የዘፍጥረት 6:9-11:9ን በመመርመር፣ በኖኅ ዘመን ከታላቁ ጎርፍ በኋላ ሕዝቡን እንዲከተል የሠራውን አቅጣጫ ይገልጻል።
From the transcript
ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡
በዩክሬን አስተምር የነበረበትን አንድ ዘመን አስታውሳለሁ፣ አንድ ቀን ወደምሄድበት ስፍራ ለመድረስ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነበሩኝ ስለዚህ ሜትሮ ለመያዝ ወሰንኩኝ፡፡ ወደ ባቡር ጣቢያው ገስግሼ በመድረስ፣ ደረጃዎቹን ቁልቁል ተንደርድሬ በመውረድ የባቡሩ በር ሊዘጋ ሲል ዘልዬ ገባሁ፡፡ የተሳፈርኩት ባቡር ከተማይቱን ጫፍ እስከጫፍ አቋርጦ የሚዘልቅ ነበር፣ እኔም ትንፋሼ መለስ እስከሚልልኝ ድረስ ከኋላ ቁጭ ብዬ ለጥቂት ደቂቃዎች ዘና አልኩ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግን በታላቅ ድንጋጤ ተዋጥሁ፡፡ ለካስ የተሳፈርኩት ባቡር እኔ በማልፈልገው አቅጣጫ የሚጓዝ ነበር! የሚቀጥለው የሜትሮ ጣቢያ በጣም ሩቅ ስለነበር እዚያ ለመድረስ ዝንተ-ዓለም ይወስዳል፡፡ እኔ ወደ ኋላ ተመልሼ ትክክለኛ አቅጣጫዬን ገና ስይዝ፣ እጅግ በጣም የምዘገይ መሆኑ በጣም ግልፅ ነው፡፡ እኔም፣ “መልካም፣ ይህ ሁኔታ እኔ እንዲገጥመኝ የምፈልገው ሁኔታ ጨርሶ አልነበረም፣ ቢያንስ አሁን ግን ትክክለኛ አቅጣጫዬን ይዣለሁ” ብዬ ለራሴ ነገርኩት፡፡
በአብዛኛው ሕይወታችንም ይህን መሰል ሁኔታ ይገጥመዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ነገሮቻችን ሁሉ ፍፁም አይደሉም፣ ጭራሹንም የማይቀራረቡበት ጊዜም አለ፡፡ በምንሄድበት ሁሉ በርካታ ችግሮችና ተግዳሮቶች ይገጥሙናል፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ግን፣ በተሳሳተ መንገድ ከመንጎድ ትክክለኛውን አቅጣጫ መያዝ እንደሚሻል ሁላችን እናውቃለን፡፡
ይህንን ትምህርት “ትክክለኛ አቅጣጫ” የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል፡፡ በዚህም ውስጥ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 የሚገኘውንና በኖህ ዘመን ከተከሰተው የጥፋት ውሃ በኋላ እግዚአብሔር ለህዝቡ የዘረጋውን ትክክለኛ አቅጣጫ እንመረምራለን፡፡ በእነዚህ የፍጥተ ዓለም ታሪኮች ውስጥ፣ እስራኤላውያን ሊከተሉት የሚገባቸውን ትክክለኛ አቅጣጫ ሙሴ ያሳያቸዋል፡፡ ምናልባት እነርሱ ሊሄዱበት የሚፈልጉት ዓይነት አቅጣጫ ባይሆንም፣ እግዚአብሔር ወደ ታላቅ በረከት ሊወስዳቸው የዘረጋው ነበር፡፡ ደግሞም ይህ የፍጥረተ ዓለም ታሪክ ክፍል ለክርስቲያኖችም እጅግ ወሳኝ ነው፣ ምክንያቱም እኛም ይህንኑ ተመሳሳይ አቅጣጫ ልንከተል ይገባናልና ነው፡፡
በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ላይ የምናደርገው ጥናት በሦስት ይከፈላል፡ በመጀመሪያ፣ የእነዚህን ምዕራፎች ስነ-ጽሁፋዊ አወቃቀር እንመረምራለን፤ ሁለተኛ፣ ሙሴ እነዚህን እውነቶች ለእስራኤል ለምን እንደጻፈ በመለየት ቀደምት ትርጉማቸውን እንዳስሳለን፤ ሦስተኛ፣ እነዚህን ምዕራፎች ከእኛ ሕይወት ጋር ለማዛመድ አዲስ ኪዳንን እንመለከታለን፡፡ የእነዚህን ምዕራፎች ስነ-ጽሁፋዊ አወቃቀር በመመርመር የትክክለኛ አቅጣጫ ጥናታችንን እንጀምር፡፡
ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ያለው ክፍል ከፍጥረተ ዓለም ታሪክ ትልቁን አንጓ ይይዛል፣ ስለዚህም በበርካታ መንገዶች ውቅር ሊሠራለት ይችላል፡፡ ለእኛ ዓላማ ግን፣ እነዚህን ምዕራፎች በሁለት ዋና ክፍሎች እንከፍላቸዋለን፡፡ የመጀመሪያው አንጓ ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 9 ቁጥር 17 ያለውን ያካትታል፣ “ነፃ የማውጣት ጎርፍ” የሚል ርዕስም ሰጥተነዋል፡፡ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ዘፍጥረት ምዕራፍ 9 ቁጥር 18 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ያለውን ይሸፍናል፣ “አዲስ ሥርዓት” የሚል ርዕስም ሰጥተነዋል፡፡ ከጥፋት ውሃ በኋላ የተከናወኑ ወሳኝ ሁነቶችን ይዳስሳል፣ ደግሞም ከጥፋት ውሃ በኋላ በነበረው ዓለም ዘላቂ የነበረውን መርህም ያስቀምጣል፡፡ የእነዚህን ምዕራፎች ስነ-ጽሁፋዊ ዘይቤ በትክክል ለመገንዘብ፣ ሁለቱንም ዐቢይ ክፍሎች እንመለከታለን፡፡ አስቀድመን ስለ ኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ ሙሴ የጻፈውን ታሪክ አወቃቀር በመመርመር እንጀምር፡፡
ነፃ የማውጣት ጎርፍ
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ተርጓሚዎች የኖህ የጥፋት ውሃ ታሪክ ግልፅ የአፃፃፍ ዘይቤ እንደሚከተል እያስተዋሉ መጥተዋል፡፡ ይህንንም ዘይቤ በበርካታ መንገዶች መግለጥ ቢቻልም እንኳን፣ በዚህ ጥናታችን እነዚህ ምዕራፎች የተመጣጠነ ባለ አምስት እርከን ድራማ እንደሚያዋቅሩ ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
የመጀመሪያ ቃል ኪዳን
የዚህ ትረካ የመጀመሪያ ክፍል የሚገኘው በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ 22 ባለው ውስጥ ሲሆን፣ ይህንንም ከኖህ ጋር የተደረገ “የመጀመሪያው መለኮታዊ ቃል ኪዳን” ብለነዋል፡፡ በዚህ የትረካ ክፍል ውስጥ፣ ኖህ መራራ በሆነው ዓለም ጻድቅ የነበረ ሰው መሆኑን ሙሴ ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ዘር ለምን እንደሚያጠፋ ለኖህ ይነግረዋል ይገልጥለታልም፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 13 እንዲህ እናነብባለን፡፡
እግዚአብሔርም ኖኅን አለው፦ የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። (ዘፍጥረት 6፡13)
ሆኖም፣ የዚህ ትረካ የመጀመሪያ ክፍል እግዚአብሔር አንድን ሰውና ቤተሰቡን ያም ጻድቁን ኖህን በማዳን ነገሩን ሁሉ እንደገና የመጀመር ዕቅድ እንዳለው ይነግረናል፡፡ ያንን ያደረገበትን ዓላማ ለኖህ ለማረጋገጥ፣ እግዚአብሔር ከኖህ ጋር የመጀመሪያውን ቃል ኪዳን ይገባል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 17 እስከ 18፣ እግዚአብሔር ለኖህ የተናገረውን እንዲህ እናነብባለን፡
እኔም እነሆ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል።
ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አቆማለሁ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ። (ዘፍጥረት 6፡17-18)
በጥፋት ውሃ ትረካ ጅማሬ ላይ፣ ከሚመጣው የጥፋት ውሃ ኖህንና ቤተሰቡን እንደሚያድን እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን በመሃላ ያፀናል፡፡ ቃል ኪዳኑ የኖህን መዳን ያረጋግጣል፣ እርሱም ከጥፋት ውሃ በኋላ የሚመጣው አዲስ የሰው ዘር ራስ ይሆናል፡፡
የጥፋት ውሃ ታሪክ እግዚአብሔር ከኖህ ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ላይ በማትኮር እንደሚጀምር ከተመለከትን፣ የመጀመሪያውን ክፍል ሚዛን ወደሚያስጠብቀው ሁለተኛ ክፍል መዘዋወር ይገባናል፣ ይህም ምዕራፍ 8 ከቁጥር 20 እስከ ምዕራፍ 9 ቁጥር 17 የሚገኘውና ከኖህ ጋር የጸናው መለኮታዊ ቃል ኪዳን ብለን የሰየምነው ነው፡፡
የጸናው ኪዳን
ርዕሳችን እንደሚያመለክተን፣ በዚህ ምንባብ እግዚአብሔር ከጥፋት ውሃ በኋላ እንደገና ወደ ኖህ በመምጣት ከእርሱ ጋር ሌላ ቃል ኪዳን ያደርጋል፡፡ በዓለም ላይ አዲስን ስርዓት ለሰው ዘር የመዘርጋትን ዕድል ለመስጠት እግዚአብሔር ይወስናል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 8 ቁጥር 22 እንዲህ እናነብባለን፡
በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም። (ዘፍጥረት 8፡22)
የዚህን አዲስ ስርዓት እርግጠኝነት ለማፅናት፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 9 ከቁጥር 11 እስከ 15 ውስጥ በሚገኘው የጥፋት ውሃ ትረካ ማብቂያ ላይ እግዚአብሔር ለኖህ አዲስ ቃል ኪዳን ይገባለታል፡፡
ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።
እግዚአብሔርም አለ፦ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው
ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል።
በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች
በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። (ዘፍጥረት 9፡11-15)
የኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ ታሪክ የሚደመደመው የጥፋት ውሃ ዳግመኛ ምድርን እንደማያጠፋ በተሰጠው የቃል ኪዳን ተስፋ መሆኑን አይተናል፡፡ እግዚአብሔርም ይህንን ቃል ኪዳኑን የማያጥፍ መሆኑን ለማጽናት የቀስተ ደመና ምልክትን አስቀምጧል፡፡ ይህም የቃል ኪዳን ተስፋ ኖህ በፍጥረተ ዓለም ታሪክ ውስጥ እንደነበር በጽኑ ያመለክታል፡፡ እርሱ የቃል ኪዳኑ መካከለኛ ነበር፣ ቃል ኪዳኑም በእርሱ አማካይነት ወደ ቀጣዩ ትውልድ ይዘልቃል፡፡
የዚህን ታሪክ የመክፈቻና የመዝጊያ ክፍል በልቡናችን ይዘን፣ በጥፋት ውሃ ታሪክ ውስጥ የተከናወኑ ውስጣዊ ተግባራትን እንመረምራለን፡፡ መካከለኛው ክፍል ከእግዚአብሔር የመጀመሪያ ቃል ኪዳን ወደ መጨረሻው ቃል ኪዳን በሦስት ዋና እርከኖች ሽግግር ያደርጋል፡፡
ከጥፋት ውሃ ማምለጥ
የዚህ ትረካ ሁለተኛ እርከን የሚገኘው ምዕራፍ 7 ከቁጥር 1 እስከ 16 ባለውና “የኖህ ከጥፋት ውሃ ማምለጥ” ብለን ርዕስ በሰጠነው ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ይህ ክፍል ቀጥተኛነት የሚታይበት ነው፡፡ ኖህ መርከብን ሠርቶ የእንስሳትን ዝርያ ከየወገኑ ሰብስቦ ገባ፣ ጎርፍም ምድርን ይሸፍን ጀመር፣ ሆኖም ኖህና ቤተሰቡ፣ ደግሞም እርሱ የሰበሰባቸው እንስሶች ሁሉ በመርከቡ ውስጥ ያለ ስጋት ነበሩ፡፡
ወደ ደረቁ ምድር መውጣት
የኖህ የጥፋት ውሃ አራተኛ ክፍል ለሁለተኛው እርከን አንፃራዊ የሆነ ድራማዊ ዘገባ ያቀርባል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 8 ከቁጥር 6 እስከ 19 የኖህን ወደ ደረቀው ምድር መውጣት ይገልጣል፡፡ ውሃው መጉደል ሲጀምር፣ ኖህ ከመርከቡ ወጥቶ የሚያርፍበትን ደረቅ ምድር መናፈቅ ጀመረ፡፡ ከጥቂት ጥበቃ በኋላ፣ ደረቁ ምድር ተገለጠ እግዚአብሔርም ኖህን እንዲገባ እንዳዘዘው ሁሉ ከመርከብ እንዲወጣም አዘዘው፡፡
መለኮታዊ መታሰቢያ
አሁን ደግሞ የዚህን ትረካ ማዕከል ወይም የአቅጣጫ ለውጥ የተደረገበትን ነጥብና በዘፍጥረት ምዕራፍ 7 ከቁጥር 17 እስከ ምዕራፍ 8 ቁጥር 5 ድረስ የሚገኘውን እኛም የኖህ “መለኮታዊ መታሰቢያ” ብለን የሰየምነውን እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የሚጀምሩት የጥፋት ውሃ በምድር ላይ የሚገኘውን ሕያው ፍጥረት ሁሉ ማውደም መጀመሩን በመግለጥ ነው፡፡ በዚህ ክፍል ማብቂያ ላይ ግን ጎርፉ መጉደል ይጀምራል፡፡
በዚህ ክፍል ማዕከል ውስጥ እግዚአብሔር ይህንን መዓት የተሞላ የጥፋት ውሃ ለምን እንዲቀልል እንዳደረገ የሚያመለክት ቀላል ግን መሠረተ ፅኑ መግለጫ እናገኛለን፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 8 ቁጥር 1 ውስጥ ሙሴ ያንን የጻፈው በማዕበሉ መሃል ነበር፡
እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊቱን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ አሰበ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አሳለፈ፥ ውኃውም ጎደለ (ዘፍጥረት 8፡1)
እግዚአብሔር በታላቅ ምህረቱ፣ ለኖህና አብረውት ላሉት ሁሉ የገባውን ቃል ኪዳን አልዘነጋም፡፡ በመርከቡ ውስጥ የተሳፈሩትን ሁሉ አሰበ፣ ስለዚህም መዓት የተሞላውን ውሃ ስለ እነርሱ አዘዘ፡፡
የኖህ የጥፋት ውሃ አጭር መግለጫ የታሪኩን ቀደምት ዓላማ ወደ ብርሃን አመጣው፡፡ ሙሴ ስለ ጥፋት ውሃ የጻፈው እንደ ነፃ የማውጣት ውሃ አድርጎ ነው፡፡ ምንም እንኳን በምድር ክፉዎቸ ላይ ፍርድ ቢፈፀምም፣ የሙሴ ዋና ዓላማ እግዚአብሔር በኖህ አማካይነት የሰውን ዘር አስደናቂ በረከት ወዳለባት ዓለም ማምጣት መሆኑን ማሳየት ነበር፡፡
የዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ድረስ ያለውን የመጀመሪያ አንጓ ካየን፣ አሁን ደግሞ ወደ ሁለተኛው ዐቢይ ክፍል መሸጋገር ይገባናል፡፡ ያም በዘፍጥረት ምዕራፍ 9 ቁጥር 18 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 የሚገኘውና አዲስ ሥርዓት የተሰኘው ክፍል ነው፡፡
አዲስ ሥርዓት
ከምዕራፍ 9 እስከ 11 የሚገኘው የሙሴ የአዲስ ሥርዓት ዘገባ በሁለት መሠረታዊ ክፍሎች ይከፈላል፡፡ በአንድ በኩል፣ ዘፍጥረት ምዕራፍ 9 ከቁጥር 18 እስከ ምዕራፍ 10 ቁጥር 32 ያለው ክፍል በኖህ ልጆች ላይ ያተኩራል፡፡ በሌላ በኩል፣ ዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ከቁጥር 1 እስከ 9 ያለው ደግሞ፣ ስለ ባቢሎን ግንብ መፍረስ ያወሳል፡፡ ጅማሬ ላይ እነዚህ ምንባቦች የማይዛመዱ ቢመስሉም፣ ለአዲሱ የዓለም ሥርዓት ወጥ መስመር ለመዘርጋት በአንድነት ይሰለፋሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የሚቀጥለውን የዓለም ታሪክ ማዕከላዊ ገፅታ በይፋ ያመለክታሉ፡፡ አስቀድመን የኖህን ልጆች ታሪክና ለዚህ የዓለም ሥርዓት ገፅታ ምን አስተዋፅዖ እንዳላቸው እንመልከት፡
የኖህ ልጆች
በምዕራፍ 9 እና 10 ሙሴ ስለ ኖህ ልጆች ያቀረበው ዘገባ ርዕስና ሁለት ዐቢይ ክፍሎችን የያዘ ነው፡፡ በምዕራፍ 9 ቁጥር 18 እና 19 ውስጥ ይህ የዘፍጥረት ክፍል በተቀዳሚነት በኖህ ሦስት ልጆች እና በምድር ላይ በመበተናቸው ላይ የሚያጠነጥን ርዕስ ሰጥቶናል፡፡
ከዚህ ርዕስ ጋር በሚጣጣም መንገድም፣ ሙሴ ስለ ኖህ ልጆች ያቀረበው ዘገባ በሁለት ዋና ክፍሎች ይከፈላል፡፡ በመጀመሪያ፣ በምዕራፍ 9 ከቁጥር 20 እስከ 29 ባለው ክፍል ውስጥ የሚገኘው ታሪክ በልጆቹ መካከል ያለውን ልዩነት ይገልጣል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ ምዕራፍ 10 ከቁጥር 1 እስከ 32 ያለው ክፍል የኖህን ልጆች መበተን እና ዝርያዎቹን ያሳየናል፡፡ እነዚህን ክፍሎች በተናጠል መመልከቱ ይጠቅማል፡፡
ምዕራፍ 9 ከቁጥር 20 እስከ 29 ያለው ክፍል ታዋቂና በካም ልጅ በከነዓን ላይ ስለመጣው እርግማን የሚናገረው ነው፡፡ ሙሴ በምዕራፍ 9 ከቁጥር 24 እስከ 27 የጻፈውን አድምጡ፡
ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ።
እንዲህም አለ፦ ከነዓን ርጉም ይሁን ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።
እንዲህም አለ፦ የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን። (ዘፍጥረት 9 ፡ 24-27)
በቀላሉ ስናስቀምጥ፣ ይህ ትረካ በኖህ ዝርያዎች ላይ ወሳኝ የሆነ ልዩነት የተደረገባቸውን ሁነቶች ይዘግባል፡፡ ኖህ የካምን ልጅ፣ ከነዓንን ረገመው፡፡ ከነዓን የወንድሞቹ ሁሉ የበታችና ባሪያ ይሆናል፡፡ ሆኖም፣ ኖህ በሌሎቹ ልጆቹ፣ በሴምና በያፌት ላይ በረከትን ያውጃል፣ ምክንያቱም ለእርሱ ከበሬታን አሳይተዋልና፡፡
ሙሴ ይህንን ታሪክ ከጥፋት ውሃ በኋላ ስለመጣው አዲስ ሥርዓት በሰጠው መግለጫ ውስጥ ያካተተው መላው የሰው ዘር ከሦስቱ የኖህ ልጆች ስለተገኘ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ የተቀመጠው መለያ ከዚያን ዘመን ጀምሮ በሚመጣው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የሚታየውን ሰብዓዊ ግንኙነት ይገልፃል፡፡
ይህ በኖህ ልጆች መካከል ባለ ልዩነት ላይ የተገለጠ አመለካከት፣ የኖህ ልጆች ስብጥር በተገለጠበት በምዕራፍ 10 ተረጋግጧል፡፡ ከኖህ ዘመን ረጅም ዓመታት በኋላ የመጣውን የትውልድ ሐረግ ስንመለከት፣ ሙሴ በምዕራፍ 10 ውስጥ የሴም፣ የካምና የያፌት ዝርያዎች በመላው ዓለም የተበተኑባቸውን ስፍራዎች ናሙና ያቀርባል፡፡ እንደ ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 አገላለጥ፣ የያፌት ዝርያ ሰሜናዊ፣ ሰሜን ምሥራቃዊ እና ሰሜን ምዕራባዊ የከነዓንን ድንበሮች ወርሷል፡፡ የካም ዝርያዎች ግን፣ በጣም የተወሰኑት ወደ ሰሜናዊ አፍሪካ ተንቀሳቅሰዋል፣ ከነዓን ተብሎ የሚጠራው የካም ልጅ ደግሞ፣ ለእስራኤል በተስፋ በተሰጣት ምድር በከነዓን ውስጥ ተቀምጧል፡፡ ሴማውያን ደግሞ በአብዛኛው የሰፈሩት በአረቢያ ባህረ-ሰላጤ ውስጥ ነው፡፡
የዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ዘገባ በእጅጉ የሚያተኩረው በተመረጡና የስደትን አጠቃላይ መርህ የሚያሳዩ መረጃዎችን በመስጠቱ ላይ ነው፡፡ እነዚህ አጠቃላይ መርሆች ግን ከጥፋት ውሃ በኋላ በመጣው አዲስ ሥርዓት የሰው ዘር የሚመራባቸውን የረጅም ዘመን ሰብዓዊ ግንኙነቶች ለመግለጥ ለሙሴ ከበቂ በላይ ነበሩ፡፡
በዘፍጥረት ምዕራፍ 9 እና 10 ሙሴ በኖህ ልጆች ላይ በሰጠው ትኩረት ላይ የተመሠረተውን ስነ-ጽሁፋዊ አወቃቀር ከተመለከትን፣ ከጥፋት ውሃ በኋላ የመጣውን አዲስ ስርዓት ወደ ምንመለከትበት እርከን እንሸጋገራለን፡፡ ያም በምዕራፍ 11 ከቁጥር 1 እስከ 9 የተጠቀሰው የባቢሎን ውድቀት ነው፡፡
የባቢሎን ውድቀት
የባቢሎን ግንብ ታሪክ በአምስት ተመጣጣኝ ድራማዊ እርከኖች ይከፈላል፡፡ በቁጥር 1 እና 2 የተቀመጠው የመጀመሪያው እርከን አብዛኛው የሰው ዘር በአንድነት ሲኖር የሚያሳየው ነው፡፡ በንፅፅሩ ግን፣ ታሪኩ የሚደመደመው እግዚአብሔር የሰውን ዘር ቋንቋ በመደባለቅ በምድር ሁሉ መበተናቸውን በሚናገረው በቁጥር 8 እና 9 ነው፡፡
የሰው ዘር በአንድ ቋንቋ በአንድነት ከመኖር ወደ ብዙ ቋንቋና ወደ መበታተን እንዴት ተሸጋገረ? በመካከል ያለው ክፍል ምን እንደተከናወነ ይነግረናል፡፡ በቁጥር 3 እና 4 የሚገኘው ሁለተኛ እርከን ሰዎች ያቀዱትን ዕቅድ ይዘግባል፡፡ ወደ ሰማይ የሚደርስ ማማ ያለባት ከተማ በመገንባት በየዘመናቱ ሁሉ ተዋቂና ፈፅመው የማይበገሩ የመሆን ዓላማ ነበራቸው፡፡ የሆነ ሆኖ፣ በቁጥር 6 እና 7 የሚገኘው የዚህ ትረካ አራተኛ እርከን እግዚአብሔር ያቀደውን አፍራሽ ዕቅድ በመዘገብ ሚዛኑን ያሳየናል፡፡ የከተማይቱን ሰዎቸ ቋንቋ በመደባለቅ የጀመሩትን የከተማና የማማ ግንባታ ሥራ ያስቆሙ ዘንድ እግዚአብሔር ሰማያዊ ሠራዊቱን ያዝዛል፡፡
የዚህ ታሪክ አቅጣጫ የሚቀየረው፣ እግዚአብሔር ከተማይቱንና ማማዋን በተመለከተበት በቁጥር 5 ነው፡፡ እግዚአብሔር የከተማዋንና በውስጥዋ የሚኖሩትን ሰዎች ትዕቢት ሲመለከት፣ የባቢሎን ከተማ ወደ ፍፃሜዋ መምጣት እንደሚገባት ወሰነ፡፡
እንደ ሙሴ አገላለጥ፣ ሕይወት ከጥፋት ውሃ በኋላ እኛ በገነት ከምንጠብቀው ሕይወት እጅግ የራቀ እንደሆነ አይተናል፡፡ በተቃራኒው፣ የኖህ ልጆች ዘገባ አዲሱ ሥርዓት በሰው ዘር መካከል ያመጣውን ውስብስብ ግንኙነት የሚያካትት መሆኑን ያሳየናል፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔርን መፈታተን እጅግ እየበዛ መሄዱን፣ በስተመጨረሻም እግዚአብሔርን የሚፈታተኑት የገጠማቸውን ሽንፈትም ይዘግባል፡፡ እነዚህ የአዲሱ ሥርዓት አወቃቀሮች ለእኛ ዘመነኛ ዓለም ጆሮ እንግዳ ቢመስሉም፣ እነዚህም ምዕራፎች በመጀመሪያ ለተጻፈላቸው ለእስራኤላውያን ግን በግልፅ የሚናገሩ መሆኑን እናያለን፡፡
የዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ድረስ ያለውን ክፍል ስነ-ጽሑፋዊ አወቃቀር ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ሁለተኛውን ጥያቄ መጠየቅ እንችላለን፡፡ ሙሴ ስለ ጥፋት ውሃ እና ስላስከተለው አዲስ ሥርዓት ለምን ጻፈ? እስራኤላውያን እርሱን ተከትለው ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሲጓዙ ከዚህ ምን ሊያስተምራቸው ፈልጎ ነው?
ቀደምት ትርጉም
ሙሴ ስለ ኖህ የጥፋት ውሃ እና ስላስከተለው አዲስ ሥርዓት የጻፈው እስራኤላውያንን ስለዚህኛው የፍጥረተ ዓለም ክፍል እውነታ ሊያሳውቃቸው መሆኑን መናገር የሚያስፈልገን አይመስለንም፡፡ ሆኖም፣ ዘገባው በጣም የተመረጠና በውሱን መሪ ሃሳቦች ላይ የሚያጠነጥን በልቡም ያለው ያ ነው ያሰኛል፡፡ ሙሴ የጻፈው ስላለፈው ለመዘብ ብቻ ሳይሆን፣ በእርሱ ዘመን የሚገኙትን እስራኤላውያን ለመምራትም ነበር፡፡
የሙሴን ዓላማ ገለጥ አድርን የምናየው የዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ያሉትን ሦስት ክፍሎች በመመልከት ነው፡፡ በመጀመሪያ፣ የጥፋት ውሃውን ትረካ ቀደምት ትርጉም እንመረምራለን፡፡ ከዚያም ወደ ኖህ ልጆች የሙሴ ዘገባ እንሸጋገራለን፤ በመጨረሻም፣ በፍጥረተ ዓለም ታሪክ የመጨረሻ ክፍል ማለትም በባቢሎን ውድቀት ቀደምት እንድምታዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ አስቀድመን ሙሴ የኖህን ዘመን ጎርፍ በእርሱ ዘመን ከነበሩ እስራኤላውያን ልምምድ ጋር ያዛመደባቸውን መንገዶች እንመልከት፡፡
ነፃ የማውጣት ጎርፍ
የሙሴን የጥፋት ውሃ ትረካ አጠቃቀም በውል ለመገንዘብ፣ የታሪኩን ሁለት ገፅታዎች እናያለን፡ በመጀመሪያ፣ በውሃ ሙላቱና በዘፀአት መካከል የመሠረታቸውን ትስስሮች፣ ሁለተኛ እነዚህ ትስስሮች ለእስራኤላውያን ያላቸውን አንድምታ እንመለከታለን፡፡ ሙሴ የጥፋት ውሃውን ከእርሱ ዘመን ጋር ያገናኘው፣ ኖህን ከራሱ ሕይወትና አገልግሎት ጋር በሚመሳሰል መንገድ በመግለጥ ነው፡፡ እንግዲህ፣ የኖህና የሙሴ ሕይወት በብዙ ረገድ የተለያየ መሆኑና ይህም ልዩነት ቸል ሊባል እንደማይገባ እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ ሆኖም ሙሴ ኖህን የገለፀው እስራኤላውያን አንባቢዎቹ እንደ እርሱ ቀዳሚ አመልካች ወይም ጥላ እንዲመለከቱት አድርጎ መሆኑም ግልፅ ነው፡፡
ትስስሮች
በኖህና በሙሴ መካከል ቢያንስ ስምንት ጉልህ ትስስሮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ፣ ሙሴ በእርሱና በኖህ መካከል ትስስር እንዳለ ያሳየው በክፋት ጭብጥ ውስጥ ነው፡፡ ከዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 13 እንደምታስታውሱት የኖህ የጥፋት ውሃ የተከሰተው ምድር በክፋት ስለተሞላች ነበር፡፡ ዘፀአት ምዕራፍ 1 እና 2 ግልፅ እንደሚያደርግልን፣ ከሙሴ መጠራት ቀደም ብሎ ግብፃውያን በእስራኤላውያን ላይ ጽኑ መከራ አብዝተውባቸው ነበር፡፡ ሙሴ እስራኤልን ከግብፅ ነፃ ማውጣቱ በእስራኤላውያን ላይ ለተፈፀመው ግፍ የአፀፋ ምላሽ ነበር፡፡ እንግዲያው፣ የኖህና የሙሴ ሥራ ከክፋት ነፃ ማውጣት ነበር፡፡
ሁለተኛው ትስስር የሚታየው ሙሴ መርከብ የሚለውን ቃል ሲጠቀም ነው፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 እስከ 9 ባሉት ክፍሎች ውስጥ የኖህ መርከብ የተጠቀሰበት የዕብራይስጥ ቃል ቴቫህ tevah (תֵּבָה) የሚል ነው፡፡ ሙሴ ይህን ቴቫህ የተሰኘ ቃል በሌላ ስፍራ የተጠቀመው በዘፀአት ምዕራፍ 2 ቁጥር 3 እና 5 ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ በዚያም ስፍራ እናቱ እርሱን በመርከብ ወይም ቴቫህ ውስጥ ማስቀመጧን ይጠቅሳል፡፡ የኖህ መርክብ እጅግ ግዙፍ የሙሴ ግን እጅግ ትንሽ ብትሆንም እንኳን፣ ኖህም ሆነ ራሱ ሙሴ ከጥፋት ውሃ የዳኑት በመርከብ ወይም ቴቫህ አማካይነት መሆኑን ያመለክታል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ፣ የመለኮታዊ ቃል ኪዳኖቹ ወሳኝነት ኖህ የሙሴ ቀዳሚ አመልካች መሆኑን ያሳያል፡፡ እንደተመለከትነው ሁሉ፣ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 18 እና ምዕራፍ 9 ከቁጥር 11 እስከ 17፣ ኖህ የሰውን ዘር ወክሎ ከእግዚአብሔር ጋር የቃል ኪዳን ግንኙነት አድርጓል፡፡ እንደዚያውም፣ ሙሴ ለእስራኤል ከሰጣቸው አገልሎቶች አንዱ መለኮታዊ ቃል ኪዳንን ስለ እነርሱ መቀበል ነበር፡፡ ዘፀአት ምዕራፍ 19 እስከ 24 በግልፅ እንደሚያሳየን፣ እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ ሲመጡ ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ልዩ የቃል ኪዳን ትስስር ውስጥ እንዲገቡ ሊመራቸው ሙሴ ተመርጧል፡፡
በውሃ አማካይነት የተፈፀመው ፍርድ ማዕከላዊ አስተዋፅዖም በሁለቱ ሰዎች መካከል የሚገለጠው አራተኛው ትስስር ነው፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 እስከ 9 ውስጥ፣ የተቀረው ዓለም በጥፋት ውሃ ሲቀጣ፣ እግዚአብሔር ግን ኖህንና ቤተሰቡን እንዳዳነ እናነባለን፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ ዘፀአት ምዕራፍ 13 እስከ 15 እንደሚነግረን፣ ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ ያወጣው በቀይ ባህር ውስጥ በማሳለፍ ነበር፡፡ ያው ውሃ ግን ግብፃውያን አሳዳጆቻቸውን አጥፍቷል፡፡
