ራሱን ካሸሸ፣ ኮብላይ ነው፤ ሆኖም የሠራው ጥፋት የሚያስከትልበትን ቅጣት በእናቱ ልመና ማቅለልን ዓላማ አድርጎ ከሄደ ግን ኮብላይ አይባልም፡፡
በተመሳሳይም፣ በመጀመሪያው ክፈለ ዘመን መነሻ አካባቢ ጸሐፊ የነበረው፣ ፕሮኩለስ እንዲህ ይላል፣
ጌታው አካላዊ ቅጣት ሊቀጣው እንደሚችል በማሰብ የሰጋ አንድ ባሪያ፣ በእርሱ ምትክ ጌታውን የሚለምንለትን ሰው ፍለጋ ቢሄድ፣ ኮብላይ አይባልም፡፡
በሁለተኛው ምዕተ-ዓመት ማገባደጃ አካባቢ ደግሞ፣ ጳኡሉስ፣ እንዲህ ሲል ዘግቧል፡
አማላጅ እንዲሆነው ወደ ጌታው ወዳጅ የሸሸ ባሪያ ኮብላይ አይደለም፡፡
ነጻነታቸውን በዓመጻ ለማስከበር ሳይሆን፣ አንደ የሚረዳቸው ሰው ለመፈለግ ባሮች ከጌቶቻቸው እንዲሸሹ ህጉ እንደሚፈቅድላቸው የተመለከትናቸው ህጋዊ ትንታኔዎች ያሳዩናል፡፡ ስለዚህም፣ አናሲሞስ ጳውሎስ እንዲያማልደው ወይም ጣልቃ እንዲገባለት ፈልጎ ስለሸሸ፣ ኮብላይ ተብሎ ሊፈረጅ አይችልም፡፡
ጠቅለል ስናደርገው፣ በፊልሞና ቤት ውስጥ የተፈጠረው ችግር መነሻው፣ አናሲሞስ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ማለትም፣ በቸልተኝነት፣ በስንፍና ወይም በምቀኝት፣ ፊልሞናን አክስሮታል፡፡ እናም ይህ ችግር በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል ውጥረት ፈጥሯል፣ ውጥረቱም ፊልሞናን በጣም ስላስቆጣው፣ አናሲሞስን ሊቀጣው አስቦ ይሆናል፣ ይህም አናሲሞስን አስፈርቶታል፡፡ በመጨረሻም፣ አናሲሞስ ከጌታው ከፊልሞና እንዲሸሽ አደረገው፡፡ ምናልበትም ፊልሞና አናሲሞስን እንደኮብላይ ሊቆጥረው ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም የአናሲሞስ እውተኛ ተነሳስቶ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡
አማላጅነት
ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ ያካተታቸውን ሰዎችና ችግሮች ለይተናል፣ አሁን ደግሞ ጳውሎስ በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል ገብቶ ያከናወነውን የአማላጅነት ሥራ ወደ መመልከቱ እንሸጋገር፡፡ የጳውሎስን አማላጅነት ስንቃኝ፣ ሁለት ጉዳዮችን እንመለከታለን፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ ጥብቅና እንዲቆምለት አናሲሞስ ያቀረበውን ልመና፤ ሁለተኛ ደግሞ፣ ጳውሎስ የአናሲሞስ ጠበቃ ሊሆን መስማማቱን እናያለን፡፡ አስቀድመን አናሲሞስ ለጳውሎስ ያቀረበውን ልመና እንመልከት፡፡
የአናሲሞስ ልመና
በዚህ ወቅት፣ ጳውሎስ እስር ቤት ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ትምህርቶች እንዳወሳነው፣ የታሠረውም በሮም ሳይሆን እንደማይቀር የሚገመት ሲሆን፣ ሆኖም ደግሞ በቂሳርያዋ ማርቲማ ሊሆንም ይችላል፡፡ በሮምም ይሁን በቂሳርያዋ ማርቲማ፣ ፊልሞና ከሚኖርበት ከቂሳርያ በጣም የራቀ ነበር፡፡
አንዳንድ ምሁራን፣ ጳውሎስ እንዲያማልደውና ጥብቅና እንዲቆምለት ሊፈልግ የተጓዘው ይህ ርቀት ለአናሲሞስ ከበድ ያለ ርቀት ነው፡፡ ስለዚህ፣ አናሲሞስ ከፊልሞና ራቅ ብሎ አዲስ ኑሮ ለመጀመር ፈልጎ ነበር፣ ሆኖም ግን ጳውሎስን ያገኘው በድንገት ነው ብለው ይደመድማሉ፡፡
አናሲሞስ ከፊልሞና ሲኮበልል ምን አስቦ እንደነበር፣ ወይም ጳውሎስን በእስር ቤት ለማግኘት እንዴት እንደመጣ ቅዱሳት መጻሕፍት ምንም የሚሉት ነገር እንደሌለ ልንቀበል ይገባናል፡፡ ሆኖም ግን፣ ጥብቅና እንዲቆምለት ሊለምነው አናሲሞስ ጳውሎስን ፍለጋ ስለመሄዱ አንዳንድ ዝርዝሮችን ይነግሩናል፡፡
አንዱ ነገር፣ አናሲሞስ የሄደው ጳውሎስ ታስሮባት ወደነበረው ከተማ መሆኑ ነው፡፡ ጳውሎስ በዚያ እንደሚኖር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፣ ምክንያቱም በቆላስይስ የነበረችው ቤተክርስቲያን ኤጳፍራ በእስር ላይ የነበረውን ጳውሎስን እንዲንከባከብ ድጋፍ ታደርግለት የነበረ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንንም የምናገኘው በቆላስይስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 12 እና 13 ውስጥ፣ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ በጻፈበት ስፍራ ነው፡
ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።
ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና። (ቆላስይስ 4፡12-13)
አናሲሞስ የቆላስይስ ሰው እስከሆነ ድረስ፣ የእርሱ ጌታ ፊልሞና የቤተክርስቲያኒቱ እውቅ ሰው እስከሆነ ድረስ፣ ጳውሎስ የት እንደነበረ አናሲሞስ ሊያውቅ ይችላል፡፡ ይህንን እውቀት በልቡናችን ይዘን፣ አናሲሞስ በዚያችው ከተማ ለመቆየት መምረጡን መናገር እንችላለን፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ በከተማው ውስጥ በአንድ ወቅት፣ አናሲሞስ ከጳውሎስ ጋር ለመገናኘት ብርቱ ፍላጎት ነበረው፡፡ ጳውሎስ ደግሞ በቤት ውስጥ በእስር ላይ ነበር፣ ስለዚህም በነፃነት መንቀሳቀስ አይችልም ነበር፡፡ እንግዲያው አናሲሞስ በድንገት ጳውሎስን አይቶ ሮጦ ተጠመጠመበት ብሎ ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ አናሲሞስ ወደ ጳውሎስ የሄደው በዓላማ ነበር ማለት ነው፡፡
በመጨረሻ፣ ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈው አናሲሞስ አስቀድሞ ለእርሱ የተወደደ ወንድም ከሆነለት በኋላ ነው፡፡ ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ፣ አናሲሞስ የክርስትናን እምነት እንዲቀበል እንዳደረገው እና ጳውሎስ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት እንክብካቤ እንዳደረገለት ጠቅሷል፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ ጳውሎስ ለአናሲሞስ የተሟገተው አናሲሞስ ለጳውሎስ ታማኝነቱን ካሳየ በኋላ ነው፡፡ አናሲሞስ የጳውሎስን ትብቅና ለማግኘት ረጅም ጊዜ ከጳውሎስ ጋር እስከቆየ ድረስ፣ ጳውሎስ ደግሞ በእርሱ ችግር ውስጥ ገብቶ እንዲረዳው አስቦበት እንዳደረገው ማሰብ እንችላለን፡፡
ጳውሎስ ጥብቅና እንዲቆምለት አናሲሞስ ያቀረበውን ልመና ከተመለከትን፣ ጳውሎስ ደግሞ በጌታው በፊልሞና ፊት ለአናሲሞስ ሊሟገትለት ስለመስማማቱ ለመመልከት ዝግጁ እንሆናለን፡፡
የጳውሎስ ስምምነት
ጳውሎስ በአናሲሞስና በፊልሞና መካከል አማላጅ ለመሆን ወዲያውኑ አልተስማማም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ፣ አናሲሞስ የማያምንና እርባና የሌለው ባሪያ ነበር፣ ፊልሞና ደግሞ መልካም እና አፍቃሪ ሰው ነበር፡፡ ፊልሞና በአናሲሞስ ላይ ሊቆጣና ሊቀጣው መብት ነበረው፣ ይህንንም ፍትሃዊ ባልሆነና አግባብነት በሌለው መንገድ ሊያደርገው እንዳቀደ ፍንጭ የሚሰጠን ምንም ነገር የለም፡፡ ፊልሞና አናሲሞስን የመቅጣት መብቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ጳውሎስ ለአናሲሞስ የሚሟገትለት ከሆነ፣ የሙግቱ መሠረት ምህረት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ለአናሲሞስ ምህረት እንዲደረግለት ከመጠየቁ አስቀድሞ፣ አናሲሞስ ከልቡ ንስሓ የገባ መሆኑን በመጥቀስ ልመና ማቅረብ ነበረበት፡፡
ጳውሎስ ጅማሬው ላይ ያሳየው ቁጥብነት የሚደነቅ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ፣ አጥፊዎች ቅጣትን በመፍራታቸው ብቻ ይቅር እንዲባሉ መማለድ ሞኝነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ፣ ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 13 ቁጥር 4፣ የህዝብ ገዢዎች በዚህ ረገድ ስለሚኖራቸው ሚና የተናገረውን እናድምጥ፡
ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። (ሮሜ 13፡4)
ይኸው ተመሳሳይ መርሆ በበርካታ የዝምድና የሥልጣን እርከኖች ውስጥ ማለትም በወላጆችና በልጆች፣ በአንደኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የሮሜ ማኅበራዊ የሥልጣን ተዋረድ፣ በጌቶችና በባሪያዎች መካከልም ተፈፃሚነት አለው፡፡ እግዚአብሔር በሥልጣን ላይ የሚያስቀምጣቸወ ሰዎች ተገቢ የቅጣት እርምጃ ይወስዳሉ ምክንያቱም ሊደረግ የሚገባው ትክክለኛ ተግባር ነውና፡፡
እናም ስለዚህ፣ አንድ ባሪያ ወይም አገልጋይ የጌታው ወዳጅ አማላጅ እንዲሆንለት ልመና ሲያቀርብ፣ ያም ወዳጅ ጉዳዩ ቅጣት የሚገባው መሆኑንና ያንንም ማድረግ አግባብነት እንዳለው አስረግጦ ሳይናገር፣ ዝም ብሎ ጌታው ምህረት እንዲያደርግለት ወዳጁን አያስገድድም፡፡
