ከተመሳሳይ ተከታታይ ትምህርት 5 ጋር የተያያዘ የቪዲዮ አጋር伴 ነው። ይህ ትምህርት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠይቃል፡- ፊሊጰንስ ስለመከራየ ሁሉንም አይነት መከራዎች ወይም የመከራ ብቻ ለወንጌል አስተናግዶአል? የጳውሎስ ደስታ ከመከራው ጋር የተያያዘ ነው ወይንስ ከፊሊጰንስ ጋር ካለው ግንኙነት ጋር? ጳውሎስ የመሞትን ፍላጎት መያዙ ኃጢአት ነበር? ጳውሎስ የተገለጸው ደስታ ከክርስቶስ እውቅና በላይ ስሜታዊ ተሞክሮ ነው? ጳውሎስ በአንድ ጊዜ 우울 እና ደስተኛ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? ክርስቲያን ወይንስ ዓለማዊ መልካም ባሕርያት ፊሊጰንስ ጳውሎስን እንዲንከባከቡ አነሳስቷቸው? ጳውሎስ ለፊሊጰንስ ያለው ጠንካራ ፍቅር ለምን ተሰማቸው? የተለያዩ ቡድኖች በአንድ የአካባቢ ጉባኤ ውስጥ መሳተፍ የተለመደ ነበር? ፊሊጰንስን እንደ መገጣጠሚያ ደራሲዎች ጳውሎስንና ቲሞቴዎስን ልናተኩስ ይገባል? ከጳውሎስ ኤውዲያና ሲንቲቼን ስለመክረዛት ምን መማር እንችላለን? ኢየሱስ ራሱን ምንም አድርጎ ሲል ምን ማለት ነው? ጽናትና ጥበቃ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? መልካም ሥራዎቻችን ለእንዳን救ነ contribute አስተዋጽኦ ያደርጋሉ? እግዚአብሔር ከአማኞች ውጭ የመልካም ሥራዎቻቸውን አንዳንድ ጊዜ እምነት እንዲያመጡላቸው ይጠቀማል? የመልካም ወንጌልን wicked ዓላማዎች ጋር ሲሰብኩ መልካም ነገር ሊመጣ ይችላል? Wicked ዓላማዎች ጋር ወንጌሉን የሚሰብኩ ሰዎች ላይ ምን መልኩ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል? "እውነተኛው ቍርንስ" ማን ናቸው? ወንጌሉ ዋና ዋና ጽንሰቶች ምንድን ናቸው? የውሸት አስተማሪዎችን እንዴት መለየትና መያዝ ይቻላል?
From the transcript
ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡
ወታደሮች አንድን ጦርነት በድል የማጠናቀቃቸው ነገር ካጠራጠራቸው፣ አዕምሯቸው ማሰብ የሚጀምረው ስለ ሞት ነው፡፡ ራሳቸውን እና በቤት ጥለዋቸው የመጡትን ቤተሰቦቻቸውን የሚያጽናኑበትን መንገድ ያፈላልጋሉ፡፡ አብዛኛውንም ጊዜ፣ ለቤተሰቦቻቸው የምሥጋናና የምክር ደብዳቤዎችን ይጽፋሉ፣ ደብዳቤውም የሚወዷቸው ሰዎች የሚያልፉበትን ሁኔታ በብልኅነትና በጸጋ እንዲቀበሉ፣ ደግሞም እነርሱን ሊያስከብራቸወ በሚችል መንገድ እንዲኖሩ የሚያበረታታ ነው፡፡
እንግዲህ፣ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውም ደብዳቤ በብዙ መንገዶች በቅርቡ ሞቱን የሚጠብቅ ወታደር ለቤተሰቦቹ እንደሚጽፈው ደብዳቤ ዓይነት ነው፡፡ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈው በብርቱ መከራ ውስጥ በነበረበት ጊዜ፣ ምናልባትም በቅርቡ ሊገደል እንደሚችል በሚያስብበት ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህ ለሚወዳቸው ሰዎች ይጽፍላቸዋል፡፡ እናም፣ በፊልጵዩስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የጻፋቸው ቃላት ከባዶች ግን አሳቢነት ያለባቸው፤ አዘኔታ ያለባቸው ግን የሚያጽናኑ፤ አድናቆት ያለባቸው መራራ ጥፍጠት የተላበሱ ነበሩ፡፡ እንደ ጳውሎስ አስተሳሰብ፣ ታማኝ ለሆኑ ወዳጆቹ የሚያስተላልፋቸው የመጨረሻዎቹ የምክርና የልባዊ ምሥጋና ቃሎች ናቸው፡፡
“የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች” ከተሰኘው ተከታታይ ትምህርታችን ይህ አምስተኛው ነው፡፡ ርዕሱንም “ጳውሎስና የፊልጵስዩስ ሰዎች” ብለነዋል ምክንያቱም ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን የጻፈውን መልእክት ስለምንመረምር ነው፡፡ በደብዳቤውም፣ እያለፈበት ስላለው መከራ የተጨነቁትን የፊልጵስዩስ ሰዎች ሊያበረታታቸው ይጽፍላቸዋል፡፡ በቅርቡ በሞት የሚለያቸው መሆኑን በማሰብ፣ እርሱና የፊልጵስዩስ ሰዎች በሚገጥማቸው መከራና ጭንቀት ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ተስፋና ብርታት ጳውሎስ ይጽፍላቸዋል፡፡
ጳውሎስና የፊልጵስዩስ ሰዎች የተሰኘውን ጥናታችንን በሦስት ክፍሎች እንከፍለዋለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ ዳራ እንቃኛለን፡፡ ሁለተኛ፣ የፊልጵስዩስን አወቃቀርና ይዘት በጥልቀት እንመለከታለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ የዚህን ደብዳቤ ዘመነኛ ተዛምዶ እንቃኛለን፡፡ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልእክት ዳራ በመመልከት እንጀምር፡፡
በዚህ ተከታታይ ትምህርታችን ደጋግመን እንዳነሳነው፣ ጳውሎስ የነበረበትን ሁኔታና የሚጽፍላቸው ሰዎች የነበሩበትን ሁኔታ ማወቅ ዘወትር ወሳኝነት አለው፡፡ እነዚህን ዝርዝሮች ማወቃችን የሚጠቅመን ለጳውሎስ መልእክት ራሳችን ዝግጁ እንድናደርግና የጻፈበትን ዓላማ እንድንጨብጠው ያስችለናል፡፡
ስለዚህ፣ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ ጠጋ ብለን ስንመለከተው፡ የፊልጵስዩስ ሰዎች እነማን ናቸው? በእነርሱ ሕይወትና በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ምን እየተከናወነ ነበር? ጳውሎስስ ለእነርሱ ለምን ጻፈላቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ያስፈልገናል፡፡ እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታችን ጳውሎስ በመልእክቱ ያሰፈረውን ሥልጣን የተላበሰ አስተምህሮ እንድንገነዘብና በሕይወታችን እንድናዛምደው ያግዘናል፡፡
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልእክት ዳራ ስንመረምር፣ በሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ ከፊልጵስዩስ ሰዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት እናያለን፡፡ ሁለተኛ፣ ጳውሎስ በእስር ቤት የሚቀበለውን መከራ በዝርዝር እናነሳለን፡፡ ሦስተኛ፣ ጳውሎስ ለእነርሱ በጻፈበት ወቅት በፊልጵስዩስ የነበረውነ ሁኔታ እንቃኛለን፡፡ አስቀድመን በጳውሎስና በፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን መካከል የነበረውን ግንኙነት እንመልከት፡፡
ፊልጵስዩስ በሮማውያን የመቄዶንያ ግዛት ውስጥ እጅግ ወሳኝ ስፍራ ያላት ከተማ ስትሆን፣ በአሁኑ ዘመን ደግሞ በግሪክ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የምትገኘውም የሮሜን ከተማ ከምሥራቃዊው ግዛቶች ጋር በሚያስተሳስረው ቪያ ኤግኔሺያ በተሰኘው አውራ ጎዳና ላይ ነው፡፡ ስለዚህም ከሮሜ አቻ የሆነ ልዩ ስፍራ ያገኘች ስትሆን፣ በኢጣሊያ ውስጥ ከሚገኙት የሮም ቅኝ ግዛቶች አቻ በሆነ መንገድ መብት ያላት ሲሆን ለዜጎቿም የሮማዊ ዜግነት መብት ታጎናጽፋለች፡፡
ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ቤተክርስቲያን የተከለው በሁለተኛው ሚሲዮናዊ ጉዞው፣ ምናልባትም በ49 ወይም በ50 ዓ.ም. አካባቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ፊልጵስዩስ ከመድረሱ አስቀድሞ፣ በእስያ ያገለግል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አንድ ቀን ባየው ራእይ አንድ የመቄዶኒያ ሰው ወደ መቄዶኒያ መጥቶ ወንጌልን እንዲሰብክ ሲለምነው ያያል፡፡ ላየው ራእይ ምላሽ ለመስጠትም፣ ጳውሎስ ወደ መቄዶኒያ በመርከብ ተሳፈረ ወደ ናፖሊ ደረሰ፣ ብዙም ሳይቆይ በየብስ ላይ ከናፖሊ በስተሰሜን ምዕራብ 10 ማይል ወደምትርቀው ወደ ፊልጵስዩስ አቀና፡፡
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ያደረገው በርካታ እንቅስቃሴ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 16 ከቁጥር 12 እስከ 40 ውስጥ ተመዝግቧል፡፡ ለምሳሌ፣ ጳውሎስ በአውሮፓ ውስጥ የመጀመሪያውን የወንጌል ፍሬ ማለትም ነጋዴዋን ሴት ሊድያን የማረከው በዚያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለጌቶቿ በጥንቆላ ስራ ጥቅም ታስገኝ የነበረችውን ባሪያ ነጻ በማውጣቱ የታሰረውም በፊልጵዩስ ነበር፡፡ እጅግ ታዋቂ የነበረውም የወህኒ አዛዥ ጳውሎስ ለእርሱ ባሳየው ርኅራኄ ተነክቶ በክርስቶስ ያመነው በዚህ ስፍራ ነው፡፡
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የነበረው አገልግሎት ስኬታማ ነበር ምክንያቱም ከከተማዋ ለቅቆ ከሄደ በኋላ እንኳን ችግር ሲገጥመው የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በየጊዜው የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ጳውሎስን ይደግፉ ነበር፡፡ ጳውሎስ ልግስናቸውን አስመልክቶ በተናገረበት በምዕራፍ 4 ቁጥር 15 እና 16 የተቀመጠውን እናድምጥ፡
ከመቄዶኒያ በወጣሁ ጊዜ፣ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፣ አንድና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና፡፡ (ፊልጵስዩስ 4፡15-16)
በፊልጵስዩስ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ጳውሎስን ትወድደው ነበር፣ ስለዚህም በየጊዜው የገንዘብ ስጦታ ትልክለት ነበር፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 10 እና 18 እንደተጠቀሰው፣ ጳውሎስ ደብዳቤውን በሚጽፍበት ወቅት አካባቢ የፊልጵስዩስ ሰዎች ስጦታ ልከውለት ነበር፡፡ በዚህ ስፍር ጳውሎስ የተናገረውን እናድምጥ፡
ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፣ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፣ ጊዜ አጣችሁ እንጂ ማሰብስ ታስቡ ነበር፡፡ … በተሰሎንቄ እንኳን ሳለሁ… ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበር… ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ፡፡ (ፊልጵስዩስ 4፡10፣18)
ከፊልጵስዩስ አማኞች መካከል የገንዘብ አቅማቸው ስጋት በሌለበት ሁኔታ የተደላደለላቸው አንዳንድ ሰዎች ቢኖሩም፣ ቤተክርስቲያኒቱ በጠቅላላ ግን ጥልቅ ድህነት ውስጥ ናት፣ ስለዚህም ዘወትር ጳውሎስን በገንዘብ መደገፍ አይችሉም፡፡ እድሉን ሲያገኙ ግን፣ በልግስና ይሰጡታል፡፡
የፊልጵስዩስ ሰዎች ጳውሎስ እንደሚወድዱ ሁሉ፣ እርሱም በብርቱ ይወድዳቸው ነበር፡፡ ይወዳቸው የነበረውም ለጌታ ካላቸው መሰጠት፣ ደግሞም በወንጌል አገልግሎት የእርሱ አጋሮች ስለሆኑም ነበር፡፡ የቅርብ ወዳጆቹ ነበሩ፣ ከእነርሱ ሲለይ በጣም ጉድለት እንዲሰማው ያደረገው ደስ የሚያሰኝ ኅብረት ነበራቸው፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 4 እስከ 8 ስለ እነርሱ የተናገረውን እናድምጥ፡
ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፣ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌል በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ … በልቤ ትኖራላችሁና … በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና፡፡ (ማርቆስ 1፡4-8)
እንዲያውም፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 12 እና ምዕራፍ 4 ቁጥር 1፣ ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ሰዎችና የእርሱን የተወደዱ ወዳጆች ለመግለጽ የተጠቀመው agapetos (avgaphti.j) የሚለውን የግሪክ ቃል ነው፡፡ ጳውሎስ agapetos የተሰኘውን ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀመው የቅርብ የሥራ አጋሮቹን እና የተወደዱ ጓደኞቹን ማለትም፣ ቲኪቆስ፣ ኤጳፍራ፣ ፊልሞና፣ አናሲሞስን እና ሉቃስን የመሳሰሉትን ለመግለጽ ነው፡፡ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን የነበረው ፍቅር ለበርካታ ሌሎች አብያተክርስቲያናት እንዳው ፍቅር ዓይነት ሳይሆን፣ በጣም ብርቱና ቀረቤታን የሚያመለክት ፍቅር ነበር፡፡ ይህም ይገለጽ የነበረው በቀረቤታና በቤተሰባዊነት ስሜት ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም እያደገ በሚሄድ መልክ ቀጣይነት የሚኖረውን ወዳጅነት በሚያመለክት መንገድ ነበር፡፡
ይህም ሊያስገርመን አይችልም፡፡ በቤቷ ተቀብላ ባስተናገደችው በሊዲያና በጳውሎስ መካከል፤ በጳውሎስና ሕይወቱን ባተረፈው በእስር ቤቱ አለቃ መካከል፤ በእርሱና ከአጋንንት እስራት ነፃ በወጣችው ባሪያ መካከል የጠበቀ ወዳጅነት ሊኖር እንደሚችል መገመት አዳጋች አይሆንም፡፡ በእነዚህ ሁሉ ክንዋኔዎች፣ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የሚኖሩ አማኞችን ይበልጥ እየወደዳቸው ሄደ፡፡ እነርሱም ለእርሱ ተመሳሳይ ስሜት ነበራቸው፡፡
በጳውሎስና በፊልጵስዩስ ሰዎች መካከል ያለውን አንዱ ለአንዱ ግድ የመሰኘትና የመደጋገፍ እውነታ ከተመለከትን፣ ሐዋርያው በእስር ቤት ያሳለፈውን መከራ ወደመመልከቱ እንሸጋገር፡፡ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ሲጽፍ ያለፈበት መከራ ምን ነበር?
