በኢየሱስ እናምናለን
ትምህርት ሦስት
ነቢይ
We Believe in Jesus
Lesson Three
The Prophet
ተርጓሚ፡ እሸቴ በለጠ
ማውጫ
- መግቢያ
- ብሉይ ኪዳን
መመዘኛዎች
በእግዚአብሔር መጠራት
የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል
ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን
በመፈፀሙም ተአማኒነትንና ሥልጣንን መቀበል
ተግባር
ሥልጣን
ሥራ
ዘዴ
ተስፋ የሚደረገው/ ጥበቃ
ታሪካዊ እድገት
ቅድመ-ነገሥታት
የነገሥታት ዘመን
ግዞት
ተሃድሶ
ውሱን ትንቢቶች
- ምልዓት በኢየሱስ
መመዘኛዎች
በእግዚአብሔር መጠራት
የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል
ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን
በመፈፀሙ ተአማኒነትና እርግጠኝነት
ተግባር
ሥልጣን
ሥራ
ዘዴ
ተስፋ የሚደረገው/ ጥበቃ
የጌታ ድምፅ
እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ
የነቢይነት አገልግሎት ኅዳሴ
- ዘመነኛው ተዛምዶ
መጠነ ራእይ
የራእዩ ይዘት
ቅዱሳት መጻሕፍትን መፍታት
ለቅዱሳት መጻሕፍት መገዛት
- ማጠቃለያ
እናስተዋውቅዎ
የሰርድ ሚሊኒየም ሚኒስትሪ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1997 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡ ይህ አገልግሎት አትራፊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎችን ለመላው ዓለም በነጻ ለማዳረስ የተቋቋመ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ጤናማ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ - መሠረት ያለው ክርስቲያናዊ የአመራር ስልጠና ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት፣ ምንም ዓይነት የስልጠና ግብዓቶች የማግኘት እድል ለሌላቸው ክርስቲያን መሪዎች የሴሚነሪ ሥርዓተ-ትምህርቶችን በማዘጋጀት እናሰራጫለን፡፡ ሰርድ ሚሊኒየም ሚኒስትሪ በመላውም ዓለም ለሚገኙ ክርስቲያን መሪዎችና ፓስተሮች የተመጣጠነ ዋጋ ያለው፣ በደጋፊዎች የሚታገዝ፣ ለተጠቃሚው ምቹ፣ በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች የታገዘ ሥርዓተ-ትምህርት በአምስት ቋንቋዎች (በእንግሊዝኛ፣ በስፓኝ፣ በራሺያኛ፣ በማንዳሪን ቻይንኛ እና በአረብኛ) አስተርጎሞ አሰራጭቷል፡፡ ሁሉም ትምህርቶች የተጻፉት፣ የተዘጋጁት እና የታተሙት በአገልግሎቱ ውስጥ ሲሆን በ The History Channel©. In 2009 ካሉት ጋር በቅርፅና በጥራት ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ የሰርድ ሚሊኒየም ሥራ ማለትም ጥራት ላለው የማስተማሪያና የአኒሜሽን የቪዲዮ ፕሮዳክሽን ሥራዎቹ ሁለት የቴሊ አዋርድ ሽልማቶችን ተቀብሏል፡፡ የማስተማሪያ ግብዓቶቻችን በዲቪዲ፣ በህትመት፣ በኢንተርኔት ማስተላለፊያ ዘዴዎች፣ በሳተላይት የቴሌቪዥን ስርጭት፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን ስርጭቶች ለማቅረብ በሚያስችል መልክ የተቀረፁ ናቸው፡፡
ስለ አገልግሎታችን የበለጠ መረጃ ለማግኘትና እንዴት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችሉ ማወቅ ከፈለጋችሁ፣ www.thirdmill.org የተሰኘውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡፡
- መግቢያ
ሰዎች ችግር ሲያጋጥማቸው አሊያም አስፈላጊ ውሳኔዎችን ሊወስኑ ሲፈልጉ፣ ምክር ፍለጋ ፊታቸውን ወደሌሎች ይመልሳሉ፡፡ ጉዳዩ ትንሽም ይሁን የተለመደ፣ ቤተሰቦቻቸውን አለበለዚያም ጎረቤቶቻቸውን ያማክራሉ፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ከበድ ያለና፣ ረዘም ላለ ጊዜ የሚዘልቅ ውጤት/ፋይዳ የሚኖረው ከሆነ ግን፣ ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ሊነግራቸው የሚችል ሥልጣን የተሰጠውን እውነተኛ አማካሪ የሆነን ሰው ሰዎች ይፈልጋሉ፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ታሪክም ውስጥ፣ እግዚአብሔር በነቢያቱ አማካይነት ይህንን የመሰለውኝ አስተማማኝ ምክር ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ እነዚህም ወንዶችና ሴቶች የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳኖች ከሕዝቡ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ በሥልጣን ተግባራዊ ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡
በኢየሱስ እናምናለን በሚል ዐቢይ ርዕስ በተከታታይ ከምናቀርባቸው ትምህርቶቻችን ውስጥ ይህኛው ሦስተኛውና “ነቢይ” ብለን ርዕስ የሰጠነው ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት፣ ኢየሱስ የነቢይነትን አገልግሎት እንዴት ወደሙላት እንዳመጣና፣ የአግዚአብሔርንም ቃል ኪዳን በሕይወታችን እንዴት በሥልጣን ተግባራዊ እንዳደረገ እንዳስሳለን፡፡
ቀደም ባለው ትምህርት፣ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን መንግሥቱን ስላስተዳደረባቸው ሦስት ቢሮዎች ማለትም፡ የነቢይነት፣ ክህነትና የንጉሥነት ቢሮዎች አንስተናል፡፡ በዘልማድ አዲስ ኪዳን ብለን በምንጠራው፣ የእግዚአብሔር መንግሥት የመጨረሻ እርከን ውስጥ፣ ሦስቱም ቢሮዎች በክርስቶስ ምልዓታቸውን አግኝተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ በየታሪክ ዘመናቱ የእነዚህን ቢሮዎች ጠቀሜታና አገልግሎት ማጥናታችን በዘመኑ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተግባር የገለጠበትንና የእርሱ ታማኝ ተከታዮች የሚያገኙትን በረከትና ያሉባቸውን ግዴታዎች መረዳት እንድንችል ያግዘናል፡፡
ብዙ ሰዎች “ነቢይ” የሚለውን ቃል ሲሰሙ፣ የወደፊቱን ስለሚነግራቸው አንድ ሰው ወደማሰቡ ያዘነብላሉ፡፡ ይህም ነገር ለአብዛኛዎቹ ክርስቲያኖችም እንኳን እውነት ሆኖ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነቢያትም አንዳንድ ጊዜ የወደፊቱን የሚናገሩ ቢሆንም፣ ዋናው የአገልግሎት ትኩረታቸው ግን እርሱ አልነበረም፡፡ በመሠረታዊነት፣ የእግዚአብሔር ነቢያት የእርሱ አምባሳደሮች ናቸው፡፡ አገልግሎታቸውም፣ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳኖች ማብራራትና ህዝቡ ለእርሱ ታማኝ እንዲሆኑ ማበረታታት ነው፡፡ የኢየሱስ የነቢይነት አገልግሎት ማዕከልም ይኸው ነበር፡፡
ከዚህ የነቢይነት አገልግሎት ተግባራት መረዳታችን በተጓዳኝ፣ ነቢይን እንዲህ እንፈታዋለን፡
የእግዚአብሔርን ቃል የሚያውጅ፣ ኃጢአት ስለሚጠብቀው ፍርድ የሚያስጠነቅቅ፣ ለእግዚአብሔርም የሚገባውንና ወደ በረከት የሚደርሰውን አገልግሎት እንዲሰጡ በማበረታታት ቃሉ በሰዎች ሕይወት ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ የሚያመለክት፣ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን አምባሳደር ነው፡፡
በዚህ ትምህርታችን ከኢየሱስ የነቢይነት አገልግሎት ሃላፊነት ጋር የሚዛመዱ ሦስት ርዕሶችን እንዳስሳለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ለእርሱ የነቢይነት አገልግሎት ብሉይ ኪዳናዊ ዳራውን እንመረምራለን፡፡ ሁለተኛ፣ በኢየሱስ ሙላቱን ስላገኘው የነቢይነት ቢሮ አዲስ ኪዳናዊ አስተምህሮ እንዳስሳለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ የኢየሱስ የነቢይነት አገልግሎት በዘመናችን የሚኖረውን ተዛምዶ እንመለከታለን፡፡ ስለ ኢየሱስ የነቢይነት አገልግሎት ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ በመመልከት እንጀምር፡፡
- ብሉይ ኪዳን
መቼም ይሁን መቼ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የእኛ ነቢይ ስለመሆኑ ስናስብ፣ እግዚአብሔርንና ቀልኪዳኑን ያገለገለ የመጀመሪያው ነቢይ እንዳልነበረ ማሰብ ጠቃሚ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ ዘመናት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች የጌታ ነቢያት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኃይልና በሥልጣን ከኢየሱስ ጋር እኩል አልነበሩም፡፡ ለእግዚአብሔር የሰጡት አገልግሎት ግን ኢየሱስ መጥቶ ያሟላውን የመንግሥቱን ቢሮ በጥላነት ያመለክቱ ነበር፡፡ እንግዲያው፣ ኢየሱስ እንደ ነቢይ ያደረገውን አገልግሎት መረዳት ከፈለግን፣ ከእርሱ ቀድመው የመጡ ነቢያትን አስቀድመን መመልከት ይተቅመናል፡፡
የኢየሱስን የነቢይነት አገልግሎት ቢሮ ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ ውይይታችንን በሦስት ከፍለን እንመለከተዋለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የነቢይነት አገልግሎት መመዘኛዎችን እናነሳለን፡፡ ሁለተኛ፣ የነቢያትን ተግባር እንመለከታለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ ብሉይ ኪዳን ከነቢያት ቢሮ ይጠብቅባቸው የነበረውን እንቃኛለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የነቢያት አገልግሎት መመዘኛዎችን እንመልከት፡፡
መመዘኛዎች
ቀደም ብለን እንዳመለከትነው፣ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን አምባሳደሮች ወይንም መልእክተኞች ነበሩ፡፡ በቃል ኪዳኖቹም፣ እግዚአብሔር ራሱን የሕዝቡ ታላቅ ንጉሥ አድርጎ የገለጠ ሲሆን፣ ነቢያቶቹ ደግሞ በሰማይ ያለው መንበሩ መልእክተኞች ወይንም ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደሮች ሆነው አገልግለዋል፡፡ የእግዚአብሔርንም ቃል ለህዝበ እስራኤልና ለተለያዩ ሌሎች መንግሥታትም ያመጡ ሲሆን፣ እግዚአብሔርንም እንደ ንጉሣቸው ታማኝ እንዲሆኑለት ተማፅነዋል፡፡ እርግጥ ነው፣ በእስራኤል ዙሪያ ያሉ ነገሥታትም የእገዚአብሔርን እውነተኛ ነቢያት የሚቀናቀኑ አስመሳይ ነቢያት ነበሯቸው፡፡ እነዚህ የሃሰት ነቢያት ግን አታላዮች፣ የአጉል እምነት አራማጆች ሲሆኑ ሃሰተኛ አማልክቶቻቸውንም ለመግለጥ አጋንንታዊ ኃይላትን ይጠቀማሉ፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ ዘመናት ውስጥ፣ በእስራኤልና በዙሪያቸው በሚገኙ ሌሎች አገሮች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የሃሰት ነቢያት፣ በአብዛኛው እንቅስቃሴያቸው ያደርጉ፣ ይናገሩ፣ ያታዩና ይገለጡ የነበሩት ልክ እውነተኞቹን ነቢያት በማስመሰል ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ግን እኔ እንደማስበው፣ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከሌሎቹ ራሳቸውን እንደ እውነተኛ ነቢያት የሚለዩበት ምክንያት በራሱ በጌታ ስም የሚናገሩ መሆናቸው መሆኑን የነገሥታትን፣ የመዋዕለ ዜናንና ሌሎች የትንቢት መጻሕፍትን ስታነቡ ትመለከታላችሁ፡፡ በራሱ በጌታ ስም ሲናገሩም፣ እግዚአብሔር በቃሉ የሚናገረውን ነገር በፍፁም አይተላለፉም፡፡ ሌሎች እውነተኛ ነቢያትም የተናገሯቸውንም ነገሮች አይተላለፉም እናም በዚህ መንገድ ራሳቸውን ይለያሉ፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ፣ እጅግ ወሳኝ የሆነው ሌላ መለያቸው ደግሞ፣ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የነበሩ ሰዎች በወቅቱ ከነበረው እውቅና ካገኘ የእምነት አቋም በተቃራኒው ይቆሙ የነበሩ መሆናቸው ሲሆን፣ እንደ አለመታደል ሆኖ በተለይም በሰሜናዊው እስራኤል፣ ነቢያት ደመወዝተኛ (ምንደኛ) የነበሩበት ዘመን ነበር፡፡ በትንቢተ አሞጽ ምዕራፍ 7 ላይ አሞጽ “እኔ ነቢይ ወይንም የነቢይ ልጅ አይደለሁም” በማለት በሰሜናዊው እስራኤል ለሚኖረው ለሊቀ ካህኑ ለአሜስያስ ሲነግረው፣ በንጉሡ ወይንም በሊቀ ካህኑ የደመወዝ መክፈያ ሰነድ (ፔሮል) ውስጥ ያልነበረ መሆኑን ሲያመለክት ነበር፡፡ “ነቢይ አይደለሁም” ማለቱ ባለሙያ ነቢይ አይደለሁም ማለቱ ነበር፡፡ “የነቢያትም ልጅ አይደለሁም” ሲልም፣ “በነቢያት ትምህርት ቤትም አልተማርኩም፡፡ ስለዚህም መናገር የሚገባኝን አንተው ንገረኝ” ማለቱ ነው፡፡ አሞጽ ለአሜስያስ ይህንን ያለበት ምክንያት አሜስያስ “እዚህ በሰሜን የምንኖረውን አታውከን፣ ወደ ቤትህ ሂድ፣ ወደ ደቡብህ ተመለስ” ብሎት ስለነበር ነው፡፡ አሞጽም መልሶ፣ “ይህንን ላደርግ አልችልም ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዳደርገው አዝዞኛልና” ሲል ነገረው፡፡ እንደ ኤርምያስ፣ ሚክያስ እና ሌሎችም በነገሥታቱ የደመወዝ መቀበያ መዝገብ ውስጥ የነበሩትን ሃሰተኛ ነቢያቶችን ፊት ለፊት ይጋፈጧቸው እንደነበር በተደጋጋሚ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለ ነቢያት ከማኅበረሰባዊ ግንኙነት አንፃር የምንናገረው አንድ ነገር ቢኖር፣ በነገሥታት የደመወዝ መክፈያ መዝገብ ውስጥ ያልነበሩ መሆናቸውን ነው፡፡ በካህናቱም የደመወዝ መቀበያ መዝገብም ውስጥ አልሰፈሩም፡፡ በምድር ላይ ስለሚፈፀመው ግፍ፣ ወንጀልና ክፉ ድርጊት ሁሉ የእግዚአብሔር ምስክር ሆነው የሚቆሙና በነገሥታትና በካህናትም እንግልት ይደርስባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ [ዶ/ር ሪቻርድ ኢል. ፕራት፣ ትንሹ]
በርካታ ሃሰተኛ ነቢያት በሚገኙበት ዓለም ውስጥ፣ የእግዚአብሔርን እውነተኛ ነቢያት ከሃሰተኞቹ ነቢያት መለየት የመቻሉ ነገር ለእስራኤላውያን እጅግ ወሳኝ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር እውነተኛ ነቢያት የሚለዩበትን መመዘኛ በትክክል አስቀምጧል፡፡
እነዚህም መመዘኛዎች ሙሴ እንዲህ ብሎ በጻፈበት በዘዳግም ምዕራፍ 18 ከቁጥር 17 እስከ 22 ባለው ክፍል ውስጥ ተዘርዝረዋል፡
እግዚአብሔርም አለኝ፦ የተናገሩት መልካም ነው |
ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል |
በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ። |
ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል። |
በልብህም። እግዚአብሔር ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ |
ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው። |
በዚህ ምንባብ፣ የእግዚአብሔር እውነተኛ ነቢያት የሚለዩባቸውን ቢያንስ አራት መመዘኛዎችን እንመለከታለን፡፡ በዚህ ስፍራ ሙሴ እንዳስተማረው፣ እውነተኛ ነቢያት በእግዚአብሔር የተጠሩ ናቸው፡፡ ለህዝቡ የሚናገሩት የእግዚአብሔር ቃል ይሰጣቸዋል፡፡ በትዕዛዛቱም መሠረት በስሙ በመናገር ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝት ይገልፃሉ፡፡ በመልእክታቸውም መፈፀም የአገልግሎታቸው እውነተኝነት ይረጋገጣል፡፡
የብሉይ ኪዳን ነቢያት መመዘኛ ዳሰሳችን ሙሴ በጠቀሳቸው አራት መመዘኛዎች ላይ ያተኩራል፡፡ በመጀመሪያ፣ እውነተኛ ነቢያት በእግዚአብሔር የተጠሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ሁለተኛ፣ የሚናገሩት የእግዚአብሔር ቃል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ሦስተኛ፣ እንደ ትዕዛዛቱ ብቻ በመናገር ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ይገባቸዋል፡፡ አራተኛ ደግሞ፣ አገልግሎታቸውም በመልእክታቸው መፈፀም ይረጋገጣል፡፡ እውነተኛ ነቢያት በእግዚአብሔር የተጠሩ የመሆናቸውን እውነታ በማስቀደም፣ እያንዳንዳቸውን መመዘኛዎች በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
በእግዚአብሔር የተጠሩ
በብሉይ ኪዳን፣ እግዚአብሔር በርካታ ሰዎችን በነቢይነት እንዲያገለግሉት ጠርቷል፡፡ ይህም ጥሪ ግብዣ አይደለም፤ የበላይ (የፍርድ ቤት) መጥሪያ ዓይነት መለኮታዊ ጥሪ ነው፡፡ መለኮታዊው ንጉሥ፣ እግዚአብሔር፣ ከዜጎቹ አንዱን የእርሱ አምባሳደር ሆኖ እንዲያገለግለው ያዝዘዋል፡፡ ብሉይ ኪዳንን በምናነብበት ጊዜ ሁሉ ስለ ነቢያት ጥሪ ተመዝግቦ የምናገኘው ይህንኑ መለኮታዊ ትዕዛዝ ነው፡፡
ለአብነት ያህል፣ በሕዝቅኤል ምዕራፍ 2 ቁጥር 1 እና 2 የተጠቀሰውን የሕዝቅኤል ጥሪ ተመልከቱ፡
እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእግርህ ቁም እኔም እናገርሃለሁ አለኝ። |
በተናገረኝም ጊዜ መንፈስ ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገረኝንም ሰማሁ። |
በዚህ ስፍራ፣ እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን በፊቱ እንዲቆም ሲያዝዘውና ተልዕኮውንም ሲሰማ፣ ሕዝቅኤል እንዲታዘዝ የሚያስችለውንም የእርሱን መንፈስ ልኮለት ነበር፡፡ የነቢይ ጥሪ እግዚአብሔር የህዝቡ ሰማያዊ ንጉሥ መሆኑ የሚረጋገጥበት የእግዚአብሔር ባለሥልጣናዊ ምርጫ ማረጋገጫ ነው፡፡
እግዚአብሔር በተደጋጋሚ እነዚህን ነቢያዊ ጥሪዎች ያቀርብ የነበረው ለነቢያቱ በቀጥታ የነበረ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም በግልጽ በሚሰማ ድምፅ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሳሙኤልን በ1ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 3፣ ኢሳያስን በኢሳያስ ምዕራፍ 6፣ አሞጽን በአሞጽ ምዕራፍ 7 እና ኤርምያስን በኤርምያስ ምዕራፍ 1 ላይ በቀጥታ ጠርቷቸዋል፡፡
በሌላ ወቅት ደግሞ፣ እግዚአብሔር ነቢያትን በሌሎች በኩል ይልካቸዋል፣ አንዱ ነቢይ ሌላውን እንዲጠራው በማዘዝ ተግባራዊ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ፣ በ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 19 ቁጥር 16 ላይ፣ እግዚአብሔር ኤልያስን የእርሱ ተከታይ የሆነውን ኤልሳዕን እንዲቀባው እግዚአብሔር አዝዞታል፡፡ ይህ የውክልና ጥሪ በነቢያት ጉባኤ ላይ ወይንም በነቢያት ልጆች ላይ (አነርሱም በመለኮታዊ ጥሪ በነቢይነት አገልግሎት የተሰማሩ ቡድኖች ናቸው) የብርሃን ፋና ፈንጥቆ ነበር ይህንንም በ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 20 እና በ2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 2 ላይ እናገኘዋለን፡፡ ጥሪው በቀጥታ ለነቢዩም ይምጣ፣ ወይንም ከእግዚአብሔር ሥልጣን በተሰጠው አገልጋይም በኩል ይሁን፣ የነቢይ ጥሪ የሚመጣው ከጌታ ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን መልካም ምኞት ቢኖረውም፣ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ቢሆንም ወይንም የእግዚአብሔርን ቃል ቢያውቅም፣ ያለዚህ መለኮታዊ ጥሪ፣ ማንም ሰው ነቢይ መሆን አይችልም፡፡