ለማነፃፀር ይረዳን ዘንድ፣ አንድ የሮሜ ባሪያ የጌታው ወዳጅ የሆነ ሰው እንዲያማልደው ስላቀረበው ልመና ታሪክ ያስቀመጠልንን ምሳሌ እንመልከት፡፡ ከ111 ዓ.ም. ጥቂት ቀደም ብሎ፣ የሮሜው ሴናተር ታናሹ ፕሌኒ ለወዳጁ ሳቢኒያኑስ ደብዳቤ ጽፎ ነበር፡፡ ደብዳቤውም የሳቢኒያኑስ ባሪያ በነበረውና አሁን ነፃ በወጣው ሰው ምትክ የተፃፈ ነበር፡፡ ደብዳቤውም በታሪክ ተመዝግቦ ለእኛ ተላልፎልናል፡፡ ከፕሌኒ ደብዳቤ የተቀነጨበውን አድምጡ፡
የአንተ የነበረውና አሁን ነፃ የወጣው ሰው ምንኛ እንዳስቆጣህ ለእኔ የነገርከኝ ሰው፣ በእግሮቼ ላይ ተጠምጥሞ፣ እኔንም ልክ አንተን ያገኘ ያህል ተጠምጥሞብኝ ነበር፡፡ በብዙ እንባ እንድረዳው ተማፀነኝ … ከልቡ እንደተፀፀተ አሳምኖኛል፡፡ እኔም እንደተለወጠ አምኛለሁ፣ ምክንያቱም ስህተት እንደፈፀመ አስተውሏል … እባክህ የወጣትነቱን ዘመን፣ እንባውን እና የአንተንም ገር ልብ በማሰብ ራራለት፣ ስለዚህም እርሱንም ሆነ ራስህን ማሰቃየትህ ይብቃ፡፡
ልክ እንደ አናሲሞስ ሁሉ፣ ከሳቢኒያኑስ ባርነት ነጻ ወጥቶ የነበረው ሰው ለእርዳታ ወደ አሳዳሪው ጓደኛ ሄዶ ነበር፡፡ ደግሞም ልክ እንደ ጳውሎስ ሁሉ፣ ፕሌኒም ነጻነቱ እውነተኛ ንስሓን እና ቅን ዓላማን የተላበሰ መሆኑን እስኪያረጋግጥ ድረስ አስታራቂ ለመሆን ፈቃደኛ አልነበረም፡፡
ስለዚህ፣ አናሲሞስ በመጀመሪያ ጊዜ ከጳውሎስ ጋር የኖረው ዓላማው ከቅንነት የመነጨ መሆኑን ሐዋርያውን ሊያሳምነው ፈልጎ ነበር፡፡ እናም በዚህ ወቅት፣ ጳውሎስ ለአናሲሞስ ወንጌልን ሰበከለት መንፈስ ቅዱስም በክርስቶስ ወደ ማመን አመጣው፡፡ እውነተኛ ንስሓ ኃጢአትን በእውነት በመናዘዝ ከታጀበ፣ ፊልሞናን አስቆጥቶት የነበረውን በደል ሁሉ ተናዝዟል ብለን ብንደመድም ችግር የለበትም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም አናሲሞስ በክርስቶስ ካገኘው ከዚህ አዲስ ሕይወት የተነሳ፣ በእስር ላይ ያለውን ጳውሎስን ለማገልገል ራሱን ሰጠ፡፡ ጳውሎስም፣ በበኩሉ፣ ለዚህ አዲስ የእግዚአብሔር ልጅ አስፈላጊውን እንክብካቤ አደረገለት፣ ደግሞም እንደ ልጅ ይወድደውም ጀመር፡፡
አናሲሞስም አንድ ጊዜ በጳውሎ ፊት ሞገስን ካገኘ በኋላ፣ ወደ ፊልሞና መመለሱ አግባብነት ነበረው፡፡ ስለዚህም፣ አናሲሞስ የጳውሎስን የአማላጅነት ደብዳቤ ይዞ ወደ ቆላስይስ ሄደ፡፡ ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ መሠረት፣ እንደ ህጉ፣ አናሲሞስ እንደ ኮብላይ ሳይቆጠር ከጳውሎስ ጋር ሊቆይ ይችል ነበር፡፡ ከሞራል አንፃር ስንመለከተወ ግን ይህኛው ተመራጩ መፍትሄ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ ክርስቲያናዊው የደግነትና የእርቅ እሴት ወደ ፊልሞና የመመለሱን ነገር በብርቱ ይጠይቅ ነበር፡፡
ለዚህም ምክንያት የሆነውን ነገር በፊልሞና ከቁጥር 12 እስከ 16 ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ባሰፈራቸው ቃላት ውስጥ እናገኘዋለን፡
እርሱን እልከዋለሁ፤
አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፥
ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም።
ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤
ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፥ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በስጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም። (ፊልሞና 12-16)
ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ፊልሞና የመለሰው ስጦታው በፈቃድ ላይ የተመሠረተ እንጂ ግዴታው ስለሆነበት እንዳይሆን ፈልጎ ነው፣ ምክንያቱም የእርሱ ፍላጎት ፊልሞና እና አናሲሞስ በክርስቶስ ባገኙት ወንድማማችነት እርቅን እንዲፈጥሩ ነው፡፡
እርቃቸው የተዋጣለት የሚሆነው ፊት ለፊት ተገናኝተው አናሲሞስ ጥፋቱን ሲናዘዝ እና ፊልሞናን ይቅርታ ሲጠይቀው፣ ፊልሞናም በደግነት ይቅር ሲለውና አናሲሞስን ሲቀበለው እንደሆነ ይገመታል፡፡ ፊልሞና ጥልቅ ፍቅር ያለው ክርስቲያን ስለመሆኑ ጳውሎስ ያቀረበውን ምሥጋና፣ ደግሞም ጳውሎስ የአናሲሞስ ብርቱ ጠበቃ የመሆኑን ነገር ስናስብ፣ ጳውሎስ ይጠብቅ የነበረው ውጤት ይህ እንደሆነ እንገምታለን፡፡
አወቃቀርና ይዘት
ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን ደብዳቤ ዳራ ከመረመርን፣ አሁን ደግሞ አወቃቀሩንና ይዘቱን ወደ መመልከቱ እንሸጋገራለን፡፡ ያንንም የምናደርገው ጳውሎስ አናሲሞስንና በፊልሞናን ለማስታረቅ የተጠቀመበትን ስልትና የመከራከሪያ ነጥቦች መዳሰስ ነው፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈው ደብዳቤ በብዙ መንገዶች ለየት ያለ ነው፡፡ አንደኛው፣ ከጳውሎስ ደብዳቤዎች መካከል በቅዱሱ መጽሐፍ ካኖን ውስጥ የተካተተና በአስተምህሮ ላይ ያላተኮረ መሆኑ ነው፡፡ በፊልሞና፣ ጳውሎስ የጻፈው እንደ አስተማሪ ሳይሆን አንደ ጠበቃ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ በተቀሩት ደብዳቤዎቹ ሁሉ ላይ፣ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ይጠቅሳል፣ ያንንም ያደርግ የነበረው ነገሮች በእርሱ ትእዛዝ መሠረት እንዲከናወን ብሎ ነው፡፡ በፊልሞና ግን፣ ጳውሎስ ወዳጁን ላለማዘዝ የቆረጠ ይመስላል፣ ይልቁኑ በወንጌል አብሮ ሠራተኛ እንደሆነ ሰው ሊቀርበውና በጎነትን እንዲያደርግለት ሊጠይቅ ወደደ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ፊልሞና የጳውሎስ ግለሰብ ተኮር ደብዳቤ ሲሆን፣ ለአናሲሞስና ለፊልሞና ያለውን ጥልቅ ሸክም የገለጠበት ደግሞም ወዳጅነታቸውን መሠረት አድርጎ ጥያቄውን ያቀረበበት ነው፡፡
በአጭሩ፣ በፊልሞና ውስጥ፣ ትሁት የሆነውን የእግዚአብሔር ሰው በተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ማለትም፣ ሃላፊነት ሲወስድ፣ ሌሎችን ተጠያቂ ሲደርግ እና የክርስቶስን ፍቅር ሲገልጥ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ በደብዳቤ ውስጥ ያሉትን ዝርዝሮች መመልከት ስንጀምር፣ በጳውሎስ ክርስቲያናዊ ዝንባሌ እና ተግባር ላይ ለየት ያለ ትኩረት እናደርጋለን፣ ያንንም የምናደርገው እነዚያኑ ሃሳቦች በሌሎች የእስር ደብዳቤዎቹ እንዴት ተግባራዊ እንዳደረጋቸው በመመልከት ነው፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ አወቃቀርና ይዘት ላይ የምናደርገው ውይይት በራሱ በደብዳቤው ውስጥ ያለውን አስተዋፅዖ ይከተላል፣ ከቁጥር 1 እስከ 3 በሚገኘው ሰላምታ ይጀምርና ከቁጥር 4 እስከ 7 በሚገኘው የጳውሎስ ምሥጋና ይቀጥላል፣ ከዚያም ከቁጥር 8 እስከ 21 በሚገኘውና ጳውሎስ በአናሲሞስ ምትክ ያቀረበውን ልመና ያቀርባል በስተመጨረሻም ከቁጥር 22 እስከ 25 በሚገኘው የመጨረሻ ሰላምታ ይጠናቀቃል፡፡ እስኪ ከቁጥር 1 እስከ 3 የሚገኘውን ሰላምታ በመመልከት እንጀምር፡፡
ሰላምታ
ከቁጥር 1 እስከ 3 የሚገኘው ሰላምታ፣ ጳውሎስን የደብዳቤው ተቀዳሚ ጸሃፊ አድርጎ ያቀርበዋል ደግሞም ደብዳቤው በተጨማሪም ከጢሞቴዎስም እንደመጣ ይገልፃል፡፡ ከዚያም ፊልሞናን እንደ ደብዳቤው ተቀዳሚ ተቀባይ ይጠቅሰውና በደብዳቤው ሰላምታ የተቸራቸውን ሌሎች ሰዎች ማለትም አፍብያ፣ አክርጳ ደግሞም ፊልሞና አባል የሆነባት አጥቢያ ቤተክርስቲያንም ተጠቅሰዋል፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና እጅግ ከባድ የሆነና የጠየቀውን በጎነት ለማድረግ ፈታኝ ሊሆንበት የሚችለውን ጉዳይ እንደሚያነሳ ያውቃል፡፡ ስለዚህ፣ ጉዳዩ በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል ብቻ እንዲቆይ ከማድረግ ይልቅ፣ ጳውሎስ ለአናሲሞስ አማላጅ የሚሆንበትን ተግባር የፊልሞና ቤተሰብና ቤተክርስቲያኒቱም በእማኝነት እንዲሳተፉበት መጋበዝን ምርጫው ያደርጋል፡፡ በርካታ አማኞች ጉዳዩን በንቃት የሚከታተሉት መሆኑን የማወቁ ነገር ፊልሞና ለአናሲሞስ ገርነትን እንዲያሳይ እንደሚያበረታታው ጳውሎስ ያለ ጥርጥር ያውቅ ነበር፡፡ ሰላምታውን የሚያጠናቅቀው በተለመደው የሰላምታ አቀራረብ ዘይቤ ቡራኬ በመስጠት ነው፡፡
ምስጋና
ሰላምታውን አስከትሎም፣ በቁጥር 4 እስከ 7 ውስጥ ጳውሎስ ለፊልሞና ያቀረበውን ምሥጋና እናገኛለን፡፡፡ ጳውሎስ በተለምዶ በደብዳቤዎቹ ውስጥ እዚህ ነጥብ ላይ ምስጋና ያቀርባል፡፡ ጳውሎስ በዋናነት የተናገረው ፊልሞና ለቤተክርስቲያን ስላለው ፍቅር፣ ደግሞም በቆላስይስ ለሚኖሩ አማኞች ፊልሞና በረከት የሆነባቸውን መንገዶች በማንሳት ጌታን ያመሰግናል፡፡ ጳውሎስ ከቁጥር 5 እስከ 7 ድረስ ፊልሞናን አንዲህ በማለት ያመሰግነዋል፡
በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ፥ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤
የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ (ፊልሞና 5-7)
ጳውሎስ ፊልሞና ያደረጋቸውን ነገሮ አልዘረዘረም፣ ሆኖም ለቅዱሳን ሁሉ መነቃቃት እንደሆነ ግን ጠቅሷል፡፡ ምናልባትም ፊልሞና ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች አሳርፏቸው ሊሆን ይችላል፣ ወይም እነርሱን በአንድ መንገድ አገልግሎ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ደግሞ አንድ ሌላ በረከት የሆነ ነገር አድርጎ ይሆናል፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ ፊልሞና አንድ መልካም ሆነ ነገር ከቀና ልብ አድርጓል ማለት ነው፡፡ እናም አናሲሞስም የቤተክርስቲያኒቷ አካል እስከሆነ ድረስ፣ ፊልሞና ለሌሎች የሚያሳየውን ፍቅር ለእርሱም እንዲያሳይ ጳውሎስ ይጠብቃል፡፡
በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል የነበረውነ ሁኔታ ጳውሎስ በቆላስይስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 12 እስከ 14 ባስቀመጠው ትምህርት መነጽር ተመልከቱት፡፡ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፡
እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤
በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። (ቆላስ 3፡12-14)
እግዚአብሔር አማኞችን ሁሉ እንደሚወድድና ይቅርም እንደሚላቸው እንዲያስታውሱ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች ፊልሞናን ጨምሮ ጥሪ ያቀርባል፡፡ ስለዚህ እርሰ በርሳቸው ያንኑ ፈቅር እንዲለማመዱ፣ አንድ ስህተት ሲፈጸምም እርስ በርስ በትዕግሥት እንዲሸካከሙ ደግሞም ካሳ ከመጠበቅ ይልቅ በተበደሉት ነገር ይቅር እንዲሉ ያበረታታቸዋል፡፡
ስለዚህ በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል የነበረውን ነገር ከዚህ አንፃር ማዛመድ አይከብድም፡፡ አናሲሞስ ፊልሞናን በድሏል፣ ጳውሎስም ይህንን አረጋግጧል፡፡ ሆኖም ግን፣ ፊልሞና ለሌሎች በሚያሳየው ፍቅር ልክ አናሲሞስንም አዘውትሮ እንዲወድደው ይጠይቀዋል፡፡ የደረሰበትን በደል በትዕግሥት እንዲሸከም እና አናሲሞስንም ከመቅጣት ይልቅ ይቅር እንዲለው ፊልሞናን ይጠይቀዋል፡፡ ጳውሎስ ለፊልሞና ፈቅር እውቅና በመስጠት፣ ይኸው ባህርዩ እንዳይዋዥቅ፣ በአናሲሞስም ጉዳይ ቁጣው ፈቅሩን እንዳይሸለሽረው ያበረታታዋል፡፡
ልመና
ጳውሎስ የምሥጋና መልእክቱን ካጠናቀቀ በኋላ፣ ከቁጥር 8 እስከ 21 ድረስ ጳውሎስ ልመናውን ለፊልሞና ያቀርባል፡፡ ልመናው የዳብዳቤውን ዋና ዓላማ ያነገበ ሲሆን፣ ይህም በፊልሞና ፊት የአናሲሞስ ጠበቃ ሆኖ መቆም ነው፡፡ ልመናውንም በበለጠ ጥልቀት የምንመለከት ሲሆን፣ ከታች በተዘረዘሩት ስድስት ውቅረ ነገሮች እንቃኘዋለን፡
ከቁጥር 8 እስከ 10፣ ጳውሎስ የጥብቅና ድርሻውን ያብራራል፤
ከቁጥር 11 እስከ 13 ደግሞ አናሲሞስ እንደ ልመና አቅራቢ ያለውን ድርሻ ያብራራል፤
በቁጥር 14 ደግሞ ፊልሞና እንደ ጌታ ያለውን ድርሻ ያብራራል፤
በቁጥር 15 እና 16 ደግሞ የፍጥረተ ዓለም መጋቢ የሆነውን የእግዚአብሔርን ድርሻ ያብራራል፤
ከቁጥር 17 እስከ 20 ደግሞ የጳውሎስን የራሱን ልመና ያቀርባል፤
በቁጥር 21 ደግሞ ጳውሎስ ያቀረበወ ልመና እንደሚሰማለት ያለውን እርግጠኝት ያስረዳል፡፡
እስኪ አስቀድመን ጳውሎስ እንደ ጠበቃ ስለሚኖረው ድርሻ የሰጠውን ማብራሪያ እንይ፡
ጳውሎስ እንደ ጠበቃ
በፊልሞና ቁጥር 8 እስከ 10 ጳውሎስ የተናገረውን እናድምጥ፡
ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥
ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ።
አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። (ፊልሞና 8-10)
ጳውሎስ የክርስቶስ ሐዋርያ ስለሆነ፣ ፊልሞና ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርግ የማዘዝ ሥልጣን ነበረው፡፡ ከዚሕ ይልቅ ግን፣ የፊልሞናን ርኅራኄና ደግነት ሊቀሰቅስ በሚችል መንገድ ለፊልሞና መጻፍን መረጠ፡፡
በዚህ ምንባብ ውስጥ፣ ጳውሎስ እንደ አንድ እርዳታ እንደሚፈልግ ደካማ ሽማግሌ ነው የሚናገረው፡፡ በሌሎቹ ደብዳቤዎቹ ይጠቀምባቸው የነበሩትን ጠንካራ የአጻጻፍ ስልቶች ለሚያውቁ ሰዎች ይህኛው ያልተለመደ ዓይነት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ጳውሎስ ሰዎች ሥልጣኑን እንዲያከብሩና ለአስተምህሮዎቹም ራሳቸውን እንዲያስገዙ ሲጠይቅ ነው የምናገኘው፡፡ ታዲያ አሁን የፊልሞናን ልብ በማባባት ሊያግባባው እየሞከረ ይመስላችኋል? አይደለም፡፡ ይህኛው ጳውሎስ በሌሎች ደብዳቤዎቹ ተገልጦ የማናገኘው ሌላኛው የጳውሎስ ትክክለኛ ገጽታ ነው፡፡
ያኛውን የጳውሎስ ማንነት አስመልክቶ የቆሮንቶስን ቤተክርስቲያን የወቀሰበትን መንገድ በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 10 ውስጥ እንመልከት፡
መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። (2ኛ ቆሮንቶስ 10፡10)
ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ እጅግ ኃይለኛ፣ ሊገመት በሚያዳግት መንገድ በእስር ቤት ውስጥ ግን ትሁት የመሆኑ ነገር ነቀፋውን የሰላ አድርጎበታል፡፡ ጳውሎስ በስብዕናው፣ በጣም ትኁት ነው፡፡ ይህም ሊያስገርመን አይገባም፡፡ እንዲያውም ጳውሎስ ክርስቶስን የመምሰል ናፍቆት ነበረው፣ እርሱም ደግሞ መቼ ጉልበተኛ መቼ ደግሞ ትኁት መሆን እንደሚገባ ያውቃል፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁር 5 እስከ 8 ጳውሎስ ያስተማረውን እንመልክት፡
በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።
እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። (ፊልጵስዩስ 2፡5-8)
ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰው የሆነው አምላክ፣ ብርቱ አስተማሪ ነበር፡፡ ሆኖም አሰቃቂ ወንጀለኞች በሚቀጡበት ስቅላት በተራ ፍጡራን እስኪገደል ድረስ ራሱን ትኁት ያደረገ ነበር፡፡ እንግዲያው፣ እርሱን በተመሳሳይ መንገድ ሊመስለው የሚገባውም የእርሱ ሐዋርያ ብቻ ነው፡፡ ያም ማለት አንዳንድ ጊዜ በጣም ብርቱ ስብዕና ደግሞም የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልገው እና ለሌሎች ደግሞ ረጋ ያለ ሰው መሆን ማለት ነው፡፡
ጳውሎስ ሐዋርያ ስለነበር፣ ፊልሞናን ማታለል ወይም መጠቀሚያ ማድረግ አያስፈልገውም፡፡ ቢፈልግ ኖሮ፣ ፊልሞና እንዲታዘዘው ማድረግ ይችል ነበር፡፡ አድርጎት ቢሆን ኖሮ፣ ፊልሞናም ምናልባት እሺ ይል ይሆናል፡፡ ሆኖም ጳውሎስ ፊልሞና ለዚህ ሁኔታ ምላሽ እንዲሰጥ የፈለገው በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ነበር፡፡ ስለዚህም፣ የፊልሞናን ልብ መማረክ ፈለገ፣ እናም በእስር ላይ ለሚገኝ ሽማግሌና በቅርቡም በክርስቶስ ያመነ ወንድምና የእርሱም አገልጋይ ለሆነው ሰው እንዲራራ ጠየቀው፡፡ ጳውሎስ ራሱን እንደ አናሲሞስ ጠበቃ ያቀረበው በዚህ ዓይነት አመለካከት ነበር፡፡
ጳውሎስ ራሱን እንደ አናሲሞስ ተሟጋች ካስተዋወቀ በኋላ፣ ስለ አናሲሞስ ደግሞ ከቁጥር 11 እስከ 13 ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም ሐዋርያው የአናሲሞስን ልመና በፊልሞና ፊት ሊያቀርብ የተነሳሳበትንና በአናሲሞስና በጳውሎስ መካከል የነበረውንም ግንኙነት በጥልቀት አብራርቷል፡፡
አናስሞስ እንደ ልመና አቅራቢ
በፊልሞና ቁጥር 11 እስከ 13 ጳውሎስ እንዲህ ጽፏል፡
አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ።
እርሱን እልከዋለሁ፤
አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፥ (ፊልሞና 11-13)
ጳውሎስ አሁን እየገለጸው ያለው አናሲሞስ፣ አማላጅ እንዲሆነው ሊጠይቀው ከመጣው ሰውዬ ለየት ያለ ሰው ነው፡፡ አናሲሞስ ምንም እርባና ያልነበረወ ባሪያ ነበር፡፡ ሆኖም ወደ ክርስቶስ መጣ፤ ኃጢአቱንም ተናዘዘ፣ መንገዱንም አስተካከለ፣ መልካም እምነቱንም በእስር ላይ የነበረውን ጳውሎስን በቅንነትና በትጋት በማገልገል አሳየ፡፡ ፊልሞና አፍቃሪ ክርስቲያን እንደሆነ ጳውሎስ ስሚያውቅ፣ አናሲሞስ ወደ ክርስቶስ መምጣቱን ሲሰማ ደስ እንደሚለውና ሌሎች ክርስቲያኖች ሲበድሉት ይቅር እንደሚል ሁሉ የእርሱንም መተላለፍ ይቅር እንደሚለው ይጠብቅ ነበር፡፡