የእስር ቤት መከራ
ጳውሎስ ባሳለፈው የረጅም ዘመን አገልግሎት፣ በብዙ መከራ ውስጥ አልፏል፡፡ ደጋግሞ ተገርፏል፣ በዱላ ተደብድቧል፣ በቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ታድኗል፡፡ ብዙ ጊዜ ታስሯል፣ አንድ ጊዜ ደግሞ በድንጋይ ተወግሮ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበር፡፡ እነዚህን ያለፈባቸውን መከራዎች ሁሉ ያለምንም ችግር አላለፋቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጣም ጠጨንቆ ነበር፣ እንዲያውም ተስፋ ቆርጦም ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ በሦስተኛው የሚሲዮናዊ ጉዞው፣ በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 8 እንዲህ ጽፏል፡
ወንድሞች ሆይ፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቆርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር (2ኛ ቆሮንቶስ 1፡8)፡፡
በዚህ ስፍራ ጳውሎስ፣ የተሸናፊነትን ስሜት ያስተናገደ ይመስላል፣ ከገጠመው ፈታኝ መከራ የተነሳ እና በሚያልፍበት ክፉ ሁኔታ ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን ተስፋ ቆርጦ ነበር፡፡
ሕይወት በእርግት ተስፋ ቢስ እንዳልሆነች፣ እግዙአብሔር ከመከራችንም ሁሉ እንደሚያወጣን ጳውሎስ ያውቃል፡፡ ሆኖም ደግሞ እርሱም ሰብዓዊ ፍጡር ነበር፤ ልክ እንደሁላችንም ድካሞች ነበሩበት፡፡ እውነቱ ምንድነ ው፣ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት ማወቅና መማን ከተስፋ መቁረጣችን ለማዳን ብቻውን ብቁ የማይሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ጳውሎስም ተፈትኗል፡፡ ጳውሎስም እርግፍ አድርጎ መተው ፈልጎ ነበር፡፡ ጳውሎስም የተተወ መስሎት ነበር፡፡
ለፊልጵስዩስ የጻፈውን መልእክት በዝርዝር ስንመለከት፣ ለዚህች አጥብቆ ለሚወድዳት ቤተክርስቲያን ሲጽፍ ተመሳሳይ በሆነ ስሜት ውስጥ ሆኖ የጻፈ ይመስላል፡፡ የነበረው ነገረ-መለኮት በእውነቱ ላይ በብርቱ እንዲቆም አድርጎታል፣ እግዚአብሔር በመከራው ውስጥ እንኳን ሁሉን ለመልካም እንደሚያደርግ በማሰብ እንዲበረታ አድርጎታል፡፡ ሆኖም የጳውሎስ ልብ ግን አሁንም እንደከበደው ነበር፣ ሃዘኑም ደግሞ ጥልቅና ምክንያታዊ ነው፡፡
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክት፣ በልቡናው የነበሩትን ችግሮቹን ሁሉ ዝርግፍ አድርጎ አልገለጣቸውም፡፡ ጥቂቶቹን ግን ጠቅሷቸዋል፣ ደግሞም ሁሉም በአንድነት በልቡናው ላይ ያሳደሩበትን ተጽዕኖ ግን ግልጾታል፡፡ ለምሳሌ፣ ደግሞ ደጋግሞ ሞትን ከመከራው እንደሚገላገልበት መንገድ በመቁጠር በደስታ የሚጠብቀው መሆኑን ገልጧል፡፡ ለአብነት፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 10 እንዲህ ጽፏል፡
ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ፣ በሥቃዩ ተካፋይ እንድሆንና በሞቱም እርሱን እንድመስል እመኛለሁ፤ ፊልጵስዩስ 3፡10
በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ፣ አሁን እያለፈበት ያለው መከራ እጅግ ብርቱ ከመሆኑ የተነሳ የተሻለው የማምለጫ መንገድ ሞት መሆኑን ጳውሎስ ገልጧል፡፡ አሁን ያለበትን መከራ የመሞቻው መንገድ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁር 20፣ ጳውሎስ የነበረውን አመለካከት እንዲህ ይገልጸዋል፡
በምንም ዐይነት መንገድ አፍሬ እንዳልገኝ ጽኑ ናፍቆትና ተስፋ አለኝ፤ ነገር ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም በሕይወትም ሆነ በሞት ክርስቶስ በሥጋዬ እንዲከበር ሙሉ ድፍረት ይኖረኛል፡፡ (ፊልጵስዩስ 1፡20)
ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ብርታቱ ተሟጦበታል፣ ሆኖም ግን ከመፈተኑ አስቀድሞ ማትረፊያው እንደሚሆን ተስፋ ነበረው፡፡ የሚሻው ክርስቶስን ማክበር ነው፡፡ ማለትም አንድም በጸጋው በመከራው በመጽናት፣ አሊያም ደግሞ ንጽህናውን እንደጠበቀ፣ እምነቱም ሳይሸረሸር መሞት ማለት ነው፡፡
ይህንንም ካለ በኋላ ወዲያውኑ፣ ጳውሎስ በሚከተሉት ቃላት ሞትን የሚናፍቅ መሆኑን ገልጧል፡
ለእኔ መኖር ክርስቶስ ነው፤ ሞትም ማትረፍ ነው፡፡ በሥጋ ከቆየሁ፣ ፍሬያማ ተግባር ይኖረኛል፤ ነገር ግን የትኛውን እንደምመርጥ አላውቅም፡፡ በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ፣ ከክርስቶስም ጋር ልሆን እናፍቃለሁ፤ ይህ እጅግ የተሻለ ነውና፡፡ (ፊልጵስዩስ 1፡21-23)
ጳውሎስ ይህን በጻፈበት ወቅት፣ ሞትን ተመኝቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ዘወትር ሊኖርና ሊሰብክ ይፈልጋል፡፡ ወደ አዳዲስ ቦታዎች በመሄድ ወንጌልን ለሰዎች ሁሉ ለመስበክና ለዓለም ሁሉ ድነትን ለማምጣት ይፈልግ ነበር፡፡
በጤናማ ሁኔታዎች ውስጥ፣ ክርስቲያኖቸ ሞትን ሊናፍቁ አይገባም፡፡ አዎን በሞታችን ከክርስቶስ ጋር እንሆናለን፣ ያንንም በናፍቆት ልንጠባበቅ ይገባናል፣ ሆኖም ግን ሞትን እንደ ወዳጃችን ልንጠመጠምበት ግን አይገባም፡፡ እኛ የተፈጠርነወ ለሕያውነት ነው፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስተምሩን ሞት እርግማን ነው፡፡ ጳውሎስም ራሱ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቁር 26 ሞትን “ጠላት” ብሎታል፡፡ ሆኖም ጳውሎስ አሁን ባለበት የሕይወቱ ምዕራፍ፣ ያለበት ሁኔታ አስጨናቂ ነበር ስለዚህ በአገልግሎት ከመቀጠል ይልቅ ደግሞም ለሞት ካለው ጥላቻ ይልቅ ከክርስቶስ ጋር የመሆኑ ናፍቆት ሚዛኑ ደፍቶበታል፡፡
ጳውሎስ የተቸገረ ልቡናውን ሞትን በመናፈቅ ብቻ አይደለም የገለጠው፡፡ በተለያዩ ቦታዎችም በተለያየ መንገድ ገልጦታል፡፡ ለምሳሌ፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 27 እና 28፣ አፍሮዲጡ ከሕመሙ እንዲድን የሚናፍቅ መሆኑን እንዲህ ይገልጸዋል፡፡
በእርግጥም ታምሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ምህረት አደረገለት፤ በሐዘን ላይ ሐዘን እንዳይደራረብብኝ፣ ለእኔም ጭምር እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህ እርሱን እንደገና ስታዩ ደስ እንዲላችሁና የእኔም ጭንቀት እንዲቀል ልልከው በጣም ጓጉቻለሁ፡፡ (ፊልጵስዩስ 2፡27-28)
የአፍሮዲጡ ሞት የጳውሎስን ሐዘን በእጅጉ ያባብሰው ነበር፡፡ ምንም እንኳን የአፍሮዲጡ ወደ ፊልጵስዩስ መመለስ የጳውሎስን ጭንቀት ቢቀንሰውም ሊያጠፋው ግን አይችልም፡፡
የጳውሎስን ሃዘንና ጭንቀት፣ ደግሞም ስለ ሞት ያሰፈረውን ዐረፍተነገር ይበልጥ ሊያስረዳ የሚችለው፣ በዚህ ወቅት ሕይወቱ በስጋት ላይ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ባለው ትምህርት እንዳየነው፣ ይህንን ደብዳቤ የጻፈው አንድም ከሮም ወይም ከቂሳርያ ማርቲማ ሊሆን ይችላል፡፡ የጻፈው ከሮም ከሆነ፣ ቄሳር እንደሚያስገድለው ያስባል፡፡ የጻፈው ከቂሳርያ ማርቲማ ከሆነ ደግሞ፣ አይሁድ ሊያስገድሉት ስላላቸው እቅድ ተጨንቆ ሊሆን ይችላል፡፡ ፈተናው ምንም መልክ ይኑረው ምንም፣ ጳውሎስ በቅርቡ በሞት ሊለያቸው የሚችልበትን እውነታ ይገልጽላቸዋል፡፡
ለምሳሌ፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 20፣ “ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፣ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከበራል” በማለት በተስፋ ጽፏል፡፡ ደግሞም በምዕራፍ 1 ቁጥር 22 ውስጥ፣ “ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፣ ምን እንድመርጥ አላስታውቅም” በማለት ሞትን እንደሚመርጥ አመልክቷል፡፡ በምዕራፍ 2 ቁጥር 17 ውስጥ ሕይወቱ “እንደ መጠጥ ቁርባን” ልትፈስስ እንደምትችል ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም በምእራፍ 3 ቁጥር 10 ውስጥ፣ አሁን በክርስቶስ መከራ ለመካፈል እያለፈበት ያለው መከራ “በሞቱም ክርስቶስን ወደ መምሰል” ጳውሎስን በትክክል እንደሚመራው ሃሳብ ሰንዝሯል፡፡
ሆኖም ግን ጳውሎስ መቶ በመቶ እንደሚሞት አላረጋገጠም፡፡ በዚህ ደብዳቤው በአንድ ስፍራ የመትረፍ ተስፋ እንዳለው ገልጧል፡፡ ለምሳሌ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 25 “እንደምቆይ አውቃለሁ” በማለት በሕይወት ኖሮ የፊልጵስዩስን ሰዎች የማገልገል ናፍቆት እንዳለው አሳይቷል፡፡
በእርሱ ላይ ምን ሊደርስ እንደሚችል ጳውሎስ በእርግጠኝነት አያውቅም ነበር፡፡ በአንድ በኩል፣ ሞቱ አይቀሬ እንደሚሆን ያውቃል፣ ስለዚህም በፊልጵስዩስ ያሉት ወዳጆቹ ለከፋው ነገር ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሊተርፍ እንደሚችልም ደግሞ ጥቂት ተስፋ አለው፣ እናም የተሻለውን ነገር ተስፋ እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል፡፡ ለእርሱ የወደፊቱ ምንም ይሁን ምን፣ ደብዳቤውን ሲጽፍላቸው ግን በታላቅ መከራ ውስጥ ነበረና በሐዘንና በወደፊት ስጋት ውስጥ ነበር፡፡
ጳውሎስ ከፊልጵስዩስ ሰዎች ጋር ነበረውን ወዳጅነትና በእስር ቤት የነበረበትን መከራ ከተመለከትን፣ ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈላቸወ ወቅት በፊልጵስዩስ የነበሩትን ሁኔታዎች ወደ መመርመሩ እንሸጋገራለን፡፡ የጳውሎስን ማበረታቻና ትኩረት በሚፈልግ በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እያለፉ ነበር?