የብሉይ ኪዳን ነቢያት በእግዚአብሔር ከመጠራታቸውም ባሻገር፣ የሚናገሩት የእግዚአብሔር ቃል የተሰጣቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል የተሰጣቸው መሆኑ
ነቢያት እግዚአብሔር ያዘዛቸውን የትኛውንም ነገር መናገር ይችሉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አብርሆትን ይሰጣቸው ነበር፡፡ እውነተኛ ነቢያት ከዚያ ውጪ ትንቢት ሲናገሩ የሚያደርጉት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ነገር ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተለያዩ ነቢያት ይናገሩ የነበረበትን መንገድ ስንመለከት፣ አብርሆተ መለኮት ማለት የሚናገሩትን ነገር መቆጣጠር አይችሉም ማለት አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ በተቃራኒው ግን፣ መንፈስ ቅዱስ የነቢያቱን ስብዕና እና አመለካከት በመጠቀም የማይሻረውን ትንቢታዊ መልእክቱን በእነርሱ ውስጥ ያስተላልፍ ነበር፡፡ በዚህም ረገድ፣ ትንቢታዊው አብርሆት ከሌሎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት አብርሆት ጋር ፍፁም አንድ ነው፡፡
ጴጥሮስ ነቢያትን እንዴት መንፈስ ቅዱስ እንደነዳቸው በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 20 እና 21 ላይ የተናገረውን አድምጡ፡
ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ |
ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ። (2ጴጥ 1፥20-21) |
በዚህ ስፍራ እንደምንመለከተው፣የብሉይ ኪዳንን እውነተኛ ነቢያት ቃል የሚወስነው መንፈስ ቅዱስ ነበር፡፡ ይህም ቃሎቻቸው ሥልጣን ያላቸውና የማይሻሩ ለመሆናቸው ዋስትናን ይሰጣል፡፡
መንፈስ ቅዱስ በወቅቱ ሊጠቀምበት በፈለገው ነቢይ ስብእናና አመለካከት አልፎ ይሠራል፡፡ እኔ እንደምገምተውም ትውፊታዊ የሆነውን ይህንን መረዳት በነገረ-መለኮታዊ መንገድ እንረዳው ብንል “ሕያው መነዳት” ይህም ማለት እግዚአብሔር በባሪዎቹ፣ በነቢያቶቹ፣ አልፎ ሲሠራ ስብእናቸውን በመጠቀም፣ ያላቸውን የየራሳቸውን አተያይ እና የእነርሱን ትምህርት በመጠቀም ሁሉን ለእርሱ ዓላማ ያውለዋል ማለት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደምገምተው እግዚአብሔር ሰብዓዊ የሆኑትን፣ ምድራዊና ቁሳዊ ነገሮች ለራሱ ዓላማ በመቀደስ፣ በራሱ መንገድ የሚጠቀምባቸው መሆኑን የሚያስተምረውን ትምህርተ ቅድስና በማንሳት ለነቢያትም ይህንኑ አድርጓል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ ይህንን ካልን በኋላ ግን፣ በትንቢታዊ ጽሑፎች ውስጥ አንድ የምታገኙት ነገር አለ፡፡ ይህም አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለነቢያቱ ቃል በቃል የሚናገሩትን ሲሰጣቸውና “ሂድና ለህዝብህ እንዲህ ብለህ ተናገር” ሲላቸው እነርሱም ማለትም፡ ኢሳያስ ወይንም ኤርምያስ ወይንም ሕዝቅኤል በቀጥታ ሄደው ያንኑ ሲናገሩ እናገኛለን፡፡ እንግዲያው፣ በነቢያት ጽሑፎች ውስጥ እግዚአብሔር ነቢያቱን ቃል በቃል እንዲናገሩ የሚያዝባቸው ነጥቦች እንደነበሩ የምንመለከት ሲሆን፣ በተመሳሳይ መንገድም ደግሞ፣ እግዚአብሔር ማንነታቸውን ይጠቀም ነበር፡፡ ይህንንም ሲያደርግ ትንቢታዊ መልእክቱን ለጥንታዊቷ እስራኤልም ሆነ ለአሁኗ ቤተ ክርስቲያን ሲያስተላልፍ ስብዕናቸውን ሳይጫን ያስተላልፍ እንደነበረ እንገነዘባለን፡፡ [ዶ/ር ማርክ ጊግኒሊት]
ሦስተኛው የብሉይ ኪዳን ነቢያት መመዘኛ ትንቢቶቻቸው ከእርሱ ሕግጋት ጋር እንዲስማሙ በማድረግ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆናቸው ነው፡፡
ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑ
ምንም እንኳን ነቢያት ቃል በቃል ከእግዚአብሔር መልእክት ባይቀበሉም፣ ደስ ያሰኛቸውን እንዲናገሩ ግን መንፈስ ቅዱስ ያልተገደበ ነፃነት አይሰጣቸውም ነበር፡፡ እግዚአብሔር እንዲናገሩ ያዘዛቸውን መናገር ብቻ ሳይሆን፣ ትንቢቶቻቸው ከእግዚአብሔር ቀደምት መገለጥ፣ በተለይም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከተመዘገበው ጋር የሚስማማ መሆኑንም ሊያረጋግጡ ይገባቸው ነበር፡፡
ሙሴ በዘዳግም ምዕራፍ 13 ከቁጥር 1 እስከ 4 የተናገረውን አድምጡ፡
በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥ |
እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም፦ ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፥ |
አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ። |
አምላካችሁን አግዚአብሔርን ተከተሉ፥ እርሱንም ፍሩ፥ ትእዛዙንም ጠብቁ፥ ቃሉንም ስሙ፥ እርሱንም አምልኩ፥ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ። (ዘዳ13፥1-4) |
ሙሴ በዚህ ስፍራ በጣም ጠቃሚ ትምህርት አስተምሯል፡፡ ነቢይ ምንም ያህል ተአምራት ቢገለጥበት፣ የወደፊቱንም ቢናገር እንኳን፣ የሚናገራቸው ንግግሮች ከእግዚአብሔር ሕግጋት ጋር የሚተላለፍ ከሆነ ሊወገዝ ይገባል፡፡
ይህንኑ የሚመስል ተመሳሳይ አፅንኦት በሰቆቃወ ኤርምያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 13 እና 14 ላይ፣ በእስራኤል የሚኖሩ ሃሰተኛ ነቢያት ምድሪቱን ወደ አዘቅት እየነዷት ስለ መሆኑ እውነታ ሰቆቃውን ባሰማበት ስፍራ ላይ እንመለከተዋለን፡፡ እነዚህ ነቢያት “ኃጢአትን የማያጋልጡ” እንደነበሩ በዚህም የእግዚአብሔርን ሕግጋት የሚተላለፉትን የሚያጸድቁ እንደነበሩ ኤርምያስ ተናግሯል፡፡ ህዝቡ ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ፣ አለመታዘዝን ያበረታቱ ነበር፡፡ እናም በዚህ መንገድ፣ ሃሰተኛ ነቢያት መሆናቸውን ይገልጡ ነበር፡፡
በመጨረሻም፣ አራተኛው የብሉይ ኪዳን ነቢያት መመዘኛ ትንቢቶቻቸው በመፈጸማቸው ሊረጋገጥ የሚገባው መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት፣ ትንቢቶቻቸው እውን ሊሆኑ ይገባል ማለት ነው፡፡
በመፈፀሙ ተአማኒነትና እርግጠኝነት
በዘዳግም ምዕራፍ 18 ቁጥር 22 ሙሴ የተናገረውን አድምጡ፡
ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው። (ዘዳ 18፥22)
የአግዚአብሔር ነቢያት ቃሎች ሁሉ ሊተማመኑባቸው የሚገቡ ናቸው ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ የሚደገፉት በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ሲሆን፣ ባህርያቸውና ቃል ኪዳናዊ ተስፋዎቻቸውም በከፍተኛ ሁኔታ የታመኑ ነበሩ፡፡
እውነተኛ ትንቢቶች በፍፁም አይወድቁም ምክንያቱም እግዚአብሔር እርሱ በወደደው መንገድ ወደ ፍፃሜ እንዲመጡ የማድረጉ አቅምም ሆነ ሥልጣን ስላለውና ቃሉንም ለመፈፀም የታመነ በመሆኑ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ፣ ትንቢቶች በፈጣን ፍጻሜያቸው ምክንያት የበለጠ ይረጋገጣሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 17 ቁጥር 1 ላይ፣ ነቢዩ ኤልያስ ከአፉ ቃል በስተቀር በምድሪቱ ላይ ጠል ወይንም ዝናብ እንደማይኖር አወጀ፡፡ ከ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 18 እንደምንረዳውም፣ እግዚአብሔር ድርቁ ይበቃል እስካለበት ጊዜ ድረስ ለሦስት ዓመታት ድርቅ ሆነ፡፡ በ2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 7 ከቁጥር 17 እስከ 20 ላይ፣ የንጉሡ ባለሙዋል እንደሚሞት ኤልሳዕ የተናገረው ትንቢት በፍጥነት ሲፈፀም እንመለከታለን፡፡
በሌላ ወቅት ደግሞ፣ ትንቢታዊ ፍፃሜዎች በፍጥነት አይከናወኑም፡፡ ለምሳሌ፣ በ930 ዓ.ዓ. አካባቢ አንድ እውነተኛ ነቢይ ከዳዊት ቤት ታማኝ የሆነው ኢዮስያስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናገረ፡፡ ይህ ትንቢት በ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 13 ቁጥር 2 ላይ ተመዝግቧል፡፡ ትንቢት የተነገረለት ኢዮስያስ ግን እስከ 630 ዓ.ዓ. አካባቢ ድረስ አልተወለደም ነበር፡፡ 2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 22 ቁጥር 1 ላይ እንደምናነብበው ከትንቢቱ በኋላ 300 ዓመታት ያህል ቆቶ ነበር፡፡ ስለ ኢየሱስ መወለድ የተነገሩ ትንቢቶችም ከመፈፀማቸው በፊት ከዚህም የበለጡ ዓመታትን ወስደዋል፡፡
አሁን፣ በዚህ ነጥብ ላይ ቆም ብለን አንዳንድ ጊዜ የእውነተኛ ነቢያት ቃሎች እንኳን ሳይቀሩ እነርሱ በገለጡዋቸው ጊዜያት በቀጥታ ላይፈጸሙ እንደሚችሉ መግለጥ እንወዳለን፡፡ በሙሴ አስተምህሮ መሰረት፣ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ፣ የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች በምናነብበት ወቅት፣ አንዳንድ ጊዜ ስለ ንግርታቸው የተሳሳተ አግራሞት ውስጥ የምንወድቅ መሆኑን መረዳት ጠቃሚ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ነቢያት የወደፊቱን ነገር ሲናገሩ ፈፅሞ ሊቀለበስ የማይችል ነው ብለው ቢያስቡም፣ እውነታው ግን፣ ጉዳዩ ዘወትር እንዲህ ላይሆን ይችላል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ፣ ሰዎች በኃጢአታቸው እስከፀኑ ድረስ እርግማን እንደሚመጣ ያስጠነቅቃሉ፣ ሰዎች በታማኝነት ከፀኑ ግን በረከት እንደሚያገኛቸው ይናገራሉ፡፡ የእነዚህ ትንቢቶች ግብ ሰዎች ኃጢአታቸውን እንዲናዘዙና ለእግዚአብሔርና ለቃል ኪዳኑ ያላቸውን ታማኝነት እንዲጠብቁ ማበረታታት ነው፡፡ እውነተኛ ነቢያት እግዚአብሔር አንድ ነገር ሊያደርግ እንደማለ ማመልከታቸው የትንቢቶቻቸው አንከን አልባነት ማመልከቻ ነው፡፡
በውጤቱም፣ አንድ ትንቢት ለመፈፀሙ ሕጋዊው መንገድ ከትንቢቱ ጫና የተነሳ ሰዎች በባህርያቸው ላይ የሚታየው ለውጥ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሰጡዋቸው ማስጠንቀቂያዎች ወይንንም የተባሉት አንድ ባንድ በተነገሩበት መንገድ ባይፈፀሙም ትንቢቶቹ በዚህ ረገድ ይፈፀማሉ፡፡
ለዚህም በርካታ ምሳሌዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መሠረታዊው መርህ ግን በኤርምያስ ምዕራፍ 18 ከቁጥር 7 እስከ 10 የተገለጠው ነው፡፡
ስለ ሕዝብ ስለ መንግሥትም እነቅል አፈርስም አጠፋም ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ |
ይህ ስለ እርሱ የተናገርሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፥ እኔ አደርግበት ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ። |
ስለ ሕዝቡም ስለ መንግሥትም እሠራውና እተክለው ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ |
በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ ቃሌንም ባይሰማ፥ እኔ አደርግለት ዘንድ ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ። (ኤር 18፥7-10) |
እንግዲያው፣ እግዚአብሔር በኤርምያስ 18 ውስጥ እንዲህ በማለት መርህ አስቀምጦልናል፣
ስለ ሕዝብ ስለ መንግሥትም እነቅል አፈርስም አጠፋም ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ |
ይህ ስለ እርሱ የተናገርሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፥ እኔ አደርግበት ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ። |
በሌላው ጉኑ ደግሞ፣
ስለ ሕዝቡም ስለ መንግሥትም እሠራውና እተክለው ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ |
በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ ቃሌንም ባይሰማ፥ እኔ አደርግለት ዘንድ ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ። |
እንግዲህ እነዚህ መርሆች በዚህ ስፍራ እንደተገለፀው የሚሠሩት በግልጥ በተቀመጠው ሁኔታ ሲሆን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በአንዳንድ ምንባቦች ተገልፆ እንደምንመለከተው በስውር የሚቀመጡበትም ሁኔታ አለ፡፡ ይህም እግዚአብሔር ፍርድን ወይንም በረከትን አመጣለሁ ብሎ ይናገርና ለንግግሩ በሚሰጠው ምላሽ በእግዚአብሔር የሩቅ ሃሳብ መሠረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ለዚህም በጣም ጥሩው ምሳሌ በትንቢተ ዮናስ ውስጥ የተቀመጠው ነው፡፡ በዚህ ክፍል ዮናስ በነነዌ ህዝብ ላይ የፍርድን መልእክት እንዲናገር እግዚአብሔር ያዘዋል፣ ዮናስም ይህንኑ ያደርጋል፣ የነነዌ ህዝብ ንስሓ ይገባል፣ ይህም እግዚአብሔር አስቀድሞውኑ በልባቸው ውስጥ ሊያነሳሳ የፈለገው ይህንኑ ከሰው የሚጠበቀውን ሁኔታ እንዲያሟሉ ይመስላል፡፡ [ዶ/ር ሮብ ሊስተር]
በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ፣ የእውነተኞቹ ነቢያት ቃሎች ዘወትር ተፈፃሚ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደተነገረው በቀጥታ ይፈፀማሉ፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ሰዎች ለትንቢቱ ምለሽ ሲሰጡ በዚያ ምክንያት ውጤቱ የተለየ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በሁሉም መንገድ፣ የእውነተኛ ትንቢት የመጨረሻ ውጤቶች ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳንና ባሕርይ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፣ እናም የእርሱን እውነተኛ ነቢያት ተአማኒነት ይረጋግጣሉ፡፡
የአግዚአብሔር ህዝብ የትኞቹ ነቢያት በእውነት የእግዚአብሔር የሆነውን እንደሚናገሩ ለመለየት በሚያስችለው መንገድ ሙሴ የነቢይነትን አገልግሎት ቢሮ መመዘኛዎች ያስቀምጣል፡፡ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት የእውነተኞቹን ነቢያት መልዕክቶች ለይተው እንዲያውቋቸው እና እንዲታዘዙ ደግሞም ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታማኝ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲል ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እነዚህን መመዘኛዎች በልቡናችን መያዝ ያስፈልገናል፣ ምክንያቱም በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ እንደ እግዚአብሔር ነቢይ ባገለገለበት ወቅት ያሟላቸው እነዚያኑ መመዘኛዎች ነበርና ነው፡፡
የነቢይነትን አገልግሎት መመዘኛ ከተመለከትን አሁን ደግሞ የአገልግሎቱን ተግባር እንመለከታለን፡፡
ተግባር
በዚህ ነጥብ ስር የነቢያትን ተግባር ሦስት ገፅታዎች እናነሳለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ስለ ሥልጣናቸው እንነጋገራለን፡፡ ሁለተኛ፣ ተግባራቸውን እናነሳለን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ፣ እነዚህን ተግባራት ለመፈፀም የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች እንነካካለን፡፡ በመጀመሪያ ሥልጣናቸውን እንመልከት፡፡
ሥልጣን
በዚህ ትምህርት ጅማሬ ላይ እንደጠቀስነው፣ ነቢይ፡
የእግዚአብሔርን ቃል የሚያውጅ፣ ኃጢአት ስለሚጠብቀው ፍርድ የሚያስጠነቅቅ፣ ለእግዚአብሔርም የሚገባውንና ወደ በረከት የሚደርሰውን አገልግሎት እንዲሰጡ በማበረታታት ቃሉ በሰዎች ሕይወት ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ የሚያመለክት፣ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን አምባሳደር ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን፣ እግዚአብሔር የተገለጠው በቃል ኪዳኖቹ አማካይነት በህዝቡ ላይ እንደሚገዛ ታላቅ ንጉሥ ዓይነት ሆኖ ነው፡፡ ነቢያቶቹም እግዚአብሔር ከሰማይ ዙፋኑ ለእነርሱ የገለጠላቸውን የሚያብራሩ የእነዚህ ቃልኪዳኖች አምባሳደሮች ናቸው፡፡
በጥንታዊቷ ቅርብ ምሥራቅ፣ ኃያል የሆኑ ነገሥታት ወይንም “ሱዜሪያኖች” ታናናሽ መንግሥታትን ወይንም “ቫሳሎችን” በዋና ከተሞቻቸው ተቀምጠው ከርቀት ይገዛሉ፡፡ እነዚህም ሱዜሪያኖች ከቫሳሎቻቸው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት የሚደነግጉ ውሎችን በግልጥ ያስቀምጣሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ቃል ኪዳንን ይህንን በመሰለው መንገድ ያስቀምጠዋል፡፡
ሱዜሪያኖቹ እነዚያን ውሎች ለማስተዳደርና ለማጠናከር ሲሉ፣ በእነርሱ ስም የሚናገሩላቸውን አምባሳደሮች ይሾማሉ አግባብነት ያለውንም ሥልጣን ይሰጧቸዋል፡፡ ቫሳል መንግሥታቶቹ እነዚያን ውሎች መተላለፍና ለውሎቹ ታማኝ አለመሆን ስለሚያመጣባቸው ፍዳ የማስጠንቀቅ፣ ደግሞም ውሎቹ የሚያስገኙትን በረከት በሙላት ለመካፈል መንግሥታቱ ታዛዥ እንዲሆኑ የማበረታታቱ ሥራ የአምባሳደሮቹ ሥራ ነው፡፡
ይህንን ጥንታዊ የቅርብ ምሥራቅ ታሪክ ማወቅ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን፣ እግዚአብሔር በተደጋጋሚ ጊዜ ከሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚገልጠው ከሱዜሪያዊ-ቫሳል የቃል ኪዳን ትስስር አንፃር በመሆኑ ነው፡፡ እንደ ሱዜሪያዊ፣ የእርሱን ቃል ኪዳን ዝርዝሮች ለቫሳል ህዝቡ ያሳስቡለት ዘንድ ነቢያትን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሮች አድርጎ ይሾማልና፡፡
ነቢያት የእግዚአብሔር አምባሳደሮች በመሆናቸው ምክንያት፣ ቃሎቻቸው ልክ እግዚአብሔር ራሱ እንደሚናገር ዓይነት ተቀባይነት ነበራቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ነቢያትን ስለሚነዳቸው ለእስራኤል ህዝብ እግዚአብሔር ያለውን ሃሳብና መሻት በትክክለኛ መንገድ ያውጃሉ፡፡ በዚህም መንገድ፣ ነቢያቱ ዘወትር በሥልጣንና በእውነት እርሱን ወክለው እንዲናገሩ እግዚአብሔር ያደርጋል፡፡