ጳውሎስ በፊልሞና ቁጥር 11 እስከ 13 ስለ አናሲሞስ መለወጥ አፅንዖት ለመስጠት የቃላት ጨዋታን ተጠቅሟል፡፡ በተለይም chrēstos (χρηστος) በሚገርም መንገድ christos (χριστος) ማለትም ክርስቶስ ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ጳውሎስ የማይጠቅም ለሚለው ሃሳብ የተጠቀመው ቃል achrēstos (α’χρηστος) “አ” ከተሰኘችው የግሪክ ቀዳሚ ፊደል ትርጉሙም “ያልሆነ” እና ሥርወ ቃሉ chrēstos “የሚጠቅም” የሚል ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ጳውሎስ “የሚጠቅም” ለሚለው የተጠቀመው ቃል euchrēstos (ευ’χρηστος) ዩ የምትለው የግሪክ ቀዳሚ ፊደል መልካም ወይም ጥሩ ማለት ሲሆን፣ ስርወ ቃሉ chrēstos የሚጠቅም ማለት ነው፡፡ የቃላት ጨዋታው እንግዲህ ይህ ነው፡ አናሲሞስ ከክርስቶስ ውጪ achristos በነበረ ጊዜ የማይጠቅም ወይም achrēstos ነበር፡፡ ሆኖም ክርስቶስን ሲቀበል በጣም የሚጠቅም euchrēstos (ευ’χρηστος) ሆነ ማለት ነው፡፡
አናሲሞስ መተላለፉን የማካካሱን ሥራ የጀመረ መሆኑን የሚያሳዩ መንገዶችንም ጳውሎስ አመልክቷል፡፡ ጳውሎስ እንደጻፈው፣ አናሲሞስ ጳውሎስን በማገልገል የፊልሞናን ድርሻ እየተወጣለት ነበር፡፡
በጥንታዊው ዓለም፣ አንድ ጌታ ባሪያውን ለሌላ ሰው የማበደሩ ጉዳይ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ይህ ተግባር ልክ እንደ ክቡር ስጦታ ይቆጠራል፣ ማለትም ጌታው ባሪያውን በሰጠበት ወቅት ሳይሠራለት ሚቀረው ሥራ፣ ባሪያውን ለሰጠው ሰው ግን ትርፍ ነው፣ ስለዚህ አንድ ሰው ባሪያውን በመስጠት ቸርነት ያደርጋል፡፡ በዚህ ረገድ፣ በአናሲሞስ አማካይነት፣ ፊልሞና ጳውሎን በእውነት አገልግሏል ማለት ነው፡፡ ጳውሎስም ስለ አናሲሞስ ሲናገር አናሲሞስ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለፊልሞናም ጠቃሚ ሆኗል ያለው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ፊልሞና ለአናሲሞስ ምህረትን እንዲያደርግ የሚያስገድደው ብዙ ምክንያት አለ፡፡
በስተመጨረሻም፣ ጳውሎስ በዚህ ክፍል አናሲሞስን እንደገና ወደ ፊልሞና እንደሚልከው ይናገራል፣ የሚገመተውም የጳውሎስን ደብዳቤ ለፊልሞና ያደርሳል፣ ምናልባትም ከቲኪቆስ ጋር አብሮ ይሄድ ይሆናል፡፡ ጳውሎስ ይህንን በፊልሞና ቁጥር 12 ውስጥ፣ እንዲህ በማለት ጠቅሶታል፡
እርሱን እልከዋለሁ፤ (ፊልሞና 12)
አናሲሞስ ወደ ቆላስይስ የሚመለሰው ከፊልሞና ምህረትን ሊለምን፣ ከእርሱ ጋር የመታረቅንም ተስፋ ሰንቆ ሲሆን፣ ምናልባትም ነፃ መውጣትንም ተስፋ ሊያደርግ ይችላል፡፡ አናሲሞስ ኩብለላን ምርጫ አላደረገም፣ ወደ ጌታው በመመለስ የጌታውን ፍርድ መቀበልን ምርጫው አደረገ፡፡
ፊልሞና እንደ ጌታ
ጳውሎስ የራሱን ድርሻ እንደ አማላጅ፣ የአናሲሞስን ደግሞ እንደ ለማኝ ከገለጸ በኋላ፣ በቁጥር 14 ውስጥ የፊልሞናን ድርሻ እንደ ጌታ ወደ መጥቀሱ ይሸጋገራል፡፡
በዚህ ስፍራ፣ ጳውሎስ ፊልሞና በአናሲሞስ ላይ ላለው ሥልጣን እውቅና ይሰጣል፣ ደግሞም ፊልሞናን ከማዘዝ ይልቅ ልመና ማቅረብ መረጠበትን ተነሳስቶውን ይገልፃል፡፡ ጳውሎስ በፊልሞና 14 እንዲህ ይጽፋል፡
ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም። (ፊልሞና 14)
ጳውሎስ ይፈልግ የነበረው ፊልሞና በራሱ መልካም ማድረግን እንዲመርጥ ነበር፡፡ ስለዚህም ልመናው፣ በጥያቄ መልክ እንጂ በሐዋርያዊ ሥልጣን በትዕዛዝ መልክ እንዳልሆነ ግልጽ አድርጎታል፡፡
የሚወድደው ሰው ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛ ምክንያት በማድረግ ሰማያዊ ብድራት እንዲቀበል ፈልጎ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በፍፁም ፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ እርቅ በክርስቶስ ያላቸውን የወንድማማች ግንኑነት ብርቱ እንደሚያደርገውም ያስባል፡፡ በተጨማሪም፣ ጳውሎስ ለፊልሞና አክብሮትን ማሳየት ፈልጓል፣ የእርሱም ቸርነት ደግሞ ለእዳው ማካካሻ እንዲሆንም የሚጠቅስ ይመስላል፡፡ ከዚያም፣ ፊልሞና አናሲሞስን በአግባቡ ቢቀበለው፣ ለጳውሎስም ሆነ ለቤተክርስቲያን ትልቅ ማበረታቻ ይሆናል፡፡ ጳውሎስ በፊልሞና ቁጥር 7 እስከ 9 እንዲህ ብሎ የጻፈው በዚህ ምክንያት ነበር፡
የቅዱሳን ልብ በአንተ ስራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ፥ በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና።
ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥
ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። (ፊልሞና 7-9)
በመሠረታዊነት፣ ፊልሞና ለቤተክርስቲያን የነበረው የቀደመ ፍቅር አሁን ደግሞ ለአናሲሞስም እንደሚገለፅ ጳውሎስ ያለ ጥርጥር እንዲያስብ አድርጎታል፡፡
በየትኛውም መስፈርት፣ ጳውሎስ በብዙ ምክንያቶች ይህኛውን መንገድ መርጧል፣ አንደኛው ፊልሞና ሮማውያን ጌቶች በባሮቻቸው ላይ በፈራጅነት በሚቀመጡበት ትውፊታዊ መንገድ እንዲጓዝና የጭካኔ ውሳኔ በመወሰን፣ አናሲሞስን መቅጣትን እንዲመርጥ መተው፡፡ ወይም ደግሞ ስለ ክርስቶስ እና ስለ ወዳጁ ስለ ጳውሎስ ሲል፣ አናሲሞስን በምህረት እንዲመለከተው ማድረግ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጳውሎስ ትክክለኛው ምርጫ የትኛው እንደሆነ ጳውሎስ ደጋግሞ ቢገልጽም፣ የወደደውን የማድረግ ምርጫ ግን የእርሱ ነው፡፡
እግዚአብሔር እንደ ገዢ
ጳውሎስ ሰዎች እርስ በርስ የሚኖራቸውን የግንኑነት ሃላፊነትና ድርሻ ከጠቀሰ በኋላ፣ በቁጥር 15 እና 16 ውስጥ የእግዚአብሔርን መግቦታዊ ገዢነት ለፊልሞና ያሳስበዋል፡፡ በዚህ ክፍል፣ እግዚአብሔር የአናሲሞስን ኃጢአት ይቅር በማለት የሰጠው መልካም በረከት፣ ወደላቀ እርከን የሚደርሰው ፊልሞና ልመናውን ሲቀበል እንደሆነ ይገልጻል፡
ጳውሎስ እነዚህን የሚያበረታቱ ቃላት በቁጥር 15 እና 16 ውስጥ በመጥቀስ የእግዚአብሔርን መግቦታዊ ገዢነት አመልክቷል፡
ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤
ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፥ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በስጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም። (ፊልሞና 15-16)
ጌታ በመግቦቱ በፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ይቆጣጠራል፡፡ የእርሱን በጎ ዓላማዎች ለማሳካትም ክፉ ነገሮች እንዲከናወኑ ይፈቅዳል፡፡ በዚህ ጉዳይም ረገድ፣ እግዚአብሔር አናሲሞስ የጳውሎስን አማላጅነት ፍለጋ እንዲሄድ ያደረገውን ጠብ በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል እንዲፈጠር አድርጓል በማለት ጳውሎስ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ ጌታም ይህ እንዲሆን የፈቀደው፣ በጳውሎስ አገልግሎት አማካይነት፣ አናሲሞስን በክርስቶስ ወደ ማመን ለማምጣት እና ከፊልሞናም ጋር በማስታረቅ አናሲሞስም በጌታ ከፊልሞና እኩል ወደሚሆንበት እርከን ለማምጣት ነው፡፡
ጳውሎስ እግዚአብሔር በፍጥረተ-ዓለሙ ላይ ያለውን መግቦታዊ ቁጥጥር በመጥቀስ፣ ፊልሞና ከአናሲሞስ ጋር ከመጣላት እንዲታቀብና ጉዳዩን ከእግዚአብሔር አቅድ አንፃር እንዲመለከተው ይጠይቀዋል፡፡ አዎን፣ ፊልሞና ተቆጥቷል፣ የመቆጣትም መብት አለው፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር በመከራቸው አልፎ ሊያመጣ ካለው በረከት ጋር ሲነፃፀር ከአናሲሞስ ጋር የተፈጠረው ችግር ከቁጥር የሚገባ አልነበረም፡፡
ፊልሞና መልካም ሰው ነበር፡፡ ከአናሲሞስ ጋር የተፈጠረውን ግጭት እግዚአብሔር የተፋውን ነፍስ ለማዳን እንዳቀናበረው ሲገባው፣ ልክ ጳውሎስ ተስፋ እንደሚያደርገው ቁጣው ወደ ደስታ ይለወጣል፡፡
ልመና
በአማላጅነቱ ውስጥ ድርሻ ያላቸውን ገጸ-ባሕርያት ካስተዋወቀ በኋላ፣ ጳውሎስ በስተመጨረሻ ከቁጥር 17 እስከ 20 ልመናውን ያቀርባል፡፡ በተለይም፣ ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር እንዲለው እና ከባሪያው የሚጠብቀውም ካሳ ካለ ራሱን በአናሲሞስ ምትክ በማቅረብ ዕዳው በእርሱ ላይ እንዲቆጠር ይለምናል፡፡
ጳውሎስ ያቀረበው መንታ ልመና በፊልሞና ቁጥር 17 እና 18 ውስጥ ጠቅለል ብሎ ቀርቧል፡
እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ብትቈጥረኝ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው።
በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቍጠር፤