በፊልጵስዩስ የነበረው ሁኔታ
ጳውሎስ የዳሰሳቸው በርካታ ሁኔታዎች በፊልጵስዩስ ቢኖሩም እኛ ግን በሁለት ጉዳዮች ላይ ብቻ እናተኩራለን፡ የፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን ለጳውሎስ የነበራት በጎ ሃሳብ እና በፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን ውሰጥ የነበሩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ናቸው፡፡ አስቀድመን ለጳውሎስ የነበራቸውን በጎ ሃሳብ እንመልከት፡፡
ለጳውሎስ በጎ ማሰብ
በጥቅሉ፣ በፊልጵስዩስ የነበረችው ቤተክርስቲያን ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ጠንካራና በፍቅር ላይ ተመሠረተ ወዳጅነት ነበራት፡፡ በእስር ላይ እየደረሰበት ስላለው መከራ ሲሰሙ፣ ስለ እርሱ አሰቡ ተጨነቁም፡፡ ስለዚህም፣ አቅማቸው በፈቀደ መጠንና ጊዜ በቶሎ፣ የጳውሎስን ምድራዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ስጦታ በመላክ ደግሞም ስጦታቸውን እንዲያደርስላቸውና በእስር ላይ ሳለ ያገለግለውም ዘንድ አፍሮዲጡን ወደ ጳውሎ በመላክ ለእርሱ የነበራቸውን በጎ ሃሳብ ገለጡ፡፡
ጳውሎስም ይህንን ስጦታ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 18 ውስጥ እንዲህ በሚል የምስጋና ቃል ገልጾታል፡
ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። (ፊልጵስዩስ 4፡18)
ቀደም ብለን እንደጠቀስነው፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች ባለጠጎች አልነበሩም፣ ስለዚህ ይህ ስጦታ በእነርሱ ወገን ከፍተኛ መስዋእትነት የተገለጠበት ነው፡፡ ሆኖም ግን ስለ ጳውሎስ ደህንነት ግድ ስላላቸው በትልቅ ጉጉት ነው የላኩለት፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 25 እንደምናነብበው፣ የፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን ጳውሎስን በእስሩ ወቅት እንዲያገለግለው አፍሮዲጡንም ልካለታለች፡፡ ጳውሎስ በዚያ ስፍራ የተቀሰውን እናድምጥ፡
ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤ (ፊልጵስዩስ 2፡25)
በግልጽ እንደምናየው፣ ሞት በላዩ ላይ ያንዣበበ እስኪመስል ድረስ፣ ጳውሎስ በሌሎች አማኞች ከፍተኛ መከራ እየደረሰበት መሆኑን ሲሰሙ የፊልጵስዩስ ሰዎች ስለ እርሱ እጅግ እንደፈሩ አፍሮዲጡ ሪፖርት አድርጎለት ነበር፡፡ ስለዚህም ለእነርሱ በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ፣ ያለበትን ሁኔታ የፊልጵስዩስ ሰዎች በትክክል እንደተረዱ ያረጋገጠላቸው ሲሆን፣ ስለ እርሱ ግድ በመሰኘታቸውም ያለውን አድናቆት ገልጦላቸዋል፡፡
ለምሳሌ፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 15 እስከ 17 ድረስ፣ አንዳንድ የወንጌል አገልጋዮች እየተፈታተኑት መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የነበረበትን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡
አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር …የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤
… እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። (ፊልጵስዩስ 1፡15-17)
እንዲያውም፣ ጳውሎስን ካሳዘኑት ምክንያች አንዱ በዙሪያው ካሉት አማኞቸ መካከል፣ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ፣ ለወንጌል አገልግሎት ልባቸውን የሰጡት ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸወ ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ በፊልጵስዩስ 2፡21 የተናገረውን እናድምጥ፡
ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። (ፊልጵስዩስ 2፡21)
በአጭሩ፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች በዚህ ወቅት ተለዩት ለጳውሎስ ባላቸው በጎ ሃሳብ ነው፡፡ የጳውሎስ መከራ ብዙ ስለነበር ደጋፉም የሳሳ ነበር፡፡
የፊልጵስዩስ ሰዎች የጨነቃቸው ጳውሎስ መከራ መቀበሉ ብቻ አልነበረም፡፡ በቅጥር ነፍሰ ገዳዮችም ይሁን በአደባባይ በህዝብ ፊት ሊገደል እንደሚችል ስላሰቡ በጣም ተጨንቀው ነበር፡፡ እነዚህም ፍርሃቶች የተረጋገጡም ነበሩ፡፡ ቀደም ባለው ትምህርት እንዳየነው፣ አይሁድ ጳውሎስን ለማስገደል ከአንድ ጊዜ በላይ ሞክረዋል፣ የተከሰሰበትም ወንጀል በሞት የሚያስቀጣ ነበር፡፡ ስለዚህ የፊልጵስዩስ ሰዎች ለሐዋርያው ከነበራቸው ጥልቅ አሳቢነት የተነሳ፣ ስለ ጳውሎስ ለመጸለይ ራሳቸውን ሰጥተው ነበር፡፡ ጳውሎስም በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 19 እና 20 ውስጥ ስለጸሎታቸው እንዲህ በሚሉ የምሥጋና ቃላት ያመሰግናቸዋል፡
ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል።
(ፊልጵስዩስ 1፡19-20)
ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ሰዎች ስለ ጸሎታቸው ምሥጋናውን እየገለጠላቸው፣ ሞትን ግን ከዚህ መከራው እንደሚገላገልበት መንገድ እንደሚያየው ያረጋግጥላቸዋል፡፡
የፊልጵስዩስ ሰዎች ስለ ጳውሎስ የነበራቸውን አሳቢነት ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘናቸውንና በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የነበሩትን ችግሮች በጥቂቱ ወደመመልከቱ እንሸጋገራለን፡፡
ቤተክርሰቲያኒቱን የገጠሟት ችግሮች
የፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ሦስት ችግሮች ደርሰውባታል፡ አንደኛ፣ ከቤተክርስቲያኒቱ ውጪ ካሉ ሰዎች ስደት ደርሶባታል፡፡ ሁለተኛ፣ በሌሎችም አብያተክርስቲያናት ውስጥ ሰርጎ ገብቶ ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው የሐሰት እየተፈታተናት ነበር፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የእርስ በርስ ግጭትም ነበረባት፡፡ በፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረውን መከራ ጳውሎስ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 27 እስከ 30 እንዲህ ይገልጸዋል፡
ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።
በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤
ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤
በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና። (ፊልጵስዩስ 1፡27-30)
ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ የፊልጵስዩስን ቤተክርስቲያን ከመሠረተ በኋላ፣ አጎራባቿ በነበረችው የተሰሎንቄ ከተማ ነዋሪ ከነበሩት አይሁድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 ከቁጥር 5 እስከ 13 እንደምናነብበው፣ እነዚህ በቁጣ የተነሳሱ አይሁድ ጳውሎስንና ሌሎቹንም አማኞች የሮሜን ህግ ጥሰዋል ብለው ከሰዋቸው ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ፣ ጳውሎስ ከአይሁድ ሊደርስበት ከሚችለወ የከፋ መከራና በመንግስት አስተዳደሩ ከመታሰር ለማምለጥ በሌሊት ሸሽቶ ነበር፡፡ እነዚህ የተሰሎንቄ አይሁድ እጅግ ቀናተኞች ስለነበሩ ጳውሎስን እስ ቤርያ ድረስ ተከታትለውት ነበር፡፡ ስለዚህም፣ እነዚያው አይሁዶች ወይም ሌሎች እነርሱን መሳዮች፣ የፊልጵስዩስን ቤተክርስቲያን እንደተፈታተኑና የአካባቢውንም የመንግሥት አካል በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እንዳስነሱ ማሰብ ምክንያታዊ ነው፡፡ ሆኖም በፊልጵስዩስ የነበረው መከራ ልዩ ባህርይ ታወቀም አልታወቀም፣ ቤተክርስቲያኒቱ በማያምኑት ሰዎች በእውነት መከራ ውስጥ እንደነበረች ግልጽ ነበር፡፡
ሁለተኛው የፊልጵስዩስን ቤተክርስቲያን የገጠማት መከራ፣ የሐሰት ትምህርት ፈተና ነው፡፡ በዚህ ወቅት፣ የሐሰት ትምህርት የፊልጵስዩስን ቤተክርስቲያን ገና በጥልቀት ያላስቸገረበት ወቅት ይመስላል፣ ምክንያቱም ጳውሎስ በቀጥታ አልተጋፈጠውምና ነው፡፡ ሆኖም ወደ እነርሱ ከተማ ሊመጣ ለሚችለው የሐሰት ትምህርት የፊልጵስዩስን ሰዎች እያዘጋጃቸው ነበር፡፡ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ 3 ስለ መገረዝ የተናገረውን እናድምጥ፡
በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው።
ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።
እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና። (ፊልጵስዩስ 3፡1-3)
ግርዛትን በተጣመመ መንገድ የሚያስተዋውቁ የሐሰት መምህራን የፊልጵስዩስን ቤተክርስቲያን ሊያውኩ እንደሚችሉ ጳውሎስ አስቧል፡፡ በተጨማሪም በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 18 እና 19 የሀሰት ትምህርትን ረግሟል፡፡
ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ።
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። (ፊልጵስዩስ 3፡18-19)
ጳውሎስ በዚህ ስፍራ የተጠቀመው ቋንቋ በርካታ የሐሰት ትምህርቶችን ሊገልጥ ይችላል፣ የብሉይ ኪዳንን የአመጋገብ ህግ በማጣመም ስለሚበሉና ስለማይበሉ ነገሮች የሚያስተምሩትን ትምህርት የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
እነዚህን የመሳሰሉ የሐሰት ትምህርቶች ከሁለት ምንጮች ሊፈልቁ ይችላሉ፡፡ በአንድ በኩል፣ የቆላስይስን ቤተክርስቲያንና በሊከስ ሸለቆ የነበሩ አብያተክርስቲያናትን ያናወጠው የሐሰት ትምህርት ጳውሎስን አሳስቦት ሊሆን ይችላል፡፡
ቀደም ባለው ትምህርት እንደጠቀስነው፣ በሊከስ ሸለቆ የነበሩ የሐሰት ትምህርቶች ክርስቲያናዊ አስተምህሮን ከግሪክ ፍልስፍና፣ ከወግ አጥባቂነትና የአይሁድን ሕግ በመበረዝ የተደበላለቁ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፣ በቆላስይስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 11 እስከ 12 ውስጥ ጳውሎስ ይህንን የሐሰት ትምህርት ግርዘትን አዛብቶ ከመጠቀም ጋር እና በቆላስይስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 20 እስከ 23 ከአትያዝ አትቅመስና አትንካ ጋር አያይዞታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከኢየሩሳሌም የመጡት ክርስቲያን አክራሪ አይሁዶች (ጁዳይዘርስ) ጉዳይም አሳስቦት ሊሆን ይችላል፡፡ እነርሱም ገና ቀደም ብሎ በገላትያ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 11 እስከ 21 እና በቅርቡም ደግሞ በሮሜ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 9 እስከ 17 የጻፈባቸው ናቸው፡፡ ምናልባትም ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው ጉዞ ከእነርሱ ጋር ተፋልሞ ሊሆን ይችላል ያም ለአሁን መታሰሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ልክ በሊከስ ሸለቆ እንዳት የሐሰት መምህራን፣ ጁዳይዘሮቹም ግርዘትንና የአመጋገብ ሥርዓትን በማጣመም፣ አህዛብ አማኞች የብሉይ ኪዳንን ሕግ ወጎች እንዲጠብቁ ያስገድዳሉ፡፡
በመጨረሻም፣ ከስደቱና ከስህተት አስተምህሮ ባሻገር ፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች በቤተክርስቲያን ውስጥ በአማኞች መካከል ከተፈጠሩ ግጭቶች ጋር እየታገሉ ነበር፡፡ ጳውሎም እነዚህን ግጭቶች ጠቅለል ባለ አነጋገር በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 3 ውስጥ ባቀረበው ማሳሰቢያ ዳስሶታል፡
በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤
በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ (ፊልጵስዩስ 2፡1-3)
በፊልጵስዩስ ምእራፍ 4 ቁጥር 2 ደግሞ፣ ችግሮቻቸውን መፍታት ያቃታቸውን ሁለት ሴቶች እንዲህ በማለት ያሳስባል፡
በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። (ፊልጵስዩስ 4፡2)
በፊልጵስዩስ የነበረው የውስጥ ግጭት የከፋ የዲሲፕሊን ቅጣት አልተጣለበትም፡፡ ሆኖም፣ ሰላምን ያናጉ፣ ፍሬያማነትን የሚያጨናግፉና ኃጢአትን የተሞሉ ናቸው፡፡ ራስ ወዳድነት ያለበት፣ ያልተፈታ ግጭት በቤተክርስቲያን ውስጥ መቼም ቢሆን ስፍራ የለውም፡፡ ስለዚህ፣ ጳውሎስ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሊገለጥ ስለሚገባው አንድነትና ፍቅር ለመግለጽ ጠቀም ያለ ስፍራ ሰጥቶ ዳስሶታል፡፡
የፊልጵስዩስን መልእክት ዳራ ከዳሰስን፣ ሁለተኛውን ርዕሳችንን ለመመልከት እንዘጋጃለን፡ ያም ለፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን የተጻፈውና በቅዱስ መጽሐፍ እንዲካተት የተደረገው የጳውሎስ መልእክት አወቃቀርና ይዘት ነው፡፡
አወቃቀርና ይዘት
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልእክት አወቃቀርና ይዘት ለመመልከት፣ ደብዳቤውን በስድስት ዋና ክፍሎች ከፍለን እንቃኘዋለን፡፡ ይህም፡ በምዕራፍ 1 በቁጥር 1 እና 2 የሚገኘውን ሰላምታ፤ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 3 እስከ 8 የሚገኘውን ምሥጋና፤ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 9 እስከ 11 ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጸለየው ጸሎት፤ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 12 እስከ ምዕራፍ 4 ቁጥር 20 የሚገኘውን የደብዳቤውን ዋና አካል፤ ደግሞም በምዕራፍ 4 ከቁጥር 21 እስከ 23 የሚገኘውን የጳውሎስን የመጨረሻ ሰላምታ ይሆናሉ፡፡ እስኪ በቁጥር 1 እና 2 በሚገኘው ሰላምታ እንጀምር፡፡
ሰላምታ