በአምስተኛ ደረጃ፣ በኖህም ዘመን ሆነ በሙሴ እግዚአብሔር ውሃውን ለማድረቅ የላከው ንፋስ ነበር፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 8 ቁጥር 1 እንደምናነብበው፣ የኖህን ዘመን የጥፋት ውሃ ለማድረቅ እግዚአብሔር የላከው ንፋስን ነበር፡፡ በተመሳሳይም፣ በዘፀአት ምዕራፍ 14 ቁጥር 21 እንደምናየው፣ “እግዚአብሔር ብርቱ የምሥራቅ ንፋስ በማንፈስ ወንዙን ወደ ኋላ መለሰው”
ስድስተኛው ትስስር በእንስሳት ላይ በተሰጠው አፅንዖት ውስጥ ነው፡፡ ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 19 እንደሚነግረን፣ ኖህ እንስሶችን ወደ መርከቡ እንዲያስገባ እግዚአብሔር ያዝዘዋል፡፡ በዘፀአት መጽሐፍም ውስጥ ከአራት ለማያንሱ ጊዜያት፣ በርካታ እንስሶች ከእስራኤላውያን ጋር ግብፅን ለቅቀው እንደወጡ ተጠቅሷል፡፡ ልክ እግዚአብሔር ኖህን በእርሱ ዘመን እንስሶችን ይዞ ወደ መርከብ እንዲገባ እንዳዘዘው ሁሉ፣ ሙሴም ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንስሶችን ይዞ እንዲገባ እግዚአብሔር አዝዞታል፡፡
ሰባተኛ፣ የመለኮታዊ መታሰብ መሪ ሃሳብም ኖህንና ሙሴን ያቆራኛል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 8 ቁጥር 1 በኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ ምድርን ሲያጥለቀልቅ፣ እግዚአብሔር ኖህን እንዳሰበና ስለ እርሱ እንደሠራ እናነባለን፡፡ እግዚአብሔር በጥፋት ውሃ ውስጥ እንደሚያሳልፈው ለኖህ ቃል ኪዳን ገባለት፣ ያንን ቃል ኪዳንም አሰበ፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብፅ ነፃ የሚያወጣው ቃል ኪዳኑን ስለሚያስብ እንደሆነ ለሙሴ ነግሮታል፡፡ በዘፀአት ምዕራፍ 6 ቁጥር 5 እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን አድምጡ፡
ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። (ዘፀአት 6፡5)
መለኮታዊ መታሰብም በጥፋት ውሃና በዘፀአትም ውስጥ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
በመጨረሻም፣ የፍጥረት በረከት ኖህን ከሙሴ ጋር ያስተሳስረዋል፡፡ ኖህ የሰውን ዘር ወደ አዲስ ዓለም ይዞ ወጥቷል፡፡ ያም ዓለም የሰው ዘር የሚጠቀምበት ዘላቂና የተረጋጋ ተፈጥሮአዊ ሥርዓት እንደሚኖር እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠበት ነው፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ በተስፋዪቱ ምድር፣ ተፈጥሮ ሚዛኑን የጠበቀ እና የሚጠቅም እንደሚሆን ሙሴ ለእስራኤላውያን ነግሯቸዋል፡፡
በኖህና በሙሴ መካከል ያሉ ትስስሮችን በልቡናችን ይዘን፣ እነዚህ ትስስሮች ለእስራኤል ህዝብ ያላቸውን አንድምታ እንመለከታለን፡፡ ሙሴ እነዚህን ትስስሮች ለምን መሠረተ?
እንድምታዎች
የዚህን ጽሑፍ ቀደምት እንድምታ ለመጨበጥ፣ ሥልጣኑን፣ ነፃ የማውጣትና የማውረስ ዕቅዱን በመጠራጠር እስራኤላውያን በሙሴ ላይ በብርቱ ማመፃቸውን ማስታወስ ይገባናል፡፡ ሙሴ በአገልግሎቱ ላይ የተጋረጠበት ይህ ተግዳሮት በኖህና በራሱ መካከል ትስስሮችን እንዲፈጥር አድርጎታል፡፡
እግዚአብሔር የሰውን ዘር ከአሰቃቂው የፍጥረተ ዓለም ክፋት በነፃ ማውጣት ጎርፍ ለመታደግ ደግሞም ታላቅ በረከት ባለበት አዲስ ዓለም የሰውን ዘር እንደገና ለማስፈር ኖህን ተጠቀመ፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ እስራኤልን ከአሰቃቂው የግብፅ ክፋት ለመታደግ እና ወደ አዲሲቷ የተስፋ ምድር ለማምጣት ሙሴን መረጠ፡፡ ሙሴ ለእስራኤል ያወጣው ዕቅድ ከኖህ የጥፋት ውሃ ጋር ተመሳሳይ ነው ያንንም የእግዚአብሔር እጅ እንዳደረው ማንም ሊስተው በማይችል መንገድ የተከናወነ ነው፡፡
ነፃ የማውጣትን ጎርፍ ቀደምት ትርጉም ከተመለከትን፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 9 ከቁጥር 18 እስከ ምዕራፍ 10 ቁጥር 32 ወደተመዘገበው የኖህ ልጆች ትረካ እንሸጋገር፡፡
የኖህ ልጆች
ሙሴ በፍጥረተ ዓለም ታሪክ ውስጥ ይህንን ለምን አካተተው? ይህንንስ ጉዳይ እስራኤል ልብ እንድትለው ያደረገበት ዓላማ ምንድን ነው? የዚህን ክፍል የሙሴን ዘገባ ለመመርመር ሦስት ጉዳዮችን እንመለከታለን፡ አንደኛ፣ በከነዓን ላይ ያደረገው ልዩ ትኩረት፤ ሁለተኛ፣ የግጭት መሪ ሃሳብ፤ ሦስተኛ፣ እነዚህ ጭብጦች ለእስራኤል ያላቸው አንድምታ ናቸው፡፡ አስቀድመን ሙሴ ስለ ከነዓን የሰጠውን አትኩሮት እንቃኝ፡፡
ከነዓን
ኖህ ከስካሩ ሲነቃ ካም እንዳቃለለው፣ ሴምና ያፌት ደግሞ ነውሩን መሸፈናቸውን ማወቁን ታስታውሳላችሁ፣ ኖህ በካም ላይ መቆጣቱና ሌሎቹን ወንድሞቹን ሲባርክ እርሱን መርገሙ ምክንያታዊ ይመስላል፡፡ የሆነው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እስኪ በዘፍጥረት ምእራፍ 9 ከቁጥር 25 እስከ 27 ኖህ የተናገረውን አድምጡ፡
እንዲህም አለ፦ ከነዓን ርጉም ይሁን ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።
እንዲህም አለ፦ የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
(ዘፍጥረት 9፡25-27)
በዚህ ምንባብ እንደምንመለከተው፣ ሴምና ያፌት ለጽድቅ ተግባራቸው ተገቢ በረከት ተቀብለዋል፣ ሆኖም ካም ስሙ እንኳን አልተጠቀሰም፡፡ ይልቁኑ፣ የኖህን እርግማን የተቀበለው፣ ልጁ ከነዓን ነው፡፡
ይህንን ታሪክ በጥንቃቄ ስንመለከት፣ ካም ከወንድሞቹ ለየት ያለ ድርሻ እንዳለው እንመለከታለን፡፡ በአጭሩ፣ ካም የከነዓን አባት ተብሎ ከመጠቀሱ ውጪ ብዙም ስፍራ አልተሰጠውም፡፡ ሙሴ በትረካው ውስጥ ስለ ካም የጻፈውን ልብ በሉ፡ በምዕራፍ 9 ቁጥር 18 እንዲህ እናነባለን፡
ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት ካምም የከነዓን አባት ነው። (ዘፍጥረት 9፡18)
በምዕራፍ 9 ቁጥር 22 ውስጥም ተመሳሳይ መግለጫ እናገኛለን፡
የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ (ዘፍጥረት 9፡22)
በብዙ መንገዶች፣ ካም ከታሪኩ ጀርባ ሲሰወር ልጁ ከነዓን ግን የእርሱን ስፍራ ተክቶ ከሴምና ከያፌት ጋር ይጠቀሳል፡፡
ሙሴ በከነዓን ላይ የሰጠውን ይህንን ልዩ አፅንዖት በልቡናችን ይዘን፣ የኖህን ልጆች ወደ ገለጠበት ሁለተኛ ጉዳይ እንሸጋገር፡፡ ያም ከጥፋት ውሃ በኋላ በአዲሱ ሥርዓት የተፈጠረው ግጭት ነው፡፡
ግጭት
ሙሴ በኖህ ልጆች ላይ ካቀረበው ዘገባ አብላጫውን የሚይዘው የግጭት መሪ ሃሳብ ነው፡፡ ይህንን መሪ ሃሳብ መሳት የታሪኩን ወሳኝ ገፅታ መሳት ነው፡፡ የግጭት ጉዳይ በዘፍጥረት ምዕራፍ 9 ከቁጥር 25 እስከ 27 ይገለጣል፡፡
እንዲህም አለ፦ ከነዓን ርጉም ይሁን ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።
እንዲህም አለ፦ የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
(ዘፍጥረት 9፡25-27)
በዚህ ምንባብ ውስጥ የከነዓንን መረገም ሦስት ጊዜ ደጋግሞ በመዘገብ የግጭቱን እርግጠኝነት ሙሴ እንዴት ጫን ብሎ እንዳመለከተ ልብ በሉ፡፡ በቁጥር 25 ውስጥ ከነዓን “የባሪያዎች ባሪያ” ወይም ከባሪያዎች ሁሉ ዝቅተኛው እንዲሆን መረሙን ያሳያል፡፡ በቁጥር 26፣ ከነዓን የሴም ባሪያ እንደሚሆን ይተነብያል፡፡ በቁጥር 27 ደግሞ፣ ከነዓን በተጨማሪም የያፌትም ባሪያ እንደሚሆን ሙሴ ጨምሮ ይናገራል፡፡ በዚህ ድግግሞሽ፣ ከነዓን በወንድሞቹ ድል እንደሚነሳ ሙሴ በእርግጠኝነት ይናገራል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ሴም ከነዓንን ድል እንደሚያደርገው እነዚህ ጥቅሶች የሚያመለክቱ መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ በቁጥር 27፣ “ያፌት በሴም ድንኳን ይደር ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን” የሚሉት ቃላት “ያፌት በሴም ድንኳኖች ቢያድር ከነዓን ባሪያው ይሆናል” ቢባል የተሻለ ይገልጠዋል፡፡ የኖህ ሃሳብ የሚመስለው፣ ከነዓን የያፌት የበታች ሊሆን የሚችለው ያፌት ከሴም ሠራዊት ጋር ከተባበረ ነው የሚል ነው፡፡ በሙሴ እምነት ከነዓንን ለመውረር ሴም የመሪነት ሚና አለው፡፡
በዚህ ምንባብ ውስጥ ከጥፋት ውሃ በኋላ ይሆናል ተብሎ በማይጠበቅ መንገድ አዲስ ስርዓት የመመሥረቱን ወሳኝ ገፅታ ሙሴ እያመለከተ መሆኑን አይተናል፡፡ ከዚያ በኋላ በሚመጣው የሰው ዘር ውስጥ የሴም ዘር የከነዓንን ዘር የሚወርርበት ድራማዊ ግጭት አይቀሬ መሆኑን ተረድቷል፡፡