(ፊልሞና 17-18)
በዚህ ስፍራ ጳውሎስ ያደረገውን ነገር ልብ በሉ፡ ፊልሞና የግል ቸርነት እንዲያደርግለት ይለምናል፣ ያን ሲያደርግም ጳውሎስ ራሱ የፊልሞና ደግነት እንደሚያስፈልገው ዓይነት አድርጎ ራሱን ያቀርባል፡፡ አናሲሞስ ወደ ፊልሞና የመመለስ መብት አለው ብሎ አይከራከርም፡፡ በተቃራኒው፣ አናሲሞስ ቅጣት እንደሚገባው ያመለክታል፡፡ ፊልሞና ለአናሲሞስ የክርስቶስን ዓይነት ይቅርታ እንዲያደርግለት አልጠየቀውም፡፡
በተለዋጭ ዘይቤያዊ አቀራረብ፣ ጳውሎስ ራሱን የአናሲሞስ ተከላካይ ጠበቃ አስመስሎ በማቅረብ፣ ፊልሞና ስለ አናሲሞስ ሲል ምህረት እንዲያደርግለት አልለመነም፡፡ ይልቁኑ፣ በአናሲሞስ ፊት እንደ አባትና ጠባቂ በመቆም፣ ፊልሞናን ይከላከልለታል ደግሞም ስለ ጳውሎስ ሲል ፊልሞና ምህረት ሊያደርግ የሚገባባቸውን ምክንያቶች ያቀርባል፡፡
ጳውሎስ በፊልሞና ቁር 20 ልመናውን የደመደመበትን ቃል አድምጡ፡
አዎን፥ ወንድሜ ሆይ፥ በጌታ እኔ እንድጠቀምብህ ይሁን፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ። (ፊልሞና 20)
ፊልሞና ለጳውሎስ ካለው ከበሬታ የተነሳ ለጳውሎስ መንፈሳዊ ልጅ ለአናሲሞስ ምህረትን እንደሚያደርግለት ጳውሎስ ተስፋ ያደርጋል፡፡ እናም፣ ጳውሎስ በልመናው፣ በፍፁም ልቡ ለሚወድደው ለልጁ በጎነትን በማድረግ ሐዋርያውን እንዲያገለግል ጳውሎስ ፊልሞናን ይጠይቃል፡፡
በዚህ ስፍራ ጳውሎስ የተጠቀመውን ቋንቋ ልብ በሉ፡፡ በመጀመሪያ ጳውሎስ የአናሲሞስ ስም የተመሠረተበትን ο’νιναμαι የግሪክ ቃል በመጠቀም ፊልሞና “እንዲጠቅመው” ይጠይቃል፡፡ በመሠረታዊነት የሚያነሳው፣ ፊልሞና ጳውሎስን በመጥቀም ረገድ የባሪያውን ምሳሌ እንዲከተል ነው፡፡
ሁለተኛ፣ ጳውሎስ “ማሳረፍ” የሚለውን ቃል እንደገና ያነሳዋል፡፡ በቁጥር 7 ውስጥ ፊልሞና የቅዱሳንን ልብ እንዳሳረፈ ጠቅሷል፡፡ በዚህ ስፍራ ደግሞ፣ ፊልሞና በእስር ላይ ያለውን ሐዋርያ በማሳረፍ ደግነቱን እንዲያበዛ ጳውሎስ ያበረታታዋል፡፡
ምሁራኑ የጳውሎስን ልመና አስመልክቶ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ አንዳዶቹ ጳውሎስ ፊልሞናን እየጠየቀ ያለው አናሲሞስን በምህረትና በበጎነት እንዲቀበለው፣ ላጠፋውም ጥፋት ምንም ዓይነት ካሳ እንዳይይቀውና የሚገባውንም ቅጣት እንኳን እንዳይቀጣው ነው ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ፣ ጳውሎስ ፊልሞናን እየጠየቀ ያለው ከዚያ የዘለለ ነገር ነው፣ ያም አናሲሞስን ነፃ በማውጣት፣ ነፃነቱን እንዲያውጅለት ነው ብለው ያምናሉ፡፡
ይህም አባባል የተንተራሰው ጳውሎስ በፊልሞና 15 እና 16 እንዲህ ብሎ የተናገረውን ቃል ነው፡
ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤
ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፥ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በስጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም? (ፊልሞና 15-16)
እነዚህን ጥቅሶች ስናነብብ ጳውሎስ ፊልሞና እንዲያደርግ የሚፈልገው፣ አናሲሞስን ነፃ እንዲያወጣውና ከዚያም በኋላ አናሲሞስ ተመልሶ ባሪያ እንዳይሆን ነው በሚል ትርጓሜ ማንበብ ይቻላል፡፡ ይህ ሃሳብ ይበልጥ የሚጠናከርልን በዚህ ስፍራ የተጠቀሰው የግሪክ ቃል αινωνιον, በትክክለኛዎቹ የእንግሊዝኛ ቅጂዎች ሲፈታ “ለዘላለም” የሚል ፍቺ ነው የያዘው፡፡ (በዚህ ረገድ አማርኛውም ለዘላለም ተብሎ ነውና የተተረጎመው ከግሪኩ ቃል ጋር ይስማማል፡፡) ምንም እንኳን የሮማውያን የባሪያ ሥርዓት አብዛኛውን ጊዜ ለዕድሜ ልክ ቢሆንም፣ በቴክኒካዊ ይዘቱ ግን ለጊዜው የሚደረግ ውል ነው፣ ስለዚህ ጳውሎስ አናሲሞስ ለዘላለም የእርሱ ባሪያ ሆኖ እንዲኖር ማረጋገጫ እንደማይሰጥ እሙን ነው፡፡ ለዘላለም የሚዘልቀው በክርስቶስ ያገኘነው ወዳጅነት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ጥቅስ ስናነብብ ፊልሞና ለአናሲሞስ ነፃነቱን ይሰጣል ወይስ በባርነቱ እንዲቀጥል ያደርጋል የሚለው ነገር ግርታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
ግን በዚህ ወቅት፣ አንድ ነገር ልብ ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ ክርስቲያን ጌቶች ያመኑ ባሮቻቸውን ነፃ ማውጣት አለባቸው የሚል ትምህርት ጳውሎስ አላስተማረም፡፡ ልክ ነው በ1ኛ ቆሮንቶስ 7፡21 ነፃነት የባርነት ትልቅ ደስታ ነው ብሎ አስተምሯል፡፡ ሆኖም ግን ያመኑ ባሮች ጌቶቻቸውን በበለጠ ትኅትና ሊያገለግሉ እንጂ ሊንቋቸው እንደማይገባ አስተምሯል፡፡ ለምሳሌ በ1ኛ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 2 እንዲህ አስተምሯል፡፡
የሚያምኑም ጌቶች ያሉአቸው፥ ወንድሞች ስለ ሆኑ አይናቁአቸው፥ ነገር ግን በመልካም ሥራቸው የሚጠቅሙ የሚያምኑና የተወደዱ ስለ ሆኑ፥ ከፊት ይልቅ ያገልግሉ። (1ኛ ጢሞ 6፡2)
በበርካታ መንገዶች ስንመለከተው ባርነት በታሪክ ዘመናት ሁሉ እጅግ አሰቃቂ ሥርዓት እንደሆነ እናስታውሳለን፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሲናገር መስማት እንግዳ ሊሆን ይችላል፡፡ የዘመናችን ሰዎች ስለ ባርነት ሲያስቡ፣ አብዛኛውን ጊዜ የሚያስቡት ዘግናኝ የሆነውን የአፍሪካን የባሪያ ንግድ ነው፡፡ በቶሎ ወደ አዕምሯችን የሚመጡት በጉልበት ለባርነት የሚሰጡትን፣ ከቤተሰቦቻቸው የሚገነጠሉትን እና በሰው አዕምሮ ለማሰብ አንኳን የሚዘገንን ግፍ የሚፈጸምባቸውን ሰዎች ነው፡፡
ተደፍረዋል፣ ተደብድበዋል፣ በጋለ ብረት ተተኩሰዋል ደግሞም ተገድለዋል፡፡ በሚያሳፍር መንገድም በርካታ ክርስቲያኖችም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ባርነት የሚያስተምረውን ጠምዝዘው በመተርጎም ይህንን አሰቃቂ ድርጊት ጥብቅና ሲቆሙለት መኖራቸው ነው፡፡ ሆኖም ግነ እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ስህተት ፈጽመዋል፡፡ ጳውሎስም ሆነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ይህን ልምምድ እውቅና አልሰጡትም፡፡ ይልቁኑ፣ ይህንን የሚያደርጉትን እጅግ በከባዱ ቃላት ኮንነዋቸዋል፡፡
ጳውሎስ መቼት ግን፣ ባርነት የተለየ ነው፡፡ በተለይ ባሪያና ጌታ ሁለቱም ክርስቲያኖች ከሆኑ፣ እጅግ የላቀ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው በጎ ተግባር ነው፡፡ እውነታውም፣ ሁለቱም በአንድ ቤት ስለሚኖሩ፣ አንዳቸው ሌላቸውን እንዲያገለግሉና እንዲዋደዱ እግዚአብሔር ይጠብቅባቸዋል፡፡ በየትኛውም መመዘኛ እና ዓላማ የሚዋደዱ ቤተዘመዶች ናቸው፡፡
እነዚህ ግንኙነቶች እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኙና ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ በሚያደርጉ መንገዶች እስከተመሩ ድረስ፣ ቤተክርስቲያን ማኅበረሰባዊ ተቋማትን እንድታፈራርስ ጳውሎስ መመሪያ ሊሰጥ አይችልም ማለት ነው፡፡ ይልቁኑ፣ ባርነትን ክርስቶስን በሚመስል አፈፃፀም እንዲይዙት ያስተምራል እንጂ፡፡
ጳውሎስ ለአናሲሞስ እጅግ የተሻለው ነገር እንዲሆንለት ይፈልጋል፣ ፊልሞና ደግሞ የሐዋርያውን ፍላጎት እንዴት እንደሚሳካ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሆኖም ግን ጳውሎስ የተጠቀመው ግልፅ ያልሆነ ቋንቋ ጳውሎ እየጠየቀ ያለው ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር ብሎት በቤቱ ውስጥ እንደተከበረ ባሪያ እንዲቀበለው ይሁን ወይም አናሲሞስን በነፃነት እንዲለቅቀው በእርግጠኝተን እንዳናውቅ ያደርገናል፡፡ ደግሞም የአናሲሞስን ክህሎትና ያለበትን ሁኔታ በዝርዝር እስካላወቅን ድረስ፣ ለእርሱ ከሁሉ የተሻለ ጠቃሚ ሊሆንለት የሚችለው የትኛው እንደሆነ መገመት አንችልም፡፡ ምንም ይሁን ምን፣ የጳውሎስ ልመና አናሲሞስ የተቃና ሕይወት እንዲኖረው ለማድረግ ማለትም በክርስቲያናዊ ከበሬታ፣ ደግሞም በፍቅርና በምህረት ቤተክርስቲያን እንድትቀበለው ታስቦ የተደረገ መሆኑን በግልጽ እንረዳለን፡፡
መተማመን
በመጨረሻም፣ ጳውሎስ ለፊልሞና ልመናውን ካቀረበ በኋላ፣ በቁጥር 21 ላይ ያለውን መተማመን በመግለጽ ሃሳቡን ይደመድማል፡፡ በዚህ ስፍራ ጳውሎስ፣ ፊልሞና ሐዋርያው የጠየቀውን እንደሚፈጽም ያለውን እምነት ይገልጻል፡፡ የጳውሎስ ልመና የተደመደመበትን ሃሳብ በፊልሞና ቁጥር 21 ላይ እናነብባለን፡
ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ እንድትታዘዝም ታምኜ እጽፍልሃለሁ። (ፊልሞና 21)