በምዕራፍ 1 ቁጥር 1 እና 2 የሚገኘው ሰላምታ ጳውሎስን ተቀዳሚው የመልእክቱ ጸሐፊ አድርጎ ያስዋውቀንና መልእክቱ ከጢሞቴዎስም ጭምር እንደተላከ ይገልጻል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን፣ ጳውሎስ በደብዳቤው ውስጥ በዘላቂነት የተከተለው የአጻጻፍ ዘይቤ ራሱን የጠቀሰው “እኔ” በሚለው ነጠላ ቁጥር እንጂ “እኛ” በሚለው የብዙ ቁጥር አይደለም፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 21 እስከ 23 ውስጥ ስለ ጢሞቴዎስ የጠቀሰው በሦስተኛ መደብ ነው፡፡
በፊልጵስዩስ ውስጥ የምናገኘው ሰላምታ ከአብዛኞቹ የጳውሎስ ደብዳቤዎች ለየት ይላል ምክንያቱም የጳውሎስን ሐዋርያነት አለመጥቀሱ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው 1ኛ እና 2ኛ ተሰሎንቄ ደግሞም ፊልሞና ብቻ ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህ ሦስት ደብዳቤዎች የጳውሎስን ሐዋርያዊ ሥልጣን ከሰላምታው ውጪ ሌላ ስፍራ ጠቅሰውታል፡፡ ጳውሎስ ከሐዋርያዊ ሥልጣኑ ረገድ ምንም ዓይነት አትኩሮት ያላደረገበት መልእክት የፊልጵስዩስ መልእክት ብቻ ነው፡፡
ይህ ማለት ግን፣ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈው መልእክት ሐዋርያዊ ሥልጣን የለውም የማለት አንድምታ አለው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁኑ ከፊልጵስዩስ ሰዎች ጋር ያለው ወዳጅነት፣ ለጳውሎስ ያላቸው ታላቅ አክብሮት እና ጌታን ደስ ለማሰኘት ያላቸው ከፍተኛ ናፍቆት ምስክር ነው፡፡ ጳውሎስ አንድም ጊዜ እንኳን ስለ ቢሮውና ስለ ሥልጣኑ አልጠቀሰላቸውም፡፡
ጳውሎስ ከሰላምታው በማስከተል፣ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 3 እስከ 8 ወደሚገኘው የምሥጋና ክፍል ይሸጋገራል፡፡ ይህ ከሰላምታ ወደ ምሥጋና የሚደረገው ሽግግር በተቀሩት የጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ የተለመደ ሲሆን ከዚህኛው የሽግግር ዓይነት ለየት የሚሉት የገላትያና የቲቶ መልእክቶች ብቻ ናቸው፡፡
ምሥጋና
የመጀመሪው የጳውሎስ ምሥጋና የሚገኘው፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 3 እስከ 6 ውስጥ ሲሆን፣ በዚህም ውስጥ የተለመደውን ምሥጋናውን፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች ለጳውሎስ ያስገኙለትን ደስታ በስተመጨረሻም እርሱ የሚጠባበቀውን ድነታቸውን ይዳስሳል፡፡
ሆኖም በምዕራፍ 1 ቁጥር 7 እና 8 ውስጥ የተቀመጠው ምሥጋና ግን ከጳውሎስ የምሥጋና አቀራረብ ይለያል፣ ይህም ለፊልጵስዩስ ሰዎች ያለውን ጥልቅ ፍቅር አጽንዖት የሰጠበት ነው፡፡ በዚያ ስፍራ የተናገረውን እናድምጥ፡
በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል።
በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና።
(ፊልጵስዩስ 1፡7-8)
እነዚህ ቁጥሮች ጳውሎስ ከፊልጵስዩስ ሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት እጅግ ብርቱና ልብን የሚነካ መሆኑን ያሳዩናል፡፡
ጸሎት
ከምሥጋናው በማስከተል ጳውሎስ፣ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 9 እስከ 11 ድረስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ይጸልያል፡፡ ይህ ጸሎት እጥር ምጥን ያለ ሲሆን፣ በደብዳቤው ውስጥ አጽንዖት ሰጥቶ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች እምቅ አድርገው የያዙ ናቸው፡፡
በመሠረቱ፣ ጳውሎስ የጸለየው የፊልጵስዩስ ሰዎች ክርስቲያናዊ ፍቅራቸውን እግዚአብሔርን በሚያከብር መንገድ በመኖር እንዲገልጹ ነው፡፡ በመጀመሪያ፣ ትክክለኛ የሆነውን ፍርድ መፍረድ የሚችሉበት የመለየት መንፈስ እንዲኖራቸው ይጸልያል፡፡ ሁለተኛ፣ ይህም የመለየት መንፈስ መልካምን ስራ ወደማድረግ እንዲመራቸው፣ ክርስቶስ ዳግመኛ ሊፈርድ እስኪመለስም ድረስ በእምነት እና በኑሮ እንዲጸኑ ጸልዮላቸዋል፡፡ በመጨረሻም፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች በመልካም ሥራዎቻቸውና በጽናታቸው ለእግዚአብሔር ክብርንና ምሥጋናን እንዲመጡ ጸልዮላቸዋል፡፡
ጳውሎስ ከጸሎቱ በኋላ፣ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 12 እስከ ምዕራፍ 4 ቁጥር 20 ወደሚገኘው የመልእክቱ ዋና አካል ይሸጋገራል፡፡ ይህ ክፍል በተለያዩ ምሁራን በተለያየ መንገድ ይከፋፈላል፡፡ በዚህ ትምህርታችን ግን፣ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በሰጠው ማበረታቻና መመሪያ ላይ የተመሠረተውን አመክኖአዊ ፍሰት የተከተለውን አከፋፈል እንጠቀማለን፡፡
አካል
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ሲጽፍ፣ በብርቱ መከራ ውስጥ ነበር፣ እናም የግል ሕይወቱ እንኳን በትልቅ ስጋት ውስጥ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በችግርና በጭንቀት ተውጦ ነበር፡፡ ምናልባትም ተስፋ መቁረጥ ውስጥም ገብቶ ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ለፊልጵስዩስ ሰዎችም የጻፈላቸው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነበር፡፡
እነዚህ ንግግሮቹ ለእነርሱ የመጨረሻ ሊሆኑም እንደሚችሉ ጳውሎስ ያውቃል፡፡ ስለዚህ፣ ምን ያህል እንደሚወዳቸው፣ ስለ ወዳጅነታቸውና ስለ አገልግሎታቸው ምን ያህል ምሥጋናና አድንቆት እንዳለው እንዲያውቁ በማድረግ ውስጣዊ ስሜቱን ይገልጽላቸዋል፡፡ በስተመጨረሻም የሚያልፉበትን ፈተና እግዚአብሔርን በሚያከብር መንገድ እንዲያልፉት የመጨረሻ ጥበባዊ ምክሮቹን ይለግሳቸዋል፡፡
በፊልጵስዩስ መልእክት ውስጥ ያለውን ይህንን ገዢ ሃሳብ በልቡናችን ይዘን፣ በደብዳቤው አካል ውስጥ ያሉትን ሃሳቦቹን በሚከተሉት ቅደም ተከተሎች እንመረምራቸዋለን፡፡ አንደኛ፣ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 12 እስከ 26 የጳውሎስ የእስር ላይ ፅናት፤ ሁለተኛ፣ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 27 እስከ ምዕራፍ 4 ቁጥር 9 ለፊልጰስዩስ ሰዎች የሰጠው ማሳሰቢያ፤ ሦስተኛ፣ በምዕራፍ 4 ከቁጥር 10 እስከ 20 ስለ ፊልጵስዩስ ሰዎች ፅናት ጳውሎስ የሰጠወ ማረጋገጫ ናቸው፡፡ አስቀድመን በምዕራፍ 1 ከቁጥር 12 እስከ 26 ያለውን የጳውሎስን የእስር ላይ ፅናት በመመልከት፣ እያንዳንዳቸውን ክፍሎች በጥልቀት እንመለከታቸዋለን፡፡
የጳውሎስ የእስር ላይ ፅናት
ጳውሎስ በእስር ቤት በፅናት የቆው መከራውን በመካድ ወይም መከራውን ዝም ብሎ በመቀበል ሳይሆን፣ በመከራው ውስጥ ደስተኛ ሆኖ ማለፍ የሚችልባቸውን ምክንያቶች በመረዳት ነበር፡፡ የፊልጵስዩስ ሰዎች ስለ እርሱ መጨነቃቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግና ለማበረታታት ጊዜ ወስዶ ስለ ደስተኛነቱ ያብራራላቸዋል፡፡ ስለ እርሱ ግድ መሰኘታቸውን እያደነቀ፣ ያለበትን ሁኔታ እያሰቡ እንዲጨነቁ ግን አልፈለገም፡፡
በዚህ የደብዳቤወ ክፍል ውስጥ፣ በመከራው ውስጥ ባላስተዋላቸው ሦስት የደስታ ምንጮች ላ ያተኩራል፡፡ እነርሱም፡ ከቁጥር 12 እስከ 18ሀ ወቅታዊ የአገልግሎቱ ስኬታማነት፤ ከቁጥር 18ለ እስከ 21 ወደፊት ስለመለቀቁ ያለው ተስፋ፤ ከቁጥር 22 እስከ 26 ስለ ወደፊት አገልግሎቱ ያለው ጉጉት ናቸው፡፡ በእነዚህ በጎ ነገሮች ላይ በማተኮር፣ መከራውን በበለጠ አቅም መቋቋም እንደሚችል ጳውሎስ ያብራራል፡፡
ለምሳሌ፣ ከቁጥር 12 እስከ 18ሀ፣ ምንም እንኳን በእስር ላይ መከራ እየተቀበለ ቢሆንም፣ አገልግሎቱ ፍሬያማ ሆኖ እየቀጠለ ስለሆነ ደስ እንደሚለው ያብራራል፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 17 እሰከ 18 የጻፈውን እናዳምጥ፡
እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ።
ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። (ፈልጵስዩስ 1፡17-18)
በአንድ ወገን፣ ጳውሎስ መከራ የሚቀበለው በቅናት የተናደዱ ወንጌላውያን በፈጠሩበት ችግር ነው፡፡ እርሱን በግሉ ቢጎዱትም፣ እውነተኛውን ወንጌል ስለ ሰበኩ ግን ደስተኛ ነበር፡፡
ጳውሎስ በተጨማሪም ደስተኛ የሆነው ወደፊት መለቀቁን ተስፋ በማድረግ መሆኑን፣ በቁጥር 18ለ እስከ 21 ውስጥ ገልጧል፡፡ በስተመጨረሻው ከእስር የመለቀቅ ተስፋ እንዳለው አትኩሮት አድርጎ ጽፏል፡፡ ሆኖም ቀደም ብለን እንደተናገርነው፣ የጳውሎስ መከራ እጅግ ብርቱ ስለነበር ሞት እንኳን እንኳን ደህና መጣህ የሚባል መገላገያ ነበር፡፡ ስለዚህም፣ በነጻ በመለቀቁም ይሁን በሞቱ ከመከራው እንደሚገላገል ባለወ ተስፋ ይበረታታል፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 18 እስከ 21 አመለካከቱን እንዲህ ገልጾታል፡
ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።
ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል።
ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። (ፊልጵስዩስ 1፡ 18-21)
በአንድ በኩል፣ የሞቱ ፈተና ጳውሎስን አስቸግሮታል፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ ከሞት በስቲያ በሰማያት በክርስቶስ ፊት የሚጠብቀውን ደስታ ማየት ችሏል፡፡ እናም በመለቀቁና በመንግሥተ ሰማያት ላይ በማትኮር፣ በመከራው መካከል የላቀ ደስታ የሚያጣጥምበትን አቅም አግኝቷል፡፡
በተመሳሳይም መንገድ፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 22 እስከ 26፣ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ስለሚሰጠው የወደፊት አገልግሎት በማሰብ ደስ ይለዋል፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 25 እስከ 26 የጻፈውን ማበረታቻ እናድምጥ፡
ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ። (ፊልጵስዩስ 1፡25-26)
የፊልጵስዩስ ሰዎች ጳውሎስን ይወዱታል፣ ስለዚህ አሁንም የመለቀቅ ተስፋ እንዳለው ሲሰሙ ጭንቀታቸው ቀለል ይልላቸዋል፡፡ እርሱም ደግሞ ይወድዳቸዋል፣ ስለዚህም በክርስቶስ ያላቸውን ብልጽግና በማሰብ በዚያ ይጽናናል ይረካልም፡፡
እንዲጸኑ የቀረበ ማሳሰቢያ
ጳውሎስ በእስር ውስጥ ያለፈበትን ጽናቱን የፊልጵስዩስ ሰዎች ስለ እርሱ እንዳይጨነቁ ለማበረታታት ከተጠቀመበት በኋላ፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 27 እስከ ምዕራፍ 4 ቁጥር 9 ባለው ሰፊ ክፍል ውስጥ የፊልጵስዩስ ሰዎችም እንዲጸኑ ማሳሰቢያውን ያቀርባል፡፡ በዚህ ስፍራ፣ አስጨናቂ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይቀር ለክርስቶስ ታማኝ ሆነው በመዝለቅና ተምሳሊታዊ ሕይወት በመምራት እንዲጸኑ ጳውሎስ መመሪያ ይሰጣል፡፡
በጳውሎስ ማሳሰቢያ ላይ የምናቀርበው ዘገባ በሚከተሉት አራት ረዕሶች ላይ የመወያያ ሃሳቦችን ያቀርባል፡ በምዕራፍ 1 ከቁጥር 27 እስከ ምዕራፍ 2 ቁጥር 18 ስለ መጽናት አስፈላጊነት፤ በምዕራፍ 2 ከቁጥር 19 እስከ 30 አገልጋዮች ህዝቡን ለማጽናት ስለሚያደርጉት እገዛ፤ በምዕራፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ ቁጥር 16 የራሱ የጳውሎስ መጽናት ተምሳሊት፤ በስተመጨረሻም በምዕራፍ 3 ከቁር 17 እስከ ምዕራፍ 4 ቁጥር 9 ጽናትን ስለሚፈታተኑ ተግዳሮቶች የሰጠው መመሪያ ናቸው፡፡ በመጀመሪያም፣ በክርስትና እምነትና ልምምድ ውስጥ መጽናት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጳውሎስ ምን እንዳለ እንመልከት፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 27 እስከ 29 ድረስ የፊልጵስዩስ ሰዎች በመከራ ውስጥ እያለፉ ስለመሆኑ እውቅና ከሰጠ በኋላ፣ ጳውሎስ በሚከተሉት ቃላት ያበረታታቸዋል፡
ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።
በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤
ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ (ፊልጵስዩስ 1፡27-29)
የፊልጵስዩስ ሰዎች መከራ አስጨናቂና ስቃይ የሞላበት ነው፡፡ ሆኖም ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጪ አይደሉም፡፡ በተቃራኒው፣ እግዚአብሔር ራሱ እነርሱን ለመባረክ በእቅድ ያመጣው ነው፡፡ ስለዚህም፣ በእነዚህ ፈታኝ ወቅቶች ውስጥ በጽናት በማለፍ ደግሞም በጽድቅ በመኖር እምነታቸውን ጠብቀው የመዝለቃቸው ነገር እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
በሌሎቹ ትምህርቶች እንደተመለከትነው፣ የኢየሱስ በመከራ የማለፍ ተግባር ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ይዘልቃል፡፡ ይህንንም ወደ ፍፃሜ የሚያመጣው ቤተክርስቲያን እርሱ ባቀደላት መከራ ውስጥ እንድታልፍ በማድረግ ነው፡፡ አማኞች ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናቸው ምክንያት፣ እኛ መከራ ስንቀበል፣ ኢየሱስም መከራ ይቀበላል፡፡ እንደ ጳውሎስ አመለካከት፣ ይህ ጉዳይ በክርስቶስ የታቀደውን መከራ የመፈጸም ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የክብር ማዕረግም ጭምር ነው፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 27 እስከ 29 ስናነብብ፣ እግዚአብሔር የፊልጵስዩስ መከራ እንዲቀበሉ “መፍቀድ” ብቻ ሳይሆን በመከራ ማለፋቸው “አይቀሬ” መሆኑንም አረጋግጧል፡፡ ጳውሎስ ይህንን ሃሳብ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 5 እስከ 9፣ እንዲህ በመጻፍ ገልፆታል፡
በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።
እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ (ፊልጵስዩስ 2፡5-9)
ኢየሱስ ለቤተክርስቲያን ጥቅም ሲል በመከራና በስቃይ ውስጥ በፍፁም ፈቃዱ አለፈ፣ ለዚህ መስዋዕትነቱም የተቀበለው ብድራት ሊቆጠር የማይችል እጅግ ታላቅ ነበር፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ ክርስቲያኖችም ስለ ቤተክርስቲያን ጥቅም ሲሉ መከራንና ስቃን በትህትናና በጽናት ሊቀበሉ ይገባቸዋል፡፡ ይህንን የምናደርግ ከሆነ ብድራታችን እጅግ ታላቅ ይሆናል፡፡