ሙሴ በከነዓን ላይና በግጭት መሪ ሃሳብ ላይ ባሰጠው አፅንዖት መሠረት፣ ለጥንታዊቷ እስራኤል የኖህ ልጆች የሚኖራቸውን ቀደምት አንድምታ መመልከት እንችላለን፡፡
አንድምታዎች
ከጥፋት ውሃ በኋላ በተለጠው አዲስ ስርዓት ውስጥ ሙሴ እነዚህን ክስተቶች ማካተት ለምን አስፈለገው? ሙሴ አዲሱን ስርዓት በዚህ መንገድ የገለጠበት የራሱ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ በሴምና በከነዓን መካከል የነበረው ግጭት ለእስራኤላውያን ተደራሲያኑ በቀጥታ የሚያስተላልፈው መልእክት አለ፡፡ ወሳኝ የሆኑ የሕይወት ገፅታዎቻቸውን ይዳስሳል፡፡
የሙሴን ዓላማ የምንገነዘብበት ቁልፍ የሚገኘው በዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ከቁጥር 18 እስከ 19 ባለው ውስጥ ነው፡፡ ሙሴ የከነዓንን ዝርያ ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ ጽፏል፡
ዐሩኬዎንንም፥ ሲኒንም፥ አራዴዎንንም፥ ሰማሪዎንንም፥ አማቲንም ወለደ። ከዚህም በኋላ የከነዓናውያን ነገድ ተበተኑ።
የከነዓናውያንም ወሰን ከሲዶን አንሥቶ ወደ ጌራራ በኩል ሲል እስከ ጋዛ ድረስ ነው ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ፥ ወደ አዳማና ወደ ሰቦይም በኩልም ሲል እስከ ላሣ ድረስ ነው።
(ዘፍጥረት 10፡18-19)
እነዚህ ውሱን መልክዓምድራዊ ማጣቀሻዎች በሙሴ እስራኤላውያን አንባቢዎች ዘንድ የታወቁ ናቸው፡፡ የከነዓን ዝርያዎች ወይም ከነዓናውያን፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ማለትም ከሲዶን እስከ ጋዛ ደግሞም እስከ ሰዶምና ገሞራ ባሉት ግዛቶች ውስጥ ሰፍረው ነበር፡፡ ሙሴም በተስፋይቱ ምድር በሰፈሩት በእነዚህ የከነዓን ዝርያዎች ላይ ለየት ያለ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በእግዚአብሔር እንደተጠሩ የሴም ዝርያዎች፣ የእስራኤል ህዝብም ወደ ከነዓናውያን ምድር በመሄድ የእኛ ነው ማለት ነበረባቸው፡፡
ስለዚህ ሙሴ ስለ ኖህ ልጆች ያቀረበው ዘገባ የተቀረፀው ያለፈ ታሪክ መረጃ ለመስጠት ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በፍጥረተ ዓለም ታሪክ እንደደነገገው ሁሉ፣ እስራኤላውያን ምድሪቱን ለመውረስ እንዲወጡ ሙሴ ለሚያቀርበው ጥሪ አስተማማኝ ዳራ ለመስጠት ነበር፡፡ በውጤቱም፣ የከነዓንን ምድር እንዲወርሱ ሙሴ የሚያቀርበውን ጥሪ የሚቃወሙ ሰዎች የሚቃወሙት ሙሴን ብቻ አይደለም፡፡ በመሠረቱ የሚቃወሙት የእግዚአብሔርን ዕቅድ፣ ማለትም ከጥፋት ውሃ በኋላ እግዚአብሔር የደነገገውን ሥርዓት ነው፡፡
እንግዲህ የጥፋት ውሃ እና የኖህ ልጆች ታሪክ ከቀደምት ተደራሲያኑ ከእስራኤላውያን ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ከተመለከትን፣ ወደ ሦስተኛው ትኩረታችን መሸጋገር ይገባናል፡፡ ያም በዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ከቁጥር 1 እስከ 9 ሙሴ ስለ ባቢሎን ውድቀት ሲጽፍ ስለነበረው ቀደምት ዓላማ የሚያወሳው ነው፡፡
የባቢሎን ውድቀት
እስራኤላውያን የባቢሎንን ውድቀት ታሪክ ከሕይወታቸው ጋር እንዲያዛምዱ ሙሴ እንዴት ይፈልግ እንደነበር በውል ለመጨበጥ፣ ይህንን ምንባብ በሦስት ገፅታዎች መመልከት ይገባናል፡ በመጀመሪያ፣ ሙሴ ስለ ከተማዋ የሰጠው መግለጫ፤ ሁለተኛ፣ ስለ ያህዌ ድል አድራጊነት የሰጠው መግለጫ፤ ሦስተኛ ደግሞ፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሲጓዙ ስለሚኖራቸው አንድምታ ናቸው፡፡ አስቀድመን ስለ ከተማዪቱ የሰጠውን መግለጫ እንመልከት፡፡
ከተማ
ባቢሎን የተሰኘው የከተማዪቱ ስም፣ በኋለኞቹ ዘመናትም ታዋቂ የሆነ ዝና ያላት ባቢሎን የምትጠራበት ስም ሆኗል፡፡ በሙሴ ዘመን፣ የባቢሎን ከተማ በጥንታዊው ቅርብ ምሥራቅ ውስጥ ታዋቂ ነበረች፡፡ ለበርካታ ዓመታትም የስልጣኔ ማዕከል በመሆን ዘልቃ ነበር ክብርና ዝናዋም ወደ ጥንታዊ አማልክትነት ድንበር አድጎ ነበር፡፡ ስለዚህ ሙሴ ከጥፋት ውሃ በኋላ ባቢሎን ስለተባለ ስፍራ ሲፅፍ፣ ያ ስፍራ የከተማ ሥልጣኔ ቀደምት መሠረት የነበረው መሆኑን እስራኤላውያን አንባቢዎቹ በቶሎ ይገነዘባሉ፡፡
ድል
የዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ከቁጥር 1 እስከ 9 የሚገኘው ሁለተኛው ወሳኝ ገፅታ ያህዌ በታላቁ ፍጥረተ ዓለም ላይ ስለተቀዳጀው ድል ሙሴ የገለጠበት መንገድ ነው፡፡ ሙሴ የባቢሎናውያንን አመለካከት ከራሱ አመለካከት ጋር በማነፃፀር የእግዚአብሔርን ድል ታላቅነት በታሪኩ ውስጥ ደግሞ ደጋግሞ ያንፀባርቃል፡፡ ለምሳሌ፣ ሙሴ የመበታተንን ወይም በእብራይስጡ puts (פּוּץ) የተባለውን መሪ ሃሳብ ያቀረበበትን አቀራረብ ልብ በሉ፡፡ በአንድ ወገን፣ የባቢሎን ሰዎች ሊበታተኑ እንደሚችሉ በማሰብ ይጨነቃሉ፡፡ በምዕራፍ 11 ቁጥር 4 ውስጥ ከተማይቱን የገነቡት “በምድር ዙሪያ እንዳይበተኑ እንደነበር” እንመለከታለን፡፡
በተቃራኒው ግን፣ ሙሴ ሁለት ጊዜ እንደዘገበልን የባቢሎን ሰዎች እንዲሆን የማይፈልጉትን ያንኑ እግዚአብሔር አድርጎባቸዋል፡፡ በምዕራፍ 11 ቁጥር 8 እንዲህ እናነብባለን፡
እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው …. ። (ዘፍጥረት 11፡8)
እንደገና በምዕራፍ 11፡9 ደግሞ፣
… ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል። (ዘፍጥረት 11፡9)
በብሉይ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ “መበተን” የሚለው ቃል በጦርነት ጊዜ ሊያንሰራሩ በማይቻልበት መንገድ መሸነፍን የሚያሳይ አሉታዊ ሃሳብ ነው፡፡ የተሸነፉ ወታደሮች ጠላቶቻቸው ሲያሳድዷቸው ይበታተናሉ፣ ሲያገኟቸውም አንገታቸውን ይቀሏቸዋል፡፡ በዚህ ታሪክም ውስጥ ያለው ሃሳብ ይህንኑ የሚመስል ነው፡፡ ሙሴም ይህንን ታሪክ የሚያቀርበው እንደ ያህዌ አስደናቂ ድል አድርጎ ነው፡፡ በባቢሎን ከተማ ጦርነት ለመግጠም ያህዌ ሰማያዊ ሠራዊቱን ይጠራል፣ ከዚያም የሚሸሹትን ነዋሪዎቿን በምድር ዙሪያ ሁሉ ያሳድዳቸዋል፡፡
ሙሴ የራሱን አመለካት ከባቢሎናውያን ጋር ያነፃፀረበት መንገድ ከከተማዋ መጠነ ልክና ከግንቧ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እንደ ዘፍጥረት 11 ቁጥር 4 አገላለጥ፣ ባቢሎናውያን ወደ ሰማይ ማለትም አማልክቶቻቸው ወደሚኖሩበት ስፍራ የሚደርስ ግንብ ፈለጉ፡፡ ሙሴ ግን በዚህ ሃሳብ ያላግጣል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ቁጥር 5 እንደምናነብበው፡
እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። (ዘፍጥረት 11፡5)
በዚህ ስፍራ ወረደ ተብሎ የተተረጎመው yarad (יָרַד) የተሰኘው የዕብራይስጥ ቃል፣ በዚህ ታሪክ ውስጥ ሌላ ግልፅ ሃሳብ ያዘለ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዝም ብሎ ከተማይቱን አላያትም፤ ወይም ዝም ብሎም አልመጣም፡፡ የባቢሎን ሰዎች ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለመሥራት ሲፈልጉ፣ ያህዌ ከፍ ካለው ሰማይ ከተማይቱን ለማየት መጣ ሲል ሙሴ ያመለክተናል፡፡ ሙሴ በባቢሎናውያን ግብዝነት ያፌዛል፡፡ ከያህዌ አተያይ አንፃር፣ ከተማይቱ ከጉድፍ ዘለል የማትል ናት፡፡
በስተመጨረሻ፣ ሙሴ የዚያን የፍጥረተ ዓለም ከተማ ትዕቢት ያፌዝበት ዘንድ የባቢሎን ሽንፈት እንዴት እንዳገዘው ልብ ማለት ይገባናል፡፡ ነዋሪዎቿ ከተማዋን ባቢሎን ብለው ይጠሯታል፡፡ በሜሶፖታሚያ ቋንቋ፣ ባቢሎን ማለት “የአማልክት በር“ ማለት ነው፡፡ ይህ ስም የሚገልፀው ዚግራት የተሰኘው ጣዖት የአማልክት በር ነው፣ ስለዚህም በሰማይ ኃይላት ተጠብቀናል የሚለውን እምነታቸውን ነው፡፡
ሙሴ ግን ስለ ከተማይቱ ስም የተለየ አመለካከት አለው፡፡ ያህዌ ባቢሎንን በብርቱ እስካሸነፈ ድረስ፣ ከተማይቱ የአምላክ በር ልትሆን አትችልም፡፡ ስለዚህ፣ ታዲያ ስሟ ምን ትርጉም አለው? የሙሴ አስደማሚ ስላቃዊ መልስ በዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ውስጥ ይገኛል፡
ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል። (ዘፍጥረት 11፡9)