ፊልሞና ያቀረበለትን ጥያቄ እንደሚቀበል ጳውሎስ እርግጠኛ የሆነባቸው ሁለት ጠንካራ ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛ፣ ፊልሞና ጳውሎስን ይወደዋል ያከብረውማል፣ ስለዚህም እርሱን ደስ ለማሰኘት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ ፊልሞና አናሲሞስ በቅርቡ የተቀላቀለባትን ቤተክርስቲያን ይወድዳል፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት ፊልሞና ስለሰጠው ምላሽ ወይም አናሲሞስ ምን እንደገጠመው ምንም የዘገቡልን ነገር የለም፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሲታመን የኖረው ግን፣ ፊልሞና ነፃ እንዳወጣውና በስተመጨረሻም የኤፌሶን ቢሾፕ እንደሆነ፣ በ95 ዓ.ም. በሮም መስዋዕት ሆኖ እንዳለፈ ነው፡፡ በእርግጥም በ1ኛው ምዕተ ዓመት ጢሞቴዎስ የተካው ቢሾፕ አናሲሞስ ነበር፡፡
ወደ እውነታው ስንመጣ፣ አናሲሞስ የተለመደ ስም ነበር፣ ስለዚህ ምናልባት ባሪያው ያ ቢሾፕ ላይሆንም ይችላል፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም ግን፣ በጳውሎስ ስር የሰለጠነ ሰው በቀላሉ ወደ እውቅናው መንበር እንደሚመጣ ይታወቃል፣ ስለዚህ የትኛው ሊሆን እንደሚችል ፍርድ መስጠት አንችልም፡፡
የቱም ይሁን የቱ፣ ጳውሎስ በፊልሞና ላይ የነበረው መተማመን፣ ለአናሲሞስ የተሻለውን ነገር ሁሉ እንደሚያደርግለት ወደመጠርጠሩ እንድናዘነብል ያደርገናል፡፡ አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ደግሞ፣ ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን ደብዳቤ የማግኘታችን አንድምታ ፊልሞና ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዳደረገ ነው፡፡ ጳውሎስ ያቀረበለትን ልመና ያልተቀበለ ቢሆን ኖሮ የጻፈለትን ደብዳቤ ያጠፋው ነበር፡፡
የመጨረሻ ሰላምታ
ጳውሎስ ለፊልሞና ያቀረበውን ልመና ካቀረብን፣ አሁን ደግሞ ወደ ደብዳቤው የመጨረሻ ክፍል እንሸጋገራለን፡፡ ይህም በፊልሞና ቁጥር 22 እና 23 የተመዘገበውና ለፊልሞና እና ለቤተሰቡ ያቀረበው የመጨረሻ ሰላምታ ነው፡፡
ይህ ክፍል የተለመደውን ሰላምታ በቁር 24 ውስጥ፣ የተለመደውን ቡራኬ ደግሞ በቁጥር 25 ውስጥ አካትቷል፡፡ ቀደም ባሉት ጥቅሶች ውስጥ የምናገኛቸው ሁለት ዝርዝሮች ግን ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
አንደኛው፣ በቁጥር 22፣ ጳውሎስ በቅርቡ ከእስር ሊፈታ እንደሚችል ያለውን ግምት ይጠቅሳል፣ ስለዚህም ፊልሞና ለእርሱ ቤት እንዲያዘጋጅለት ይጠይቀዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ማለትም ሐዋርያውን በቅርቡ ፊት ለፊት የሚያገኘው እስከሆነ ድረስ፣ ፊልሞና ጳውሎስ ላቀረበለት ጥያቄ ይሁንታ እንዲሰጥ እንደሚያበረታታው አያጠራጥርም፡፡
ሁለተኛ፣ በዚህ ትምህርት ቀደም ብለን እንዳሳነው፣ በቁጥር 23 ውስጥ ጳውሎስ ከኤጳፍራ የከበረ ሰላምታ ያቀርብላቸዋል፣ ያም የሚያመለክተው ኤጳፍራ ፊልሞና ጉዳዩን ከአናሲሞስ ጋር የጨረሰ ለመሆኑ ምስክር ሳይሆን እንደማይቀር ነው፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን መልእክት ዳራ እንዲሁም አወቃቀሩንና ይዘቱን ተመልክተናል፣ አሁን ደግሞ፣ ጳውሎስ ለአናሲሞስ ጥብቅና የቆመበት ምሳሌያዊ ተግባር በዘመናችን የሚኖረውን ተዛምዶ ለመመልከት የምንችልበት እርከን ላይ ደርሰናል፡፡
ዘመነኛው ተዛምዶ
ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈው መልእክት ወሳኝ ነው የምንልበት አንዱ ምክንያት ጳውሎስ ያነገበውን ነገረ-መለኮት እንዴት በግል ሕይወቱ ተግባራዊ እንደሚያደርገው በግልጽ እንድናስተውል ስለሚያደርገን ነው፡፡ የቆላስይስንና የኤፌሶንን መልእክቶች በምንመለከትበት ወቅት፣ የሚያስተምራቸው ትምህርቶች ተግባራዊ የሚደረጉባቸውን ጥቅል የተዛምዶ ነጥቦች እናስተውላለን፡፡ እነዚያም ለእኛ በእጅጉ ጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ለፊልሞን በጻፈው መልእክት ግን ጉዳዩ ከጥቀልና ከመላምታዊ ተዛምዶ ወደ ግልጽና ቀጥተኛ ተዛምዶ ማለትም ከመመሪያነት ወደ ተግባራዊ ምላሽነት ይሸጋገራል፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ የሚያስተምረውን ነገር በተግባር እንደሚገልጥ ክርስቲያን እንመለከተዋለን፡፡
እናም፣ የፊልሞናን መጽሐፍ ዘመነኛ ተዛምዶ ስንመለከት፣ ጳውሎስ በፊልሞናና በአናሲሞስ መካከል አማላጅ ሆኖ የቀረበበትን ሁኔታ የምንቃኘው በሌሎቹ መልእክቶቹ በተለይ ደግሞ በቆላስይስና በኤፌሶን መልእክቶቹ ካስተማራቸው ትምህርቶች አንፃር ሆናል፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን መልእክት ዘመነኛ ተዛምዶ ስንመለከት፣ በሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡ በመጀመሪያ፣ በክርስቲያኖቸ መካከል ተጠያቂነት ሊኖር የሚገባ መሆኑን፤ ሁለተኛ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚኖረን ግንኙነት የርኅራኄን ፋይዳ፤ በመጨረሻ ደግሞ፣ በእግዚአብሔር ቤተሰብ መካከል የእርቅን አስፈላጊነት ይሆናል፡፡
ተጠያቂነት
ቀደም ብለን እንደጠቀስነው፣ ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው መልእክቱ ለአናሲሞስ አማላጅ መሆኑን ነገር ለማጽናት፣ በርካታ ምስክሮችን ማለትም አፍብያን፣ አክርፓጳን፣ ኤጳፍራን እና በቆላስይስ የምትገኘውን ቤተክርስቲያን ጠቅሷል፡፡ ጳውሎስ ይህንን ያደረገበትን ምክንያት በግልፅ ባይጽፍም፣ ተመራጭ የሆነው ግምት የተጠቀሱት ሰዎች ዐይን በንቃት የሚመለከተወ መሆኑን ማወቁ ፊልሞና ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርግ ያበረታታዋል የሚለው ነው፡፡
ይህ ስልት በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ከቁር 11 እስከ 21 ካለው አስተምህሮ ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ከዚህ ምንባብ ውስጥ የተወሰኑ ቁጥሮችን በአንጓ በአንጓ እየከፋፈልን እንመለከታቸዋለን በመጀመሪያም፣ ምዕራፍ 5 ከቁጥር 11 እስከ 15 ያለውንና ጳውሎስ እንዲህ ሲል መመሪያ የሰጠበትን እንይ፡
ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥
እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤
ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና።
ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል።
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ (ኤፌሶን 5፡11-15)
ክርስቲያኖች ኃጢአትን ማጋለጥ እንደሚገባቸው ጳውሎስ አስተምሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኃጢአት ያደረጉ ሰዎች ኃጢአታቸው ሲታወቅ ስለሚያሳፍራቸው ነው፡፡ ስለዚህ ብልህነት የሞላበት ድርጊት፣ ሕይወታችንን ለብርሃን ማጋለጥ ነው፣ ማለትም፣ ለብርሃን መንግሥት ኅብረት ማጋለጥ ማለት ነው፣ ያን ስናደርግ ኃጢአትን ከማድረግ እንጠበቃለን፡፡
አንግዲህ አሁን፣ ጳውሎስ ክርስቲያኖች አንዱ ለሌላው ፖሊስ በመሆን ማንም ሰው ለብቻው እንዳልሆነ እንዲያውቅ አድርጉ፣ ወይም አንዱ የሌላው ሰላይ ይሁን አላለም፡፡ ይልቁኑ እያመለከተ ያለው፣ አንዱ ለሌላው ተጠያቂ የሚሆንበትን ጥበብ ነው፡፡ ሕይወታችንን በብርሃን የምንመራ ከሆነ፣ እያደረግን ያለነውን ሌሎች ካወቁ፣ ለፈተና ያለን ተጋላጭነት ያንሳል፡፡ የዚህም ምክንያቱ የምንሠራቸው ኃጢአቶች በሌሎች ሲታወቁ ስለሚያሳፍሩን ነው፡፡
በአናሲሞስና በፊልሞና ጉዳይ፣ ሰው ስለ ጳውሎስ መልእክት ምንም እውቀት ከሌለው እና ጳውሎስም ጉዳዩን ከፊልሞና ጋር ባያነሳውና ባይከታተለው ኖሮ፣ ማንም ሰው ፊልሞና ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርግ ሊጠብቅበት አይችልም፡፡ አናሲሞስን በከፋ ሁኔታ ቢቀበለው፣ የጳውሎስን ጥያቄ እንዳቃለለ የሚያውቀው ፊልሞና ራሱ ብቻ ነው፡፡
ሆኖም ጉዳዩን የአደባባይ ጉዳይ በማድረግ፣ ፊልሞና አናሲሞስን በክፋት ቢቀበለው፣ ከራሱ ቤተሰብና ከቆላስይስ ቤተክርስቲያን ብርቱ ፈተና እንደሚገጥመው ሊያረጋግጥለት ፈልጓል፡፡ ይህም ነገር ፊልሞና ትክክለኛውን ነገር ማድረግን እንዲመርጥ ያበረታታዋል፡፡ ጌታም ራሱ በብሉይ ኪዳን ሕዝቡ ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርግ ለማበረታታት ተመሳሳይ ሆነውን በሰው ፊት አሳፋሪ ነገር ከማድረግ የመቆጠብን ስልት ይጠቀም ነበር፡፡
ለምሳሌ፣ በዕንባቆም ምዕራፍ 2 ቁጥር 16፣ ነቢዩ ለይሁዳ ህዝብ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መልእክት እንዲህ አቅርቦታል፡