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 17 እና 18 ውስጥ እንዲህ ሲል የጻፈው ለዚህ ነው፡
ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤
እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ። (ፊልጵስዩስ 2፡17-18)
ጳውሎስ ይፈልግ የነበረው የፊልጵስዩስ ሰዎች እንዲያልፉበት በተመደበላቸው ፈተና ውስጥ በጽናት እንዲያልፉ ብቻ ሳይሆን፣ የሚያስገኘውን በረከት እያሰቡ በመከራቸው ደስ እንዲላቸው ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ መከራቸውን ተከትሎ የሚመጣውን በረከት በማሰብ እርሱ ደስ እንደሚለው ሁሉ፣ እነርሱም በእርሱ መከራ በተገኙት በረከቶችም ደስ እንዲላቸው ይፈልጋል፡፡
አማኞች በሚገጥሟቸው እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ሳይቀር፣ በእምነትና በተቀደስ አኗኗር ለመጽናት መከራዎቻቸው በሚያስገኙላቸው በረከቶችና ብድራቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጳውሎስ አበረታትቷቸዋል፡፡ በመከራ እስካልጸኑ ድረስ፣ መከራ ከሚያስገኛቸው በረከቶች ተቋዳሽ መሆን እንደማይችሉ እሙን ነው፡፡
ጳውሎስ በመጽናት አስፈላጊነት እና በሚያስገኛቸው በረከቶች ላይ አፅንዖት በመስጠት ብርሃን ከፈነጠቀላቸው በኋላ፣ በመከራ ውስጥ እንዲጸኑ እገዛ የሚያደርጉ አገልጋዮችን በመላክ ተገቢውን ክብካቤ እንዲያደርጉ በማድረግ ተግባራዊ እገዛ ያደርግላቸዋል፡፡
የፊልጵስዩስ ሰዎች መከራን እንዴት ሊይዙት እንደሚገባ የጻፈላቸው መልእክት አስተማሪ እንደሚሆን ጳውሎስ ያውቃል፡፡ በመከራ መጽናትን ከሁሉ ይልቅ ቀላል የሚያደርገው ደግሞ በዕለት ከዕለት ገጠመኞቻችን ከጎናችን በመሆን፣ በመከራ እየጸኑ መጽናትን በተግባር የሚያሳዩንን ሰዎች ማግኘት እንደሆነም ያውቃል፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስ ከመልእክቱ በተጨማሪ በዚህ ፈታኝ ወቅት የፊልጵስዩስን ሰዎች እንዲግዙ ወዳጆቹን ወደ እነርሱ ይልካቸዋል፡፡
በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ ያቀደው አፍሮዲጡን ሊልከው ነበር ያቀደው፣ እርሱም ጳውሎስን እንዲረዳ እነርሱ ራሳቸው የላኩት መልእክተኛቸው ነበር፡፡ በመሠረቱም አፍሮዲጡ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልእክት ያደረሰ ሰው ነበር፡፡ ከፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁር 25 እስከ 30 እንደምንረዳው፣ አፍሮዲጡ በመታመሙ ምክንያት የፊልጵስዩስ ሰዎች ተጨንቀው ነበር፣ በዚህም ምክንያት ደግሞ አፍሮዲጡ ራሱም ስለ እነርሱ ተጨንቆ ነበር፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ አስቀድሞ ልባቸውን እንዲያረጋጋ ደግሞም በሚያስፈልጋቸው ነገር እንዲያግዛቸው አፍሮዲጡን መልሶ ላከው፡፡
ቀጥሎም፣ ጢሞቴዎስንም ወደ ፊልጵስስ ሊልከው ወስኗል፡፡ ለጊዜው፣ ከጳውሎስ ጋር በእስር ቤት ይቆያል፣ ሐዋርያውንም በዚህ የጭንቅ ወቅት ያገለግለዋል፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 19 እንደምናነበው ግን የፊልጵስዩስን ሰዎች እንዲያግዛቸው ወደፊት በቶሎ እንደሚልከው ጳውሎስ ተስፋ ያደርጋል፡፡
በመጨረሻም፣ ራሱም ከእስር እንደሚፈታና የፊልጵስዩስንም ሰዎች ለማገልግል የመምጣት ተስፋ እንዳለው ጳውሎስ ይነግራቸዋል፡፡ ይህንንም ተስፋውን በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 24 ውስጥ እንዲህ በማለት ገልጾታል፡
ራሴ ደግሞ ግን ፈጥኜ እንድመጣ በጌታ ታምኜአለሁ። (ፊልጵስዩስ 2፡24)
በዚህ ስፍራ “ታምኛለሁ” ተብሎ ነው የተተረጎመው pepoitha (pe,poiqa) ተሰኘው የግሪክ ቃል፣ የተሻለ የሚሆነው “አምኛለሁ” ተብሎ ቢፈታ ነው፡፡ ጳውሎስ መፈታቱን ተስፋ ያደርጋል፣ ሆኖም እርግጠኛ አልነበረም፡፡
በሁሉም ሁኔታዎች፣ በፊልጵስዩስ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ከመከራ ዶፍ ጋር ትንቅንቅ በሚገጥሙበት ወቅት የሰው ችግር የሚገባቸው አዛኝ ሰዎች እጅግ አስፈላጊና ተወዳጅ እንደሆኑ ጳውሎስ ያውቃል፡፡ ስለዚህም፣ በመከራ ውስጥ የማለፍን ጎዳና የሚያስተምሯቸው አፍቃሪና የተካኑ አገልጋዮችን በመደበኛነት ሊልክላቸው እቅድ ያወጣል፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ከቁር 1 እስከ 16 በሚገኘው ቀጣይ የማሳሰቢያ ክፍል፣ በአስተሳሰብም ሆነ በባህርይ ረገድ በመከራ ውስጥ በእምነት ጸንቶ የመቆምን የራሱን ምሳሌነት አዎንታዊ ገጽታ ጳውሎስ ያቀርብላቸዋል፡፡
በተለይም፣ በክርስቶስ ወደ ማመን ሲመጣ የእግዚአብሔርን ሞገስና በረከት ለማግኘት በምድራዊ ነገሮች መደገፍን እንዳቆመና ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ መታመንን እንደጀመረ ጳውሎስ ያብራራላቸዋል፡፡ ይህንን ያደረገው ግን ምድር የምታወጣቸውን መስፈርቶች ማሟላት ስላቃተው አልነበረም፡፡ ይልቁኑ፣ በምድራዊ መመዘኛዎች ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በፊቱ ሞገሰ ከሚሰጣቸው ሰዎች ተቀዳሚ የሚሆነው ጳውሎስ ነበር፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 4 እስከ 6 ስለ ማስረጃዎቹ ጳውሎስ የተናገረውን እናዳምጥ፡
እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ።
በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤
ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። (ፊልጵስዩስ 3፡4-6)
ህግን በመፈጸም የእግዚአብሔርን በረከት መቀበል የሚችል ሰው በምድር ላይ ሊገኝ ቢችል ኖሮ ያ ሰው የሚሆነው ጳውሎስ ነበር፡፡
ሆኖም የጉዳዩ እውነታ ግን፣ የወደቀው የሰው ዘር የእግዚአብሔርን ማዳንና የዘላም ሕይወት በረከት እንዲቀበል የሚያስችለው መልካምነት ሊኖረው አለመቻሉ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ጳውሎስ በምድራዊ ነገሮቹ መታመንን አሻፈረኝ በማለት፣ በእምነት የእርሱ ሆኖ እንዲቆጠርለት እግዚአብሔር በወሰነው የክርስቶስ ሥራ መታመንን መረጠ፡፡
እንዲሁም ደግሞ፣ አማኝ ነኝ ብሎ መናገር ብቻ ድነትን እንደማያስገኝም ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ይልቁንም፣ ከዳንን በኋላም በእምነታችን ጸንተን በመቆም ድነታችንን እስከ ፍፃሜው ማጽናት ይገባናል፡፡ ይህም ማለት እምነታችን አጽንተን መያዝ፣ የተቀደሰ ሕይወት መኖር ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ ካልሆነ ግን ያመንነው በከንቱ ነው ማለት ነው፡፡
በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ከቁር 12 እስከ 16 ስለ መጽናት ከፍተኛ አፅንኦት የሰጠውና በክርስቶስ ስለሚገኘው ድነት እንዲህ ሲል የጻፈው በዚህ ምክንያት ነው፡
አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ።
ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥
በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ።
እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤
ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። (ፊልጵስዩስ 3፡12-16)
አማኝነትን ማወጅ ብቻውን በቂ አይደለም፣ ማመንን በመጽናት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ እስከ ፍፃሜው ካልጸናን፣ በክርስቶስ ያገኘነውን እምነት ወይም ድነታችንን አጽንተን ካልያዝን እና በተቀደሰ አኗኗር ለእርሱ ታማኝ ሆነን ካልዘለቅን እምነታችን ሐሰት መሆኑን አረጋገጥን ማለት ነው፡፡
ጳውሎስ አይቀሬ በሆነው መከራ ጸንቶ ስለ መዝለቅ ያቀረበው የመጨረሻ ሙግት፣ የሚገኘው በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 17 እስከ ምዕራፍ 4 ቁጥር 9 ድረስ ነው፡፡ እነዚህ ማሳሰቢያዎች በተቀዳሚነት የያዙት የፊልጵስዩስ ሰዎች የእርሱን የመጽናት ተምሳሊት ተከትለው እነርሱም እንዲጸኑ ያሳሰበበትን የተዛምዶ ሃሳብ ነው፡፡
ጳውሎስ ስለ መጽናት ሲሞግታቸው፣ የሐሰት መምህራን፣ ወይም በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ግጭት፣ ወይም መከራ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት ለማላላት ምክንያት እንዳይሆንባቸው የፊልጵስዩስን ሰዎች በእጅጉ ያበረታታቸዋል፡፡ አስቀድሞ የሚያነሳውም የሐሰት ትምህርት የቤተክርስቲያንን ጽናት ለመፈታተን ወረራ በሚያደርግባቸው መንገዶች ላይ በማትኮር ነው፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 18 እና 19፣ ያሰፈረውን ብርቱ እርግማን እናድምጥ፡
ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ።
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። (ፊልጵስዩስ 3፤18-19)
እነዚህ የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች አማኞች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም፣ ቤተክርስቲያንን በሚፈታተኑበት ስፍራ ላይ ናቸው፤ ያም የሆነው በሚያባብል ቃል ስለሚናገሩ ወይም በቤተክርስቲያን ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ምንም ይሁን ምን፣ አማኞች የክርስቶስ ጠላቶች የሆኑትን የሐሰት ትምህርቶች በመቃወም፣ በንፁህ የክርስትና እምነትና ልምምድ መጽናት እንደሚገባቸው ጳውሎስ ያሳስባል፡፡ ከመከራና ከስቃይ ለመሸሽ ሲባል በወንጌል ያለን እምነት ለመጣል በቂ ምክንያት አይደለም፤ ደግሞም የማይረቡ ሙግቶችና ክርክሮች የጌታ ኃይል ምትክ ሊሆኑ አይገባቸውም፡፡
በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ እውነተኛ አማኞች የተቀሩት አማኞችም እንዲጸኑ ሊሞግቷቸው እንደሚገባ ጳውሎስ ያስጠነቅቃል፡፡ ለዚህ አንዱ ምሳሌ የሚሆነን፣ በኤዎድያና በሲንጤኪ መካከል ስላለው ሙግት የጠቀሰው ነው፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 3 ያለውን እናንብብ፡
ስለዚህ፥ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ፥ እንዲሁ በጌታ ቁሙ፥ ወዳጆች ሆይ።
በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ።
አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎቹ ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና። (ፊልጵስዩስ 4፡1-3)
ኤዎድያና ሲንጤኪ በነበሩበት በዚህ ግጭት ምክንያት በተቀደሰ አኗኗ እንዳይጸኑ ፈተና ሆኖባቸዋል ደግሞም የነበራቸው ተፅዕኖ በፊልጵስዩስ ሚኖሩ አማኞችንም ጽናት ተፈታትኗል፡፡
በመጨረሻም፣ ጳውሎስ በግላቸው የሚደርስባቸው ፈተና ጽናታቸውን እንዳይፈታተን የፊልጵስዩስን ሰዎች እያሳሰበ፣ ይልቁኑ በነገር ሁሉ ደስ የሚሰኙበትን አስተሳሰብ በመያዝ፣ መጨነቅ ተስፋ እንዲቆርጡ እንዳያያደርጋቸው ይመክራል፡፡ ይህም አስተሳሰቡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 4 እስከ 7 በአግባቡ ተቀምጧል፡፡
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ።
ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ።
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።
አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። (ፊልጵስዩስ 4፡4-7)
ጳውሎስ የሰጠው ተግባራዊ መመሪያ እግዚአብሔር ጭንቀታቸውን እንዲያስወግድላቸው አማኞች እንዲለምኑ ነው፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች፣ እግዚአብሔር ይህንን የሚያደርገው አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን ዘወር በማድረግ ነው፡፡ በብዙዎቹ ጉዳዮች ግን ጳውሎስ የሚጠብቀው፣ በልብና በአዕምሮ ውስጥ ያለው ዝንባሌና አመለካከት እንዲለወጥ ነው፡፡
የጽናት ማረጋገጫ
በመጨረሻም፣ በምዕራፍ 4 ከቁጥር 10 እስከ 20 ድረስ፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች በክርስትና እምነትና ኑሮ፣ በተለይም ለጳውሎስ ለራሱ በሚሰጡት አገልግሎት በጽናት መቀጠላቸውን በመጥቀስ በመከራ መጽናታቸውን አረጋግጦ የደብዳቤውን አካል ያጠናቅቃል፡፡
በዚህ ክፍል፣ በእስር ቤት የነበረበትን መከራ ለማቅለል ስለላኩለት ገንዘብ በመጥቀስ ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ሰዎች ያመሰግናቸዋል፡፡ የጳውሎስ የምስጋናው ማስታወሻ ገንዘቡ የደረሰው መሆኑን ደግሞም ያለበትንም ሁኔታ ሻል ለማድረግ እንደረዳውም አረጋግጦላቸዋል፡፡ ገንዘቡ ለጳውሎስ ያበረከተው ከሁሉ የሚበልጠው ፋይዳ ስሜቱን በእጅጉ መጠገኑ ነው፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ከቁር 12 እስከ 14 የተናገረውን እናድምጥ፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ።
ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።
ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። (ፊልጵስዩስ 4፡12-14)
ምናልባት ገንዘቡ የጳውሎስን መከራ ቀነስ አድርጎት ሊሆን ይችላል፣ እርካታው የተገኘው ግን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ ድጋፍ ያበረከተው ትልቅ አስተዋፅዖ የጳውሎስን ልብ መንካቱ ነው፡፡ እነዚህ ችግረኛ ክርስቲያኖች ስለ እርሱ ሲሉ የከፈሉት መስዋዕትነት፣ በእውነት ምን ያህል እንደሚወድዱት ጳውሎስ እንዲረዳ አድርጎታል፡፡
የፊልጵስዩስ ሰዎች ለጳውሎስ የነበራቸውን ፍቅር የገለጡት በጥሩ ሁኔታ ውስጥ አልነበረም፡፡ በዚህ ወቅት የጳውሎስ እሥራት እጅግ ከብዶበት ነበር፡፡ እየተሰቃየና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት እጅግ በርካታ ሰዎች እንደሚወድዱት ደግሞም የመከራው ተካፋዮች ሊሆኑ እንደሚፈቅዱ መረዳት ምንኛ ልብን ይደግፋል!