በዚህ ጥቅስ ውስጥ የሙሴን ስላቅ በአግባቡ ለመረዳት ሙሴ ሁለት የእብራይስጥ ቃል ድምፆችን እንዴት እንደተጠቀመባቸው መገንዘብ ይገባናል፡፡ በመጀመሪያ፣ “ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ” ይላል፡፡ ባቢሎን ለሚለው የእብራይስጡ ቃል babel (בָּבֶל) ማለት ሲሆን፣ ይህም ሜሶፖታማውያን ስፍራውን የሚጠሩበት መጠሪያ የዕብራይስጥ አቻው ነው፡፡ ሙሴ ግን ከተማዋ ይህን ስም ያገኘችው እግዚአብሔር የሰውን ዘር ቋንቋ በዚያ ስለደባለቀ ነው ይለናል፡፡ ደባለቀ ለሚለው ቃል የእብራይስጡ አቻ balal (בָּלַל) የሚለው ሲሆን፣ በዕብራይስጡ babel ከተሰኘው ጋር ተመሳሳይ ድምፅ አለው ሙሴም ስላቁን ያስቀመጠው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ባቢሎን ተብላ የተጠራችበት ምክንያት በዚያ ስፍራ መደበላለቅ ስለተከሰተ ነው በማለት የዚያችን ጥንታዊት ከተማ ጉድ ይገላልጠዋል፡፡ ስለዚህ፣ ሙሴ ባቢሎን ስለተሰኘው ስም ያለው አመለካከት ለስፍራው እግባብነት አለው፣ ያም የአማልክት በር በመሆኗ ሳይሆን፣ የግራ መጋባት ማለትም የመላው ዓለም ግራ መጋቢያ ስፍራ በመሆኗ ነው፡፡ ሙሴ በዚህ ስላቅ መሠረት፣ ባቢሎን በእርሱ ዘመን የነበራትን የከበረ ስም እስከወዲያኛው ግልብጥብጡን ያወጣዋል፡፡ እስራኤላውያን ተደራሲያኑ የእነርሱ አምላክ ያህዌ በፍጥረተ ዓለም ታሪክ ውስጥ ገናና በነበረችው ከተማ ላይ የተቀዳጀውን ድል ሲያወሳላቸው በከተማይቱ ላይ በታላቅ ስላቅ ይሳለቃሉ፡፡
ስለ ከተማይቱ የተሰጠውን መግለጫና የያህዌን ድል በልቡናችን ይዘን፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚያደርጉት ጉዞ ይህ ታሪክ ስለሚኖሩት አንድምታዎች መመልከት እንጀምራለን፡፡
እንድምታዎች
እንደምናውቀው፣ በቃዴስ በርኔ፣ ክፉ ሪፖርት ይዘው የተመለሱ ሰላዮችን ወደ ከነዓን ምድር ሙሴ ልኮ ነበር፡፡ ሰላዮቹም፣ በምድሪቱ ውስጥ ያሉት ሠራዊቶች እጅግ ኃያል ከመሆናቸው የተነሳ እስራኤል ከነዓንን ልትወርስ አትችልም ብለው ነበር፡፡ በውጤቱም፣ እስራኤላውያን ምድሪቱን ለመውረስ ከሚያደርጉት ጉዞ ፊታቸውን መልሰው ቀጣዮቹን አርባ ዓመታት በምድረ በዳ ተንከራትተዋል፡፡ ሙሴ እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደገና መምራት የጀመረው ቀጣዩ ትውልድ ለአቅመ አዳም ሲደርስ ነበር፡፡
የዚህ ክፉ ሪፖርት አንደኛው ገፅታ ጥንታዊቷ ባቢሎን የመውደቋን ወሳኝነት እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ በዘዳግም ምዕራፍ 1 ቁጥር 28 ሰላዮቹ ስለ ከነዓናውያን ከተሞች ያቀረቡትን ዘገባ አድምጡ፡
… ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ … (ዘዳግም 1፡28)
እንደ አለመታደል ሆኖ፣ አብዛኞቹ የዘመናችን ትርጉሞች በዚህ የከነዓናውያን ከተሞች መግለጫና በባቢሎን ግንብ መካከል ያለውን ትስስር ማመልከት ተስኗቸዋል፡፡ ሰላዮቹ “እስከ ሰማይ የደረሱም” ብለው ሲናገሩ፣ ሰማይ የሚለው ቃል በዕብራይስጡ shamayim (שָׁמַיִם), የሚለውና አብዛኛውን ጊዜ “ሰማይ” ብለን የምንተረጉመው ነው፡፡ በመሠረቱ፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ቁጥር 4 “ራሱ ወደ ሰማይ የደረሰ ” ተብሎ ስለ ባቢሎን ግንብ የተጻፈውም በተመሳሳይ ቃል ነው፡፡ በሁለቱም ወቅት፣ ሃሳቡ የሚያመለክተው የከተሞቹ ከፍታ ወደ ሰማይ የደረሰ ስለሆነ የማይበገሩ መሆናቸውን ነው፡፡
ስለዚህ ሙሴ በዚህ መንገድ በጥንቷ የባቢሎን ከተማና በከነዓን ከተሞች መሃል ያለውን ትስስር ያሳየናል፡፡ የባቢሎንን ግንብ ይገነቡ የነበሩ ሰዎች የእነርሱ ጣዖት ወደ ሰማይ እንደሚደርስ ያስቡ እንደነበር ሁሉ፣ የከነዓንን ከተሞች የከበቡት ግንቦች ወደ ሰማያት እንደሚደርሱ እስራኤላውያንም አስበዋል፡፡ በባቢሎን ከተሞችና በከነዓን ከተሞች መሃል ያለው ይህ ትስስር የሙሴን ዓላማ ወደ ብርሃን ያወጣዋል፡፡ በቀላሉ ስናስቀምጠው፣ የከዓናውያን ከተሞች በእስራኤላውያን ፊት ወደ ሰማይ የደረሱ ይመስሉ ነበር፣ ከያህዌ ኃይል ጋር ግን ጨርሶ ሊቀራረቡ አይችሉም፡፡ በጥንቱ ቀናት፣ በሰው ዘር ዘንድ ታዋቂ በሆነችው እና ግንቧ ወደ ሰማይ ይደርሳል ተብሎ በሚታሰበው ከተማ ላይ ዘምቶባት ነበር፡፡ ሆኖም፣ ይህች ጥንታዊ እና፣ ከከነዓን ከተሞች ይልቅ እጅግ ታላቅ የነበረችው ከተማ በያህዌ በቀላሉ ወድማ ነበር፡፡
ልክ እግዚአብሔር በጥንታዊው የጥፋት ውሃ የሰው ዘር አድኖ ወደ አዲስ ስርዓት እንዳስገባ ሁሉ፣ እስራኤልም ከግብፅ ነፃ አውጥቷል፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር በሴምና በከነዓን መካከል ግጭትን እንደደነገገ ሁሉ ሙሴም እስራኤላውያንን ወደ ከነዓን ምድር እየመራቸው ነበር፡፡ ልክ እግዚአብሔር ታላቂቱን ባቢሎንን እንዳሸነፈ ሁሉ፣ ለእስራኤላውያንም በከነዓንን ከተሞች ላይ ፈጥኖ ድልን ይሰጣቸዋል፡፡ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ሙሴን ተከትሎ መጓዝ በትክክለኛው አቅጣጫ መጓዝ መሆኑን እስራኤላውያን ከእነዚህ የፍጥረተ ዓለም ታሪኮች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
እስከዚች ነጥብ ድረስ የዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ያለውን የሙሴን ዘገባ ስነ-ጽሁፋዊ ውቅርና ቀደምት ትርጉም ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ፣ እነዚህን ዘገባዎች በዛሬው ሕይወታችን ልናዛምድ የምንችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? የሚለውን ሦስተኛ ጥያቄ እንጠይቃለን፡፡
ዘመነኛው ተዛምዶ
በተለመደው አቀራረባችን መሠረት የዘመነኛውን ተዛምዶ ጥያቄያችንን የምንዳስሰው አዲስ ኪዳን የክርስቶስን መንግሥት የገለጠባቸውን ሦስት እርከኖች በመከተል ነው፡፡ በመጀመሪያም የነፃ ማውጣቱ ጎርፍ እና ያስከተለው አዲስ ሥርዓት በክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት ከታወጀው የመንግሥቱ ጅማሬ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ እንመለከታለን፡፡ ከዚያም በቤተክርስቲያን ታሪክ ሁሉ ውስጥ እነዚህ ጉዳዮች ከመንግሥቱ እድገት አንፃር ምን ፋይዳ እንዳላቸው እናያለን፡፡ በመጨረሻም፣ ክርስቶስ በክብር ተመልሶ ሲመጣ ከሚገለጠው የመንግሥቱ ፍፃሜ ጋር እነዚህን የፍጥረተ ዓለም ክፍሎች አዲስ ኪዳን እንዴት እንደሚያዛምዳቸው እንመረምራለን፡፡
ሙሴ ስለ ፍጥረተ ዓለም ታሪክ ያቀረበውን ዘገባ የመጨረሻ ምዕራፎች በዚህ መንገድ ስንቀርበው፣ ሙሴ ለእስራኤል ያነገበውን ቀደምት ዓላማ አዲስ ኪዳንም በሦስቱም የክርስቶስ መንግሥት እርከኖች ማለትም በቀድሞው ዘመን፣ በአሁኑና በወደፊቱ ሥራዎቹም ውስጥ እንዳነገበው እንመረምራለን፡፡ አስቀድመን አዲስ ኪዳን ከክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት አንፃር እነዚህን መሪ ሃሳቦች እንዴት እንደሚመለከታቸው እንቃኝ፡፡
ምሥረታ
በመንግሥቱ ምሥረታ ውስጥ፣ ክርስቶስ ስለ ህዝቡ ታላላቅ ድሎችን ተቀዳጅቷል፡፡ ይህም በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ድረስ ሙሴ አፅንዖት ከሰጠበት ጋር በሚዛመድ መልኩ ነው፡፡ ይህንንም ትስስር ቢያንስ በሁለት መንዶች እንመለከተዋለን፡፡ እነርሱም፡ ክርስቶስ መካከለኛ የሆነበት ቃል ኪዳን እና የተቀዳጀው ድል ናቸው፡፡
ቃል ኪዳን
በአንድ በኩል፣ ክርስቶስ ለህዝቡ ነፃነትን ያስገኘው ህዝቡን ከእግዚአብሔር ፍርድ በሚያስመልጥ ቃል ኪዳን አማካይነት ነው፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው፣ ኖህ የቃል ኪዳን መካከለኛ የመሆን ልዩ ሚና ነበረው፡፡ ሙሴም ይህንን ነጥብ ያመለከተው እርሱ ራሱ ለእስራኤል ስለ ነበረው አገልግሎት ሲያብራራ ነው፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ ክርስቶስ ነፃ አውጪያችን መሆኑን አዲስ ኪዳን ያስተምራል ምክንያቱም እርሱ ወደ ምድር በመጣ ወቅት የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ሆኗልና ነው፡፡
ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው የእግዚአብሔር ህዝብ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍርድ ስር በወደቀበት ወቅት መሆኑን ክርስቲያኖች ደጋግመው ይስቱታል፡፡ እስራኤል የብሉይ ኪዳንን ቃል ኪዳን በጉልህ በመተላለፏ ምክንያት፣ በ586 ዓ.ዓለም፣ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ደመሰሱ እናም የእስራኤል ህዝብ ከዚያን በኋላ ሙሉ በሙሉ ከውጪ ወራሪዎች ጫና ሊላቀቅ አልቻለም፡፡ ሆኖም ነቢዩ ኤርምያስ እግዚአብሔር ወደፊት አዲስን ኪዳንን በመመሥረት ህዝቡን ከስደት እሳት እንደሚታደግ ተነበየ፡፡ በኤርምያስ 31 ቁጥር 31 ውስጥ ነቢዩ እንዲህ ያውጃል፡
እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር (ኤርምያስ 31፡31)
አብዛኞቹ ክርስቲያኖች እንደሚያውቁት፣ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው የአዲሱ ኪዳን መካከለኛ ሆኖ እንደሆነ አዲስ ኪዳን ያስተምራል፡፡ ኢየሱስም ራሱ በመጨረሻው እራት ወቅት ለደቀመዛሙርቱ ሲናገር ይህ ተግባር የእርሱ ስለመሆኑ እውቅና ሰጥቷል፡፡ በሉቃስ ምዕራፍ 22 ቁጥር 20 እንደምናነብበው፣ እንዲህ ብሏቸዋል፡
እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፦ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። (ሉቃስ 22፡20)
ልክ ኖህ የመለኮታዊ ቃል ኪዳን መካከለኛ በመሆን ከፍርድ እንዳዳነ ሁሉ፣ ኢየሱስም በመንግሥቱ ምሥረታ ወቅት በመስቀል ላይ ባፈሰሰው፣ ደሙ አማካይነት የአዲስ ኪዳን መካከለኛ በመሆን በእርሱ ያመኑትን ከፍርድ አድኗል፡፡
ድል
አዲስን ቃል ኪዳን ከማምጣት በተጨማሪ፣ የኢየሱስ ምድራዊ አልግሎት በቅዱስ ጦርነት ድል የመንሳትንም ምስጢር ፈጽሞታል፡፡ ቅዱስ ጦርነት ከጥፋት ውሃ በኋላ የተዘረጋው አዲስ ሥርዓት አካል እንደሆነ ሙሴ ትኩረት አድርጎበታል፡፡ ያንንም ያደረገው እስራኤል ከነዓንን ለመውረስ ወደፊት መግፋት የሚጠበቅባት መሆኑን አዲሱ የዓለም ሥርዓት እንደሚደነግግና ድል ማድረጋቸውም አይቀሬ መሆኑን ሊያረጋግጥላቸው ነው፡፡ በተነፃፃሪም፣ በቆላስያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 15 ውስጥ በመንግሥቱ ምሥረታ ወቅት ክርስቶስ የተቀዳጀውን ድል ጳውሎስ እንዴት እንደገለጠው አድምጡ፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። (ቆላስያስ 2፡15)
በዚህ ስፍራ እንደምንመለከተው፣ ኢየሱስ በመጀመሪያ መምጣቱ የተቀዳጀው መንፈሳዊ እንጂ ፖለቲካዊ ድል አይደለም፡፡ የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በእርሱ ዘመን ዓለምን ይገዙ በነበሩ የክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ላይ ድልን አብስሯል፡፡ ልክ ያህዌ በጥንታዊቷ የባቢሎን ከተማ ላይ እና በኋላም በታላላቆቹ የከነዓናውያን ከተሞች ላይ የደመቀ ድልን እንደተቀዳጀ ሁሉ የእርሱም የቤዛነት ሥራ በአደባባይ ሽንፈታቸው እንዲታወጅ አድርጓል፡፡
በዚህ መሠረት፣ ኢየሱስ በአዲሱ ኪዳኑ ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ በሞቱና በትንሣዔው አማካይነት በክፉው መንፈሳዊ የጨለማ ኃይላትም ላይ ድልን ተቀዳጅቷል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች የክርስቶስን የአደባባይ አገልግሎት የሚመለከቱት ከብዙ ዘመናት በፊት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ተስፋ የተነገረለት የፍፃሜ ድል ጅማሬ እንደሆነ አድርገው ነው፡፡
አዲስ ኪዳን የዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 መሪ ሃሳቦችን ከኢየሱስ የመጀመሪያ መምጣት ጋር ብቻ በማዛመድ አያበቃም፡፡ ከመንግሥቱ ዕድገት ማለትም አሁን እኛ ከምንኖርበት ዘመን ጋርም ያዛምዳቸዋል፡፡
ዕድገት
አዲስ ኪዳን በክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣትና በሁለተኛው መምጣቱ መካከል ያለውን ወቅት የሚገልጠው ከሙሴ የፍጥረተ ዓለም ታሪክ የመጨረሻ ምዕራፎች ጋር በሚዛመዱ ቢያንስ በሁለት መንገዶች ነው፡፡ እነዚህ አመለካከቶች በክርስትና ሕይወት ውስጥ ጥምቀትና መንፈሳዊ ውጊያ ካላቸው ጠቀሜታ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን የክርስትናን ሕይወት ስንኖር፣ ከኖህ የጥፋት ውሃና ከጥፋት ውሃው በኋላ ከተዘረጋው አዲስ ስርዓት ጋር መተዋወቅ እንጀምራለን፡፡
ጥምቀት
በአዲስ ኪዳን በተለይ አንድ ጥቅስ ጥምቀትን ከኖህ ዘመን የነፃ ማውጣት ጎርፍ ጋር አያይዞ ይገልፀዋል፡፡ በ1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 20 እስከ 22 ድረስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ምን እንደፃፈ አድምጡ፡
ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።
ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤
እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ። (1ኛ ጴጥሮስ 3፡20-22)
ጴጥሮስ በዚህ አስደናቂ ምንባብ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው በመንግሥቱ እድገት ወቅት የሚለማመደውን ድነት በቀጥታ ከኖኅ የጥፋት ውሃ ጋር ያገናኘዋል፡፡ ኖኅና ቤተሰቡ በውሃ የዳኑ መሆናቸውን በመጥቀስ ይጀምራል፡፡ በውሃ አማካይነት መዳናቸው ለሰው ዘር በሙሉ ወደታደሰ የበረከት ዓለም የሚገባበትን መንገድ ከፍቷል፡፡
በተጨማሪም ጴጥሮስ በጥምቀት ላይ ትኩረት በማድረግ በኖኅ ዘመን የጥፋት ውሃና በክርስትና ሕይወት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት መመሥረቱንም ልብ በሉ፡፡ በኖኅ ዘመን የነበረው ውሃ ክርስቲያኖች የሚጠመቁበትን ውሃ በተምሳሊትነት ያመለክታል ይላል፡፡ በዚህ ትምህርት እንደተመለከትነው፣ በኖኅ ዘመን የነበረው ውሃ ዓለምን ከአሰቃቂው እርኩሰት እንዳፀዳ እና የአዲስ ጅማሬን ጎዳና እንደከፈተ ሁሉ የሙሴም በኤርትራ ባሕር መሻገር የግብፅን አምባነናዊ ድርጊት በማስወገድ ለእስራኤል አዲስ ጅማሬን አስገኝቷል፡፡ በተመሳሳይም መንገድ፣ የጥምቀትም ውሃ አማኞች ከኃጢአት መንፃታቸውን የሚያመለክት ሲሆን በክርስቶስ የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት ጅማሬም ያፀናላቸዋል፡፡
ግን በዚህ ስፍራ 1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 21 ጥምቀት ያድናል ብሎ የገለጠው ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የበጎ ሕሊና ልመና እንደሆነ አድርጎ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ በሌላ አባባል በጥምቀት ወቅት በውሃ ውስጥ ተነክሮ መውጣት ብቻውን ማንንም አያድንም፡፡ ይልቁኑ፣ ጥምቀት በክርስቶስ በማመን ልብ ይቅርታ እንዲቀበልና እንዲነፃ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ልመና ከሆነ እርሱ ድነትን በተምሳሊትነት ያመለክታል፡፡ ስለዚህ አዲስ ኪዳን በኖኅ ዘመን የነበረውን የማንፃት ውሃ በመንግሥቱ ዕድገት ወቅት እያንዳንዱ ሰው በሚያድን እምነት ወደ ክርስቶስ ሲመጣ፣ የመንፃት ተምሳሊት በሆነው ጥምቀት ውስጥ ሲያልፍና ወደ አዲስ ሕይወት ከሚመጣበት ልምምድ ጋር ሲያገናኘው፣ ተምሳሊትነቱ ኖኅ በጥፋት ውሃ አማካይነት ወደ አዲስ ዓለም እንደገባው ዓይነት ይሆናል ማለት ነው፡፡
መንፈሳዊ ውጊያ
ሆኖም፣ እንደተመለከትነው፣ የሙሴ የፍጥረተ ዓለም ታሪክ በኖኅ ዘመን የነበረው ውሃ የሰውን ዘር ነፃ አውጥቶ ወደ ቅዱስ ጦርነት ከትቶታል ይለናል፡፡ ሙሴ ቀድሞውኑ ወደ እነዚህ እውነታዎች ትኩረትን የሚስበው፣ እስራኤላውያን ከነዓንን ለመውረስ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ሊያፀናላቸው ነው፡፡ በተመሳሳይም ሁኔታ፣ አዲስ ኪዳን ይህንን አስተምህሮ የሚያዛምደው ከመንግሥቱ ዕድገት ጋር ማለትም እያንዳንዱ አማኝ ከሚጋፈጠው መንፈሳዊ ውጊያ ጋር ነው፡፡ እስኪ ይህንን ጉዳይ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 11 እና 12 ውስጥ እንዴት እንዳስቀመጠው እናዳምጥ፡
የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።
መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። (ኤፌሶን 6፡11-12)