በክብር ፋንታ እፍረት ሞልቶብሃል፤ አንተ ደግሞ ጠጥተህ ተንገድገድ፤ የእግዚአብሔር የቀኙ ጽዋ ይመለስብሃል፥ እፍረትም በክብርህ ላይ ይሆናል። (ዕንባቆም 2፡16)
ይሁዳ ከኃጢአቱ እንዲመለሰ ለማድረግ እግዚአብሔር አሳፍሮታል፡፡ በሕዝቅኤል ምዕራፍ 7 ቁጥር 18 ደግሞ፣ እስራኤልን ወደ መታዘዝ ለማምጣት አሳፋሪ የሆነን ድርጊት በማሳሰብ ከመንገዷ እንድትመለስ ያበረታታል፡
ማቅም ይለብሳሉ ድንጋጤም ይሸፍናቸዋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ እፍረት ይሆናል፥ ራሳቸውንም ሁሉ ይነጩታል። (ሕዝቅኤል 7፡18)
በተመሳሳይም መንገድ፣ በዘመናችንም ቤተክርስቲያን በርካታ ድብቅ ኃጢአቶች አሉ፡፡ ክርስቲያኖችም እነዚህን ኃጢአቶች በመለማመድ መኖር አይከብዳቸውም፣ ሆኖም ሌሎች ሲያውቁ ግን ያፍራሉ፡፡ ስለዚህ፣ ቤተክርስቲያን እነዚህን ኃጢአቶች አስመልክቶ እኛን ተጠያቂ ለማድረግ የምትጠቀመው ስልት አማኞች በቅርብ ግንኙነት እንዲኖሩ ማድረግን ነው፡፡
ክርስቲያናዊ እርስ በርስ ተጠያቂነት የሚያቀርበው የመከላከያ መንገድ እፍረት ብቻ አይደለም፡፡ በተቃራኒው፣ ጳውሎስ በፊልሞና የጠቀሰው ምሳሌ አጽንዖት የሚሰጠው ክርስቲያኖች እርስ በርስ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው አንዳቸው ከሌላቸው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው የሚለውን ነው፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን 5 ቁጥር 19 የተናገረውን አድምጡ፡
በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ (ኤፌሶን 5፡19)
ክርስቲያኖች በተጨማሪም ኃጢአት እንዳይሠሩ ሊጠበቁ የሚችሉት አንዳቸው ለሌላቸው የሚያበረታቱ ቃላቶችን በመነጋገር ነው፡፡ እንግዲህ እንደ ዘመኑ ክርስቲያኖች አንዳችን ለሌላችን በዚህ መንገድ ተጠያቂ መሆንን ልንለማመድ ይገባናል፡፡ የእፍረት ጉዳይ በየዘመኑ ይኖራል፣ ጳውሎስ ግን ለፊልሞና ሲናገር በእፍረት ላይ አላተኮረም፣ ምክንያቱም ፊልሞና በአሳፋሪ ሕይወት እየኖረ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ፣ ጳውሎስ አፅንኦት የሰጠው ፊልሞና ባደረጋቸው መልካም ነገሮች ላይ ሲሆን አሁንም እነዚያን በጎ ተግባራት ማድረጉን እንዲቀጥል ያበረታታዋል፡፡ እኛም እንዲሁ፣ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ውስጥ ባለው መልካም ነገር ላይ አጽንኦት ልንሰጥ ይገባናል ያንንም የምናደርገው ወደፊትም በእነዚያ መልካም ነገሮች እንዲገፉና በነዚያው መሠረትም ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማበረታታት ነው፡፡
በመጨረሻም፣ አንዳችን ለሌላችን ተጠያቂ የምንሆነው አማኞች ሁሉ አንዳቸው ለሌላቸው በሚያሳዩት በአክብሮት ላይ በተመሠረተ መሰጠት ላይ መሆን እንደሚገባው ጳውሎስ ያመለክታል፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ቁጥር 21 የተናገረውን አድምጡ፡
ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። (ኤፌሶን 5፡21)
ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን መታዘዝ ምርጫቸው ያደረጉ ሰዎች ኅብረት የሚያደርጉባት፣ የተቀደሰች ስፍራ ናት፡፡ ይህም ማለት የቤተክርስቲያን ጉባዔ እግዚአብሔራዊና የተቀደሰ ነው ማለት ነው፡፡
እንግዲህ፣ እርስ በርሳችን በኅብረት ስንኖር፣ መልካም በማድረግ እርስ በርስ ስንበረታታ፣ የቤተክርስቲያን መሪዎችና በጎ ልማዶቻችን ያስተማሩንን መልካም ነገሮች ደግሞም የጠቢባንን እና እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ቅዱሳን ምክር ልብ ልንላቸው ይገባናል፡፡
በጥቅሉም፣ ጳውሎስ ፊልሞና ከአናሲሞስ ጋር ስላለው ጉዳይ ሲያነሳ ምስክሮችን መጥቀሱን ስንመለከት፣ ቤተክርስቲያን መልካም ስራን በማበረታታትና ኃጢአትን በመኮነን፣ ሰዎችንም ለበጎ ነገር በማነሳሳት ደግሞም ለቤተክርስቲያን ብልህ ምክር ራስን በማስገዛት ኃጢአትን መከላከል እንደሚቻል እንማራለን፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና የጻፈውን መልእክት በቤተክርስቲያን ውስጥ ስለሚኖረው ተጠያቂነት የሚያወሳ የመሆኑን አንድምታ ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ወደ ሁለተኛው የተዛምዶ ነጥባችን እንሸጋገራለን፡ ያም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ባለን ግንኙነት ርኅራኄ አስፈላጊ መሆኑ ነው፡፡
ርኅራኄ
ክርስቶስ በምድር የአገልግሎት ዘመኑ ከገለጣቸው ባህርያት ሁሉ፣ ርኅራኄ እጅግ አስገራሚ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አዎን፣ እርሱ ለቅድስናና ለአክብሮት፣ ለጽድቅና ለግብረገባዊነት ብርቱ ቅናት እንደነበረውም የማይካድ ነው፡፡ በተጨማሪም አምሳያ ወይም ተፎካካሪ የሌለውን ጥበብ፣ ንጽህናና ከበሬታን እንዳሳየም ለሁላችን ግልፅ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ደግነቱ፣ አዛኝነቱ፣ ለሰው ግድ መሰኘቱ፣ ለሌሎች ያለው ፍቅር፣ ይቅር ለማለት ያለው ናፍቆት፣ ሌሎችን ከስቃይ ለማትረፍ መከራን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑ እጅግ የሚታወሱ ናቸው፡፡ ሙታንን ማስነሣቱ፣ በሕይወት ያሉትን ማጽናናቱ፣ የታመሙትን መፈወሱ፣ ሽባውን ማዘለሉ፣ የተራቡትን ማጥገቡ፣ ለጠፉት፣ ለተጎዱት እና በፍርሃት ለተከበቡት እረኛ መሆኑ፣ ለሚጠሉትም ጭምር በመስቀል ላይ መሞቱ ሁሉ የእርሱ ታሪኮች ናቸው፡፡ በአጭሩ፣ ልባችንን በጥልቀት የነካው የክርስቶስ ርኅራኄ ነው፡፡ ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ ባስተላለፋቸው የምስጋና፣ የአስተምህሮ እና የተምሳሊታዊ ሕይወት መግለጫዎች የሚያበረታታን በዚህ የርኅራኄ ሃሳብ ነው፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው መልእክቱ ያሰፈረውን የርኅራኄ ሃሳብ ሁለት ገጽታ እንመለከታለን፣ የምንጀምረውም በበጎነትና በደግነት ተግባር ሲሆን፣ ከዚያም የምልጃን ተግባር እንመለከታለን፡፡ ክርስቲያናዊ ርኅራኄ በተግባር በሚገለጥበት የበጎነት ተግባር እንጀምር፡፡
በጎነት
ፊልሞና ለቤተክርስቲያን ስለ ሰጠው አገልግሎት ሲያመሰግነውና ያንንም መሠረት አድርጎ ፊልሞናን ለቀጣይ በጎነት ሲለምነው አማኞቸ ሁሉ በጎነትንና የቸርነትን ተግባር እንዲለማመዱ አስተምሯል፡፡ በፊልሞና ቁጥር 7 እስከ 9 ጳውሎስ ያሰፈራቸውን ቃላት አድምጡ፡
የቅዱሳን ልብ በአንተ ስራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ፥ በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና።
ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥
ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። (ፊልሞና 7-9)
ፊልሞና የቅዱሳንን ልብ ያሳረፈባቸውን መንገዶች፣ ማለትም ለሌሎች አማኞች በጎነትን ያሳየባቸውን መንገዶች በማንሳት ጳውሎስ ያበረታታል፡፡ ጳውሎስም እያነሳ ያለው፣ በዚያው በጎነት መሠረት አሁን እስረኛ ለሆነውና በዕድሜው ለሸመገለው፣ የሌሎችን ርኅራኄና ደግነት ለሚፈልገው ሰው እንዲያደርግለት ነው፡፡ በቆላስይስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 11 እና 12 ውስጥ እንደጻፈው ማለት ነው፡
በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።
እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ (ቆላስይስ 3፡11-12)
አማኞቸ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር ከመተባበራቸው የተነሳ፣ አንዳችን ሌላችንን የምንቀበለው እኛ ለጌታ እንደምንሆነውና ጌታም ለእኛ እንደሚሆነው፣ ሁሉን አቀፍ እንክብካቤ በማድረግ እና የሚያስፈልጋቸውንም ሁሉ እንዲያገኙ በመርዳት ይሆናል፡፡
በእነዚህና በሌሎችም በርካታ መንገዶች፣ በጎነትና መልካም ተግባር ለክርስቲያናዊ አኗኗር እጅግ ወሳኝ ገጽታዎች መሆናቸውን ጳውሎስ ያሳያል፡፡ ስለዚህም፣ ልክ እንደ ጳውሎስና እንደ ፊልሞና ሁሉ፣ የዘመናችንም ክርስቲያኖች በቤተክርስቲያን ለሚገኙ ሰዎች በርኅራኄና በፍቅር ተገፋፍተው፣ ለችግሮቻቸው ሊደርሱ እና እስከቻሉ ድረስ ሊረዱ ይገባቸዋል፡፡
ምልጃ