ምናልባትም ጳውሎስን ከጭንቀቱ የገላገሉት የፊልጵስዩስ ሰዎች ይሆኑ? በማለት አንድ ሰው ቢጠይቅ አግባብነት አለው፡፡ ተስፋውስ እንዲለመልም ያደረገው የእነርሱ ግድ መሰኘት ይሆን? በተከበበት መከራ ውስጥ ደስ እንዲለው ያነቃቃው ፍቅራቸው ይሆን? ጳውሎስ የተረሳ ወይም ብቸኛ እንዳልሆነ ያሳሰበው ወዳጅነታቸው ይሆን? አንድ ነገር የተረጋገጠ ነው፣ ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ሰዎች በሙሉ ልቡ ይወድዳቸዋል፡፡ ስጦታቸው ከማበረታታት በስተቀር ሌላ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡
የመጨረሻ ሰላምታ
በመጨረሻ፣ መልእክቱ የሚጠናቀቀው በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 21 እስከ 23 በሚገኘው የጳውሎስ የመጨረሻ ሰላምታ ነው፡፡ ይህ ክፍል የተለመደው ዓይነት ነው፣ ሆኖም ግን ከመጨረሻ ሰላምታዎቹ አንዱ ገፅታ ሃሳብ ሊሰጥበት ይገባል፡፡
በተለይም፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 22፣ ጳውሎስ ከቄሳር ቤተሰብ ለሆኑት ቅዱሳን ሰላምታ ያስተላልፋል፡፡ በጥንት ጊዜ፣ የቄሳር ቤተሰብ የሚለው መጠሪያ ምንም እንኳን ከቄሳር ጋር በአንድ ስፍራ ባይኖሩም በያሉበት ያሉትን የእርሱን ቤተሰብ አባላት እና ሠራተኞች ያካትታል፡፡ የእርሱ አገልጋዮች የሚባሉት የቤት ሠራተኞቹ ብቻ አይደሉም፤ የግል ልዩ ጥበቃዎቹን፣ ደግሞም በርካታ የመንግሥት ሠራተኞችንም ያካትታል፡፡
በዚህ ስፍራ የቄሳር ቤተሰዎች መጠቀሳቸው በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የሚከተለውን ድምዳሜ እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፣ ያም፣ ጳውሎስ የጻፈው ከሮም፣ ማለትም ቄሳር ከሚኖርበትና ከሚገዛበት ከተማ ስለሆነ አብሮት ያለውን ቤተሰብ ያመለክታል የሚል ነው፡፡ ሆኖም ይህንን ድምዳሜ በቶሎ ለመቀበል መቸኮል የለብንም፡፡ የቄሳር መንግሥት ሠራተኞች በጠቅላላ እና ጥበቃዎቹ፣ በቂሳርያ ማርቲማ የሚኖሩትን ጨምሮ ማለት ነው፣ እንደ ቄሳር ቤተሰዎች ይቆጠራሉ፡፡
ምንም ይሁን ምን፣ ከቄሳር ወገን የሆኑት አማኞች መጠቀሳቸው የሚያመለክተው የጳውሎስ መታሰር የወንጌል አገልግሎቱን እንዳላስቆመው ነው፡፡ ይልቁኑ፣ ጳውሎስ ከአሳሪዎቹ ቤት እንኳን ሳይቀር ደቀመዛሙርት በማፍራት እንዲገሰግስ አድርጎታል፡፡
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልእክት ዳራ፣ አወቃቀሩንና ይዘቱንም ጭምር ከመረመርን፣ አሁን ደግሞ ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ያስተላለፈው ትምህርት በእኛ ዘመን የሚዛመድበትን መንገድ እንቃኛለን፡፡
ዘመነኛው ተዛምዶ
የፊልጵስዩስ መጽሐፍ በእኛ ዘመን ሰዎች ሕይወት ሊዛመድ የሚችልባቸው በርካታ የተለያዩ መንገዶች መኖራቸው አነጋጋሪ አይሆንም፡፡ ሆኖም በዚህ ትምህርት ጳውሎስ በምድር የመቆት ዘመኑ መጨረሻ በመሰለው በዚህ ወቅት ሌሎችን ለማበረታታት ያደረገውን ጥረት ትኩረት ሰጥተን እንመለከተዋለን፡፡ በዚህ አስተሳሰብ አንፃር፣ አንድ መሪ ሃሳብ ጎላ ብሎ ይወጣል፡፡ ያም፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች እንዲጸኑና በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ጳውሎስ የሰጠው ማበረታቻ ነው፡፡ የፊልጵስዩስ መልእክት ለእኛ የሚኖረውን ፋይዳ ስንመረምር፣ ትኩረታችንን በመልእክቱ ሁለት ገጽታዎች ላይ እናደርጋለን፡፡
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈው መልእክት ለዘመነኛው የክርስትና ሕይወት የሚኖረውን አንድምታ ስንቃኝ፣ የክርስቲያኖችን ጽናት ሦስት ገፅታዎች እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የመጽናትን ባህርይ እንዳስሳለን፡፡ ሁለተኛ፣ የመጽናትን ልቡና እንቃኛለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ የቤተክርስቲያንን የመጽናት አገልግሎት እንወያይበታለን፡፡ አስቀድመን የመጽናትን ባህርይ እንመልከት፡፡
የመጽናት ባህርይ
በፊልጵስዩስ መልእክት ውስጥ፣ ጳውሎስ ስለ መጽናት ያስተላለፋቸው ትምህርቶች በሦስት ዐበይት እውነታዎች አንፃር በቀላሉ ልንረዳቸው የምንችላቸው ናቸው፡፡ የመጽናት ትርጓሜ፤ የመጽናት አስፈላጊነት፤ የመጽናት ማረጋገጫ፡፡ ስለዚህ፣ ጳውሎስ ስለመጽናት የሰጠውን ማብራሪያ በመመልከት እንጀምር፡፡
ትርጓሜ
ጳውሎስ መጽናትን የሚቃኘው እውነተኛ እምነትና የተቀደሰ አኗኗር በሚሉ መንታ እውነታዎች አንፃር ነው፡፡ በአንደ በኩል፣ ጽናት በክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል ያመንንበትን እምነት ማለትም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ተብለን ለመቆም የቻልንበትን የእርሱን ሥራ ብቻ በመደገፍ እንድንዘልቅበት ያደርጋል፡፡ ጳውሎስ ይህን ጉዳይ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 27 ውስጥ፣ ስለፊልጵስዩስ ሰዎች ያለውን ተስፋ እንዲህ በማለት ሲጽፍ አንጸባርቆታል፡
ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። (ፊልጵስዩስ 1፡27)
እንደ አማኝነታችን፣ ስለ ወንጌል ባለን ቁርጠኝነት ልንጸና ደግሞም ከእምነት ዘወር አለማለት ያስፈልገናል፡፡ በእምነት ስለ መጽናት ስንናገር ይህንን ማለታችን ነው፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ወንጌል በእውነት ማመን በበርካታ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል፣ ሆኖም ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 8 እና 9 ውስጥ ስለ ክርስትና እምነት ማእከላዊ ትኩረት የገለጸውን አንድ ነጥብ እናዳምጥ፡
አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ (ፊልጵስዩስ 3፡8-9)
በዚህ ምንባብ፣ ጳውሎስ የነበረው ሰብዓዊ ማንነትና መልካም ሥራዎቹ እውነተኛ ጽድቅንና ድነትን ለማስገኘት ብቃት የሌላቸው መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ ለእርሱ ድነትን ያስገኘለት በእምነት የተቀበለው የክርስቶስ ጽድቅ ብቻ ነው፡፡
ለጽድቃችን ክርስቶስ በሠራው ሥራ ላይ ብቻ ተደግፈን እስከቆምን ድረስ፣ እንጸናለን፣ እምነታችንም ሳይዋዥቅ እስከ ፍጻሜ ይዘልቃል፡፡ እንግዲህ ይህን ስንል፣ ጽናት ጥርጥር በአጠገቡ ዝር አይልም ማለታችን አይደለም፡፡ ይልቁኑ እያልን ያለነው፣ ጽኑ እምነት ሄዶ ሄዶ በስተመጨረሻው የወንጌልን እውነት አይክድም ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ እውነተኛ የክርስትና እምነት መያዝ ማለት በነገረ-መለኮታችን ግድፈት ጨርሶ አይኖርም ማለታችንም አይደለም፡፡ በነገረ-መለኮታችን እጅግ በርካታ ግድፈቶች ሊኖሩ ይችላሉ ሆኖም ለድርድር በማይቀርቡት የወንጌል እውነታዎች ላይ ግን በታማኝነት እንቆማለን፡፡ በክርስቶስና በክርስቶስ ብቻ የመዳናችንን ማዕከላዊ እውነት እስካልተቀበልን ድረስ፣ ፈጽሞ ልንጸና አንችልም፡፡ ጳውሎስ መጽናትን ከእውነተኛ እምነት አንጻር ከማብራራቱ ባሻገር፣ ስለ ጽናት ከተቀደሰ አኗኗርም አንጻር ማብራሪያ ሰጥቷል፣ ይህም በመልካም ሥራና በሚመሰገኑ ተግባራት መጽናት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁር 12 እና 13 ውስጥ፣ እንዲህ ብሏል፡
ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤
ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። (ፊልጵስዩስ 2፡12-13)
ጳውሎስ በዚህ ስፍራ እየተናገረ ያለው በመልካም ስራ መጽናትን ከድነት ጋር አጣጥሞ ነው፡፡ እንግዲህ፣ በመልካም ሥራ መጽናት ማለት ፍፁም ንፁሃን እንሆናለን ማለት አይደለም፡፡ በዚህ ምድር ሕይወታችን ወደ ፍፅምና አንደርስም፣ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም በከባድ ሁኔታ እንደነቃቀፋለን፡፡ ሆኖም ግን፣ ክርስቶስን በታማኝነት ለመታዘዝ ስንጨክን በመልካም ሥራ እንጸናለን፡፡
አስፈላጊነት
አማኞች የመጽናትን ፍቺ ብቻ በመገንዘብ እንዲቆሙ ጳውሎስ አይፈልግም፤ ድነትን ለማግኘት የመጽናትን አስፈላጊነት በእምነትም በአኗኗርምም በአግባቡ እንዲረዱና በዚያም መረዳት አማካይነት ለመጽናት እንዲበረታቱ ይፈልጋል፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 8 እስከ 11 ጳውሎስ የተናገረውን ንግግር እናድምጥ፡
አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤
እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። (ፊልጵስዩስ 3፡8-11)
በቀላሉ ስናስቀምጠው፣ በእውነተኛ እምነት መጽናት ካቃተን፣ በክርስቶስ ሆነን አንገኝም፣ ስለዚህ ወደ ዘላለም ክብር የሚገባውን የትንሣኤ ሕይወት አንቀበልም፡፡ በሌላ አባባል፣ በእምት መጽናት ለፍፃሜ ድነታችን እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
በተመሳሳይም፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁር 14 እስከ 16፣ ስለ ተቀደስ አኗኗር የሚከተለውን ማሳሰቢያ ይሰጣል፡
በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤
በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። (ፊልጵስዩስ 2፡14-16)
ማንጎራጎርንና ክፉ ንግግርን በማስወገድ፣ ማለትም፣ በተቀደሰ አኗኗር በመኖር፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች ነቀፋ የሌለባቸው ንፁሐን ይሆናሉ፣ ስለዚህም ጳውሎስ በአገልግሎቱ የሚመካበትን ምክንያት ያገኛል፡፡ መጽናት ከተሳናቸው ግን፣ የእግዚአብሔር ልጆች አለመሆናቸውን ገለፁ ማለት ነው፡፡ ያም ማለት፣ በክርስቶስ በእውነት አልታመኑም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በመጨረሻው ቀን አይድኑም ማለት ነው፡፡ ለእኛም ነገሩ እንዲሁ እውነትነት አለው፡፡ በተቀደሰ አኗኗር ካልጸናን፣ የማናምን መሆናችንን እያረጋገጥን ነው ማለት ነው ስለዚህ ካላመንን አንድንም፡፡
ለአብዛኞቻችን፣ ጳውሎስ ስለ መጽናት የሰጠው ማብራሪያና ስለ አስፈላጊነቱ የሰጠው ትምህርት ተስፋ አስቆራጭ እንዲያውም በጣም ጭካኔ ያለበት ይመስለናል፡፡ ሆኖም የጳውሎስ አስተምህሮ፣ የሚያበረታታ ሦስተኛም ገጽታ አለው፡፡ ይህም፣ የመጽናት ማረጋገጫ ነው፡፡ ከመጽናት አንፃር፣ ጳውሎስ ስለ መጽናት ያስተማራቸው ትምህርቶች ለአማኞች የአማኞች ፈተናዎች ሳይሆኑ መጽናኛዎች ናቸው፡፡
ማረጋገጫ
እውነተኛ አማኞች በእምነትም ሆነ በተቀደሰ አኗኗር በእርግጠኝነት እንደሚጸኑ፣ ስለዚህም ድነታችን የተረጋገጠ መሆኑን ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ያረጋግጥላቸዋል፡፡ እንዲሁም፣ በሐሰተኛ መንገድ አማኝ ነን ያሉት ደግሞ፣ አይጸኑም፡፡ እነዚህም ሰዎች አስቀድሞውኑ እውነተኛ የመዳን እምነት ያልነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ግን፣ ያጸናቸው ዘንድ በውስጣቸው የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ አላቸው፡፡ በፊልጵስስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 6 ጳውሎስ የተናገረውን እናድምጥ፡
በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ (ፊልጵስዩስ 1፡6)
የፊልጵስዩስን ሰዎች የማዳኑን ስራ የጀመረው እግዚአብሔር ከሆነ፣ የፊልጵስዩስን ሰዎች የማዳኑን ስራ ወደ ፍፃሜ እንደሚያመጣው ጳውሎስ እርግጠኛ ነው፡፡ ማናቸውም እንዲጠፉ አይፈቅድም፣ ይልቁኑ በእውነት ያመኑት እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ እንዲጸኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ የጳውሎስ ልበ ሙሉነት የእኛም ሊሆን ይችላል፡፡ በእውነት ካመንን፣ ከእምነት ወይም ከጸጋ የምንወድቅበት ምንም መንገድ የለም፡፡
ጳውሎስ ይህንን ሃሳብ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 13 ውስጥ አስረግጦ ይናገርበታል፡
ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤
ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። (ፊልጵስዩስ 2፡12-13 )
ሊኖረን ሚገባው ፍርሃት በስተመጨረሻው ከጸጋ እንደምንጎድል በማሰብ የምንጨነቅበት አይነት ሳይሆን፣ እርሱ የምናስበውን እንድናስብና እንድናደርግ ለማስቻል ሉዓላዊው እግዚአብሔር በውስጣችን እየሠራ መሆኑን ስናውቅ የሚገጥመን አዕምሮን የሚያልፍ አድናቆት ነው፡፡ ለበጎ ዓላማው ልባችንን እና አዕምሯችንን ይቆጣጠራል፣ ያም ጽናታችንንም ያካትታል፣ ስለዚህ እስከ ፍጻሜ ጸንተን ላንቆም የምንችልበት ምንም መንገድ የለም፡፡
የመጽናት ልቡና
የመጽናትን ባህርይ ከመረመርን፣ አሁን ደግሞ አማኞች ገንዘባቸው ሊያደርጉት ስለሚገባው የመጽናት ልቡና ወደምንነጋገርበት እርከን እንሸጋገራለን፡፡ በውይይታችንም፣ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ጳውሎስ አጽንኦት የሰጠባቸውን ሦስት የልቡና ገፅታዎች ላይ እናተኩራለን፡፡ እነርሱም፣ ትህትና፣ ቀና አሳቢነት እና ደስታ ናቸው፡፡ አስቀድመን ልቡናችን በትኅትና የተቃኘ ስለመሆኑ ጳውሎስ ያቀረበውን ሃሳብ እንቃኝ፡፡