የእውነተኛ ነቢያትን ቃሎች በቁም ነገር መቀበል የሚገባን ለምንድን ነው? እውነተኛ ነቢያት እርሱን በመወከል የሚናገሩ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ቃሎቻቸውን በአትኩሮት የማንቀበል ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በልባችንና በጆሮዎቻችን ያልተገረዝን እንሆናለን ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ልባችን ገና አልተለወጠም ማለት ነው፡፡ እኛም፣ በእግዚአብሔር ላይ እናምፃለን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ፣ የነቢያትን ቃል የማንቀበል ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመቀበል አሻፈረኝ ማለታችን ነው ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሔር በራሱም ላይ ማመፃችን ነው፡፡ ይህም፣ እጅግ የከበደ ጉዳይ ነው፡፡ [ዶ/ር ፒተር ቾው]
ስለነቢያት ሥልጣን ያነሳነውን መረዳት በልቡናችን ከያዝን፣ አሁን ደግሞ እግዚአብሔር ለነቢያቱ ወደ ሰጣቸው ሥራ እንሸጋገር፡፡
ኃላፊነት/ሥራ
የነቢያትን ኃላፊነት ለመረዳት፣ አሁንም መለስ ብለን በጥንታዊቷ ቅርብ ምሥራቅ የነበረውን የሱዜሪያዊ-ቫሳል ግንኙነት ውሎችን እንመልከት፡፡ በጥንታዊቷ ቅርብ ምሥራቅ ሱዜሪያኖቹ ለቫሳል መንግሥታቱ የቃል ኪዳን ውሎችን ሲደነግጉ፣ ቃል ኪዳኖቹ በመካከላቸው ያሉትን ዝርዝር ግንኙነቶችም አንድ በአንድ በመጥቀስ ይዘጋጃሉ፡፡ ዝርዝሮቹም፡ ባለፉት ጊዜያት ሱዜሪያኖቹ ያሳዩት ቅንነት፣ ያም፣ ሱዜሪያኑ ለቫሳሎቹ ያደረጓቸው በጎ ነገሮች፤ ቫሳሎቹ ለሱዜሪያኖቹ ሊያሳዩ የሚገባቸው ተአማኒነት፣ ማለትም ቫሳሎቹ ሊከተሉዋቸው የሚገቧቸው ህግጋትና ስምምነቶች፤ በውሉም መሠረት ቫሳሎቹ በመታዘዝና ባለመታዘዝ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ተመሥርቶ የሚጠብቃቸውን በረከት ወይንም ፍርድ፣ ቢታዘዙ በረከት፣ ቢያምፁ ደግሞ ፍርድ የሚጠብቃቸው መሆኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
በተመሳሳይም መንገድ እግዚአብሔር ከቃል ኪዳን ህዝቡ ጋር ያለውም ግንኙነት እንዲህ ዓይነት ገጽታዎች ይኖሩታል፡፡ እግዲያው፣ ነቢያትም እንደ እግዚአብሔር የቃል ኪዳን አምባሳደሮች፣ የእግዚአብሔርን ህዝብ ስለ ቃል ኪዳኑ ዝርዝሮች ለማሳሰብ፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግና ህዝቡንም ለማነሳሳት ስለ ፍርድና ስለ በረከት የመናገር ኃላፊነት ተቀብለዋል፡፡
እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር በጥሩ አቋም ላይ በምትገኝበት ወቅት፣ ነቢያቱ የድርጊቶቻቸውን ውጤት ለህዝቡ በማመልከት በታማኝነታቸው እንዲዘልቁ ያበረታቷቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ይህንን መሳይ ድርጊት በኤርምያስ ምዕራፍ 7 ከቁጥር 5 እስከ 7፤ ምዕራፍ 21 ቁጥር 12 እና ምዕራፍ 22 ቁጥር 4 እና 5 ላይ እናገኛለን፡፡
ነገር ግን እስራኤል ለረጅም ዘመናት ከቃል ኪዳኑ አንፃር ባለመታዘዝ በመዝለቅ ከእግዚአብሔር ጋር በመልካም ሁኔታ ላይ ካልተገኘች፣ ነቢያቱ ስለ አመፃቸውና ታማኝነታቸውን ስለ ማጉደላቸው ተጠያቂ እንደሆኑ ያስጠነቅቋቸዋል፡፡ የእስራኤልንም ኃጢአት በመዘርዘር የቃል ኪዳኑን ህዝብ በዚህ መንገድ በመሄድ የሚጠብቀውን እርግማን በማሳሰብ ወደ ንስሓ እንዲመጣ ያደርጋሉ፡፡ የዚህንም ምሳሌ በኤርምያስ ምዕራፍ 8 እና በአሞጽ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 3 ባለው ውስጥ እንመለከታለን፡፡ በብዙ ጉዳዮችም ላይ፣ እስራኤል የቀረበላትን የንስሓ ጥሪ ስትቀበል ከእግዚአብሔር የሚመጣላትን በረከትም ይናገራሉ፡፡ ይህንን መሳዩን ትንቢት በኢዩኤል ምዕራፍ 2 ከቁጥር 12 እስከ 27 እና በሌሎችም ስፍራዎች ውስጥ እናገኛለን፡፡
የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ነቢያትን ሥራና ሥልጣን ከተመለከትን፣ ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች በጥቂቱ መመልከት ይገባናል፡፡
ዘዴዎች
ያለምንም ጥርጥር፣ ነቢያት ይህንን ሃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚጠቀሙበት የተለመደ መንገድ መናገር ነው፡፡ ነቢያት ሥራቸውን የሚከናውኑት የእግዚአብሔርን ቃል ለህዝቡ በማወጅ ነው፡፡ ህዝቡን ስለ ኃጢአት ይወቅሳሉ፣ እንዲታዘዙም ያዛሉ፣ እንዲፀኑ ያበረታታሉ፣ ስለ ፍርድ ያስጠነቅቃሉ ደግሞም በረከትን ያውጃሉ፡፡ ምሳሌዎችን ይናገራሉ፡፡ የወደፊቱንም ይተነብያሉ፡፡ ይጸልያሉም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ህዝብም ይማልዳሉ፡፡ ይህንንም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት እንመለከታለን፡፡ ከዚህም በላይ፣ በርካታ ነቢያት ቃሎቻቸውን ይጽፋሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ የትንቢትና ሌሎችንም ዓይነት ጽሁፎች የምናገኘው ለዚህ ነው፡፡
ነገር ግን ነቢያት በንግግር ከሚደረግ ተግባቦት ባሻገር በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ ተደግፈው መልእክታቸውን የማስተላለፍ ዘዴዎችንም ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ፣ መንፈስ ቅዱስ ትንቢታዊ ተዓምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያደርጉ ዘንድ ለአንዳንድ ነቢይት ኃይልን ይሰጣቸዋል፡፡ እነዚህ አስደናቂ የኃይል ሥራዎች ነቢያት የእግዚአብሔር አምባሳደሮች መሆናቸውን፣ ነቢያት ያወጇቸው ማስጠንቀቂያዎችና በረከቶች የእግዚአብሔርን መሻት የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡
ለምሳሌ አንዱን ብንጠቅስ፣ ነቢዩ ሙሴ ለእስራኤላውያንም ሆነ ለግብፃውያን የአግዚአብሔርን ፈቃድ አውጇል፣ ቃሎቹም ቁጥር ስፍር በሌላቸው ተዓምራትና ምልክቶች የታጀቡ ነበሩ፣ ከነዚህም ውስጥ በግብፅ ላይ የተደረጉ ዐሥሩ መቅሰፍቶች፣ የኤርትራ ባህር መከፈል እና በዘፀዓት፣ በዘሌዋውያን እና በዘኁልቁ መጻሕፍት የተመዘገቡ በርካታ ተዓምራት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ የኃይል ሥራዎች ሙሴ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን የመሰከሩ ሲሆን፣ ግብፃውያንም ሆኑ እስራኤላውያን እንዲታዘዙት የሚያስጠነቅቁ ናቸው፡፡
ከ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 17 እስከ 2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 13 እንደምንመለከተው፣ በነቢዩ ኤልያስና ኤልሳዕ የትንቢት አገልግሎት በርካታ ተዓምራዊ ክስተቶች ተካትተዋል፡፡ ነቢዩ ሳሙኤልም ተዓምራትን አድርጓል፣ ለምሳሌ በ1ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 12 እንደተመዘገበው መብረቅና ዝናብ እንዲዘንብ አድርጓል፡፡ አንድ ስሙ ያልተጠቀሰም ነቢይ በ1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 13 ውስጥ የንጉሡ የኢዮርብዓም እጅ ደርቃ እንድትቀር በማድረግ ተዓምራት አሳይቷል፡፡
ከተዓምራቱም በተጨማሪ፣ በርካታ ነቢያት በንግግር ያስተላለፉትን መልእክት የሚያፀኑ ተምሳሊታዊ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ በተጨማሪም የእግዚአብሔር ህዝብ የቃል ኪዳኑን ዝርዝሮች እንዲፈፅሙ ሲማፀኑ ከመንፈሳዊ አካላትም ጋር ግብ ግብ ገጥመዋል፡፡
ነቢያትን እንደ እግዚአብሔር የቃል ኪዳን መልእክተኞች መመልከታችን መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚዘረዝራቸው የእርግማን ዳፋዎችና በረከቶች ሁሉ በእግዚአብሔርና በህዝቡ መካከል ካለው ቃል ኪዳናዊ ግንኙነት ጋር የተሳሰሩ መሆኑን እንድንገነዘብ ያስችሉናል፡፡ እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር ባለው ጉዳይ ሃሳቡን አይለዋውጥም፤ አስቀድሞም ሳይናገር በዱብ ዕዳ አንድ ነገር አያደርግም፡፡ ይልቁኑም፣ የቃል ኪዳኑን ዝርዝሮች የበለጠ ያፀናል፣ ውሎቹም ምስጢር አይደሉም፡፡ ህግጋቱን በጸጋው ይሰጠናል፣ በሚለዋወጠውም ሁኔታዎቻችን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርጋቸው ያሳዩን ዘንድ የእርሱን አምባሳደሮች ይልክልናል፡፡ የእርሱ ህዝብ የሚፈልግበትን እንዲያውቅና በእርሱም ፊት በታማኝነት እንዲመላለስ፣ በረከቶቹንም እንዲያገኝና ለመንግሥቱም ያሉትን ዓላማዎች ከግብ እንዲያደርስ ይፈልጋል፡፡
የነቢይነትን አገልግሎት መመዘኛዎችና ተግባራት ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ ብሉይ ኪዳን ከወደፊት የነቢይነት አገልግሎቶች የሚጠብቀውን ወደመመልከቱ እናተኩራለን፡፡
ተስፋ የሚደረገው/ጥበቃ
ብሉይ ኪዳን ከወደፊቱ የትንቢት አገልግሎት የሚጠብቃቸው በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ዓይነቶችን ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ አንዳንዶቹ ጥበቃዎች የተፈጠሩት ከአገልግሎቱ ታሪካዊ እድገት ጋር በተያያዘ መንገድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሌሎቹ ጥበቃዎች ደግሞ የተፈጠሩት ስለ ወደፊቱ ነቢያት በተነገሩ ግልፅ ትንቢቶች ምክንያት ነው፡፡ ሁለቱንም ዓይነት ጥበቃዎች እንመለከታለን፣ ሆኖም በነቢይነት አገልግሎት ታሪካዊ እድገት ላይ በተመሠረቱት እንጀምራለን፡፡
ታሪካዊ እድገት
እግዚአብሔር ከሰው ዘር ጋር ያለው ግንኙነት ዘወትር የሚመራው በቃል ኪዳኑ መሠረት ስለሆነ፣ ህዝቡን ስለ ቃልኪዳኑ ዝርዝር ውሎች ዘወትር የማሳሰብ ሃላፊነት የሚኖራቸው ነቢያት መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ታሪክን በምንመረምርበት ወቅት ግን፣ እነዚህ ሃላፊነቶች አንዳንድ ጊዜ ይለዋወጣሉ፡፡ በታሪክ ዘመናት ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ሲያድግና ከአንዱ እርከን ወደ ሌላው ሲሸጋር፣ የነቢያቱም ሃላፊነት ለእድገቱ በሚመጥን ልክ እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡
የነቢያትን የአገልግሎት ድርሻ በተለያዩ አራት የታሪክ እርከኖች ለመመልከት እንሞክራለን፣ ቅድመ- ነገሥታት ብለን ከምንጠራውና እስራኤል ያለ ንጉሥ ከኖረችበት ረጅም የታሪክ ዘመን እንጀምራለን፡፡ ይህ ክፍለ ዘመን እግዚአብሔር ከአዳም፣ ከኖህ፣ ከአብርሃም እና ከሙሴ ጋር ከገባው ቃል ኪዳን ጋር የሚስማማ ነው፡፡
ቅድመ-ነገሥታት
በቅድመ -ነገሥታት የታሪክ ክፍለ ዘመን ጅማሬ ላይ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት በአንድ በተደራጀ መንግሥት ከሌላው ዓለም የተለየ አልነበረም፡፡ ያም መንግሥት በአብርሃም ዘመን ከተለየም በኋላ እንኳን፣ ንጉሥ አልነበረውም፡፡ በዚህ ወቅትና ጊዜም፣ ነቢያት የተለያዩ ሃላፊነቶችን ይወጡ ነበር ደግሞም በተለያዩ ገላጭ ማዕረጎች ይጠሩ ነበር፡፡ በጥቅሉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገሩ ነበር፣ ራዕይ ይቀበሉ ነበር፣ የሰው ዘርም ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተጠያቂ እንዲሆን ያደርጉ ነበር፡፡
ለምሳሌ፣ እግዚአብሔር ዓለምን በፈጠረ ወቅት፣ እግዚአብሔር ከአዳምና ከሔዋን ጋር በቀጥታ ይነጋገር ነበር፤ ዘፍጥረት ምዕራፍ 2 እና 3 በምናነብበት ወቅት፣ ከእርሱ ጋር አብረው በመጓዝና በመነጋገር መገለጥን ይቀበሉ እንደ ነበር እናያለን፡፡ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ ቃል ኪዳኑ ልጆቻቸውን በማስተማር የነቢይነት ድርሻቸውንም ይወጡ ነበር፡፡ ከዝርያዎቻቸውም አንዳንዶቹ ከእግዚአብሔር ጋር ተመሳሳይ ግንኙነት ነበራቸው፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 5 ቁጥር 24 የተጠቀሰው ሄኖክ አንዱ ነው፡፡
በኖኅ ዘመን፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 እስከ 9 እንደምናነብበውም፣ እግዚአብሔር በቀጥታ ከኖኅ ጋር ይነጋገር ነበር፡፡ በተጨማሪም ኖኅ ጴጥሮስ በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 5 እንደሚያስተምረን፣ ዓለም በጠቅላላው በእግዚአብሔር ላይ በማመፁ ምክንያት ሊመጣበት ስላለው ፍርድ ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያም ይሰጥ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ኖኅ መርከብን በመሥራትና የመልዕክቱንም እርግጠኝነት ለማሳየት ከየእንስሳቱ ዝርያ ወደ መርከቡ በማስገባት ለሁሉ ግልፅ የሆነ ትንቢታዊ ተግባርም አከናውኗል፡፡
እግዚአብሔር ለአብርሃምም በቀጥታ ተናግሯል፣ ወደፊት ስለሚያከናውነውም ነገር ገልጦለታል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 20 ቁጥር 7 ላይ እንደምንመለከተውም፣ ከእግዚአብሔር ባደረጋቸው በነዚህ ንግግሮችና እነዚያንም ለሌሎች ሰዎች በማስተላለፍ አብርሃምም የነቢይነትን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ የአብርሃም ዝርያ የሆኑት ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ዮሴፍም እንደ እግዚአብሔር ነቢያት አገልግለዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ህልምንና ራዕይን ተቀብለዋል፣ በተጨማሪም መላእክቶችም ጎብኝተዋቸዋል፡፡ እያንዳንዳቸው ነቢያትም የአግዚአብሔርን ቃል በማወጅ ህዝቡ ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተጠያቂ እንዲሆን እና ለጌታም ታማኝ ሆኖ እንዲዘልቅ ያሳስባሉ፡፡
በሙሴ ዘመን፣ አንድ ሌላ ወሳኝ የሆነ ቅድመ ነገሥታት የነቢያት እንቅስቃሴ ዘመን እናገኛለን፡፡ እንደ ዘኁልቁ ምዕራፍ 12 ቁጥር 6 አገላለጥ፣ በዚህ ዘመን ሙሴ ራሱ ላቅ ያለው የእግዚአብሔር ነቢይ እንደነበር እንረዳለን፡፡ በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ላይ፣ በዘፀዓት ምዕራፍ 20 እስከ 23 እንደምንመለከተው እግዚአብሔር ለህዝቡ የተፃፈ ቃል ኪዳን በዐሥርቱ ትዕዛዛት መልክ ደግሞም የቃል ኪዳን መጻሕፍትንም ሰጥቷል፡፡ ስለዚህም እነዚህን ቃል ኪዳኖች ለህዝቡ የማብራራት፣ እንደ ህግጋቱም እነርሱን የማስተዳደር እና የቃል ኪዳኑን በረከቶች ይቀበሉ ዘንድ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው እንዲዘልቁ ማሳሰብና በአመፃቸው በቃል ኪዳኑ የተጠቀሱት እርግማኖች እንዳይደርሱባቸው ማስጠንቀቅ የሙሴ ኃላፊነት ነበር፡፡ ምንም እንኳን አንዳቸውም በሙሴ የአገልግሎት መጠነ ልክ ሊያገለግሉ ባይችሉና ተፅዕኖአቸውም የእርሱን ያህል ባይሆንም፣ በእርሱም ዘመን ሆነ ከእርሱም በኋላ የነበሩ ነቢያትም እነዚያኑ ተግባራት ያከናውኑ ነበር፡፡ በቅድመ-ነገሥታት ዘመን የነበረው የነቢያት አገልግሎት እጅግ የተበታተነ ቢሆንም፣ እስራኤል የተስፋዪቱን ምድር ከወረሰችና ተረጋግታም በንጉሥ አመራር ስር በነበረችበት በነገሥታት ዘመን ግን ግልፅ ሥርዓት ተበጅቶለት ነበር፡፡
የነገሥታት ዘመን
የነገሥታት ዘመን የጀመረው በመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ በሳዖል ነበር፡፡ ግን ብዙም ሳይርቅ የእርሱ ተከታይ ከሆነው ከዳዊትና ከዘሩ ጋርም የተያያዘ ነበር፡፡
በነገሥታቱ ዘመን የነቢያት አገልግሎት፣ በማዕከላዊው የኃይል እርከን ላይ፣ በተለይም በንጉሡ ችሎትና በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ ያነጣጠረ ከመሆኑ ባሻገር የነቢያትም ቁጥር ጨምሮ ነበር፡፡ ንጉሡ ለእግዚአብሔር የቫሳል ህዝብ ማዕከላዊ አትኩሮት የሚሰጠው እንደመሆኑ መጠን፣ ህዝቡን ስለ ቃል ኪዳኑ ድንጋጌዎች የማሳሰቡ የነቢያት ሥራ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ከንጉሡ ጋር በሚኖር የቀጥታ ግንኙነት ይሆናል፡፡
በዚህ ዘመን፣ የነቢያት ተቀዳሚ ተግባር ነገሥታት እና ሃገራዊ ሃላፊነት የሚወጡባቸው ችሎቶቻቸው እግዚአብሔርን በታማኝነት ከማገልገል አንፃር የተቃኙ እንዲሆኑ ማሳሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ 1ኛ እና 2ኛ ነገሥት፣ 2ኛ ዜናም በነቢያትና በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መካከል የተደረጉ በርካታ ግንኙነቶች ተመዝግበው እናገኛለን፡፡ ቢሆንም፣ ነቢያቱ በአጠቃላይ ለህዝቡም ጭምር መናገራቸውን እና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን መመዘኛዎች ደግሞም ባህርያቸው የሚያስከትልባቸውን ጣጣ ማሳሰባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ነቢያት በተጨማሪም ጎረቤት አገሮች ከእስራኤልና ከይሁዳ ጋር በሰላም እንዲኖሩም ያዝዛሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤልንና ይሁዳን እንደ ሁለት መንግሥታት የሚጠቅስበት ምክንያት አለው፡፡ እውነት ነው በመጀመሪያ አንድ መንግሥት ነበሩ፣ ሆኖም በሰለሞን ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ለሁለት ተከፈሉ፡፡ ያም የሆነው በ920 ዓ.ዓ. አካባቢ ሲሆን፣ የሰሜኑ መንግሥት ዐሥሩን ነገዶች፣ የደቡቡ ደግሞ ሁለቱን ነገዶች ይዞ ነበር፡፡ የሰሜኑ መንግሥት እስራኤል ተብሎ ይጠራል፡፡ በርካታ ቁጥር ያለው ነገድ ኤፍሬም ቢሆንም፣ ዐሥሩም በጠቅላላው ግን እስራኤል ተብለው ተጠርተዋል፡፡ የደቡቡ መንግሥት ደግሞ ይሁዳ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ትልቁም ነገድ እርሱ ነበር፡፡ በመሠረቱ፣ የደቡቡ መንግሥት ዋና ከተማ ኢየሩሳሌም ናት፡፡ [ዶ/ር ፍራንክ ባርከር]
ከሰለሞናዊ መንግሥት በኋላ፣ የሰሜኑ መንግሥትና የደቡቡ መንግሥት ተከፋፈለ፡፡ የሰሜኑ መንግሥትም እስራኤል ተብሎ ተጠራ፣ እናም በጋራ የሚያመልኩበት ማዕከላዊ ስፍራም ለብቻቸው ነበራቸው፡፡ ደቡባዊውም መንግሥት ይሁዳ ተብሎ ተጠራ፡፡ ከመንግሥታቱ መለያየትም በኋላ ነቢያቶቹ ወደ ተለያየ ስፍራ ሲሄዱ ትመለከታላችሁ፡፡ ሆሴዕ የእስራኤል ነቢይ ሲሆን፣ በይሁዳ ደግሞ ኢሳያስን ታገኛላችሁ፡፡ ሰሜንና ደቡብ ተብለው በተከፋፈሉት መንግሥታትም መሠረት ይሰጥ የነበረውም አገልግሎት አድማስም ከዚያው ጋር የተዛመደ ነበር፡፡ [ዶ/ር ማርክ ጊግኒሊአት]
የሚያሳዝነው፣ የእስራኤል ነገሥታትም ሆኑ ህዝቡ ነቢያቱን አይታዘዙም ነበር፡፡ በውጤቱም፣ በስተመጨረሻው ከተስፋዪቱ ምድር በግዞተኝነት በመወሰድ ለቃል ኪዳኑ እርግማን ታልፈው ተሰጡ፡፡
ግዞት