ጳውሎስ ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ የገለጸው ያበረታታበት ርኅራኄ ሁለተኛው ገጽታ ምልጃ ነው፣ ያም አንድ አማኝ ለሌላው ጥብቅና የሚቆምበት ነው፡፡ ምልጃ በብዙ መንገዶች ይገለፃል፡፡ በአንደኛው ጎን፣ አንድን ሃሳብ እንደማንጸባረቅ ዓይነት፣ ለከፋ አደጋ ራስን ማጋለጥ ሳይኖርበት፣ ለአንድ ሰው በጎ እንዲደረግለት ሁኔታዎችን ወዲያ ወዲህ በማድረግ በቀላሉ ሊገለጽ የሚችል ይሆናል፡፡ በሌላኛው ጎን ደግሞ፣ አንድን ወንጀለኛ የሆነን ሰው ለማዳን ሲባል የራስን ሕይወት አሳለፎ እስከመስጠት ድረስ የሚዘልቅ ብርቱ ተግባርም ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ምልጃ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው ክርስቶሰ ለኃጢአተኞች ድነትን ለማስገኘት ሲል የከፈለው መስዋዕትነት ነው፡፡
እናም በእነዚህ ሁለት የተራራቁ ምሳሌዎች መካከል፣ በርካታ ዓይነት ምልጃዎችም ይኖራሉ፡፡ ጳውሎስ ለፊልሞና በአናሲሞስ ምትክ ሆኖ ያቀረበውን ልመና ከቁጥር 17 እስከ 19 እንመልከት፡
እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ።
ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው። (ፊልሞና 17-19)
የጳውሎስንም ምሳሌነት በመከተል፣ የዘመናችንም ክርስቲያኖች በተመሳሳይ መንገድ ለሌሎች አማኞች መማለድ አለባቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቀለል ባለ መንገድ እንድንማልድ ተጠርተናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ የሚኖረን ርኅራኄ ላቅ ወዳለው የምልጃ እርከን እንድንዘልቅ ጥሪ ያቀርብልናል፡፡
ደግሞም በአንዳንድ ጉዳዮች፣ ርኅራኄ ስለሌሎች ጥቅም ወይም ጥበቃ ሲባል ሕይወታችንንም እንኳን ወደ መሰዋት ሊያደርሰን ይችላል፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 5 ቁጥር 1 እና 2 እንደጻፈው ማለት ነው፡
እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥
ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ። (ኤፌሶን 5፡1-2)
ጳውሎስ በፊልሞና ባሰፈረው ትምህርት ውስጥ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠያቂነትና ክርስቲያናዊ ርኅራኄ በእኛ ዘመን የሚዛመድባቸውን ጥቂት መንገዶች ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ወደ መጨረሻው ርዕሳችን እንሸጋገራለን፤ ያም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካነት በአማኞች መካከል ሊገለጽ የሚገባው እርቅ ነው፡፡
እርቅ
ስለ እርቅ ስንናገር፣ ከዚህ ቀደም ምንም ባልነበረበት ስፍራ አንድነትና ፍቅርን ስለመመስረት ብቻ እየተናገርን እንዳልሆነ ግልጽ ማድረግ ይገባናል፡፡ እያልን ያለነው፣ ጠላትነት ከዚህ ቀደም ገንኖ በነበረባቸው ስፍራዎችአንድነትና ፍቅር ይመሥረት ነው፡፡ እርቅ የሚመሠረተው በይቅርታና በምህረት ሲሆን፣ የሚጠበቀው ደግሞ በትዕግሥትና በመጽናት ነው፡፡ በመካከላችን የግጭት ምንጭ ሊኖር እንደሚችል እንገምታለን፣ ሆኖም ለተሻለ ነገር ስንል ግጭቶቻችንን ወደ ጎን በመተው፣ አንዳችን ከሌላችን ጋር መቀባበል ያለበት ሰላም፣ አንዳችን ለሌላችን ፍቅርን መስጠት እና አንዳችን ሌላችንን ማገልገል ይገባናል፡፡
ጳውሎስ በቆላስይስና በኤፌሶን መልእክቶቹ በአማኞች መካከል ማለትም በግልም ሆነ በጋራ እስከ ጎሳዊ እርከን ድረስ እርቅ ሊኖር እንደሚገባ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ ይህንንም እርቅ የገለጸው ከወንጌል ውቅረ-ነገሮች መካከል ወሳኙ ክፍል እንደሆነ አድርጎ ነው፡፡
ጳውሎስ አናሲሞስንም ሆነ ፊልሞናን የሚያበረታታቸው ወዳጅነታቸውን እንዲያድሱ፣ ቂምን አስወግደው በክርስቶስ ወንድማማች እንደሆኑ ሰዎች እርስ በርስ የመቀባበል ግዴታ እንዳለባቸውም ያሳስባቸዋል፡፡ አናሲሞስ በድርሻው፣ በጳውሎ አገልግሎት ወደ ክርስትና እንደተለወጠ ሰው፣ የሠራቸውን ኃጢአቶች ሊናዘዝ ይገባዋል፡፡ ደግሞም እንደ ፊልሞና ባሪያነቱ፣ ራሱን ለፊልሞና ፍርድ ሊያስገዛ ይገባዋል፡፡ ፊልሞናም በበኩሉ፣ አናሲሞስን ሊወድድ፣ በበጎነትም ሊመለከተው፣ በደሉንም ይቅር ሊለው፣ በክርስቶስ እንዳገኘው ወንድምም ሊቀበለው ይገባዋል፡፡ የዘመናችንም አማኞች በተመሳሳይ መንገድ እርስ በርስ ለመናዘዝና ይቅር በመባባልም ወደ ትክክለኛው ግንኙነታችን ለመመለስ ልንናፍቅ ይገባናል፡፡
ልክ አሁን እንደምናየው ሁሉ፣ በጳውሎስም ዘመን፣ በተለያ ጎሳዎች፣ እና ወገኖች መካከል በቤተክርስቲን ውስጥ ውጥረት፣ ቂም በቀል ነበር፡፡ እናም ጳውሎስ ይህን በመሰለ ሁከት ውስጥ የተገኙ ሰዎች አልዳኑም የሚል ሙግት አላቀረበም፡፡ ይልቁኑ፣ ያለው ለእነዚህ መሳይ ድርጊቶች መሠረት የሆነው ነገር በክርስቶስ ተወግዷል፣ ስለዚህ በበቤተክርስቲያን ውስጥ የሚነሱ ይህንን መሳይ ሁከቶች እርባና ቢስና ኃጢአት ናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁጥር 14 እስከ 16 ውስጥ በአይሁድና በአህዛብ አማኞች መካከል ስለተካሄደው እርቅ እንዲህ ሲል ጽፏል፡
እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥
ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። (ኤፌሶን 2፡14-16)
ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ያቀረበውን ሙግት ስንመለከት፣ በአይሁድና በአህዛብ አማኞች መካከል በክርስቶስ የተገኘው እርቅ እኛ ከክርስቶስ ጋር ያለን አንድነት ገጽታ ነው፣ እናም እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ለታረቅንበት እርቅ ወሳኝ እርከን ነው ማለት ነው፡፡
እንግዲህ በእኛም ዘመን ዘርንና ጎሳን አስመልክቶ ለሚነሱ ሁከቶች፣ እንዲሁም በክርስቲያኖች መካከል የችግሮች ምክንያቸ በሚሆኑ ነገሮችም ላይ ጉዳዩ እውነትነት አለው፡፡ ምክንያም እኛ በክርስቶስ አንድ ሆነናል፣ እኛ ሁላችን ይቅር ተብለናል ደግሞም ተባርከናል፡፡ ስለዚህ፣ ከየትኛውም አማኝ ጋር ላለመታረቅም ሆነ ለመገፋፋት መሠረት የሚሆን ነገር የለም፡፡ በእኛ መካከል ለሚፈጠረው ግጭት መሠረት የሆኑትን ነገሮች ጌታችን አስወግዷቸዋል፣ ስለዚህ ሁከታችንን እንደ ኃጢአት በመቁጠር፣ በክርስቶስ አካል ውስጥ ሊገለጥ ለሚገባው አንድነት፣ ፍቅርና ወዳጅነት ልንተጋ ይገባናል፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 4 ቁር 32 የጻፈውን እናድምጥ፡
እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። (ኤፌሶን 4፡32)
በቆላስይስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 13 እስከ 15 ያስተማረውንም ትምህርት ልብ እንበል፡
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤
በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። (ቆላስይስ 3፡13-15)
ጥላቻንና ቅሬታን አስወግደን እርስ በርስ እንድንዋደድ፣ እያንዳንዱንም ክርስቲያን በክርስቶስ ዐይን ልንመለከት፣ ሰላምንም በአንድነት እንድናጣጥም ተጠርተናል፡፡ በዘመናችንም ቤተክርስቲያን በአማኞቸ መካከል እርቅ ከፍተኛውን ተቀዳሚ ስፍራ ሊይዝ ይገባዋል፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ ትምህርታችን ጳውሎስ ለቆላስይስ ወዳጁ ለፊልሞና የጻፈውን መልእክት በጥልቀት ተመልክተናል፡፡ የደብዳቤውን ዳራ አይተናል፣ የመልእክቱንም አወቃቀርና ይዘት አጥንተናል፡፡ በመጨረሻም፣ ጳውሎስ በፊልሞና መልዕክቱ ካስቀመጠልን ተምሳሊቶች ለዘመናችን የምንወስዳቸውን ተዛምዶዎች ዳስሰናል፡፡
የፊልሞና መልእክት በጣም አጭር ነው ግን እጅግ አስደናቂ የአዲስ ኪዳን ክፍል ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር እንዴት ያለ ቀረቤታ እንደነበረውና የሚያስተምራቸውንም ትምህርቶች እንዴት በተግባር በመኖር እንደሚገልጣቸው ማረጋገጫን በመስጠት ለየት ያለ ግንዛቤን ያስጨብጠናል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ አንዳችን ለሌላችን ልንሰጠው ስለሚገባን ዋጋ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለው፡፡ ያንንም ዋጋ በተለይም ትክክለኛውን ግንኙነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ከማድረግ አንፃር የሰዎችን እሴቶች እንዴት ማክበር እንዳለብንም ብዙ ያስተምረናል፡፡
ጳውሎስ ለፊልሞና በላከው መልእክቱ ውስጥ ያሰፈራቸውን ምርሆች ሞዴል አድርገን ስንኖር፣ አንዳችን ሌላችንን ለማገልገልና ቤተክርስቲያንን ለክርስቶስ ክብር ለመገንባት እጅግ ታላቅ የሆነን እርምጃ እንወስዳለን ማለት ነው፡፡
Continue reading the full transcript