ይህና ሌሎችም የአዲስ ኪዳን ምንባቦች በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ከክፉው ጋር እንደሚዋጉ በግልፅ ያስተምራሉ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን፣ ዛሬ በርካታ ክርስቲያኖች ይህን የመንፈሳዊ ሕይወት አድማስ የራሳቸው አያደርጉትም፣ ሙሴን ይከተሉ የነበሩ አብዛኞቹ እስራኤላውያን ከነዓንን ላለመውረስ እንዳፈገፈጉ ሁሉ ማለት ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን አስተምህሮ ግን ግልፅ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ልንሳተፍ ይገባናል፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 6 ቁጥር 13 እንዳስቀመጠው፡
ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። (ኤፌሶን 6፡13)
የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ከለበስን፣ በመንፈሳዊ ውጊያችን ድልነሺዎች እንሆናለን፡፡
አዲስ ኪዳን በጥፋት ውሃ አማካይነት ኖኅ መዳኑን እኛ በጥምቀት ምሳሌነት ከመዳናችን ጋር እንዳገናኘው አይተናል፣ በተጨማሪም ጥንታዊው ዓለም ወደ ውጊያ እንደገባ ሁሉ፣ የክርስቲያን ጥምቀትም በዕለት ከዕለት ሕይወታችን ወደምንጋፈጠው መንፈሳዊ ውጊያ አስገብቶናል፡፡
ፍፃሜ
አዲስ ኪዳን የፍጥረተ ዓለም ታሪክን የመጨረሻ ምዕራፎች ከመንግሥቱ ምሥረታና ዕድገት ጋር ባዛመደባቸው መንገዶች ብርሃን ፈንጣቂነት፣ የመንግሥቱ ፍፃሜም በኖኅ የጥፋት ውሃና በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ መገለጡን ማረጋገጥ አያስገርምም፡፡
የፍፃሜው መቅሰፍት
የአዲስ ኪዳን ጸሐፍት ይህንን ትስስር ያመለከቱት ክርስቶስ በክብር ተመልሶ የሚመጣበትን ጊዜ የፍፃሜው መቅሰፍትና የፍፃሜው ጦርነት የሚካሄድበት መሆኑን በመግለፅ ነው፡፡ በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ውስጥ በኖኅ ጥንታዊ የጥፋት ውሃና በክርስቶስ የክብር መመለስ መካከል ቀጥተኛ ትስስር እናገኛለን፡፡ ጴጥሮስ ከቁጥር 3 እስከ 6 የተናገረውን አድምጡ፡
በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤
እርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።
ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤
በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ (2ኛ ጴጥሮስ 3፡3-6)
ጴጥሮስ በዚህ ምንባብ የተፈጥሮ ሚዛን ተጠብቆ መዝለቁን ክርስቶስ ላለመመለሱ ማረጋገጫ አድርገው የሚያላግጡትን ሰዎች አርሟቸዋል፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሁሉ እንዳለ ይኖራል በማለት ያምናሉ፡፡ ዓለምን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከፈጠረበት ሁኔታ ያዛነፋት ነገር የለም፡፡ ምንም ነገር እስካልተለወጠም ድረስ፣ ሌላ አዲስ ነገር ሊመጣ አይችልም ይላሉ፡፡
ጴጥሮስ ግን የሙሴን የኖኅ ጎርፍ ዘገባ በመጥቀስ ነገሩ በተቃራኒው መሆኑን አሳይቷል፡፡ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ዓለምን የፈጠረው ከውሃ ነበር፣ በኖኅ ዘመን ግን፣ ዓለም በጎርፍ ጠፋች፡፡ በዓለም ታሪክ ውስጥም ታላቁ መቅሰፍት ተከሰተ፡፡ እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን ጣልቃ በመግባት ዓለምን አጠፋ፡፡ በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 7 ጴጥሮስ የሰጠውን መደምደሚያ አድምጡ፡
አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። (2ኛ ጴጥሮስ 2፡7)
በቀላሉ ስናስቀምጠው፣ ጥንታዊው ዓለም በውሃ እንደጠፋ ሁሉ፣ አሁን ያሉት ሰማይና ምድር ደግሞ ክርስቶስ በፍርድ ቀን ሲመለስ ወደ ፍፃሜያቸው እንደሚመጡ ጴጥሮስ መከራከሪያውን ያቀርባል፡፡ በእርግጠኝነት፣ የዚህ ወቅቱ ፍርድ የሚፈፀመው በውሃ ሳይሆን በእሳት ነው፡፡ በመጨረሻዋ ቀን አግዚብሔር ዓለምን ስለ ኃጢአት ሲያጠፋ፣ ፍጥረተ ዓለሙን ሁሉ ያወድመዋል፣ ይህም በጥንታዊው ጎርፍ እንደሆነው ነው፡፡
በዚህ መንገድ፣ የክርስቶስን መመለስ ከኖኅ የጥፋት ውሃ ጋር እያስተያየን እንድንመለከተው አዲስ ኪዳን ያስተምረናል፡፡ በኖኅ ዘመን፣ ክፉዎች ተፈረደባቸው በፈለካዊ ውድመትም ከምድር ገፅ ተወገዱ፡፡ ከዚህም በላቀ መንገድ፣ ክርስቶስ በክብር ሲመለስ፣ አሁን የምናውቃት ዓለም በታላቅ መቅሰፍት ትጠፋለች፡፡ ክፉዎች ከምድር ይወገዳሉ በክርስቶስ ያመኑትም ሁሉ ወደ አዲስ ሰማይና ምድር ይገባሉ፡፡
የፍፃሜው ጦርነት
ግን፣ እንደተመለከትነው፣ በፍጥረተ ዓለም ታሪክ የተከሰተው የኖኅ ጎርፍ በእግዚአብሔር ሰዎችና በእግዚአብሔር ጠላቶች መካከል በተደረገ ግጭትና ጦርነት የታጀበ ነበር፡፡ ከዚህ ትስስር ጋር በሚጎዳኝ መንገድ፣ የክርስቶስም መመለስ የፍፃሜው ፈለካዊ ጦርነት ወቅት እንደሚሆን አዲስ ኪዳን ያስተምራል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ምእራፍ 19 ከቁጥር 11 እስከ 16 ስለ ክርስቶስ መመለስ የጻፈበትን መንገድ አድምጡ፡
ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም።
ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤
በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።
በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።
አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል።
በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት። የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው። (ራእይ 19፡11-16)
በዚህ አቡቀለምሲሳዊ ቋንቋን በተሞላ ራእይ ውስጥ፣ የክርስቶስ መመለስ ዓለም አቀፋዊ ጦርነት የሚካሄድበት ጊዜ እንደሚሆንና ክርስቶስ ራሱ በመገለጥ ጠላቶቹን ድል እንደሚያደርግ ዮሐንስ ያውጃል፡፡ ለድነታቸው በክርስቶስ ለታመኑ ሁሉ የዘላለማዊ ድል ክብር ተዘጋጅቶላቸዋል፣ እርሱን በተቃወሙት ላይ ግን ፍርድና ጥፋት ይሆንባቸዋል፡፡
የክርስቶስ መንግሥት ፍፃሜ እግዚአብሔር በክፋት ላይ የማያዳግመውን ድል የሚያፀናበት ጊዜ ስለ መሆኑ አዲስ ኪዳን እንደሚገልጥ ተመልክተናል፡፡ እግዚአብሔር መንግሥቱን በጠላቶቹ ላይ ለመመሥረት ዛሬም ቁርጠኛ ነው፡፡ ክፉዎች ይጠፋሉ በክርስቶስ ያመኑት የእግዚአብሔር ሕዝብ ደግሞ በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር በዘላላማዊ ደስታና ክብር ይኖራሉ፡፡
ማጠቃለያ
በዚህ ትምህርት ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 9 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 9 ድረስ ያለውን ተመልክተናል፡፡ በዚህ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል፣ ወደ ተስፋዪቱ ምድር በእርሱ መሪነት የሚጓዙት እስራኤላውያን ሊጓዙበት የሚገባውን ትክክለኛ አቅጣጫ ሙሴ ገልጦላቸዋል፡፡ የእነዚህን ምዕራፎች ስነ-ጽሑፋዊ ውቅር እና እስራኤላውያን ከነዓንን ለመውረስ በሚያደርጉት ጉዞ በልበ ሙሉነት እንዲገሰግሱ ለማበረታታት እንዴት እንዳቀነባበራቸው አይተናል፡፡ በተጨማሪም አዲስ ኪዳን እነዚህን መሪ ሃሳቦች ከክርስቶስ መንግሥት ሦስት እርከኖች ጋር እንዴት እንዳዛመዳቸውም አይተናል፡፡
በዚህ በወደቀ ዓለም ውስጥ ለክርስቶስ የመኖርን ተግዳሮትና ትግል ስንጋፈጥ፣ ከብዙ ዓመታት በፊት ሙሴ ለእስራኤላውያን ያስተላለፈውን መልእክት ልብ ልንል ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር በኖኅ አማካይነት የቀደመውን ዓለም እንዳዳነ ሁሉ፣ እኛንም በክርስቶስ፣ ከኃጢአት እድፈት አንፅቶናል፡፡ ሆኖም ክርስቶስ በፍፃሜው ለህዝቡ የመጨረሻውን ድል ይዞ እስኪመለስ ድረስ እየተጠባበቅን ሳለ ግጭትና ትግል ወዳለበት ጎዳናም አስገብቶናል፡፡ እስከዚያች ቀን ድረስ፣ እኛ የምንኖርባት ዓለም ፍፁም እንደማትሆን እናውቃለን ሆኖም ክርስቶስ በዓለም ላይ በሚያደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ እርሱን የምንከተለው ከሆነ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዝን እንደሆነ እናውቃለን፡፡
Continue reading the full transcript