የሰሜኑ መንግሥት እስራኤል የተጋዘው በ723 ወይንም 722 ዓ.ዓ. ሲሆን ወደ አሶርም በግዞተኝነት ተወሰዱ፡፡ የደቡቡ መንግሥት ይሁዳ የተጋዘው ደግሞ በ587 ወይንም በ586 ዓ.ዓ. ሲሆን ወደ ባቢሎን በግዞተኝነት ተወሰዱ፡፡
በግዞት ላይ በነበሩበትም ዘመንም እንኳን፣ የነቢያት አገልግሎት ለእግዚአብሔር ህዝብ ነገሥታት አዋጅ ነጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን በዚህ የታሪክ ዘመን፣ ንጉሥ አልነበረም፣ ስለዚህ ትኩረቱ ንጉሦቻቸውን እንደገና ማደስና የእግዚአብሔርንም ህዝብ መንግሥት በማስመለሱ ላይ ነበር፡፡
ወደዚህ ግብም ለመድረስ፣ የእግዚአብሔር ህዝብ ስለ ኃጢአቱ ንስሓ እንዲገባ፣ ወደ ቃልኪዳናዊ ታማኝነቱ እንዲመለስና እግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑን በረከቶች እንዲያፈስስላቸው ነቢያት ህዝቡን ያበረታቱ ነበር፡፡ በተጨማሪም ነቢያት ህዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቢመለስ፣ ቃል ኪዳኑን መጠበቅ እንዲችሉ ስለሚያበረታቸው ደግመው በቃል ኪዳኑ እርግማን ውስጥ በሚጥላቸው ውድቀት ውስጥ እንደማይገኙ ያውጁ ነበር፡፡ በኤርምያስ ምዕራፍ 31 ቁጥር 33 እና 34 ውስጥ፣ ከዚያን በኋላ ደግመው ቃል ኪዳኑን መተላለፍ እንዳይችሉ ጌታ እንደሚያደርጋቸውና በፈንታው ግን በትልቅ መሰጠት እንደ ህጉ እንደሚኖሩ ተጽፎ እናነባለን፡፡ በዚህም አገልግሎት፣ በጽድቅ በሚሄዱና ከዳዊት ዘር በሆኑ ነገሥታት አማካይነት በተስፋዪቱ ምድር ውስጥ እንደ ገና መንግሥታቸውን እንደሚመልስላቸው ተስፋ በማድረግ ነቢያቱ እግዚአብሔርን ይማፀኑ ነበር፡፡
በስተመጨረሻም፣ የምርኮው ዘመን በተሃድሶ ዘመን ውስጥ ወደ ፍፃሜው አጋማሽ ላይ ደርሶ ነበር፡፡
ኅዳሴ
ይህ የድኅረ-ምርኮ ወይንም የተሃድሶ ዘመን የጀመረው በ539 ወይንም 538 ዓ.ዓ. ላይ ነው፡፡ በዚያን ወቅት በእስራኤልም ሆነ በይሁዳ ንጉሥ አልነበረም፣ ኢየሩሳሌም ግን መልሳ ተገንብታ ነበር ደግሞም በርካታ ቤተሰቦችም በተስፋዪቱ ምድር ውስጥ ለመኖር ተመልሰው ነበር፡፡
በአንፃራዊነት ግን በዚያኑ ወቅት ጥቂት ነቢያት ነበሩ፡፡ ግን ሐጌና ዘካርያስን የመሳሰሉ ታማኝ ነቢያት፣ መሪዎችንና ጠቅላላውን ህዝብ በንቃት በመጠበቅ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው እንዲዘልቁ ያበረታቱ ነበር፡፡ በተሃድሶው ዘመን ውስጥ ታማኝ ሆነው እንዲዘልቁና እግዚአብሔርም ኅዳሴውን ወደ ሙላት እንዲያመጣው ይማፀኑ ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን ህዝቡ የነቢያትን ተማፅኖ ባለመስማቱ ኅዳሴው ተደናቀፈ፡፡
በኅዳሴው ዘመን፣ መንግሥታቸው እንዲመለስ ይጠብቁ የነበረው እግዚአብሔር ለዳዊት በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ከዝርያዎቹ አንዱን አስነስቶ በእስራኤልና በይሁዳ ዙፋን ላይ እንደሚያስቀምጠው ተስፋ በማድረግ ነበር፡፡ ይህንንም ተስፋ በዘካርያስ ምዕራፍ 12 እና 13 ላይ ተገልፆ እናገኘዋለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ተስፋው የህዝቡ መታዘዝ እግዚአብሔርን እንዲባርካቸው ያነሳሳዋል የሚል ነበር፡፡ ኅዳሴው ሲደናቀፍ ግን፣ ተስፋው ምንም እንኳን ኃጢአታቸው ቢበዛም እግዚአብሔር በመጨረሻው ለህዝቡ በመራራት፣ ስለስሙ ሲል መንግሥታቸውን መልሶ ያፀናላቸዋል በሚለው ላይ ፀና፡፡
የነቢይነትን አገልግሎት ታሪካዊ እድገት በመመልከት፣ ነቢያት የእግዚአብሔር ህዝብ ከአምላኩ ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ተጠያቂ መሆኑን የማሳሰብ አደራ የተሰጣቸው የአግዚአብሔር ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደሮች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ ይህም ወጥነት የወደፊቱ የነቢይነት አገልግሎት ምን እንደሚጠበቅበት የሚያመለክት ሆነ፡፡ በተለይም፣ የእግዚአብሔር የወደፊት ነቢያት ሁሉ ባለሙሉ ሥልጣን መልእክተኞች እንደሚሆኑ፣ ሥራቸውም እግዚአብሔር ስለ ህዝቡ ያለውን ቅንነት ማሳሰብ፣ ከእነርሱ የሚጠብቀውንም ተአማኒነት ማመልከት እና እንደ ምላሻቸውም የሚጠብቃቸውን መርገም ወይንም በረከት ማሳየት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የነቢያት አገልግሎት ሲለዋወጥ ከአገልግሎቱ የሚጠበቁም ነገሮች በዚያው መንገድ ተቀያይረዋል፡፡ በመጀመሪያ፣ የእግዚአብሔር ነቢያት ከንጉሥ ቢሮ ጋር ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡ አንድ ጊዜ ግን እስራኤል ባለ ንጉሥ ከሆነች በኋላ፣ ነቢያቱ ከንጉሣዊ ቢሮው ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ሆኑ፣ በእያንዳንዱም ወቅት የሚመጡት ለውጦች በንጉሣዊ ቢሮው ላይ ጫና ይፈጥሩ ነበር፣ ስለዚህም በነቢይነት አገልግሎት ላይ መዘዝ ይከተል ነበር፡፡ እንግዲያው፣ ይህ የሚያመለክተን በአዲስ ኪዳን ዘመን የሚሰጠው የነቢይነት አገልግሎት በብሉይ ኪዳን ዘመን ታሪክ መጨረሻ ላይ፣ ማለትም ድኅረ-ምርኮ ተብሎ ከሚጠራውና ህዝቡም ከዳዊት ዘር የሆነው ንጉሥ ይነግሣል ብሎ ይጠብቅ ከነበረበት ዘመን አገልግሎት እንደሚመነጭ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ፣ ይጠበቅ የነበረው የወደፊቱ የነቢያት አገልግሎት መሲሃዊውን ንጉሥ የሚያውጅና ከእርሱም ጋር የሚቆም መሆኑ ነው፡፡
ብሉይ ኪዳን በአገልግሎቱ ታሪካዊ ዕድገት ላይ ተመሥርቶ በወደፊቱ ነቢያት ይከናወናል ብሎ ከሚጠብቀው ባሻገር፣ ከወደፊቱ ነቢያት ስለሚጠበቀው ነገር ከተነገሩ ትንቢቶች የተነሳም ከወደፊቱ ነቢያት የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡
ውሱን ትንቢቶች
ስለወደፊቱ ነቢያት የተነገሩ በርካታ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ስላሉ ሁሉንም ዘርዝረን ልንጨርሳቸው አንችልም፡፡ የዚህን ትምህርታችንን ዓላማ ለማሳካት ግን፣ በሦስቱ ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ በመጀመሪያ የምንጠቅሰው አንድ የተለየ ነቢይ የጌታ የራሱ ድምፅ እንደሚሆንና ጌታም የምርኮ ዘመን ትንቢቶችን እግዚአብሔር በስተመጨረሻ ተፈፃሚ እንደሚያደርጋቸው ተስፋ የተሰጠበት ነው፡፡
በኢሳያስ ምዕራፍ 40 ከቁጥር 3 እስከ 5 እንደተገለፀው አንድ ልዩ ነቢይ መጥቶ ጌታ እንደሚመጣና ጠላቶቹንም ድል በመንሣት የዳዊትን መንግሥት እንደሚመልስ ያውጃል፡፡ እናም ይህ አዋጅ ከታወጀ በኋላ፣ ኅዳሴው አይቀሬ ይሆናል፡፡
ሁለተኛ፣ ልክ በቅድመ ንግሥና ዘመን ሙሴ ያደርግ እንደነበረው ሁሉ፣ ሰዎች እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ እንደሚነሳና፣ ሰዎችን ወደ ጽድቅ እንደሚመልስ ይጠብቃሉ፡፡
በዘዳግም ምዕራፍ 18 ቁጥር 18 ለሙሴ የተነገረውን የጌታ ቃል እናስታውስ፡
ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል (ዘዳ 18፥18)
በብሉይ ኪዳን፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ከሥራው፣ ከነቢይነቱ ከካህንነቱና ከንጉሥነቱ አንፃር የተነገሩ ጥበቃዎች እንደነበሩ እንመለከታለን፡፡ ዘዳግም 18 ደግሞ፣ ሙሴን የሚመስል ነቢይ ወደፊት እንደሚመጣ የሚናገር እጅግ ወሳኝ ምንባብ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን አውድ መሠረት፣ እንደ ሙሴ ያለ ማለት፣ ልክ እንደሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የተገናኘ፣ ለየት ባለ መንገድም የእግዚአብሔርን ራዕይ ያየ ማለት ነው፡፡ በመሠረቱ ሙሴ፣ የነቢያት ሁሉ ቁንጮ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ብሉይ ኪዳንን ዳር እስከዳር ስንመለከት፣ በተለይም በዘዳግም ምዕራፍ 34 መጨረሻ ላይ፣ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ እንዳልተነሳ ተጽፏል፡፡ ይህም ነገር ወደፊት የሚመጣውን እንደሙሴ ያለውን ከእርሱም የሚበልጠውን፣ የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገረውን፣ የእግዚአብሔርን እውነት የሚነግረንን፣ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የሚያውቀውን እንድንጠብቅ ይቃኘናል፡፡ ይህም የተፈፀመው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዮሐንስ ምዕራፍ 1 ይህንን ያመለክተናል፡፡ ጌታችን ከዘላለም ጥንት አብን የሚያውቅ፣ እርሱንም ለእኛ የገለጠ ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 3 የተከናወነው ነገር ሁሉ የዚህ ፍፃሜ መሆኑን፣ ስለዚህም ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያመጣ፤ የእግዚአብሔርንም ራዕይ የፈፀመ ነው፡፡ እርሱ የሙሴን ተግባራት በላቀ መንገድ ያሟላ ነው፡፡ ዕብራውያን ምዕራፍ 1 ደግሞ እግዚአብሔር ሙሴን ጨምሮ በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት እንደተናገረ፣ አሁን ግን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጡን ወደ ሙላት እንዳመጣው በግልጥ ያሳየናል፡፡ [ዶ/ር ስቴፈን ዌሉም]
በአንድ ወገን፣ የእግዚአብሔር ህዝብ ጌታ እንደ ሙሴ ያለውን ነቢይ እንዲልክላቸው ዘወትር ይጠብቃሉ፡፡ አሳዛኝ በሆነ መንገድ፣ ሙሴ እንደነበረው ዓይነት ኃይለኛ መንፈሳዊ ስጦታ ሊገለጥበት የቻለ ወይንም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ወደሙላት ያመጣ አንድም የብሉይ ኪዳን ነቢይ አልነበረም፡፡ በኅዳሴው ዘመን ግን፣ መንግሥቱን መልሶ እንደገና የሚመሠርት መልዕክተኛውን እግዚአብሔር በመጨረሻ እንደሚልክ የሚገልፅ አዲስ ተስፋ ተሰጠ፡፡
ሦስተኛ፣ መንግሥቱ ወደፊት እንደገና በሙላት ሲመሠረት፣ የትንቢትም ኅዳሴ ይኖራል፡፡ ሐሰተኛ ነቢያት ከምድርቱ ይወገዳሉ፣ እውነተኞቹ ነቢያት ደግሞ ይበዛሉ፡፡
እንደ ተሃድሶ ነቢይ ዘካርያስ በምዕራፍ 13 ቁጥር 2 ላይ እንዲህ ጽፏል፡
በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ። (ዘካ 13፥2)
በተጨማሪም፣ ህዝቡ አሁንም በነቢዩ በኢዩኤል የተነገረውንና የእግዚአብሔርን የቃልኪዳን በረከት ሙላት የሚናገሩ እውነተኛ ነቢያትን መብዛት ይጠብቃሉ፡፡
በኢዩኤል ምዕራፍ 2 ቁጥር 28 እና 29 ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት አድምጡ፡
ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ |
ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ (ኢዩ 2፥28) |
ኢዩኤል “ከዚያም በኋላ” በማለት ያመለከታቸው የወደፊት ቀናት፣ የመጨረሻዎቹ ቀናት ሲሆኑ እግዚአብሔር መንግሥቱን በምድር ሁሉ የሚያፀናበትና በህዝቡም ላይ ድንቅ በረከቱን የሚያፈስስባቸው ናቸው፡፡ በዚያንም ዘመን ትንቢት የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ለህዝቡ ለማስተዋወቅ፣ እርሱንም ያመልኩ ዘንድ እርስ በርስ ለመበረታታት በእግዚአብሔር ታማኝ ህዝብ መካከል የተለመደ ይሆናል፡፡
ብሉይ ኪዳን የሚደመደመው እስራኤል ተተረማምሳ መንግሥቱንም በቶሎ ከማምጣት አንፃር በመነመነ ተስፋ ውስጥ ሆና ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን፣ በእስራኤል ውስጥ የሚገኙት ጥቂት ታማኝ ቅሬታዎች እግዚአብሔር ስለ መንግሥቱ የተናገራቸውን ነገሮች ሁሉ በመጨረሻው ወደ ሙላት ያደርሳል ይህንንም በነቢያት ቢሮ በኩል በከፊል ይፈጽመዋል በማለት በመተማመን ይጠባበቁ ነበር፡፡ በኢየሱስ አገልግሎትም ተከናውኖ የምናየው ይኸው ነበር፡፡
ብሉይ ኪዳናዊውን ዳራ በመመርመር እግዚአብሔር ለነቢያቱ የሰጠውን ሃላፊነትና አገልግሎት ከተመለከትን፣ ወደ ሁለተኛው ርዕሳችን፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደሙላት የመጣው የትንቢት አገልግሎት ወደሚለው እንሸጋገራለን፡፡
- ምልዐት በኢየሱስ
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ታላቅ ነቢይ መሆኑን አዲስ ኪዳን ግልፅ ያደርግልናል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ባለ ሙሉ ሥልጣን የቃል ኪዳን አምባሳደር ለማገልገል ያለ እንከን መመዘኛውን ያሟላል፡፡ የአገልግሎቱንም ተግባራት በፍፁምነት አከናውኗል፡፡ በእርሱም፣ ብሉይ ኪዳን ከነቢያት ይጠብቃቸው የነበሩ ነገሮች ሁሉ ተፈፅመዋል፡፡
ኢየሱስ የነቢይነትን አገልግሎት ስለመፈፀሙ የምናደርገው ውይይት ስለ ብሉይ ኪዳን ነቢያት እና ስለ ተግባሮቻቸው ካነሳናቸው ጋር መሳሳይነት አለው፣ በተለይም፡ መመዘኛዎቹ፣ ተግባሮቹ እና ከአገልግሎቱ የሚጠበቀውን ነገር ይጠቀሳሉ፡፡
መመዘኛዎች
ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፣ በእስራኤል የሚገኙ ነቢያት አራት መመዘኛዎችን ሊያሟሉ ይገባል፡፡ እነርሱም፡ በእግዚአብሔር መጠራት፣ ለህዝቡ የሚናገሩትን ቃል መቀበል፣ እንዲናገሩ እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ብቻ በመናገር ታማኝ መሆን እና የተናገሩትም ቃል በመፈፀሙ ሊረጋገጥ የተገባው መሆኑ ናቸው፡፡ ቀጥለን እንደምንመለከተውም፣ ኢየሱስም እነዚህን መመዘኛዎች አሟልቷል፡፡ በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ተጠርቷል፡፡
በእግዚአብሔር መጠራት
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ነቢይ እንዲሆን ተለይቶ ተጠርቷል፡፡ ይንንም በልደቱ፣ በጥምቀቱ እና በተራራው ላይ በቅፅበት በመለወጡ ውስጥ በግልፅ እንመለከታለን፡፡ ለመነሻ እንዲሆነን፣ በሉቃስ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 30 እስከ 38 በኢየሱስ መወለድ ምክንያት ነቢዩ ስምዖን የተናገረውን አድምጡ፡
ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ |
ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። |
ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባለው ነገር ይደነቁ ነበር። |
ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም። እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት። (ሉቃ 2፥30-35) |
ከኢየሱስ መወለድ አንስቶ፣ ጌታችን ትንቢታዊ መገለጥ እና ለህዝብም ምልክት ተብሎ የተጠራ መሆኑን ስምዖን ገልጧል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ በኢየሱስ ጥምቀት ወቅት እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሁለቱም ኢየሱስን እንደ ነቢይ ጠርተውታል፡፡ ይህንንም በማቴዎስ ምዕራፍ 3 እና 4፣ በማርቆስ ምዕራፍ 1 እና በሉቃስ ምዕራፍ 3 እና 4 ውስጥ እናገኛለን፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉ በሚሰማ ድምፅ ተናግሯል መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ተገልጦ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑንና ለተለየ አገልግሎት የተቀባ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡ በነዚህ ሁሉ ምዕራፎች ውስጥ፣ የኢየሱስ ጥምቀት የንስሓን ትንቢታዊ መልእክትና የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ለሚያውጅበት የአደባባይ አገልግሎቱ እንዲለይ አድርጎታል፡፡
ሆኖም ግን የኢየሱስ ትንቢታዊ አገልግሎት በግልፅ የተመለከተው በመገለጥ ተራራ ላይ ነው፡፡ ይህም በማቴዎስ ምዕራፍ 17 ቁጥር 2 እና 3 ላይ እንዲህ ተገልጧል፡
በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። |
እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። (ማቴ 17፥2-3) |
ኢየሱስ ከብሉይ ኪዳን ታላላቅ ነቢያት ጋር ታየ፡፡ እነርሱም ሙሴ፣ ሕግ ሰጪውና የእግዚአብሔርን ቃል ለህዝቡ ስለሚናገሩት መለኪያውን የሰጠ፤ ኤልያስ፣ ተዓምራት አድራጊውና ስብከቱም ከእምነት ርቆ የነበረውን የዳዊትን ቤት ወደ ንስሓ የመራ ነበር፡፡ ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ጋር በመታየቱ ብቻ፣ ኢየሱስ ታላቅ ነቢይ መሆኑ ታይቷል፡፡
በማቴዎስ ምዕራፍ 17 ቁጥር 4 እና 5 ቀጥሎ ምን እንደሆነ ልብ በሉ፡
ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። |
እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። (ማቴ 17፥4-5) |
እግዚአብሔር ጴጥሮስንና ሌሎቹን ደቀመዛሙርት ሦስቱንም ነቢያት ሁሉ እንዲያደምጡ ሳይሆን ኢየሱስን ብቻ እንዲሰሙ አዘዛቸው፡፡ ከሙሴና ከኤልያስ ይልቅ እርሱን ሊሰሙ ይገባቸው ነበር፡፡ በዚህም መንገድ፣ እግዚአብሔር ራሱ፣ ኢየሱስ በየትኛውም ዘመን ከተነሱ ነቢያት የሚልቅ መሆኑን ገልጧል፡፡
በመገለጥ ተራራ ትረካ ውስጥ እግዚአብሔር ደቀመዛሙርቱ ኢየሱስን እንዲሰሙ ግድ ማለቱ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ እኔ እንደማስበው ለኢየሱስ ቀደምትነትን እንዲሰጡ እንጂ ሙሴን ወይንም ኤልያስን ቸል እንዲሉ አላዘዛቸውም፡፡ በዚያን ወቅት የተከናወነው ነገር ዋናው ነጥብ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር መገለጥ ቁንጮ የመሆኑን እውነታ ማስታወቅ ነው፡፡ በአይሁድ ትውፊት መሠረት ሙሴን እንደ ህጉ አርአያ ከበሬታን ይሰጡታል፣ ኤልያስን ደግሞ እንደ አንድ እጅግ ታዋቂ ነቢይ ያከብራሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ህጉ ዘመን ያለፈበት ወይንም ነቢያቱ ዘመን ያለፈባቸው ናቸው ማለት አይደለም፡፡ በእርግጠኝነት፣ ብሉይ ኪዳናችንን ማቃለል አንሻም፡፡ በዚህ ስፍራ የተሰመረበት፣ በኢየሱስ የተገለጠው መገለጥ ላቅ ያለ አርአያነት ያለውና ላዕላይ ተስተካካይ የሌለው የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ነገሩ በዕብራውያን ምዕራፍ አንድ እንደተገለፀው
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ |
ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ ስለዚህም ወደ ሙላቱ መጥተናል፤ እግዚአብሔር መልእክተኛን ሳይሆን የላከልን እርሱ ራሱ በእኛ መካከል አደረ፡፡ እኔ እንደማስበውም፣ በመገለጥ ተራራ ላይ የተነገረው ንዑስ ምንባብ ይኸው ነው፡፡ [ዶ/ር ግሌን ስኮርጂ] |
ሁለተኛው መመዘኛ፣ ሊናገር የተገባው ቃል እንደተሰጠው ኢየሱስ በግልጥ ተናግሯል፡፡
የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል
በዮሐንስ ምዕራፍ 14 ቁጥር 24 ላይ ኢየሱስ የተናገረውን ለምሳሌ እንውሰድ፡
የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። (ዮሐ 14፥24)
ኢየሱስ ተመሳሳይ የሆኑ ንግግሮችን እንደ ዮሐንስ ምዕራፍ 12 ቁጥር 49 እና ምዕራፍ 14 ቁጥር 10 በመሳሰሉትም ክፍሎች ላይ አድርጓል፡፡ እንዲያውም፣ በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ተብሎ ተገልጧል፡፡
በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ላይ አገልግሎት ላይ የዋለው “ቃል” የሚለው ቃል፣ በግሪኩ “ሎጎስ” የተሰኘው ቃል ለረጅም ዓመታት በነገረ-መለኮቱ ሊቃውን ሲወሳበት ቆይቷል፣ እናም በእርግጠኝነት በግሪኮቹ ዘንድ ስለ እግዚአብሔር አመክንዮ ወይንም እግዚአብሔር ጥበብ ስለመሆኑ አንድ መረዳት መኖሩ እውን ነው፡፡ የጌታ ቃል የሚለው ሃሳብ ግን፣ በብሉይ ኪዳን ገዢ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው፣ እናም ዮሐንስ በግሪኩ ፍልስፍና ውስጥ በብዥታ የምንጠቀምበትን ነገር በውል በማንሳት፣ ኢየሱስን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያዛምደዋል፣ ያንንም ሲያደርግ “ብርሃን ይሁን” አለ ሆነም ያለውን እግዚአብሔር የገለጠ ማለቱ ነው፡፡ ዮሐንስ እየተናገረ ያለው፣ ቃል ሥጋ ሲሆንና በእኛም መካከል ሲያድር፣ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመናት ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ በሙሉ ሥልጣንና በተግባቦታዊ ኃይል መጣ የሚለውን ነው፡፡ [ዶ/ር ስምዖን ቫይበርት]
በመጀመሪያ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ አንድ ስብዕና፣ ሁለተኛ ደግሞ፣ እንደ እግዚአብሔር ንግግር እናየዋለን፣ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዮሐንስ ግን እርሱን እንደ “እግዚአብሔር ቃል” ያቀርብልናል፡፡ በዚያ ረገድ ለእኛ እየነገረን ያለው አብን ለእኛ እንዲታወቅ ያደረገ የሚለውን የጌታችንን ሃላፊነት ነው፡፡ እናም የዕብራውያን ጸሐፊ ጌታን መቼም ቢሆን ያየው የለም፣ በእቅፉ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በግልፅ መጥቶ እርሱን ለእኛ ገለጠው ይለናል፡፡ [ዶ/ር ላሪ ኮክሬል]
ዮሐንስ፣ ከወንጌል ጋር የተገናኘ የትኛውንም ነገር ሲያደርግ፣ እርሱ እግዚአብሔር ነው፣ ምላሽ ልትሰጡት ይገባል፣ ወደሚለው ተመሳሳይ ነጥብ ነው የሚወስደን፡፡ ያም ወደ ዮሐንስ 20፥28 ያደርሰናል፡፡ በዚያም ዮሐንስ ኢየሱስን እንደ እግዚአብሔር፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለእኛ እንደሚናገር እንድንመለከተው ይፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ልንታመነው ይገባል፡፡ [ዶ/ር ጆን ማኬንሌይ]
ሦስተኛ፣ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ታማኝ የመሆንን ነቢያዊ ሃላፊነት ፈፅሟል፡፡
ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን
በአገልግሎቱ ዘመን ሁሉ፣ የአብን ፈቃድ ያስፈፀመ መሆኑን ኢየሱስ ደግሞ ደጋግሞ አመልክቷል፡፡ ይናገርና ያደርግ የነበረው ሁሉ አብ እንዲያደርግ ያዘዘውን ነበር፡፡ ይህንንም በበርካታ ስፍራዎች እንመለከታለን፣ ለምሳሌ፣ ዮሐንስ 5 ቁጥር 19 እና 30 እና ምዕራፍ 8 ቁጥር 28 ይጠቀሳሉ፡፡ ቃሎቹና ሥራዎቹም ከእርሱ በፊት በመጡ ነቢያት ከተነገሩት ጋር የሚጣጣሙ መሆኑን ኢየሱስም ግልፅ አድርጓል፡፡
ለአብነት ያህል፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 11 ከቁጥር 9 እስከ 14 የተጠቀሰውን የመጥምቁን ዮሐንስ አገልግሎት በማፅናት ተናግሯል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 12 ከቁጥር 38 እስከ 45 ነቢዩ ዮናስን ማረጋገጫ ሰጥቶበታል፡፡ በሉቃስ ምዕራፍ 4 ደግሞ በኢሳያስ ምዕራፍ 61 የተነገረውና በጌታ የተቀባው ነቢይ የመምጣቱ ሙላት አድርጎ ስለ አገልግሎት ተናግሯል፡፡ እንዲያውም፣ በተደጋጋሚና ባልተቋረጠ መንገድ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተገለጡ እውነቶችን ያረጋገጠ ሲሆን በእርሱም ውስጥ ምልዓታቸው መኖሩን ኢየሱስ አረጋጧል፡፡
ይህንንም በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 17 እንዲህ በመናገር ገልፆታል፡
እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። (ማቴ 5፥17)
በነዚህና በሌሎችም መንገዶች፣ ኢየሱስ የሚናገረውና የሚያደርገው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት በሚገልጥ መንገድ መሆኑን አሳይቷል፡፡
በመጨረሻ፣ ኢየሱስ የእርሱ ትንቢታዊ መልእክቶች በመፈፀማቸው የተረጋገጡ የመሆኑን መመዘኛ አሟልቷል፡፡
በመፈፀማቸው መረጋገጡ
ትንቢቶቹ የተፈፀሙ ስለሆኑ ኢየሱስ ባሙሉ ሥልጣን ነቢይ መሆኑን ወንጌላት በተደጋጋሚ ያረጋግጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ንግግሮቹ ወዲያውኑ እውን ይሆናሉ፣ ለምሳሌ ተፈጥሮን መቆጣጠሩ፣ አጋንንትን ማስወጣቱ፣ የታመሙትን መፈወሱ እና ሙታንን ማስነሣቱ ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም ረገድ፣ እንደ አየር፣ አጋንንቶች፣ በሽታ እና ሞትም እንኳን የእርሱን በሥልጣን የተሞላ ትንቢታዊ ትዕዛዝ ተቀብለው ይታዘዛሉ፡፡ በሌላ ወቅት ደግሞ፣ ትንቢቶቹ ቆየት ብለው ይፈፀማሉ፣ ያም የሚሆነው ስለወደፊቱ ሲናገር ነው፡፡
ለምሳሌ፣ በዮሐንስ ምዕራፍ 18 ቁጥር 9 ላይ ዮሐንስ ይህንን አስተያየት ሰጥቷል፡
ይህም። ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። (ዮሐ 18፥9)
በዚህ ስፍራ፣ ዮሐንስ እያጣቀሰ ያለው በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ቁጥር 2 ላይ ኢየሱስ የጸለየውን ካህናዊ ፀሎት ሲሆን፣ የሚያመለክተው የኢየሱስ ቃሎች መፈፀማቸውን ነው፡፡
እንዲያውም፣ ማቴዎስ ምዕራፍ 16 ቁጥር 21 እና ምዕራፍ 20 ቁጥር 18 እና 19 እና ዮሐንስ ምዕራፍ 18 ቁጥር 32 ውስጥ እንደምንመለከተው ስለማይቀረው ሞቱና ትንሣኤው ኢየሱስ የተናገረውም ተፈፅሟል፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ የትንቢት ፍፃሜዎች፣ ኢየሱስ እውነተኛው የእግዚአብሔር ነቢይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
የኢየሱስ ትንቢቶች ሁሉም በምድር ዘመኑ ተፈፅመዋል ማለት ግን አይደለም፡፡ ብዙዎቹ ወደፊት የሚፈፀሙ ነበሩ፣ አብዛኛውንም ጊዜ በቅርብ የወደፊት ጊዜ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮችም፣ የእነዚህ ትንቢቶች ፍፃሜ በታሪክም በሌላ ስፍራ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
ለምሳሌ፣ ኢየሱስ በሉቃስ ምዕራፍ 21 ከቁጥር 5 እስከ 6 የተናገረውን ትንቢት አድምጡ፡
አንዳንዶቹም ስለ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ። ይህማ የምታዩት ሁሉ፥ |
ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል አለ። (ሉቃ 21፥5-6) |
አይሁድ ኃጢአታቸውን ለመናዘዝ አሻፈረኝ በማለታቸው ምክንያት መቅደሳቸው የሚደመሰስ መሆኑን ኢየሱስ ተናገረ፡፡ ኢየሱስ ሲሞት ግን መቅደሱ አልፈረሰም ነበር፡፡ ግን ብዙም ሳይቆይ፣ ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ሲወርሩ በ70 ዓ.ም. ላይ ፈረሰ፡፡
የኢየሱስ ትንቢቶች በጠቅላላ አለመፈፀማቸው ግልፅ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት በሙላት ሊያፀና ገና ተመልሶ አልመጣም፡፡ ሆኖም ግን ይሆናል፡፡ ኢየሱስ የተናገራቸውን ተስፋዎች ሁሉ እንደሚፈፅም ያለምንም ጥርጥር ልናምንና ልናረጋግጥ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም የእርሱን ትንቢቶች በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በታሪክ ስንመረምር፣ ንግግሮቹ ሁሉ በመፈፀማቸው የተረጋገጡ ናቸው፡፡ ስለዚህም እርሱ የተናገራቸው ነገሮች ባለፉት ጊዜያት የተፈፀሙ ከሆነ፣ ወደፊትም እንደሚፈፀሙ እንጠብቃለን፡፡
ይህንን ያህል እንድንተማመን የሚያደርገን ነገር፣ ወደ ኋላ መለስ ብለን የብሉይ ኪዳንን ታሪክ ስንመለከት በጌታ ኢየሱስ መጀመሪያ መምጣት እግዚአብሔር የተናገራቸውን ተስፋዎች ሁሉ እንዴት እንደፈፀመ ማየታችን ነው፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ቁጥር 15 ከሰጠው የመጀመሪያ ተስፋ አንስቶ ደረጃ በደረጃ ዛሬ እኛ በእጃችን ያሉንን የትንቢት ቃሎች ጨምሮ፣ እግዚአብሔር ስለ ልጁ፣ ስለሚመጣው መሲህ ይናገር ነበር፡፡ እነዚያ ሁሉ ተፈፅመዋል፡፡ ከዛሬ 2000ዓመታት በፊት ሁሉም ተፈፅመዋል፡፡ እንግዲያው ኢየሱስ ተመልሶ እንደሚመጣ ሲናገር፣ በመጀመሪያው መምጣቱና በተጠናቀቀው ሥራው ምክንያት እና እግዚአብሔርም ባለፉ ዘመናት የተናገረውን ተስፋ እንደፈፀመ ሁሉ አሁንም የተናገረው እንደሚፈፀም እርግጠኞች እንሆናለን፡፡ [ዶ/ር ስቴፈን ዌሉም]
በበርካታ ምክንያቶች ስለ ኢየሱስ ዳግም መመለስ የተነገሩ ትንቢቶች እንደሚፈፀሙ እርግጠኞች ነን፡፡ ከሁሉ የሚቀድመው፣ ስለ መምጣቱ በብሉይ ኪዳን የተነገሩ ትንቢቶችን ፈፅሟል፡፡ ስለ እርሱም የተነገሩ ትንቢቶችም እንደተፈፀሙ እናውቃለን፡፡ ሁለተኛው ነገር ደግሞ፣ ከሞቱ፣ ከትንሣኤውና ወደ ሰማይ ከማረጉ በኋላ ተመልሶ ሁለት ጊዜ ለተከታዮቹ ተገልጦላቸዋል፡፡ አንደኛው፣ በደማስቆ መንገድ ላይ ለጠርሴሱ ለሳውል ኋላም ለሐዋርያው ጳውሎስ የተገለጠው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በፍጥሞ ደሴት ለሐዋርያው ዮሐንስ የተገለጠው ነው፡፡ እንግዲያው፣ ኢየሱስ ሕያው እንደሆነና በሰማያትም እንደሚኖር ለተከታዮቹም እንደሚገለጥ ማስረጃ አለን ማለት ነው፡፡ እንደማስበው ሦስተኛው ደግሞ፣ እንደ አማኞች በግል ሕይወታችን ያለፍንበት ልምምድ ሲሆን፣ ይህም የገባልን ተስፋ በሕይወታችን መፈፀሙ ነው፡፡ ራሳችንን ለእርሱ በሰጠን ወቅት ለወጠን ልጆቹም አደረገን፣ መንፈስ ቅዱስንም ወደ ሕይወታችን ላከ፡፡ ይህም በመላው ዓለም በተለያየ ስፍራ በሚገኙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ይፈፀማል፣ አንዳችን ከሌላችን ጋር ምንም ግንኙነት የለንም፣ ይህም የማያቋርጥ ልምምድ ሆኖ ይዘልቃል፣ አንድ ዓላማም እንዳለው እናውቃለን፡፡ አደርገዋለሁ ብሎ የተናገረውን ተስፋ ይፈፅማል ምክንያቱም መጀመሪያ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በእኛ ሕይወት ሲያደርገው አይተናልና አሁንም ያደርገዋል፡፡ ስለዚህም እኛም ይህንን ልናውቅና ልንታመነው ይገባናል፡፡ [ዶ/ር ጌራልድ ብሬይ]
ኢየሱስ የነቢይነትን አገልግሎት መመዘኛ ማሟላቱን ከተመለከትን፣ የነቢይነትን አገልግሎት ተግባራት የፈፀመበትን ሁኔታ ደግሞ እንመለከታለን፡፡
ተግባራት
በዚህ ትምህርት እንደተመለከትነው፣ ነቢያት የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን አምባሳደሮች ናቸው፡፡ ለህዝቡ የእርሱን ፈቃድ ያብራራሉ፣ ከዓመፃቸውም እንዲመለሱ ያሳስባሉ ደግሞም እግዚአብሔርን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ያበረታታሉ፡፡ በተለይ ደግሞ፣ ሦስቱን የተግባሮቻቸውን ገፅታዎች ማለትም፡ ሥልጣናቸውን፣ ሥራቸውን እና ዘዴዎቻቸውን ተመልክተናል፡፡
በዚህኛው በአሁኑ ነጥባችን ደግሞ፣ ኢየሱስ እንደ ነቢይ ያከናወናቸውን ተግባራት ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ተግባራት ጋር በማነፃፀር እናብራራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ኢየሱስም የእግዚአብሔርን ቃል የመናገር ሥልጣን እንደነበረው እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ፣ የእርሱ ሃላፊነት ከብሉይ ኪዳኖቹ ነቢያት ጋር ተመሳሳይ እንደነበር እናያለን፡፡ ሦስተኛ፣ ዘዴዎቹም ከእነርሱ ጋር ተመሳሳይ እንደነበር እናያለን፡፡ አስቀድመን ኢየሱስ እግዚአብሔርን ለመወከል ያለውን ሥልጣን እንመለከታለን፡፡
ሥልጣን
አዲስ ኪዳን ኢየሱስ በአባቱ ምትክ ሆኖ የመናገር ሥልጣን የነበረው መሆኑን እጅግ በስፋት ግልፅ ያደርግልናል፡፡ ይህንንም እንደ ዮሐንስ ምዕራፍ 7 ከቁጥር 16 እስከ 19፤ ምዕራፍ 12 ቁር 49 እና 50 እና ምእራፍ 14 ቁር 24 በመሳሰሉት ስፍራዎች እናየዋለን፡፡ በነዚህም ምንባቦች፣ ከእግዚአብሔር አብ በተሰጠው ሥልጣን ይናገራል፡፡
በዮሐንስ ምዕራፍ 7 ከቁጥር 16 እስከ 19 በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ሰዎች ኢየሱስ እንዲህ ተናግሯል፡
ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ |
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። |
ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም። |
ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? (ዮሐ 7፥16-19) |
ኢየሱስ ከአብ የተቀበለው ሥልጣን አርሱን የተቀበለ አብን መቀበሉን፣ እርሱን የናቀ ግን አብንም መናቁን በተናገረበት ትምህርትም ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ይህም እጅግ ብዙ ብዙ በሆኑ ምንባቦች ውስጥ እንደ ማቴዎስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 40፤ ማርቆስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 37፤ ሉቃስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 48፤ ዮሐንስ ምዕራፍ 13 ቁር 20 እና ምዕራፍ 12 ቁጥር 44 የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
አንዱን ለምሳሌ ብንወስድ፣ በሉቃስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 46 ኢየሱስ የተናገረውን አድምጡ፡
የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል። (ሉቃ 10፥16)
ከእግዚአብሔር ባለ ሙሉ ሥልጣን መልዕክተኛና ከመልእክቱ የሚሸሹ ሁሉ በስተመጨረሻ የመልእክቱን እርግጠኝነት መረዳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን፣ ይህንን ሲያደርጉ ምላሽ የመስጠት እድላቸውን እያጡ ነው፡፡
ኢየሱስ በዮሐንስ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 26 እስከ 28 ለተቃዋሚዎቹ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ አድምጡ፡
ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ አላቸው። |
ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም። |
ስለዚህም ኢየሱስ፦ የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። (ዮሐ 8፥26-28) |
ይህንን የኢሱስን ትንቢታዊ ሥልጣን በልቡናችን ይዘን፣ አሁን ደግሞ ኢየሱስ ሊያከናውን የመጣውን ተግባር እንመለከታለን፡፡
ተግባር/ሥራ
ቀደም ብለን እንደጠቀስነው፣ ነቢያት የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን አምባሳደሮች በመሆናቸው ምክንያት፣ የቃል ኪዳኑን ዝርዝር ጉዳዮች ለእግዚአብሔር ህዝብ የማሳሰብ እና በዚያም መሠረት እንዲታዘዙ የማበረታታትን ተግባር እንዲያከናውኑ ተሹመዋል፡፡ ኢየሱስም እንደ ነቢይነት ሃላፊነቱ፣ ይህም ለእርሱ የተሰጠ ሥራ ነው፡፡ በተለይም ይህንን የምንመለከተው ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት የመጨረሻው እርከን የመጣ መሆኑን ባወጀበት የምሥራች ወንጌል ውስጥ እንመለከታለን፡፡
በመጀመሪያ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ባስተማረባቸው ትምህርቶቹ ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ንጉሥነትና ሥልጣን ያውጃል፣ በዚህም እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እውንነት ያረጋግጣል፡፡ ይህንንም በማቴዎስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 10፣ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር እንድትመጣና ፈቃዱም እንዲፈፀም ያስተማረበትን የጌታን ጸሎት ጨምሮ በበርካታ ስፍራዎች እንመለከተዋለን፡፡
ሁለተኛ፣ ኢየሱስ በተጨማሪም ዛሬም ቢሆን የቃል ኪዳኑ ዝርዝሮች በብርቱ ትግል ውስጥ እንዳሉና ሰዎችም ሊታዘዙዋቸው እንዳልቻሉ አረጋግጧል፡፡ ይህንንም ሰዎች ከኃጢአታቸው በንስሓ እንዲመለሱ ባሳሰበበት መልእክት ማለትም በማቴዎስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 17፤ ማርቆስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 15 ውስጥ ይገኛል፡፡
ሦስተኛ፣ ኢየሱስ ቃል ኪዳኑን ተከትለው የሚመጡ ቅጣቶችንም አመልክቷል፡፡ ለምሳሌ፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 23 በተገለጡት ሰባቱ ወዮዎች ውስጥ፣ የእግዚአብሔር ሰዎች ከእርሱ ፍርድ ያመልጡ ዘንድ እንዲታዘዙ ኢየሱስ ያነሳሳቸው ነበር፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ከቁጥር 3 እስከ 12 ባለው በተራራው ስብከት መግቢያ ላይ በተቀመጠው ቡራኬ፣ የእግዚአብሔር ህዝብ የእርሱን በረከት ይቀበሉ ዘንደ ምህረትን እንዲለምኑ ኢየሱስ አበረታቷል፡፡
በሉቃስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 17 እስከ 21 ውስጥ ኢየሱስ በአደባባይ አገልግሎቱ ጅማሬ ላይ ተግባሩን ጠቅለል አድርጎ ያቀረበበትን መንገድ አድምጡ፡
የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። |
መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። |
እርሱም፦ ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር። (ሉቃ 4፥17-21) |
በዚህ ስፍራ፣ ኢየሱስ ራሱን በኢሳያስ ምዕራፍ 61 እንደተተነበየው የእግዚአብሔር መንግሥት ተሃድሶ ምሥራች አብሳሪ ወይንም ተናጋሪ አድርጎ አቅርቧል፡፡