ትኅትና
ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን እንደተሰጠው ሐዋርያነቱ፣ ጨካኝ ሊሆን የሚችልባቸው እድሎች ነበሩት፡፡ እግዚአብሔር ጳውሎስን በልዕለ-መለኮታዊነቱ መሪ አድርጎ አሰልጥኖታል፤ ወንጌልን ለአህዛብ ያደርስ ዘንድ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ጳውሎስን መርጦታል፤ በእርሱም አማካይነት በርካታ ተዓምራትን ሠርቷል፡፡ በመላው ዓለም በሚገኙ በርካታ አብያተክርስቲያናት ውስጥ ጳውሎስ የጀግና ከበሬታ ይሰጠዋል፡፡
እናም፣ በእስር ላይ መከራ ሲቀበል፣ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሊያስብ ይችላል፣ “ከዚህ ሁሉ ሕዝብ መሃል ይህ ሁሉ ነገር በእኔ ላይ እንዲደርስ እግዚአብሔር ለምን ፈቀደ? ለእርሱ ታማኝ ነበርኩ ነኝም፣ እርሱ ግን ሊባርከኝ አልወደደም! እኔ የሚገባኝ የተሻለ ነገር ነበር!”እውነታው ግን፣ በእግዚአብሔር ፊት ትኁት ሊሆንበት የሚገባ በርካታ ምክንያት እንዳለ ጳውሎስ ያውቃል፡፡ ይህንን እውነታ በመቀበል፣ በእግዚአብሔር እጅ ለመታነፅ ደግሞም የሚያልፍበትን መከራ በጽናት ለመወጣት ራሱን ዝግጁ አደረገ፡፡
በዚህ ረገድ፣ ጳውሎስ የራሱን ልቡና የቃኘው በክርስቶስ ልቡና መሠረት ሲሆን፣ እርሱም የእግዚአብሔርን በረከት ለመቀበልና ስለ እኛም ሲል ፈቅዶ ራሱን ትኁት አደረገ፡፡ እንዲያውም፣ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁር 6 እስከ 11 በጻፈውና ትኁት መሆን እንደሚገባ ማሳሰቢያ በሰጠበት ክፍል ውስጥ ከጠቀሰው ታዋቂ “ክርስቶሳዊ ዝማሬ” ጋር ይጣጣማል፡፡
አንዳንድ ምሁራን እነዚህ ጥቅሶች ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች መልእክቱን ከመጻፉ አስቀድሞም በቤተክርስቲያን ውስጥ ዘመር የነበረ ዝማሬን የሚያሳዩ ናቸው የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ጳውሎስ እነዚህን ጥቅሶች የጻፈው በተለይ ለዚህ ወቅት ሳይሆን እንደማይቀር ይጠረጥራሉ፡፡ ምንጫቸው ምንም ይሁን ምን፣ የጥቅሶቹ ትርጓሜ እጅግ ግልፅ ነው፡ ኢየሱስ ትኁት ነው እኛም የእርሱን ፈለግ ልንከተል ይገባናል፡፡
ይህ ምንባብ ክርስቶስን በሦስት እርከኖች ይገልጸዋል፡ ቅድመ ትስጉቱ፣ መዋረዱና መክበሩ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሚናገረው ሥጋ ከመሆኑ አስቀድሞ ስለነበረው ሁኔታ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር ፍፁም አንድ፣ በኃይልና በክብርም እኩል የሆነ እግዚአብሔር ወልድ ነበረ፡፡ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 6 የክርስቶስን ቅድመ ትስጉት እንዲህ በማለት ገልፆታል፡
እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ (ፊልጵስዩስ 2፡6)
ይህ ጥቅስ ስለ ክርስቶስ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ይነግረናል፡፡ በመጀመሪያ፣ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ፣ ክርስቶስ ከበረ ነበር፡፡ ወይም ጳውሎስ እንዳስቀመጠው፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ማንት ወይም መልክ ነበረው፡፡ ጳውሎስ የተጠቀመበት isos (i;soj) የተሰኘው የግሪኩ ቃል፣ በጥቅሉ የአንድን ሰው ውጫዊ ገጽታ የሚያመለክት ነው፡፡ ጳውሎስ ሊያሳይ የፈለገው ነጥም ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ተገልጧል የሚለውን ነው፡፡
እንግዲህ፣ ጳውሎስ እያለ ያለው ክርስቶስ ቁርጥ እግዚአብሔር አብን ነው አይደለም፡፡ ይልቁኑ፣ የእርሱ መገለጥ የክርስቶስን አምላክነት ለሚያረጋግጠው እውነታ ምስክር መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡ በመሰረቱ፣ እግዚአብሔር ለሌሎች ለማናቸውም የመለኮት ባህርይ ተካፋይነትን አልሰጠም፡፡
ሁለተኛ፣ ክርስቶስ ትኁት እንደነበረ ጳውሎስ አመልክቷል፡፡ ይህንን ትኅታናውን በይፋ ከማሳየቱም አስቀድሞ፣ ሌላ ቅርፅ ወይም ማንነት ለመያዝ ፈቃደኛ በመሆን እንዲታወቅ አድርጓል፡፡ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁር 6 ውስጥ በግልጽ እንዲህ አስቀምጦታል፡፡
እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ (ፊልጵስዩስ 2፡6)
በዚህ ስፍራ ጳውሎስ፣ የክርስቶስን ከእግዚአብሔር ጋር “መስተካከል” ወይም “አንድነት” ለመጥቀስ isos የተሰኘውን ቃል ነው የተጠቀመው ትርጓሜውም የክርስቶስ “ማንነት” ወይም “የሚታየው ክብሩ” በእግዚአብሔር አብ እንደተገለጠው ዓይነት ክብር ነው፣ ክርስቶስ ግን ይህንን ማንት አብን ደስ ለማሰኘት ሲል ለቀቀው የሚል ነው፡፡
ቀጥሎ ደግሞ ጳውሎስ፣ የክርስቶስን ውርደት ይገልጻል፣ ይህም በምድር ዘመኑ ያሳለፈው ሕይወት ማለትም በማርያም ማኅፀን ከተፀነሰበት ጊዜ አንስቶ፣ በመስቀል ላይ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ መዋረድ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 7 እና 8 ውስጥ የተናገረውን እናድምጥ፡
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። (ፊልጵስዩስ 2፡7-8)
ክርስቶስ ከትስጉቱ በፊት ስለነበረው ማንነቱ ከተናገራቸው ቃላት በተጓዳኝ፣ እነዚህ ጥቅሶች ደግሞ ክርስቶስ በመዋረዱ ወራት ስለነበረው ማንነት ቢያንስ ስለ ሁለት ነገሮች ይነግሩናል፡፡ በመጀመሪያ፣ የክርስቶስ መዋረድ አሳፋሪ ነበር፡፡ ያም፣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ በሰው ምሳሌ ለመገኘት ሲል መለኮታዊ ክብሩን መተዉ ነው፡፡ እንደገና ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ውጫዊ መልኩን መለወጡን ለማመልከት morphē የተሰኘውን የግሪክ ቃል ተጠቅሟል፣ ማለትም እርሱ ከዚያ በኋላ መለኮታዊ ክብሩን አላሳየም፣ ይልቁኑ በግልጽ የሚታየውን የሰብዓዊ ማንነት መልክ ያዘ፡፡
አሁን እንግዲህ፣ ልክ የክርስቶስ መለኮታዊ ማንነት እርሱ እውነተኛና ፍፁም መለኮት እንደሆነ የመግለፁን ያህል፣ የእርሱ ሰብዓዊ ማንነትም እርሱ በእውነትና በፍፁም ሰው እንደነበር ያመለክታል፡፡ ሆኖም ሰው በመሆኑ፣ ክርስቶስ መለኮታዊ የማንነቱ መገለጫዎችን ወዲያ ጣላቸው ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ግን በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ይልቁኑ በፍፁም መለኮትነቱ ላይ ፍጹም ሰውነትን ያዘ ማለት ነው፣ ስለዚህም እርሱ ፍፁም ሰው ፍፁምም አምላክ ነው ብሎ በትክክል መናገር ይቻላል፡፡
ሁለተኛ፣ ፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 7 እና 8 ክርስቶስ ትኁት እንደነበር ያረጋግጣል፡፡ ልክ በቅድመ ትስጉቱ የነበረውን ክብር ለመልቀቅ እንደፈቀደ ሁሉ፣ በመዋረዱም ዘመን ያንን ማንነቱን በትክክል ለቅቆታል፡፡ እንዲያውም፣ ትኅትናው እጅግ ጥልቅ ስለነበር በተራ ሰብዓዊ ፍጡራን ለመገደል ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡
በመጨረሻም፣ ጳውሎስ ክርስቶስን በክብሩ ዘመን ይገልጠዋል፡፡ ይህም ዘመን ከሞት ከመነሣቱ አንስቶ ወደ ሰማይ እስካረገበትና አሁንም ፍጥረተ ዓለሙን ሁሉ በመግዛት ላይ ያለበትን ዘመን ያካትታል፡፡ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ መክበር የጻፈው በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 9 እስከ 11 ባለው ክፍል ውስጥ ሲሆን አገላለጡም እንዲህ ይነበባል፡
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤
ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥
መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። (ፊልጵስዩስ 2፡9-11)
እንደገናም ጳውሎስ፣ በዚህ እርከን ላይ ክርስቶስን ሲገልፀው ቢያንስ ሁለት እጅግ ወሳኝ ነገሮችን አመልክቷል፡፡ በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ የቀደመውን ክብሩን ማለትም የፍጥረት ሁሉ ገዢ፣ ፍጥረት ሁሉ ለእርሱ የሚገዛለትና የሚያመልከው ይሆን ዘንድ እጅግ ከፍ ያለውን ክብሩን መልሶ ያዘ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ በዚህ የከበረ ማንነቱ፣ በፍጥረተ ዓለሙ ላይ ሉዓላዊ ሆኖ ሳለ እንኳን፣ ትኁት መሆንን መረጠ፡፡ እንዲያውም፣ የፍጥረታት ገዢነቱ ራሱን ለማክበር ሳይሆን ለእግዚአብሔር አብ ክብርን ለማምጣት ነበር፡፡
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መልእክት፣ እነዚህን ሃሳቦች የሚያቀርበው አማኞች የክርስቶስን ፈለግ እንዲከተሉ ስለሚፈልግ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ይህንን የመሰለ አስከፊ ውርደት ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆነ፣ የእርሱም አገልጋዮች ያለ ጥርጥር እንደ እርሱ ትኁታን ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ትኅትናው ክርስቶስን በመከራውና በሞቱ እንዲጸና ካደረገው፣ እኛንም ትኁት መሆን እንድንጸና ያግዘናል፡፡ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 2 እስከ 4 በሰጠው መመሪያ ውስጥ ያስቀመጠውም ነጥብ በትክክል ይህንን የሚያመለክት ነው፡
በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤
እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። (ፊልጵስዩስ 2፡2-4)
ትኅትና በተቀደሰ ሕይወትና በእምነት ጸንተን እንድንኖር ያስችለናል፡፡ በአንድ ጎን፣ አንድ ልብ እንዲኖረን፣ አንድ እንድንሆን፣ ሌሎችን እንድንወድድና እንድናከብር እና ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት እንድንተጋ ያስችለናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ያለንበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝ ቢሆንም፣ መከራና ስደት ቢደርስብንም፣ አልፎም ብንሰዋም ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆንና እርሱን ማክበር እንደሚገባን ያስታውሰናል፡፡
ቀና አሳቢነት
በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚገለጥ ትኅትና የጽናት መንገድ መሆኑን በማመልከት ከማበረታታት ባሻገር፣ ጳውሎስ ቀና አሳቢነት በሚኖረወ ፋይዳ ላይ አፅንኦት ይሰጣል፣ ያም፣ ሕይወትን በአዎንታዊና ተስፋን በተሞላ መንገድ መመልከት ነው፡፡ በዘመነኛው ዓለም፣ ሰዎች ቀና አሳቢነትን የሞኛሞኞች ከንቱ ልፋትና ከገሃዱ ዓለም ጋር የማይጣጣም፣ እንዲያው ዝም ብሎ ነገሮች እንደሚታዩት ሳይሆን ደህና ናቸው ብሎ ማስመሰል ነው ሲባል መስማት እንግዳ አይደለም፡፡ ጳውሎስ የሚቅሰው ቀና አሳቢነት ግን ይህን መሳዩን አይደለም፡፡ የእርሱ ቀና አሳቢነት እውነትን ያለወ ነው፡፡ በሕይወት ውስጥ የሚገጥሙትን ክፉ ነገሮች ቸል አላላቸውም፣ እንዲያውም እርሱ ራሱ አበሳውን እያየባቸው ነው፡፡ የጳውሎስ ቀና አሳቢነት ከመሠረቱ፣ በሕይወት ውስጥ በሚገጥሙ እውነተኛ ክፉ ነገሮች ላይ ከማትኮር ይልቅ በሕይወት ውስጥ በሚገጥሙ መልካም ነገሮች ማትኮርን ዓላማ ያደረገ ቁርጥ ውሳኔን ያነገበ ነው፡፡ ይህም የተገኘው በዚህ በምንነፐርበት ዓለም በእግዚአብሔር መግቦትና በረከት ደግሞም በወደፊቱ ቤዛነቱና እግዚአብሔር ወደፊት በሚሰጠን ብድራት ላይ ካለ ጽኑ እምነት ነው፡፡
ለምሳሌ፣ በእስር ላይ መከራ ሲቀበል፣ ወንጌልን በእውነተኛ ልብና መንፈስ በማያገለግሉ አገልጋዮች ሲፈተን፣ ምንም እንኳን ሰባኪዎቹ የነበራቸው ተነሳስቶ ክፉ ቢሆንም፣ በዚያም ቢሆን ክርስቶስ በመሰበኩ በሚገኘው በረከት ላይ ያተኩር ነበር፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 17 እና 18 የጻፈውን እናድምጥ፡
እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ።
ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። (ፊልጵስዩስ 1፡17-18)
የጳውሎስ ስሜታዊ ሁኔታ የተወሳሰበ ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ መከራ እየተቀበለ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ በክፉ ነገሮች ላይ ከማትኮር ይልቅ በበጎ ነገሮች ላይ ለማትኮር ውሳኔ አድርጓል፡፡ ይህም ምርጫው በእስር ቤት ውስጥ የነበረበትን መከራ በጽናት እንዲያልፍ ደግሞም በእነዚህ ሰባኪዎች እየደረሰባት ያለውን እንግልት እንዲቋቋም አስችሎታል፡፡ እናም ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 6 እስከ 8 በፊልጵስዩስ ለምትገኘው ቤተክርስቲያን የሰጠው ምክር ከዚህ አስተሳሰብ ጋር ይጣጣማል፡፡ በዚህ ስፍራ ያሰፈረውን እናድምጥ፡
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።
አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ (ፊልጵስዩስ 4፡6-8)