እግዚአብሔር በጠላቶቹ ላይ ሊፈርድና መንግሥቱንም በእስራኤል አማካይነት በምድር ሁሉ ሊያሰፋ ሲመጣ፣ ይህንን ሥራውን በአንድ ልዩ ነቢይ በኩል ይጀምራል በማለት ኢሳያስ ያስተምራል፡፡ ያም ነቢይ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች በማለት የምሥራቹን ወይንም ወንጌሉን ያውጃል፡፡ በዚያም አዋጅ ፍሰት ውስጥ፣ ነቢዩ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ህዝብ ስለሚጠበቅበት ግዴታ ያሳስባል፣ ከቃልኪዳኑ እርግማን ያመልጥም ዘንድ ንስሓ እንዲገባ፣ ደግሞም የቃል ኪዳኑን በረከቶች ይቀበል ዘንድ በታማኝነቱ እንዲፀና ያበረታታል፡፡ ኢየሱስ ራሱ በሰጠውም ምስክርነት መሠረት፣ ጌታችን ያ ነቢይ ነበር፡፡
በእግዚአብሔር መንግሥትና በወንጌል መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ውስጥ፣ የተመዘገበው የኢየሱስ የመጀመሪያ ቃሎች “ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” የሚሉ ነበሩ፡፡ ወንጌል የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ልትገዛ የመጣች መሆኗን የሚያውጅ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ኢየሱስ ያደረጋቸው ተዓምራት በጠቅላላ የመጣችው መንግሥት ምልክቶች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት እና ህጉ በዚህ እስከ ሆነ ድረስ ኃጢአታችን ተሰርዮአል፡፡ ዕውራን አይተዋል፡፡ አንካሶች ዘለዋል፡፡ ለምፃሞች ነፅተዋል፡፡ አጋንንቶች ወጥተዋል፣ ሙታንም ተነሥተዋል፡፡ የምሥራቹ ያ ነው፡፡ በመሠረቱ የምሥራች ዋነኛው አስኳል መስቀሉ ነው፡፡ ያም የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው፡፡ ኢየሱስ ካልሞተና ካልተነሣ፣ ድነትን ሊያስገኝልን አይችልም፡፡ የሞትንም ኃይል ሊሰብር አይችልም፡፡ የእግዚአብሔርም መንግሥት ወደ እኛ አትመጣም ነበር፡፡ ስለዚህም፣ ወንጌል ከሁሉ የሚልቅ ዜና ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት ለሰው ዘር ሁሉ ታላቁ በረከትና ደስታ ነው፡፡ [ዶ/ር ፒተር ቾው]
በአዲስ ኪዳን ቸል ከማይባሉ ጥያቄዎች መካከል አንዱ በእግዚአብሔር መንግሥትና በወንጌል መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት በወንዶችና በሴቶች ልብ ውስጥ የእግዚአብሔር ህግጋት ሲገዙ፣ አገዛዙና ንግሥናውም በህይወታቸው በእያንዳንዲቷ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲገለጥ ነው፡፡ አገዛዙና ንግሥናው የሚመጣበትም መንገዱ የወንጌሉ መልእክት፣ ኢዋንጀሊዮን፣ የምሥራች የምንለው ሲሆን፣ ያም ኃጢአታቸውን ያስተሰርይ ዘንድ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ነፍሱን ሰጠ የሚለው ነው፡፡ በዚያም የሚለውጥ የወንጌል ኃይል አማካይነት፣ በአካባቢያቸው ያለውን ዓለም ይለውጡና የእግዚአብሔርም መንግሥት ሥራ በሕይወታቸው ይገለጥ ዘንድ ተጠርተዋል፡፡ [ዶ/ር ጄፍ ሎውማን]
የኢየሱስን ነቢያዊ ሥልጣንና ተግባር ከተመለከትን፣ አሁን ደግሞ አገልግሎቱን ለመፈፀም የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች እንመለከታለን፡፡
ዘዴዎች
እንደ ብሉይ ኪዳኑ ነቢያት ሁሉ፣ ኢየሱስም ነቢያዊ ተግባሩን ለማከናወን የተጠቀመበት ተቀዳሚ ዘዴ መናገር ነው፡፡ ማለትም፣ ሰዎች ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርገው የእግዚአብሔርን ቃሎች ለእነርሱ በመናገር ነው ማለት ነው፡፡ ስለ ኃጢአት ይወቅሳቸዋል፤ በቅዱሳት መጻሕፍትም እንደተገለጠው ይናዘዙና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይፈፅሙ ዘንድ ያዛቸዋል፤ በታማኝነትም እንዲጠብቋቸው ያበረታታቸዋል፤ ስለ መጪው ፍርድ ያስጠነቅቃቸዋል ደግሞም ታማኝ የሆኑት ስለሚጠብቃቸው በረከትም ይናገራል፡፡ ምሳሌዎችን ይነግራቸዋል፡፡ ስለወደፊቱ ይነግራቸዋል፡፡ ይጸልያል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ህዝብም ይማልዳል፡፡
አስገራሚ የሆነው ነገር፣ ኢየሱስ ያላከናወነው አንድ ነገር ቢኖር ትምህርቶቹን ለእኛ በጽሑፍ አለማስቀመጡ ነው፡፡ ግን፣ ልክ እንደ አንዳንድ የብሉይ ኪዳን ነቢያት፣ ይህንን በእርሱ ፋንታ የሚያከናውኑለት ነቢያት ነበሩት፡፡ አዲስ ኪዳን የኢየሱስን ነቢያዊ አገልግሎት የያዙና በደቀመዛሙርቱ የተፃፉ አራት ወንጌላት አካቷል፡፡ እነርሱም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ናቸው፡፡
አሁንም አንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያት ሁሉ፣ ኢየሱስም ትንቢታዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከንግግር ባሻገር ሌሎች ዘዴዎችንም ተጠቅሟል፡፡ እነዚያም ዘዴዎች በንግግር ከሚደረግ ተግባቦት ይልቅ በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ይህም እውነተኛ መሆኑን የሚያረጋግጡልን ተዓምራቶቹ ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር ህዝብ ታሪክ ውስጥ ከተነሱ ነቢያት ሁሉ ይልቅ ኢየሱስ በርካታ ተዓምራትን አከናውኗል፡፡ የኢየሱስ ተአምራዊ የአገልግሎት ኃይል የእግዚአብሔር ህጋዊ አምባሳደር መሆኑን አረጋግጠዋል፤ ኢየሱስ የተናገራቸው ንግግሮችም ሁሉ ጠንካራ አምላካዊ ይሁንታ ያላቸው መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
ኢየሱስ በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ቁጥር 25 እንደተናገረው፡
ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ (ዮሐ 10፥25)
እንደ ብሉይ ኪዳኑ ነቢያት ሁሉ ኢየሱስ ተምሳሊታዊ ተግባራትንም አከናውኗል፡፡ ለምሳሌ፣ በማቴዎስ 3 ከቁጥር 15 እስከ 17 እንደተመዘገበው ኢየሱስ በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል፡፡ በተጨማሪም እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያት ሁሉ፣ ከመንፈሳዊ ኃይላትም ጋር ተፋልሟል፡፡ ለምሳሌ፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 11 እና በሉቃስ ምዕራፍ 4 ከቁጥር 1 እስከ 13 እንደተመዘገበው የዲያቢሎስን ፈተና ድል አድርጓል፡፡ በማርቆስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 25 እና 26 ደግሞም ምዕራፍ 5 ቁጥር 13 እንደምናየው አጋንንትን አስወጥቷል፡፡
የኢየሱስን ነቢያዊ ሥልጣን፣ ሥራ እና ዘዴ በመመልከት፣ እርሱ በእውነት የነቢይነትን አገልግሎት እንደፈፀመ እናያለን፡፡ በዚህም ምክንያት፣ እርሱ የተነበያቸው ሁሉ እንደሚፈፀሙ፤ የኢየሱስም ንግግሮች የታመኑና እውነተኛ መሆናቸውን እናረጋግጣለን፡፡ እንግዲያው እርሱን ልንሰማውና ንግግሮቹንም ልንፈፅም ግዴታ አለብን፡፡ በእግዚአብሔር ማኅበረሰብ ውስጥ ለምንገኘው ለእኛም፣ የኢየሱስን ንግገሮች መታዘዛችን የቃል ኪዳኑን በረከቶች ወደመቀበል ያመራናል፣ አለመታዘዛችን ደግሞ ቅጣቱን ያስከትልብናል፡፡ የእግዚአብሔር ህዝብ ላልሆኑት ደግሞ፣ የኢየሱስ ትንቢታዊ ንግግሮች እርሱን የተቃወሙ ሁሉ ስለሚጠብቃቸው ፍርድ የሚናገሩ ማስጠንቀቂያዎች ሲሆኑ ከኃጢአታቸው በንስሓ ለሚመለሱና እርሱን በእምነት ለሚቀበሉ ሁሉ ደግሞ የዘላለምን ሕይወት የሚያስገኙ ናቸው፡፡
ኢየሱስ የነቢይነትን አገልግሎት መመዘኛዎችና ተግባራት ያሟላ መሆኑን ከተመለከትን፣ ብሉይ የወደፊት ነቢያት እንዲያሟሉ የሚጠብቅባቸውን እንዴት እንዳሟላ በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
ጥበቃ
በዚህ ትምህርታችን ጅማሬ ላይ፣ በብሉይ ኪዳን ማክተሚያ ላይ፣ በእግዚአብሔር መንግሥት የመጨረሻ እርከን ላይ ከነቢያት የሚጠበቁ ቢያንስ ሦስት ነገሮች ነበሩ፡፡ እነርሱም፡- ስለ ጌታ የሚነገር ትንቢታዊ ድምጽ፤ እንደ ሙሴ ያለ የመጨረሻ ነቢይ እና ትንቢታዊ ህዳሴ ናቸው፡፡ ቀጥለን እንደምንመለከተውም፣ ሦስቱም ጥበቃዎች በኢየሱስ ስብዕናና አገልግሎት ወደ ፍፃሜ መጥተዋል፡፡ ስለ ጌታ ከተነገረ ትንቢታዊ ድምፅ በመጀመር፣ ከኢየሱስ ጋር በተገናኘ መንገድ ሦስቱንም ጥበቃዎች እንዳስሳለን፡፡
ስለ ጌታ የሚነገር ትንቢታዊ ድምፅ
የሚጠበቀው ትንቢታዊ ድምጽ በኢሳያስ ምዕራፍ 40 ከቁጥር 3 እስከ 5 ባለው ተጽፏል፣ እንዲህም ይነበባል፡፡
የአዋጅ ነጋሪ ቃል። የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካክሉ። |
ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል |
የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። (ኢሳ 40፥3-5) |
በዚህ ስፍራ ጌታ እንደሚመጣና ጠላቶቹን ድል በማድረግ የዳዊትን ዙፋን እንደሚያስመልስ አንድ ለየት ያለ ነቢይ እንደሚያውጅ አስቀድሞ ተነግሮ እንመለከታለን፡፡
በመሠረቱም፣ ኢየሱስ ራሱም ጠላቶቹን ድል ሊነሳ እና በዳዊት ዙፋንም ላይ ሊቀመጥ መጥቷል፡፡ ስለ መጨረሻው ዘመንና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የተነገሩ ትንቢቶች ሁሉ በኢየሱስ በኩል እንዲፈፀሙ እግዚአብሔር አድርጓል፡፡ ግን አዋጅ ነጋሪው ማን ነበር? ስለ ጌታ የተነገረው የትንቢት ቃል በኢየሱስ የተሟላው እንዴት ነው? ስለ ኢየሱስ መምጣት ያወጀው፣ መጥምቁ ዮሐንስ ነበር፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ቁጥር 23 ላይ መጥምቁ ዮሐንስ የተናገረውን አድምጡ፡
እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። (ዮሐ 1፥23)
መጥምቁ ዮሐንስ ጠላቶቹን ድል ሊነሳና ህዝቡን ሊባርክ እንደሚገሰግስ ጦረኛ እግዚአብሔር የሚመጣ መሆኑን እንዲያውጅ ተልኳል፡፡ መጥምቁ አዋጅ የነገረለትም ኢየሱስ ነው፡፡
በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 32 እስከ 34 የተፃፈውን አንብቡ፡
ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። |
እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። |
እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ። (ዮሐ 1፥32-34) |
ዮሐንስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ፣ ጠላቶቹንም ድል በመንሳት የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደሚያመጣና በዳዊት ዙፋን ላይ እንደሚቀመጥ በማወጅ ትንቢታዊ ተልዕኮውን ፈጽሟል፡፡
ኢየሱስ የፈፀመውና ብሉይ ኪዳን ከወደፊት ነቢያት ከሚጠብቀው አንዱ እንደሙሴ ያለ ነቢይ የሚመጣ መሆኑ የተነገረበት ነው፡፡
እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ
በዘዳግም ምዕራፍ 18 ቁጥር 16 ላይ፣ ሙሴ እነዚህን ቃላት ለእስራኤል ተናግሯል፡
አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል እርሱንም ታደምጣለህ። (ዘዳ 18፥16)
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 3 ቁጥር 22 እና 23 ላይ፣ ጴጥሮስ ኢየሱስ ብሉይ ኪዳን የተናገረለት እንደ ሙሴ ያለው ነቢይ እንደሆነ ለይቶ ተናግሯል፡፡
ኢየሱስ ከሙሴ ዘመን አንስቶ ተደርገው የማያውቁ ተዓምራቶችን አከናውኗል፡፡ ከሙሴ ዘመን ጀምሮ ማናቸውም ከነበራቸው ኃይል በላይ በሆነ መጠን ትንቢት ተናግሯል፡፡ እንደ ሙሴ ሁሉ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አይቷል፡፡ ለእርሱ ትንቢታዊ አስተምህሮዎች ከእምነት የሆነ ምላሽ የሚሰጡ ሁሉ ቃል ኪዳኑን እንደሚጠብቁ ፍፁማን እንደሚቆጠሩና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን መንግሥት በረከቶችን በሙላት እንደሚወርሱ ኢየሱስ ዋስትና ሰጥቷል፡፡
ይህንንም በዕብራውያን ምዕራፍ 3 ቁጥር 5 እና 6 ላይ እናነብባለን፡
ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ፥ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው፤ |
እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን። (ዕብ 3፥5-6) |
በመሠረቱ፣ ኢየሱስ ከሙሴ ዘመን ጀምሮ ታላቅ የሆነው ነቢይ ብቻ ሳይሆን፣ በየትኛውም ዘመን ከተነሱት ሁሉ የሚልቅ ነቢይ መሆኑን አዲስ ኪዳን ያስተምራል፡፡ ዕብራውያን ምዕራፍ 1 ቁጥር 1 እና 2 እንደሚያስተምረን፣ ከኢየሱስ በፊት የእግዚአብሔር ሥራ በነቢያቱ አማካይነት ለረጅም ዘመናት የተከናወነ ሲሆን በተለያዩ መንገዶችና ጎዳናዎችም ይከናወኑ ነበር፡፡ በዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት ኅዳሴ ዘመን ግን፣ በዘመናት ሁሉ ከተነሱት በሚበልጠው በልጁ በኩል ኩሁሉ የላቀውን መገለጡን ሰጠን፡፡ በዮሐንስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 18 እና ምዕራፍ 14 ቁጥር 9 ላይ እንደምናየው፣ ኢየሱስ የአብ ማንነት፣ ፈቃድና ማዳን ምሉዕና ግልፅ መገለጥ ነው፡፡ በመሠረቱ፣ እንደ ዮሐንስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 14 አገላለጥ ኢየሱስ ሥጋ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡
የኢየሱስ መገለጥ ከእርሱ ከቀደሙት ከሌሎቹ ነቢያት ሁሉ የላቀ የመሆኑ እውነታ የሚያርፈው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል አዋጅ ነጋሪ በመሆኑ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ሥጋ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ላይ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በአካል ገለጠው፡፡ ከእርሱ በፊት የነበሩት ነቢያት ሁሉ፣ አገልግሎታቸው የሚደነቅ ቢሆንም፣ የእግዚአብሔር ቃል መልእክተኞች ብቻ ነበሩ፡፡ ኢየሱስ፣ ሲመጣ ግን፣ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል መልእክተኛ ነው፤ በእርግጥም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሰብኳል፤ የንስሓ ስብከትም ሰብኳል፤ የእግዚአብሔርንም ትዕዛዛት አውጇል፤ ይህንን ያደረገው ግን ትስጉተ እግዚአብሔር በመሆኑ ምክንያት ነው፣ እርሱ የእግዚአብሔር ማንነት መገለጫ ነው፡፡ [ዶ/ር ሮብ ሊስተር]
ኢየሱስ እንደ ነቢይ ሲመጣ፣ ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ ሆኖ እነዚህን ሁሉ ሃላፊነቶቹን በእስራኤል ውስጥ ሊፈፅም መጣ፣ ሁሉም በክርስቶስ ተፈፅመዋል፡፡ እንደ ነቢይ ሙሴ ራሱ እንደ እኔ ያለ ብሎ ተንብዮለታል፡፡ ስለዚህም ሌሎቹንም ትንቢቶች ወደ ፍፃሜ ያመጣቸዋል፣ ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር በልጁ በኩል ለመጨረሻ ጊዜ የተናገረን ሌሎቹ ሁሉ አምላክ ስላልሆኑና የእግዚአብሔርን ሙሉ መገለጥ በውስጣቸው በሙላት ስላልያዙ ነው፡፡ አሁን ግን እውነተኛ የሆነው ገላጭ መጣ፡፡ እርሱ ራሱ አምላክ ነውና እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ያውቃል፡፡ የእግዚአብሔርን እቅዶች ሁሉ ያውቃል፣ የእግዚአብሔርንም ቅድስና ያውቃል፡፡ እግዚአብሔርን ለመማፀን ምን እንደሚያስፈልግ በትክክል ያውቃል፡፡ እግዚአብሔር ግድ የሚለውን ነገር ሁሉ ያውቃል፣ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔር የሚፈልገውን ሁሉ ያውቃል፡፡ እናም፣ የክርስቶስ ደግነትና ትኅትና በማንነቱ፣ ከዚያም በንግግሮቹ እንደ እኛ ነቢይ መገለጡ ክርስቶስ ፈቅዶ ከገለጠልን ውጪ ሌላ መገለጥ የማያስፈልገን መሆኑን ያሳያል ምክንያቱም እርሱ ሊገለጥልን የሚገባውንና ሊገለጥልን የማይገባውን የሚያውቅ ጥበበኛ ነውና፡፡ እርሱ በሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ እንከን የለሽ ተምሳሊታችንና መደምደሚያ የሆነውን እውነት የገለጠልን ራሱን የማይሰውር ሊታወቅ የሚችል አምላክ ነው፡፡ እርሱ ፍፁም የሆነ ነቢይ ነው፡፡ [ዶ/ር ቶማስ ኒትለስ]
ኢየሱስ የነቢይነት አገልግሎት ምልዓት የመሆኑ ወሳኝነት ተጋነነ ሊባል አይገባም፡፡ እርሱ ፍፁም ግልፅ የሆነው፣ የአብን ፈቃድና ዓላማዎች የገለጠ እውነተኛው መገለጥ ሲሆን፣ መንግሥቱንም ለማምጣት አብ የሚሻቸውንና ተስፋዎቹን የገለጠ ነቢይ ነው፡፡
ብሉይ ኪዳን ከትንቢት አገልግሎት የሚጠብቀውና በኢየሱስ የተፈፀመው ሦስተኛ መንገድ ከነቢይነት አገልግሎት ኅዳሴ ጋር በተገናኘ መንገድ የተገለፀው ነው፡፡
የነቢይነት አገልግሎት ኅዳሴ
እንደተመለከትነው፣ ብሉይ ኪዳን ሀሰተኛ ነቢያት ተወግደው እውነተኞቹ ግን በእግዚአብሔር ህዝብ መካከል ደጋግመው የሚገለጡበት ዘመን እንደሚመጣ ተስፋ ሰጥቶ ነበር፡፡ እናም በኢየሱስ በኩል፣ ይህ ጥበቃ እውን ሆኗል፡፡ የእውነተኞቹን ነቢያት መበርከት አስመልክቶ፣ ነገሩ የጀመረው በርካቶቹ ሐዋርያት በዓለም ዙሪያ ቃሉን በኃይል እንዲሰብኩ በሾመበት ወቅት ነው፡፡ በበዓለ ሃምሳ ቀን መንፈሱን በቤተክርስቲያን ላይ ሲያፈስስ፣ በውጤቱም ሁሉም በልሳኖች በመናገራቸው በስፋት እየቀጠለ ሄደ፡፡
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4 ላይ የዚህ ሁነት መግለጫ የተቀመጠ ሲሆን፣ ጴጥሮስም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 14 እስከ 18 የሰጠውን ማብራሪያ አድምጡ፡
በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። |
ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው። አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። |
ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ |
ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። |
እግዚአብሔር ይላል። በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ |
ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። (ሐሥ 2፥4.፣14-18) |
በቀደመችው ቤተክርስቲያን፣ ኢየሱስ ቤተክርስቲያንን ለትንቢት አገልግሎት ለማዘጋጀት መንፈሱን ላከ፡፡ ምንም እንኳን በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ያንን መሳዩ የትንቢት አገልግሎት ስለመቀጠሉ ሙግት ቢኖርም፣ መንግሥቱን በምድር መመሥረት በጀመረበት የመጀመሪያ ዘመን ውስጥ ቤተክርስቲያኑን ለመመሥረት ኢየሱስ የተጠቀመበት እጅግ ወሳኝና ኃይለኛ አገልግሎት የመሆኑን ነገር ማንም አይጠራጠርም፡፡