ቀና ማሰብና ጭንቀትንና ተስፋ መቁረጥን መፋለም ማለት፣ ልባችንንና አዕምሯችንን እንዲጠብቅልን ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ መጮህ ማለት ነው፡፡ ደግሞም ለጽናት እጅግ ወሳኝ መንገድ ነው፡፡
ደስታ
በመጨረሻም፣ ከትኅትናና ከቀና አሳቢነት በተጨማሪ ከክርሰቲያናዊ መጽናት አንፃር የደስተኝነት ልቡና ስለሚኖረው ትልቅ ፋይዳ ጳውሎስ ያስተምራል፡፡ በአንድ ወገን፣ ጳውሎስ ራሱ በሚያልፍበት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ደስ በመሰኘት ላይ አተኩሯል፡፡ በእርሱም ምሳሌነት መሠረት፣ በፊልጵስዩስ የሚኖሩ አማኞችም ያንኑ እንዲደርጉ ያበረታታል፡፡ ለምሳሌ፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ከቁር 18 እስከ 20 ድረስ ጳውሎስ ስለ ደስታው እንዲህ ጽፏል፡
ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።
ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥
ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል። (ፊልጵስዩስ 1፡18-20)
ጳውሎስ የሞቱ ነገር አይቀሬ እንደሆነ ስላወቀ ፈርቷል፡፡ ሆኖም፣ በሞቱ አሉታዊ ገጽታ ላይ ከማትኮር ይልቅ፣ ሞቱ ሊያስገኝ በሚችለው አዎንታዊ ውጤት ላይ ማትኮርን ምርጫው አድርጓል፣ ስለዚህ እርሱ ቀና አሳቢ ነበር፡፡ በውጤቱም፣ ደስ መሰኘት ችሏል፡፡
በዚህ ረገድ፣ የጳውሎስ ደስታ ስቃይንና መከራን በድርቅና የመካድ ጉዳ ወይም በድንገት የገነፈለ የደስተኝነት ስሜትም እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ በተቃራኒው ግን፣ እንደተመለከትነው በጳውሎስ ውስጥ የብዙ ሃዘንና የመከራም ስሜቶች ተደበላልቀው ነበር፡፡ ሆኖም ጳውሎስ፣ ከመከራው ባሻገር በሕይወት ውስጥ በሚገጥሙ መልካም ነገሮች ላይ ማትኮርና በእነርሱም ደስ መሰኘት ችሎ ነበር፡፡ ክርስቶስን ያለፍርሃት በሚቀበለው ሞቱ ሊያከብረውና በእርሱም ሊረካ እንዲያውም የክርስቶስ ክብር ተካፋይ ለመሆን ሲል በክርስቶስ ሞት ቢካፈል ደስ ይለው ነበር፡፡ ይህም እርካታው ደስታን ፈጠረለት፡፡ ጳውሎስ የተሰማው ባዶ ደስታ ብቻ ሳይሆን፣ እውነተኛ ደስታ ነበር፡፡ ይህም ደስታ ወደፊት እንዲገሰግስና መከራውም ዓላማ ያለው እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ጳውሎስ በተጨማሪም በፊልጵስዩስ የሚኖሩ ወዳጆቹም ይህንኑ አስተሳሰብ እንዲላበሱና ደስታቸውም የመጽናት አቅም እንዲሆናቸውም ያበረታታቸዋል፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 4 እስከ 6 የሰጠውን ምክር እናድምጥ፡
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ።
ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ።
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። (ፊልጵስዩስ 4፡4-6)
በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሊረዳቸውም ሆነ፣ እንደ ንጉሥነቱ የሰላም አገዛዙን በመላው ዓለም ሊያሰፍን ደግመኛ የሚመለስ ጌታ ቅርብ በመሆኑ ደስተኛ እንዲሆኑ ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ሰዎች ያበረታታቸዋል፡፡ በሁለቱም ምክንያቶች፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች ጭንቀትን እንዲያስወግዱ ከማድረግ አንፃር ደስታ ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋል ያስችላቸዋልም፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ጌታ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ እንዲጸኑ ያዘጋጃቸዋል፡፡
በትህትና፣ በቀና አሳቢነት እና በደስታ ላይ በማትኮር ከጳውሎስ ልቡና ጋር ልቡናችንን አጣጥመን፣ በጭንቀትና በተስፋ መቁረጥ ላይ ራሳችንን ብርቱዎች አድርገን እናዘጋጃለን፡፡ መከራ የመምጣቱ ነገር፣ እኛም በመከራ ውስጥ ማለፋችን፣ እንዲውያም አንዳንድ ጊዜ የከፋ ሊሆን የመቻሉ ነገር አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ያ በሚሆንበት ወቅት፣ የጳውሎስን ተምሳሊትና ምክር ማስታወስ ይገባናል፡፡ መከራችንንም በትኁት መንፈስ ማለዘብ ደግሞም አሁን በምንኖርበትም ሆነ በወደፊቱ ሕይወታችን ስለሚገጥሙን መልካም ነገሮች በማሰብ በተስፋ ልንጸና ይገባናል፡፡ በምናልፍበት ሁኔታ ውስጥ በሚገጥሙን ፈተናዎች ደስ በመሰኘት ችግሮቻችንን ድል ልንነሳና አሁንም በደስታ ልናስተናግዳቸው እንደሚገባ ልናውቅ ያስፈልገናል፡፡ በእነዚህ መንገዶች እግዚአብሔር እርዳታ ልንበረታና ልንጸና ያስፈልገናል፡፡
የመጽናት አገልግሎት
የጽናትን ባህርይና ልቡና ከመረመርን፣ አሁን ደግሞ ወደ ሦስተኛው ጉዳይ እንሸጋገራለን፡፡ ያም የቤተክርስቲያን የመጽናት አገልግሎት ሲሆን፣ ይህም የሚገለጸው አንዳችን ለሌላችን በምናከናውነው ተግባር ነው፡፡
የፊልጵስዩስ ሰዎች በአገልግሎቱ ልዩ ልዩ እርከኖች ላይ እንዳገዙት ጳውሎስ እውቅና ይሰጣል፣ ይህም አሁን ያለበትን እስር ይጨምራል፡፡ በተለያዩ በርካታ ጊዜያት በገንዘብም በስሜትም ደግፈውታል፡፡ እንዲያውም በእስር ላይ ሳለ ያገለግለው ዘንድ አፍሮዲጡን ልከውለታል፡፡ እነርሱ ለጳውሎስ የሰጡትን አገልግሎት በቁሳቁስ ድጋፍ፣ በማበረታታት፣ እና በአካል አብሮ በመገኘት በሚሉት ቃላት ጠቅለል አድርገን ልናቀርበው እንችላለን፡፡ በእነዚህ በእያንዳንዳቸው መንገዶች የፊልጵስዩስ ሰዎች የጳውሎስን መንፈስ ደግፈውታል ደግሞም ይበልጥ እንዲጸና ጉልበት ሆነውታል፡፡
ለምሳሌ፣ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 4 ቁር 13 እና 14 ጳውሎስ ያሰፈራቸውን ልብ የሚነኩ ቃላት እናድምጥ፡
ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።
ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ።
(ፊልጵስዩስ 4፡13-14)
በአንዳንድ መንገዶች፣ እነዚህ ቀላል ቁጥሮች የፊልጵስዩስ ሰዎች ለጳውሎስ የሰጡትን አገልግሎት ልብ እና እርሱም ስለእነርሱ የሚሰማውን ስሜት ያንጸባርቃሉ፡፡
አፍሮዲጡ የፊልጵስዩስን ሰዎች ስጦታ ለጳውሎስ ከማድረሱ አስቀድሞ፣ ሐዋርያው የሚጸናበትን ጉልበት ያገኘው ከጌታ ከራሱ ነበር፡፡ ከሌሎች ግን እምብዛም የሞራል ድጋፍ አያገኝም ነበር፣ ስለዚህምቀና አሳቢነቱና ደስታው ደብዝዞበት ነበር፡፡ ጽኑ ነበር፣ ግን እጅግ ከባድ ሥራ ነበር፡፡ የፊልጵስዩስ ሰዎች የላኩለት ስጦታ ግንመከራውን ቀለል የሚያደርግለትን ቁሳዊ ድጋፍ አስገኘለት፣ ስለዚህም የመጽናቱ ነገር ቀለል አለለት፡፡ ለእርሱ ያላቸውን ሸክም፣ በስጦታቸውና አፍሮዲጡን በመላክ ገልጸዋል፣ ያም ቀና አስተሳሰቡና ደስታው እንዲያንሰራራ አግዞታል፡፡ በእርግጥም፣ የአፍሮዲጡ በአካል አብሮት መሆን የጳውሎስን ምድራዊ ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ ከቀድሞው በበለጠ እንዲጸና የሚያግዘውን ባልደረባነትና ወዳጅነትንም አስገኝቶለታል፡፡
ስለዚህም፣ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ከልብ የሆነ ምሥጋናውን ሲያቀርብ በችግሬ ተካፋይ በመሆናችሁ መልካም አደረጋችሁ በማለት ይገልጸዋል፡፡ ጳውሎስ በገሃድና በእውነት አገልግሎታቸውን ያደንቃል፡፡ ስለዚህም እነርሱን ወዳጆቼ ብሎ መጥራት የሚችልበትን መጽናናትና ደስታ አስገኝቶለታል፣ እናም እምነቱን ይበልጥ በማጠንከር ለመጽናት ደግሞም ክርስቶስን በሚያስከብር መንገድ ለመኖር ብርታት ሆኖለታል፡፡
እናም ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የሚሰጠው አገልግሎት በመከራዎቻቸው ወቅት እንዲጸኑ ማገዝን ዒላማ እንዲያደርግ አቅዷል፡፡ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 3 እና 4 ውስጥ እንደምናነብበውም፣ ለእነርሱ ይጸልይላቸዋል፡፡ እንዴት መጽናት እንዳለባቸው ለማስተማርም ደብዳቤ ጽፎላቸዋል፡፡ ከዚህም በበለጠ፣ አፍሮዲጡ ያገለግላቸው ዘንድ፣ ምናልባትም የቤተክርስቲያኒቱ መሪ እንዲሆን መልሶ ልኮላቸዋል፡፡
በዘመናችን ቤተክርስቲያን፣ የፊልጵስዩስ ሰዎች የማቴሪያል ድጋፍ በማድረግ ለጳውሎስ ከሰጡት አገልግሎት ብዙ እንማራለን፡፡ በመላው ዓለም የማቴሪያል ድጋፍ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ አንዳንዶቹም በጣም ድሆች ከመሆናቸው የተነሳ የአልባሳትና የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላት የዘወትር ፈተናቸው ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በምድር ላይ በሚኖሩ ክፉ ሰዎች የሚሰቃዩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ለባርነት የተሸጡና ብርቱ እንግልት የሚደርስባቸው ናቸው፡፡ በእርግጥም፣ በመላው ዓለም በሁሉም ስፍራ በሚገኙ ክርስቲያኖች መካከል፣ እጅግ ገሃድ የሆኑ ግን አምብዛም ግነት የማይታይባቸው የማቴሪያል ድጋፍ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለእነዚህ አማኞች ድጋፍ ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ፣ የማቴሪያል ፍላጎቶቻቸውን በማሟላት ተስፋቸው እንዲለመልምና እንዲጸኑ ማገዝ ነው፡፡
የፊልጵስዩስ ሰዎች በፍቅራቸውና በማበረታቻቸው ለጳውሎስ ከሰጡት አገልግሎት እጅግ ብዙ የምንማራቸወ ነገሮች አሉ፡፡ ለጳውሎስ ገንዘብ ብቻ አይደለም የላኩት፤ ፍቅራቸውንም ጭምር ነው፡፡ ጳውሎስ በአፍሮዲጡ አማካይነት፣ ስለ እርሱ እንደሚያስቡ እና በእርሱ ልብ ውስጥ እነርሱ እንዳሉ ሁሉ በእነርሱም ልብ ውስጥ እርሱ እንዳለ እንዲያውቅ አድርገዋል፡፡
የዘመናችን ክርስቲያኖችም የሚያጸና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያበረታቱ ቃላቶችን በመለዋወጥ፣ በስልክ፣ በደብዳቤ ወይም መልእክተኛ በመላክ ወይም በብዙ መንገዶች መበረታታት ይቻላል፡፡ ነጥቡ ምንድን ነው ሰዎች እንደተወደዱ እና እንዳልተረሱ እንዲያውቁ የምናደርግበትን አንድ መንገድ መፈለግ አለብን የሚል ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ከሰዎች ጋር በአካል የምንገናኝበትን ጊዜ መመደብ ይገባናል፣ ያንንም ከእነርሱ ጋር አብሮ በመቀመጥ፣ አጠገባቸው በመሆን፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን በማሟላት ረገድ በማገዝ ማለትም የፊልጵስዩስ ሰዎች አፍሮዲጡን ወደ ጳውሎስ እንደላኩት ዓይነት መደጋገፍ ይቻላል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥም፣ በርካታ ሰዎች ብቸኞች ናቸው፣ ብዙዎችም ጓደኛ ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንዶቹም በጣም ጥቃቅን በሆኑ ነገሮች እንኳን ማለትም ቤትን እንደማጽዳት እና ገበያ እንደመሄድ በመሳሰሉት የሚያግዛቸውን ደግሞም እነርሱንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያግዝላቸውን ይፈልጋሉ፡፡ በአማኞች አጠገብ በአካል መገኘት አንዱ እንዲጸኑ የምናግዝበት መልካም መንገድ ነው፡፡
ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ሰዎች ካገለገለባቸው መንገዶች ሌላም ብዙ የምንማረው ነገር አለ፡፡ በጤናማ አስተምህሮና ተግባራዊ ምክር በመለገስም እንዴት መጽናት እንደሚችሉ ልናስተምራቸው እንችላለን፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ በአንድ ሥልጣን ላይ የምንገኝ ከሆነ፣ ቤተክርስቲያንን በሚያበረታታና በኃላፊነት ስሜት ልንመራ እንችላለን፡፡ ያም ማለት በቃልና በኑሮ ምሳሌ በመሆን መከራ የእግዚአብሔር መንገድ እንደሆነ ደግሞም አይቀሬ መሆኑን በሚያስረዳ መንገድ ማለት ነው፡፡ ማንም እንሁን ማን፣ የትም እንኑር የት፣ አማኞች በሚያልፉበት ጎዳና ሁሉ የሚጸኑበትን አቅም እንዲሰጣቸው ወደ እግዚአብሔር አዘውትረን መጸለይ ይገባናል፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ ትምህርት የእስትንፋሰ መለኮትነት ሥልጣን ከተሰጣቸው ከጳውሎስ መልእክቶች መካከል ለፊልጵስዩስ ሰዎች የተጻፈውን ተመልክተናል፡፡ በዚያም ውስጥ፣ የደብዳቤውን ታሪካዊና ማኅበራዊ አውድ የሚቃኘውን ዳራ፣ የመልእክቱን አወቃቀርና ይዘት፣ በመጨረሻም መልእክቱ በዘመናችን ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚኖረው ተዛምዶ ተካትተዋል፡፡
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ በክርስትና እምነታችን ጸንተን ልንቆም ስለ ምንችልባቸው መንገዶች ደግሞም በጭንቅና በመከራ ጊዜዎቻችንም እንኳን ሳይቀር በቅዱሱ አምላካችን ፊት በተቀደሰ ሕይወት ስለ መኖር የሚያስተምሩ በርካታ አስደናቂና የዳበሩ እውነቶችን ይዟል፡፡ ለጳውሎስ ትምህርቶች ራሳችንን ስንሰጥ፣ ጽናት ምን ያህል ወሳኝነት እንዳለው እንገነዘባለን እናም ለዚህ አስደናቂ አደራ ራሳችንን ለመስጠት በእጅጉ እንበረታታለን፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ፣ የጳውሎስን ምክር በመከተል በግል ሕይወታችን ስንጸና ደግሞም ሌሎችም እንዲጸኑ ስናግዝ እጅግ ለከበረው ጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብርንና ውዳሴን እናመጣለን፡፡
Continue reading the full transcript