ግን የሃሰተኛው ትንቢትስ ጉዳይ? ብሉይ ኪዳን የሃሰተኛ ነቢያትን ማክተም አስመልክቶ የነበረው ጥበቃ በኢየሱስ የተፈፀመው እንዴት ነው? ከሁሉ በላይ፣ በርካታ የአዲስ ኪዳን ምንባቦች የሃሰት ትንቢት የቤተክርስቲያን ቀጣይ ችግር መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ይህንንም በማቴዎስ ምዕራፍ 7 ቁጥር 15፣ ምዕራፍ 24 ቁጥር 11 እና 24፤ 2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 1፤ 1ኛ ዮሐንስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 1 እና በሌሎችም በርካታ ምንባቦች ውስጥ እንመለከተዋለን፡፡
መልሱ መንታ ነው፣ በአንድ ወገን፣ የሃሰት ትንቢት መገታት የሚጀምረው እውነተኞቹ ሲበዙና ተግባራቸውም ሃሰተኛ ነቢያትን መለየትና ማውገዝ ሲሆን ነው፡፡
ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14 ቁጥር 29 በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ትምህርት አድምጡ፡
ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ (1ቆሮ 14፥29)
የእውነተኞቹ የቤተክርስቲያን ነቢያት አንዱ ተግባር ሃሰተኞቹን ትንቢቶች ከስረመሠረታቸው መመርመር መሆኑን ጳውሎስ ግልፅ አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሃሰት ትንቢት ቀጣይ ችግር መሆኑ ነው፡፡ በስተመጨረሻ ግን፣ ኢየሱስ ሃሰተኛ ነቢያትንና ንግግሮቻቸውን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳቸዋል፣ ለፍርድ ሲመጣና መንግሥቱንም ሲያፀና፣ ሊሻር በማይቻል ሁኔታ ሀሰተኛ ነቢያትን ያጠፋል፡፡ እስከዚያች ቀን ድረስ፣ ኢየሱስ መንግሥቱን እንዳወጀ እና ሀሰተኛ ትንቢትንም እንደሚገታ እናውቃለን ሆኖም ግን ሀሰተኛ ትንቢትን ለዘላለም የሚያስወግድበት ፍርድ ገና ባለመምጣቱ በውጥረት ውስጥ እንኖራለን፡፡
ኢየሱስ የነቢይነትን አገልግሎት መመዘኛ ያለ እንከን አሟልቷል፤ በታማኝነትና በእውነትም የነቢይነትን ተግባር ፈፅሟል፤ ብሉይ ኪዳን ከነቢይነት አገልግሎት የሚጠብቀውንም አሟልቷል፡፡ ያም የምሥራች ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ እንደሚነሳና ህዝቡንም ለቃል ኪዳኑ ታማኝ ወደመሆን እንደሚመራ እግዚአብሔር ለህዝቡ ተስፋ ሰጥቷል፡፡ እናም አሁን፣ በኢየሱስ፣ ያ ተስፋ ተፈፅሟል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ኢየሱስን በዘመናት ሁሉ ከተነሱት ነቢያት ሁሉ በላይ እውቅናና ከበሬታ ልንሰጠው ይገባል፤ ንግግሮቹንም ልናደምጥና ልናምናቸው ይገባል፤ ለትምህርቶቹም ልንገዛና ልንታዘዝ ይገባናል፡፡ ትንቢታዊ ቃሎቹም፣ እርግጠኛ መሆናቸውን በማመን፣ ወደ እግዚአብሔር የቃል ኪዳን በረከቶች እንደሚመሩንም በማሰብ የምናደርገውን ሁሉ ልናደርግ ይገባናል፡፡
ስለ ትንቢት አገልግሎት የብሉይ ኪዳኑን ዳራና የአዲስ ኪዳኑን ሙላት ከመረመርን፣ አሁን ወደ ሦስተኛው ርዕሳችን እንሸጋገራለን፣ እርሱም የኢየሱስ ትንቢታዊ ሥራ ለዘመኑ ያለው ተዛምዶ ነው፡፡
- ዘመነኛው ተዛምዶ
የክርስቶስን ትንቢታዊ ሥራ ከዘመናችን ጋር የማዛመዱን ነገር ለመመልከት ምቹው አቀራረብ በትልቁ ካቴኪዝም፣ መልስ ቁጥር 34 ውስጥ የተቀመጠውን መመልከት ነው፡፡ እንዲህም ይላል፡
ኢየሱስ የነቢይነትን አገልግሎት የፈጸመው፣ በቃሉና በመንፈሱ ራሱን በመግለጥ፣ የእግዚአብሔርንም ምሉዕ ፈቃድ ማለትም ድነታቸውንና መታነፃቸውን ጨምሮ በየዘመናቱ በምትገኘው ቤተክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ መንገዶች በማስተዳደር ነው፡፡
በዚህ መልስ ውስጥ፣ ካቴኪዝሙ የክርስቶስን ነቢያዊ ሥራ ለቤተክርስቲያን ራሱን ከመግለጡ አንፃር ጠቅለል አድርጎ አቅርቦታል፡፡ ቢያንስ ሁለት የክርስቶስን የመገለጥ ሥራዎች ጠቅሷል፡፡ በመጀመሪያ፣ ስለ ክርስቶስ መጠነ ርዕይ የሚናገር ሲሆን፣ በየዘመናቱ ሁሉ፣ በተለይም፣ በመንፈሱና በቃሉ፣ እና በተለያዩ አስተዳደራዊ መንገዶች መገለጡን ያወሳል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ የክርስቶስን ትንቢታዊ መገለጥ ይዘት ይገልፃል፣ ለመጥቀስም፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ ማለትም መታነፃቸውንና ድነታቸውንም ጭምር ማለት ነው፡፡
የዌስት ሚኒስትሩ ትልቅ ካቴኪዝም የሰጠው ማጠቃለያ ጠቃሚ በመሆኑ ምክንያት የኢየሱስን ትንቢታዊ ሥራ አስመልክቶ በዘመናችን ለምንጠቀምበት ተዛምዶ እንደ ሞዴል እንጠቀምበታለን፡፡ በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ የሰጠውን ትንቢታዊ መገለጥ መጠነ ርዕይና በሕይወታችን ያለውን አንድምታ እንመለከታለን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ ከክርስቶስ በተቀበልነው ትንቢታዊ መገለጥ ይዘት እና በእኛ ላይ ባኖረው ግዴታ ላይ እናተኩራለን፡፡ እስኪ ከነቢያችን ከኢየሱስ ከተቀበልነው መጠነ ርዕይ እንጀምር፡፡
መጠነ ርዕይ
ካቴኪዝሙ በየዘመናቱ ሁሉ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን በቃሉና በመንፈሱ፣ ደግሞም በተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች መገለጥን የሰጠ መሆኑን ሲናገር፣ ክርስቶስ በቅዱሳት መጻሕፍት በጠቅላላና በእውነተኛ ትንቢት የተናገረን የመሆኑን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ማረጋገጡ ነው፡፡
ኢየሱስ ራሱ ብዙ ትንቢታዊ ቃላትን ተናግሯል፣ ግን ደግሞ ከእርሱ በፊትና በኋላ የተነሱ እውነተኛ ነቢያትን አብርሆት ይሰጥና እነርሱም አገልግሎታቸውን በተለያዩ መንገዶች ይፈፅሙ ዘንድ ቅዱስ መንፈሱንም ልኳል፡፡ ከዚህ ሂደት ልንመለከት የሚገባን እጅግ ጠቃሚ ነገር፣ ብሉይና አዲስ ኪዳንን ያካተተው፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለቤተክርስቲያኑ የሰጠው ትንቢታዊ ቃል መሆኑን ነው፡፡
ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ቃል ነው ብሎ ማሰብ እንግዳ ሊመስል ይችላል፡፡ እንዲያውም፣ ኢየሱስ ከቅዱሳት መጻሕፍት አንዳቸውንም አልጻፈም፡፡ በወንጌላት ውስጥ እንኳን፣ የእርሱ ንግግሮች ከተጠቀሱባቸው ውጪ በርካታ ነገሮች ተካትተዋል፡፡ ግን በቤተክርስቲያን የታሪክ ዘመናት ሁሉ ያልተቋረጠ አስተምህሮ ሆኖ ዘልቋል፡፡
ለአብነት ያህል፣ ቀደምት የቤተክርስቲያን አባት የሆነው ኦሪገን በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ጅማሬ ላይ በተጻፈው First Principles በተሰኘው ጽሁፉ መቅድም ውስጥ የቅዱሳት መጻሕፍትን አብርሆት ከመስጠት አንፃር ስለ ክርስቶስ ትንቢታዊ ሥራ ጽፏል፡፡ እስኪ ምን እንዳለ አድምጡ፡
የክርስቶስ ንግግሮች ስንል፣ ይህንንም ስንል ሰው ሆኖ ሲመጣ የተናገረውን ብቻ ማለታችን ሳይሆን… ከዚያን ዘመን ቀደም ብሎ፣ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ቃል በሙሴና በነቢቱም ውስጥ ነበር… ከዚያም ባሻገር… ወደ ሰማይ ካረገም በኋላ በሐዋርያቱ ውስጥ ተናግሯል ማለታችን ነው፡፡
በቤተክርስቲያን የታሪክ ዘመናት ውስጥ ተቀባይነትን ያገኘው የኦሪገን ንግግር፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ በውስጣቸው ያሉት መጻሕፍት ሁሉ፣ የክርስቶስ ትንቢታዊ ቃላት መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ ይህም ሃሳብ ያልተፋለሰ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ ነው፡፡
በአንድ በኩል፣ የኢየሱስ ትንቢታዊ አገልግሎት ከትስጉትነቱና ከምድራዊ አገልግሎቱ ይቀድማል ምክንያቱም ለብሉይ ኪዳን ነቢያት አብርሆትን የሰጠ እርሱ ነበርና፡፡
በ1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 10 እና 11 ውስጥ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገረውን አድምጡ፡
ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ |
በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። (1ኛ ጴጥ 1፥10-11) |
ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን የላከው የብሉይ ኪዳን ነቢያት የእግዚአብሔር የመቤዠት ተስፋ እንዴት ይፈፀም ይሆን ብለው ሲጠባበቁና የተስፋ ቃሎቹን ሲያጠኑ አብርሆትን ሊሰጣቸውና ሊያነሳሳቸው መሆኑን ጴጥሮስ ያስተምራል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ብሉይ ኪዳን በጠቅላላ የክርስቶስ ቃል ነው ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይም መንገድ የኢየሱስ የነቢይነት አገልግሎት ከእርሱ መምጣት ቀደም ብሎ የጀመረና ወደ ሰማይ ካረገም በኋላ የቀጠለበት ምክንያት ሐዋርያትን እና ሌሎችንም የአዲስ ኪዳን ጸሐፍት በሥራቸው አብርሆትን ሊሰጣቸው መንፈሱን የላከ በመሆኑ ነው፡፡
ኢየሱስ በዮሐንስ ምዕራፍ 16 ከቁጥር 13 እስከ 15 እንደተናገረው፡
ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። |
እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። |
ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ። |
ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ለእኛ የተላከ የክርስቶስ ቃል መሆኑን እውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው፣ ምክንያቱም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ያሉ መጻሕፍት ሁሉ በዘመናችን ቤተክርስቲያንም ውስጥ ለሕይወት የሚጠቅምና አግባብነት ያለው ባለሥልጣን ቃል መሆናቸውን ያረጋግጣልና ነው፡፡ ኢየሱስን እንደ ነቢያችን መቀበል ማለት ንግግሮቹን ሁሉ በብሉይም በአዲስም ኪዳናት የሰፈሩትን ሁሉ እንደ እግዚአብሔር መንግሥት እና ቃል ኪዳን መገለጥ መቀበል ማለት ነው፡፡ በወንጌላት የሰፈሩትን የኢየሱስ ንግግሮች ብቻ ወይንም አዲስ ኪዳንን ብቻ በመከተል ልንረካ አይገባንም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ሁሉ ልናነብብ፣ ልንረዳና ልንታዘዘው ይገባል ምክንያቱም ሁሉም ለእኛ የተሰጠ የክርስቶስ ቃል ነውና፡፡
እንግዲህ፣ ይህንን ስናከናውን አስፈላጊ የሆኑትን ታሪካዊ አውዶችና ለውጣቸውን በጥንቃቄ በመመርመር ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ፣ በኋላ የመጣው መገለጥ ማለትም አዲስ ኪዳን ደግሞ ደጋግሞ የሚያሳየን የቀደመውን መገለጥ ማለትም ብሉይ ኪዳን እንዴት ልንረዳና ልናዛምደው እንደሚገባ ነው፡፡ ሆኖም ግን መሠረታዊው መርሆ አይለወጥም ያም ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ዘመን ለምትገኘው ቤተክርስቲያኑ የተሰጠ የክርስቶስ ቃል ነው የሚለው ነው፡፡
ሁላችንም፣ ወደ መጽሐፍ ቅዱሳችን ስንቀርብ፣ የምንመርጣቸው ስፍራዎች እንዳሉን አስባለሁ፣ ከቃሉ ውስጥ የምንመርጣቸው ክፍሎች አሉን እናም ብዙ ሰዎች ከሁሉ አስቀድመው ወደ ወንጌላት እና ወደ ኢየሱስ ንግግሮች ይከፍታሉ፡፡ እንግዲህ ጉዳዩ፣ ቃሉ ራሱ እንዳረጋገጠው፣ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችና ቀደምት ትውልዶችም በተደጋጋሚ እንዳረጋገጡት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በጠቅላላ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለባቸው፣ ለማስተማር፣ በሕይወታችን ውስጥ ያሉ ስህተቶችን ለማረም ና ትክክለኛውን መንገድ ለማሳየት፣ ቀናውና የተስተካከለው ሕይወት የሚገኝበትን ጎዳና ለማመልከት የሚጠቅም መሆኑን መገንዘብ ነው፡፡ እንግዲያው፣ ምንም እንኳን አንዳንድ ምርጫዎች እንዳይኖሩን ባንከለከልም ወደ አንዳንድ መጻሕፍትና ንግግሮች ብንሳብም፣ ለምሉዕ ስብዕናችን የመላው ቃለ እግዚአብሔር ምክር ያስፈልገናል እናም ከሌሎች ጋር በሚኖረንም ግንኙነት የእግዚአብሔር ቃል ማዕከላዊ ዳኛችን ሊሆን ይገባል፡፡ [ዶ/ር ጀምስ ዲ. ስሚዝ ሳልሣዊ]
የጠቅላላዎቹ ትንቢታዊ መገለጦች ፍፃሜ የሆነውን፣ በእርሱም የእግዚአብሔር ተስፋዎች ሁሉ እውን የሆኑበትን ኢየሱስን እንደ ነቢያችን በትክክል መረዳት ማለት፣ የብሉይ ኪዳን መገለጥም የእርሱ ቃል መሆኑን መረዳት ነው፡፡ ራሱ በቀጥታ የተናገረባቸው የወንጌል መልእክቶች ቃሎቹ ናቸው፡፡ በመቀጠልም ደግሞ፣ ሐዋርያቱን ሲጠራ ይንቀሳቀሱ የነበሩት እንደ እርሱ አምባሳደሮች፣ በመንፈሱ መነዳትም ውስጥ በመሆን ቃሎቹን እንደሚሰጡን፣ እርሱ ማን መሆኑን፣ ምንስ እንዳደረገ እንደሚያስተምሩን አስተማሪዎች ሆነው ነበር፡፡ እንግዲያው፣ ብሉይ ኪዳንም ይሁን፣ ወንጌላት ወይንም መልእክቶች ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ለእኛ መመሪያ ይሆን ዘንድ ተሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ስለ እኛም ስለ ሠራው ሥራ የሚናገረን ለእኛ የተላከ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ በመረዳት በሙሉ ልብ ልንከተለውና ልናነብበው ይገባል፡፡ [ዶ/ር ስቴፋን ዌሉም]
ይህንን የክርስቶስን ነቢያዊ አገልግሎት መጠነ ርዕይ ግንዛቤ በልቡናችን ይዘን፣ አሁን ደግሞ ከክርስቶስ ወደተቀበልነው ትንቢታዊ መገለጥ ይዘት እና በእኛ ሕይወት ላይ ስላስቀመጣቸው ግዴታዎች እናምራ፡፡
የራእይ ይዘት
የዌስት ሚኒስትሩ ትልቅ ካቴኪዝም የቅዱሳት መጻሕፍትን ይዘት ያጠቃለለው ክርስቶስ ለቤተክርስቲያኑ በነቢይነት የተገለጠው “የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ፣ ለመታነፅና ለድነት የሚሆነውን ሁሉ” በሚል ቃል ነው፡፡ በአንድ መንገድ፣ ይህ አባባል የቅዱሳት መጻሕፍትን ብቁነት የሚያረጋግጥ ጥቅል አባባል ነው፡፡ ከክርስቶስ ትንቢታዊ አገልግሎት አንፃር ስንመለከተው ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ በጠቅላላ ስለ ቃል ኪዳኑ መመሪያን እናገኝበት ዘንድ፤ ከእርግማኑም እንርቅ ዘንድ ያበረታታን ዘንድ እና በታማኝነት በመታዘዝም በረከቶቹን እንሻ ዘንድ በእግዚአብሔር ዋነኛ አምባሳደር፣ በክርስቶስ ለእኛ የተሰጠ ቃል እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እንግዲያው፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ማለት፣ የቃል ኪዳኑ ዝርዝሮችና ከሕይወታችን ጋር ያላቸው ተዛምዶ ነው ማለት ነው፡፡ እናም መታነፃችን (መሰልጠናችን) ማለት የቃል ኪዳኑን ዝርዝሮች በውል መረዳታችን ሲሆን ድነታችን ደግሞ የቃል ኪዳኑን በረከቶች ያካትታል ማለት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በጠቅላላ ለህዝቡ የተሰጠ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ቃል ነው ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ አምላክ እስከሆነ ድረስ፣ መጽሐፍ ቅዱስም በጠቅላላ የእርሱ ቃል ነው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ኢየሱስ በተደጋጋሚ የብሉይ ኪዳንን ዘለቄታዊ ፋይዳ አረጋግጧል፡፡ በምድር አገልግሎቱ ማብቂያም ላይ፣ ለመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸውና ተጨማሪ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲፅፉ ሙሉ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ተስፋ ሰጥቷል፡፡ ዛሬ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የምናገኛቸው የዚህ ውጤት ናቸው፡፡ ኢየሱስ በተጨማሪም የእርሱ ተከታዮች ብሉይ ኪዳን በዘመናቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚጠብቅባቸውን ነገርም አስተምሯቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ እንዲፈፅሙና የቃል ኪዳኑን በረከት እንዲቀበሉ ከመለኮታዊ ፍርድም እንዲያመልጡ ያበረታታቸው ነበር፡፡ በኋላም ጳውሎስ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ጌታን እንድንታዘዝና እንድናገለግል እኛን ለማስታጠቅ ለቤተ ክርስቲያን እንደተሰጡ ጽፏል፡፡
ከነዚህ ሃሳቦች ጎን ለጎን፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተቀመጡት የክርስቶስ ትንቢታዊ መገለጥ ይዘት ሁለት ገፅታዎች ላይ እናተኩራለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የእርሱን ትንቢታዊ አገልግሎት በትክክል መረዳታችን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመፍታት አንፃር እንዴት እንደሚረዳን፣ ከእግዚአብሔርም ፈቃድ አንፃር እንዴት እንደምንታነፅ እናብራራለን፡፡ ሁለተኛ፣ የክርስቶስን ትንቢታዊ አገልግሎት በትክክል መረዳታችን ራሳችንን ለቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት እንደምናስገዛና የመዳንንም ቃልኪዳናዊ በረከት እንዴት እንደምንቀበል እናብራራለን፡፡ ክርስቶስ እንደ ነቢይ የነበረው ሃላፊነት ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመፍታት አንፃር የሚኖረውን አንድምታ በመመልከት እንጀምር፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍትን መተርጎም
በጥንታዊቷ ቅርብ ምሥራቅ፣ የሱዜሪያኑ ነገሥታት በአምባሳደሮቻቸው አማካይነት ለሚልኳቸው መልእክቶች ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ሰዎች ያውቃሉ፡፡ እነዚህን መልእክቶች ቸል ማለት የሚያስከትለው ቅጣት ቀላል አይደለም፡፡ ለእግዚአብሔርም መገለጥ ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱን ለህዝቡ ሲገልጥ፣ የሚፈልግብን ነገር ምን እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ቃሎቹን እንድናደምጥና በመታዘዝም ምላሽ እንድንሰጠው ይጠብቅብናል ያን ጊዜም ማዳኑን እንቀበላለን፡፡ በዚህ አንፃር ስንመለከተው፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ክርስቶስ የሰጠን የቅዱሳት መጻሕፍቱ ቃሎች ልንታዘዛቸው የሚገቡ የታላቁ ንጉሥ ቃል ኪዳናዊ መልእክቶች ናቸው እንጂ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተሰነዘሩ ግለሰባዊ አመለካከቶች ወይንም የእውነታ መግለጫዎች ብቻ አይደሉም፡፡
በዕብራውያን ምዕራፍ 2 ቁጥር 2 እና 3 ላይ እንዲህ እናነባለን፡
በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን? |
ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥ (ዕብ 2፥2-3) |
የክርስቶስን ቃል የማይቀበሉ ሁሉ በዘላላማዊ የቃል ኪዳን እርግማን ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ መልእክቱን በእምነትና በመታዘዝ የሚቀበሉ ደግሞ የቃል ኪዳኑን የድነትና የዘላለም ሕይወት በረከት ይቀበላሉ፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የተመዘገቡት የክርስቶስ ቃሎች እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ማስተዳደርን ዒላማ ያደረጉ ስለሆነ፣ የተመረጠው የአፈታት ዘዴም በቃል ኪዳኑ ውቅረ ነገሮች ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል፡፡ እንደተመለከትነውም፣ የዚህ ውቅር ዝርዝሮችም፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያሳየን ደግነት፣ ከእኛ የሚጠብቅብን ታማኝት፣ በመታዘዝ ስለሚገኘው በረከትና ባለመታዘዝ ስለሚጠብቀን ፍርድ የሚያወሱ ናቸው፡፡
ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፣ እነዚህ ውቅረ ነገሮች ኢየሱስ ከመወለዱ አስቀድሞም በብሉይ ኪዳን የነበሩ ናቸው፡፡ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገም በኋላ የክርስቶስ ሐዋርያትም ስለእነዚሁ ርዕሰ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ጽፈዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ በክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎት ዘመን በሰጠው ትንቢታዊ አገልግሎትም ውስጥ እነዚህኑ ርዕሰ ጉዳዮች እናገኛቸዋለን፡፡ ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር ደግነት በማቴዎስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 45 እና ምዕራፍ 6 ከቁጥር 26 እስከ 33 ውስጥ ተናግሯል፡፡ በማቴዎስ ምዕራፍ 25 ከቁር 14 እስከ 30 እንደምንመለከተው ደግሞ ከሰው ስለሚጠበቀው ታማኝነት እንመለከታለን፡፡ በሉቃስ ምዕራፍ 13 ከቁጥር 1 እስከ 8 እና ምዕራፍ 12 ከቁጥር 35 እስከ 38 ደግሞ ሰው የሚሰጠውን ምላሽ ተከትሎ ስለሚመጣው ውጤት እንመለከታለን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብብ እነዚህን የቃል ኪዳን ውቅሮች በልቡናችን ከያዝን፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም እንድንረዳ ያግዘናል፡፡ ታሪካዊ መጻሕፍትን፣ የግጥምና የጥበብ መጻሕፍትን፣ ደብዳቤዎችን፣ ወይንም ትንቢታዊ ሥራዎችን ስናነብብ፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልንጠይቅ ይገባል፡ ይህ ምንባብ እግዚአብሔር ለህዝቡ ያለውን ደግነት የሚገልጠው እንዴት ነው? ከህዝቡ የሚጠብቀውን ታማኝትስ እንዴት ይገልጠዋል? ታማኝ አለመሆንን በመረጡት ላይ ስለ ሚመጣው እርግማን ምን ይናገራል? የሚሰሙና የሚታዘዙትስ ስለሚያገኙት በረከት ምን ይላል? ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩት ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ደግነት፣ ሞገስና እርዳታ ጋር፤ ለእርሱ ባለንም ታማኝነት ልንጠብቃቸው ከሚገቡን ህግጋት ጋር እና ያንንም ተከትሎ ስለመታዘዛችን ከምንቀበለው ሽልማት፣ ስላለመታዘዛችን ደግሞ ከሚጠብቀን እርግማን ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች በዘመነኛው ዓለም ውስጥ ከበርካታ ጥያቄዎችና ምርጫዎች ጋር ይፋጠጣሉ፡፡ በየዕለቱ፣ ስለ ራሳችን፣ ስለ ቤተሰባችን፣ ስለ ግንኙነቶቻችን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያኖቻችን እና ሰለ ብሔራዊ ፖለቲካ ውሳኔዎቻችን እንወስናለን፡፡ የክርስቶስ ትንቢታዊ ቃልም እነዚህን ጉዳዮችና ሌሎችንም አስመልክቶ በቂ ምላሽ ይሰጠናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሁለንተናችንን ይሸፍናል፡፡ በዚያም ቃል ኪዳን ውስጥ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ እንድንኖር ክርስቶስ ቃሉን እንደሰጠን ስንረዳ፣ ያንን ቃል ይበልጥ ለመረዳት ደግሞም እግዚአብሔርን በሚያከብርና ወደ በረከቱም በሚወስድ መንገድ ለመኖር ራሳችንን እናዘጋጃለን፡፡
ክርስቶስ እንደ ነቢይ የሰጠው አገልግሎት ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመተርጎም አንፃር እንዴት እንደሚያግዘን ከተረዳን፣ ለቅዱሳት መጻሕፍት በመገዛት የቃል ኪዳኑን የድነት በረከት ስለ ምንቀበልበት መንገድ እንመለከታለን፡፡
ለቅዱሳት መጻሕፍት መገዛት
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ለተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ የመገዛት ግዴታችንን ጠቅለል አድርገን የምናይባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፣ በነዚህ ተከታታይ ትምህርቶቻችን ሁሉንም እንነካካለን፡፡ በዚህኛው ትምህርት ግን እነዚህን ጉዳዮች ከክርስቶስ ትንቢታዊ አገልግሎት አንፃር ብቻ እንመከታቸዋለን፡፡
ነቢያት በመደበኛ ሁኔታ በሚያተኩሩባቸው ሁለት ሃሳቦች ላይ እናተኩራለን፣ እነርሱም፡- ከቃል ኪዳኑ እርግማን ለማምለጥ ንስሓ መግባት፤ የቃል ኪዳኑን በረከት ለመቀበል በእግዚአብሔር ማመን ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ንስሓን እንመልከት፡፡
እንደምታስታውሱት፣ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ተቀዳሚ ተግባር ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለማምጣት የቃል ኪዳኑን እርግማኖች ማመልከት ነበር፡፡ በአዲስ ኪዳን የኢየሱስ አገልግሎትም ይኸው ነበር፡፡
በማቴዎስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 17 ላይ የኢየሱስን ስብከት ማቴዎስ እንዴት እንዳጠቃለለው አድምጡ፡
ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር። (ማቴ 4፥17)
በመሠረቱ፣ ይህ መሪ ቃል በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳናት የሚገኝ ቃል ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት በጠቅላላ የሚገኝ ተለመደ ቃል ነው፡፡ እያንዳንዲቷ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍልፋይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለህዝቡ የምትጠቅስ እስከሆነች ድረስ፣ እንደ ፈቃዱ መኖር በተሳነን ጉዳይ ሁሉ ላይ ንስሓ መግባቱ የእያንዳንዱ ምንባብ አግባብነት ያለው ተዛምዶ ነው፡፡
ሁላችን እንደምናውቀው፣ ንስሓ በእግዚአብሔር ላይ ከማመፅ የመመለስና ለፈቃዱም ራስን የማስገዛት ተግባር ነው፡፡ ከኃጢአታችን እንመለሳለን፣ በተመሳሳይም መንገድ ወደ እግዚአብሔር በእምነት እንመለሳለን፡፡ የመጀመሪያው ንስሓ የሚከናወነው ሰዎች ለድነት በሚያበቃ እምነት ወደ ክርስቶስ ሲመጡ ነው፡፡ የወንጌልን ቃል እንሰማለን በኃጢአታችንም እንናዘዛለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግን ንስሓ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ሁሉ ዘወትር የሚከናወን ተግባር ነው፡፡
የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጅ ማርቲን ሉተር በ1517 ዓ.ም. በተጻፈው በመጀመሪያው ታዋቂ ጽሁፉ ይህንን ሃሳብ አንስቷል፡፡ እስኪ ምን እንደተናገረ አድምጡ፡
ጌታችንና ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ተናዘዙ” ሲል፣ በአማኞች ሕይወት ከሚከናወነው አንዱ ንስሓ እንዲሆን ይፈልጋል ማለት ነው፡፡
ሉተር የወደቀው የሰው ዘር ዘወትር ኃጢአትን እንደሚሠራ አውቋል፣ እናም አማኞች ራሳቸው ንስሓ የየዕለት ልምምዳቸው ሊሆን ይገባል ይላል፡፡
ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ የምናበረታታበት አንዱ መንገድ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ውሎች በማወጅ የኢየሱስንና የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ተምሳሊት መከተል ነው፡፡ ለማያምኑት እግዚአብሔር የሚጠብቅባቸውን ስንናገር፣ ከእግዚአብሔር የእርግማን ፍርድ ያመልጡ ዘንድ ከኃጢአት እንዲርቁ ልናሳስባቸው ይገባል፡፡ አማኞች የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰሙ እና ጉድለታቸውንም ሲረዱ፣ ንስሓ ሊገቡ ይገባል፡፡ በመሠረቱ፣ እውነተኛ አማኞች በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍርድ ስር በመውደቅ ስጋት ሊጨነቁ አይገባም፡፡ ኢየሱስ በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ በሞተበት ወቅት ከእርግማን ማምለጣችንን እውን አድርጎታል፡፡ ነገር ግን ዕብራውያን ምዕራፍ 12 ከቁጥር 5 እስከ 11 የመሳሰሉትን ምንባቦች ስንመለከት፣ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ከቃል ኪዳኑ እርግማን ጋር በሚመሳሰል መንገድ ይቀጣናል፡፡
አማኞች በየዕለቱ የንስሓ ሕይወት እንዲኖረን በማበረታታትና በመለማመድ፣ የክርስቶስ ትንቢታዊ ሥራ አክብሮታችንን ልንገልፅና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳነ በረከት ልንከታተል እንችላለን፡፡ ይህን ስናደርግ ግን፣ እውነተኛ ንስሓ ማለት በበደለኝነታችን ተስፋ በመቁረጥ አዘቅት ውስጥ መዘፈቅ አለመሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ይህ በደለኝነትን የመረዳት ነገር ማዘንን ሊያመጣ ቢችልም፣ ዓላማው ወደ ተስፋ መቁረጥ ማምራት አይደለም፡፡ በምትኩ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እና በእርሱም ያለንን ደስታ ያድሳል፡፡
ይህንንም በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 7 ቁጥር 10 እንዲህ እናነባለን፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። |
እኔ እንደማስበው፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ ለመደበኛው የንስሓ ሕይወት ተጠርቷል፡፡ ያም ኃጢአትን መናዘዝና በጌታ ፊት ንፁህ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ኢየሱስ ራሱ መስቀላችንን በየዕለቱ መሸከም እንደሚገባን ተናግሯል፣ ያም ማለት እንዲያው ዝም ብለን ለመከራ እንድንዘጋጅ ብቻ ሳይሆን፣ በመስቀሉ መንገድ ላይ እንደንጓዝ ያም ለኃጢአታችን እንድንሞትና የእግዚአብሔርን ይቅርታ እንድንቀበል ፍንጭ የሚሰጠን ነው፣ መስቀል በመሠረቱ ስለዚያው ነው፡፡ አዎን አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጌታ ሲመጣና ኃጢአቱን ሲናዘዝ፣ አዲስ ሰው ይሆናል ከበደሉም ይነፃል፣ ይህም አጥብቀን ልንይዘው የሚገባ ታላቅ እውነት ነው፡፡ ሆኖም፣ በግልፅ ለመነጋገር፣ ልብሶቻችንን የምናቆሽሸው በየዕለቱ ነው፣ ሁል ጊዜ የነፃ ልብስ ከፈለግን እንደገና ታጥቦ እንዲነፃ እናደርጋለን፡፡ እንደምታውቁት፣ በብሉይ ኪዳን፣ አመፃን የማይወዱና በልባቸውም የማይሰውሩ ይልቁኑ በኃጢአታቸው የሚናዘዙና ወደ ጌታ የሚመለሱ ስለሚጠብቃቸው በረከት በግልጽ የሚናገር አንድ ጥቅስ በመዝሙር 32 ውስጥ አለ፣ እንዲህ ይላል
መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። |
እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው። |
በዚያ መዝሙር ውስጥ፣ አንድ ሰው ይቅርታን ሲቀበል ምን ዐይነት ታላቅ ደስታ እንደሚሰማው ትመለከታላችሁ፡፡ ክርስቲያኖችም ቀን በቀን ሊኖራቸው የሚገባ ደስታ ያን የመሰለ ደስታ ነው፡፡ ያም ደስታ በደልን ይቅር የመባል ደስታ ነው፡፡ ያንን የጌታን ተግሳፅ የምንሻ ከሆነ አስደናቂ በረከት ይከተለናል፣ ንስሓ ወደ አዲስ ሕይወት ይመራናል፡፡ [ደ/ር ፒተር ዎከር]
ከኃጢአታችን በንስሓ የመመለስን ግንዛቤ በልቡናችን ይዘን አሁን ደግሞ በእግዚአብሔር የማመንን ጉዳይ እንመለከታለን፡፡
ኢየሱስም ሆነ የብሉይ ኪዳን ነቢያት በእግዚአብሔር ማመንና ለቃል ኪዳኑም መታዘዝ ዘወትር እንዲቀጥል ያበረታታሉ ይህንንም የሚያደርጉት አድማጮቻቸው የእግዚአብሔርን በረከት እንዲቀበሉ ነው፡፡ ይህም መርህ ለዘመናችን ክርስቲያኖችም ይሠራል፡፡ መንግሥቱ በሙላት ስትመጣ፣ የድነትን በረከት እንደምንቀበል ተስፋ የምናደርግ ከሆነ፣ በእምነታችን ልንፀና፣ እምነታችንንም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን በመታዘዝ ልንገልጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን በአዲስ ኪዳን ውስጥ በበርካታ ስፍራዎች እንመለከታለን፣ ለምሳሌ፣ ኤፌሶን ምዕራፍ 2 ከቁር 8 ስእከ 10፤ 2ኛ ተሰሎንቄ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 4 እስከ 12፤ ዕብራውያን ምዕራፍ 12 ከቁር 1 እስከ 11 እና ያዕቆብ ምዕራፍ 2 ከቁር 14 እስከ 18 ይጠቀሳሉ፡፡
አንዱን ብንመለከተው፣ እስኪ የ1ኛ ዮሐንስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 3 እና 4 አድምጡ፡
ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። |
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። (1ኛ ዮሐ 5፥3-4) |
ዮሐንስ በዚህ ስፍራ እንዳስተማረው፣ እውነተኛ ክርስቲያናዊ እምነት ለእግዚአብሔር በመሰጠት እና ትዕዛዛቱንም በመፈፀም ይፀናል ዓለምንም ድል ያደርጋል፡፡
እግዚአብሔር ተስፋዎቹን ሁሉ እስኪፈፅም በእምነትና በመታዘዝ ፀንቶ የመጠበቁ ነገር ትግል መሆኑን እንቀበለዋለን፡፡ ይኸው ተመሳሳይ ተግዳሮት በየዘመናቱ የነበረውን የእግዚአብሔር ህዝብ ገጥሞት ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ በአዲስ ኪዳን እና በቤተክርስቲያን ታሪክ ሁሉ ውስጥ እውነትነት ነበረው፡፡ የእግዚአብሔር ተስፋዎች የተረጋገጡ እንደሆኑ፣ ክርስቶስም የጀመረውን ሊፈፅም በመጨረሻ ተመልሶ እንደሚመጣ እናውቃለን፡፡
ታውቃላችሁ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቶስ ታማኝ በመሆን እንድንፀና ስለሚያነሳሳን ነገር በፃፈው ደብዳቤ ላይ በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ ያም ክርስቶስ ለእኛ ያደረገውን ለማስታወስ፣ ድነታችንንም ለማስታወስ ነው፡፡ እጅግ መሠረታዊ የሆነው ተነሳስቶ እርሱ ነው፡፡ ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በተጨማሪም ሌሎች ተነሳስቶዎች እንደሚኖሩም በግልፅ ይነግሩናል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ፣ የፍርድ ቀን የመኖሩን እውነታ በግልፅ ያመለክታሉ፡፡ ስለምንናገረው ከንቱ ንግግርና ከንቱ ተግባር መልስን እንሰጣለን፡፡ ይህም አንዱ በታማኝነት እንድንዘልቅ የሚያነሳሳን ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም የሚልቅ ትልቅ መነሳሳት አለን ያም በውስጣዊ ማንነታችን በመታዘዛችን የምናገኘው ታላቅ ደስታ ነው፡፡ ያንን ደስታ የማይፈልግ ማን ይኖራል? የምንታዘዘው ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ ብቻ ሳይሆን በመታዘዛችን የሚገኘውን የእግዚአብሔርን በረከት ለመቀበል መሆኑን እያወቅን ለምን ያንን ደስታ እናስወስዳለን? ቅዱሳት መጻሕፍት በተጨማሪም ስለ አንድም ነገር በጣም ግልፅ ናቸው፡፡ የምንኖረው እኛን በፅኑ በሚከታተለን ዓለም ውስጥ ነው፣ ስለዚህም የሚያየን ዓለም በእውነት ለክርስቶስ ታማኝ በመሆን መኖር አለመኖራችንን በማየት እንደ ክርስቲያን ዋጋ ይሰጠናል ወይስ አይሰጠንም የሚለው ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ታውቃላችሁ፣ ለጌታ ታማኝ ሆነን እንድንኖር የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የጠቃቀስናቸውን ነገሮች ያሳስቡናል፡፡ [ዶ/ር አር. አልበርት ሞህለር፣ ትንሹ]
አንድ ቀን፣ እምነታችን ይረጋገጣል፣ ኢየሱስ ሲመለስ እርሱ የተናገራቸውን በረከቶች በሙላት እንቀበላለን፡፡ ንስሓ ስለለፈው ነገራችን ሲሆን፣ እምነታችን ደግሞ ብድራት አለው፡፡ በዚያን ጊዜም፣ በምሉዕ ማንነቱ በሚገለጠውና ፍፁም በሆነው የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፣ የቃል ኪዳኑን በረከቶች ሁሉ በመቀበል ደስ ይለናል፡፡ እሰከዚያው ግን፣ ከእግዚአብሔር ጋር በቃል ኪዳን የምንኖረው ኑሮ ከኃጢአታችን በንስሓ በመመለስ እና በእምነት በመፅናት ሊገለጥ ይገባዋል፡፡ ለጌታ ታማኝ በመሆን ስንኖር፣ የአሁኑ ዘመን ቅጣታችን ይቀልልናል የወደፊት በረከቶቻችንም ይትረፈረፋሉ፡፡
- ማጠቃለያ
በዚህ ትምህርት፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ የነቢይነትን አገልግሎት እንዴት እንዳከናወና እንደፈፀመ ተመልክተናል፡፡ የነቢይነትን አገልግሎት ብሉይ ኪዳናዊ ዳራ ተመልክተናል፡፡ ይህ አገልግሎት በኢየሱስ ያገኘውን ሙላት፣ የአገልግሎቱን መመዘኛዎች ማሟላቱን፣ የአገልግሎቱን ተግባራት ማከናወኑን እና ብሉይ ኪዳን ከአገልግሎቱ የሚጠብቀውን ወደ ፍፃሜ ማምጣቱን ተመልክተናል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት በተመዘገበው የክርስቶስ ትንቢታዊ አገልግሎት መጠነ ልክና ይዘትም ላይ በማተኮር እነዚህ ሃሳቦች በእኛ ዘመን የሚኖራቸውን ተዛምዶ መርምረናል፡፡
የክርስቶስን ትንቢታዊ አገልግሎት መረዳት ለእያንዳንዱ አማኝ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ዓላማዎቹም ተገቢውን መረጃ እንድናገኝ ያግዘናል፡፡ በጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡትን የኢየሱስ ትምህርቶች እንድናደምጥና እንድንገዛም ያስተምረናል፡፡ ለእኛ የገለጠልንንም መገለጥ ልንረዳ የምንችልበትን ማዕቀፍም ይሰጠናል፡፡ ኢየሱስ ዳግም ስለመምጣቱና ስለምንቀበለውም ዘላለማዊ መዳን የተናገራቸውን ትንቢቶች እግዚአብሔር በእርግጠኝነት እንደሚፈፅማቸው ያረጋግጥልናል፡፡

